Skip to content

የሙስና ምርመራ እየተወሳሰበ ነው

Posted on

መበላላት እንዳይጀመር ስጋት አለ

By Goolgule.com

June 18, 2013

Sheraton Addis
Sheraton Addis

በጉምሩክና ገቢዎች ባለስልጣን የተጀመረው የጸረ ሙስና ዘመቻ ተከትሎ እየተካሄደ ያለው ምርመራ እየተወሳሰበ መሔዱ ተሰማ። በከፍተኛ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ተከሳሾች የሚሰጡት መረጃ መበላላት ያስነሳል የሚል ፍርሃቻ እያስነሳ ነው። “ሰፈር የለየው” የጸረ ሙስና ዘመቻ የፈጠረው ስጋት የሃይል ሚዛን የያዙትንም ስጋት ውስጥ ከትቷል።

በኢትዮጵያ ባለፉት 10 ዓመታት ውስጥ የታየው የውስን ሰዎች በድንገት በመበልጸግ ከባለስልጣኖችና ከከፍተኛ የስርዓቱ ሰዎች ቤተሰቦች ጋር በሚከናወን መተሳሰር አማካይነት እንደሆነ ከህዝብ የተሰወረ አይደለም። ሰሞኑንን ይፋ የተደረገው የባንክና የንብረት እግድ እንዳመለከተው የዝርፊያው ሰንሰለት በቤተሰብ የታጠረ መሆኑን ነው።

አቶ መለስ ከድነው ያቆዩትና የሳቸውን ሞት ተከትሎ ከፖለቲካው ልዩነት ጋር በተያያዘ እንደተጀመረ የሚነገርለት የጸረ ሙስና ዘመቻ፣ በመንግስት በኩል “ቆራጥ” አቋም የተያዘበት እንደሆነ ቢነገርም አስጊ ሁኔታ እየተፈጠረ ስለመሆኑ የጎልጉል የጸረ ሙስና ኮሚሽን ምንጮች ይናገራሉ።

እየተካሄደ ካለው ምርመራ በተገኙ ጭብጦች መታሰር የሚገባቸው ባለስልጣናት እንዳሉ የሚጠቁሙት እነዚሁ ክፍሎች፣ ምርመራው እየሰፋና እየጠለቀ ሲሄድ ችግር ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋት ማሳደሩን አይሸሽጉም።

“የመጨረሻው መጠፋፋት መጀመሪያ ላይ እንዳሉ የሚሰማቸው አሉ” በማለት ለጎልጉል መረጃ የሰጡት ክፍሎች “እየሰፋ የሄደውንና መጨረሻው ወዴት እንደሚያመራ የሚታወቀውን የጸረ ሙስና ዘመቻ የማስቆም ፍላጎት እንዳለ የሚያመላክቱ ሁኔታዎች በቢሮ ደረጃ እየሰማን ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ዘመቻው ተጠናክሮ መቀጠል አለበት የሚሉ ክፍሎች ስላሉ በሙስና የሚጠረጠሩ ፕሮጀክቶችና ከፍተኛ ግንባታዎችን አስመልክቶ በስፋት መረጃ የሚደርሰው ኮሚሽኑ፣ ከነገ ዛሬ ይመጣብናል በሚል የተፈጠረው መደናገጥ በህገወጥ ሃብት የሰበሰቡትን በሙሉ ስጋት ላይ ጥሏቸዋል። በባንኮች አካባቢ ገንዘብ የማሸሽ፣ ከዶላር ገበያ ራስን የማግለልና የሃይል ሚዛን በመመልከት የመተጣጠፍ ሩጫ በስፋት እንደሚስተዋል የጎልጉል ሰዎች ተናግረዋል።

በሙስናው ሰለባ የሆኑት ቡድኖች አቅማቸውና ትስስራቸው ቀላል ባለመሆኑ፣ የታጠቁ ሃይሎችም ስላሉበት የርስ በርስ መተላለቅ ሊከተል ይችላል በሚል ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚደረግ ያመለከቱት ምንጮች “አቶ መለስ የዘረጉትን ሰንሰለት ሙሉ በሙሉ የመቆጣጠር ችግር እየታየ ነው። መተላለቁ በዚህ ክፍተት ውስጥ ሊከሰት ይችላል” የሚል ስጋት መንገሱን አመልክተዋል።

የሚታወቁ ባለስልጣናትና የክልል አመራሮች “ልማታዊ” ከሚባሉት ኢህአዴግ ሰራሽ ባለሃብቶች ጀርባ ሆነው ፕሮጀክትና ጨረታ በማጸደቅ ምዝበራውን እንደሚመሩ መረጃ ስለመኖሩ የሚናገሩት ምንጮች፣ “በቅርብ ተመስርተው ከፍተኛ ሃብት በሰበሰቡ ሪል ስቴት፣ የኮንስትራክሽን ድርጅቶች፣ አስመጪና ላኪዎች፣ ሰፋፊ መሬት ለአረብ አገር ባለሃብቶች በማስማማት አየር በአየር የሚጫወቱ፣ በአገሪቱ ከሚታዩት ታላላቅ ግንባታዎች ጋር በተያያዘ ወዘተ ዋናዎቹ ባለስልጣኖችና ቤተሰቦቻቸው ተዋናይ መሆናቸው ይታወቃል። የህወሃት ሰዎች ግንባር ቀደም ናቸው” በማለት የስጋቱን መጠን ይገልጻሉ።

ከአገር ውስጥ በተጨማሪ በአፍሪካና በተለያዩ አገራት የሽርክና ንግድ የከፈቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት እንዳሉ የሚገልጹት የኢህአዴግ የቅርብ ሰዎች “አሁን አመራር ላይ ያሉት የህወሃት ሰዎች የእነዚህን ባለስልጣናት በቤተሰብና ከፍተኛ አቋም በገነቡ ድርጅቶች አማካይነት የተበተቡት ሰንሰለት በቀላሉ መበጠስ ስለማይችሉ የሙስናው ዘመቻ አደጋ ይገጥመዋል። አለያም እርስ በርስ መበታበት ሊከተል ይችላል” በሚል ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከቀረጥ ነጻ በማስገባት ከፍተኛ የመንግስት ገቢ ለግል ተጠቅመዋል በሚል በተከሰሱት ሰዎች ላይ እየተካሄደ ባለው ምርመራ ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ በከፍተኛ ባለስልጣናት ትዕዛዝ አማካይነት የቀረጥ ነጻ ፈቃድ መስጠታቸውን ለምርመራ መኮንኖች መናገራቸውን የጎልጉል ምንጮች አመልክተዋል።

በዚህም የተነሳ ሸራተንን ተገን ያደረጉት የባለሃብቱ ወኪል ከፍተኛ ስጋት ውስጥ መውደቃቸው ተሰምቷል። በነባር የህወሃት ሰዎች የማይወደዱት እኚሁ የባለሃብቱ ወኪል፣ ወ/ሮ አዜብን፣ አቶ አዲሱ ለገሰና የባለሃብቱ ዋና ሸሪክ የሆኑትን አቶ በረከትን ቢተማመኑም ምርመራው ወደእርሳቸው ሊሄድ እንደሚችል የጎልጉል ምንጮች ማረጋገጣቸውን ጠቁመዋል። አንዳንዶቹ የቀድሞ ሸሪኮቻቸው ስልካቸውን ስለማያነሱላቸው ጭንቀት ውስጥ መግባታቸውና ከወትሮው የተለየ ያለመረጋጋት እንደሚታይባቸው የቅርብ ሰዎቻቸውን ሳይቀር ሰላም እንደነሳ ለማወቅ መቻላቸውንም ተናግረዋል።

አብዛኛውን የንግድ በሮች በስጋ ዘመዶቻቸውና በአገር ልጆች ተብትበው የያዙት የባለሃብቱ የኢትዮጵያ ወኪል ምርመራ ዙሪያ የሚነሱትን ጉዳዮች ከመጥቀስ የተቆጠቡት ምንጮች፣ በቅርቡ አዲስ ነገር እንደሚሰማ መረጃዎች እንዳሏቸው አመልክተዋል። ለሸራተኑ ሰውና ለሸራተኑ ቡድኖች እጅግ ቅርብ ነን የሚሉ በበኩላቸው “ወ/ሮ አዜብ መስፍንና አቶ አዲሱ ለገሰ እስካልተነኩ ድረስ ሸራተን ሰላም ነው። አቶ ጌታቸውም እዛው ናቸው” ሲሉ የለበጣ ቀልድ ቀልደዋል። እነዚሁ ክፍሎች ቢያንስ “የኤች አይ ቪ/ኤድስ እድሜ ማራዘሚያ እናመርታለን፣ ለወገን እንደርሳለን በሚል ሰበብ በከፍተኛ ማጭበርበር የተፈጸመውን ወንጀል ጉዳይ ዝም አይበሉት” ሲሉ ለጠ/ሚ/ር ሃይለማርያም ደሳለኝ አደራቸውን አስተላልፈዋል።

Leave a Reply