Skip to content

Miscarriage of justice (Judge Woldemichael Meshesha)

Judge Woldemichael Meshesha writes about the gross miscarriage of justice in Ethiopia, including the injustice against Teddy Afro, in this article written in Amharic.

Click here for pdf.


“አሁንም በፍትህ ስም ለይቅርታ?!”


ዳኛ ወልደሚካኤል መሸሻ

ወዳሰፈርኩት ርዕስ በቀጥታ ከመግባቴ በፊት፣ በዳኝነት በፌዴራል ፍ/ቤትች ውስጥ በነበርኩበት ጊዜ ከነበሩት አንድንድ ገጠመኝ አሰራሮችን ጠቀስቀስ አድርጌ አልፋለሁ።

የባህል ዕሴቶቻችን፣

ኢትዮጵያ ዕንቁ የሆኑ የባህል ዕሴቶች ያሉባት አገር መሆኗን እኛ ብቻ ሳንሆን የዓለም ማህበረሰቡ የሚመስክረው ነው። ከነዚህም መካከል በሽምግልና ጉባኤ የሚሰጠው ፍትህ ዋነኛው ነው። ወንድም ከወንድሙ፣ እህት ከወንድሟ፣ እህት ለእህት፣ ባል ከሚስቱ በዘመዳሞች፣ ወይም በአጠቃላይ በኢትዮጵያዊያን መካከል ቅራኔ ሲፈጠር የሽምግልና ጉባኤ ይመሰረትና አንተም ተው፣ አንችም ተይ በማለት ይቅር ለእግዚአብሔር አስብለውና በዳዩ ለተበዳዩ እንዲክስ አድርገው ሰላም አውርደው ይመለሳሉ። የግድያ ወንጀል በተፈጸመ ጊዜም የጉማ የሽምግልና ጉባኤ ወዲያውኑ ከአካባቢው ማህበረሰብ ይመረጥና ገዳይን ከሟች ቤተሰብ ይቅርታ አሰጥቶ ያስታርቃል፤ ገዳይም ለሟች ቤተሰብ ጉማ(ካሳ) እንዲከፍል ያደርጋል። በዚህም በሁለቱ ቤተሰብ መካከል ተረግዞ የነበረው ብቀላ ከእንጭጩ ይቀጭና ሰላም ይወርዳል። መቆየት ደግ ነው ሆነና ዛሬ፣ ዛሬ ደግሞ የተገላብጦሽ ሆኖ የሽምግልና ሥራ በፍ/ቤት ተገን፣ በፍትህ ስም ተበዳይ በዳይን ይቅርታ እንዲጠይቅ ወደ ማድረግ ተሸጋግሮአል፣ ያውም ‘የሕዝብ ጠባቂ’ በሆነው መንግሥት።

የሰብአዊ መብት ጥሰት፣

እንደሚታወቀው፣ ወያኔ(ኢህአዴግ) በመንግሥትነት በኢትዮጵያ በትረ-ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ በሚያስተዳድረው ሕዝብ ላይ የሚፈጽመውን የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ ግድያና ሽብር ከቀን ወደ ቀን ከጊዜ ወደ ጊዜ ቅርጹንና ስልቱን እየለዋወጠ ቀጥሎአል። ሥልጣኑን በያዘ ሰሞን ራሱ እየገደለ፣ ለይምሰል እገሌ የሚባል ሰው ባልታወቀ ሰው መገደሉን፣ ፖሊስም ምርመራውን እያጣራ መሆኑን በሚቆጣጠሯቸው ሚዲያዎች ያስነገራል። ከቀናት በኋላ ነገሩ ቄሱም ዝም መጽሓፉም ዝም ይሆናል። ከዚያም ደሙ ደመከልብ ሆኖ እንዳይቀር ፖሊስን እባካችሁ እያለ የሚጨቅጭቀው ቤተሰብ ይሆናል። ግን ከከንቱ ጩኸት አያልፍም። ጠበቃውና የመስተዋት መጽሔት አዘጋጅ በነበረው በተስፋዬ ታደሰ ላይ የተፈጸመው ግድያ፣ በመምህራን ማህበር ዋና ጸሐፊ በነበረው በአሰፋ ማሩ ላይ በጠራራ ፀሐይ የተፈጸመው ግድያ በአጭሩ የተጠቀሰውን እዉነታ ለማሳየት በቂ ነው። እነዚህ በከተማው በግላጭ በሚታይበት፣ ይብዛም ይነስ የሕዝብ ጩኸት የሚሰማበት ሆኖ ነው እንጂ በየገጠሩ የሕዝብ ጩኸት በማይሰማበት የሚፈጸመውን መሰል ግፎችን እንዲያው ቤት ይቁጠረው ነው። በወንጀል ሰበብ እየተያዙና እየተወገሩ ወደ ዘብጥያ ወርደው አስተዋሽ አጥተው፣ ፍርድ ቤት እንኳ የማያውቃቸውን ሰዎች ቤት ይቁጠረው፤ በዚያም እንዳሉ ለአንዴና ለመጨረሻ ያሸለቡትን ቤት ይቁጠረው ከማለት ባለፈ በእንዲህ ባለ አገር ሌላ ምን ሊባል ይቻላል?

ይህ አሰራራቸው ሲነቃባቸው፣ ሲደረስባቸው የሽረባ መንገዳቸውን ይለወጡና የማይደረስባቸው መስሏቸው፣ ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ የጮሃል እንዲሉ፣ ገድለው፣ ጨፍጭፈው በሌሎች ላይ ማላከክ፤ ለገደልኋቸው ተጠያቂዎች ናቸው እንደማለት ዓይነት ያገጠጠና ያፈጠጠ ክስ በተቀናቃኞች ላይ ማቅረብ ሆኖአል ሥራቸው። ለነገሩ እነርሱ አላወቁትም እንጂ ሕዝቡ እንኳን አይደለም ሰርተው፣ እንኳን አይደለም ፈጽመው፣ በአንድ ወቅት ምን ለመሥራት እንዳሰቡ እያወቀባቸው መጥቶአል። እነርሱም ሕዝቡ እንደነቃባቸው አውቀውታል፤ ግን የተያያዙት አንደ ያዶቀነ ሰይጣን ሳያቀስ አይለቀም አይነት ሆነው ቀጥለውበታል። ተቀናቃኝ ነው፣ ጠንከር ያለ ተቃዋሚ ነው ያለውን ወደ ዘብጥያ ያወርደውና ሐሰተኛ ማስረጃዎችን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን ከራሳቸውና ከሆዳቸው በስተቀር፣ ስለምንም ደንታ በሌላቸው ሰዎች ድጋፍ ለመከላከልም አስቸጋሪ በሆነ መልኩ ማዘጋጀትና ማሰማት። ለዚህም ዓይነተኛ ምሳሌ አድርገን የፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስን፣ የቅንጅት መሪዎችና አባሎች እንዲሁም ሰብአዊ መብት ታጋዮችን ጋዜጠኞች ጉዳዮችን ልንወስድ እንችላለን። በውዱ የንጹሐን ደም ተበቃይ፣ የቁርጥ ቀን ልጅ በፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ ላይ የተፈጸመው በዚህ ዓይነት እንደነበረ በወቅቱ በምርመራው ላይ ነበርኩኝ ያለው ፖሊስ እውጭ በወጣበት ወቅት በሚዲያዎች ያጋለጠው ተደምጦአል። አብሯቸው ይሰሩ የነበሩት ናቸው የዚያን የጀግና ሰው ፊርማ ያለበትን ሰነድ አውጥተው ለፖሊስ ሰጥተው ለመንግሥት እኩይ ተግባር የተባበሯቸው። ጀግናና ወገንን አሳልፎ መስጠት ከክህደቶች ሁሉ የከፋ ክህደት ነው። ከአገር መሸጥ ተለይቶ የማይታይ ነው። ታዲያም እንዲህ ዓይነት ሰዎች አሉ፤ ይኖራሉም፤ ሳይሞቱ በቁም የሞቱ፣ ሳያሳድዷቸው የሚሸሹና የሚሮጡ፣ ጥላቸውን የማያምኑ ሆነው እንደቃዡ እድሜያቸውን ይጨርሳሉ። ከእንዲህስ ዓይነት ባህርይ፣ ከእንዲህስ ዓይነት ኑሮ አድነኝ ማለት ትልቅ ጸሎት ነው። አበው ጌታዬ አሟሟቴን አሳምርልኝ የሚሉትስ ለዚሁ አይደል?

የቅንጅት አመራርና የተቀነባበረው ክስ፣

የቅንጅት አመራርና ከምርጫ 97 ጋር በተያያዘ ወያኔ ያሰራቸውና የተቀነባበረ ክስ ባቀረበባቸው ጀግኖች ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ አሰጥቶ የእድሜ ልክ ካስፈረደባቸው በኋላ ይቅርታ አስጠይቆ የፈታቸው መሆኑ ይታወቃል። በምንም ምንም የማያውቁ በገንዘብ ኃይል ተገዝተው የቀረቡት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በማስረጃነት እንደሰማሁት በአብዘኛ የተቆጠሩት የቅንጅት አባል የነበሩትና ደጋፊ የተባሉ ናቸው። በምርጫ 97 የሆነውን ከሞላ ጎደል ሁሉም ኢትዮጵያው ያውቀዋል። የዘረኛ ፖለቲካ፣ የከፋፋይ ፖለቲካ ብሎም የሰው መብት ረገጣ ፖለቲካ ይዞ የገባው የወያኔ(ኢህአዴግ) መንግሥት ለይስሙላ ያህል ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት መርሆችን በሕገ መንግሥቱ ላይ በማስፈር ከእኔ በለይ ሰብአዊ መብት አስከባሪ፣ የዲሞክራሲ አባት የለም የለም ሲል የነበረ፣ ያለመታደለ ሆኖ ጠንካራና እርሱን የሚቋቋም ፓርቲ ያለመፈጠሩን፣ ቢፈጠር ግማሽ መንገድ ሄዶ እንደሚቀበል እስከ ግንቦት 1997 ዓ.ም ድረስ ሲያላዝን መቆየቱ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። ታዲያ በግንቦት 97 አገር-አቀፍ ምርጫ ደረሰና እንደ ጎርፍና እንደማዕበል ከኋላው አገር ወዳዱን፣ ኢትዮጵያዊነት ናፋቂውን ሰብአዊ መብቴን በምርጫ ማስከበር አለብኝ ብሎ የተነሳውን ሕዝብ አሰልፈው ሕብረትና ቅንጅት ብቅ አሉ። ልቡ በቁጭት እየነደደ የቆየውና ነጻነቱን፣ አንደበቱን፣ በአጠቃላይ ሰብአዊ መብቱን በምርጫ በዲሞክራሲ ጎዳና መሪውን ለመወሰን ከዳር እስከ ዳር የኢትዮጵያ ሕዝብ ታጥቆ ተነሳ። ይህንኑ ተናፋቂው ግንቦት 7 ደርሶ ህዝቡ በነጻነቱ እንዴትና ማንን መምረጥ እንደሚችል የኢትዮጵያ ሕዝብ ወያኔን እንዳሳየ ይታወቃል። እንደዚያ ጠንካራ ፓርቲ ከመጣ ግማሽ መንገድ እንቀበላለን ሲል የነበረው የወያኔ ቁንጮ በምርጫው ማግሥት የወሰደው ርምጃ፣ በዚያ ሰበብ እስረኞች ሳይቀሩ የተወሰደው የፍጅትና የእሥራት ርምጃ፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። እነዚያ በምርጫው መንግሥትን ለመመሥረት የሚያበቃቸውን ድምጽ አግኝቶአል ተብሎ የተነገረለት የቅንጅት ፓርቲ መሪዎች ሕዝቡ ድምጻችን ተሰርቆአልና ወደ ፓርላማ እንዳትገቡ ያሏቸውን ተቀብለው አንገባም ስላሉ ብቻ እንደ ወንጀለኛ ተቆጥረው ወደ ዘብጥያ መወርወራቸውን እናስታውሳለን። ቀጥሎም የወንጀል ዓይነቶች እየተለቀሙ ተመሰረተባቸው። በተለይ ሁኔታውን በቅርብ ይከታተሉ የነበሩት አዋቂዎች፣ የሕግ ሰዎች ክሱንስ ይመስርቱ ግን ምን ማስረጃ ሊያቀርቡቧቸው ይሆን? እያሉ ነበር በአግራሞት። በሌላም ደግሞ ወያኔ ማለት ሃይል ማለት ነው፤ ወያኔ ማለት ጡንቻ ማለት ነው። እናም ማስረጃ ማቅረብ ምን ይሳነዋል አንዳንዶቻችን እንል ነበር። እንዳየነውም የሆነውን አድርገውታል።

በነገራችን ላይ የዚያ ክስ አመሰራረት፣ የችሎቱን ዐቃቤ ሕግ ከመሰየም ጀምሮ ፍጹም በየትኛውም ዓለም ጥንትም ዛሬም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የተፈጸመ እንደነበር ይታወቃል። ሺመልስ ከማል ወያኔ ሥልጣን እንደያዘ የማዕከላዊ ፍ/ቤት የከፍተኛ ፍ/ቤት ዳኛ የነበረ፣ ሕገ መንግሥቱ ታውጆ ፌዴራል ፍ/ቤቶች ሲመሠረት የተቀነሰ፣ የጥብቅና ገበያው አላዋጣ ሲለው ወደ ግል ጋዜጣ(ምኒልክ) አዘጋጅነት ዞሮ የነበረ፣ ይህም አላስኬደው ሲል ወደ ወያኔ(ኢህአዴግ) በአባልነት ጥልቅ ያለ፣ ከዚያም የዜና አገልግሎት ድርጅት(Broadcast Agency) ተብሎ በኢትዮጵያ ሚዲያዎችን እንደ ራዲዮኖችና ቴሌቪዥኖች ሲቋቋሙ ፈቃድ ለመስጠትና ለመቆጣጠር የሚያስችል ሥልጣን የሚያሰጥ የብሮድ ካስት አዋጅ ወደ 1989 ዓ.ም አካባቢ ሲታወጅ፣ የዚሁ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ሆኖ ተሾመ። ድርጅቱ ግን እስከአሁን ድረስ በተግባር ላይ ያልታየ ነው። ልክ የቅንጅት መሪዎችና በተመሳሳይ በምርጫ 97 ምክንያት ወደ እሥር የተወረወሩት ጉዳይ ሲከሰት እንደሙስና አዋጁ በአንድ ሌሊት ሺመልስ የዐቃቤ ሕግ ሰራተኛ ሆኖ በቅንብር የተዘጋጀውን ክስ ይዞ ወደ ፍ/ቤት ብቅ ማለቱ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። ከማል ከዚያ ከነበረበት መ/ቤት በአንድ ሌሊት በተደረገ ጥቆማ ተሹሞ ወደዐቃቤ ሕግነት የዞረው። የዐቃቤ ሕግ ምሥሪያ ቤት በፍትህ ሚኒስተር ሥር ሲሆን፣ ብሮድ ካስት የዜና አገልጎሎት ድርጅት እንደማቋቋሚያው አዋጅ ራሱን የቻለ መሥሪያ ቤት ነው። ልክ የሆነው እነ ብርቱካን በስዬ አብርሃ ጉዳይ የዋስትና መብቱ እንዲከበርለት በሰጡት ትዕዛዝ ምክንያት በሙስና የተጠረጠረን ሰው ሁሉ የዋስትና መብት የሚነፍግ አዋጅ በአንድ ሌሊት እንደ ወጣ ዓይነት ነው የከማል ሹመት። ሌላው አስገራሚው ደግሞ ረዳት ሆኖ የቀረበው ሁሴን መሐመድ ከፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ዳኝነቱ በዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ውሳኔ በሙስና ወንጀል የተባረረው መሆኑ ነው። ይጠበቅ የነበረው በዚህ ሰው ላይ ክስ ይመሰረትበታል ተብሎ እንደነበር ነው። በወቅቱ የሽመልስ እንደዚያ መተተታጠፍ እየገረማቸው፣ በተለይም የሕግ ሰዎች የዘመኑ የሕግ ሰው ካታሊስት ይሉት እንደነበር ትዝ ይለኛል።

በወቅቱ ብዙ ልምድ ያላቸው ዐቃቤ ሕጋውያን እያሉ የሺመልስ ከማል በእንዲህ ወደ ዐቃቤ ሕግነት መምጣቱ፣ ወንጀለኛ ተብሎ ከፍርድ ቤት የወጣው የሁሴን መሐመድ መጨመሩ ለምን ይሆን? ከሚል ጥያቄ ተነስተን ምናልባትም፣ እዚያው ፍትህ ሚኒስተር ያሉ ዐቃቤ ሕጎች ክሱን ለማዘጋጀት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተው ይሆን? እያልን ግራ ቀኙን እንዳስስ ነበር። ለጥርጣሬያችንም መሠረቱ፣ አልፎ አልፎ በሰዎች ላይ የሚቀርበው ውንጀላና ክስ በሕግ አግባብ አይደለም በማለት በተናጠል ለሰለጠኑበት ሙያ ዘብ የሚቆሙ ዐቃቤ ሕጎች አልጠፉም፤ አይጠፉምም። ለምሳሌ እንደ አለማየሁ ዘመድኩን የመሳሰሉት። አለማየሁ ዘመድኩን በአሁኑ ጊዜ በስደት አሜሪካን አገር የሚኖር ሲሆን፣ ስደት ከመውጣቱ በፊት በፍትህ ሚኒስተር የአንድ መምሪያ ሃላፊ ነበር። መንግሥት በበለጠ በቅንጅት መሪዎች ላይ ጫና ለማሳደር በዚያ ከምርጫው በኋላ በተደረገው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ምክንያት ለወደመው ንብረት በሃላፊነት እንዲጠየቁ ክስ እንዲመሰረትባቸው ሲታዘዝ ፈቃደኛ ባለመሆን አገር ጥሎ በመውጣት ሊያጋልጥ ችሎአል። ሌሎችም በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ሲጠየቁ ፈቃደኛ ያልሆኑ ግን ምንም አይነት ሥራ እንዳይሰሩ እንደዕቃ እንዲቀመጡ የሚደረጉ፣ ወይም በሁለት መስመር ትዕዛዝ ከሥራ የሚባረሩ አሉ። ታዲያም የተገላቢጦሽ ሆነና አንድ ሰው ወንጀል ሰርቶአል በሚል ጥቆማ ሲደርሰው፣ ያለ አግባብ እንዳይያዝ፣ ችግር እንዳይደርስበት፣ ሰብአዊ መብቱና ስብዕናው እንዳይነካ ከዳኛ በፊት የሚታገለው፣ መብቱን የሚያስከብረው የዐቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤትና ዐቃቤ ሕጉ ነው። ይህ አለም አቀፍ መርህ ነው። በተለየም በኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕጉ ላይ በግልጽ ተደንግጎአል። ያለ መታደል ሆኖ ገዢዎቻችን እጃቸውንና እግራቸውን ጥልቅ እያደረጉበት የሕጉ መሰረታዊ መርሆዎች ደብዛቸው እየጠፋ ሂዶ አሁን ወዳለንበት ደርሷል። ሁሉም ለዳኛው ነው የሚወረወረው። መቼም ሕሊና ያለው ሰው፣ ያ ከምርጫው በኋላ በመንግሥት ሕዝቡ ላይ እንደዚያ ሲፈጸም ያየ ሰው፣ ክሱም የፈጠራ መሆኑ ይታወቃል። እንደዚያ ዓይነት ክስ ተዘጋጅቶ ደረቱን ነፍቶ ወደ ፍ/ቤት ይዞ ይወጣል ብሎ መገመት በእጅጉ አስቸጋሪ ይሆናል። ግን ሽመልስ አይኑን በጨው ታጥቦ የሞት ፍርድ ካልተሰጠባቸው በማለት ተከራክሮአል።

ከፍ/ቤት ገጠመኞች፣

አንዳንድ ዐቃቤ ሕጋውያን አንዳንድ የማያምኑባቸውን ጉዳዮች ሲሰጣቸው ተቃውሞ ቢያቀርቡም፣ ምን አገባህ? ዳኛ ይበለው፣ አንተ ብቻ አቅርብ እየተባለ በጭንቀት ይዞ ወደ ፍ/ቤት የሚወጡ አሉ። ለዚህም በፍ/ቤት በነበርኩበት ወቅት ካጋጠሙኝ ሁለት ጉዳዮች ምክንያት ጉዳዮቹን ይዘው ቀርበው የነበሩት ዐቃበ-ሕጋዊያን የመለሱልኝ ቃል አስረጅ ይሆናል ብዬ አስባለሁ። እ.ኢ.አ በ1993 ዓ.ም ይመስለኛል ጠበቆችን ለመቆጣጠር በሚል በአብዘኛው የቆዩና በዳኝነትና በጥብቅናው መስክ የብዙ ጊዜ ልምድ ያላቸውን ከገበያው የሚያስወጣ አዋጅ በፍትህ ሚኒስተር አማካይነት መንግሥት አዋጅ ያወጣል። በአዋጅ መሠረት በሚል ወዲያውኑ ከጥቂት የአዋጁን መስፈርት ያሟላሉ ከሚሏቸው በስተቀር፣ የአብዘኛዎቹ የጥብቅና ፈቃዳቸው ይታገዳል። ወያኔ የሚያስፈራኝ ክፍል ነው ወይም አካል ነው፣ወይም ሰው ነው ካለ፣ ያለ ምንም ርኅራኄ እንዴት እስከ ግል ሕይወት ድረስ እንደሚገባ ይህ ሁኔታ እውነታውን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ መስተዋት ነው ብዬ እገምታለሁ። ለምን በጠበቆች ላይ? በአዕምሮአችሁ ሳይጫር እንዳልቀረ እገምታለሁ። ነገሩ ባጭሩ እንዲህ ነው እላለሁ። በተለይ በአዲስ አበባ ታዋቂ ጠበቆች፣ ፕሮፌሰር አሥራት ሲታሰሩ፣ ዶ/ር ታዬ ሲታሰር በነጻ ያለክፍያ ለመከራከር በአብዘኛው ተሰልፈው እንደነበር አስታውሳለሁ። ለነገሩ ከአዋጁ በኋላ ሆነ እንጂ፣ በቅንጅት ጉዳይ ላይ እኔ፣ እኔ ተባብለው በሽሚያ በእሰረኞቹ ውሳኔ እስከተሰናበቱ ድረስ፣ ከሰባ በላይ ጠበቆች በነጻ ለመከራከር ተሰልፈው እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። እናም ወያኔ-ኢህ አዴግ አገሪቱን በመንግሥትነት ከተቆጣጠረበት ጊዜ አንስቶ ጠበቆች በተገኘው ቀዳዳ እየገቡ ለመንግሥት ነቀርሳ ከመሆን እንዳልተቆጠቡ አውቃለሁ። እናም፣ ለአዋጁ መንደርደሪያ ሆኖ የቀረበው የጠበቆች ሙስና ውስጥ መዘፈቅ የሚል ይሁን እንጂ፣ ዋናውና ድብቅ ምክንያቱ ይህ አድራጎታቸው እንደሆነ ሕሊና ለነበረው ሰው መገመቱ አስቸጋሪ አልነበረም። በአውጁ ንድፍ(draft) ላይ ውይይት ሲደረግ የተገኘነው ዳኞች በወቅቱ በከፍተኛ ስሜት ተቃውመን ነበር። ሰው ጤፉ የሆነው መንግሥት ሁሌ እንዲህ ዓይነት ሕጎችን ካስቀረጸ በኋላ ለውይይት የሚያቀርበው ገንቢ አሳቦችን ለመቀበል ሳይሆን ሕዝቡን አወያይቻለሁ፤ ሕዝቡም የዲሞክራሲ መብቱን ተጠቅሞ አዋጁ ወይም ሕጉ እንዲወጣ ወስኖአል ለማሰኘት ነው።

ታዲያም እነዚያ የታገዱት ጠበቆች እግዱ እንዲነሳ ክስ በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በፍትህ ሚኒስተር ላይ ክስ ይመሰረታሉ። ክሱ የፍትሐብሄር እንደመሆኑ መጠን፣ ጉዳዩ እልባት እስከሚሰጠው ድረስ በፈቃዳቸው ላይ የተደረገው የእገዳው ትዕዛዝ እንዲታገድላቸው ያቀረቡትን አቤቱተ ፍ/ቤቱ ተቀብሎ እግዱ ለጊዜው እንዲነሳ ትዕዛዝ ይሰጣል። በዚህ ላይ ቅር ተሰኝቻለሁ በማለት ለፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ያቀርባሉ። በፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ጉዳዩን በአቶ ሐጎስ ወልዱ ሰብሳቢነት ያየው ችሎት የከፍተኛውን ፍ/ቤት ትዕዛዝ ይሽራል። ጠቅላይ ፍ/ቤቱ ትዛዙን ሲሽር መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ፈጽሞአልና ይታረምልን በማለት አቤቱታቸውን ጠበቆቹ በጠቅላይ ፍ/ቤቱ ለሰበር ችሎት(court of cessation) ያቀርባሉ። በወቅቱ እኔ በዚሁ ችሎት ከመሥራቴም በላይ እያጠናሁ የማቀርበው እኔ ነበርሁ። የዚህ ችሎቱ ሰብሳቢ የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት ወይም ም/ፕሬዚዳንት ነው። አቤቱታው ያስቀርባል አያስቀርብም ለማለት ከሰብሳቢዎች ጋር ሦስት ዳኞች ነን የምንቀመጠው። አዋጁ በጣም አስቀያሚ አዋጅ ነበር። በሙሉ ሲነበብ ትርጉም የሚሰጥ አንድ የመሸጋገሪያ ድንጋጌ አገኘሁ። ከሌሎች ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ቢያንስ በመጀመሪያ ደረጃ ጥብቅና መብት ለማስገኘት የሚያበቃ። መጀመሪያ በዳኝነት የብዙ ጊዜ ልምድ ያለው አብዱልቃድር መሐመድ የሚባል ዳኛን ማሳመን እንደሚገባኝ ዘየድሁ። እርሱ ባለቤቱ በጠና ታማበት በሆስፒታል አስታማሚው እርሱ ስለነበር በሳምንት ሁለት ቀን ብቅ እያለ ነበር የሚሰራው በወቅቱ። ሁሉን ነገርሁት፣ የአዋጁን አተረጓገሙንም አሳየሁት፣ ተስማማን። ምክትል ፕሬዚዳንቱን አቶ መንበረፀሐይን እንዴት አድርገን እንደምናሳምን ተነጋገርን። ይዘን ወደ ቢሮው ሄድንና እንዴት አድርገን የአንድ ሚኒስተርን አስተዳዳራዊ ውሳኔን እንሽራለንና የመሳሰሉት ነጥቦችን እያነሳ ቢያስቸግረንም፣ እኛም ፍ/ቤት በሕግ አግባብ ያልሆነን ጉዳይ ካላረመ ሕጋዊነት ከቶ እንዴት ሊኖር ይችላል? ዋናው ነገር እኛ አዋጁን ተረጎምን እንጂ አዋጁን አልሻርነውም በሚሉትና በመሳሰሉት ተከራክረን ተቀበለን። እናም አቤቱታው ያስቀርባል በማለት ትዕዛዝ ከሰጠን በኋላ የጠቅላይ ፍ/ቤቱን ውሳኔ አገድነው። በኋላም ዋናው ጉዳይ እንደዚሁ በተመሳሳይ ሁኔታ ሲመጣ ለመወሰን የተደረገው እጅግ እልህ አስጨራሽና ፈተና ነበር። ሆኖም በመጨረሻ ተሳክቶልን እነዚያ ጠበቆች ይነስም፣ ይብለጥ ጾም ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዳያድሩ አድርገናል።

በነገራችን ላይ ይህን ሕግ ነድፎ በማውጣት ያስወሰነውና በጠበቆች ጥርስ ገብቶ የነበረው፣ በነፕሮፌሰር አሥራት ላይ፣ በዶ/ር ታዬ ላይና በታምራት ላይ ክሶቹን መስርቶና ተከራክሮ ያስወስን የነበረውና በኋላም ወደ ፍትሕ ሚኒስተር ም/ሚኒስትር ያደገው መስፍን ግርማ እንደነበር ይታወቃል። በእንዲህ ካሰሩት በኋላም በሙስና ሰበብ በአንድ መስመር ጽሑፍ ከሥራው እንዳባረሩት ይታወቃል። የጥብቅና ፈቃድ አውጥቶ ወደ ፍ/ቤት ሲቀርብ እነዚያ አዋጁ የወጣባቸው ጠበቆችች መላወሻ መድረሻ አሳጥተውት፣ በጨረሻም እዚያው ከፍተኛ ፍ/ቤት አጠገብ ወደ 1992 ዓ.ም አካባቢ እሁድ ዕለት ጸጉሩን ለመስተካከል ደሴ ሆቴል አጥገብ ወዳለ ጸጉር አስተካካይ ለመግባት ትንሽ ሲቀረው፣ በመንገድ ዳር የቆመች የትራፊክ ምልክት የያዘች ብረት በመኪና ተገጭታ ጭንቅላቱን መታችውና ከሰአታት በኋላ ነፍሱ ሊያልፍ ችሎአል። እንደሰማሁት፣ በዚያ ትልቅ ሰው መሳይ ቀብር ላይ የተገኘ ሰው ከሰባት ያልበለጠ እንደነበር ነው። ፣ የሕዝብ ዓይን በስውር ይወጋል። ጊዜው ይዘገይ እንጂ በክፉዎች ላይ የኢትዮጵያ አምላክ ፍርዱን ይሰጣል። በደርግ ሥልጣናትም ላይ ያየነውና እያየን ያለነው መሰል እውነታ ነው። ብቻ ችግሩ አይነጋ መስሏት… ዓይነት እየሆነ መሄዱ ላይ ነው።

በሌላም ታምራት ላይኔ ከአላሙዲን በሙስና መልክ 16ሚሊዮን ብር መውሰዱ በማስረጃ ተረጋግጦበታል በሚል ተወስኖበት፣ ሼህ አላሙድን ገንዘቡ እንዲመለስለት በጠቅላይ ፍ/ቤቱ ለሰበር ችሎቱ አቤቱታ በአንድ በኩል ሲያቀርብ፣ መንግስትም በፍትህ ሚኒስተር አማካይነት ገንዘቡ ወንጀል ነክ በመሆኑ ለእኔ ይገባኛል በማለት የራሱ አቤቱታ አቅርቦ ነበር። በወቅቱ የፍ/ቤቱን ውሳኔ እንደተመለከትነው፣ አላሙዲን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስተርነት ቦታ የነበረው ታምራት ላይኔ አገራችን እዳዋን የምትከፍልበት አጥታ ችግር ውስጥ ገብታለችና ወደፊት ቡና ተሰጥቶህ ይመለስልሃል ተብሎ ነው ገንዘቡን የሰጠው። በወቅቱ ሼህ አላሙዲን ለታምራት ገንዘቡን የሰጠውም አንድም ተታሎ ነው ወይም ፈርቶ ተገዶ ነው የሚል ግምት ኖሮናል። ያም ሆነ ይህ፣ በወንጀሉ ፍርድ መሰረት ገንዘቡ ከአላሙዲን የተወሰደው ያለአግባብ ተብሎ ነው። እንዲህ ከሆነ ደግሞ ገንዘቡ መመለስ ያለበት ለሼህ አላሙዲን እንጂ ለመንግሥት ያለመሆኑን በመተንተን ወሰንን።

ይህን ጉዳይና የነዚያን የጠበቆችን ጉዳይ ይዘው የቀረቡት በፍትህ ሚኒስተር የብዙ ጊዜ ልምድ ያላቸው ሁለት ዐቃቤ ሕጋውያን ነበሩና ከወጡ በኋላ ጠርቻቸው ኧረ ለመሆኑ እናንተ እንደዚህ ዓይነት ክርክሮችን የምታደርጉት አምናችሁበት ነው? ብዬ ጠየቋቸው። አይ አቶ ወልደሚካኤል አለኝ አንደኛው ዐቃቤ ሕግ! በቃ እኔ አሁን፣ አሁንስ ሕግን ለመማር የወሰንኩባትን ቀን እየረገምኋት ነው አለኝ። በኛ አገር በፍጹም ሕግ መማር አያስፈልግም አለኝ። ልጆቼ ወደ ሕግ ትምህርት ቤት ለመግባት እንዳያስቡ እያደርግሁ ነኝ። የምንሰራው የሕግ ሳይሆን፣ የተላላኪነት ነው አለኝ። ግን የምንሰራው አእምሮአችን እየቆሰለ ነው። ዛሬ ለምን እንደደፈርሁ አልገባኝም? በቃ የሆዴን ተነፈስሁልህ እንዳለኝ ሁለቱም ከቢሮዬ ተያይዘው ወጡ።

የሕግ ሰው በኢትዮጵያ ውስጥ የተላላኪነት ሥራ እንዲሰራ ተደርጎ መታየቱን ነገረ-ፈጅ በነበርኩበት ወቅት ጠንቅቄ አውቃለሁ። አንድም አስመርሮኝ ወደ ፍ/ቤት ያስገባኝ ይኸው ነበር። የኛ አገር መሪዎች ሁሉን ነገር አዋቂዎች ናቸው። ለሙያ ክብር አይሰጡም። ወያኔ-ኢህአዴግ ደግሞ ይብሳል። ራሱ ያወጣውን ሕግንም ይጥሳልና። በፍ/ቤቶች የመንግሥት ጣልቃ ገብነትን ለመቀነስ በሕገ-ምንግሥቱ ላይ የፍ/ቤቶችና የዳኞች ነጻነት ተደንግጎአል። በእንዲህ ቢደነገግም፣ የይስሙላ ሆኖ ይገኛል። ይህን በሕግ የተሰጠውን መብት የማስከበር ትልቁ ሥልጣንና ሃላፊነት የተጣለው በፍ/ቤቶች መሪዎች ላይ ነው። የኛ ፍ/ቤቶች መሪዎች በተለይም የፌዴራል ፍ/ቤቶች በተቃራኒው ነው የተሰለፉት። እናም፣ በፍ/ቤቶቹ የፍትህ መዛባት፣ መሞትና መውደቅ ከተጠያቂነት የሚያመልጡ አይሆኑም። ለነገሩማ በሕግ እንደኛ ሰፍሮ ሳይሆን፣ በልማድ ዳኛንና ፍ/ቤትን ማክበር ሁሉም አፍሪካ አገሮች እንደሰለጠኑት አገሮች ባህል አድርገውታ። ይህንኑ አንድ ጊዜ በአፍሪካ ለእንግሊዝኛ ተናጋሪ አገሮች ዳኞች በሲዋዚላንድ በተዘጋጀው የአእምሮአዊ ሀብት(Intellectual property) ስምፖዚየም ላይ ተገኝቼ ከየአገሮቹ ዳኞች አረጋግጫለሁ። ያለመታደል ሆኖ እንዲህ ያለው ነጻነት በኛ አገር በሕግም ተቀርጾ ይብሱን እየተሽመደመደ ሄዷል።

ከሕግ በላይ ምንም የለም እንላለን። እንዲህ ከተባለ ደግሞ ይህንኑ ለማስፈጸም መሳሪያ የሆነውን ፍ/ቤት ማክበር ከሁሉም ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። ስለሰላም ሲጠቀስ፣ ስለደህንነት ሲጠቀስ፣ ስለመናገርና መጻፍ፣ ስለፍትህና ስለዲሞክራሲ ሲጠቀስ፣ ብሎም ስለሰብአዊ መብት ሲጠቀስ፣ ከበስተኋላው ፍ/ቤት አለ። የመጨረሻው ገላጋይ ነውና። አንድ የድሮ ዳኛ አብሪያቸው በከፍተኛ ፍ/ቤት ስሰራ፣ አንዳንድ በችሎቱ የሚያስቸግሩ ተጠርጣሪዎችን ሲያስጠነቅቁ ዋ! ይህ ፍ/ቤት ነው፤ ሰይፍ ነው፤ ይቆርጣል ይሉ ነበር። አካሄዳቸው ትክክል ባለመሆኑ ልናስለውጣቸው ብንችልም፣ ግን በሌላ ጎኑ አባባላቸው ሲወሰድ ፍ/ቤት ክቡር ነው፣ ከሁሉም በላይና የማይደፈር ነው የሚያሰኝ እንደምታ ያለው ነው።

ከፍ ሲል በዐቃቤ ሕግነታቸውና ምለው በገቡት ቃል መሠረት ምንም ዓይነት ጫና ከአለቆቻቸው ቢደርስም፣ እምቢ አሻፈረኝ ባዮች እንደመኖራቸውም ከዳኞችም እንዲሁ አሉ። ከፍ ሲል የጠቃቀስኳቸው ሁለት ጉዳዮች የኔ ታላቅ ተግባር ለመግለጽ ሳይሆን እገረ መንገዴን የአንዳንድ ጉዳዮችን ሁኔታ በምሳሌነት ለማስታወስ ነው። በአገራችን የዳኝነት ተቋሙ ተከላካይ አጥቶ እየሞተ ይሂድ እንጂ ቆራጥ ዳኞችንም ፍ/ቤቶቹ አላጡም። ቀደም ሲል ኢህአዴግ በትረሥልጣኑን እነደያዘ በተነደፈው ቻርተር(መሰል ሕገመንግሥት) መሠረት የተቋቋመው ማዕከላዊ ፍ/ቤቶች፣ ከአሁን ሕገመንግሥት በኋላ በፌዴራል ፍ/ቤቶች የተተካው በሥራ ላይ በነበረ ጊዜ የነ መንግሥቱ ኃይለማሪያም ጉዳይን የጊዜ ቀጠሮ የሚያየው ማዕከላዊ ከፍተኛ ፍ/ቤት እንደነበር፣ በተለይም የእንዳለ ተሰማን የሐቤስ ኮርፐስ(habeas corpus) ወይም የተያዘው ሰው በአካል ፍ/ቤት ቀርቦ ጉዳዩ በሕግ የእንዲታይ ጥያቄ ያስተናግድ የነበረው ችሎት ልዩ ዐቃቤ ሕግ እንዳለ ተሰማን የያዘበትን ምክንያት ቀርቦ በማስረጃ እንዲያስረዳ በታዘዘ ጊዜ ቀርቦ ባለማስረዳቱ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕጉ መሰረት ከእስር ይለቁታል። ልክ እነ ብሩቱካን ሥዬ አብርሃን በለቀቁበት ጊዜ እንደተፈጸመው ዓይነት እንዳለ ተሰማ የተያዘው በር ላይ እንደነበረ አስታውሳለሁ። ከችሎቱ ዳኞች አንዱአሁን በጥብቅና ሥራ ላይ የሚገኘው ጥበቡ ምህረቴን አስታውሳለሁ። በሙሉ የፌዴራል ፍ/ቤቶች ሲቋቋሙ እንዚህም ዳኞች የመባረር ዕጣ አጋጥሟቸዋል። እንግዲህ ወያኔ እጁን ወደ ፍ/ቤት ያስገባው በዚህን ጊዜ ነበር። ከዚህ በኋላ ዳኞች በዓይነ-ቁራኛ ይታዩ ጀመር። በያለበት በዳኞች ላይ ዘመቻ መካሄድ እንደተጀመረ አስታውሳለሁ። ዳኛ እያስቻለ እያለ እስከነካባው ከችሎት እየተወሰደ ወደ እስር ቤት ይወረወር እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። ብዙ ዳኞች ሥራቸውን እየለቀቁ ወደ አዲስ አበባ ፈለሱ። በተለይም በደቡብ ክልል፣ በቤንሻንጉል፣ በጋንቤላ፣ በአፋርና ሱማሌ በመሳሰሉት ክልሎች በዳኞች ላይ ብዙ ግፎች እንደተፈጸመባቸው ከየአካባቢው ይመጡ የነበሩት ይነግሩን እንደነበር አስታውሳለሁ።

በመሰረቱ በወቅቱ ኢህአዴግ የደርግ ሹሞችን እየያዙ ወደ ዘብጥያ ሲያወርዱ ቤተሰብ የሐቤስ ኮርፐስ ጥያቄ ይዞ ወደ ፍ/ቤት ይቀርባል። ዳኞችም ዐቃቤ ሕግ ሰውዬው ለተያዘበት ብቁ ማስረጃ ካላቀረበ በነጻ ይለቁታል። ታዲያ ይኸው እየቀጠለ ሲሄድ ዳኞች ለመንግስት ወገንነታቸውን ፍጹም አያሳዩም ማለት ተጀመረ። በዚህም በዳኞች ላይ የሚደረገው ዘመቻ በያለበት ተጧጧፈ። በተለይም በክልሎች ይብስ ነበር። ከሁሉ፣ ከሁሉ በደቡብ አዋሳ ዙሪያ ወረዳ አካባቢ ይመስለኛል በአንድ ዳኛ ላይ ተፈጽሞአል ተብሎ የተነገረው ለሰሚው እጅግ አሰቃቂ እንደነበር ነው። በወቅቱ ማቆጥቆጥ በጀመሩት የግል ጋዜጦች ላይ ዜናው ወጥቶ ማየቴም ትዝ ይለኛል። ባልሳሳት የአዋሳ ዙሪያ ወረዳ አስተዳዳሪው ትዕዛዝ አንድ ሰው ይታሰራል። ዳኛው ጉዳዩን ካየ በኋላ ሰውየውን በነጻ ይለቀዋል። ከዚያ ችሎት ዳኛው ሳይነሳ ካባውን እንደለበሰ ከችሎቱ ተነስቶ ወደ እስር ቤት እንዲወርድ ይደረጋል። እንዲታሰር ያደረጉት ደግሞ በጋዜጣው ላይ እንደተገለጸው እርሱ ከፈረደባቸው ፍርደኞች ጋር እንደነበረ፣ እነዚያም ይህን ዳኛ ሽንት ቤት ወስደው በፊቱ ላይ እየሸኑበት እንዳሰቃዩት መስማቴና ከጋዜጣውም ማንበቤ ትዝ ይለኛል። ይህ የወረዳው አስተዳዳሪ የነበረው በኋላ የመጀመሪያው ፓርለማ ሲቋቋም ከክልሉ በግል ተመርጦ ወደ ፓርለማ ገብቶ፣ በዳኞች የእሙንቲ ወይም እንደማንኛውም ሰው ያለመከሰስ መብት ላይ ውይይት በምክር ቤቱ ላይ ሲደረግ ከመለስ ተቀብሎ ዳኛ ምንድነው? ከማን ይለያል? የምን እሙንቲ ነው? በሚል በአጽንዖት ተከራክሮ እንዲከሽፍ ካደረጉት አንዱ ሰው በስተመጨረሻም የቅንጅት አባል ሆኖ ታስሮአል። ይህም አቶ እጅጉ የሚባል መሆኑ ተነግሮኝ ሰውየውንም አይቼዋለሁ። እናም ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ፍ/ቤቶች ላይ በክፉኛ ዓይናቸውን የተከሉት ዛሬ ሳይሆን ቀደም ብለው ቢሆንም፣ የአሳ ግማቱ ከአናቱ እንዲሉ ከአናት ዳኝነቱ ወርዶ እየተቀበረ ቢሆንም፤ አሁንም ለሙያቸው፣ ምለው ተግዝተው ለገቡት ቃል በተናጠል በልበ-ሙሉነት የሚቆሙ ዳኞች አሉ። ችግሩ ከመንግሥት ጋር የተያያዘ ጉዳይ ሲቀርብ፣ አሁን አሁንማ ወደ አንድ ውስን ችሎት ሳይሆን ጉዳዩ የሚመራው፣ በጣም ታማኝ ናቸው የተባሉ ዳኞች ይመረጡና አዲስ ችሎት በመንበረፀሐይ ትዕዛዝ መሰየሙ ነው። በቅንጅት መሪዎችና መሰል ተከሳሾች ጉዳይ ላይ የተፈጸመው በዚህ መልኩ ነው። በስበዕናቸው፣ በአቋማቸው ጠንካራ የሆኑ፣ ግን በብሔረሰብ ስብጥራቸው ምክንያት ኢህአዴግን የማይደግፉ ናቸው በሚል ምክንያት ለሹመት ያልታደሉ ዳኞች በፌዴራል ከፍተኛና የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤቶች እንደሚገኙ እስከወጣሁበት ጊዜ ድረስ አውቃለሁ።

የቅንጅት መሪዎችና አባሎች እንዲሁም አብሯቸው የተከሰሱት የሕሊና እስረኞች መሆናቸውን ገልጸው የማይከራከሩ መሆኑን ለፍ/ቤቱ ነግረው እስከመጨረሻው ያለመከራከራቸው ይታወቃል። ይሁንና እንዲህ በሆነ ጊዜ ጉዳዩን የሚያየው ፍ/ቤት ለፍትህ ሲል ሕግ ያስገድዳልና የክሱን አቀራረብን በሚመለከት ማለትም ያስከስስ አያስከስስ እንደሆነ በወ.መ.ሥ.ሥ.ሕግ ቁጥር ከ117_119 ባሉት ድንጋጌዎች መሠረት ማጣራት፣ በኋላም በማስረጃዎቹ ብቃት ላይ እውነቱ ነጥሮ እንዲወጣና እንዲታይ በማጣሪያ ጥያቄዎች መጠቀም ይኖርባቸዋል። የቅንጅት መሪዎችና ሌሎች ተይዘው የታሰሩበት በይፋ እንደሚታወቀው በመራጩ ጥያቄ ምክር ቤት አንገባም ስላሉ እንደሆነ የአደባባይ ምስጢር ነው። በመሠረቱ በማስረጃ አቀራረብ ከሁሉ የሚቀድመው የአይን ምስክር ነው። የጽሑፍና የመሳሰሉት ብቻ የሚቀርቡት የዓይን ማስረጃ በታጣ ጊዜ፣ ወይም ለዓይን ማስረጃ በደጋፊነት ነው። በቅንጅት ላይ የተሠራው በተቃራኒው ነው። በመጀመሪያ በልበ-ሙሉነት ዐቃቤ ሕግ ያስረዳልኛል ብሎ ያቀረበባቸው ማስረጃ በአብዘኛው ከምርጫው በፊት ፓርቲው ለምርጫ ቅስቀሳ ያደረጋቸውን ንግግሮች የያዙ ሰነዶች፣ የኤሌክትሮንክስ መሳሪያዎችና የመሳሰሉ ነበሩ። የኋላ ኋላ የማስረጃዎቹ ባዶነት በሚያሳፍር ደረጃ ላይ መድረሱን ሲያዩት ደግሞ፣ ለሆዳቸው ያደሩ፣ ሕሊናቸውን የሸጡ ሰዎችን በማስጠናት አምርተው እንዳቀረቡ ምስጢር አልሆነም። ምንም እንኳ ውጤቱ ይለወጣል ተብሎ ላይገመት ቢችልም፣ እንደዳንኤልና ነጻነት ሌሎቹ ተከራክረው ቢሆኑ ኖሮ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ አይደለም፣ የአለሙ ማህረሰብ፣ ጉዳዩን እንደጉዳያቸው አድርገው የሚከታተለው ሁሉ ፍጹም ድራማ፣ ታይቶ የማይታወቅ ድራማ በፍትህ መድረክ ያዩ፣ ይሰሙ ነበር እላለሁ። ያም ሆኖ ግን፣ ከእስራቱ ጀምሮ እስከ ተፈቱ ድረስ በቅንጅት ላይ የተሰራው ድራማ ግልጽ ድራማ የፍ/ቤቱን ሥራና አካሄድ፣ ከድጥ ወደ ማጥ የከተተ፣ የመንግሥትን ጣልቃገብነት ከመቼውም ጊዜ ያጎላ እንደነበር ማየት ተችሎአል። ለዚህም ማስገንዘቢያ ሌላ ሳያስፈልግ፣ መከላከያዎችን ለማቅረብ ይፈልጉ አይፈልጉ እንደሆነ ፈቃዳቸውን እስረኞቹ ተጠይቀው ለማሰብ ጊዜ እንዲሰጣቸው በመጠየቅ መልስ ሲሰጡ፣ ፍ/ቤቱ ለአሥር ደቂቃ ያህል ጠብቁን ብለው ወደ ጽ/ቤታቸው ገቡ። ከአሁን አሁን ይመጣሉ እያሉ ሲጠብቁ፣ ደቂቃዎችም እያለፉ ሄደው፣ እስከ ሶስት ሰዓት ድረስ ቆይተው ዳኞቹ ይዘው ወደ ችሎቱ ብቅ ያሉት ትዕዛዝ ሳይሆን ውሳኔ፣ ያውም በመሪዎቹ ላይ የዕድሜ ልክ እስራት የሚያሰጥ። ይህን ስሰማ ትዝ ያለኝ በግንቦት ኩደታ ተካፍለዋል ተብለው በጦር ፍ/ቤት ላይ የተከሰሱት እነዚያ እኔ እስከአሁንም፣ ጀግኖች በምላቸው ምርጥ የኢትዮጵያ ልጆች በነበሩት ላይ የተሰየመው ፍ/ቤት ሳይወስን ራሱ መንግሥቱ ተቀብሎ በመወሰን ወዲያውኑ እንዲረሸኑ ማድረጉ ነው። የሁለቱ ልዩነት ከጦርና ከስቪል ፍ/ቤት ባሻገር፣ መለስ ፍ/ቤትንና ዳኛን ተንተርሶ ማስወሰኑና መንግሥቱ ደግሞ ፍ/ቤቱንና ሕጉን ነጥቆ በራሱ ወስኖ ርምጃ ማስወሰዱ ነው።

አንድ ዳኛ ውሳኔ የሚሰጠው ለውሳኔ ቀጥሮ የግራ ቀኙን ማስረጃዎችን ከክሱና ከሕጉ ጋር አመዛዝኖ፣ ጊዜ ወስዶ ተጨንቆበት፣ ተጠቦበት ነው። የኢትዮጵያን ሕግ ብቻ ሳይሆን የተመሳሳይ አገር ሕጎችንና ጁሪስፕሩደንሶችን ማለትም የሕግ ሳይንሶችን አምብቦና መርምሮ ነው። በተለይ ከሞት ወይም ዕድሜ ልክ እስራት በሚሆንበት ወቅት በተከሰሰው ሰው ላይ መጠነኛ የሆነ ጉዳት ያለአግባብ እንዳይደርስበት በእጅጉ ተጨንቆ ነው ወደ ውሳኔ የሚደርሰው። መጨረሻም ላይ ሲደርስም በዚህም ወጣን፣ በዚያም ወረድን፣ ከዚህ ውጭ የቀረቡበት ማስረጃዎች ሊያሳዩኝ አልቻሉም፣ በመሆኑም በሕግ አግባብ የሞት ወይም የእድሜ ልክ እስራት ቅጣት ሊወሰንበት ይገባል እስከማለት መድረስ አለበት። ሰው ክቡር ፍጡር ነው። ከአምላክ በተሰጠው ጸጋ ዓለምን የሚለውጥ ነው። የዚህ ዓይነቱ ፍጡር ቀርቶ የማንኛውም ነፍስ ያለአግባብ መጥፋት የለበትም። እንኳንስ ሞት አይደለም፣ እንኳንስ ዕድሜ ልክ አይደለም፣ በአንዳንዱ ላይ ከአምስት ዓመት በላይ ቅጣት መወሰን ለአንድ ሕግን በአግባቡ ለሚተረጉመው ዳኛ ምጥ ነው። በኛ አገር ዳኞች በወንጀል አድራጊው ላይ የሞት ቅጣት ባሳረፉ ጊዜ በችሎት ላይ ውሳኔው የሚነበበው ዳኞችና በችሎቱ የሚከታተሉት ሁሉም ቆመው ነው። ይህም እንግዲህ የሰው ልጅ ክብር በፍ/ቤቶቻችን እንዴት እንደሚታይ ነው። ቅንጅት ላይ እነሓይሉ ሻውል በሚለው መዝገብ ላይ የተሰጠውን ውሳኔ ስናይ፣ ዳኞቹ ውሳኔውን የጻፉት ከችሎቱ ወደ ጽሕፈት ክፍላቸው ወዲያውኑ እንደገቡ መሆኑ ነው ሁኔታዎች ያሳዩን የነበሩት። ይህም የሚያሳየን ዳኞቹ ማን ላይ ምን እንዲወስኑ ይነገራቸው እንደነበር ነው። ለዚህም ተያያዥነት ያለውን ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። በመሠረቱ፣ በአንድነት የተከሰሱ ሰዎች ላይ የሚሰጥ ውሳኔ በአንድ ቀን መጠናቀቅ ሲኖርበት፣ ለሳምንት ያህል መጓዙ ነው። ይህም ያሳየን የነበረው በአንድ በኩል ፍ/ቤቱ በወቅቱ ውሳኔ ለመስጠት ያልተዘጋጀ መሆኑን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ዳኞቹ በቀረቡት ማስረጃዎች ላይ ተመርኩዘው በራሳቸው ነጻ ሕሊና ሳይሆን፣ አንድ በአንድ ከላይ ትዕዛዝ እየወረደላቸው እዚያው እችሎቱ ጽ/ቤት ቅጽበታዊ በሆነ መልኩ መወሰናቸውን ነው።

በእኔ ግምት በወቅቱ ለዚህ ቅጽበታዊ ድርጊት መንግሥት የተነሳሳው፣ በተለይም እዚህ ሳይበሩ ያለው ኢትዮጵያዊ በየመንግሥታቱ ደጃፍ እየሄደ፣ በኤዎሮፓ ዪኒየን፣ በአሜሪካ ኮንግረስ ጭምር በሚያደርገው ጫና እንዲሁም የገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽን የደረሰበት ውጤትና የውጤቱ መታፈን ይፋ ሆኖ ሲጋለጥ በየቦታው ሁሉ እንቅስቃሴው እየጨመረ በመሄዱ፣ ከዚህም በመነሳት የኤዎርፓ ዩኒየን ፓርላማና ልዩ ልዩ ክፍሎች፣ በአሜሪካ በኮንግረስ ማን በሆነው ዶናልድ ፔየን የተዘጋጀው ስምፖዚየም መከፈቱ፣ ኤች.አር 2003 በአዲስ መልክ በነ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገ/ማርያምና በሌሎቹ ተዘጋጅቶ ወደ አሜሪካን ኮንግረስ መቅረቡ ስላሰጋቸው ከወዲሁ ለማምለጥ ነው። ከውሳኔው ለጥቆ የመጣው መለስ አስቀድሞ ባደራጃቸው ሽምግልና ጉባኤ እነዚያን ይህንኑም ፈጽሞ ሲያበቃ መንግሥት አስቀድሞ በፍርድ ቤትና በፍትህ ስም ለመሸወድ ባዘጋጀውና በቀመረው፣ “የአገሩ በሬ በአገሩ ሰርዶ” በሚል መሰሪ ወጥመድ ውስጥ በማስገባት፣ የአገር ሽማግሌዎችን አዘጋጅቶ ያለ ችግር አብረው ለመሥራት እንድሚቻል፣ እንደቀድሟቸው ሊንቀሳቀሱ እንደሚችሉ በሽማግሌዎች አማካይነት ቃል ገብቶ እንደነበር፣ ለመፈታት ግን ይቅርታ እንዲጠይቁ በማድረግ፣ ከእስር የቅንጅት መሪዎችን እንደለቀቃቸው ሰምተናል፤ አይተናልም። በተለይም መሪዎቹ ከተለቀቁ በኋላ የሆነውን ደግሞ ሁላችንም አይተናል።

ዳንኤልና ነጻነት፣

ዳንኤልና ነጻነት ከመጀመሪያው ጀምሮ እየተከራከሩ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃዎችን አፈር ድሜ እያስገቡ ቢሄዱም፣ በድምጽ ብልጫ እንዲከላከሉ ተበየነባቸው። ከዚያም የቀረበባቸውን ክስ ብቁ በሆነ ማስረጃ ቢከላከሉም በነዚያ ዳኞች ተወስኖባቸአል። ግን ለዓለም ማህረሰብ የቀረበባቸው ክስ ባዶነት በግልጽ አሳይተዋል። ሆኖም፣ እነርሱም ይቅርታ እንዲጠይቁ ተደርገው አናደርገውም ብለው ቢቆዩም፣ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ መሠረት ከተፈረደበት ቅጣት ሁለት ሦስተኛውን ከፈጸመ ለማንም የሚፈቀደውን በአመክሮ የመለቀቅ መብታቸውን ተከለከሉ። ከዚህም በተጨማሪ በቀረበባቸው ይግባኝም አስፈራሯቸው። በዚህም ላይም የመለስ ሽማግሌዎች አስጨነቋቸውና የፍትህ ጀግንነታቸውን አሳይተው ይቅርታቸውን ፈጽመው ወጡ።

ወጣቱ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሣን ክስ በሚመለከትል፦

እኔ ለአንዳንድ ግንዛቤዎች አህል እግረመንገዴን አንዳንድ ነገሮችን ከፍትህ ዙሪያ ያሉትን፣ የነበሩትን ነካ ነካ አድርጌ ለማለፍ ሞከርሁ እንጂ ዋና አነሳሴ በፍርድ ቤት ስም በፍርድ ስም በመንግሥት አሁን፣ አሁን ስለተያዘው ይቅርታ የማስጠየቅ አባዜ ለቴድም ይታደል ይሆን? በሚለው መነሻ ላይ የቴድን ጉዳይና ጉዳዩን የያዘውን ችሎት አካሄድ ላይ የታየኝን አንዳንድ አካሄዶችና ውሎች ላይ የራሴን ግምገማ ለማሳየት ነው።

ቴዎድሮስ ካሣ ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም ከሌሊቱ 7፡10 ላይ ፊት በር ላይ የጎዳና ተዳዳሪ የሆነውን ሰው ገጭቶ እርዳታ ሳያደርግለት አምልጦአል የሚል አቤቱታ ቀርቦበት፣ በጊዜ ቀጠሮ ፍ/ቤት ቀርቦ የዋስ መብቱ ተጠብቆለት ከእስር መለቀቁ ይታወሳል። ከዓመት ቆይታ በኋላ በጉዳዩ ላይ ዐቃቤ ሕግ ክስ እንደመሠረተበትና እንደገና ወደ ዘብጥያ እንዳወረደው፣ የዋስትና መብቱን እንዲያጣ መደረጉም ተስተውሎአል። በመሠረቱ፣ አንድ ሰው የወንጀል ድርጊት ፈጽሞአል ተብሎ ምርመራ ከተካደበት በኋላ በይርጋ ክሱ እስካልተቋረጠ ድረስ፣ ዐቃቤ ሕግ ጉዳዩ የሚያስከስስ ሆኖ ሲያገኘው ክሱን በማናቸውም ጊዜ አዘጋጅቶ ለፍ/ቤት ሊያቀርብ ይችላል። በመሆኑም፣ ከፍ ሲል ከጠቃቀስኳቸው ጋር በተያያዥነት ላተኩርበት የፈልግሁት ክሱ ዓመት ቆይቶ መቅረቡ ላይ ሳይሆን፣ ክሱ በቀረበበት ወቅት፣ በክሱ የአዘገጃጀት ቅንብርና በተሰማው ማስረጃ ላይ ነው። ይህንኑ በሚከተለው ዓይነት ለማሳየት እሞክራለሁ።

ክሱ የቀረበበት ሁኔታና ጊዜ፦ ቴዎድሮስ በተለይም የወያኔ መንግሥት ከሚያደርገው የበቀል አካሄድ ራሱን ዞር ብሎ አይቶ ከሕዝቡ ጋር እንዲታረቅ በጥዑመ-ዜማዎቹና ግጥሞቹ ገና ከጧት የወጣትነ ዕድሜው በሕዝቡ አይን የገባ ብርቅና ውድ አርቲስት ሆኖአል። “ያስተሰሪያልና ዳህላክ ነው ቤቴ” ወያኔ-ኢህአዴግ ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ ከወዲያ ወዲህ የሚንጓለለውን የሕዝባችንን ብሶት ሜዳ ላይ በማውጣት በመጠኑም ቢሆን የቆሰለው አንጀቱ እንዲርስ አድርጎአል። እነዚህ ዜማዎች እኔ ከአገር እስከወጣሁ ድረስ በመንግሥት ሚዲያዎች አልተሰሙም። በዚህና በመሳሰሉት ዜማዎች የታዳሚውን ቀልብ በቅጡ የገዛ፣ ግን ለከፋፋዩ መንግሥታችን የጎን ላይ ውጋት ሆኖባቸው ሰነባበተ። በዚያ በንጉሡ የመጨረሻ ዘመን ላይ ልክ እንዳሁኑ እንደቴዲ የወጣቱን ቀልብ ግዝቶ የነበረው ታውቂው አርቲስት አለማየሁ እሸቴ “በስቀሽ አታስቂኝና እኔስ አልረባሽም” ዜማው የጊዜውን ብሶት ቁልጭ አድርጎ በማሳየት በተለይም ወጣቱን አታግሎአል። በተለይም ስቀሽ አታስቂኝ ዜማ የተፈታችው ያ ጠባሳ ታሪክ ትቶ የሞተው የ66 አብዮት እንደፈነዳ መሆኑ ትዝ ይለኛል። እናም በዕድሜዬ ቴዲ ሁለተኛው አርቲስትና ሙዚቀኛ መሆኑ ነው ዘፈኑ በመንግሥት ሚዲያ ሲታሰር። ልዩነታቸው እንዲህ እንደአሁኑ ያ መንግሥት በቀለኛ ያለመሆን ነው። ወያኔ በየትኛው ዘመን ከነበሩት መንግሥታት አረሳስቶና ቀን ጠብቆ በመበቀል ተወዳዳሪ የሌለው በቀለኛ ነው። ቴድን በዚህ መልኩ ነው አጥምዶ ሊበቀለው ወደ ዘብጥያ ያወረደው። ቴዲ የዋስትና መብቱ ተረጋግጦለት ከእስር ወጥቶ ለአንድ ዓመት እውጭ መቆየቱ ይታወሳል። ጥያቄው ዓመት በመሙላቱ ላይ ሳይሆን፣ የቀረበበት ሁኔታና ጊዜ ላይ ነው። በዚህ ላይ የኔ ግምት የወጣቱ ታዳሚ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከገመተው የሚርቅ አይሆንም። የዛችን አገር ሰላምና አንድነት ለማየት በሙያዬ ምንም አደርጋለሁ ብሎ የተነሳው ወጣቱ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን፣ ከአምላክ ምስጋና ዝማሪ ጋር ኢትዮጵያን ጠብቃት የሚል አነጋገር አክሎ ነጠላ ዜማ የኢትዮጵያ ትንሳኤ(ፋሲካ) አካባቢ አወጣ። እነርሱ ቀድሞውን ቢሆን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት አለርጂካቸው ነውና ይኸው ዝማሪና የግጥሙ ይዘት ስለው ባስቀመጡት ቢለዋ ካፎት ውስጥ ገባላቸው። የፋሲካንም በዓል እንኳ እቤቱ እንዳይውል አድርገው በፋሲካ ሰሞን ቀበተቱት። የበቀሎች በቀል አይደለም ትላላችሁ? ታዲያም ወያኔ-ኢህአዴግ ለዚህች ነጠላ ዜማ ብቻ አይመስለኝም ቴዲን በእንዲህ ተቻኩሎ ለእስር ያዳረገው። ሌላም የባሰ እንዳይስከትል ከወዲሁ በንዲህ ዘዴ ለመቆጣጠርና ለማፈን ነው የሚልም ጥርጣሬም አድሮብኛል። እናንተስ? የኢትዮጵያ ሕዝብ በዘር ተከፋፍሎ አንድነቱ እየታጣ እንዲሄድ በሚደረግበት በአሁኑ ሰዓት፣ ሕዝቡ በአስተዳዳሪው መንግሥት የበደል፣ የጭቆና፣ ፣ የመገደል፣ ስብዕናውን የመነካት፣ ብሎም የሰብአዊ መብት መደፈር እየደረሰበት የሃይማኖት መሪዎች እያዩ፣ እያስተዋሉ አፋቸውን እንደተሸበቡ ዓይነት ዝምታን በመረጡበት በዚህ ወቅት በሃይማኖቱ ቋንቋና ዝማሪ ብቅ ብሎ ፈጣሪ ኢትዮጵያን እንዲታደጋት በድምጹ የጮኸው ኧረ ተው ያላቸው ቴዲ አንበሳው ነው። ለነገሩ ታዲያ እንዴት አድርገው ይተኙለት?

ክሱን የአዘገጃጀትና የዋስትና መብት የመከልከሉ ቅንብር፦ የዋስትና መብቱ ተጠብቆለት የተለቀቀ ተጠርጣሪ ወንጀለኛ ሌላ ተጨማሪ ወንጀል ካልፈጸመ በስተቀር ወይም የተሰጠው ዋስትና በይግባኝ እስካልተሻረ ድረስ፣ ዋናው ክስ በተመሰረተ ጊዜ የዋስትና መብቱን የሚነፈግበት ምክንያት አይኖርም። ቴዲ ግን ይግባኝም ተጠይቆ ሳይሻር፣ ወይም ሌላ የወንጀል ድርጊት ሳይፈጽም ተሰጥቶት የነበረውን የዋስትና መብቱን ተነፍጎታል። ለመንፈግም የተደረገው ቅንብር ቀደም ሲል ፖሊስ ምርመራውን አጠናቅቆ ፍ/ቤቱ የዋስትና መብቱን በሚጠብቅለት ወቅት፣ ያልተጠቀሰ ወንጀል መንጃ ፈቃድ ሳይኖር መኪና ማሽከርከር የሚል ተጨምሮበት፣ በአዲሱ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ መሠረት ቅጣቱን ወደ 15 ዓመታት ከፍ ያደርገዋል። በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥ ዓት ሕግ ቁጥር 63 መሠረት ደግሞ የተፈጸሙ ወንጀሎቹ 15 ዓመትና በላይ የሚያስቀጡ ከሆነ የዋስትና መብት አያሰጡም። ስለዚህም ዋስትናውን የሚነፍገው ፍ/ቤቱ ሳይሆን፣ ራሱ የተጠቀሰበት የሕግ ድንጋጌ ይሆናል ማለት ነው። እንግዲህ ቴዲ ዋስትናውን የተነጠቀው በዚህ ዓይነቱ ሽረባ ነው።

በቴዲ የቀረበውን ማስረጃ በሚመለከት፦ ዐቃቤ ሕግ በቴዲ ላይ ያቀረባቸውን የዳበሳ ክሶቹን ያስረዱልኛል በማለት ሦስት የሰው ማስረጃዎችንና ሁለት የጽሁፍ ማስረጃዎችን አቅርቦ አሰምቶአል። በአጭሩ የቀረበውን የምስክሮችን ቃል ከዌብ ሳይቶች ላይ እንደተመለከትነው፣ በፍጹም ያለምንም ጥርጥር ምስክሮቹ በጥናት የቀረቡ ለመሆናቸው እንኳንስ አይደለም ለሕግ ሰው ፣ እንኳንስ አይደለም ለዳኛ ፣ ፊደል ለቆጠረ ለማንም ቁልጭ ብሎ የተቀመጠ ነው። ይህንኑ በሚከተለው መልክ እናያለን።

1. በዋናነት ቴዲ በሚያሽከረክረው መኪና በክሱ ላይ የተጠቀሰውን ሰው ገጭቶ ለመግደሉ ይመስክርልኛል ብሎ ያቀረበውኮንስታብል ከበደ ወየሳ የሰጠውን ቃል በመጀመሪያ እንመልከት። ኮንስታብል ከበደ፣ ጥቅምት 23 ቀን 2000 ዓ.ም ከሌሊቱ 7፡10 ላይ ግራና ቀኝ በላዳ ታክሲዎች የታጀበችው አረንጓዴ የቤት መኪና በፊት በር አካባቢ በፍጥነት እየበረረች ስትሄድ በሀያ ሜትር ላይ ሆኖ መመልከቱን፣ በዚህን ወቅት ፊት ለፊት ካለው ቀበሌ በኩል አንድ ሰው ከቀኝ ወደ ግራ ሲቋርጥ መመልከቱን፣ ይኸው ሰው አስፋልቱ ላይ ሲወድቅ ይህችዋ አረንጓዴ መኪና ገጭታው አምልጣ መሄዷን፣ መኪኗ ወደ ሄደችበት አቅጣጫ ደርሶ የሰሌዳ ቁጥሯን ጽፎ መመለሱን፣ ሲመለስም በአካባቢው የነበረውን ጓደኛውን ይዞት ወደ ተገጭቶአል ወደ ተባለው ሰው መሄዳቸውን፣ ሰውዬውን ሲያዩት ሕይወት እንደነበረው፣ ሲያሸቱትም የመጠጥ መንፈስ እንደነበረበት፣ ከአምስት ደቂቃም በኋላ ሕይወቱ ማለፉን፣ ስለሁኔታውም ለሚመለከተው የፖሊስ ክፍል በወቅቱ ማስታወቁን ነው የመሰከረው።

ለነገሩ ድርጊቱ ተፈጽሞአል ተብሎ ክሱ ላይ የተጠቀሰው፣ ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም ሲሆን፣ በምስክሩ ቃል ላይ ግን የተጻፈው በ2000 ዓ.ም ተብሎ ተጠቅሶአል። ይህ የዌብሳይቱ(ኢትዮጵያ ዛሬ) ስህተት ካልሆነ በስተቀር ምስክሩ ገና ከጧቱ ነው ያጠናው የጠፋበት ማለት ይቻላል። እውነት ያልሆነና የሰሚ ወይም የጥናት ነገር እያደር መትነኑ አይቀርምና። በመሠረቱ ፊት በር ላይ መንገዱ ሰፊ ነው። ከአራት ኪሎ ወደ ካዛንችስ ወይም ሸራተን ሲወረድ መንገድ ግራና ቀኝ ሁለት መኪኖችን ሊያስሽከረክር ሲችል፣ ከካዛንችስ ወደ አራት ኪሎ በተጨማሪ በቤተመንግሥቱ በኩል አንድ መኪና ያስሽከረክራል። ስለዚህም እንደኮንስታብል ከበደ ቃል መሠረት ሦስቱ መኪኖች ጎን ለጎን መሽከርከራቸውን ምሽት ነውና እንቀበለው። እንደቃሉ ከሆነ ምስክሩ ቆሞ ገጪውን መኪና መልክ ከሦስቱ የለየው ከሀያ ሜትር ርቀት ላይ ነው። ጥያቄው በዚህ ርቀት ላይ የነበረ ሰው በዓይኑ ብቻ የመኪኖችን ቀለም ለይቶ በርግጠኝነት መናገር ይችላል ወይ? ነው። እንኳንስ በምሽት በዚያን ሰዓት፣ በዚህ ርቀት፣ በዚያን ግማሽ ክብ በሚመስል መንገድ ያውም እየበረረ የሚሄድን መኪና መልክ ከሀያ ሜትር ርቅት ላይ ሊለይ ቀርቶ፣ በዚያ ርቀት ላይ የቆመ ሰው በቀንም ሊለይ አይችልም። ንጹህ አዕምሮ ያለው፣ አስተውሎት ያለው ሰውም እለያለሁ ብሎ ለመናገር አይደፍርም እላለሁ። ከእንዲህ ያህል ርቀት ላይ ቡና፣ ቀይ፣ ጥቁርና አረንጓዴ መኪኖችን መለየት እጅግ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፣ ተመሳስለው ስለሚገኙ ነው። እንደቃሉ ደግሞ መኪናው በከፍተኛ ፍጥነት መብረሩ በእይታ አንድ ነው የሚሆነው። ምናልባትም እንደዚያ መለየት የሚቻለው፣ ኮንስታብሉ ከርቀት የሚያሳይ አጉሊ መነጽር ያዞ ቢሆን ነበር። ለመያዙ ደግሞ የገለጸው ነገር የለም። እናም፣ አመስካከሩ ጤነኛ አዕምሮ ያለው ሰው በማናቸውም መልክ ቢሆን በእውነተኛነቱ የሚቀበለው አይሆንም።

ሌላው ይህ ሰው አስቀድሞ በአስፋልቱ ላይ ወድቆአል እንደምስክሩ አባባል። እንዲህ ከሆነም መባል ያለበት ሰውዬው ተገጨ ሳይሆን ተደፈጠጠ፣ ወይም ተጨፈለቀ ወይም በላዩ ላይ ተነዳበት ነው እንደእኔ ከሆነ። በወደቀ ሰው ላይ መኪና በዚያ ምስክሩ በተናገረው ፍጥነት ቀርቶ በመሀከለኛ ፍጥነትንም ቢሽከረከር፣ በተዓምር ካልሆነ በስተቀር ሟቹ ተጨፈላልቆ አጥንቱ ነው የሚለቀመው። አይመስላቹም? ከምስክሩ ቃል እንደተረዳነው ግን፣ እርሱ መኪናውን በሩጫ ተከታትሎት ሂዶ መዝግቦ እስከሚመለስ ድረስ የሟቹ ሕይወት እንዳላለፈ ነው። ይህ የምስክሩ ቃል እንግዲህ እንዴት ተብሎ ነው ትክክለኛ አዕምሮ ባለው ሰው ሊታመን የሚችለው? ራሱ ምስክሩ በእንዲህ የሰጠውን ቃል መልሶ መላልሶ ቢያዳምጠና ቢያስተውለው እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ የሚያስበረግገውና የዕድሜ ልክ ነቀርሳ እንደሚሆንበት ጥርጣሬ የለኝም። ዋሽቶ ሰውን ለመከራ፣ ለስቃይ ብሎም ለሞት ማዳረግን የመሰለ ነቀርሳ የለምና።

እኔ ዳኛ ሆኜ እንዲህ የጥናት ማስረጃዎችን በማቅረብ ይታወቁ የነበሩት አንዳንድ እሰረኞች ናቸው፤ የመከላከያ ማስረጃዎችን ለማቅረብ የማይችሉ። ከሰሩት ወንጀል ለማምለጥ ሲሉ እዚያው አብሯቸው የታሰሩትን ጓደኛቸውን አስጠንተው እየቀረቡ አንዳንድ ጊዜ ሲነቃባቸው አውቃለሁ። ዛሬ ደግሞ የጉድ ዘመን ላይ ደረስንና፣ ያለወንጀላቸው ወንጀለኛ ለማሰኘትና ሰርትፊኬት ለማሳወጅ በሚያስተዳድራቸውና በሚጠረጥራቸው ዜጎች ላይ ዓይኑን ጨፍኖ፣ በተደጋገመ የጥናት ምስክሮችን ሲያቀርብ አየን። ዕድሜ መስተዋት ነው ልበል ወይስ…?

ሌላው የምስክሩ አስገራሚ ቃል፣ ከሀያ ሜትር ርቀት ተነስቶ እየበረረ ያውም ወደ ሸራተን በኩል ቅልቁለት የሚወርድን መኪና ደርሶበት የሰሌዳ ቁጥሩን መዝግቦ መመለሱ ነው። መጀመሪያውኑ መኪናውን የመለየቱ አጥራጣሪነት ከላይ እንዳልሁት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በትክክለኛ አዕምሮ አስተሳሰብ በዚያ ምሽት ምናልባትም በአይሮፕላን ካልሆነ በስተቀር ከሀያ ሜትር ተነስቶ በመኪና እንኳን ቢከታተል ሊደርስበት አይችልም። ያለዚያም መኪናው ወደ ሸራተን እንደወረደ ቆሞ መጠበቅ አለበት። ይህ ደግሞ በምስክሩ አልተነገረም። በዚህ ላይ መገንዘብ ያለብን፣ ገጭቶ የሚያመልጥ መኪና የበለጠ ፍጥነቱን ይጨምራል እንጂ ይቀንሳል ተብሎ አይገመትም። ይህም የምስክሩን ቃል ሐሰተኛነት ያጎላል።

2. ሁለተኛውና የዓይን ምስክር ሆኖ የቀረበው ኮንስታብል ታምራት ዱላ አደጋው ደርሶአል በተባለበት ዕለት የመሰከረው፣ የመኪናውን መልክ፣ ፍጥነቱን በአንደኛው ምስክር ተጠርቶ ሂዶ ተገጨ የተባለው ሰው ከመሞቱ ከአምስት ደቂቃ በፊት ደርሶ ማየቱንና የመጠጥ ሽታ እንዳለበት መለየቱን ብቻ ነው። በመኪናው ሰው ሲገጭ ግን አላየም።

ይህ ምስክር ባለአረንጓዴ ቀለም መኪና በሁለት የላዳ ታክሲዎች ታጅባ በፍጥነት እርሱ በሥራ ላይ በነበረበት ግንብ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በኩል ስታልፍ ፍጥነቱን እንዲቀንስ ፊሽካ መንፋቱን ገልጾ፣ ስለሆነው ነገር ግን የሰማውና የተለመከተው በአንደኛው ምስክር አማካይነት መሆኑን ነው ለፍ/ቤቱ ያስረዳው። በመሆኑም ምስክሩ የአይን ሳይሆን ደጋፊ ወይም አካባቢያዊ ማስረጃ(collaborative evidence) ሆኖ ነው ሊወሰድ የሚገባው። እርሱ የቀረበው የመኪነዋን ወለምና በወቅቱ የነበራትን ፍጥነት ለማስረዳት ብቻ ነው። ይህም የመኪነዋ ፍጥነት በተጨማሪ በዚህ ምስክር መነገሩ ሟቹን በርግጥም ገጭቶ ያመለጠው ይኸው አረንጓዴ መልክ ያለው የቴዲ መኪና ለመሆኑ የአንደኛ ምስክሩን ቃል ለማጠናከርና የበለጠ ግንዛቤ በፍ/ቤቱ ላይ ለማሳደር ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ነው። ሆኖም ከላይ በአጭሩ ለማብራራት እንደሞከርሁት የመኪነዋን ቀለም ከሦስቱ አረንጓዴ መሆኗን ከዚያ ርቀት የመለየቱ አስቸጋሪነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ፍ/ቤቱ ከዚህ ላይ ለትክክለኛ ፍትህ የሚጓዝ ከሆነ ሦስት መሠረታዊ ነጥቦች ላይ አትኩሮት ሊጥልባቸው ይገባል።

1. በሁለቱም የምስክሮች ቃል ላይ ገጭዋ መኪና በግራና ቀኝ በታክሲዎች ታጅባና ነው ስትበር የነበረችው። ይህ ከሆነ ደግሞ ሦስቱም መኪኖች በእኩል ፍጥነት ይበሩ እንደነበሩ፣ እና
2. ሦስቱ አንዱ ላይ ጎን ለጎን እኩል የሚበሩ ከሆነ ደግሞ እንዴትስ በትክክል የተባለችው አረንጓዴዋ መኪና መግጨቷ ሊለይ እንደተቻለ፣ እና
3. ሁለተኛው ምስክር የመኪኗን ሰሌዳ ቁጥር እስካልያዘ ድረስና ሌላ አረንጓዴ ቀለም ያለው የቤት መኪና በከተማው ውስጥ ያለምኖሩ እስካልተረጋገጠ ድረስ፣ የተባለችው አረንጓዴ መኪና የቴዲ መሆኗን እንዴት ሁለተኛው ምስክር እንደቻለ በተባሉት ላይ።

የሦስተኛውን ምስክር ቃል ስናጤን ደግሞ ምስክሩ የመኪና ግጭት ፕላን አንሽ ባለሙያ ነው። የሰጠውም ምስክርነት የባለሙያ ነው። ከቃሉም እንደተደመጠው፣ ምስክሩ ፕላኑን በሚያነሳበት ወቅት የሟቹ ሬሳ ጭንቅላቱ ወደ ካዛንችስ አቅጣጫ፣ እግሩ ወደ አራት ኪሎ አቅጣጫ እንደነበር ነው። ይህ እንግዲ የሚያረጋግጥልን ሟቹ ደጉ ይበልጣል የሞተው የመደፈጠጥ ወይም የመጨፈለቅ ጉዳት ሳደርስበት ነው። ከዚህ በተለየ እንዳይባል የሬሳ ምርመራ ውጤቱ ለመቅረቡ የተጠቀሰ ነገር የለም። ከዚህ ተነስተን ደጉ የሞተው በወደቀበት ቦታ በመኪና ተገጭቶ ሳይሆን፣ እየሄደ ባለበት ወቅት ሰክሮ ተሸንፎ በዚያ አስፋልት ላይ ወድቆ መሆን አለበት፤ ወይም እውነትም በመኪና ተገጭቶ ከሆነ መኪናው ወደ ጎን ገፍትሮ ጥሎት አስፋልቱ ተቀብሎት ለሞት ተዳርጎ ይሆናል ወደሚል መደምደሚያ እንደርሳለን። እናም ከፍ ሲል በአንደኛው ምስክር ላይ እንደሰጠሁት ትንተና፣ መኪናው በወደቀ ሰው ላይ ከተሽከረከረ፣ መኪናው ሄዶበት ወይም ጨፍልቆት ሞተ ነው ሊባል የሚችለው እንጂ ተገጭቶ ሊባል አይችልም። በተባለው ፍጥነት ደግሞ መኪና በወደቀ ሰው ላይ ያውም አስፋልት ላይ ከሄደበት ቀሪ የአካላቱን ክፍል ከተለያየ ቦታ ስለማግኘቱ ነው አንድ ምስክር መናገር የሚችለው እንጂ እንደ ፕላን አንሽው የሟቹን ሙሉ አካል የተጋደመበትን አቅጣጭ ሊናገር የሚችልበት ሁኔታ አይኖርም። የዚህን ምስክር ቃል በእንዲህ ከታየ ደግሞ፣ የአንደኛውን ምስክርነት ቃል በበለጠ ጥርጣሬ ላይ እንደሚጥለው መገንዘብ ይቻላል።

አራተኛው ማስረጃ ያልተገኘው ሰው ለፖሊስ የሰጠው ቃል ነው። ይህም በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ ቁጥር 143 መሠረት መሆኑ ነው። በዚህ ሥነ-ሥር ዓት ድንጋጌ መሠረት የእንዲህ ያለ ምስክርነት ቃል ቀርቦ በማስረጃነት እንዲያያዝለት ዐቃቤ ሕግ ሊጠይቅ ይችላል። ከሌላው ወገን ተቃዉሞ ቀረበ አልቀረብ ካመነበት ፍ/ቤቱ ሊቀበለው ይችላል። ቁም ነገሩ መቀበል ያለመቀበሉ ላይ ሳይሆን፣ ምዘናው ላይ ነው። ለፖሊስ የሚሰጥ የምስክርነት ቃል በራሱ ተአማኒነት የለውምና። ምክንያቱም ተከሳሹ ኖሮ መስቀለኛ ጥያቄ እያቀረበ ቃሉን የሚያፈርስበት ሁኔታ አይኖርምና ነው። ከሌሎች ላይ በማዳበሪነቱ ነው ሊያገለግል የሚችለው። ከላይ የሌሎችን ቃል እንደተመለከት ነው እርስበርስ የሚጋጭ በማናቸውም መልክ ቢታይ ሊታመን የማይችል ሆኖ ይታያል።

መቼም አንድ ለፍትህ የቆመ ዳኛ፣ ወገናዊነት የሌለው ዳኛ እንካውንስ እንደዚህ ያፈጠጠ አጠራጣሪ ማስረጃዎች ቀርበው ቀርቶ፣ መጠነኛ ምክንያታዊ ጥርጣሬ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ካሳየ፣ ተጠርጣሪውን ተከሳሽ ከክሱ በነጻ ሊለቀው ይገባል። ምክንያቱም ዐቃቤ ሕግ ክሱን ምክንያታዊ ከሆነው ጥርጣሬ(beyond reasonable doubt) ውጭ ማስረዳት መቻል አለበትና። ይህ ዓለም አቀፍ መርህ ነው።

ለነገሩ ዳኛው ልዑል ገ/ማሪያም ነው። እንደምናስታውሰው ልዑል በቅንጅት ጉዳይ የቀኝ ዳኛ የነበረ ነው። በሕግ ያለውም የእውቀት ደረጃው በአማርኛ በሕግ ት/ቤት የሚሰጠው ዲፕሎማ ድረስ ነው። በእንዲህ ያለ ጉዳይ አንድ የከፍተኛ ፍ/ቤት ዳኛ የተለያዩ የውጭ የህግ መጽሐፎችን፣ መጽሄቶችን አምብቦ የሚረዳ መሆን አለበት። ይህን ደግሞ ልዑል ሊያሟላ የሚችል አይደለም። ስለሆነም፣ ል ዑል ለእንዲህና ለመሳሰሉ ጉዳዮች የሚመረጠው ባለው በዳኝነት ዕውቀቱ ሳይሆን፣ በትክክለኛ ፈራጅነቱ ሳይሆን፣ በወገናዊነቱ ነው ለማለት ይቻላል። እናም፣ የምስክሮቹ ቃል እውነታው እንደዚያ ቁልጭ ብሎ የሚታይ ቢሆንም፣ ዳኛው ልዑል እንደመሆኑ መጠን የዐቃቤ ሕግ ማስረጃነትን በብቁነት ተቀብሎ እንዲከላከል ብይን ከመስጠት ወደኋላ የሚል አይመስለኝም። ቢከላከልም፣ በመጨረሻ የጥፋተኝነት ውሳኔ ከመስጠት ወደኋላ የሚል ሰው አይደለም። እናም፣ አሁንም በፍትህ ስም ቴዲን ለይቅርታ? የሚል ጥርጣሬ ታይቶኛል። እናንተስ? ወገኖቼ! የጊዜው የወያኔ ቫይሬስ ነውና።

ድምዳሜ

ይህ በቴዲ ላይ የደረሰው በትር፣ “መተማን አረሱት፣ አርማጮን አረሱት….ከኛ ሰው ሲታጣ….” በሚለው ዜማው ብቅ ብሎ ተንፍሶ ያስተነፈሰውን ፋሲልና ሌሎች በዚህ በኩል ብቅ፣ ብቅ የሚሉትን ወጣት ሙዚቀኞችን ለማስጠንቀቅና ወኔያቸውን ለመስለብ ሆን ተብሎ የተቀነባበረ የሂደት ጅምር ነው። ነገ ደግሞ ሌላ ማየታችን አይቀርም። የቴድ ጉዳይ እንደአየነው፣ ሊበሏት ያሰቧትን ወፍ ጅግራ ይሏታል ዓይነት ነው።

ታዲያ እኛ እንደዚህ በተናጠልና በጅምላ በሕዝባችን ላይ የእሥራት፣ የግድያና የአፈና ሰቆቃ፣ የሰብአዊ መብት ረገጣው እየደረሰባቸውና እየሰፋ ሂዶ በማን አለብኝነት የኢትዮጵያን መሬት ተቆርሶ በተሰጠበት በአሁኑ ወቅት፣ እኛ ደግሞ እየበረታን ያለነው የራሱ የወያኔ ሳያንስ የወገን ማህበሮችን፣ ድርጅቶችን በማፍረስ፣ በማጠላለፍና ስም በማጥፋት ላይ ተሰልፈናል። ይህ መቼ ነው የሚቆመው? የድርጊታችንን አስከፊነት ቆም ብለን ተመልክተን ራሳችንን በሕሊና መነጽራችን መቼ ይሆን የምናየው? መቼ ነው አንዳንዶቻችን በአንድነት ስም፣ በኢትዮጵያዊነት ስም መነገዳችንን የምናቆመው? አንዳንዶቻችን ከፍርሃትና ከአድርባይነት ዋሻ መቼ ነው የምንወጣው? እናም እናስብበት። ዛሬ ነው ጊዜ ያለን፤ ከተጠያቂነት የምናመልጠው ዛሬ ነው፤ ነገ ሌላ ነውና። እናም፣ ዛሬ በቁርጠኝነት ለአንድነት እንነሳ። አንድነት ኃይል ነውና። አንድ ከሆንን አገራችንን ከገባችበት ማጥ እናወጣታለን። ድር ቢያብር አንበሳ ያስር ያባል የለ!!

Leave a Reply