Skip to content

Amharic

2013 የኢትዮጵያ የአቦሸማኔ ትውልድ ዓመት ይሁን!

ከፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም

ትርጉም ከነጻነት ለሃገሬ

የአቦሸማኔዎች ዓመት

2013 የኢትዮጵያዊያን አቦሸማኔዎች (የወጣቱ ትውልድ) ዓመት መሆን አለበት፡፡

‹‹የአቦሸማኔው ዘመን የሚያመላክተው የአፍሪካን ጉዳይና ችግር በአዲስ መንገድና አመለካከት ማየት የሚችለውን አዲሱንና ቁጡውን ወጣት፤ አዲስ ተመራቂዎችንና ብቁ ባለሙያዎችን የሚመለከት ነው፡፡ ምናልባትም ‹‹ቁንጥንጥ ትውልድ›› ተብለው ሊጠቀሱ ይችላል:: ያም ሆኖ ግን የአፍሪካ አዲሶቹ ተስፋ ወጣቶቹ ናቸው፡፡ ግልጽነትን፤ ተጠያቂነትን፤ሰብአዊ መብትን፤ መልካም አስተዳደርን የቀለጠፈና ፈጣን አስተሳሰብን፤የሚረዱና ተግባራዊ እውነታንም የሚያስቀድሙ ናቸው›› የታወቀውና የተከበሩት ጋናዊው ኤኮኖሚስት ጆርጅ አይቴ አስረድተዋል:: ቀጥለዉም ሲናገሩ  ‹‹ አብዛኛዎቹ አሁን በአፍሪካ  በስልጣን ላይ ያሉት መሪዎቻቸው ከመጠን ባለፈ ምግባረ ብልሹ እንደሆኑና፤ የሚመሩትም መንገስት በስድብ የተካነ ግን በተግባራዊ መልካም ሀገርና ሕዝብን በሚጠቅም ጉዳይ እርባና ቢስ የሆኑ፤ ማለቂያ የሌለው የሰብአዊ መብት ድፍረትን የፈጸሙ መሆናቸውን ወጣቶቹ ጠንቅቀው ያውቃሉ››::

በኔ አመለካከት የኢትዮጵያ አቦሸማኔዎች ትውልድ፤የሚያካትተው ወጣት ተመራቂዎችንና ባለሙያዎችን፤ምርጥና ብቃት ያላቸው ምሁራንን ብቻ ሳይሆን፤ በነጻ ለማሰብ ለመወያየት፤ ለመመካከር ለመተንፈስ ፍላጎታቸው ያቆበቆበውንና በወገንተኝነት፤አድሎአዊነት፤በምግባረ ብልሹዎች  ቦታቸውና ሁለንተናቸው የተያዘባቸውን፤ፍርድ አልባ ለሆነ  ለእስርና እንግልት ስለሰብአዊ መብት መከበር በጮሁ  ቢያንስ አምናችሁ በስራ ላይ የዋለው  ሕገ መንግስት ተከብሮ ይተግበር ባሉና ለመከራና ስቃይ የተዳረጉትን የኢትዮጵያ ወጣቶችን በሙሉ ያካትትታል፡፡የኢትዮጵያ አቦ ሸማኔ ትውልድ የእስክንድር ነጋና የሰርካለም ፋሲል ትውልድ ነው፡፡ የአንዱዓለም አራጌ፤ውብሸት ታዬ፤ የርዕዮት ዓለሙ፤የበቀለ ገርባ፤ የኦልባና ሌሊሳ፤ እና የሌሎችም መሰሎቻቸው ትውልደ ዘመን ነው፡፡ የኢትዮጵያው አቦ ሸማኔ ትውልድ ብቻ ነው ኢትዮጵያን ከብረት ጥፍራሞች የግፍ አገዛዝ ቡጥጫና ከዲክታተር ሺፕ ማነቆ የሚያላቅቃት፡፡ ከእባብ ጥርስ፤ ከዕብድ ውሻ ክራንቻ፤ ከዋጣት የጨለማ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ፤ በማላቀቅ ወደ ብሔራዊ ዕርቀ ሰላም በማምጣት የበሰበሰና የአለቀለት ተስፋ ቢስ  በሃሰት መሰረት ላይ የተንሳፈፈውን ገዢ መንግስት በመለወጥ የሕዝብ አመኔታ ያለውና በሕዝቡ ፍላጎት ላይ በጠንካራ ሕዝባዊ መሰረት ላይ የተገነባ ስርዓት ለማቆም የሚችለው፡፡

አሁን ያለው ገዢ መንግስትና ከስሩ ኩስ ኩስ ባዮቹ የኢትዮጵያው የጉማሬ ትውልድ (ወይም አበው ነን ባይ ትውልድ) ወደ ጎን እልፍ በማለትና  በቃን በመቀበል ለአቦሸማኔዎቹ መንገዱን ማስተካከልና መልቀቅ አለበት፡፡ አይቴ እንዳለው ‹‹የጉማሬው ትውልድ ምሁራዊ አመለካከቱ ከዘመናት አገልግሎቱ የተነሳ ሞራ ሸፍኖታልና አስተሳሰቡ አሁንም በቅኝ ገዢዎች  መምህርነት ላይ እንደተጣበቀ ነው›› ጠጣር ድንጋይማ ከባድ  በመሆን የአሮጌው ኮሎኒያሊዝም ኢምፔሪያሊዝም አርአያን ከሃገር ሃይልና እምነት ጋር ጉማሬዎቹ አስተሳስረውታል፡፡ማንኛቸውንም የአፍሪካን ችግርና መከራ አገዛዙ ሊለውጠው ይገባል በሚል ባዶ ተስፋ ብቻ በመመኘት ራዕይ አልባ ሆነው፤ በምቹ መንበራቸው ላይ ተሰይመዋል፡፡ አገዛዙ ስልጣኑን የምያራዘመዉና የበለጠ ሥላጣንና ሃይል፤   የሚየዘው የበዛ የውጭ ዕርዳታና ችሮታ ሰለሚያገኝ ብቻ ነው፡፡ የጥቅም መፍሰሻ ቧንቧው እስካልደረቀ ድረስ፤ አገዛዙ ሃገሪቱ እንዳለች ብትጠፋ፤ ሕዝቡ ጨርሶ ቢያልቅ ደንታቸው አይደለም፡፡

የኢትዮጵያ ጉማሬ ትውልድ በተጠናበረ አመለካከት ኢላማውን የሳተ ብቻ ሳይሆን፤ ቅርብ አላሚና አስተሳሰበ ጥቂት፤ ለራሱ ብቻ እርባና ቢስ አጀንዳ የሚያወጣ ጭፍን ትውልድ ነው፡፡ በስልጣን ላይ ያለው የጉማሬ ገዢው መንግስት በረግረግ የሚሰጥም አሸዋ ላይ ባለ የከፋፋይ የዘር ፖለቲካና ክፉኛ በተጠናወተው ብቀላ ላይ ተጠምዷል፡፡ ምንም የማይሳነው ነው የሚሉት የግዛት መንግስታቸው ዐመጸኛ እንጂ  ሌላ ሊሆን የማይችል ነው፡፡ ከንፈሮቻቸው በተላቀቁ ቁጥር ምላሳቸው ለሆዳቸውና ለኪሳቸው መሙያ የሚገለገሉበትንና መመሪያችን በማለት በየአደባባዩ የሚያሞካሹትን ‹‹ኒዎሊቤራሊዝምን›› ለማውገዝና ለመንቀፍ ታጥቀው ተነስተዋል፡፡ ስልጣንም ላይ የሰመጠ መርከብ ላይ እንደሚጣበቁበት ሐዋሳት ሰፍረውበት ለመኖር ነው እቅዳቸው፡፡ ከውጭ መንሥታት የሚቸራቸውን ዳረጎት እንደከፍተኛ የእድገታቸው ግብ አድርገው ይቆጠሩታል ጉራቸዉንም ይነሰነሱበታል፡፡ ለነዚህ ጉማሬዎች ደግሞ ወጣቱ  ዋነኛ መገልገያ መሳርያቸው ነው፡፡ የአፍ ዳረጎት ይቸሩታል፡፡ መለስ ዜናዊ በዚያ ዝነኛው የ99.6 የምርጫ ሃፍረተ ድሉ ወቅት ባደረገው ዲስኩር፤ ወጣቱን በማይጨበጥ ባዶ ቃላት ሸረደደው፡፡ ‹‹በመካሄድ ላይ ባለው የሃገሪቱ ልማትና እድገት ላይ የሃገራችን ወጣት ትውልድ ተሳታፊ መሆን በመጀመሩና በተሰማራበትም (የኮብል ስቶን ባለሙያነት) መስክ ውጤታማ በመሆኑ ወጣቱን ላመሰግን እወዳለሁ፡፡ ወጣቱ ላሳየውና ላረጋገጠው ድጋፉ ለማይታጠፍ አቋሙ ምስጋናችን ይድረሰው፡፡›› በማለት ማሞካሻና በንብረትንት ማሰባሰቢያ ዲስኩር ነበር ያደረገው፡፡

ከስልጣን የገተገለሉትም ጉማሬዎች ወጣቱንና ሴቶችን በፓርቲያቸው መዋቅር ውስጥ አመራር ላይ ለማካተትና ተግባራዊ ተሳትፎ እንዲያደርግ  ለማሰባሰብ አልቻሉም፡፡ በዚህም ምክንያት እራሳቸውን  ባልተረጋጋ ፖለቲካ ሂደት ውስጥ በማስገባት ፖለቲካውንም አሽመድምደውታል፡፡ ስለዚህም እንደገና ለማንሰራራትና ለመታደስ፤ በአዲስ ሃይልና ዘዴ ለመደራጀትና ብቃትም ለማግኘት፤ ለማገገም ወጣቱ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ወጣቱን ያላቀፈና ስልጣን የተነፈገው የጉማሬ ትውልድ፤ በስልጣን ላይ ላለው የጉማሬ ስብስብ መቀለጃ፤ መተረቻ መዘባበቻ መሆን ብቻ ነው ትርፋቸው፡፡

የታገተው አቦሸማኔ

አሳፋሪው አሉባልታ መሰል ባዶ ቃል ደግሞ ‹‹በመካሄድ ላይ ካለው ልማት ወጣቱ ትውልድ ተጠቃሚ ሆኗል›› መባሉ ነው፡፡ ሃቁ የሚያሳየው ደግሞ ፈጽሞ ከአባባሉ ጋር የማይገናኝ ተቃራኒ ነው፡፡ ከ18 ዓመት በታች የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት 41 ሚሊዮን አለያም  ከአጠቃላይ የሕዝቡ ቁጥር ገሚስ ነው ተብሎ ቢገመትም፤ የ ዩኒሴፍ ዘገባ እንደሚያመለክተው ደግሞ፤  ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑት ሕጻነት በሞት መቀጠፍ ዋነኛ መንስኤው የተመጣጠነ የምግብ እጥረት መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ ኢትዮጵያ በ5 ሚሊዮን የሚገመቱ ወላጅ አልባ ሕጻናት አሏት ወይም 15 በመቶ ይሆናሉ፡፡ ከኒህ ውስጥ 800,000 የሚሆኑት ለዚህ የተዳረጉት በኤይድስ ሳቢያ ነው፡፡ የገጠሩ ስራአጥ ቁጥር ሰባ በመቶ ደርሷል፡፡ በ2011 በተካሄደው የተባበሩት መንግስታት ካፒታል ዴቬሎፕመንት ፈንድ  ሪፖርት መሰረት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ካሉት ሃገራት ሁሉ አነስተኛው መጻፍና ማንበብ የሚችሉ ወጣቶች ያሉባት ሃገር ናት ብሎአል፡፡ በ15-24 የዕድሜ ክልል ውስጥ ያለው የትምህርት ሁኔታ በአሳፋሪ 43 በመቶ ነው:: በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ምዝገባው  ዘገምተኛ 30.9 በመቶ፤ ሲሆን: በሚያሳዝን መልኩ 77.8 በመቶው የኢትዮጵያ ወጣት ኑሮውን ከ2 የአሜሪካን ዶላር እጅግ ባነሰ ሂሳብ ነው የሚኖረው፡፡

ወጣት ኢትዮጵያውያን ሥራ ለማግኘት ሕልውናቸውን ለመሸጥ እየተገደዱ ነው፡፡ የአሜሪካን ስቴት ዲፓርትመነት የሰብአዊ መብት 2010 ዘገባ መሰረት፤ “ታማኝ ምንጮች እንዳስታወቁት፤ ስራ አጥ ወጣት ዜጎች የገዢው ፓርቲ አባል መሆናቸውን ካላረጋገጡ ፎርሙን ሞልተው ታማኝነታቸውን ካላረጋገጡ በስተቀር  የዜግነት መብታቸው የሆነውን የስራ ማፈላለጊያ የቀበሌ ማስረጃ ጨርሶ ማግኘት አይችሉም” ሲል አትቶዋል፡፡ በመንግስት መስሪያ ቤትም ለመቀጠር የገዢው ፓርቲ አባልነት ዋነኛው መሟላት ያለበት ግዴት ነው፡፡ የፖሊስ አስተዳደር ባለባት ሃገር ኢትዮጵያ ለመኖር ዋስትና፤ ለመማር ዋስትና፤ ለመቀጠር ዋስትናው የገዢው ፓርቲ አባልነት ብቻ ነው፡፡ የአሜሪካን ስቴት ዲፓርትመነት የሰብአዊ መብት 2010 ዘገባውን ሲያጠቃልል ብቸኛና ለስራ መቀጠርም ተቀባይነት ወዳለውና የውጭ ትምህርትም ለማግኘት ዋነኛ ማሟያ ነጥብ የሆነው የአዲስ አበባ ዩኒቬርሲቲም ገብቶ ትምህርት ለመከታተል የሚመኝ ወጣት በቅድሚያ የገዢው ፓርቲ አባል በመሆን ፎርሙን ሞልቶ፤ ቃለ መሃላ ፈጽሞ፤ ታማኝነቱን አረጋግጦ፤ በዩኒቨርሲቲው የሚታሰበውን አድማ ላለመሳተፍና ለማክሸፍም ለሚመለከተው በማሳበቅ ማገልገሎ እንዳለባቸው ቃል ገብተው ነው ተቀባይነት የሚያገኙት፡፡

ተስፋ በመቁረጥና እርካታ በማጣት፤በርካታ ወጣቶች ትምህርታቸውን በማቋረጥ በጣም አሳፋሪና ሕሊናን አድካሚ፤ ስብዕናን ገፋፊ  ወደ ሆኑ ተግባር በመሰማራት ወደ አደንዛዥ እጽ፤ መጠጥ፤ ትምባሆ፤  ሱሰኝነት እና እንዲሁም ወደ ወንጀልና ልቅ የግብረስጋ ግንኙነት በመሰማራት በወሲብ ለሚመጡ በሽታዎች፤ ኤይድስን ጭምር በሽተኞች በመሆን ላይ ናቸው፡፡ ችግረኞች የሆኑት ወጣቶች (ሰፊውን ቁጥር የሚይዙት ወጣቶች) ከትምህርትና ከስራ ማግኘት እድል የተነፈጉ ናቸውና በራሳቸውም በሃገራቸውም ላይ ተስፋ ቆርጠዋል፡፡ የተከበሩት የሙስሊሙ ሕብረተሰብ የሃይሞነት አባትና መሪ ሃጂ ሞሃመድ ሰኢድ ያነሱት ጥያቄ እንቅልፍ ነስቶ በሃሳብ ያዋዥቀኛል፡- ‹‹ለመሆኑ አሁን የተረፈ የኢትዮጵያ ትውልድ አለ? ወደ ዩኒቨርሲቲው የገቡት ወጣቶች እኮ ሕሊናቸው በጫት ሱስና በሲጋራ የተጠመደ ነው፤ ይሄ ገዢው ፓርቲ እኮ ትውልዱን አጥፍቶታል” ሲሉ አኝህ የተከበሩ  የሃይማኖት አባት ተናግረዋል ፡፡

አቦሸማኔዎቹን ፍታ

በርካታ የጦማሬ አንባቢዎች ለሃገራቸው ነጻነትና ለውጥ ስለሚናፍቁት ግን በገዢው ማነቆ ተጠፍረው ስላሉት  ወጣት ኢትዮጵያዊያን ግንዛቤ እንዳለቸው አማናለሁ፡፡ በተጨማሪም አንባቢዎቼ ለኩሩዎቹ አቦሸማኔዎች ለእስክንድር ነጋ፤ ሰርክዓለም ፋሲል፤ አንዱዓለም አራጌ፤ ውብሸት ታዬ፤ ርዕዮት ዓለሙ፤ በቀለ ገርባ፤ ኦልባና ሌሊሳና ለሌሎችም በርካታ ቆራጥና አልበገር ባይ አቦሸማኔዎች  ሕገመንግስታዊ መብታቸውንለማስጠበቅ፤ የስልጣንን እውነተኛ ገጽታና ምንነት ለገዢዎች በማሳወቃቸውና ድምጻቸውን በማሳማታቸው ለእስር ስለተዳረጉ አኔም የማያቋርጠውንና ወደፊትም የሚቀጥለዉም ጥብቅናዬን አይዘነጉትም፡፡ በዚህ በአቦሸማኔዎቹ ዓመት፤ ወሳኝና አጣዳፊ ለሆነው የኢትዮጵያ ወጣቶች ስለተጋፈጡት ከፍተኛና ወሳኝ ግጥሚያ ከፍተኛ የትኩረት ጥሪ እያደረግሁ እንዲሁም ለጉማሬዎቹ፤ በተለይም በዲያስፖራው ላሉት ምሁራን አቦሸማኔዎች  የስነምግባር አስተዋጽኦና ትብብር በማድረግና ከወጣቱ ጋር ውህደት በመፍጠር፤ የአመራር ድጋፍ፤ማነሳሳት ድጋፍ፤ ማበረታቻ ምክርና ድጋፍ በማድረግ ከወጣቱ ጋር አንድነት እንዲፈጥሩ ነው፡፡

በጁን 2010 ሊካዱ በማይችሉ እውነቶች ላይ ተመስርቼ ጥሪ አቅርቤ ነበር፡- ለማስታወስ ያህል ‹‹ወጣቱ እንደፈንጂ ቦምብ ነው›› በማለት አቅርቤው የነበረውን ጦማር መመልከት ይቻላል፡፡ በዚህ ጦማሬ ላይ ወጣቱ ስለተጫነበት መከራና እራሱን እንዳይሆን ስለሚሸረብበት ደባ በሰፊው አቅርቤያለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ወጣት በመላው ዓለም ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ በችግር፤ በመከራ ሽሽት፤ ከገዢው የእስራት ማነቆ ለማምለጥ እንደተበተነም አሳሰቤያለሁ፡፡

በዚህ በኢትዮጵያዊያን የአቦሸማኔ ዓመት፤ እኛ በጉማሬ ትውልድ ሕሊና ውስጥ ያለነው፤ ለፈጠምነው ስህተትና ጥፋት ንስሃ በመግባት፤ከወጣቱ የአቦሸማኔ ትውልድ ጋር እርቅና መግባባት ማድረግ ይገባናል፡፡ ምንም እንኳን ትግበራው እስከዚህም ባይሆን፤ ፕሬዜዳንት ኦባማ በአፍሪካ ስለሚከሰተው መጥፎና አስቸጋሪ ሁኔታ ያላቸው ግምትና አስተሳሰብ ትክክል ነው፡፡ አንዳሉትም ‹‹ በአፍሪካ ለውጥ የሚያመጡት እንደ ንክሩማና ኬንያታ ያሉት ታላላቅ ግዙፎች እንዳልሆኑ ለመገንዘብ ችለናል፡፡ ባለፉት ትውልዶች ሳይታወቅ የቀረው፤ ይሀን ለውጥ በአፍሪካ ውስጥ እውን ለማድረግ ብቃቱ ችሎታውና እውቀቱ፤ ፈቃደኝነቱና የጸና አቋም ያላቸው ወጣተቶች ናቸው::›› እኛ  ጉማሬዎች የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ ለሕልፈት በተዳረጉ ዲክታተሮች፤ በጣዕረሞታቸው አለያም በሙት መንፈስ አምላኪዎቻቸው የሚወሰን አለመሆኑን አጢነን ልንረዳው ይገባናል፡፡የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ ሃገሪቱን እንደግል ንብረታቸው ለመያዝ በሚፍጨረጨሩት፤ የቁማር መጫወቻ ሜዳቸው ሊያደርጓት በሚያልሙት፤ ወይም በስልጣናቸው ላይ ለመቆየት የላቸውን ሊዛዊ ዘመን ለማራዘም በመዳክሩ፤ የጎሳ ልዩነት ፖለቲካ በሚረጩት፤ ፈጥሞ አይወሰንም፡፡ የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው ጠንካራና ጤናማ በሆነው የአቦሸማኔዎች ጥምረትና አንድነት በአንድ ድምጽ በመናገር፤በተጨበጠ መዳፍ ውስጥ እንዳሉ ጣቶች የተባበረና የተጣመረ አካሄድ፤በመመራት ለአንድ ወሳኝ ግብ በተሰለፉት አቦሸማኔዎች ብቻ ነው፡፡

ከስልጣን ውጪ ለሆኑት ጉማሬዎችና፤ በጎን ሆነው የሚሆነውን ለሚጠብቁት አንድ መልእክት አርቅቄያለሁ፡፡ በቃችሁ፤ ተነሱ፤ ንቁ፤ በትክከለኛው ጎዳና መራመድ በመጀመር  ቁጥራችሁን ከወጣቱ ጋር አስተካክሉ፡፡ ከተጣለብን የራሳችን የጥላቻ ጎሳ ፖለቲካ ሊያላቅቁንና በትክክለኛው መንገድ ሊያራምዱን የሚችሉት እነዚህ ወጣቶች ብቻ ናቸው፡፡ ከተጫነብን የሃይማኖት ወገንታዊነት፤ ሊያገላግሉን የሚችሉት እነዚህ ወጣቶች ብቻ ናቸው፡፡ ካደረብን የፖለቲካ ዘይቤ ግጭት ነጻ የሚያደርጉንም እነሱው ወጣቶቹ ናቸው፡፡ ከዲክታተርሺፕ ማነቆና ጫና፤ የሚያድንኑም እነዚሁ ወጣቶቹ ናቸው፡፡ ወደ አቦሸማኔዎቹ ወጣቶች በመቅረብ፤ ደግ ደጉን ማስተማር፤ ማሳሰብ፤ ማሳመንና ከሕሊና ባርነት ነጻ በማድረግ ፈጠራቸውን በስራ ላይ ለማዋል እንዲችሉ መንገዱን ልናጠራላቸውና ልንደግፋቸው ግዴታችን ነው፡፡

በየአቅጣጫው መደራረስ አለብን፡: አቦሸማኔዎቹ ባሉበት የዘመኑን ቴክኒዎሎጂ በመጠቀም፤ያለንን እውቀትና የስራ ልምዳችንን ሁሉ በሁሉም መስክ ማካፈል አለብን፡፡ ሊሉ የሚፈልጉትን ማዳመጥ አለብን፡፡ እነሱ በጉልህ የነደፉትን እቅድና አስፈላጊ ነው በማለት የሚያነሷቸውን ነጥቦች መቀበልና መርዳት አለብን፡፡ ለረጂም ጊዜ ወጣቱን ከጉዳዩ፤ ከውይየቱ፤ ከድርድሩ አግልለን አርቀን አቆይተነዋል፡: ማድረግ ያለባቸውን በድፍረትና በፍጥነት እየነገርናቸው፤ እነሱ ለሚሉት ግን ጆሮ ዳባ ልበስ ብለናል፡፡ ከችልታ መለስ ባልን ቁጥር ብቻ መግለጫ እንሰጣቸዋለን፡፡ የሚገባቸውን ከበሬታ የምንቸራቸው ግን አልፎ አልፎ ነው፡፡ የነሱን ብቃትና ችሎታ እያሳነስን የራሳችንን ችሎታ በማምጠቅ የራሳችንን ዓላማና እቅድ አስፈጣሚ እናደርጋቸዋለን፡፡ በአቦሸማኔዎቹ ዓመት ከጉማሬዎቹ ምሁራን መሰሎቼ ጋር ወጣቱን አቦሸማኔ እንድንቀርበውና እንድናውቀው እማጸናለሁ፡፡

ወጣቱን ማስተማር አለብን:: ለሁላችንም አስፈላጊ የሆነውን ሁሉ እንዲያውቅ ማድረግ አለብን፡፡ ሃጂ ሞሃመድ ሰኢድ አንደተናገሩት ከአንድነት ውጪ ምንም ሊኖረን አይችልም በማለት አስጠንቅቀውናል፡፡ ‹‹ሃገር ከሌለን ሃይማኖት አይኖረንም፤ ሃገር ሲኖረን ብቻ ነው ማንኛውም ነገር የሚኖረን::›› ለዚህም ነው ወጣቶቹ ሁሉ በአንድ ላይ የእማማ ኢትዮጵያ ልጆች በመሆን ሊተባበሩና ፤በዘር፤በሃይማኖት፤በጎሳ፤ በጾታና በሌላም ሰበብ የሚከፋፍላቸውን ማንኛውንም የፖለቲካ ዘይቤ በማራቅ ወደ ጎን በማለት፤ በመሰባሰብ ፤አንድ መሆን  የሚገባቸው፡፡ ዲክታተሮችና አምባገነኖች ምንም ከማያውቁት ወጣቶች ላይ መብታቸውን መስረቅ አያስቸግራቸውም፡፡ ‹‹ምንገዜም ያለማወቅ ለአምባገነኖችና ጨካኝ ገዢዎች ትልቁ የማሰመሰያና የማጭበርበሪያ የመሳርያ ፋብሪካቸው ነው::›› ኔልሰን ማንዴላ ሲያስተምሩን፤ ‹‹ዓለምን ለመለወጥ የምንጠቀምበት ታላቁ መሳርያ የምንገበየው እውቀት ነው›› ብለዋል፡፡ ከጨቋኞችና ከፈላጭ ቆራጭ ገዢዎች የመከራ ጫና ለመላቀቅ ዋናው መሳሪያችን ወጣቱን በትምህርት በማነጽ እውቀትን ማስገብየት ነው፡፡  በአቦሸማኔዎቹ ዓመት፤ከጉማሬዎቹ ምሁራን መሰሎቼ ጋር አቦሸማኔዎቹን ማሃይምነትንና መሃይሞችህን እንዲዋጉ፤አላዋቂነትን በችሎታ፤ በማስረዳትና በበሰለና በዳበረ አእምሮ እንዲተኩት ማስተማር ይኖርብናል፡፡

ማሳመንም አለብን:፡ የሰላምን፤ የዴሞክራሲን፤የሰብአዊ መብትን፤ የሕግ የበላይነትን፤የተጠያቂነትንና የግልጽነትን መንገድ፤ ወጣቶቹን ማሳየት አለብን፡፡ ማንም ቢሆን እራሱን እንደሕግ ማድረግ አይችልም፡፡ ሰብአዊ መብትን የደፈሩና በዘር ማጥፋት ወንጀል የተሰማሩ ሊጠየቁ ይገባል፡፡በመንግስት ውስጥ መንግስት፤ በብሔር ውስጥ ብሔር፤ በሃገር ውስጥ ሃገር ሊኖር አይችልም፡፡ በዲያስፖራው ያሉትን ወጣቶች በዓላማ ሰንሰለት፤ በእጣ ፈንታ ሰንሰለት ከኢትዮጵያ ካለው ወጣት ጋር የምናስተሳስርበትን መንገድ መቀየስ አለብን፡፡ በከፊል እርግጥ የተሰራ ካርታ አለ፤ መደብ አለ፡፡ ያ መጥበብ አለበት፡፡ በኢትዮጵያ ያሉትም ወጣቶች ከሌሎች በኢትዮጵያ ካሉ ወጣቶች ጋር ሊገናኙ የሚችሉበትን እቅድ በመትለም፤ውጤታማ ውይይትና ምክክር በማካሄድ፤ ሃሳብ በመለዋወጥ፤ አብረው በመስራት ዴሞክራሲያዊ ተስፋን የሚያረጋግጡበትንና ተግባራዊ የሚያደርጉበትን እቅድ እንዲያወጡ ልንረዳቸው ይገባል፡፡ የኢትዮጵያን አቦሸማኔዎች ትውልድ የሚያጋጥሟቸው ፈተናዎች በርካታ ቢሆንም፤ የቻልነውን በማድረግ ወጣቱ የወደፊቱን የመሪነት ቦታ እንዲረከብ ማዘጋጀት አለብን፡፡ በርካታ ችግሮችን ሊፈታ የሚችል ጠንካራ አጀንዳ ለመቅረጽ እንዲችሉ መርዳት አለብን፡፡ ማደረግ ያለብን መንገዱን ማመላከት ነው፡፡ ጉማሬዎቹ ውሃ ለማቀበል ፈቃደኞች እስከሆኑ ድረስ አቦሸማኔዎቹ ከባዱን ጫና ለመሸከም ፈቃደኛ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ወጣቶች ለሠላማዊ ለውጥ መንገድ ለመክፈት፤ ብሔራዊ  የድርድር ሂደት ማመቻቸት አለባቸው፡፡

ቀደም ሲል ያልኩት ጉዳይ ቢሆንም አሁንም ደግሜ ደጋግሜ አነሳዋለሁ፡፡ ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ አይቀሬ ስለሆነው ከፈላጭ ቆራጭ የጭቆና አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ ሽግግሩ  አበክሬ ጽፌያለሁ፡፡ ሽግግሩንም ለማመቻቸት እንዲቻል ብሔራዊ  ውይይት እንዲካሄድ ድምጼን ደጋግሜ አሰምቻለሁ፡፡ ይህንንም ወጣቱ ተቀብሎ ከሥር መሰረቱ አንስቶ የአንድ ለአንድ በየብሄሮቹ ሁሉ በሃይማኖቶቹም፤ መንገድ ተልሞ እንዲያካሂድ ጠይቄአለሁ፡፡ ይህንንም ጥሪ ሳሰማ እምነቴ የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ ያለው ጊዜው ባለፈበት የጉማሬ መንጋጋ የስልጣን ጥመኞች ሳይሆን፤ ለስላሳና ስስ በሆነው የአቦሸማኔዎቹ መዳፍ ውስጥ እንደሆነ እርግጠኛ በመሆኔ ነው፡፡ በዚህ የአቦሸማኔዎቹ ዓመት በሃገር ውስጥ ያሉትን ወጣቶችና በዲያስፖራው ያሉትንም ወጣቶች  ዕርቀ ሰላም የሚደረገበትን አስቸጋሪ ሁኔታ በማላላት መፍትሄ እንዲያስገኙ አሁንም ተማጽኖዬ ይቀጥላል፡፡ ጉማሬዎቹ ለዚህ ዕርቀሰላም መንገዱን ሁሉ የዘጉትና  ፈቃደኝነታቸውንም የነፈጉ ይመስለኛል፡፡ ጉማሬዎች ዕርቀሰላሙን በተደጋጋሚ ቢካሂዱም የተጠቀሙበት መንገድ ግን እርስ በርስ በመጠቋቆም ነው፡፡ አንዱ ሌላውን በመወንጀል እራሱን ነጻ ለማድረግ በመሟገት ነው፡፡ ወጣቶቹ  ግን፤ ይህን በሰላማዊና መግባባት በሚቻልበት፤ የተጣመመውን በማቅናት የጠበበውን በማስፋት፤ ትእግስትንና ቻይነት ባነገበ የሰለጠነ መንገድ ከመጓዝ ባሻገር ምርጫ የላቸውም፡፡ ይህን ሳያደርጉ ቢቀሩ ደግሞ የጎሳና የሃይማኖት ነፋስን ወራሽ መሆን አይቀርላቸውም፡፡

ተማጽኖዬን ለኢትዮጵያዊያን አቦሸማኔዎች ሳቀርብ፤እርስ በርሳቸው የሚመስላቸዉን ውይይት እንዲጀምሩ ነው፡፡ እንደሚታያቸው ብሄራዊ እርቀሰላምን ይተርጉሙት፡፡ የራሳቸውን ፖለቲካዊ መንገድ በመፍጠር አንድዮሽ ውይይት በሀይማኖት፤ በቋንቋ፤በጾታ፤ በክልልና በመደብ ያካሂዱ፡፡ የጦታውን ተሳትፎ ትኩረት በመስጠት የወጣት ሴቶችን በብሄራዊ እርቅ ላየ ተሳትፎ ማበራከት አስፈላጊነት አንዳለው አሰምርበታለሁ፡፡ እርቀ ሰላምን ውጤታማ ማድረግ፤ ድርድር ማካሄድን በተመለከተ፤ በሳይነሳዊ አመለካከትም እንደተረጋገጠው፤ ሴቶች ከወንዶች የበለጠ እርቀሰላምን ውጤታማ የማድረግ ብቃቱ አላቸው፡፡

ውይይት እርስ በርስ መነጋገርን ማካተት ብቻ ሳይሆን መደማመጥንም ይጥይቃል፡፡ የኢትዮጵያ አቦሸማኔዎች የስብጥር፤ የዓይነት ብዛታቸውን እንደጥንካሬ በመቁጠር ይሄው ብዛታቸው ለመበታተኛነት፤ በመከፋፈል ለሽንፈታቸው እንዳይውል እንዳይዳረግም መጠንቀቅ አለባቸው፡፡

ብድግ አንበል ከኢትዮጵያዊያን አቦሸማኔዎች ጋር!

አፍሪካውያን ጉማሬዎች (ለሰብአዊ ፍጡራን የተመደበውን ተምሳሌታዊነት ጨምሮ) አንሰሳት ድንበራቸውን በማስከበር ረገድ አደገኛ አውሬዎች እንደሆኑና ያንን ድንበር አልፎ የመጣባቸውንም ለጥቃት እንደሚዳርጉ ጠንቅቀው ያውቃሉ፡ በየዓመቱ በአፍሪካ ውስጥ ከአንበሳና ከዝሆኖች ሰላባ ግድያ በበለጠ በጉማሬዎች አንደሚፈጸሙ (ለሰብአዊ ፍጡራን የተመደበውን ተምሳሌታዊነት ጨምሮ) የታወቀ ነው፡፡ አቦሸማኔዎችን በፍጥነት የሚያህላቸው የለም፤ድክመታቸው ግን ሌሎች አዳኝ አውሬዎች ሲያግጥሟቸው ጅብ ቢገጥማቸው እንኳን፤ ፈጥነው አደናቸውን መተዋቸው ነው፡፡ የጉማሬ መንጋዎች ግጭት፤ ውድቀት፤ ይባላል፡፡ የአቦሸማኔዎች መንጋ ደግሞ ኅብረት በመባል ይተወቃል፡፡ በጎሳ፤በሃይማኖት፤ በቋንቋ፤በክልል አወቃቀር መስመር የሚደረግ የአቦሸማኔዎች ኅብረት፤ የጉማሬዎችን ግጭት ገጭቶ ለመጣልና የጅቦችን ማስካካት በማሸነፍ ኢትዮጵያን ማዳን ይችህላል፡፡

በዚህ የኢትዮጵያዊያኖች የአቦሸማኔ ዓመት፤የኢትዮጵያን ወጣቶች ለመርዳትና በበለጠ ጥንካሬያቸውን በማጎልበትና አስተዋጽኦዬን በማጠናከር ወደ ከፍተኛው አመርታቸው እንዲሸጋገሩ ሙግቴንና ክርከሬን አቀጠላለሁ፡፡ ሁሉንም ጉማሬዎች እህቶቼንና ወንድሞቼን በዚህ ሂደት እንዲተባበሩኝና አብረውኝ እንዲወግኑ እጠይቃለሁ፡፡ ምንግዜም ጨለማ ለብርሃን መንገዱን ይለቃል፡፡ ‹‹በጨፈገገው ሰማይ ላይ ነው አንጸባራቂ ከዋክብትን የምናያቸው›› የኢትዮጵያ አቦሸማኔዎች በመንፈስና በፈቃደኝነታቸው ሊጠነክሩ ይገባል፡፡ ጋንዲ እንዳለው፡– ‹‹ጥንካሬ ከአካል ግንባታ የሚገኝ አይደለም›› ወይም ከጠብመንጃ፤ ከታንክና ከጦር አውሮፕላኖችም አይገኝም:: ‹‹የሚገኘው ከማይበገር ፈቃደኝነት ነው::›› ዊንስተን ቸርችል ከጋንዲ የተማረ መሆኑን የምናውቀው ‹‹ ለማንኛውም ነገር ትልቅም ይሁን አነስተኛ፤ ፈጽሞ- ፈጽሞ- ፈጽሞ- በጭራሽ ፈጽሞ አታሸብርክ፤ ማሸብረክ የሚገባህ ለክብርህ ከሚኖረው የጸና እምነት ውጪ ለሌላ አታሸብርክ››  ለሃይል አታጎብድድ፤ ከጠላት በኩል ለሚታየው ግዙፍ ለሚመስል የጠላት ድንፋታ አታሸብርክ›› ሲል ተነግሯል፡፡ የኢትዮጵያ አቦሸማኔዎች ጨርሶ ሊያሸበርኩ አይገባም:: በምንም አይነት! ጨርሶ ጨርሶ!

ፕሮፌስር ዓለማየሁ ገብረማርያም በካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ሳን በርናርዲኆ የፖሊቲካ ሳይንስ መምሀርና የህግ ጠበቃ ናችው።

*የተቶረገመው ጽሁፍ (translated from):   http://open.salon.com/blog/almariam/2013/01/06/ethiopia_2013_year_of_the_cheetah_generation

(ይህን ጦማር ለሌሎችም ያካፍሉ::) ካሁን በፊት የቀረቡ የጸሃፊው ጦማሮችን  ለማግኘት እዚህ ይጫኑ::

http://www.ecadforum.com/Amharic/archives/category/al-mariam-amharic

http://ethioforum.org/?cat=24