በቀጣዩ ወር በመላው አገሪቱ የሚካሄደውን የአከባቢና የማሟያ ምርጫ ከፍተኛ የመብት ጥሰትና ወከባ በመፍጠር የወያኔ ካድሬዎች በነጻ ምርጫ ስም በህዝቡ ላይ ተጨማሪ የጭቆና ዘመን ከመፍጠር ባለፈ ተቃዋሚዎች አንዳችም ወንበር የማያገኙበት በመሆኑ ከምርጫው ለመውጣት ጥምረታዊ ውይይት በማካሄድ ላይ መሆናቸውን ማንነታቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ታማኝ ምንጮቻችን ገለጹ፡፡
በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከፍተኛ አሃዝ ያለው የእጩዎች ስብስብ በግዳጅና በተለያዩ መደለያዎች ያዘጋጀው ወያኔ በቀጣዩ ምርጫ የተወሰኑ መቀመጫዎችን ራሱ ላዘጋጃቸው ተቃዋሚ ተብዬዎች ከመልቀቅ ባለፈ ህዝቡ የሚደግፋቸውን ተቃዋሚዎች የመምረጥ እድሉ ሙሉ ለሙሉ በአደጋ ስለተከበበ በምርጫው መሳተፍ ሳይጀመር መጨረሻው የታወቀውን ምርጫ ህጋዊ ካባ ማላበስ ነው ሲሉ ፓርቲያቸውን በመወከል በጉዳዩ ዙርያ ከሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች በመወያየት ላይ ያሉት ምንጫችን እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ ህዝቡ ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርግ ለምን ይፋዊ መግለጫ አትሰጡም በማለት ከዜና አገልግሎቱ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱም ያንን ማድረጋችን አይቀርም ሆኖም በአሁኑ ሰአት መግለጫውን መስጠቱ በእጩዎች ላይ እንግልት የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ ውይይቱ ስላልተቋጨ የተወሰኑ ጊዜያት ያስፈልጋሉ በሚል እምነት መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
በትግል ውስጥ ረዥም ዘመን በማሳለፍ የሚታወቁት እኒህ የፖለቲካ ሰው ጨምረው እንደገለጹት አብዛኞቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለአላማው ያሳዩት አዎንታዊ ምላሽ ከፍተኛ መሆኑን በመግለጽ ይህ ዴሞክራሲያዊ መብትን የመጠቀም እርምጃ ከዴሞክራሲ ጋር እስከወዲያኛው የተጣሉትን ወያኔዎችን አስቆጥቶ ወደ ሃይል እርምጃ ሊከታቸው ወይም በምርጫ 97 እንደሆነው ‹‹የአመጽ አማራጭ›› ተብሎ መስዋእትነት ሊያስከፍል ቢችልም አብዛኞቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መንፈሳዊ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
ውሳኔው ይፋ በሚደረግበት ወቅት ሊደርሱ የሚችሉ የመብት ጥሰቶችን አስመልክቶ በአገር ውስጥ ያሉም ሆኑ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከጎናቸው በመቆም የተለመደ ድጋፋቸውን እንደሚያሳዩዋቸው ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል፡፡