በቀድሞው የመኢአድ ቢሮ የሚገኙትና ከቅንጅት ህገ ደንብ ውጭ የአቶ ሀይሉ ሻውል ወኪል ሆነው በተሾሙት በአቶ አባይነህ ብርሃኑ የሚመሩት አባላት ደጋፊዎቻቸውን ለማነጋገር በተዘዋወሩባቸው ክልሎች ያጋጠሟቸውን ጉዳዮች አስመልክቶ በዛሬው እለት በጽ/ቤቱ የቃል ሪፖርት ማቅረባቸውን የውስጥ ምንጮች ለዜና አገልግሎቱ ገለጹ፡፡
ደጋፊዎቻቸውን የማነጋገር ተልእኮ ተሰጥቷቸው በተለያዩ ክልሎች የተጓዙት እነዚህ አባላት ያጋጠሟቸውን ችግሮች ሲገልጹ በዋንኛነት ያነሱት በፕሬዝዳንቱ ታግደዋል የተባሉት የአመራር አባላት ጉዳይ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ከወቅቱ አስቸጋሪነት የተነሳ ደጋፊዎችን ማነጋገር ብቻውን እንኳ ፈታኝ የነበረ ቢሆንም በአንድነት ትግሉን የሚመሩ አባላትን አግጃለሁ ማለቱ አብዛኛውን ደጋፊ ያስቆጣና ለገዢው ፓርቲ ያልታሰበ (አንድ የደሴ ነዋሪ አባባል) ሀይሉ ሻውል ለወያኔ ያቀረቡት የሚሌኒየም ስጦታ ነው በማለት ተችተውት እንደነበር አንድ ልኡክ በቅሬታ አንስተዋል:: ይህም ዋንኛው ልኡካኑን በየደረሱበት በተጠየቅ የሞገተ ጉዳይ እንደነበር የቃል ሪፖርቱን ያቀረቡት አባላት ሳይሸሽጉ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ እስካሁን ሊገታ ባልቻለ ወከባና እንግልት ውስጥ የገባበትን ትግል በቀድሞው የመኢአድ ቢሮ በመመሸግና ሊቀ መንበራቸውን ስጋት ውስጥ የሚከቱ የተሳሳቱ መረጃዎች በማቅረብ ስሜታዊውንና እንዴት የቅንጅት መሪ ሆነው ተመረጡ የሚል ጥያቄ በህዝቡ አእምሮ የፈጠሩትን ሀይሉ ሻውልን የሚጠቀሙባቸው የአቶ አባይነህ ቡድኖች ሪፖርቱ እንዲሰማ ያደረጉበት ዋንኛ ምክንያት በሩቅ ርቀት በመሾምና በመሻር ላይ ያሉትን ፕሬዝዳንት አስፈቅደው ጠቅላላ ጉባኤ እንዲጠራ ለማድረግ መሆኑን ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡
ጉባኤው ሲጀመር ስርአት ያለው ስብሰባ የመሰለ ቢሆንም በወ/ት ብርቱካን የሚመራው የስራ አስፈጻሚ ቡድን ሲነሳ ግን በጣም አስገራሚ ወደሚባል አሉባልታና ምክንያታዊ ወዳልሆኑ ዘለፋዎች በመግባት ረዥም ሰአታትን አሳልፈዋል፡፡
በ3ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ቅንጅትን በመወከል ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ያለፉትና በተመረጡበት ጎጃም ውስጥ ህዝቡን በማስተባበር ታዋቂ የሆኑት አቶ ይታየው ጥሩነህ ከእስር ለተፈቱት የቅንጅት አመራሮች በመወገን ሊቀሰቅሱ ይችላሉ በሚል የፈጠራ ክሶች እየቀረቡባቸው መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዜና አገልግሎቱ ገለጹ፡፡
አመራሩ ከእስር ከመውጣቱ በፊት የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች ቅንጅትን በመወከል ፓርላማ የገቡ ግለሰቦችን በማስፈራርያና በመደለያ ወደተለያዩ ቡድኖች እንዲቀላቀሉ ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን ተወካዩ የቀረቡላቸው የተለያዩ አንጃዎች የቅንጅቱን ተልእኮ ያነገቡ አይደሉም በሚል በገለልተኝነት የቆዩና አቋማቸውን በማሳወቅ በፓርላማው ውስጥ በድምጸ ተአቅቦ የተቀመጡ ሲሆን ከአመራሩ መፈታት በኋላ ለቅንጅቱ ይቀሰቅሳሉ በሚል የ16 አመት ታዳጊ ደፍረዋል የሚል የፈጠራ ክስ ተመስርቶባቸው ቆይተዋል፡፡ ይሁንና ተደፍራለች የተባለችው ወጣት ከዚህ ቀደም አግብታ የነበረች መሆኗን፤ በግለሰቡ ያለመደፈሯንና ጉዳዩ ፖለቲካዊ ጫወታ መሆኑን በመግለጽ ለተወካዮች ም/ቤት አፈ ጉባኤ ጽ/ቤት፤/ ወ/ሮ ነጻነት አስፋውን በግል በማነጋገር ጭምር ምርመራውን ለያዘው የቦሌ ክ/ከተማ ፖሊስ፤ ለሴቶች ጉዳይ ጽ/ቤትና ለመሳሰሉት ብታቀርብም ፖለቲካዊ ብትሩ ግን በግለሰቡ ላይ እስካሁን መቀጠሉን ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡
ተመራጩ በዛሬው እለት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 7ኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡ ቢሆንም በሁኔታው ግራ የተጋቡት ዳኛና አቃቤ ህግ በወ/መ/ቁ 97439 ቁጥር 988/06/99 የተያዘውን የክስ መዝገብ ለሁለተኛ ግዜ ተጠቂ እስክትቀርብ በሚል ዘግተዋል፡፡
ሁኔታውን በጥልቀት የሚያውቁ የቅንጅቱ ቤተሰቦች በዛሬው እለት የታየውን ችሎት ለመታደም በልደታ ፍርድ ቤት መሰብሰብ የጀመሩት ከጠዋቱ 2፡00 ሰአት ጀምሮ ሲሆን አዳራሹ ስላልበቃ ውጤቱን ውጭ በመሆን ሲጠባበቁ ታይተዋል፡፡
በምስራቅ ሸዋ ዞን ዝዋይ ከተማ ቀበሌ 02 የሚኖሩና በንግድ ስራ የሚተዳደሩ አራት የቤተሰብ አባላት በሚያዝያ ለሚካሄደው ምርጫ ካርድ አንወስድም በማለታቸው በታጣቂዎች ተወስደው መታሰራቸውን ሪፖርተራችን ከስፍራው ዘገበ፡፡
ወራት የቀሩትና ተመዝጋቢ በማጣት እስከቀጣዩ ወር መጀመርያ የተራዘመውን የመራጮች ምዝገባ ለመቀስቀስ በየቤቱ መዞር የጀመሩት የዝዋይ ከተማ የምርጫ አስተባባሪዎች በየቤቱ በመዞር ነዋሪዎቹ የመምረጫ ካርድ መውሰዳቸውን መጠየቅ የጀመሩት ባለፈው ሳምንት መጀመርያ ላይ መሆኑን ዘገባው ያመለከተ ሲሆን ትናንት ማምሻው ላይ በተለመደው ተግባር ላይ ተሰማርተው ማስፈራርያ የተሞላባቸው መጠይቆችን ሲያደርጉ በ02 ቀበሌ ጅንአድ ጀርባ የሚኖሩትና በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩት አቶ ግዛው አበጋዝ የምርጫ ካርድ ያለመውሰድ መብት አለኝ በማለት ባነሱት የመብት ጥያቄ በተፈጠረ ውዝግብ ከሁለት ልጆቻቸውና በግሮሰሪያቸው ውስጥ ከሚረዳቸው ዘመዳቸው ጋር ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደው እስከዛሬ ከሰአት በኋላ ከቆዩ በኋላ በዋስ ተለቀዋል፡፡
የቅንጅት ተወዳዳሪዎች በምርጫ 97 ወቅት ባሳዩት ከፍተኛ ተሳትፎ ለምርጫው ልዩ ተነሳሽነት አሳይቶ የነበረው መራጭ ህዝብ ሂደቱ ባልታሰበ መንገድ ተደነቃቅፎ ከቀረ በኋላና በተለይም የዝዋይ ህዝብ በመረጣቸው የቅንጅቱ ተወካይ ፋንታ ኦህዴድን ወክለው የተወዳደሩት ግለሰብ በማጭበርበር ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ካለፉ በኋላ ቀጣዩ የማሟያ ምርጫ ትኩረት መሳብ እንዳልቻለ የከተማዋን ነዋሪዎች አስተያየት ዋቢ ያደረገው ዘገባ ያመለክታል፡፡
በከተማዋ ኦህዴድን በመወከል የተወዳደሩትና በከፍተኛ የድምጽ ልዩነት የተሸነፉት የዝዋይ ከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ም/ር/መምህር የሆኑት አቶ ሚሊዮን ጋረደው ብሩ የሚባሉ ግለሰብ እንደሆኑ ከትናንቱ አሳፋሪ ክስተት በኋላ ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው ነዋሪዎች የጠቆሙ ሲሆኑ ቅንጅቱን በመወከል ያሸነፉት ተወዳዳሪ እንዲሸማቀቁ የሚያደርጉ ጫናዎች ሲደረጉባቸው እንደከረሙ ተገልጧል፡፡
በምርጫ ታሪክ በጣም ቀዝቃዛውና በተመዝጋቢ ድርቀት አስተባባሪዎቹን ያሸማቀቀው የሚያዝያው ምርጫ የተመዝጋቢዎች የጊዜ ሰሌዳ ዛሬ የሚጠናቀቅ ቢሆንም እስከ ቀጣዩ ወር መጀመርያ ድረስ እንዲራዘም በምርጫ ቦርድ ተወስኗል፡፡
ይህ ገዢው ፓርቲ ከራሱ ጋር የሚወዳደርበት የመሰለ የምርጫ ሂደት ለወያኔ ያለው ፋይዳ ያን ያህል ባይሆንም እንደተቃዋሚ የሚቆጠሩትን በጣት የሚቆጠሩ ፓርቲ እጩዎች ከማሰር ጀምሮ የተለያዩ ጫናዎች እያደረሰባቸው መሆኑን መሪዎቹ በመግለጽ ላይ ይገኛሉ፡፡
ምርጫ 97ትን ተከትሎ በተፈጠረው ቀውስ የቤተሰብ አባላቸውን ላጡ ዜጎች ማቋቋሚያ የሚሆን ገንዘብ በማሰባሰብ የጥቃቱ ሰለባ የነበሩት ዜጎች ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ በማመቻቸት ላይ መሆናቸውን አንድ የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ የአመራር አባል ለዜና አገልግሎቱ ገለጹ፡፡
አንዳንድ ቤተሰቦች የግፉ ሰለባ በመሆን የበለጠ ተጎጂዎች ነበሩ ያሉት እኒሁ የአመራር አባል ህዝቡ በዴሞክራሲያዊ መንገድ አመራሩን በመምረጥ ለነጻነት ላሳየው ቁርጠኝነት ምላሹ ኢ-ሰብአዊ ጭፍጨፋ ቢሆንም የሰማእቱን ዉለታ ለመዘከር ፓርቲያቸው ሰፊ እቅድ ማዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ የቅንጅት ይህን እቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ ትግሉን በተለያዩ መንገዶች ሲያግዙ ከነበሩ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጋር እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡
የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲን ህልውና ለማጥፋት ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ያለበት ፈታኝ ወቅት ቢሆንም ትግሉን የሚያጎለብቱ በርካታ ድርጅታዊ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የገለጹት እኒህ አመራር እስረኞችን ከማስፈታቱ ስራ ጎን ለጎን የግፍ ጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ቤተሰቦችን የማደራጀቱ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል፡፡
ምርጫ 97ትን ተከትሎ በተፈጠረው ቀውስ ለእስር የተዳረጉ የቅንጅት ደጋፊዎችንና አባላትን ለማስፈታት የቅንጅት ስራ አስፈጻሚ አባላትና የአገር ሽማግሌዎች በጥምር በመስራት ላይ መሆናቸውን አንድ የስራ አስፈጻሚ አባል ለዜና አገልግሎቱ ገለጹ፡፡
ህዝባዊውን ፓርቲ ህጋዊ ከማድረጉ እንቅስቃሴ ጎን ለጎን እየተካሄደ ባለው እስረኞችን የማስፈታት እንቅስቃሴ በትናንትናው እለት 24 ያህል ፍርድ የተሰጠባቸው እስረኞችን የምህረት ሰነድ ያስፈረሙ ሲሆን በዛሬው እለት በተካሄደ የስራ አስፈጻሚው ስብሰባ ደግሞ ጉዳያቸው በፍርድ እየታየ ያሉት ሌሎች እስረኞችም የምህረቱ ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ ጥረት ለማድረግ ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
በተቀዳሚ ም/ሊቀመንበር ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የሚመራው የስራ አስፈጻሚ ቡድን በፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ ከሚመራው የአገር የሽማግሌዎች ቡድን ጋር በመተባበር እስረኞቹን አስመልክቶ ለህዝቡ የገባውን ቃል ለመፈጸም ያለመታከት እንደሚሰራ የአመራር አባሉ ጨምረው ገልጸዋል፡፡