Skip to content

የህወሃት ማበስበሱ ቁማርና የደኅንነቱ ሚና

Posted on

የቀዩ መስመር ሰላባዎች?

By Goolgule.com

May 20, 2013

Woyyane

 

መለስ ህይወታቸው እንዳለፈ ከተሰጡት አስተያየቶችና ትንቢቶች መካከል ቀዳሚው የመለስ ሞት ለህወሃት ጊዜውን ጠብቆ የሚፈነዳ ፈንጂ መሆኑ ነበር። በዚሁ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በስልጣን ላይ ያሉ የኢህአዴግ ዲፕሎማት “መለስ የቆፈሩት ጉድጓድ” በሚል ርዕስ በሰጡት ቃለ ምልልስ ይህ እንደሚከሰት ቁልጭ አድርገው ተናግረው ነበር።

መለስ አፍነው የያዟቸው የፖለቲካ ችግሮች ጊዜያቸውን እየጠበቁ የሚፈነዱና በመጨረሻም ፓርቲውን እንደሚፈረካክሰው የተገለጸው በየደረጃ የሚፈነዱት ችግሮች እየበረከቱ በመሄዳቸው ነበር። መለስ አፍነው የያዟቸው ችግሮች የእርስ በርስ መበላላት ደረጃ እንደሚያደርሱ በርካታ ወገኖችና መገናኛዎች ጎልጉልን ጨምሮ አመላክተዋል። አሁን አሁን ትንቢቱ የፍጻሜው ጅማሬ ላይ እንደሚገኝ የሚናገሩም አሉ።

የፖለቲካ አቋም ልዩነት ሳይኖር የአስተሳሰብ ልዩነት ማራመድ በህወሃት ዘንድ አይቻልም። ከተሞከረም ክህደት ነው፤ መፈንቅለ መንግስት የማካሄድ ያህል ነው። የርዕዮተ ዓለም ለውጥ የማቀጣጠል ያህል ያስፈርጃል። ሽብርተኛ ያስብላል። ከቶውንም ተቀባይነት ስለሌለው ድንበር ተበጅቶለታል። ድንበሩም “ቀይ መስመር” በመባል ይታወቃል። የ”ቀይ መስመር” ሃሳብ አመንጪና ደራሲ አቶ መለስ ናቸው። “በጠቅላይ ሚኒስትርነት ማዕረግ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ” በሚል የምጸት ስም የሚጠሩት አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝም ይህንን የቀይ መስመር ጽንሰ ሃሳብ ለንግግር ያህል ይጠቀሙበታል።haile and girma

ቀይ መስመር የሚሰመርበት በውል ተለይቶ የተቀመጠ ውስን ጊዜ የለውም። መስመሩ ሁሌም አለ። ሁሉም ቆመውበታል። ከልምድ እንደሚታየው በህወሃት ህመም ኢህአዴግ ሲያተኩሰው በድንገት መስመሩ በደማቁ እንዲቀባ ይደረጋል። መስመሩ የሚቀባበት ደማቅ ቀለም የሚቀዳው አቶ መለስ አፈር ሳይልሱ “በስብሰናል” ሲሉ ከሰየሙት የኢህአዴግ የ”ማበስበሻ” ባህር ውስጥ ነው።

በኢህአዴግ የ”ማበስበሻ” ባህር ውስጥ ያልተነከረ የለም። በዚህ ባህር ውስጥ ሆነው የሚንቦጫረቁት ተቆጥረው አይሰፈሩም። አዲስ አበባ በአራቱም ማዕዘን፣ በክልልና በክልል ዋና ዋና ከተሞች፣ እንዲሁም በተለያዩ አገራት የሚሰነፍጠው የባህሩ “ግልማት” የዜጎችን የመኖር ህልውና ከተፈታተነ ቆይቷል።

በባህሩ ውስጥ በመርከብ ሆነው በጀልባ የሚቀዝፉትን የሚመለከቱ አሉ። ጀልባ የሚቀዝፉት ጌቶቻቸውንና “ልዕልቷን” እያዩ ሽታውን በለመዱት ባህር ውስጥ ይምነሸነሻሉ። በዛው ባህር ውስጥ በደረታቸው እየዋኙና እየተንቦጫረቁ ግብር የሚያስገቡ አሉ። “ዲጂታል” የሚባሉትና “ምስለኔዎቹ” ደሞ የማበስበሻውን “መረቅ የማቅለሚያ ማዕድን” ይዘው አራት ኪሎ የባህሩ አናትና ማማ ላይ ሆነው ሁሉንም ይመራሉ። የባህሩን የመጫወቻ ህግ የሚበላቸውና ከበሰበሰው ባህር ወደ እቶን የሚወረወሩት “የቀይ መስመር ሰለባዎች ” ይለያሉ። ለይተው ሲጨርሱ ለባህሩ ካፒቴን የፌዴራል የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ያቀብሉታል። በዚሁ ሂደት ይቀጥላል። አዲስ ነገር የለም። ሊኖርም አይችልም። ይህ መነሻ ነው። ወደ ጉዳዩ እናምራ።

የሰሞኑ ወግ – ኢህአዴግ አመረረ ወይስ ቀለደ?

ሰሞኑን ኢህአዴግ “ሙስና ላይ ዘመትኩ። በህዝብ ጥቆማና ትብበር ሙስና የተንሰራፋበትን ተቋም አበራየሁት። የህዝብ ትብብር አይለየኝ …” በማለት የፍርድ ቤት አሰራርና ህጋዊ የፍርድ አካሄድ እያስኮመኮመ የሚያውጀው አዋጅ ያስገረማቸው ክፍሎች “እንዴት እንመን? እንዴት እንቀበል? ማን ያልተነካካ አለ?” እያሉ ነው። ከተለያዩ አቅጣጫ “ኢህአዴግ አመረረ ወይስ ቀለደ” በሚል ክርክርም እያስነሳ ነው።

የፌዴራል ስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አሊ ሱሌማን ፓርላማ ቀርበው “ጥናቱ የተጀመረው በአቶ መለስ ትዕዛዝ ከዓመት ከአስር ወር በፊት ነበር” በማለት ምስክርነታቸውን የሰጡበት ዘመቻ አቶ መለስ በህይወት እያሉ ያልተጠናቀቀው በድንገት በመታመማቸው፣ ከዛም በመሞታቸው፣ ከዛም በላይ የሽግግር ወቅት በመሆኑ እንደሆነ አስረድተዋል። መለስ ሲሞቱ ሃይለማርያም ሙስና ላይ ዘመቱ በሚል ስባሪ ታሪክ እንዳያተርፉ፣ ከዚያም አልፎ ዘመቻው የፖለቲካ ልዩነቱ የፈጠረው “የአራግፍ፣ የመንጥር ዘመቻ” እንዳይመስል አቶ አሊ መለስን የዘመቻው “አባትና ባለታሪክ” አድርገው እንዲያቀርቡ መታዘዛቸው ዘመቻው የተለመደው የኢህአዴግ ቀልድ እንደሆነ አመላካች ስለመሆኑ በስፋት አስተያየት የሚሰነዘርበት ጉዳይ ነው።

ምንም ሆነ ምንም ኢህአዴግ ለጀመረው የሙስና ዘመቻ ሊመሰገን ይገባዋል የሚሉ ወገኖች ዘመቻው እንደ ሰደድ እሳት ተያይዞ የሚነድ ስለመሆኑ ሲናገሩ ይሰማል። የኢህአዴግ ደቀ መዝሙር በመሆን የሚታወቁ ድርጅታቸው “የመለስ ቦናፓርቲ” የተሃድሶ ዘመን ተመልሶ እንደመጣ፣ የዚህ ተሃድሶ ፊት አውራሪ ደግሞ እጩ ጠ/ሚኒስትሩ ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል እንደሆኑ በኩራት እየተናገሩ ነው።

ከደህንነቱ ራዳር የተሰወረ አለ?

በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የማናቸውም ባለሃብቶችና ባለስልጣናት እለታዊና አጠቃላይ የክትትል መረጃ ተመዝግቦ የተቀመጠ ነው። ዋናው ደህንነት የማበስበሻው ባህር ቁልፍ እጁ ላይ ነው። ሲፈለግ ከዋናው ባህር መዝገብ የሚፈልጋቸው ነቅሶ በስሩ ላላው የኢኮኖሚ ደህንነት ዘርፍ ያቀብላል። ለስራው ቅርብ የነበሩና በቅርቡ አገር ለቀው ናይሮቢ የሚገኙ እንዳሉት በዚሁ አሰራር መሰረት አሁን የታሰሩት ሰዎች ሪፖርት ተጠናቆ የቀረበው የዛሬ አምስት ወር ግድም ነው።

ደህንነቱ ማን ከማን ጋር እንደሚሰራ፣ የትኞቹ ባለስልጣናት ከየትኛው “ባለሃብት” ጋር አብረው እንደሚሰሩ፣ በየትኛው ወገኖቻቸውና ዘመዶቻቸው ስም እንደሚነግዱ፣ የኤክስፖርትና ኢምፖርት ስራ እንደሚሰሩ፣ ያለ ማስያዣ ብድር እንደሚፈቅዱና እንዲፈቀድ መመሪያ የሚሰጡ፣ ወዘተ ሙሉ መረጃ እንዳለው የሚጠቁሙት እኚሁ ሰው “ሙስና ከግል፣ ከድርጅትና ከተቋማት አልፎ በመንግስት ደረጃ የተዘረጋ ነውና ማን ማንን ይወነጅላል?” የሚል ጥያቄ ያነሳሉ። አያይዘውም “አገራችን ውስጥ ሙስና በግለሰብ ደረጃ ሳይሆን በመንግስት ደረጃ የተቋቋመ ነው” ብለዋል።

ሌሎችም እንደሚሉት ሙስናው ሊደበቅ በማይችል ደረጃ አገሪቱን እንደ ወባ ወረርሽኝ ሲያጥለቀልቃት፣ በየአቅጣጫው ሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግር ህዝብን ሲያንገሸግሸው ለምን ዝምታ ተመረጠ? የሚለው አንኳር ጉዳይ ብዙ ከመላምትነት የዘለሉ ምክንያቶች እየቀረቡበት ነው። በተለያዩ ደረጃ የኢህአዴግን የመበስበስና የእድገት ደረጃ የማሟጠጥ ጉዳይ አንተርሰው አስተያየት የሚሰጡ ቅድሚያ አጀንዳ የሚያደርጓቸው አቶ መለስን ነው።

መለስ ዝምታን ለምን መረጡ?

እርሳቸው ምን ያህል ተዋናይ እንደሆኑ አሃዝ ጠቅሶ መናገር ባይቻልም አቶ መለስ አገሪቱ በሙስና መንቀዟን እያወቁ ዝም ማለታቸው ከተባባሪነት እንደማያሸሻቸው ስምምነት አለ። በፓርላማ፤ ከነጋዴዎችና ከኢንቨስትመንት ማህበረሰብ ጋርና ከተለያዩ አካላት ጋር ሲነጋገሩ ሙስናን አስመልክቶ አስገራሚ ዲስኩር ሲያሰሙ ኖረው ያለፉት አቶ መለስ፣ ሙስናን ተሸክመው የኖሩት በፍርሃቻ እንደሆነ የአብዛኞች ማጠቃለያ ነው። አቶ መለስ ሙስናን እንደ ስልት በመጠቀም በዙሪያቸው ያሉትን “በማበስበስ” እንዳሻቸው ይነዱዋቸዋል።

በሙስና የተጨማለቁና በሙስናው ባህር ውስጥ የሚዋኙትን ባለስልጣናት፣ ካድሬዎች፣ ባለሃብቶች፣ የጊዜው ሰዎችና ዘመዶቻቸው ቢታወቁም አቶ መለስ በመፈክር አብረዋቸው ለመኖር የወሰኑትና በዚያው ይህችን ዓለም ባላሰቡበት መንገድ የተለዩት በጡረታና “ያለህን ብላ” በሚል አካባቢያቸውን ለማጽዳት የሞከሩት ሙስናው ውስን አድራሻና መንደር ስለሌለው ነው። ዛሬ ምን አዲስ ነገር ተገኘና መለስ የፈሩት ሙስና እንዴት ተደፈረ?

መለስ በህይወት እያሉ ሙስናውን ዝም አሉ የሚሉትን ክፍሎች አጥብቀው የሚቃወሙ ቡድኖች ደግሞ “አቶ መለስ የሙስናው አውራ ናቸው። በመንግስት ደረጃ ለተገነባው የሙስና መንደር ፊታውራሪና ይለፍ ሰጪ ናቸው” ሲሉ ይከራከራሉ። የሙስናውን አዝመራ የዘሩ፣ ኮትኩተው ያለመለሙት፣ መጨረሻ ላይም ባህር አዘጋጅተው የማበስበሻ አረንቋ የተከሉት አቶ መለስ በመሆናቸው ርምጃ ለመውሰድ እንደማይቻላቸው፣ ርምጃ ልውሰድ ቢሉም ሁሉም ስለተበከሉ “በአገሪቱ የጦር አዛዥ፣ የፖሊስ አለቃ፣ የደህንነት ሹም፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ ፓርላማ፣ ቀበሌ፣ ክፍለ ከተማ፣ ከንቲባ፣ መሃንዲስ፣ ሆስፒታል … የሚቀር ስለማይኖር በቅድሚያ በአገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊታወጅ ይገባል” ሲሉ የሙስናውን አደገኛነትና መንግስታዊ መዋቅር ያለው ስለመሆኑ ይከራከራሉ።

ለማስረጃ ከሚያነሱት መከራከሪያ መካከል “ዋናው የሙስና ሻርክ” በሚል ስያሜ የሚጠሩት ባለሃብትና በሳቸው መዋቅር ውስጥ ሆነው ከተራ ወንጀል እስከ አገር አቀፍና ድንበር ዘለል ዝርፊያ የሚፈጽሙ “ማፍያዎች”፣ በፌስታል ብር የሚያቀባብሉ ምስለኔዎች፣ የባለስልጣናትን ሚስቶችና ዘመዶች በንግድ ተቋሞቻቸው በመሰግሰግ የአገሪቱን ህግና ህገመንግስት እንዳሻቸው የሚጋልቡ  ማጅራት መቺዎች፣ የአገሪቱን ባንኮችና የንግድ ስርዓት በማዛባት ሰርተው የሚበሉ ዜጎችን አሟምተው የጨረሱ፣ የራሳቸው ፖሊስና የደኅንነት ሃይል በመገንባት እንደ መንግስት ያቆጠቆጡ ወዘተ በህዝብ ይታወቃሉ። እኒህ ክፍሎች የአቶ መለስን ኮሪዶርና ማረፊያ ቤት ሲመላለሱበት መለስ ዝም ማለታቸው ከምን የመነጨ ሊሆን ይችላል? የሚል ጥያቄ ለሚያነሱ መልሱ አንድ ነው። እሳቸውም፣ ባለቤታቸውም፣ ዘመዶቻቸውም፣ ወገኖቻቸውም፣ የትልቁ “የማበስበሻው ባህር” አባል በመሆናቸው ነው። ከዚያም በላይ ደግሞ ልንካው ካሉ የመገንደስ አደጋ ስለሚከተል ነው። በሌላ አነጋገር ከስር እስከ አናት በተለያየ ደረጃ በህገወጥ የበለጸጉና የትንንሽ መንግስታት መሪዎች የሆኑ ስለበዙ አቶ መለስም ሆኑ እሳቸው የሚመሩት ህወሃት መራሹ አስተዳደር የመከልበስ አደጋ እንዳያጋጥመው በመፍራት እንደሆነ ከውስጥም ከውጪም በስፋት የሚታመንበት እውነታ ነው።

ደብረጽዮን “የጎበዝ አለቃ”!!

መለስ ሲያልፉ ሃላፊነቱን ጠቅልለው የተረከቡት መለስ በመተካካት ሰበብ ያዘጋጇቸው ሰዎች ናቸው። ከነዚህ አዲስ አመራሮች መካከል ዶ/ር ደብረጽዮን ዋናው መሃንዲስ ናቸው። መለስ የፈሩትን ጉድ እሳቸው እንዴት ደፈሩት ለሚለው የሰሞኑ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጡ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ክፍሎች ዶ/ር ደብረጽዮንን ከፊት ለፊት ያስቀምጣሉ።

debretsionከደህንነት መዋቅር ቁንጮ ላይ እንዳሉና መለስ ከሞቱ በኋላ ህወሃት ፊትለፊት ያወጣቸው ደብረጽዮን ከዋናው ስራቸው በተጨማሪ በምክትል ጠ/ሚኒስትር ማዕረግ የኢኮኖሚና የፋይናንስ ክላስተር የሚመሩ ናቸው። ጉዳዩን የሚከታተሉ እንደሚሉት እንደ እሳቸው ፍላጎት ቢሆን አሁን የተወሰደው ርምጃ ከአምስት ወር በፊት መከናወን የነበረበት ጉዳይ ነበር።

አሁን በቁጥጥር ስር የነበሩት ሰዎች ከአምስት ወር በፊት በቁጥጥር ስር እንደሚውሉ ይታወቅ እንደነበር የሚናገሩት የደህንነት ሰዎች “ከመለስ ህልፈት በኋላ በተፈጠረው የሃይል ክፍፍል  አሸናፊ ሆነው የወጡት ክፍሎች ቅርንጫፍ መቆራረጥ ጀመሩ እንጂ ርምጃው የጸረ ሙስና ዘመቻ አይደለም” ባይ ናቸው። የእነ በረከት ስምዓንና የወ/ሮ አዜብን ቡድን በመጻረር በመለስ ሞት ማግስት ዘመቻ የጀመሩት ቡድኖች ከሙስናው ባህር ውስጥ ተጨልፈው ወደ እቶን ውስጥ እንዲጣሉ ሲወሰን ደረጃ ተዘጋጅቶ እንደሆነ አንዳንድ መረጃዎች ያመለክታሉ።

መለስ አፍነው የያዙት የህወሃት “የመበስበስ” ችግር ገሃድ ከሆነ በኋላ አቶ ስብሃት ነጋ ግንባር ሆነው የወጡ ቢሆንም ለምን ታለፉ? የሚል ጥያቄ ስለመነሳቱ አስተያየታቸውን የሚሰጡት እኒሁ የደህንነት ሰዎች እንደሚሉት “አሁን የተጀመረው ኦፕሬሽን አሸናፊዎቹ ሃይሎች ጉልበታቸውን የሚያሳዩበትና የተጻራሪውን ቅርንጫፍ በመቆራረጥ ዋናውን ግንዶች ማድረቅና ለማገዶ የማዘጋጀት የታሰበ ነው” ዘመቻው በቀጣይነት በጡረታ ስም የሚያስወግዳቸው አውራ ሃይሎች እንዳሉት የሚናገሩት ክፍሎች አቶ አርከበ እቁባይና አምባሳደር ብርሃነ ገ/ ክርስቶስ  በዚህ የማጥራት ቀመር ውስጥ እንዳሉበት ይጠቁማሉ።

ወ/ሮ አዜብ መስፍንና አቶ በረከት ስምዖን ላይ ያነጣጠረ ዘመቻ ጀምረው የነበሩት አቶ ስብሃት  ነጋ ምንም ዓይነት ርምጃ እንደማይወሰድባቸው ያመለከቱት ውስጥ አዋቂዎች “ስብሃት ግን ቅርንጫፎቻቸው በሙሉ ተመልምለው ብቻቸውን ይቀራሉ። በመጨረሻም እንዲደርቁ ይደረጋል” ሲሉ ስለ ስሌቱ የሚያውቁትን ይናገራሉ።

“አቶ ስብሃት ላይ ርምጃ ከተወሰደ የባህሩ ዋና ተዋናዮች በሙሉ ርቃናቸውን ይቀራሉ። ሁሉም መረጃዎች ከወጡ ህወሃት ራሱ ባሰመረው የሞት መስመር ላይ ግንባር ቀደም ተሰላፊ እንዲሆን ያደርገዋል” የሚሉት የመረጃው ሰዎች፣ ለጊዜው አሸናፊ የሆኑት ክፍሎች የተነፈሱ ቢመስላቸውም ውስጥ ውስጡን የጋመ ጉዳይ ስለመኖሩም አመልክተዋል።

የሙስና ፋይል!! የህወሃት ፓናዶል!!

የፌዴራል የስነ ምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን ከበቂ በላይ ጥቆማ እንደሚደርሰው፣ በሚደርሰው ጥቆማ መሰረት የማጣራት ስራ ባከናወነባቸው ተቋማት ላይ ርምጃ ለመውሰድ ሲጠይቅ ማዕቀብ እንደሚደረግበት ሰራተኞቹ ውስጥ ውስጡን የሚነጋገሩበት ጉዳይ ነው። ከደህንነት ጋር በቁርኝት የሚሰራው ይህ ተቋም ሳንጃ የሚሰጠው ህወሃት ሲታመም ነው። ኢህአዴግ ውስጥ ግለት ሲጨምር ሳንጃው ድንበር ተበጅቶ ይታዘዛል። ሰሞኑን የሆነውና ከዚህ ቀደም የተደረጉት ሁሉ የዚሁ አሰራር ነጻብራቆች ናቸው።

“ቴሌ በሙስና ገልምቷል” ከተባለና ዋናው ተፈላጊዎች እንዲሸሹ ከተደረገ ከአራት ዓመት በኋላ  ኮሚሽኑ “ሳንጃህን ካፎቱ አውጣው ተባለ” መባሉን የሚያስታውሱ ክፍሎች፣ በህወሃት ክፍፍል ወቅት በአንድ ጀንበር የተሰራውን የማራገፍ ድራማ ያጣቅሳሉ። አሁን በቅርቡ ኦህዴድ ውስጥ የህወሃትን የበላይነት ለመሸርሸር በተነሱ ወጣት አመራሮች ላይ ሙስናን ተንተርሶ የተወሰደውን የማጥራት ዘመቻ ያክላሉ። አሁንም በተመሳሳይ ሰሞኑን የተወሰደውን ርምጃ ከዚሁ ከኖረው የህወሃት “የመበላላት” ታሪክ ጋር የሚያገናኙት ክፍሎች፣ በግልጽ አሁን አሸናፊ ሆኖ ከወጣው ቡድን ቁንጮና “ልዕልት” ጋር አብረው የሚሰሩ ግለሰብና፣ ባለስልጣን መታሰራቸው ቢድበሰበስም የክስ ሂደቱ እየጠና ሲሄድ ምን ሊፈጠር እንደሚችል አሁን ለመገመት የሚችግር እንደሚሆን ይናገራሉ።

ህወሃት በተለይም ተሹለክልከው መሪ የሆኑት አቶ መለስ ከበረሃ ጀምሮ ተቀናቃኞችን እንዴት ይበሉዋቸው እንደነበር ያጋለጡት የቀድሞው የህወሃት የገንዘብ ቤት ኃላፊ አቶ ገ/መድህን አርአያ የሃሳብ ልዩነት አስመልክቶ ውይይት ተደርጎ መስማማት ባለመቻሉ በጣም ሲመሽ  “አሁን እንረፍ፣ እንተኛ” ከተባለ በኋላ በተኙበት በዛው እንዲቀሩ የተደረጉ ስለመኖራቸው ተናገረው እንደነበር በማስታወስ “የአሁኑ ህወሃት ውሳኔውን ተቋማዊ ለማስመሰል። ተቋሙም በህግ፣ በፍርድ ቤት ችሎት፣ በዳኞችና ራሱ መርማሪ፣ ራሱ ከሳሽ በሆነው የፌዴራል የጸረ ሙስና ኮሚሽን የሚመራ በማስመሰል መበላላቱን “ዲጂታል” አድርጎ እየሰራበት ይገኛል።

ለማጠቃለል

የድሃ ልጆች ቦዘኔ ተብለው ሲታሰሩ አገሪቱ ውስጥ የተዛባ ነገር አልነበረም። በፖለቲካ አመለካከታቸው ዜጎች እስር ቤት ሲጣሉ ህግ የተከበረ ነበር። ንጹሃኖች በፈጠራ ወንጀል ሲገረፉና በስቃይ ሲዘለዘሉ ፍትህ አልጎደለም ነበር። እናት በችግር ልጇን ለገበያ ዝሙት ስትልክ ሃፍረት አልነበረም። በዝርፊያ ገንዘብ አዲስ አበባ በህንጻ ስታብድ አግባብነት አይታይም ነበር። ህዝብ በኑሮ ግለት ሌማቱ ሲደርቅና ገንዳ ላይ ምግብ ፍለጋ ህጻናት ሲባትቱ ችግር ሆኖ አይቆጠርም ነበር። አለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰዎች እንደ ከብት በየአቅጣጫው ሲታጎሩ የፍትህ ስርዓቱ አልተዛባም ነበር … ሰሞኑን እስር ቤት የተወረወሩት አቶ ገብረዋህድ ፍርድ ቤት ቀርበው ስለ ባለቤታቸውና ልጃቸው ሲናገሩ “አገሪቱ ምን እየሆነች ነው” አሉ። ከኮብራ ወርደው ወህኒ ቤት ሲገቡ የአገሪቱ የፍትህ ስርዓትና የህግ የበላይነት እንደ ደቀቀ ታያቸው። የባለቤታቸው ከስርዓት ውጪ መታሰር አንገበገባቸው። የልጃቸው መታሰር አቃጠላቸው። ሌሎች ምን ይበሉ? የፕሮፌሰር አስራት ቤተሰቦችና ወዳጆች ምን ይበሉ? የእስክንድር ነጋ ልጅና ባለቤት ምን ይናገሩ? የነበቀለ ገርባ፣ የነ ኦልባና ለሊሳ፣ የነ ሌሊሴ ወዳጆ በኦሮሞነታቸው ብቻ ለስቃይ የተዳረጉና የመከራው ተካፋይ የሆኑት ቤተሰቦቻቸው ይህን ያህል ዓመት ችግሩን እንዴት ተሸከሙት?

የአቶ መለስ ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን የቅርብ ባልደረባና የስራ አጋር የሆኑት የአቶ ገ/ዋህድ ባለቤትና ልጃቸው መታሰር ጥፋት ከሌለባቸው የሚደገፍ ባይሆንም ለሌሎች ባለስልጣናትና የህወሃት አለቅላቂዎች ታላቅ ትምህርት የሚሰጥ እንደሆነ በተለያዩ የማህበራዊ ድረአውዶች መነጋገሪያ ሆኗል።


Leave a Reply