Skip to content

Author: EthiopianReview.com

4 ሚሊዮን ብር የተመደበለት የቦረና ዘመቻ በኪሣራ ተጠናቀቀ

በቦረና ዞን ውስጥ መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ ጀምሮ የነበረውን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር አከርካሪ ለመስበር በሚል በኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት በኦቦ አባዱላ ገመዳና በቦረና ዞን አስተዳደር በኦቦ አደም ጅሎ መካከል በተደረገ የ4 ሚሊዮን ብር የባጀት ምደባ የተካሄደው ዘመቻ ሙሉ ለሙሉ መክሸፉን የውስጥ ምንጮች በተለይ ለዜና አገልግሎቱ ገለፁ፡፡

በተለይ በደቡቡ ቦረና ውስጥ ጠንካራ መሠረት ያለው የኦነግ ሰራዊትን ድል ያደርገዋል ተብሎ የታመነውና ከአካባቢው ሕዝብ የተውጣጣው በቂ ስልጠና የወሰደና በዘመናዊ መሳሪያዎች የተደራጀ የወያኔ/ኢህዴግ ሚሊሺያ ሰራዊት ከፍተኛ ኪሣራ ደርሶበታል፡፡

ከወራት በፊት አባ ዱላ ገመዳ አስተዳዳሪውንና ሌሎች የካቢኔ አባላትን በመሰብሰብ ሰፊ ውይይት ያደረጉ ሲሆን በወቅቱ በተያዘው ቃለ ጉባኤ ላይ እንደሚታየው “ኦነግ ካለው አፍራሽ እንቅስቃሴ የተነሳ የቀድሞውን ሥርዓት ለማምጣት ከተማማሉት ቅንጅቶች ጋር ሳይቀር ተባባሪ በመሆን ከ43 ሚሊዮን ብር በላይ ተቀብሏል” የሚል ይገኝበታል፡፡

በአስተዳደሩ አማካይነት 4 ሚሊዮን ብር በመመደቡ ቀደም ሲል ስልጠና ወስደው የነበሩ በርካታ የሚሊሺያ አባላትን በአዲስ መልክ በማሰልጠን የተደረገው ኦፕሬሽን የከሸፈ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ወያኔ/ኢህዴግ የደቡብ ቦረና ቤዙን አጥቷል፡፡

ቦረና ውስጥ ወያኔ/ኢህዴግ ሚሊሺያዎቹን ለውጊያ በሚያዘገጅበት ወቅት ባሌ ዞን ዶሎ መና ላይ የኦነግ ሰባተኛ ዙር ሰልጣኞች እየተመረቁ የነበረበት ወቅተ መሆኑ ብዙዎችን አስገርሟል፡፡

የሀይሉ ሻውል”መኢአድ” ልዑካን ተቃውሞ እየገጠማቸው ነው

ከቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ አመራር እውቅና ውጪ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የፓርላማ ተመራጮችን በመላክ “ልዩ ዘመቻ” የጀመሩት የቀድሞው የመኢአድ አባላት በደረሱባቸው ክልሎች ሁሉ ከፍተኛ ተቃውሞ እየገጠማቸው መሆኑን የዜና አገልግሎቱ ምንጮች ገለፁ፡፡

በአቶ አባይነህ ብርሃኑ አመራር ስር የሚገኙት እነዚህ ቡድኖች እስካሁን ካደረጓቸው ጉዞዎች የቅንጅቱ ከፍተኛ ድጋፍ ባለበት ደሴና ጎንደር ላይ “አካሄዳችሁ የፓርቲውን ሕልውና አደጋ ላይ ጥሎታል” የሚል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡

ወደ ደሴ ተጉዘው የነበሩት የላዕላይ ም/ቤት አባል አቶ ወንዶሰን ተሾመ “የተከፈለው መስዋእትነት ለቅንጅት እንጂ ለመኢአድ አልነበረም” በማለት አባላትን በማደራጀትና በመንቀሳቀስ አጀንዳ የሄዱትን አባል ሕዝቡ ዳግም እንዳይመለሱ አስጠንቅቆ አባሯቸዋል፡፡

ለተመሳሳይ ተልእኮ ወደጎንደር የሄድት አቶ ግርማም እንዲሁ በፓርቲው ስም ከመነገድ እንዲቆጠቡ በሙሉ ድምፅ አሳስቧቸዋል፡፡

በዛሬው ዕለትም ሀገረ ማርያም የደረሰው ቡድን ተመሣሣይ ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡

ቅንጅት በመላ አገሪቱ ያሉ አባላቱንና ደጋፊዎቹን ማወያየት ጀመረ

የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ የላእላይ ም/ቤት በቅርቡ ባደረገው ጉባኤ አማካይነት ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች እየተገበረ የሚገኝ ሲሆን በተለይም ‹‹ህዝባዊውን አደራ›› ለመወጣት በመላው አገሪቱ ከሚገኙ አባላቱና ደጋፊዎቹ ጋር የሚካሄድ ውይይት ዛሬ ጀመረ፡፡

በዋና ጸሃፊው አቶ ሙሉነህ ኢዩኤል አማካይነት በመላው አገሪቱ ከሚገኙ አባላትና ደጋፊዎች ጋር ከተካሄደው የቴሌ ኮንፍረንስ ለመረዳት እንደተቻለው በአመራሩ መካከል ተፈጥሮ የነበረው ልዩነት መጠነኛ ስጋት ፈጥሮ የነበረ ቢሆንም ፓርቲው የተነሳለትንና የኢትዮጵያ ህዝብ ዘርፈ ብዙ መስዋእትነት የከፈለበትን ድርጅት ህልውና ማረጋገጥ ትግል ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑ በሰፊው ተነስቷል ሲሉ አንድ የአመራር አባል ገልጸውልናል፡፡

ከቴሌ ኮንፍረንሱ በኋላ በስልክ ያነጋገርናቸው አንድ ተሳታፊ በበኩላቸው አመራሩ የጀመረውን እንቅስቃሴ አድንቀው ይህ ፋና ወጊ ሂደት ፍሬ እንዲያፈራ በቁርጠኝነት ተዘጋጅተናል፤ትግሉም የአንድ ወቅት የወረት ስራ አይደለም በማለት እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአቶ ኃይሉ ሻውል የሚመራው የቀድሞ የመኢአድ አባላትን ያቀፈ ቡድን የፓርላማ አባላቱን ባልተመረጡባቸው ክልሎች በመላክ ልዩ ዘመቻ መጀመሩን ምንጮቻችን ገለጹ፡፡

ይህ ቡድን በደረሰባቸው ክልሎች ሁሉ የመኢአድን ህልውና የሚገነቡና ቅንጅቱ እንደቅንጅት መቀጠል የማይችል መሆኑን የሚገልጹ አፍራሽ እንቅስቃሴዎችን ጀምረዋል፡፡‹‹ፓርቲያችን በምርጫ 97 የተፈጠረ ሳይሆን 17 አመታትን ያስቆጠረ ነው›› የሚሉ አይነት የ97ቱን ህዝባዊ እንቅስቃሴ ዝቅ አድርገው የሚያሳዩና እብሪት የተሞላባቸው ዘመቻዎች እየተካሄዱ መሆኑን ከየክልሉ የደረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

የኃይሉ ሻውል መመለስ አጠራጣሪ ሆኗል

አምስት የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ የስራ አስፈጻሚ አባላትን ከፓርቲው ህገ ደንብ ውጭ አግጃለሁ በማለት ህዝባዊው ድርጅት በገዢው ፓርቲ እየተፈጸመበት የነበረውን የማፍረስ ጥረት ከፍተኛ እገዛ የሰጡት ኃይሉ ሻውል ወደ አገር ቤት የመመለሳቸው ጉዳይ አጠራጣሪ መሆኑን የቅርብ ምንጮች አመለከቱ፡፡

ሊቀ መንበሩን መመለስ ከሚጠራጠሩት ወገኖች አንደኛው በቀድሞው የመኢአድ ጽ/ቤት በመሆን የአቶ ኃይሉን ትእዛዝ የሚያስፈጽሙት አባላት ጭምር መሆናቸው ጉዳዩን አስገራሚ አድርጎታል፡፡ በጽ/ቤቱ በሚደረጉ የውይይት አጀንዳዎች ላይም ይህ ሃሳብ ተነስቶ እንደማያውቅ ማንነታቸው እንዲገለጽ ያለፈለጉ የቅርብ ወዳጆቻቸው ገልጸዋል፡፡

በተለይ ሰሞኑን ሳሪስ አቦ የሚገኘውን የአቶ ኃይሉን ቤት ለማከራየት በደላሎች አማካይነት እየተደረገ ያለው ጥረት አቶ ኃይሉ መኖርያቸውን በዘላቂነት በአሜሪካ ሊያደርጉ ይችላሉ የሚለውን ጥርጣሬ አጉልቶታል፡፡ለዚህ የመኖርያ ቤት የተጠየቀው የኪራይ መጠን 60 ሺህ ብር (U.S. $6,500 በወር) ያህል መሆኑን የተከራይ አፈላላጊዎቹ ገልጸውልናል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የፓርቲውን ሃላፊነት ተረክቦ ወሳኝ እንቅስቃሴዎችን የጀመረው የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ የስራ አስፈጻሚ አካል በእሁዱ ላእላይ ም/ቤት አባላት የተላለፉትን ውሳኔዎች ለማስፈጸም ከፍተኛ እንቅስቃሴ የጀመረ ሲሆን በትናንትናው እለት በመሰብሰብ በተግባራዊ ሂደቶች ዙርያ በሚያከናውናቸው አጀንዳዎች ዙርያ መክሯል፡፡

ከቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ የላዕላይ ም/ቤት የተሰጠ መግለጫ

Read in PDF

ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ከውስጥም ከውጭም ከፍተኛ ችግሮች አጋጥመውታል፡፡ እነዚህን ሁሉ ችግሮች ተቋቁሞ በግንቦት 97 ዓ.ም. ምርጫ አመርቂ ውጤት ያስመዘገበው፣ ከጥምረት ወደ ውህደት ለመሸጋገር የበቃውና ዛሬም ድረስ በሀገሪቱ ፖለቲካ መድረክ ላይ ዋነኛ የመነጋገሪያ አጀንዳ እንደሆነ የዘለቀበት አብይ ምክንያት በፕሮግራሙ የገለፀውና በተፈፃሚነቱም አመራሩ ቃል የገባለት ዓላማው የሕዝብን ተቀባይነትና ድጋፍ በመግኘቱ ነው፡፡

ቅንጅት ዓላማውን ተፈፃሚ ለማድረግ በሚያከናውነው ትግል ከሚመራባቸው መርሆች መካከል ሕጋዊነት፣ ዴሞክራሲያዊ የጋራ አመራር፣ የአሰራር ግልጽነትና መልካም ሥነ-ምግባር ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ እነዚህ መርሆች በአገር ደረጃም ሆነ በፓርቲው ውስጥም ተግባራዊ እንዲሆኑ ቅንጅት በጽኑ ይታገላል፡፡

ፓርቲው የተነሳለትንና ሕዝብ መስዋዕትነት የከፈለለትን ቅዱስ ዓላማ ከግብ ለማድረስ፣ ለሕዝብ የገባውንም ቃል ተግባራዊ ለማድረግ በቅድሚያ የፓርቲው ሕልውና መረጋገጥ በእጅጉ ወሳኝ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የላዕላይ ም/ቤቱ ተሟልቶና ተጠናክሮ መጀመርና በፓርቲው ውስጥ ለሚታዩ ሕገ-ወጥ ድርጊቶች እልባት መስጠት አቢይ ተግባር ይሆናል፡፡

ስለሆነም ነው የቅንጅት ሥራ አሰፈፃሚ ኮሚቴ ለሦስት ጊዜ የላዕላይ ም/ቤት ስብሰባ ጠርቶ በሦስተኛው በተገኙ አባላት አሳሪ ውሣኔ እንደሚተላለፍ ያስታወቀው፡፡፡ በዚህም መሠረት ታህሣሥ 20 ቀን 2000 ዓ.ም. በተካሄደው የላዕላይ ም/ቤት ስብሰባ፡-

1. የተጓደሉ የላዕላይ ም/ቤት አባላትን ስለሟሟላቱ፣
2. የፓርቲውን ሕጋዊነት ስለማረጋገጥና
3. ሊቀ መንበሩ ስለወሰዷቸው ሕገ-ወጥ እርምጃዎች

በሚሉ ወቅታዊና አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ምክር ቤቱ በስፋት መክሮ የጋራ ግንዛቤ ይዟል፣ ውሣኔዎችንም አስተላልፏል፡፡

ም/ቤቱ የተገነዘባቸው ጭብጦች
1. ፓርቲው ሥራውን በአግባቡ መቀጠል እንዲችል የላዕላይ ም/ቤቱ ቁጥር ማሟላት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን፣

2. በመተዳደሪያ ደንቡ አንቀጽ 9.2.3 መሠት የተጓደሉ የላዕላይ ም/ቤት አባላት የማሟላት ኃላፊነት ሥራ አስፈፃሚው በውክልና የተሰጠው መሆኑን፣

3. ከቅንጅት ለቀው የሌላ ፓርቲ አባላት በሆኑ፣ ከፓርቲው ጋር ላለመቀጠል መወሰናቸውን በተለያየ መንገድ በገለጹና በጤና ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ከሀገር ከወጡ ቢያንስ ስድስት ወራት በሆናቸውና መኖሪያቸውን በዚያው ባደረጉት የላዕላይ ም/ቤት አባላት ምትክ ማሟላት አስፈላጊ መሆኑን፣

4. የፓርቲውን ሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጥ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆኑን፣

5. ሊቀ መንበሩ አምስት የላዕላይ ም/ቤት አባላትን ማገዳቸውና እንዲሁም ተተኪዬ ሆኖ እንዲሠራ በሚል ሰው የመደቡ መሆናቸውን መግለፃቸው የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ የጣሰና መሠረታዊ የሆኑትን የዴሞክራሲያዊ አሰራር መርሆችን ያላገናዘበ መሆኑን፣

6. የሊቀ መንበሩን አካሄድ እየተከተሉ በሀገር ውስጥ በሕገ-ወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች ቅንጅትን ለማዳን በሚል ሽፋን የሚያከናውኑት ተግባር የግል ፍላጎትን ለማሳካት የሚከናወን ከቅንጅቱ መሠረታዊ ዓላማ ጭራሹኑ ባፈነገጠ መሆኑን ተገንዝቧል፡፡

የተላለፉ ውሣኔዎች

1.1 በተጓደሉ የላዕላይ ም/ቤት አባላት ምትክ ስለማሟላት፡-
ፓርቲው የገጠመውን ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች ተቋቁሞና አስተማማኝ መፍትሔ ሰጥቶ የተነሳለትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ የሚያስችለውን ተግባር ለማከናወን ላዕላይ ም/ቤቱ በአጭር ጊዜ ቁጥሩ ተሟልቶና ተጠናክሮ ሥራ መጀመር ስላለበት የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 9.2.3 በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት የማሟላቱን ሥራ አከናውኖ በአስቸኳይ ለላዕላይ ም/ቤቱ እንዲያሳውቅ፣

1.2 የፓርቲውን ሕጋዊነት ስለማረጋገጥ፡-
ቀደም ሲል ይህንን ተግባር እንዲያከናውን የተቋቋመው ኮሚቴ ያከናወናቸውን ተግባራት በመገምገምና እንደ ግብአት በመጠቀም የፓርቲውን ሕጋዊነት በአጭር ጊዜ ለማረጋገጥ የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን በማጥናት የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለላዕላይ ም/ቤቱ እንዲያቀርብ፣

1.3 አቶ ኃይሉ ሻውል የወሰዷቸውን እርምጃዎች በተመለከተ፡-

ሀ/ የፓርቲያችን መተዳደሪያ ደንብ በክፍል ሦስት አንቀጽ 24 በስምንት ንዑሳን አንቀፆች ውስጥ እንኳንስ የሥራ አስፈፃሚንና የላዕላይ ም/ቤት አባለትን ቀርቶ ማንኛውንም አባል የማገድ ሥልጣን የሚሰጥ ቦታ የለም፡፡

ለ/ እንዲሁም የግል ተወካይ የመሾምም ሆነ የመመደብ ሥልጣን ለሊቀ መንበሩ የሚሰጥ አንቀጽ የለም፡፡ ዴሞክራሲያዊ አሰራርን በሚከተል ፓርቲ ውስጥ እንዲህ ዓይነት አሰራር ፈጽሞ ሊኖር አይችልም፡፡

ሐ/ የፓርቲያችን መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 23 ንዑስ አንቀጽ 1 ሊቀ መንበሩን ተክቶ የመሥራት ኃላፊነት የተ/ም/ሊቀ መንበር መሆን በግልጽ ይደነግጋል፡፡

መ/ በፓርቱው ሊቀ መንበር፣ ተ/ም/ሊቀ መንበር፣ ም/ሊቀ መንበር፣ ዋና ፀሐፊና ሌሎች የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ላይ እርምጃ መውሰድ የሚችለው ላዕላይ ም/ቤት መሆኑን የሚደነግገው የመተዳደሪያ ደንባችን አንቀጽ 9.3.18 ይህ ሊሆን የሚችለው በ2/ኛ ድምጽ መሆኑን አስፍሯል፡፡

ስለሆነም ሊቀ መንበሩ የወሰዱት እርምጃ ፍጹም ሕገ-ወጥ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት መርህ በቅንጅት ፖለቲካ ከሚሰጠው ሥፍራ አንፃር ደግሞ እንዲህ ዓይነት የሕግ ጥሰት ሲፈፀም በቸልታ ማለፍ በፍፁም የሚቻል ነገር አይደለም፡፡ በመሆኑም ደን በሚፈቅደው መሠት ጉዳዩ በዝርዝር ታይቶ ውሣኔ እስከሚሰጥበት ጊዜ ድረስ ሊቀመንበሩ ሕገ ደንቡ ከሚፈቅድላቸው ውጭ በመንቀሳቀስ ቅንጅቱንና አጠቃላይ የፖለቲካ ትግሉን የሚጎዳና የድርጅቱን አባላትና ደጋፊዎች የሚያሳዝን ተግባር ከመፈፀም እንዲታቀቡ ም/ቤቱ በጥብቅ ያሳስባል፡፡

2.4 በሊቀ መንበሩ ሕገ-ወጥ ድርጊት ላይ ተመርተው በሀገር ውስጥ በተመሣሣይ ተግባር ላይ የተሰማሩ ጥቂት የላዕላይ ም/ቤት አባላትም በፓርቲው ሕጋዊ አሰራር ላይ እንቅፋት ከመሆን እንዲቆጠቡ ም/ቤቱ በጥብቅ ያሳስባል፡፡

በመጨረሻም ቅንጅት በሕጋዊነት፣ በጋራ አመራር፣ በአሰራር ግልጽነትና በመልካም ሥነ-ምግባር መርሆች ላይ ተመስርቶ አሁን የገጠሙትን ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች አልፎ የኢትዮጵያ ሕዝብ የጣለበትን አደራ ለመወጣትና የገባውን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ትግሉን በጽናት ይቀጥላል፡፡ ለዚህም ተግባሩ እውን መሆን ሕልናውናውን ማረጋገጥ ወሳኝ በመሆኑ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ከሚመለከታቸው ወገኖች ጋር ሁሉ ተግቶ ይሰራል፣ በሂደት የሚያጋጥሙትንም ችግሮች ለሕዝብ እያሳወቀ ጥረቱን የሚቀጥል መሆኑን እየገለፀ ሕዝቡ የተለመደ ድጋፉን እንዲሰጥ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የቅንጅት ለአንደነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ
የላዕላይ ም/ቤት
ታህሣሥ 23/2000 ዓ.ም.
አዲስ አበባ

ነገ እሁድ የቅንጅት አመራር መሰረታዊ ውሳኔዎችን ያሳልፋል

የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለዛሬ (ቅዳሜ) የጠራው የላእላይ ም/ቤት ስብሰባ ምልአተ ጉባኤ ባለመሟላቱ ባይካሄድም በህገ ደንቡ መሰረት በነገው እለት በሚገኙት የላእላይ ም/ቤት አባላት አብላጫ ድምጽ መሰረታዊ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ የፓርቲው ቃል አቀባይ ዶ/ር ኀይሉ አርአያ ለዝክር ዜና አገልግሎት ገለጹ፡፡

ዶ/ር ያቆብ ኃ/ማርያምንና ዶ/ር ብርሃኑ ነጋን ጨምሮ በተለያየ ምክንያት በአገር ውስጥ የሌሉ 11 የላእላይ ም/ቤት አባላት በነገው እለት በሚካሄደው ጉባኤ ላይ የሚተላለፉትን ውሳኔዎች እንደሚደግፉ በላኩት ደብዳቤ አረጋግጠውልናል ያሉት ቃል አቀባዩ ወሳኝ የፓርቲውን ስራዎች የምናከናውንበት ምእራፍ ላይ ደርሰናል ብለዋል፡፡

በተጓደሉና ሪፖርት ባላደረጉ የላእላይ ም/ቤት አባላት ምትክ የሚደረገውን ምርጫ አስመልክቶም ይህ የሚታወቀው በነገው እለት በሚካሄደው ጉባኤ ላይ አመራሩ ውሳኔ ከሰጠበት በኋላ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡