(DW) በሶማሊያ መዲና መቅዲሾ ዛሬ በተቀሰቀሰ ከባድ ውጊያ ቢያንስ አራት ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ ተዘገበ ። ፖሊስና የዓይን ምስክሮች እንደተናገሩት ውጊያው የተካሄደው በደፈጣ ተዋጊዎችና በኢትዮጵያ በሚታገዙት የመንግስት ኃይሎች መካከል ነው ። መቅዲሾ የሚገኘው የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘጋቢ የዛሬው ዓይነት ከባድ ውጊያ ከሚያዚያ ወር ወዲህ አይቶ እንደማያውቅ ነው የተናገረው ። ትናንት እኩለ ለሊትም እንዲሁ ደፈጣ ተዋጊዎች ደቡብ መቅዲሾ የሚገኝ አንድ የጦር ሰፈርን በሮኬት አጥቅተዋል ። ለአንድ ሰዓት ያህል በዘለቀው በዚሁ ውጊያ ሁለት ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል ። የዓይን ምስክሮች እንዳሉት የጦር ሰፈሩን ያጠቁት ቁጥራቸው ወደ ሀምሳ የሚጠጋ ሮኬት የእጅ ቦምብና አውቶማቲክ ጠመንጃዎች የታጠቁ ሰዎች ናቸው ። ይህ በእንዲህ እንዳለ ፖሊስ ዛሬ መቅዲሾ የሚገኘውን የሸበሌ ራድዮ ጣቢያ ጋዜጠኞችን ለተወሰኑ ሰዓታት አስሮ ፈቷል ። ስለሁኔታው የተጠየቀው የራድዮ ጣቢያው የእንግሊዘኛ አገልግሎት ሀላፊ አዌይስ ኦስማን ዩሱፍ ለአሶስየትድ ፕሬስ እንደተናገረው መንግስት ጋዜጠኞቹን ስለያዘበት ምክንያት ያለው ነገር የለም