Skip to content

ከ ድሪምላይነር ወደ ቅዥት ላይነር — የኢትዮጵያ አየር መንገድ አበሳ

Posted on

አየር መንገድ በድሪምላይነር አውሮፕላን ሳቢያ ገቢው ቀንሷል

ዮሐንስ  አንበርብር  |  ሪፖርተር  ጋዜጣ

July 31, 2013

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቦይንግ ኩባንያ በቅርቡ ከተረከባቸው ዘመናዊዎቹ አራት ድሪምላይነር አውሮፕላኖች መካከል በአንዱ ላይ በእንግሊዝ ለንደን አውሮፕላን ማረፊያ በቆመበት በደረሰበት ችግር ምክንያት፣ በአየር መንገዱ እንቅስቃሴና ገቢ ላይ ጉዳት ማድረሱን ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስታወቁ፡፡

The ill-fated Boeing Boeing Dreamliner creating nightmares for Ethiopian Airlines
The ill-fated Boeing Boeing Dreamliner creating nightmares for Ethiopian Airlines

 

ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም የአየር መንገዱን የሥራ አፈጻጸም አስመልክቶ ሐምሌ 19 ቀን 2005 ዓ.ም ለአየር መንገዱ ሠራተኞች ባሰራጩት የውስጥ ደብዳቤ፣ አየር መንገዱ በዘንድሮው የበጀት ዓመት አስቸጋሪ ፈተናዎች እንደገጠሙት ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል በለንደን ሒትሮው ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ቆሞ በነበረው ድሪምላይነር አውሮፕላን ላይ የተከሰተው ችግር አንዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከሁለት ሳምንት በፊት በለንደን ሒትሮው አውሮፕላን ማረፊያ ቆሞ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በድንገት ያለምንም ውጫዊ ምክንያት በደረሰው ውስጣዊ የቴክኒክ ችግር እሳት ተነስቶ በአውሮፕላኑ ላይ መጠነኛ ጉዳት ማድረሱ ይታወሳል፡፡

ይህ ክስተት የዓለም መገናኛ ብዙኃንን ትኩረት በወቅቱ የሳበና በተደጋጋሚ የተዘገበ ሲሆን፣ የለንደን አውሮፕላን ማረፊያም በአውሮፕላኑ ላይ በደረሰ መጠነኛ የእሳት ቃጠሎ ለ90 ደቂቃዎች ተዘግቶ የነበረ መሆኑ አይዘነጋም፡፡

በአውሮፕላኑ ላይ የተፈጠረው ችግር በምን ምክንያት መሆኑ በከፍተኛ ባለሙያዎች እየተመረመረ ሲሆን፣ የተጠናቀቀ የምርመራ ሪፖርት በአሁኑ ወቅት በመጠበቅ ላይ ነው፡፡

አቶ ተወልደ ለሠራተኞቻቸው ባሰራጩት ደብዳቤም የገለጹት ይህንኑ ነው፡፡ በአውሮፕላኑ ላይ የተከሰተው ችግር አውሮፕላኑ መሬት ላይ አርፎ ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ በአግባቡ በቆመበት ቦታ ላይ እንዳለ እንደነበረ፣ በዚህም ስፍራ ለስምንት ሰዓታት ከቆመ በኋላ ችግሩ መፈጠሩን ባሰራጩት የውስጥ ደብዳቤ አስረድተዋል፡፡

የተፈጠረው ችግር በምርመራ ሒደት የሚገኝ ቢሆንም፣ ክስተቱ ግን በአየር መንገዱ እንቅስቃሴ ላይ ጉዳት አድርሷል ብለዋል፡፡

አቶ ተወልደ በድሪምላይነር አውሮፕላኑ ላይ የተፈጠረው ችግር በአየር መንገዱ ላይ ያደረሰውን ጉዳት በመጠን ባይገልጹም፣ “በአየር መንገዳችን የገቢ፣ የኦፕሬሽንና የደንበኞች አገልግሎት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሮ አልፏል፤” ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም በአጠቃላይ ከተረከባቸው ድሪምላይነር አውሮፕላኖች ጋር በተያያዘ አየር መንገዱ ችግሮች እንደገጠሙት አቶ ተወልደ ጠቁመዋል፡፡

ድሪምላይነር አውሮፕላኖች በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሦስት ወራት ከግማሽ ያህል ከበረራ መታገታቸው እንደሌሎች የድሪምላይነር ባለቤት የሆኑ አየር መንገዶች የኢትዮጵያ አየር መንገድም ጉዳት ደርሶበታል ብለዋል፡፡ ይህም አየር መንገዱን በዚህ ዓመት ከገጠሙት ችግሮች መካከል አንዱና ዋነኛው መሆኑን አቶ ተወልደ ያሰራጩት ደብደቤ ያስረዳል፡፡

የአሜሪካ አውሮፕላን አምራች ኩባንያ ቦይንግ እያመረተ የሚገኘው ድሪምላይነር አውሮፕላን ወይም B787 በአሁኑ ወቅት በዘመናዊነት ደረጃ ቀዳማዊ የሚባል ቢሆንም፣ አውሮፕላኑን የተረከቡ አየር መንገዶች ግን በተለያዩ የአውሮፕላኑ ቴክኒካዊ ችግሮች ሳቢያ ተቸግረዋል፡፡ ይህም አምራቹን ኩባንያ ቦይንግ በተመሳሳይ ለኪሳራ እየዳረገው ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ካዘዛቸው 12 ድሪምላይነሮች አራቱን የተቀበለ ሲሆን፣ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የድሪምላይነር አውሮፕላን ባለቤት በመሆን ቀዳሚ ከሆኑ አየር መንገዶች በሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

እንደቀዳሚነቱ ሁሉ የአውሮፕላኑ እንከኖችንም መጋፈጡ አይቀሬ ነው፡፡ በርካታ ሌሎች ታዋቂ አየር መንገዶች በድሪምላይነር አውሮፕላኖቻቸው ላይ ችግሮች ተከስቶባቸው የነበረ በመሆኑ፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ድሪምላይነር ላይ በለንደን ካጋጠመው ችግር በኋላም ሌሎች አየር መንገዶች ተመሳሳይ ችግር ገጥሟቸዋል፡፡

ከእነዚህ መካከል የኳታር አየር መንገድ አንዱ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት በድሪምላይነር አውሮፕላን ላይ በተስተዋለ ድንገተኛ ጭስ ለቀናት ከበረራ ተስተጓጉሏል፡፡
በተመሳሳይም ኤር ኢንዲያ የተባለ አየር መንገድ ድሪምላይነር አውሮፕላን ላይ ባለፈው ሳምንት ጭስ ተከስቷል፡፡

ከዚህ ተመሳሳይና ተደራራቢ ችግር ጋር በተያያዘ አየር መንገዶች ከቦይንግ ኩባንያ ካሳ በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምን ያህል ካሳ መጠየቁ ግልጽ ባይሆንም፣ የኳታር አየር መንገድ ግን ከድሪምላይነር አውሮፕላኖቹ ጋር በተያያዘ 200 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ እንዳጋጠመው ይፋ አድርጓል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከድሪምላይነር አውሮፕላኖቹ ጋር በተያያዘ ችግሮች እየደረሱበት ቢሆንም፣ አውሮፕላኖቹ ወደፊት አዋጭ እንደሚሆኑለት ያምናል፡፡

ይህንንም አቶ ተወልደ ሲገልጹ፣ ‹‹አውሮፕላኑ በበረራ ኢንዱስትሪ ውስጥ ክስተት ቀያሪና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የያዘ ነው፤›› ይላሉ፡፡ አሁን እየገጠሙ ያሉ ችግሮች ማንኛዎቹም አዳዲስ አውሮፕላኖች  የሚገጥማቸው እንደሆኑ፣ በገበያ ውስጥ ለመርጋት ጊዜ የሚወስድ ቢሆንም፣ ነገር ግን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሁም ቢሆን በድሪምላይነሮቹ አስተማማኝነት ጠንካራ እምነት እንዳለው ለሠራተኞች ባሰራጩት ደብዳቤ ገልጸዋል፡፡

ከላይ ከጠቀሱት ችግር ባሻገር ውስጣዊና ውጪያዊ ፈተናዎች ያሉበት መሆኑን ጠቁመው፣ አየር መንገዱ በነዳጅ ዋጋ መናር፣ በከፍተኛ ብድርና የወለድ ክፍያ፣ ተገቢ ባልሆነ የንግድ ውድድር የመሳሰሉት ችግሮች የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ በዚህ ፈታኝ ችግር ውስጥ በማለፋቸውም አየር መንገዱ ውጤታማ መሆኑን በደብዳቤያቸው አስታውቀዋል፡፡

አቶ ተወልደ ባሰራጩት ደብዳቤ የአየር መንገዱ አጠቃላይ ገቢና ትርፍ ባይገልዱም፣ ባለፈው ዓመት ከተመዘገበው 33 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ በ20 በመቶ ሊጨምር እንደሚችል ውስጥ አዋቂዎች ጠቁመዋል፡፡

የሠራተኞችን የኑሮ ሁኔታና ድካም ማካካሻ ለማሻሻል በሚያደርገው ጥረት መሠረት፣ የአየር መንገዱ ሥራ አመራር ቦርድ ከስድስት እስከ ስምንት በመቶ የደመወዝ ጭማሪ ለጠቅላላ የአገር ውስጥ ሠራተኞች ማድረጉን፣ እንዲሁም የአንድ ወር ደመወዝ ቦነስ ለሁሉም ሠራተኞች መፈቀዱን አቶ ተወልደ አብስረዋል፡፡

Leave a Reply