Skip to content

Author: EthiopianReview.com

ይፋ የሆነው የወያኔ እጩዎች ዝርዝር ውዝግብ አስነሳ

በቀጣዩ ሚያዝያ ለአከባቢና ማሟያ ምርጫ በወያኔ ካድሬዎች በሚመለመሉበት ወቅት ፈቃደኛ ያለመሆናቸውን ገልጸው የነበሩ አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ይፋ በተደረገው የእጩዎች ዝርዝር ውስጥ ስማቸው በመገኘቱ በምርጫ ጣቢያዎች ውዝግብ በመነሳት ላይ ነው፡፡

ለቀጣዩ ምርጫ አራት ሚሊዮን እጩዎችን ያቀረበው ወያኔ ባልታሰበ መንገድ የተቀሰቀሰውን የቅሬታ ውዝግብ ለማብረድ በምርጫ አስፈጻሚዎች አማካይነት የማረጋጋት ስራ እየሰራ ይገኛል፡፡ እጩዎች በሚመለመሉበት ወቅት ምንም አይነት የፖለቲካ ተሳትፎ የሌላቸውን ግለሰቦች ሳይቀር በወያኔ እጩነት ለማጋበስ አሳፋሪ እንቅስቃሴ ሲካሄድ የነበረ ሲሆን በወቅቱ ‹‹ተቃዋሚዎች አይደለንም፤ ሆኖም በፖለቲካዊ ጉዳዮች በተለይም ፓርቲ ወክሎ እጩ ሆኖ ለመቅረብ ልምዱም ዝግጅቱም የለንም፡፡›› ያሉ ግለሰቦችን በዝምታ ካለፉ በኋላ የትም አይደርሱም በሚል እሳቤ ዝርዝራቸው ይፋ በመደረጉ ከምርጫ ጣቢያዎቹ ማስታወቂያ ሰሌዳዎች ላይ በአስቸኳይ ስማቸው እንዲሰረዝ ሲሟገቱ የተመለከቱት ዘጋቢዎቻችን ሪፖርት ያመለክታል፡፡

የምርጫ ጣቢያ ሃላፊዎቹ ውዝግቡ እንዳይባባስ በሚል የተፈጠረ ችግር ካለ በአስቸኳይ ይስተካከላል ከማለት አልፈው ስማችን ያላግባብ ይፋ ሆኗል የሚሉትን ቅሬታ አቅራቢዎች ስም ከሰሌዳው ላይ የመሰረዝ አስገራሚ ድራማ ሲሰሩ ተስተውሏል፡፡ ተመሳሳይ በደል የደረሰባቸው አንድ በጡረታ ላይ የሚገኙ ግለሰብ እንደገለጹልን በግድ እጩ የተደረጉት ሁሉ ይውጡ ቢባል ጉዱ ይታይ ነበር፤ ይሁንና በካድሬዎች ማስፈራርያ እየተሰጣቸው በዝምታ ሁኔታውን እየተከታተሉ ነው በማለት የሁኔታውን አስከፊነት አስቀምጠውታል፡፡

በቅንጅት አስተባባሪዎች ላይ የተከፈተው ጥቃት ቀጥሏል

በመላው አገሪቱ በሚገኙ የቅንጅት አስተባባሪዎችና ለፓርቲው ከፍተኛ አስተዋጽኦ በሚያበረክቱ ግለሰቦች ላይ የተከፈተው ያለ ህግ ስርአት የማሰርና የማንገላታት ጥቃት መቀጠሉን አንድ የአመራር አባል ለዜና አገልግሎቱ ገለጹ፡፡

በደቡብ ኦሞ ዞን የጂንካ ወረዳ የቅንጅቱ አስተባባሪ የነበሩት አቶ ከተማ በላቸው በተመሳሳይ መንገድ የጥቃቱ ሰለባ በመሆን ላለፉት ሶስት ቀናት በእስር ላይ ከቆዩ በኋላ ዛሬ ከሰአት በኋላ በዋስ ተለቀዋል፡፡ በእስር የቆዩባቸውን ቀናት አስመልክቶ የነበራቸውን የፖሊስ ጣቢያ ምርመራ አስመልክቶ በስልክ በሰጡን አስተያየት ‹‹የፈጠራ ክስ መስርቶ የሃሰት ምስክሮችን ለማቅረብ ከፍተኛ ጥረት ሲካሄዱባቸው የቆዩባቸው አስነዋሪ ቀናት ነበሩ፡፡›› በማለት ገልጸዋል፡፡ አስተባባሪው የክልሉ ተወላጅ እንደሆኑ ቢታወቅም ብሄር ላይ ያተኮረ አሉታዊ ቅስቀሳ አድርገዋል የሚል ክስ እንደቀረበባቸውና ፍርድ ቤቱ የቀረበው ክስ ተጨባጭ መረጃ የሌለው ነው በማለት በዋስ እንዲሰናበቱ ማድረጉን አብራርተዋል፡፡

እንደ አቶ ከተማ አባባል በወረዳዋ ያሉት አብዛኞቹ አባላት በየጊዜው በሚደርሱባቸው እስር፤ ዛቻና ማስፈራርያዎች ራሳቸውን ከፓርቲ አባልነት በማግለል ላይ መሆናቸውን በሃዘን በማስታወስ በተለይ ሊቀመንበሩ ወስደዋቸው የነበሩት አስገራሚ የእግድ ውሳኔዎች ለበርካታ አባላት ፓርቲውን መልቀቅ መንስኤ እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡ በክልሉ ያሉት የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች በወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ከሚመራው የስራ አስፈጻሚ ቡድን ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንደሚያደርጉ በመግለጽ ፈታኙ ትግል ፍሬ እስከሚያፈራ በጽናት ለመቆም ቁርጠኝነታቸውን ጠብቀው እንደሚቆዩ ያላቸውን እምነት ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ እጩዎች ዝርዝር ይፋ ሆነ

በአዲስ አበባ ከተማ ለቀጣዩ የሚያዝያ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የማሟያና የክፍለ ከተማ/የቀበሌ/ ም/ቤትየሚወዳደሩ እጩዎች ዝርዝር በዛሬው እለት ይፋ ሆነ፡፡ ዝርዝሩን የሚያሰራጩ ከ300 በላይ አባላት ተመድበዋል፡፡

በምርጫ ውድድሩ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች ህብረት፤ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፤ የመላው ኢትዮጵያውያን ብሄራዊ ንቅናቄ፤ የኢትጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ህብረት፤ ኢህአዴግ፤ የግል ተወዳዳሪዎችና የአየለ ጫሚሶ ቅንጅት ይገኙበታል፡፡

አብዛኞቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እጩዎቻቸውን ያቀረቡት ለተወካዮች ም/ቤት የማሟያ ምርጫ ሲሆን በአብዛኞቹ ክፍለ ከተሞች ከፍተኛ ፖለቲካዊ አንድምታ ያለውን የክፍለ ከተሞች ም/ቤት በተለያዩ ምክንያቶች ሳይሳተፉባቸው ቀርተዋል፡፡ የወያኔ ዋንኛ ትኩረት ደግሞ እነዚህ የምርጫ እድሎች በመሆናቸው ሙሉ ሃይሉን በክፍለ ከተማ ም/ቤቶች ላይ በማድረግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው እጩዎችን አቅርቧል፡፡ የእጩዎቹን መስፈርትም ከዚህ በፊት ያደርግ እንደነበረው ‹‹በታማኝነት›› ከማድረግ ይልቅ በምርጫ 97 ቅንጅት የተማረውን ሃይል በማሰባሰቡ ያገኘውን ህዝባዊ ድጋፍ ግንዛቤ ውስጥ በመክተት ዝቅተኛው የትምህርት ደረጃ 12ኛን ያጠናቀቀ እንዲሆን በማድረግ የሃይል ሚዛኑን ለመቀየር ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ በዚህ መሰረትም ለምርጫው ከሚቀርቡት ከ60 በመቶ በላይ ያህሉ የመጀመርያ ድግሪ ያላቸው እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ በዝርዝሩ ዙርያ ተቃዋሚዎች በዚህ ሳምንት መግለጫ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በክልል ለምርጫው ከቀረቡ የተቃዋሚ ፓርቲ እጩዎች በደረሱባቸው የተለያዩ ተጽእኖዎች የተወሰኑት ራሳቸውን ማግለላቸውን ፓርቲዎቻቸው የገለጹ ሲሆን በአዲስ አበባ ወረዳ 18 ሪቼ አከባቢ መኢብንን በመወከል እጩ ሆነው የቀረቡትና ቀድሞ የፓርላማ ፕሮቶኮል ሹም እንደነበሩ የሚታወቁት ወ/ሮ ገነት አየለ ተመሳሳይ ማስፈራርያ ደረሰኝ በማለት ራሳቸውን ከምርጫው ማግለላቸውን ሊቀ መንበሩ አቶ መስፍን ሽፈራው ገልጸዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በጋሞጎፋ ዞን የዛላ ወረዳ የቅንጅት አስተባባሪ የነበሩትና ባለፈው ሳምንት ከስራ ቦታቸው ታፍነው በመወሰድ ታስረው የነበሩት አቶ አየለ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ተፈተዋል፡፡ አስተባባሪው ከስራ አስፈጻሚው ቡድን ጋር አንዳችም አይነት ግንኙነት ሲያደርጉ ቢገኙ ሃላፊነቱን እንደሚወስዱ አስፈርመው እንደፈቷቸው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የተቃዋሚ ፓርቲ እጩዎች ራሳቸውን እያገለሉ ነው

በሰሜን ሸዋ ዞን ግራር ጃርሶ ወረዳ የጉለሌ ንኡስ ወረዳ የኦፌዴንና የኦህኮ እጩዎች ያለ ህግ ስርአት በእስር ላይ ከቆዩ በኋላ ራሳቸውን ከምርጫው ማግለላቸውን ለወረዳው ምርጫ ጽ/ቤት አስታወቁ፡፡

ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለፓርቲዎቻቸው በእጩነት ቀርበው የነበሩት ወጣቶች በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ታፍሰው ወደ ድሬ ዳለቲ ማረሚያ ቤት ከተወሰዱ በኋላ በደረሰባቸው ማስፈራርያና ዛቻ ከእስር እንደወጡ ራሳቸውን ለማግለል እንደተገደዱ አንደኛው እጩ ለዜና አገልግሎቱ ገልጸዋል፡፡ እርምጃው የወያኔን ካድሬዎች ሳይቀር ውዝግብ ውስጥ የከተተ ሲሆን በደሉ የተፈጸመው በእጩዎቹ ሳይሆን በመራጩ ህዝብ ላይ እንደሆነ እንቆጥረዋለን በማለት በዋና ከተማዋ የካምቦ ነዋሪ የሆኑትና የምርጫ አስፈጻሚ ተብለው ቢመረጡም ፈቃደኛ ሳይሆኑ የቀሩት አቶ ወርዶፋ ተሹ በተለይ ለዜና አገልግሎቱ ገልጸዋል፡፡ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በበኩላቸው ፍርዱን የኢትዮጵያ ህዝብ ይሰጣል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል የኦህኮ እጩ የነበሩ አንድ ግለሰብ በዚሁ ዞን ገብረ ጉራቻ ከተማ ላይ ወደ ምርጫ ጽ/ቤት ቦንብ ይዘው ሲገቡ ይዘናቸዋል በሚል ወደ እስር ቤት የተወሰዱ ሲሆን የከተማዋ የኦህኮ ምርጫ ሃላፊ አሳፋሪ የሃሰት ውንጀላ በማለት ድርጊቱን ኮንነውታል፡፡

የቅንጅት የላእላይ ም/ቤት በቀጣዩ ሳምንት ወሳኝ ስብሰባ ያደርጋል

እስካሁን በነበረውና ወደፊት ሊከናወኑ በሚገባቸው ወሳኝ የትግል እንቅስቃሴዎች ላይ አሳሪ ውሳኔዎችን ለማሳለፍ የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ የላእላይ ም/ቤት በቀጣዩ ሳምንት ስብሰባ ያደርጋል፡፡

ምርጫ 97ትን ተከትሎ በተፈጠረው ቀውስ የታሰሩ የፓርቲው አባላትን በማስፈታት፤ አደጋ ላይ ወድቆ የነበረውንና በራሱ ሊቀመንበር የማፍረስ ሙከራ የተደረገበትን ህዝባዊ ፓርቲ በማዳን፤ በክልሎች ያሉ አባላትን በማነጋገር፤ በማደራጀትና በመሳሰሉት ግዜ የማይሰጡ ተግባራት ተጠምዶ የነበረው የአመራር አካል በቀጣዩ ሳምንት በሚያደርገው ስብሰባ ለህዝቡ በቀጣዩ ሂደት ላይ የሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴዎችና የአካሄድ ስልቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የስራ አስፈጻሚ አካሉ ለቀጣዩ ሳምንት ወሳኝ ስብሰባ ዝግጅት በማድረግ ላይ ሲሆን ስብሰባው በህዝቡ አእምሮ ለሚመላለሱት በርካታ ጥያቄዎች አጥጋቢ ምላሽ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል

የዛላ ወረዳ የቅንጅት አስተባባሪ ታሰሩ

በጋሞጎፋ ዞን ዛላ ወረዳ የቅንጅት አስተባባሪ የሆኑት አቶ አየለ አርብ እለት ከሰአት በኋላ በወያኔ ካድሬዎች ከስራ ቦታቸው ታፍነው ከተወሰዱ በኋላ እስካሁን በእስር ላይ እንደሚገኙ ምንጮቻችን ገለጹ፡፡

የቅንጅት የስራ አስፈጻሚ ቡድን በደቡብ ክልል ደጋፊዎቹንና አባላቱን አነጋግሮ ከተመለሰ በኋላ በደጋፊዎቹና በአስተባባሪዎቹ ላይ ከፍተኛ የማንገላታትና ተደጋጋሚ እስሮች ያጋጠሙ ሲሆን የዛላ ወረዳ አስተባባሪ የሆኑት አቶ አየለ ያለምንም ጥፋት ከስራ ቦታቸው በፖሊች አባላት ታፍነው መወሰዳቸው የወረዳዋን ነዋሪ ቁጣ ቀስቅሷል፡፡የዛላ ወረዳ ነዋሪ ሆኑ አንድ ግለሰብ በስልክ በሰጡን አስተያየት የወረዳዋ ህዝብ ለዘመናት የተፈራረቁ ገዢዎች የግፍ በትራቸውን ሲያሳርፉባት ኖረዋል በማለት በአስተባባሪው ላይ የተፈጸመው እስር ሆን ተብሎ ህዝቡን ለማሳቀቅ የተወሰደ እርምጃ ነው ብለዋል፡፡

በአባሉ ላይ የተወሰደውን እርምጃ አስመልክቶ ምን የህግ እንቅስቃሴ ጀምራችኋል በማለት ለቅንጅቱ አመራሮች ጥያቄ ያቀረብንላቸው ሲሆን ጉዳዩን በቅርብ እየተካታተሉት መሆኑን ገልጸው እንዲህ አይነት ግብታዊ እርምጃዎች የስርአቱን አምባገነናዊነት ከማረጋገጥ የዘለለ ትግሉን ወደኋላ የሚስብበት ምንም እድል አይኖርም በማለት ገልጸዋል፡፡