በተቀዳሚ ፕሬዝዳንት ወ/ሪት ብርቱካን የሚመራው የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ በዛሬው እለት ጠዋትና ከሰአት በኋላ ሁለት የተለያዩ ውጤታማ ስብሰባዎችን አካሄደ፡፡
የመጀመርያውና እስከ እኩለ ቀን የቆየው ስብሰባ በወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳና በዶ/ር ኃይሉ አርአያ የተመራ ሲሆን የቀድሞ የቅንጅት ታዋቂና ብቃት ያላቸው አባላትን ያሰባሰበ ነበር፡፡ በዚህ 42 የአስተባባሪነት ብቃት ያላቸውን የቀድሞ አባላት ባሰባሰበ የውይይት መድረክ ላይ በርካታ ሃሳቦች ተነስተው የተንሸራሸሩ ሲሆን በቀጣዩ የትግል ሂደት ላይ መከናወን ያለባቸው አበይት ጉዳዮች ተነስተው ገንቢ ውሳኔዎች ተላልፈዋል፡፡
አባላቱ ቀደም ባሉት ቀናት በአቶ አባይነህ የሚመራውን ስብስብ በማነጋገር ወደ ትግሉ ለመመለስ ጊዜው እንዳልመሸበት ቢያሳስቡም ቡድኑ በአፍራሽ እንቅስቃሴው እንደቀጠለበት በስብሰባው ላይ ተጠቁሟል፡፡ በመጨረሻም ለትግሉ ፍሬያማነት ከምንጊዜውም በበለጠ መስራት እንዳለባቸው በመወሰን የመስራች አባላት ፊርማ የማሰባሰቡን ሂደት በሃላፊነት እንደሚረከቡ አረጋግጠዋል፡፡
ከሰአት በኋላ በተካሄደው ስብሰባ ላይ ደግሞ በ1997 ቅንጅትን በመወከል የአዲስ አበባ የቅንጅት የክልል ም/ቤት ተመራጮች የነበሩ አባላት በፓርቲው ጽ/ቤት ባደረጉት ስብሰባ ቀጣዩን የትግል ስልት አስመልክቶ የመከሩ ሲሆን ፓርቲው የሚጠናከርባቸውንና ከህዝቡ ጋር የሚኖረው ግንኙነት ከምንጊዜውም በበለጠ እንዲሻሻል ለማድረግ በየተመረጡባቸው ክ/ከተሞች ሰፊ ስራ እንደሚሰሩ በመስማማት ተጠናቋል፡፡ በስብሰባው ላይ ዶ/ር ኃይሉ የተገኙ ሲሆን በአጠቃላይ 25 ተመራጮች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡