Skip to content

ሰብአዊ መብትና: መንግሥታዊ ግፊት በኢትዮጵያ (2012)

ከፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም                                                                                                                     ትርጉም ከነጻነት ለሃገሬ

በዲሴምበር 2008 ላይ በኢትዮጵያ የ‹‹ለውጥ የሌሽ ዓመት›› በማለት እንጉርጉሮ መሰል መልእክት ጽፌ ነበር፡፡

2008 የ2007፤2006፤2005፤2004 ቅጂ ነበር… በየቀኑ ኢትዮጵያዊያን ሲነቁ ልክ እንደተሰበረ የሙዚቃ ሸክላ ባለፈው የሕይወት ስቃያቸው ድግግሞሽ መከራ ውስጥ በመዳከር ነበር የሚገኙት፡፡ እያንዳንዱ አዲስ ቀን ካለፈው የወረሰውን ይዞ ነበር የሚመጣው፡፡ ጫና፤ ማስፈራራት፤ ንቅዘት፤እስራት፤ ማጭበርበር… ጭካኔና የሰብአዊ መብት ገፈፋ… ከዚህ ክፉ ከሆነው የስቃይ፤ የጣረሞት ግርዶሽ፤ አዙሪት፤ የተስፋ እጦት፤ ውጣ ውረድ መከራ እንዴት እንደሚገላገሉ መንገዱን አያውቁትም፡፡ ስለዚህም ከዚህ መዓት ለመገላገል ያላቸው አንድ ተስፋ መጸለይ፤ መጸለይ፤ ደሞ መጸለይ ብቻ ነበር::

አሁን 2012 ዲሴምበር ነው::

ኢትዮጵያዊያኖች በ 2008፤ 2009፤ 2010፤ 2011፤ ከነበሩበት ሁኔታ አሁን የተሸለ ላይ ናቸው?

የጤፍ ዋጋ በ2008 ከነበረው ዋጋ ቀነሳል? አምና ከነበረው?

የምግብ ዘይት፤ የምርት ውጤቶች፤መሰረታዊ የምግብ አቅርቦት፤ ሥጋ፤ ዶሮ፤ እንቁላል፤ ቤት፤ ውሃ፤ መብራት፤ የምድጃ ጋዝ፤ ናፍጣ…..?

ዛሬ በኢትዮጵያ በ2008 ከነበሩት ድሆች ቁጥራቸው ጨምሯል? የባሰ ችጋር፤ ቤት አልባነት፤ ሥራ አጥነት፤ የጤና ችግር፤ አንስተኛ የትምህርት እድል ለወጣቶቹስ?

በ2008 ከነበረው ያነሰ ሙስና  አለ? ድብቅነት: ያነሰ ግልጽነት ተጠያቂነት በ2012 አለ?

በ2008 ከታየው የምርጫ ነጻነትና ፍትሃዊነት በ2012 አለ?

በ2008 ከነበሩት የፖለቲካ እስረኞች ቁጥር አሁን ቁጥራቸው የበዛ ይገኛሉ?

በ2008 ከነበረው የፕሬስ ነጻነት ያነሰ እና ካለፈው በጣም የበዙ ጋዜጠኞች በወህኒ ቤት በ2012 ይገኛሉ?

በ2012 ኢትዮጵያ ለዜጎቿ ምግብ አቅርቦት ከውጭ በሚቸር ምጽዋት ላይ በ2008 ከለመነችው የበለጠ ትጠይቃለች?

ኢትዮጵያ አሁንም በሰብአዊ መብት መድፈር  በተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት መዝገብ ላይ በመጨረሻው ደረጃ ላይ ነች? 

በ2012 የኢትዮጵያ መንግሥት የስርአት ግፊቶች ማስረጃዎች

አሁንም በተባባሰ ሁኔታ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ደፈራ ሁኔታ፤ በማያቋርጥ መልኩ በዋናነት ከሚጠቀሱ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችና እና ከሌሎች ከሚመለከታቸውና ከሚያሳስባቸው፤ አካላት ያለው አገዛዝ ውግዘቱ እየደረሰበት ነው፡፡ በ2012 ገዢው ፓርቲ፤ በባሰ ሁኔታ ከማይስማሙትና ከተቃዋሚዎች ጋር በመግባባትና መቻቻል ፈንታ በመታበት  ጨቋኝና አዳዲስ አመለካከቶችን ለመቀበል የማይሻ ሆኗል፡፡ ይሄ አገዛዝ የራሱን ሕገ መንግሥት መናድ፤ ውል የገባበትን ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች መጣስ እና ነቃፊዎቹ ላይ ተጸኖ ማድረጉን አላቆመም:: አንዳንድ ሰዎች መለስ ካለፈ በሆላ የተሻለ ሊሆን ይችላል ብለው ቢያስቡም፤ የተቃዋሚዎችን አንዳንድ ሃሳቦች መቀበል፤የሰብአዊ መብት ወንጀሉንም በመጠኑም ቢሆን ለማስመሰልና በማለባበስ፤ የመሻሻል ቀን ቢጠበቅም ከራስ ጸጉራቸው እስከ እግር ጥፍራቸው ድረስ ስብእናቸውን ወደ መለስ ግልባጭነት ለመለወጥ በሚጣጣሩት በኩል ያለው ሁኔታ፤ ‹‹ወይ ፍንክች ያባ ቢላ ልጅ›› ከመለስ መርህ ሌላ ብለዋል፡፡ በእውር ድንብራችንም ቢሆን የመለስን ራእይ  እንከተላለን፤ ማለትም 2013፤ 2014፤ 2015… ከ20012 ወይም ከ2008 አንዳችም ለውጥ አይኖርም ባይ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ የሚታየው ሥልጣንን መከታ ያደረገ ግፋዊ የሰብአዊ መብት መደፈር እንደሚያረጋግጠው እጅጉን የከፋ ለመሆኑ ማስረጃው በራሱ ይመሰክራል፡፡

የዩ ኤስ ስቴት ዲፓርትመንት የሰብአዊ መብት እንቅስቃሴ መንግስታዊ ድፍረት በኢትዮጵያ (ሜይ 2012) ድምዳሜ፡-

በኢትዮጵያ ጉልሁ የዜጎች ሰብአዊ መብት መደፈር 100 የፐለቲካ ተቃዋሚ አባላት፤ ንቁ የፖለቲካ ተሳታፊዎች፤ ጋዜጠኞች፤ ብሎግ አድራጊዎች በመንግስት ለእስር መዳረጋቸው ነው፡፡……. መንግሥት የፕሬስ ነጻነትን ገድቧል፤የእስርና የእንልት ፍርሃት ጋዜጠኞችን እራሳቸውን ሳንሱር እንዲያደርጉ አድርጓቸዋል፡፡ የችሮታና የማሕበረሰቦች አዋጅ (ሲ ኤስ ኦ ሕግ) መንግስታዊ ያለሆኑ ድርጅቶች እንቅስቃሴና ተግባርና ሌሎችም የሰብአዊ መብት መደፈር ድርጊቶች፤ስቃይን፤ድብደባን፤ጉስቁልናንና ማዋረድን፤በደህንነት ሰዎች መንገላታትን፤ሕይወትን የሚፈታተንና ለሞትም ሊያደርስ በሚችል የወህኒ ቤት ሁኔታ መታሰርን፤ ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ መያዝንና ከእስርም በኋላ በማያልቅ ቀጠሮ መቸገርን፤ ሕገ ወጥና ማስረጃ ያለቀረበበት በሶማሌ ግዛት በሚካሄደው ግጭት ላይ በሚመሰረት መሰረተ ቢስ ክስ ለስቃይ መዳረግ፤የመሰብሰብ ነጻነትን፤ የማሕበራት መደራጀትን፤ ማገድ፤ የፖሊስ አባላትና አመራሩ፤የመስተዳድሮች፤ የፍትህ አካላት በሙስና መዘፈቅ…

ላይ ይገኛል ሲል  አተቶል:: 

የሁማን ራይትስ ዎች ድምዳሜ

የኢትዮጵያ መንግስት ሃሳብን በነጻ የመግለጽን የማህበራትን በነጻ የመደራጀትን፤የመሰብሰብን፤መከልከልን በባሰ ሁኔታ ቀጥሎበታል፡፡በ2011 በመቶ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ከሕግ ውጪ ተይዘው በወህኒ ይገኛሉ፤እስካሁንም ድረስ በስቃይና በሚጎዳ እስር ውስጥ ስቃያቸው እንዳለ ነው፡፡ሴፕቴምበር 2011 ድረስና ከዚያም በኋላ፤ የኦሮሞ ተወላጆችን በገፍ ማሰር፤የተቃዋሚውን የኦሮሞ ነጻ አውጪ ድርጅትን አባላት ጨምሮ በማርች ጋዜጠኞችን፤የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን፤ከጁን እስከ ሴፕቴምበር ድረስ አፈናውን በማጠናከር የጸረ ሽብርተኛ አዋጅን መሳርያ በማድረግ ብዙዎች ለግፍ ወህኒ ተዳርገዋል፡፡

የፍሪደም ሃውስ ድምዳሜ:

የፖለቲካ መብትንና የሲቪል ማሕበረሰቡን መብት በመድፈር ረገድ አሁን ኢትዮጵያ በ2012 በዓለም አሁንም ዝቅ ብላ 6ትገኛለች:: በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ሕይወት አሁንም በአቶ መለስ ዜናዊ ከ1995 ጀምሮ እስከ ህልፈታቸው ድረስ ይመራ በነበረው በገዢው ፓርቲ ኢ ፒ አር ዲ ኤፍ መዳፍ ስር ነው፡፡ የሜይ 2011 የፌዴራልና የክልል ምርጫዎች፤በጥብቅ በኢ ፒ አር ዲ ኤፍ ቁጥጥር ስር ነበረ:: ገዢውን ፓርቲ ያልደገፉ መራጮች ዛቻና ማስፈራሪያ ይደረግባቸውና ገዢውን ፓርቲ እንዲመርጡ ይገደዱ ነበር፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ስብሰባ በደህነነቶችና በፖሊስ ሃይል ይበተኑና መሪዎችም በቁጥጥር ስር ይውሉ ነበር፡፡ ኢ ፒ አር ዲ ኤፍ የጸረ ሽብርተኝነት አዋጁን፤ተቃዋሚዎችንና የነጻው ፕሬስ አባላትን ለማሰርና ለማንገላታት የሚጠቀምበት መሳርያ ነው፡፡ ፓርላማው በርካታ ተቃዋሚዎችን ሽብርተኞች በማለት የተቃዋሚዎችንም ዘገባ የሚያትሙትን የነጻው ፕሬስ አባላት በሽብርተኝነት ፈርጇል፡፡ ለእስር ዳርጓል፤ ለስደት አብቅቷል፡፡ ሚዲያው የተያዘው በመንግስትና መበንግስት ቁጥጥር በሚንቀሳቀሱ ጣቢያዎችና ሰራተኞቻቸው ሕትመቶችና የመንግስት ተቀጣሪ ሰራተኞች ነው፡፡ በ2009 የወጣው የመንግስታዊ ያልሆኑ መጽዋች ድርጅቶች ሕግ ድርጅቶቹ በሰብአዊ መብት ጉዳይና በፖለቲካ የፋይናንስ አርድታ ላይ እንዳይንቀሳቀሱ አግዷቸዋል፡፡ ማንኛውም ሃገራዊ ድርጅትም ከውጪ ለጋሽ ድርጅቶች ሊያገኝ የሚገባውን መጠን ገድቦታል፡፡ ይህም ሕግ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን እንዳይንቀሳቀሱ ግዑዝ አድርጓቸዋል፡፡ የፍትሕ አካሉ ለይስሙላ ነጻ ነው ይባላል፤ ውሳኔውም በአብዛኛው መንግስታዊ ሃሳብን ብቻ የሚደግፍ ነው፡፡

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት የመለስን መተካት እንደ አለፈው ማረሚያና ማስተካከያ በመውሰድ ካለፈው በተለየ ሁኔታ፤በመንቀሳቀስ ተቃዋሚ የሆነን ማንንም ከመያዝና ማንም ለእስር እንዳይደረግ›› መሆን አንዳለበት ገልጻል፡፡ 

የማጣራያ ባለሙያዎች የሆኑትና በተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ካውንስል እውቅናና ይሁንታ የተሰጣቸው ልዩ ራፖርተ ማዕና ኪያይ በ2012 ይፋ የውግዘት መግለጫ በማውጣት ገዢው ፓርቲ የጅምላ ክስ በጸረ ሽብርተኝነት አዋጁ በመታገዝና አዋጁን ለራሱ በሚጠቅም መልኩ መጠቀሚያ በማድረግ፤ ነጻነትን በመግፈፍ፤ በሚያሳዝንና  በዓይነ ደረቅነት፤ቀጣይ እንዲሆን እያደረገ፤ የሰብአዊ መብትን መድፈሩን ቀጥሎበታል፡፡ በሰላማዊ መንገድ የመሰብሰብና የሙያ ማሕበራት መደራጀት ልዩ የተባበሩት መንግስታት ባለሙያ ራፖርተር፤ ሲደመድም፡-

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ባሉ ማሕበራት ላይ ታላቅ ችግር በመፍጠር እንቅስቃሴያቸውን እያገደ ያለው፤ በሃገሪቱ ላይ የተጫነው የጸረሽብር አዋጅ ነው፡፡ ገዢው መንግስት በሁሉም ዘርፍ ያሉትን በተለይም የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን እንቅስቃሴ የነጻነት ዋስትና ሊሰጥ የግድ ነው፡፡

የተባበሩት መንግሥታት በጸረሽብርና ሰብአዊ መብት ድንጋጌ ልዩ ራፖርተር ቤን ኤመርሰን፤  ሲናገሩ የጸረሽብርተኝነቱ አዋጅ ለመጉጃነት ሊውል ስለማይገባ በኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ላይ የዓለም አቀፉን የሰብአዊ መብት ድንጋጌ የማይጥስና በተቃርኖ የማይጓዝ መሆኑ ሊረጋገጥ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡

ማርግሬት ስካግያ፤ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ድፍረት መከላከያ ራፖርተር  ጋዜጠኞች፤ ብሎገርስ፤እና ሌሎችም ስለሰብአዊ መብት መከበር የሚሟገቱ ገና ለገና ሃሳባቸው ከኢትዮጵያ መንግስት አስተሳሰብና አካሄድ ጋር ስለማይስማማ ብቻ ጫና ሊፈጠርባቸው አይገባም ብለዋል፡፡

ገብሪየላ ናውል የተባበሩት መንግስታት በዳኞችና በጠበቆች ነጻነት ልዩ ራፐርቱዋር በወንጀል ፍርድ ሂደት ተከሳሾች ማስረጃ በማያጠራጥር መልኩ እስካልቀረበባቸውና ወንጀለኛነታቸው እስክላተረጋገጠባቸው ድረስ በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ላይ በሰፈረው አይነት ንጽህናቸው በተግባር ሊረጋገጥላቸው ተገቢ ነው::  እንዲሁም ተከሳሾች የሕግ ጠበቃቸውን ከችሎት ቀጠሯቸው አስቀድሞ የማነጋገር መብታቸው ሊጠበቅና የመከላከያ ሃሳባቸውን ለማቅረብ እንዲችሉ ሊመቻችላቸው ይገባል:: 

16 የአውሮፓ ፓርላማ አባላት በዲሴምበር 18/2012 አንድ ግልጽ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አቅርበዋል፡፡ ደብዳቤውም ጋዜጠኛና ብሎገር እስክንድር ነጋ በእስር መንገላታቱን የሚያሳስብ ነበር›› በደብዳቤያቸው ላይ ሲፅፉ የፓርላማ አባላቱ አንዳሉት የአቶ ሃእለማርአም መንግስት ኢትዮጵያ በፈረመችውና ልታከብረውም ቃል በገባችው በዓለም አቀፍ ድንጋጌው እንደሰፈረው በአርቲክል 19 ላይ በተቀመጠው መሰረት፤ኢትዮጵያ ቃሏን ማክበርና ለሕጉም ተገዢ የመሆን የአባልነት ግዴታ አስገንዝበዋል፡፡ 

ገዢው መንግሥት በሃይማኖት ተቋማት ላይ የሚያካሂደውን ሕገ ወጥ ጣልቃ ገብነት መተው፤ ጉዳዩን ለባለቤቶቹ መልቀቅ አለበት

የኢትዮጵያ ሕገመንግስት አንቀፅ 11 ‹‹የሃይሞኖትንና የመንግስትን ልዩነት›› በሚገባ አስቀምጧል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ዓለማዊ መንግሥት ለመሆኑ ዋስትና ስለሚሰጠው ‹‹ሃይማኖታዊ መንግሥት የለም››:: አርቲክል 27 ማንም ሰው በፍላጎቱና በምርጫው ያሻውንና ይሆነኛል ያለውን ሃይሞነት የመከተል መብቱ በራሱ ፈቃድ ላይ የተመሰረተና ማንም በጫናና በእዝ ሊያሳምነው እንደማይችል በግልጽ ሰፍሯል፡፡ በግልጽ የተቀመጠውን የሃይሞነት ተቋማትንና አማኞቹን የዜግነት ነጻነት  በኢትዮጵያ ያለው ገዢ መንግሥት በሙስሊም አማኞች ላይ ሕጉን በሚጥስ መልኩ የራሳቸውን የሃይሞኖት መሪዎች በነጻ እንዳይመርጡ ጣልቃ በመግባት ችግር ፈጥሮባቸዋል፡፡ የራሱን ሕገመንግስትም እያፈረሰው ነው፡፡ እንደ አሜሪካው የሃይሞኖት ነጻነት ኮሚሽን በኮንግሬስና በአሜሪካ ፕሬዜዳንት የተዋቀረ ነጻ አካል በዓለም አቀፍ ደረጃ የሃይሞኖትን ነጻነት የሚቆጣጠር ሲገመግም: –

ከጁላይ 2011 ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግሥት በሙስሊም አማኝ ዜጎች ላይ በተለምዶ ለዘመናት ሲከተሉት የነበረውን ሱፊ የእስልምና እምነት አል-አባሽ በተባለው የአስልምና እምነት ሊተካባቸው እያስገደደ ነው፡፡ መንግስት በሌላ በኩልም የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ካውንስል ምርጫ በራሱ ሰዎች ለመሙላት ምርጫ አካሂዷል፡፡ ቀደም ሲል እንደነጻ አካል ሆኖ ሲያገለግል የነበረው  አሁን እንደመንግስት ተቋም ሆኖ በመንቀሳቀስ ላይ ነው፡፡ አሁን ሽብርተኛ ተብሎ መፈረጅ መያዝ ለእስርም መዳረጉ መንግስት የኢትዮጵያን ሙስሊም አማኞች ለመቆጣጠር ያደረገው ሲሆን፤ ድርጊቱ በሃገሪቱ ላይ ያለውን የሃይማኖት ነጻነት መገደብ በግልጽ ያሳያል፡፡ በሃገሪቱ በመላ የሙስሊም አማኞች ሰላማዊ ተቃውሟቸውን በሚያሰሙበት ጊዜ በመያዝ ላይ ናቸው:: በኦክቶበር 29 የኢትዮጵያ መንግስት 29 ተሟጋቾች በሽብርተኝነት ስምና የእስልምና መንግስት ለማቋቋም በሚል ማስረጃ ያለተሰጠበት ሰበብ አስሯል፡፡

ገዢው አስተዳደር የራሱን ሕገመንግሥትና ዓለምአቀፋዊ ሕጋዊ ግዴታዎችን በማክበሩና በመተግበሩ ረገድ መታመን መቻልና የሙስሊሙን ሕብረተሰብ እምነታቸውን በነጻነት እንዲከተሉ ጣልቃ ገብነቱን ሊያቆም ይገባል፡፡ ከተቃውሞው ሰላማዊ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ በሕገወጥ መንገድ የተያዙትና የሃይሞነት እምነታዊ ነጻነታቸው ተገፎ ለእስር የተዳረጉት ሁሉም በነጻ መለቀቅ አለባቸው፡፡ 

ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ

ሰፋ ባለ አመለካከት በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ሁለት አይነት የፖለቲካ እስረኞች ይገኛሉ፡፡ የሕሊና እስረኞች አሉ፤ በገዛ ሕሊናቸው  የታሰሩ ደሞ አሉ፡፡ የሕሊና እሰረኞቹ የታሰሩበት ሰበብ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች እና ጋዜጠኞች በመሆናቸው የነው፡፡ ምንም አይነት ሕግ አልጣሱም ደንብ አላፈረሱም፡፡ የፈጸሙት ነገር ቢኖር ለሕሊናም ሆነ ለደንቡ ትክክል የሆነውን ብቻ ነው፡፡ ስለዕውነት መስክረዋል ዕውነትን ተናግረዋል፡፡ ለባለስልጣናትም እውነቱን ተናግረዋል፡፡ ፍትሕ ሲጓደል ተሟግተዋል፡፡ ስለነጻነት፤ ስለዴሞክራሲ፤ ስለሰብአዊ መብት መከበር፤የሕይወታቸውን ከፍተኛ ዋጋ በመሰዋት፤በነፍሳቸውና በነጻነታቸው ተሟግተው ጠብቀዋል፡፡ በአንዲት የብዕር ጠብታ ነጻ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

በገዛ ሕሊናቸው የታሰሩት ደግሞ በሰብአዊ ፍጡር ላይ ከፍተኛውን ወንጀል በመፈጸማቸው፤ ይህንንም ሲያከናውኑ በመሃይምነት በመመራት የራሳቸውን ሕሊና ስተው ነው፡፡ እነዚህ እስረኞች በስልጣን የእ ንቅልፍ ኪኒን ደንዝዘውና ራሳቸውን ስተው ነው የሚገኙት፡፡ በአንድ ዕለት ለፍርድና በሕግ  የበላይነት ተጠያቂ መሆናቸው እያባነናቸው ከራሳቸው ጋር በሙግትና ፍርሃት ላይ ናቸው፡፡ አንድ ቀን ሌሎችን በዳኙበት ሁኔታ ለፍርድ ቀርበው እንደሚፈረድባቸው ያውቃሉ፡፡ በሰፈሩት ቁና አንድ ቀን መሰፈር አይቀሬ ነው::

በራሳቸው ሕሊና የታሰሩት የሕሊና እስረኞችን ቢለቁና ነጻነታቸውን ቢመልሱላቸው እነሱም ይፈታል ነጻም ይወጣሉ፡፡ አንድ ብቸኛ መዳኛቸው ይሄው ብቻ ነው፡፡ በተቃራኒው ደግሞ የጋንዲን አደገኛውን ማስጠንቀቂያ መቀበል ነው፡፡ ‹‹ገዳዮችና ጨካኝ አምባገነኖች ነበሩ፤ ለጊዜውም የማይደፈሩ መስለው ነበር፤ በመጨረሻው ግን ዕጣ ፈንታቸው መውደቅ ነው፡፡—ምንግዜም መውደቃቸው አይቀሬ ነው:: ስለዚህ አስቡ!›› 

የሕትመት ውጤቶችን ማፈኑ ይብቃ

ናፖሊዮን ቦናባርት ‹‹ከሺ ጥይቶች ይበልጥ የሚያስፈሩት አራት የተቃዋሚ ጋዜጠኞት ናቸው ይል ነበር:: (ወይም ከሺ ጦረኛ 4 ጋዜጠኛ ይፈራል::) ይህ አባባል በኢትዮጵያ ላለው ገዢ ቡድን ትክክለኛ መልእክት ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት 3 በእስር ወህኒ ቤት ያሉና አንድ ተገፍቶ ከሃገሩ የተሰደደ አራት ጋዜጠኞች፤ የ2012 ን እጅጉን የተከበረውን ሄልማን/ሄሜት የሚባለውን ሽልማት ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ ‹‹በዓለም እጅጉን በከፋ ሁኔታ ታፍኖ ያለውን  የመናገር ነጻነትን እውን ለማድረግ ያደረጉትን ጥረት እውቅና በመስጠት ነው የተከበሩት፡፡ ተሸላሚዎቹም፤ እስክንድር ነጋ በግል የሚታገል ጋዜጠኛ ብሎገርና የ2012 የኢንተርናሽናል ፔን ተሸላሚ፤ በሃገሪቱ ካሉት ጥቂት እንስት ጋዜጠኞች አንዷ የሆነችውና በጥንካሬና በአልበገር በይነት  የዓለም አቀፍ የሴቶች ሚዲያ ተሸላሚዋ ርዕዮት ዓለሙ፤ ውብሸት ታዬ በመንግስት ጫና የፈረሰው የሳምንታዊው የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ኤዲተር፤ በመንግስት ጫና የፈረሰውና አሁን በኢንተር ኔት ስራውን የቀጠለው የአዲስ ነገር ጋዜጣው መስፍን ነጋሽ ናቸው፡፡ እነዚህ የሚዲያ ጀግኖች ለዚህ ታላቅ ሽልማት የበቁት ከተለያየ ሃገር ከቀረቡ 41 ጸሃፊዎች፤ ጋዜጠኞች ጋር ነው በማለት ሁማን ራይትስ ዎች ሲዘግብ:-

የእነዚህ 4 የታሰሩና ለስደት የተዳረጉ ጋዜጠኞች አርአያነት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የነጻ ጋዜጠኝነት አልበገር ባይነትና  አደጋውን ያሳያል፡፡ በነጻ ሃሳብን መግለጽ እንደ ክፉ ደዌ በሚቆጠርበት ዕውቀትና ነጻነት እንደጦር በሚፈሩ አምባገነኖች በምትመራ ሃገር ውስጥ አደጋውና ስቃዩ የሚያሳየው ለነጻነት በቆሙና መስዋዕት ለመሆን በቆረጡ ላይ የሚያስከፍለውን መራር አበሳና ዋጋ ነው፡፡ ገዢው መንግስት በነዚህ በተሸላሚዎቹ ለስራቸውና ለቆሙለት ዓላማቸው ተግባራዊ አለመሆን ምን ያህል ጫና እንደተደረገባቸውና ነጻ እስትንፋስ ሳይቀር ሊታገድ በሚሞከርበት የማያዛልቅ ጀብደኝነት የተቃጣባቸውን እንግልት እስራትና መከራ የሚያሳይ ነው፡፡እነዚህ ተሸላሚዎች በኢትዮጵያ እየኖሩ እራሳቸውን ሳንሱር በማድረግ የቻሉትን ያህል ለመተንፈስ የሚሞክሩትንና ግፍና መከራው ሲበዛባቸው ሃገርን ጥሎ በመሰደድ በእስራት የተንገላቱትን  ሁሉ የሚወክሉ ናቸው፡፡

ሁሉም ዲክታተሮችና ፈላጭ ቆራጭ ገዢዎች የነጻውን ፕሬስ የማስተማርና የማንቃት የማደራጀትና ለፍትሕ ለነጻነት መቆም ለዴሞክራሲ መታገልን እጅጉን ይፈሩታል፡፡ የሚዲያዎቹን ንብረትነት በግላቸው በመቆጣጠርና የነሱን ቱልቱላ ብቻ እንዲያስተላልፉ ሕሊናቸውን ለጊዜያዊ ጥቅምና ለራስ ወዳድነት ባሳደሩ ፓሮት ጋዜጠኞች ስለሚታገዙና የሃሳብን በነጻ መንሸራሸር ስላገዱ በዚህ ልክፍታቸው የሕዝቡን ልብና ህሊና ያሸነፉ ይመስላቸዋል፡፡ ይሄ ደሞ የቅዠት ምኞት ነው፡፡ ናፖሊዮን እንዳለው ‹‹ጋዜጠኛ ቁማርተኛ ነው፡፡ ገሳጭ ነው፡፡መካሪና የሃሳብ አጋሪ ነው፡፡ የነገስታት እንደራሴ ነው፡፡ የሕዝብ መምህር ነው›› ልክ እንደናፖሊዮን ፍርሃት የኢትዮጵያ እውቀት አልባ ዲካታተር ገዢዎችም ፍርሃት፤ የነጻው ፕሬስ የማስተማር ሃይል ነው፡፡—-ማስተማር፤ ኢንፎርሜሽን ባለቤት ማድረግ፤ማስረዳት፤ ማሳወቅ፤ ሕዝቡን የዕውቀት ባለቤት ማድረግን፡፡….. የነጻው ፕሬስ፤ ገዢዎች የሚፈጽሙትን ደባና ቅጥ ያጣ ድርጊታቸውን፤ በሕዝቡ ላይ የሚያሳድሩትና መከራ፤ በማጋለጥ ተጠያቂ እንደሚያደርጋቸውና የሕዝብ አጋርነቱን በሚገባ ስለሚረዱ ነው ፍርሃታቸው፡፡ ገዢዎቹ የኢትዮጵያ ባለስልጣናትም  እንደ ናፖሊዮን ነጻ የፕሬስ ሰዎችን፤ ማሰቃየት፤ ማሰር፤ ሳንሱር ማድረግ፤በመሳርያ ማስጨነቅን ስራዬ ብለው ተያይዘውታል፡፡ ሕዝቡን ማለቂያ የሌላቸው በሚመስሉ በሆዳቸው በሚያስቡ ሕሊና ቢስ የደህንነት አባላት በመክበብ፤በመግደል በማሰር የፖለቲካ ተቃዋሚዎቻቸውን ለእስር በመዳረግ፤ በሰላማዊ መንገድ መብታቸውን ለማስከበር በባዶ እጃቸው የወጡ ዜጎችን ኢላማ እያደረጉ በመግደል ዘለአለማዊ መሆን የሚቻል ይመስላቸዋል፡፡ የነጻው ፕሬስ አባላት የሚያስተምሩት የሚያሳውቁት፤ የነጻነትን ጥቅም የሚገልጡት ለተወሰነ ማሕበረሰብ ሳይሆን ለገዢው መንግስትና በገዢው መንግስት ቁጥጥር ስር ለዋሉትም ጭምር ነው፡፡ እሱም ገዢው ፓርቲ ጥፋቱን ሲረዳውና የሚያስከትልበትን ተጠያቂነት፤ የኔ በሚላቸውም አገልጋዮቹ ሳይቀር ለምን? ማለት እንደሚጀመር ሲረዳው ከፍርሃቱ የተነሳ የነጻውን ፕሬስ አባላት ለግፍና መከራ መዳረጉን ያጠናክራል፡፡ እነዚህ ተሸላሚዎችም የዚህ መከራና ጫና ፍትህ እጦት ሰለባ ናቸው፡፡

ሁሉም ለእስር የተዳረጉ የነጻው ፕሬስ አባላት አሁኑኑ ሊፈቱ ይገባል::

“ሠላማዊ ለውጥን  የሚያግዱ በቁጣ የሚቀሰቀስ አመጽን ያስነሳሉ::” ጆን ኤፍ ኬነዲ

==========

ፕሮፌስር ዓለማየሁ ገብረማርያም በካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ሳን በርናርዲኆ የፖሊቲካ ሳይንስ መምሀርና የህግ ጠበቃ ናችው።

*የተቶረገመው ጽሁፍ (translated from):   http://open.salon.com/blog/almariam/2012/12/23/ethiopia_2012_human_rights_and_government_wrongs

(ይህን ጦማር ለሌሎችም ያካፍሉ::) ካሁን በፊት የቀረቡ የጸሃፊው ጦማሮችን  ለማግኘት እዚህ ይጫኑ:: http://www.ecadforum.com/Amharic/archives/category/al-mariam-amharic

http://ethioforum.org/?cat=24

Leave a Reply