የምርጫ ቦርድ ህግ በሚያዘው መሰረት አስፈላጊውን ሂደት አሟልተው ለሚያዝያው የአከባቢና የማሟያ ምርጫ ራሳቸውን ያዘጋጁ የተቃዋሚ ፓርቲ እጩዎች ለመወዳደር ብቁ የሚያደርጋቸውን መታወቂያ ቢጠይቁም ምርጫ ቦርድ የተለያዩ ሰበቦችን በመደርደር ሊሰጣቸው እንዳልቻለ ምንጮቻችን ገለጹ፡፡
በህጋዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ ከምርጫ ቦርድ ፈቃድ ያወጡ ፓርቲዎች በምርጫ ወቅት ለመወዳደር የሚያስችላቸውን መታወቂያ ለማግኘት ፎቶ ግራፎችና አንዳንድ አስፈላጊ ፎርማሊቲዎችን አሟልተው እንደቀረቡ ቦርዱ ወዲያውኑ መታወቂያቸውን በመስጠት እጩዎቹ ወደ ህዝብ በመሄድ ራሳቸውን እንዲያስተዋውቁ መፍቀድ እንዳለበት በህጉ የተደነገገ ቢሆንም ወያኔን ላይመርጡ ይችላሉ ተብለው በሚታሰቡ የምርጫ ጣቢያዎች ላሉና ጠንካራ ተፎካካሪዎች መሆናቸው ለተረጋገጠ እጩዎች መታወቂያውን ላለመስጠት መወሰኑን በሚረጋግጥ መንገድ እስካሁን በእንቢታው እንደጸና ይገኛል፡፡
ሁኔታውን አስመልክቶ ምን እርምጃ ለመውሰድ አስባችኋል በማለት ለተለያዩ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ጥያቄ ያቀረብን ሲሆን ቦርዱ በአስነዋሪ አቋሙ የሚጸና ከሆነ በቀጣዩ ሳምንት በጋራ ሆነው ጉዳዩን ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡