Skip to content

ታላቁ የኢትዮጵያ ሩጫ ላይ ሃይሉ ሻውል ተወገዙ

Great Ethiopian Run Nov 21 2009aአውራምባ ታይምስ (አዲስ አበባ)፡- በ1994 ዓ.ም. የተጀመረው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለ9ኛ ጊዜ በዛሬው እለት ተካሄደ፡፡ ውድድሩን እንግሊዛዊቷ አትሌት ፓውላ ራድክሊፍ ከደራርቱ ቱሉ እና ከኃይሌ ገ/ሥላሴ ጋር በመሆን አስጀምራለች፡፡

በታላቁ ሩጫ የተቃውሞ ድምጾች መሰማት የጀመሩት በ1998 ዓ.ም ህዳር ወር የቅንጅት አመራሮችና ጋዜጠኞች መታሰራቸውን በመቃወም ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በየአመቱ ወቅታዊ የተቃውሞ ድምጾችን እያስተናገደ እዚህ ደርሷል፡፡ ዘንድሮም ውድድሩ በተካሄደባቸው ጐዳናዎች ላይ

እንነጋገር
የብርቱዬን ነገር
እንነጋገር
የቤንዚኑን ነገር
መሰናበቻ መሰናበቻ
የቀረችን ብርቱካን ብቻ
ልብ የሌለው ኃይሉ ሻውል ብቻ
የአለም ጅሉ
የኢትዮጵያው ኃይሉ
ወኔ የሌለው
ኃይሉ ሻውል ነው
ቡርቱካን ማንዴላ
ልደቱ ሌባ
ጫሚሶ ሌባ

እና መሰል ተቃውሟዊ ኃሳቦች የተንሸራሸሩ ሲሆን ካለፉት ዓመታት አንፃር ሲታይ ግን የበረከቱ የተቃውሞ መልዕክቶች እና ተሳታፊዎች አልነበሩም፡፡

መከላከያ ሚኒስቴር፣ ፍርድ ቤት፣ ቤተ-መንግስት፣ ፍትህ ሚኒስቴር አካባቢ የደረሱ ሯጮች (ተሳታፊዎች) በኢህአዴግ መንግስት ላይ ከፍተኛ የጩኸት እና የተቃውሞ ድምጾች ያሰሙ ነበር፡፡ ባለፈው ዓመትም ቴዲ አፍሮ እንዲፈታ ለመጠየቅ ‹ኦባማ ይፈታ› የሚል ተቃውሞ መቅረቡ አይዘነጋም፡፡

በዛሬው የታላቁ ሩጫ ውድድር በሴቶች ኮረኒ ጀሊላ፣ በወንዶች ጥላሁን ረጋሳ የውድድሩን ሪከርድ በመስበር ጭምር አሸናፊ መሆን ችለዋል፡፡

በክብረ እንግድነት የተገኘችው የዓለም የሴቶች ማራቶን ሪከርድ ባለቤቷ ፓውላ ራድክሊፍ ባለፈው አርብ ወደ አዲስ አበባ የገባች ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ በመምጣቷ ደስተኛ መሆኗን ገልፃለች፡፡ የረጅም ዓመት የሩጫ መድረክ ተፋላሚዋ ደራርቱ ቱሉን “በትራክም ሆነ በጐዳና ላይ የሩጫ ውድድር ሳውቃት ፀባዩዋ አንድ አይነት ነው፡፡ ጥሩ፣ መልካም እና ለሰው የምታስብ ታላቅ አትሌት ናት፡፡” ስትል ባለፈው አርብ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በሒልተን ሆቴል ጠርቶት በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ለአውራምባ ታይምስ ገልጻለች፡፡

Leave a Reply