Skip to content

UDJ asks parliament to investigate Ethiopia-Sudan border deal

Ato Temesgen Zewdie, an executive committee member of the Union for Democracy and Justice (UDJ), has asked the Woyanne rubber stamp parliament to investigate the reported give away of Ethiopian land to Sudan by the Meles regime. In a letter to the parliament, Ato Temesgen, who is the parliamentary leader of UDJ, said that currently Sudanese soldiers are occupying several Ethiopian towns and villages, including those located in Methema, Tach Armacheo, and Quara woredas (districts). The letter also states that Sudanese troops have recently killed 17 Ethiopians in these woredas. Another group of 20 members of parliament is circulating similar letters asking discussion on the Ethiopia-Sudan border agreement. Read more in Amharic below.
————————
Source: Reporter
ሱዳን ወሰን ጥሳ በመግባቷ ፓርላማው እንዲወያይ ተጠየቀ

የሱዳን ወታደሮች የኢትዮጵያን ወሰን ጥሰዋል መባሉን በተመለከተ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በደብዳቤ መገለጹንና ምክር ቤቱ ውይይት እንዲያደርግበት መጠየቁን ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡

እንደምንጮቻችን ገለፃ በአቶ ተመስገን ዘውዴ የሚመራው የፓርላማ ቡድን አባላት የኢትዮጵያን መሬት የሱዳን ወታደሮች ወሰን አልፈው መግባታቸውን የሚገልፅ ደብዳቤ ለፓርላማው አቅርበዋል፡፡ የቡድኑ አባላት ባቀረቡት ደብዳቤ ጉዳዩ ለምክር ቤቱ አባላት ቀርቦ ውይይት እንዲካሄድበት ጠይቀዋል፡፡

በደብዳቤው በሰሜን ጎንደር በመተማ፣ ታች አርማጭሆና በቋራ ወረዳዎች ውስጥ የሱዳን ወታደሮች ሰፍረው እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡ ደብዳቤው የኢትዮጵያ ይዞታን የሱዳን ወታደሮች መያዛቸውን ተከትሎ መንግሥት ምንም አይነት ተቃውሞ አለማቅረቡን ወቅሷል፡፡

ደብዳቤው መንግሥት የአርሶ አደሩን መሬት ለሱዳን እያስረከበ መሆኑን በመግለፅ ጉዳዩ በአስቸኳይ ለፓርላማው እንዲቀርብና ግልፅ የሆነ መረጃ እንዲሰጥበት እንዲሁም የኢትዮጵያ ሕዝብም እንዲያውቀው ጠይቋል፡፡

በሌላ በኩል በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው ስማቸው እንዳይገለፅ የፈለጉ የፓርላማ አባል ጉዳዩ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ የነበረ መሆኑንና በኢትዮጵያ የመንግሥት ለውጥ በተደረገበት በ1983 ዓ.ም የሱዳን ወታደሮች የመተማን አካባቢ መያዛቸውን አስታውሰዋል፡፡ በዚህም ወታደሮቹ ለአንድ ዓመት ገደማ ቦታውን ወረው ከቆዩ በኋላ ለቀው መውጣታቸውን ያመለክታሉ፡፡

ቀጥለውም በታህሳስ 1998 ዓ.ም የሱዳን ወታደሮች ወሰን ጥሰው ከአራት መቶ ሰባ በላይ የአርሶ አደሮችና በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሃብቶች መፈናቀላቸውን ያስታወሱት የምክር ቤቱ አባል፤ በእርሻ ይዞታው ላይ የነበረው ሰብል በሱዳን ወታደሮች መቃጠሉን አብራርተዋል፡፡ የፓርላማ አባሉ መንግሥት “የተፈናቀለ ሰው የለም” በሚል ባለሃብቶቹን አርሶ አደሮቹን በሌሎች አርሶ አደሮች ይዞታ ላይ በማሸጋሸግ ማስፈሩን አስታውሰዋል፡፡ በወቅቱ በሱዳን ወታደሮች ወረራ 17 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቀዋል፡፡

በወቅቱ በተነሳው የይዞታ ይገባኛል ውዝግብ የኢትዮጵያ መንግሥትና የሱዳን መንግሥት የድንበር ማካከሉን ሥራ መጀመራቸውን ጠቁመው፤ እስካሁን አልባት አለማግኘቱን ገልፀዋል፡፡

በዚህም በመተማ ብቻ የነበረው የመሬት ወረራ ተስፋፍቶ በቅርቡ በአርማጭሆና በቋራ አካባቢ መስፋፋቱን እኚሁ የምክር ቤት አባል ገልፀዋል፡፡ ለዚህም በመተማና በአርማጭሆ መካከል የሚገኝ “የዘለቀ እርሻ ልማት ቁጥር 4” በሱዳን ወታደሮች መወረሩንና የደላሎ የእርሻ መሬትም ተመሳሳይ ችግር እንደገጠመው በምሣሌነት ጠቅሰዋል፡፡ በቋራ ነብስ ገበያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በተደረገው ወረራ ከ28ሰዎች በላይ ታፍሰው ወደ ሱዳን መወሰዳቸውንም እኚሁ የምክር ቤት አባል አስረድተዋል፡፡

ይህንንም ሁኔታ ለመንግሥት ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ መቅረቡንና ምላሽ አለመገኘቱንና በአሁኑ ጊዜም ያለው ሁኔታ ዝም ሊባል የማይችል በመሆኑ ችግሩን በገሃድ የወጣ መሆኑን የገለፁት የምክር ቤቱ አባል በጉዳዩ ዙሪያ ፓርላማው ሊወያይበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በተያያዘ ዜና ከ20 በላይ የሚሆኑ የፓርላማ አባላት የሱዳን ወታደሮች ወሰን ማለፍ አስመልክቶ ፓርላማው እንዲወያይበት ለመጠየቅ የፊርማ ማሰባሰብ ሥራ እያከናወኑ መሆኑን ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡ በዚህም የፊርማ ማሰባሰብ ሂደት ከ20 በላይ የፓርላማ አባላት ፊርማ መፈረማቸው ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት በሰጠው መግለጫው ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት መሬት ቆርሶ ለሱዳን ሰጥቷል በሚል በአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ህዝብን ለማደናገርና ግጭት ለመፍጠር ሆን ተብሎ የሚደረግ አሻጥር እንደሆነ ይገልፃል፡፡

በሌላ በኩል ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ያረጋል አይሸሹም በሰጡት መግለጫ “ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር በምትዋሰንበት ድንበር በኩል መሬት ተቆርሶ ለሱዳን ተሰጥቷል በማለት የተሰራጨው ወሬ መሰረተ ቢስ ነው”

ሱዳን ነጻነቷን ካገኘች ጀምሮ የቀደሞው ንጉስና ደርግ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ አካላት ጋር የሁለቱን አገሮች ድንበር ለማካለል ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውንና ጥረቱ እስካሁን አለመሳካቱን ማመልከታቸውንና በዚሁ ጉዳይ ሁለቱ አገሮች እየተነጋገሩበትና በጋራ እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

Leave a Reply