Skip to content

የቴዲ አፍሮ ጉዳይ እንደገና ለአንድ ወር ተቀጠረ

ልደታ የሚገኘው የፌደራል ከፍተኛ ፍረድ ቤት መግቢያ በር ላይ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ላይ ጀምሮ የነበረውን ሰልፍ ላየ የቴዲ አፍሮ ችሎት እንደሆነ ለመገመት አያስቸግርም፡፡

በፌደራል ፖሊሶች የሚደረገውን ጠንካራ ፍተሻ ታልፎ ወደውስጥ ሲገባ በርካታ የፖሊስ ሃይል የደህንነት ሰራተኞችና ኮማንደሮች በሩን ግጥም አድርገው ይዘውት ለአንድ ሰአት ያህል ካሰለፉን በኋላ ወደ ውስጥ እንድንገባ ተደረገ፡፡

ችሎቱ በዳኛ ልኡል ገብረ ማርያም ተሰይሞ ስራውን ሲጀምር ዓቃቤህግ አቅርብ የተባለውን የሰነድ ማስረጃ ዝርዝር መግለጫ በንባብ ማሰማት ጀመረ፡፡

ያቀረባቸው ማስረጃዎች የቴዲ አፍሮ መኪና ከቤተመንግስት አካባቢ እየበረረ ሲመጣ ሟች ደጉ ይበልጣልን ከሩቅ አይቶት ማዳን እየቻለ መግጨቱን የሚያስረዳለት የፕላን ማስረጃ ማቅረቡን፣ መኪናዋ ትራፊክ ጽህፈት ቤት እንደቆመች የተነሳ ፎቶ ግራፍ፣ ሟች ከሞተ በኋላ የተነሳው ፎቶ ግራፍ፣ በመኪና ተገጭቶ ስለመሞቱ የሚያስረዳ የምንሊክ ሆስፒታል ማስረጃ እና የሰው ምስክር ማቅረቡን ገልጾ ያቀረበው ማስረጃ ታይቶለት ብይን እንዲጥ ጠይቋል፡፡

የቴዲ አፍሮ ጠበቃ አቶ ሚሊዮን አሰፋ በበኩሉ የቀረበው የሚኒሊክ ሆስፒታል የሰነድ ማስረጃ በዶክተሮች ያልተፈረመበትና እውነትነቱ የሚያጠራጥር እንደሆነ ሌላውም የአቃቤ ህግ ማስረጃ ቢሆን ተከሳሹ በመኪና ሰው ስለመግጨቱ የሚያስረዳ አንድም ማስረጃ ያልቀረበበት በመሆኑ ከክሱ በነፃ እንዲሰናበት ጠይቋል፡፡

ዳኛው አጠራጣሪ ነው የተባለውን የሚንሊክ ሆሰፒታል ማስረጃ አቃቤ ህጉ እንዲያቀርብ ሲጠይቅ የለኝም ቢልም ቀጠሮ እንሰጥሃለን አምጣ በማለቱ የለኝም ዕያለ ባለው መወሰን ሲገባው እንዴት እንደገና አምጣ ይባላል ብሎ ጠበቃው ቢከራከርም በዳኛው ግሳጼ ዝም እንዲል ተደርጓል፡፡

አቃቤ ህጉ በተባለው መሰረት በፍርድ ቤቱ ጽህፈት ቤት በኩል እንደሚያስገባ የገለጸ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ለአንድ ወር ቀጥሯል፡፡

በቀጠሮው እለት ቴዲ ወይ በነጻ ይሰናበታል አሊያም ድርጊቱን ስለመፈጸምህ አጠራጣሪ ሆኖ ስለተገኘ ተከላከል ይባላል፡፡

Leave a Reply