Skip to content

አዉራ የሌለዉ ትግል፤ እረኛ የሌለዉ መንጋ ነዉ – እኔ መሪዬን መርጫለሁ እናንተስ?

ከፍስሃ እሸቱ (ዶ/ር)

በቅርቡ ከዳር ቆሞ ለዉጥን መጠበቅ የህልም እንጀራ በሚል በትግሉ ጎራ ላይ ያለኝን የግሌን አመለካከት የሚገልፅ ፅሁፍ ለወገኖቼ ማቅረቤ ይታወሳል። ይንንኑም ተከትሎ የተለያዩ አስተያቶች ከበርካታ አንባብያን ደርሰዉኛል። ወገኖቼም በቀረበዉ ሀሳብ ላይ ተነስታችሁ ለሰጣችሁኝ ገንቢ አስተያቶች የከበረ ምስጋናዬን አቀርባለሁኝ። ከበርካታ ወገኖችም በፅሁፉ የተዘረዘሩትን ችግሮችና የመፍትሄ ሀሳቦች በመገምገም በቀጣይነት ምን ማድረግ አለብን ትላለህ የሚሉ በርካታ ጥያቄዎችም ቀርበዉልኛል። በበኩሌም ለጥያቄዉ ከፍተኛ ትኩረትን በመስጠት የላይና የታቹን በማሰላሰል፤ የግራና የቀኙን በማመዛዘን፤ በልቤ የሚሰማኝን ከህሊናዩ ጋር በመሟገት ለዉይይትና ለተግባራዊነቱ በጋራ እንድንቀሳቀስ አዲስ ሀሳብ (thesis) አቀርባለሁኝ።
ባለፈዉ አንድ አመት ጨቅላ የትግል ተመክሮዬ፤ በነፃነት ትግሉ ጎራ ዉስጥ ከበርካታ ወገኖች ደግሞ ደጋግሞ የሚነሳዉና አብዛኛዉ ህብረተሰብ የሚስማማበት ጉዳይ የህወሃት/ኢህአዴግ ስርአት ለሃያ አንድ አመታት በላያችን ላይ እንደፈለገዉ እየጨፈረብን፤ ህዝባችንንና አገራችንን እያመሰ፤ ወገኖቻችንን እያሰቃየ፤ ከሃገር እያሰደደ፤ እያሰረ ሲሻዉም እየገደለ፤ ተንሰራፍቶ አገራችንና የኢትዮጵያዊነትን ስሜት እያጠፋ ያለዉ በስርዓቱ ጥንካሬ ሳይሆን ባንፃሩ በተቃወሚ ጎራዉ አንድነት መጥፋትና መዳከም ነዉ። የህዙቡንም ስሜት ባጭር ቃላት ስናስቀምጠዉ አሰባሳቢ መሪ ወይንም አዉራ መታጣቱ ነዉ።

በትግሉ ጎራ ሁሉም ስርዓቱን የመለወጥ በምትኩም ፍትህ የሰፈነባት፤ ህዝቦቿ በእኩልነት፤ በነጻነት፤ በክብርና፤ በአንድነት የሚኖሩናት፤ በፍፁም ዲሞክራሲያዊ መንገድ ተመርጦ ህዝቡን የሚገዛ ሳይሆን የሚያገለግል መንግሥት የሚመሰረትባት ኢትዮጵያን መመስረት አንድ ቋንቋ ይናገራሉ። ሆኖም ይህንን አንድ ቋንቋ እየተናገሩ፤ እንደ ባቢሎን ቋንቋ ተቃዋሚዉ መደማመጥ፤ መከባበር፤ መተባበር፤ መቻቻል፤ አቅቶት፤ ህብረተሰቡም ማንን መደገፍ እንዳለበት ግራ ተጋብቶ ሁሉም ዉጥንቅጡ ባለበት ሁኔታ ዉስጥ እንገኛለን። ጉዳዩ ባጭሩ ሲጠቃለል የሚያስተባብረን፤ ምክር የሚሰጠን፤ አቅጣጫ የሚያሲዘን፤ ስንጣላ የሚያስታርቀን፤ ስንደክም ሚያበረታታን፤ የአንድነታችን፤ የጥንካሬያችን የተስፋችን ምልክት መሪ ማጣታችን ትልቅ ኪሳራ ላይ ጥሎናል። እኛ ለፍትህ፤ ለነጻነት፤ ለእኩልነት፤ ለዲሞክራሲ፤ ለአንድነት፤ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት ክብር ከምንም በላይ ሁላችንንም የሚያኮራ የትግል አላማ ይዘን መሪ አጥተን እየተንከራተትን ሳለን፤ ባንፃሩ ገዳዮች፤ ጨቋኞች፤ ዘረኞች፤ ከፋፋዮች፤ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በእርኩስ ተግባራቸዉ እያጠፉ ያሉች የስርዓቱ አቀንቀኞች ግን በህይወት ብቻም ሳይሆን ሞቶም እንኳን አንድ አድርጎ እስተባብሮ የሚመራቸዉ ማግኘታቸዉ ብርታትንና ጥንካሬን ሰጥቷቸዉ የመሪን፤ የመተባበርንና ያንድነትን አስፈላጊነት በተግባር እያስተማሩን ይገኛሉ።

የእራኤል ልጆች በፈርኦኖች አገር ሲማቅቁ መሪያቸዉ ሙሴ ነፃ አወጣቸዉ፤ አርባ አመትም በበረሃ ሲንከራተቱ የብርታታቸዉ፤ የጥንካሬያቸዉ፤ የአንድነትና የተስፋቸዉ ምሰሶ ሆናቸዉ፤ ጥቁሮች በነጮች ጭቆና ሲዳክሩ ማርቲን ሉተር ኪንግ የአንድነታቸዉና አቅጣጫ ጠቋሚያቸዉ ሆኖ በእርሱ ራእይ ጥቁሮች ነፃ መዉጣት ብቻ ሳይሆን ዛሬ ታላቋ ሀገር አሜሪካ በጥቁር መመራት ጀምራለች፤ በደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች አገራቸዉን ተነጥቀዉ እንደ እንስሳ ሲገዙ ማንዴላ የትግላቸዉ ምልከትና አስተባባሪያቸዉ በመሆን ነፃ እንዲወጡና በአለም ላይ የነፃነት ተምሳሌት ለመሆን በቅቷል። ሌሎችም እንደ ጋንዲ፤ አን ሳን ሱቺ፤ የመሳሰሉ የነፃነት አዉራዎችን በዚሁ አጋጣሚ መጥቀስ ይቻላል። አኛ የነፃነት ትግል እያከናወንን የመገኘታችን ያክል ከነዚህ አገሮች የመሪን አስፈላጊነት የምንማር ይመስለኛል።

ጊዜዉና ትግላችን የራሳችን ማንዴላ፤ የራሳችን ማርቲን ሉተር ኪንግ፤ የራሳችን ጋንዲ እንዲሁም የራሳችን አን ሳን ሱቺን የመሰለ የሚያስተባብረን፤ ያንድነታችን፤ የነፃነታችን፤ የአልሸነፍ ባይነታችን፤ ምልክት የሚሆን መሪን እየጠየቀ ይገኛል። ብዙዎቻችን የአሰባሳቢም ሆነ የመሪ አስፈላጊነት ላይ የምንስማማ ቢሆንም ዋናዉ ጥያቄ ግን ለመሆኑ እንዲህ አይነት መሪ በሀገራችን ይገኛል ወይ የሚለዉ ሆኗል። ለጥያቄዉ ያለኝ አጭር ምላሽ ያለመጠራጠር በትክክል ይገኛል ነዉ። ከዚህ አንጻር ሌላዉ የሚነሳዉ ጥያቄ የምንፈልገዉ መሪ ምን ምን መስፈርቶችንና ባህሪዎችን መላበስ ይኖርበታል የሚለዉ ይሆናል። በኔ እምነት መሪዬ ብዬ የምከተለዉ ፍፁም የአገር ፍቅር ያለዉ፤ ለሀገሩና ለቆመለት መርህና አላማ ለመሰዋት ወደሗላ የማይል፤ አርቆ አሳቢ፤ በሚያወራዉ ሳይሆን በተግባር የተፈተነ፤ በትግሉ ሳያሰልስ ለአመታት በመታገል መስዕዋትነትን እየከፈለ የሚገኝ፤ እንደወርቅ በእሳት የተፈተነ፤ ለማንም የፖለቲካ ቡድን የማይወግን፤ ለሰዉ ልጆች ክብር ያለዉ፤ መልካም ስብእና ያለዉና፤ ሀገራዊና አለማቀፋዊ እዉቅናና ተቀባይነት ያለዉ እንዲሆን እመርጣለሁ።

መቼም ነብይ በሀገሩ አይከበርም ሆኖብን ነዉና ኢትዮጵያ በታሪኳ የእንደዚህ አይነት ጀግኖች መካን ሆና አታዉቅም። ሀገራችን ታሪካቸዉንና ገድላቸዉን በኩራት የምንዘክርላቸዉ በርካታ ብርቅዬ ልጆች ያፈራች ስትሆን በዘመናችንም ከላይ የተዘረዘሩትን መስፈርቶች የሚያሟሉ ልንኮራባቸዉና ሊመሩን የሚችሉ የጊዜአችን ጀግኖች አሉን። ከነዚህ ብርቅዬ የሀገራችን ልጆች መካከል አንዱን መርጠን በማክበርና ልንሰጠዉ የሚገባንን ድጋፍ በመስጠት ከልባችን የምንከተለዉ መሪያችን በማድረግ አሁን በየአቅጣጫዉ የተበታተነዉን ትግል ማሰባሰብ ይጠበቅብናል። ትግሉ ከተሰባበሰ፤ ከተቀነባበረና፤ አቅጣጫና ግብ ኖሮት ከተከናወነ ጥንካሬ በማግኘት ዉጤታማ መሆኑ አይቀርም። ስለዚህ ምርጫዉ የሁላችንም ነዉ። በዘመነ መሳፍንት በታሪካችን እንዳሳለፍነዉና በወቅቱም ትግል እንደምናደርገዉ ሁላችንም የየራሳችንን ትንንሽ ዘዉዶች ደፍተን እርስ በእርሳችን እየተናቆርን ትናንሽ የሃሳብ ጉልቶችን ይዘን መቀመጥ። ወይም ፈረንጆቹ እንደሚሉት ከጊዜዉ ጥያቄ ጋር አድገን፤ ከራሳችን በላይ ሀገራችንና ህዝባችንን አስቀድመን በአንድ መሪ ዙርያ በግልም ሆነ በድርጅት ተሰባስበን ትግላችንን ማከናወን።

የኔ፤ የግሌ ምርጫ ግልፅ ነዉ። መሪ እፈልጋለሁ። የራሴን ኢትዮጵያዊ ማንዴላ እፈልጋለሁ። አስተባባሪ፤ መካሪ፤ አቅጣጫ ጠቋሚ፤ አስታራቂ፤ የተስፋ፤ የአላማና የኢትዮጵያዊነት ምልክት። ወያኔ ሟቹን መሪያቸዉን ታላቁ መሪ ብለዉ እንዳመለኩት፤ እኔም የኔ የምለዉ መሪ እፈልጋለሁ። ለመሪዬም የሚገባዉን ክብርና፤ ድጋፍ፤ ለመስጠት እሻለሁ። በመሪና በኢትዮጵአዊነት ካምፕ ዙርያ ተሰባስበን ዘላቂ፤ መሰረታዊና እዉነተኛ ለዉጥ እንዲመጣ እሻለሁ ለተግባራዊነቱም እታገላለሁ። በዚሁም የልባዊ ፍላጎትና ጽናት በመነሳት መሪዬን ከጀግኖች መካከል መምረጥ ጀመርኩኝ። የህሊና ምርጫዉም እጅግ አስቸጋሪ ነበር። ሁሉም ጀግኖቻች በተለያ ደረጃ የራሳቸዉ የሚከበር ባህሪና የከፈሉት መስእዋትነት ቢኖርም የግድ አንድ መምረጥ ስለሚኖርብኝ ሁሉምን ሚገባቸዉን ክብር በመስጠት ምርጫዬ ግን አንዱ ላይ አመዘነ።

የኔ ኢትዮጵያዊ ማንዴላ ማነዉ በምንስ መመዘኛ ተመረጠ? ለሚለዉ የኔ ኢትዮጵዊዉ ማንዴላ
1. በትግሉ ከሃያ አመታት በላይ ተፈትኖ እስካሁን ያለማመንታት በፅናት እየታገለ ያለ፤
2. ለኛ ነፃነት፤ ለፍትህ፤ ለመናገር መብት ለእኩልነት በመቆሙ ከዘጠኝ ጊዜ በላይ በፋሽሽቱ ስርዓት ለእስር የተዳረገና አሁንም ለበርካታ አመታት ተፈርዶበት ወህኒ እየማቀቀ ያለ፤
3. ሀብትና ንብረቱን ለሀገሩና ለወገኑ ክብር አሳልፎ የሰጠ፤
4. ለሀገሩና ለወገኑ ነፃነት እስከ መሞት ለመታገል በቃልኪዳኑ የፀና፤
5. እንደሌላዉ ከሀገር ተሰዶ መኖር ሲችል ባርነትንና ጭቆናን ለመታገል ሀገር ቤት በመቅረት እየታገለ ያለ፤
6. በበሳል አንደበቱና በሰላ ፅሁፎቹ ስርዓቱን በፍፁም ጀግንነት ያንገዳገደ፤
7. በፀባዩ፤ በበሳልነቱ፤ ባጠቃላይ በስብእናዉና ለሰዉ ልጆች ባለዉ አመለካከት ፈፅሞ የተከበረ፤
8. የተከበረ የቤተሰብ አስተዳዳሪ፤
9. የሀገሩን ፍቅር ከልጁ ያስበለጠ፤
10. እኛ የሚገባዉን ድጋፍና እዉቅና ባንሰጠዉም በአለም አቀፍ ደረጃ እዉቅናና በርካታ ሽልማቶችን ያገኘ፤
11. በርካታ ፅሁፎችን የፃፈና ለኛ የታገለ እንዲሁም ትምህርቶችን ያስተማረ ሲሆን ሌሎችም እጅግ በርካታ ነጥቦች ማስቀመጥ ቢቻልም በኔ እምነት እንደወርቅ አንድ የሰዉ ልጅ ሊቀበለዉ የሚችለዉን ፈተና በእሳት የተፈተነና አሁንም ድረስ እየተፈተነ ያለ ነዉ።

ከዚህ አንጻር በኔ ፍፁም የማያወላዉል እምነትም ተበታትኖ ያለዉን የትግል ጎራ አሰባሳቢ ሊሆን የሚችል መሪ ከጀግናዉ እስክንድር ነጋ የተሻለ የኛ የዘመናችንና የራሳችን ማንዴላ ይኖራል ብዬ አላምንም። በኔ አመለካከትም እንደ እስክንድር ያለ አለም አቀፍ እዉቅና ያለዉ ጀግና በመካከላችን ማግኘታችን እድለኞች ነን። ጊዜዉ ያለፈበትን በእጅ ያለ ወርቅ፤ ወይም ነብይ ባገሩ የሚለዉን ሗላ ቀር ብሂልና አለመካከት ጥለን በወርቃችን በመኩራት፤ በሱ ዙርያ መሰባሰብ እንጀምር ብዬ ጥሪዬን አቀርባለሁኝ። ስምን መላዕክት ያወጡታል እንዲሉ በታላቁ በእስክንድር ትግላችን መሪ፤ አሰባሳቢ፤ ክብር ያግኝ። የኛ የምንለዉ፤ የምናከብረዉ፡ የምንኮራበት መሪ ይኑረን። በሱ ዙርያ ሰላምን፤ ተስፋን፤ አንድነትን፤ ጥንካሬንና፤ ዉጤትን እናግኝ። ይህንንም ካደረግን በኔ እምነት የምንመኘዉን ለዉጥ እንጎናጸፋለን።

በእስር ላይ ያለና ፖለቲከኛ ያልሆነ ጋዜጠኛ ባለሙያ እንዴት ይህንን እልህ አስጨራሽ ትግል ይመራዋል የሚል ጥያቄ ሊቀርብ ይችላል። ለዚህም በአጭሩ በአለም ላይ የነበሩትና አሁንም ያሉትን የታላላቅ ለዉጥ መሪዎች ማንነትን መለስ ብለን ስናጤን፤ ስንቶቹ ፖለቲከኞች ነበሩ የሚለዉ አፀፋዊ ጥያቄ ምላሹን ይሰጣል ብዬ አምናለሁኝ። ብዙዎቹ ለእዉነት የቆሙና በአርአያነትና በቁርጠኝነት የታገሉ ምሁራን፤ የህግ፡ የሀይማኖት፤ አልፎም ተራ ሰዎች ሆነዉ እናገኛቸዋለን። መሪ በሚያሳየዉ የአላማ ፅናት፤ በመርሁ፤ በተግባር መፈተኑና ሌሎችን ለትግል ለማነሳሳት ባለዉ ፋና ወጊነት ስለሚመረጥ እንዲህ አይነት ጥያቄ እስክንድርን በተመለከተ ሚዛን አይደፋም።

እኔ ምርጫዬን አደረኩኝ። እናንተስ? መሪ አሰባሳቢ ፈላጊዎች ከሆናችሁና እርሱ ምርጫችሁ ከሆነ እንሰባሰብ። በሱ ዙርያ የኢትዮጵያዊነት አንድነት መድረክ እንፍጠርና ተሰባስበን በጋራ እንዲመራን እንጠይቀዉ። ከእስር እንዲፈታም ታላቅ አለም አቀፋዊ ዘመቻ እንጀምር። በዘመቻዉና በሱም አመራር ለትግላችን አለም አቀፋዊ ድጋፍን እናሰባስብ። በዚህም ጥንካሬን በማግኘት አገራችንና ህዝባችንን እንታደግ። ያለዉን የሰጠ እንደሚባለዉ ይህ ለኔ የተሻለዉ አማራጭ ይመስለኛል። ከዚህ በፊትም ደጋግሜ እንዳቀረብኩት ትግል ያለ አቅም አይታሰብምና ተበታትነን ከምንጓዝ አዉራችንን በመምረጥ እንሰባሰብ። በመሰባሰባችንም አቅምን አጎልብተን የኢትዮጵያ ልጆች ይሰባሰባሉ፤ ሀገራችንም አጆቿን ወደ አምላኳ ትዘረጋለች፤ ታላቅም ሀገር ትሆናለች የተባለዉን ትንቢት በኛ ግዜ አዉን እናድርገዉ። እንደ ምናደርገዉም ጥርጣሬ የለኝም!

አምላክ ኢትዮጵያን ይባርክ!

Leave a Reply