Skip to content

ኢህአዴግ ጣና በለስን ለምን አፈራረሰው? “በሩ ይከፈት፣ በአባይ ጉዳይ አገራዊ አቋም እንያዝ”

ጣና በለስን አፈራርሶ ያስዘረፈ ፓርቲና አመራሮቹ አሁን አባይን ለመገደብ የተነሱበት መነሻ ለአብዛኛው የኢህአዴግ አባላት እንቆቅልሽ ነው”

By Goolgule.com

June 7, 2013

Tana Beles
በግብጽ ረዳትነት፣ በሱዳን መሪነት መንግስት ለመሆን የበቃው ህወሃት/ኢህአዴግ ግዙፉን የጣና በለስ ፕሮጀክትና ንብረቱ
እንዲዘረፍ ያደረገበትን ምክንያት በማንሳት መከራከር እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ። የግብጽ ፕሬዚዳንት ሙርሲ እንዳደረጉት በአገር
ጉዳይ ሁሉንም ያሳተፈ ግልጽ አቋም እንዲያዝና አጋጣሚውን በመጠቀም ብሔራዊ ህብረት እንዲፈጠር ኢህአዴግ በሩን ሊከፍት
እንደሚገባ ተገለጸ።

በተለያዩ ጉዳዮች ምክንያት ስማቸው እንዳይጠቀስ በማሳሰብ ለጎልጉል አስተያየት የሚሰጡት የኢህአዴግ ሰው እንዳሉት በርካታ
ጉዶች ያሉበትን የአባይን ግድብ ተከትሎ ከግብጽ ጋር የተነሳው ውዝግብ አስቀድሞ የሚታወቅ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ስልትና ውጤት
ነው።

አሁን ድረስ አገር እየመራ በነጻ አውጪ ስም የሚጠራው ህወሃት/ኢህአዴግ አዲስ አበባ ሲገባ “ዲሞክራሲ አመጣሁ” በማለት
ኢትዮጵያን መምራት እንደጀመረ የሚያወሱት የኢህአዴግ ሰው፤ አቶ መለስ ብቻቸውን ይነዱት የነበረው ኢህአዴግ እንደፈለገ ቆዳውን
እየቀያየረ የተጠቀመበትንና በእስስት በመመሰል “ከሽፏል የሚሉትን” ስልት ያብራራሉ።

በዲሞክራሲ ስም የተጀመረው የኢህአዴግ አገዛዝ ቆየት ብሎ “ልማታዊ ነኝ፣ ልማት ግቡን የሚመታው በአብዮታዊ ዲሞክራሲ
ቀመር ነው” በማለት ፕሮፓጋንዳውን አሰፋ። የልማት ህልመኛነቱ ሲነቃበት “የትራንስፎርሜሽን ዘመቻ” በማለት አዲስ የፕሮፓጋንዳ
እቅድ ነድፎ ህዝብና አገር ሲያታልል ቆየ። ይህም አላራምድና በህዝብ የመታመን ድል ሊያስገኝለት እንደማይችል ሲታመን
“የህዳሴያችን ግድብ” ተብሎ አባይ አጀንዳ እንደተደረገ ያመለከቱት ዲፕሎማት፤ “ኢህአዴግ አገር ውስጥ የሚያምታታባቸው
መንገዶች ሲጠናቀቁበት የፕሮፓጋንዳውን ዘመቻ አንድ ደረጃ ከፍ አደርገው” በማለት አሁን ከግብጽ ጋር ስለተጀመረው ውዝግብ
አስተያየታቸውን ይጀምራሉ።

አባይን በመገደብ ኢትዮጵያን በልማት ለማሳደግ እየተጋ እንደሆነ የሚናገረው ኢህአዴግ፤ አስቀድሞ በመላው የብአዴን የበታች
አመራሮችና በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታና ቂም ስላስቋጠረው የጣና በለስ ሰፊ ፕሮጀክት ዝርፊያና ውድመት
የጠራ መልስ ሊሰጥ እንደሚገባ ዲፕሎማቱ ይናገራሉ።

በጣሊያን መንግስት ሙሉ ድጋፍ አባይ ወንዝን መሰረት አድርጎ የተገነባውን የጣና በለስ ፕሮጀክት ህዝብ እያየ አፈራርሰው
እንደወሰዱት፣ የተዘረፈው ንብረት ወደ ኤርትራ እንዲጓጓዝ መደረጉን ያመለከቱት እኚሁ ሰው፣ “ጣና በለስን አፈራርሶ ያስዘረፈ
ፓርቲና አመራሮቹ አሁን አባይን ለመገደብ የተነሱበት መነሻ ለአብዛኛው የኢህአዴግ አባላት እንቆቅልሽ ነው” ባይ ናቸው።
በማያያዝም በወቅቱ ዝርፊያው ሲካሄድ ህዝብ አካፋና ዶማ በመያዝ “ንብረቱ አይዘረፍም” በማለት መንገድ በመዝጋቱ ዝርፊያው
በሌሊት እንዲካሄድ ያደረገ ድርጅት እንዴትስ ይታመናል የሚል ጥያቄ ያነሳሉ።

“ኢህአዴግ የህይወት ዘመኑ የሚጠናቀቅበት ጠርዝ ላይ ስለሚገኝ፣ በአባይ ጉዳይ አመካኝቶ ህዝባዊ ማዕበል ለማቀጣጠል አቅዷል።
የአባይ ጉዳይ ከዚህ የተለየ ተግባርና ዓላማ የለውም” የሚሉት አስተያየት ሰጪ፣ የጣና በለስ ፕሮጀክት እንዲወድም መመሪያ
የተሰጠው ከግብጽ እንደነበር መረጃ እንዳላቸው አመልክተዋል። የኢትዮጵያ ቀንደኛ ታሪካዊ ጠላት የሆነችው ግብጽ አባይ ላይ
የሞትና የህይወት አቋም ቢኖራትም አሁን የተጀመረው ውዝግብ ከወሬ የዘለለ ግጭት እንደማያስነሳም ተናግረዋል።

በግብጽ አሁን ያለውን የፖለቲካ ትኩሳት ለማስቀየር እየሰሩ ያሉት ፕሬዚዳንት ሙርሲ፣ የአባይን ጉዳይ ልቡን ከነፈጋቸው የአገራቸው
ህዝብ ጋር ቃል ኪዳን ለማድረግ እንደሚጠቀሙበት ያመለከቱት አስተያየት ሰጪ፣ የአገራችን ተቃዋሚዎች እንደ ግብጽ
ተቃዋሚዎች መጫወቻ እንዳይሆኑ ይመክራሉ። “ኢህአዴግ የሚቃወሙትን ፓርቲዎች አባይን ተንተርሶ በአገር ክህደትና የአገርን
ብሔራዊ ጥቅምን በመጻረር ፈርጆ ከህዝብ ጋር ሊያጋጫቸው ተዘጋጅቷልና ከወዲሁ ዝግጅት አድርጉ” ሲሉ ይመክራሉ።

በሌላ በኩል ሙርሲ እንዳደረጉት ኢህአዴግ በወቅቱ ጉዳይ ላይ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን ሊያነጋግር
እንደሚገባ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ /አኢጋን/ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ ለጎልጉል ተናግረዋል።

አቶ ኦባንግ እንደሚሉት “አገር የህዝብ ነው። ህዝብ በተለያየ መልኩ ይወከላል። ከሚወከልበት መንገድ አንዱ የተቃዋሚ ፓርቲዎች
ናቸው። አገርን አስመልክቶ በየደረጃው ያሉ የህዝብ ወኪሎችን ማግለል ህዝብን የማግለል ያህል ነው። ይህን ማድረግ ይቅር
የማይባል ወንጀል ይሆናል”

አገር ቤት ያሉትን ብቻ ሳይሆን በውጪ አገር ያሉትንም ፓርቲና ድርጅቶች በዚህ ጉዳይ ማነጋገር ግድ መሆኑንን ያመለከቱት አቶ
ኦባንግ “ለዚህ አገራዊ ውይይት ማንኛውም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ ሊቀመጥ አይገባም” ብለዋል።

አጋጣሚው ለምንናፍቀውና ሁሉንም የአገሪቱን ህዝብ በእኩል ደረጃ ለማስተናገድ የሚያስችል ስርዓት ለመፍጠር እንደሚረዳ አቶ
ኦባንግ ጠቁመዋል። የተለየ አመለካከት በማራመዳቸው ብቻ ዜጎችን እስር ቤት በማጎር እስከ ወዲያኛው መዝለቅ እንደማይቻል
ያመለከቱት አቶ ኦባንግ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የውይይት በር በመክፈት የማያልፍ ታሪክ ሊሰሩ እንደሚገባ
መክረዋል።

“ሙስሊም ወንድሞች ፍትህ የጠማቸው ኢትዮጵያዊ እንደሆኑ የሚያረጋግጡበትን መድረክ አቶ ሃይለማርያም በማመቻቸት የማይረሳ
ታሪክ ሊሰሩ ይገባል” በማለት ጥሪ ያስተላለፉት አቶ ኦባንግ “አገር የህወሃት አይደለችም፤ አገር የኢህአዴግ አይደለችም፣ አገር
የግለሰቦች አይደለችም። አገር የሁሉም ነው። ባገር ጉዳይ ባይተዋር ሊደረጉ የሚገባቸው ዜጎች ሊኖሩ አይገባም። ኢህአዴግ ይህን
ጉዳይ ሊያስብበትና በሩን ለእርቅና ለውይይት በመክፈት ህዝብንና ራሱን ተጠቃሚ ሊያደርግ ይገባል” ብለዋል።

“ባድመ በተወረረች ጊዜ የተፈጠረው ህብረት በስተመጨረሻ በክህደት መጠናቀቁ፣ በዜጎች አጥንትና ደም ላይ የአገር ብሔራዊ
ጥቅም ተላልፎ እንዲሰጥ መደረጉና በበርካታ ቁልፍ አገራዊ ጉዳዮች ኢህአዴግ በህዝብና በአባላቱ ጭምር እምነት ያጣ ፓርቲ ነው”
በማለት ኢትዮጵያ የከፋ ችግር ቢያጋጥማት እንዴት ልትቋቋም ትችላለች የሚል ስጋት እንዳላቸው አቶ ኦባንግ አመልክተዋል።

ስርዓቱ በየደረጃው በችግር የተተበተበና በህዝብ የማይታመን፣ በአስር ሺህ የሚቆጠሩ ወገኖችን እስር ቤት ያጎረ፣ በሰብአዊ መብት
ጥሰት ከፍተኛ ቂም የተቋጠረበት፣ ፍትህና ርትዕ የተጓደለባቸው ያዘኑበት፣ በየአቅጣጫው ጠላት ያከማቸ፣ አገርን የሚፈትን አደጋ
ቢፈጠር ህዝብን አስተባብሮ አደጋውን ለመመከት የማይቻልበት ደረጃ መድረሱን የገለጹት አቶ ኦባንግ “ኢህአዴግ አጋጣሚውን
አሁንም ሊጠቀምበት ይገባል” ሲሉ በድጋሚ ጥሪ አቅርበዋል።

አቶ ኦባንግ የሰማያዊ ፓርቲ ያስተባበረውን ሰላማዊ ሰልፍ ተከትሎ ኢህአዴግ ክስ ለመመስረትና ዜጎችን ለማሰር እያደረገ ያለውን
ዝግጅት በመቃወም ሰሞኑን ለአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ግልጽ ደብዳቤ መጻፋቸው ይታወሳል። ከደብዳቤያቸው በተጨማሪ ከተለያዩ
አካላት ጋር በመነጋገር ኢህአዴግ ዜጎችን ከማሰሩ በፊት ሊደረጉ ስለሚገባቸው ጉዳዮች መግባባት ላይ መደረሱን ጨምረው
ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እያለ የአባይ ግድብን አስመልክቶ በከፍተኛ ደረጃ ውዝግብ ውስጥ የገቡት ኢትዮጵያና ግብጽ መጨረሻቸው ምን
ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ በርካታ አስተያየትና ትንተና እየቀረበበት ነው። ሁለቱ አገሮች ወደ ጦርነት አያመሩም፤ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ
ከመጠቀም ውጪ ሌላ አጀንዳ የላቸውም የሚሉ ያሉትን ያህል ግብጽ በጦር አቅሟ ያላትን የበላይነት በማመልክት ባልታሰበ ሰዓት
ጥቃት ለመፈጸም መዘጋጀቷን የሚያትቱም በርካታ ናቸው።

የግብጽ ፕሬዚዳንት ከተቃዋሚዎች ጋር ያደረጉትና ይፋ የተለቀቀው ቪዲዮ ላይ “ተቃዋሚዎችን በመርዳት ኢትዮጵያን ማተራመስ፣
ኢትዮጵያን መደብደብ ነው … ” በማለት ሲዝቱ የነበሩት ጽንፈኛ ጨምሮ የተለያዩ ባለስልጣናት የከረረ ቃላት ሲወረውሩ
ሰንብተዋል። ኢትዮጵያም በበኩሏ የግብጽን አምባሳደር በማስጠራት ማብራሪያ እንዲሰጣትና በይፋ ይቅርታ እንድትጠይቅ ማዘዟን
ይፋ አድርጋለች።

ግብጽ በችግር መተብተቧን፣ የሶማሌ መበታተንና፣ የሱዳን ሁለት አገር መሆን፣ የኤርትራ መሽመድመድ ኢትዮጵያን በቀጠናው
ጉልበት ያላት አገር አድርጓታል የሚሉ ተንታኞች በበኩላቸው ግብጽ ወደ ጦርነት እንደማታመራ ሰፊ መከራከሪያ በማቅረብ
ይናገራሉ። ከግድቡ ግንባታ ጀርባ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሚባሉ አገሮች እጅ እንዳለበትም የሚጠቁሙ ዘገባዎች በየፊናው
ተሰራጭተዋል።

“ኤርትራ ተነፈሰች” የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች፣ አሁን በተፈጠረው ሁኔታ ግብጽ ተቃዋሚዎችን ለመርዳት ከተንቀሳቀሰች ኤርትራ
ርዳታውን በማከፋፈልና ቀድሞውንም ቢሆን ኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነቷን የጠበቀች ጠንካራ አገር እንድትሆን ስለማትፈልግ
በችግሩ ዙሪያ ቤንዚን ለማርከፍከፍ አጋጣሚው እንደሚመቻችላት ያስረዳሉ። የአረብ ሊግ የክብር አባል የሆነችው ኤርትራ
ከኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ጋር በተያያዘ በበርካታ ጉዳዮች የምትታማ አገር እንደሆነች የሚታወስ ነው።

ዘግይታ “እኔ ከግብጽ የተለየ አቋም ነው ያለኝ” በማለት የገለልተኛነት ስሜት እንዳላት ይፋ በማድረግ ለግብጽ የድጋፍ ጥሪ መልስ
የሰጠችው ሱዳን እንደማትታመን የሚግለጹ ደግሞ “አቶ መለስ ደቡበን ሱዳን ላይ ሲከተሉ በነበረው አቋምና ደቡብ ሱዳን
እንድትገነጠል በመናደረጓ ሱዳን አቂማለች” ይላሉ፡፡ እንደነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች ምንም ይሁን ምን በአገር ውስጥ ያለውን ችግር
በውይይት በመፍታት ብሔራዊ አንድነትና ህብረትን ማጠናከሩ ለኢትዮጵያ እጅግ አስፈላጊዋ ነው። ስለዚህ “በር ይከፈት በአባይ
ጉዳይ አገራዊ አቋም እንያዝ” የሚለው የአቶ ኦባንግ ብቻ ጥያቄ አይደለም።

Leave a Reply