Skip to content

ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አሜሪካውያን በ2012 ምርጫ መሳተፍ ይገባቸዋል

ከፕሮፌሰር  ዓለማየሁ  ገብረማርያም

ትርጉም  ከነጻነት ለሃገሬ

ጉዳዩ የምርጫ  ብቻ አይደለም እኮ

ባለፈው ሴብቴምበር ስለ ፕሬዜዳንት ባራክ ኦባማ ድጋሚ መመረጥ ድጋፌን ገልጬ ነበር፡፡ ለታዳሚዎቼ  እንዳስነበብኩት በ2008 ምርጫ ተወዳዳሪ ባራክ ኦባማን ደግፌ እንደነበርና ከምርጫው በኋላ ግን በታየው በተለይም ኢትዮጵያንና  አፍሪካን በተመለከተ  ስለተካሄደው አስተዳደራዊ ፖሊሲ ግን በጣሙን ቅሬታ አድሮብኛል፡፡ እንደትጠቀስኩት:-

ፕሬዜዳንት ኦባማ በአፍሪካ ውስጥ ተግባራዊ አደርጋለሁ ያሉትን መልካም አስተዳደርን፤የሰብአዊ መብትን መከበር፤የዴሚክራሲን ተግባራዊነት በተመለከተ ቃላቸውን ጠብቀዋል?  በኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው የሰብአዊ መብት ገፈፋና ረገጣ ያሉትን አድርገዋል? በጭራሽ! ኢትዮ አሜሪካውያንስ ፕሬዜዳንቱ በአክራ (ጋና) የገቡትን ቃል ስላልጠበቁና የሰነዘሩትን የተስፋ ቃል ባለማክበራቸው ቅር ተሰኝተዋል? አስተዳደራቸውስ በኢትዮጵያ በጉልበት ስልጣን ለያዘው ፈላጭ ቆራጩ ዲክታተራዊ ገዢ ድጋፍ ማድረጋቸውስ ኢትዮ አሜሪካውያንን አሳዝኗል? አዎን በሚገባ እንጂ!

ፕሬዜዳንት ኦባማ ‹‹በአፍሪካ ጠንካራ የሆነ የዴሞክራቲክ ስርአት፤ት የሕግ የበላይ ነት የሚከበርበት፤ለፖለቲካዊ እንቅስቃሴ አድሎ የሌለበትና ሁሉም በእኩል የሚስተናገዱበት መድረክና ሰብአዊ መብትም በእውነተኛ መልኩ የሚተበርበት ኢኒስትቲዩሽን መፍጠር አስፈላጊ ነው›› ማለታቸውን እናስታውሳለን፡፡ ከዚህ ባሻገርም ‹‹አፍሪካ ጡንተኞች አየስፈልጓትም፤ በጉልበት ስልጣን ላይ በመንጠላጠል ማስተዳደርን ወደ መግዛት መለወጥ ባህሪያቸው የሆኑ ሰዎችም አያስፈልጓትም፤ የሚያስፈልጓት ጠንካራ የሆኑ ተቋሞች ነው፡፡›› ልማት ምንግዜም በመልካም አስተዳደር ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ማንም ሃገር መሪ ነን ብለው ስልጣን የተቀመጡት የሕዝቡን ካዝና የሚበዘብዙት ከሆነ ሕዝቡ በምንም መልኩ ሃብት ሊያፈራ ንብረት ሊኖረው አይችልም::  ታዲያ ፕሬዜዳንት ኦባማ እነዚህን አጓጊና የኢትዮጵያ የሌለችም አፍሪካዊያን ናፍቆት የሆኑትን ቃላት ሲናገሯቸው አምነውባቸው ከልባቸው ነው ወይስ ለማለት ብቻ ነው የተነፈሱት?

ባለፈው ጦማሬ ላይ እንዳሰፈርኩት፤ ከአፍ የወደቀ አፋፍ የሆኑ በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ ፕሬዜዳንት ኦባማ በኢትዮጵያና በአፍሪካ ያላከናወኗቸው ከንቱ ሆነው የቀሩ ተስፋዎችን በማንሳት ፕሬዜዳንቱ ላይ አመልካች ጣቶቻቸውን ሲዘረጉ በእርጋታ ማሰብና መገንዘብ ያለባቸው ሶስቱ ጣቶቻቸው መልሰው ወደ እነሱ ማመለከታቸውን ነው፡፡

ሃቅ መነገር አለበት፡፡ ፕሬዜዳንቱ አድርጋለሁ ብለው ያላደረጓቸውን ጉዳዮች በማስታወስ ለውንጀላ ስንቀርብ እኛም ትውልደ ኢትዮጵያ አሜሪካውያንም  ልክ እንደፐፕሬዜዳንቱ  ልናደርጋቸው ሲገባን ለኢትዮጵያ  ያላደረግናቸው በርካታ ጉዳዮች እንዳሉ ብናስብ ፕሬዜዳንቱ ካላደረጓቸው የማይተናነስ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ይሄ ነው መቀበል የሚከብደው እውነታ፡፡ የፕሬዜዳንቱ የገቡትን ቃል አለማከናወን ለኛ መስታወታችን ሆኖ እራሳችንን የምናይበትና የምንታዘብበት ይሆነናል፡፡ ልክ ፕሬዜዳንቱ እንዳሉት እኛም በተለያየ ሰበብና ቦታ አጋጣሚ በኢትዮጵያና በአፍሪካ በአጠቃላይ ስለዴሞክራሲ፤ መልካም አስተዳደር፤ሰብአዊ መብት አለመከበር ቁጭትና እሮሮ እናሰማለን፡፡ ሆኖም ግን እነዚህን ቃላቶች ወደተግባር ለመለወጥ ግን ሽብረክ ብለናል ሃሞታችን ፈሷል፡፡ ፕሬዜዳንት ኦባማ በሃገራቸው የደህንነት ጉዳይና የሃገር ጥቅም ላይ ተወጥረው ነበር፡፡ እኛም በግል ፍላጎታችንና በግል ጥቅማችን ታፍነን፤ ታስረን፤ አቅመቢስ ሆነን ነበር፡፡

እራሳችንን መጠየቅ ያለብን ከዚህ የከረሩ ጥያቄዎች አሉ፡፡ በኦባማ አስተዳደር ላይ ስለሰብአዊ መብት መከበር፤ስለመልካም አስተዳደር፤ስለዴሞክራሲ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ምን ተጽእኖ አድርገናል? አስተዳደሩ ላይ ጫና ለመፍጠርና መደመጥም እንድንችል እራሳችንን አደራጅተናል? ሕገመንግስታዊ መብታችንን መሰረት በማድረግ አስተዳደሩን ለተጠያቂነት አብቅተናል?

ፕሬዜዳንት ኦባባማ ባለፉት አራት የስልጣን ዘመናቸው ላከናወኗቸው ተግባራት ከፍተኛ አድናቆት አለኝ፡፡ በእሳቸው ቁጥጥር ከግሉ ክፍል 5 ሚሊዮን ስራዎች እንዲፈጠሩ አድርገዋል፡፡ ምንም እንኳ አንዳንዶች ‹‹ዲትሮይት ኪሳራ ያስመዝግብ›› በማለት ቢወተውቱም ኦባማ ግን፤የአውቶ ኢንዱስትሪው አካኪ ዘራፍ እንዲል አብቅተውታል፡፡ ከዚህ ቀደም አንድም አይነት የጤና ዋስትና የሌላቸው 40 ሚሊዮን አሜርካዊያን በሳቸው ‹‹የሚቻል የጤና ፖሊሲ›› መሰረት የጤና ዋስትና ባለመብቶች ሆነዋል፡፡ የሸማቾች የኤኮኖሚና የጥበቃ ቢሮ መስርተው፤አንዳንድ ራስ ወዳድና ስግብግብ ነጋዴዎች ለዓመታት ህብረተሰቡን ሲመዘብሩት የነበረውን እንዲቆም አድርገዋል፡፡ ለተመሳሳይ ስራ የሴቶች ክፍያ ከወንዶች እኩል እንዲሆን ህጉን ፈርመዋል፡፡ ፕሬዜዳንት የኢራክን ጦርነት ለፍጻሜ አብቅተዋል፡፡ በ2014ም የአፍጋኒስታንን ጦርነት ለማብቃት ቃል ገብተዋል፡፡አልቃይዳን ፈለጉን በመከተልና ሽብርተኛ ተግባሩን ለማምከን እጅጉን ፈታኝ የሆነውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ተግባራዊ አድርገዋል::  ይህ ባይሳካ ኖሮ የፕሬዜዳንቱን ስልጣንና ዳግም ምርጫ ፈተና ውስጥ ያስገባው ነበር፡፡ ባለፈው ሳምንት አጋጥሞ የነበረውን የጎርፍና የአውሎ ነፋስ አደጋ በተመለከተ የሪፓብሊካኑ የኒው ጄርሲ አስተዳዳሪ ክሪስ ክርስቲ ለአደጋው የኦባማን እንቅስቃሴ  ‹‹እጅጉን ውጤታማ›› ሲለው አስተዳደራዊ እንቅስቃሴውንም ‹‹በእጅጉ የተዋጣ››  ብሎታል፡፡

ፕሬዜዳንት ኦባማ እንደ ጦር አዘዥነታቸው፤ ግልጽ፤ ዝግጁ፤ ፈቃደኛ፤በትብብር ለመስራት ፈቃደኝነታቸውን በተግባር በማሳየት ያላቸውን ውጤታማና ብቃት ያላቸው መሆኑን አስመስክረዋል፡፡ በየሂደቱ ተቃውሞ እንደጋሬጣ ቢሆንባቸውም አልተበገሩም፡፡ እንቅፋት ሆነውባቸዋል፤አላራምድ ብለዋቸዋል፤ፖሊሲያቸውን ሳይሆን እሳቸውነታቸውን ፈትነዋቸዋል፡፡ የሪፓብሊካን ፓርቲ የበላይ ቁንጮ ባለስልጣን ሚች  ማኮነል  ‹‹አንድና ብቸኛ ማሸነፍ ያለብን ፕሬዜዳንት ኦባማን የአንድ ጊዜ ብቻ ተመራጭ ማድረግ ነው፡፡ የኔና የሁሉም በሃገሪቱ የሚገኙ ሪፓብሊካን ዋነኛና ብቸኛ የፖለቲካ ዓላማ ይሄው ነው››፡፡ ፕሬዜዳንት ኦባማ ገና ያላለቀ ስራ እንዳላቸውና ኤኮኖሚውንም የመገንባት ሂደት እንዳላበቃ ያውቃሉ፡፡ ይህንንና ሌሎችንም ጅምር ተግባራት ፍጻሜ ለማድረስ ተጨማሪ የአንድ ዘመን ምርጫ ማሸነፍ አለባቸው፡፡ ለዚህም የሁሉንም ኢትዮጵየዊና አሜሪካዊ ድምጽ ይፈልጋሉ፡፡

እንደ እውነት በአሜሪካ ስላለው የምርጫ መብት ጉዳይ ነው

ይህን አምድ የምጽፈው ለፕሬዜዳንት ኦባማ ያለኝን ድጋፍ በማሰልቸት ለመናገር ሳይሆን፤በአሜሪካ ስለአለው ሰፊ  የምርጫ መብት ለማሳሰብ ነው፡፡ ስለምርጫ መብት አስፈላጊነት በጠራራ ጸሃይ ሃገራችን ላይ  ከተከመረው አረመኔው ገዢ ታማኝ  ወታደሮች  በመቶ ከሚቆጠሩት ኢትዮጵያዊያን ወንድሞችና እህቶች በ2005 ሕይወታቸው ካለፈውና፤ድምጻቸው በመሰረቁ ምክንያት ያንን ለመቃወም ሕገ መንግስቱን አምነው ባዶ እጃቸውን ለሰላማዊ ተቃውሞ ወጥተው ለእስር ከተዳረጉት በ10 ሺዎች ከሚቆጠሩት የበለጠ የሚገነዘበው የለም፡፡ ኢትዮጵያዊያን አሜሪካውያን ለፐሬዜዳንት ኦባማ ድምጻቸውን እንዲሰጡ ሳሳስብ መብታቸውን በመጠቀምም ለሚፈቅዱት ተወዳዳሪ ድምጽ መስጠትና በመብታቸው መጠቀም እንደሚችሉም በማመን ነው፡፡

የአሜሪካ ፖለቲካ ተማሪዎች አለያም  ሕገ መንግስታዊ ህግን ያልተማሩ፤ ይህንን ከሁሉም በላይ የሆነውን መብት ለማስከበር ስለ ትግል ታሪኩ፤ ስለተከፈለው ዋጋ፤ስለጠፋው ሕይወት ብዙም ላይረዱ ይችላሉ፡፡ በ1787 የአሜሪካ ሪፓብሊክ ሲቀየስ ነጮችና ሃብት ያለቸው አሜሪካውያን ወንዶች ብቻ ነበሩ የመምረጥ መብት ያላቸው:: በ1790 የመጀመርያው የመራጮች ቁጥር ሲሰላ፤ በ13ቱም ቅኝ ግዛቶች 3.893.635 ብቻ ነበሩ:: ከነዚህም ውስጥ 807.094 ነጻ ወንዶች ብቻ ሲሆኑ ከነዚህ ውስጥም ከ10-16 በመቶው ብቻ ነበሩ ለምርጫ የሚያበቃ ሃብት የነበራቸው፡፡ 1.541.263 ነጻ  ሴቶች  ነጮች የምርጫ መብት አልነበራቸውም፡፡ 694.280 አፍሮ አሜሪካውያንም (ባሮች ነበሩና) የምርጫ መብት አልነበራቸውም፡፡791.850 ነጮችም የምርጫ መብት የሚያስፈልገውን ሃብት ስላልነበራቸው መብት አልነበራቸውም፡፡

ቀስ በቀስ ለመምረጥ የሃብት አስፈላጊነት እየቀረ ሄደ እና በ1850 በርካታ አሜሪካዊ ወንዶች አላአንዳች ማዕቀብ መምረጥ ቻሉ፡፡ አንዳንድ ግዛቶች ግን ለማያምኑዋቸውና አነስተኛ ብለው ለሚንቋቸው የመምረጥ መብትን ያግዱ ነበር፡፡ በ1855-57 ማሳቹሰትስና ኮነቲከት የመጻፍና የማንበብ ፈተና የአይሪሽ-ካቶሊክ ስደተኞችን ከምርጫው ለማገድ አስቀመጡ፡፡ በ1865 የአሜሪካ የሲቪል ጦርነት አበቃ፡፡ በዚህም ወቅት ባርነት ተሰረዘና የቀድሞዎቹ ባርያ ይባሉ የነበሩት የምርጫ መብት አገኙ፡፡ ይህም በ1870 አስራ አምስተኛው አሜንድመንት ሲጸድቅ ነበር፡፡ አሜንድመንቱም ‹‹የአሜሪካዊ ዜጋ የምርጫ መብት በዘርም ሆነ፤በቀለም አያም ባለፈው ጊዜ በነበረው የባርያ አገልጋይነት ወይም በሌላ ሰበብ በማንኛውም የአሜሪካ ግዛት ጨርሶ ሊነካ አይገባም›› ይላል፡፡

ሆኖም ግን ግዛቶቹ የቀድሞ ባርያዎቻቸው ከእነሱ ጋር በእኩል ደረጃ ቆመው መምረጥ መፈቀዱን አልወደዱትምና የዜግነት  መብታቸውን ሊገፏቸው ሞክረዋል፡፡ በ1889 አስር  የአሜሪካ ደቡባዊ ግዛቶች የምርጫ ታክስ የሚሉትን አውጥተው (አንድ ዜጋ መምረጥ ከፈለገ ታክስ መክፈል ይጠበቅበታል) አፍሮ አሜሪካውያንን ከምርጫ ማስቀረት ፈለጉ፡፡ ለአመታት አፍሮ አሜሪካውያንን በሰበብ አስባቡ ከምርጫ ለማስቀረት ብዙ ዘዴዎች ሰበቦችን  በመፍጠር ህጎችም ማውጣት ቀጠሉ፡፡ አፍሮ አሜሪካውያንን ከማንኛውም ፓርቲ አባልነት ማስወገድ፤ መክፈል የሚችሉ ብቻ እንዲመርጡ፤ሌላው ግራ የሚያጋበው የመራጮች ምዝገባ ሲሆን ይህም በተደጋጋሚ የሚደረግ ሆኖ፤ ከዚያም አንድ ሰው በሚመርጥበት አካባቢ ለረጂም ዓመታት በነዋሪነት የተመዘገበ፤ አለያም ምርጫ ምዝገባውን በማያመች ቀንና ሰአት በማድረግ አፍሮ አሜርካዊያንን ተስፋ ማስቆረጥ በጣም ይሞከሩ ነበር፡፡ ለምሳሌ በጥጥ ለቀማ ወቅት ምዝገባውን በማድረግ በስራ ላይ በሚጠመዱበት ጊዜና ሰአት እያደረጉ ማግለል፡፡ ከዚህም ባለፈ የምርጫ ካርዶችን ከሳጥኖች በማውጣት ለሚፈልጉት ተወዳዳሪ በማድረግ የአፍሮ አሜሪካውያኑን ተሳትፎ ላልፈለጉት ተመራጭ ማድረግ፤ ቆጠራ ማሳሳት፤ ሳጥኑን ደፍቶ ባዶውን ማስቀመጥና ሌሎችም የምርጫ ሌብነት ተንኮሎች ይካሄዱ ነበር:: አፍሮ አሜሪካውያኑን በተለያየ ጉዳያቸው ይደግፈናል ያሉትን ስለሚመርጡ በነዚህ ዜጎች ላይ ማስፈራራት፤ ጨለማን ተገን አድርጎ ጉዳት በማድረስ፤ እንዳይመርጡ ለመከላከል ይህንና መሳይ ተስፋ ማስቆረጫዎችን ያካሂዱ ነበር፡፡ ሴቶችም በምርጫ እንዳይጃፈሉ ዋጋ የሌላቸው ተደርገው ይታዩ ነበር፡፡

ምንም እንኳን የአፍሮ አሜሪካውያን የምርጫ ተሳትፎ መብት በሚገባ ተደንግጎ ቢጸድቅና ጉዳዩም በአሜሪካ ከፍተኛ የፍትሕ አካል በ1950 እና በ1960 የወጣው የመምረጥ መብት ዋጋ እንዲያጣ ቢደረግም በ1965 በድጋሚ የመምረጥ መብትን ያጸደቀው (በ70-75 እና በ82 የተጠናከረው) ሕግ ነው አፍሮ አሜሪካውያን የመምረጥ መብታቸውን በአግባቡና ሳይሸራረፍ፤ በማንም ሳይታገድና ሳይዛነፍ እንዲጠቀሙበትና መምረጥ እንዲችሉ ያደረጋቸው፡፡ ይህ ሕግ በምንም መልኩ ልዩነትን ሲከለክል እንዲሁም የመጻፍና የማንበብ ፈተናንም አገደ፡፡ እና ይህንንም አለአንዳች መደናቀፍ በስራ ላይ እንዲውል አስፈላጊ የሆኑ ሕጎችና እንዚህንም ሕጎች የሚያጸድቅ አካል ለመላ ሃገሪቱ መመርያ አውጪ አድርጎ በማስቀመጥ የነበረውን ችግር ሁሉ በማስወገድ ሁሉም ዜጋ የምርጫ መብቱ እንዲከበርለት ተደረገ፡፡

ያበቃለት 2012የመራጮች ቁጥጥር ወይም የምርጫ አስፈጻሚዎችን አመኔት መጠበቅ?

ባለፉት ጥቂት ዓመታት የምርጫውን ስርአት ለማጠናከር ሲባል የለውጥ ንፋስ በአንዳንድ ግዛቶች ታይተዋል፡፡ አንዳንዶች እነዚህ ህጎች ‹‹ፎቶግራፍ ያለበት መታወቂያ›› ይጠይቃሉ:: ለመመዝገብም ሆነ ለመምረጥ የዜግነት መታወቂያና ማረጋገጫ ይሆናል፡፡ አንዳንድ ግዛቶች ደግሞ የምርጫ መመዝገቢያ ቀኖችን ያያሳንሳሉ::  ለምሳሌ በምርጫው እለት ምዝገባን ያግዳሉ፡፡ ሌሎች ግዛቶች ደግሞ ቅድመ ወንጀል ሪኮርድ ያለባቸው በምርጫ መብታቸው እንዳይጠቀሙ ያዛሉ፡፡ በተለይም አናሳ ቁጥር ባላቸው ብሄሮች አካባቢ ማንነታቸው የማይታወቁ ሰዎች እነዚህን አናሳ ቁጥር ያላቸውን መራጮች ማስፈራሪያ ምልክት ይሰቅላሉ:: ማስፈራሪያና ዛቻ ያለባቸው ወረቀቶች አባዝተው ይበትናሉ፡፡

ሕጎቹ በደምሳሳው ሲነበቡና ሲታዩ መልካምና ምክንያተዊ መስለው ነው የሚታዩት፡፡ በምርጫ ቦታዎች የግለሰቡን ማንነት የሚገልጸው ባለፎቶግራፍ መታወቂያው ተቃውሞ ማስነሳቱ ተቀባይነት የለውም፡፡ በማንኛውም ሃገር አንድ ሰው ለመምረጥ ወደ ምርጫ ጣቢያ ሄዶ ድምጹን ሲሰጥ ማንነቱን የሚገልጽ መታወቂያ እንዲያሳይ ይገደዳል ይህም ተገቢ ነው፡፡ ከሚቀርበው በረካተ ምክንያት ጋር ሲታይ ግን ይህን ያህል አሳሳቢነቱ የሚያሳምን አይደለም፡፡ በቅርቡ የፔንሲልቫንያ ግዛት ስለመታወቂያ  መጠየቅና ማሳየት ደንቡን አጽድቋል፡፡ ግዛቱ ግን ስለምርጫ መጭበርበር አንዳችም ማስረጃ አልነበረውም፡፡ በጭራሽ! የኢንዲያና ግዛትም በ2005 እንዲሁ አንዳችም የምርጫ ማጭበርበር ሳይኖር ውዝግብም ሳይከሰት ደንቡ ጸደቀ፡፡ በ2008 እና በ2010 በቴክሳስ ከ13 ሚሊዮን የምርጫ ድምጾች ውስጥ በሌላ ሰው ስም አመሳስለው የመረጡ የተባሉ የስምንት ድምጾች አቤቱታ ነበር፡፡ እነዚህ ሁሉ አዳዲስ ሕጎች እንዲወጡ የተደረጉት የሪፓብሊካን ባለስልጣኖችና የክልል መንግስታት ሹሞች ነው፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ፤ ይሄ ፎቶግራፍ ያለበት መታወቂያ ጥያቄ የቀድሞው የመጻፍና ማንበብ ችሎታ፤የምርጫ ታክስ፤እና የመሳሰሉት ምርጫ ማጨናገፊያዎች ቅሪት ነው፡፡ አፍሪካን አሜሪካውያንን ጨምሮ በርካቶች ሂስፓኒኮች፤እና ሌሎችም በዚህ ህግ ተጠቂ ይሆናሉ፡፡ ዕድሜ ባለጸጎችና ወጣቶችም በአብዛኛው የዴሞክራቲክ ፓርቲ ደጋፊዎችም ለዚሁ ሰለባ ይዳረጋሉ፡፡ አሁን ወደ መጠናቀቁ የተቃረበውን የ 2012 ምርጫ ይህ ህግ ምን ያህል እንደሚጎዳው አይተወቅም፡፡ በአፍሪካ አሜሪካውያን ሴቶችና በሌሎችም በዘመናት በተካሄደ የደም ብዙ ላብ የፈሰሰበት፤እንባ የተረጨበት ትግል ውጤት የሆነው ህግ ምን ያህል ይጎዳ ይሆን?

እያንዳንዱ  የመራጭ ድምጽ  ዋጋው  ከፍተኛ  ነው

በ2000 በተካሄደው ምርጫ አልጎር ቡሽን ያሸነፈው፡- በ50.999.897 የቡሽ ደግሞ 50.456.002 (ወይም 543,895  በሆነ ልዩነት ነው)፡፡በተጣበበ እንዳሁኑ ባለ የምርጫ ሂደት ወቅት እያንዳንዱ ድምጽ የማሸነፊያ ሃይል ነው፡፡ የእያንዳንዱ መራጭ ድምጽ የተመራጩ ሃይል ነው፡፡

በሰሜን ቨርጂኒያ፤ፍሎሪዳ፤ኦሃዮና ኮሎራዶ በአሰርት ሺዎች የሚቆጠሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አሜሪካውያን የምርጫ ባለመብቶች ይገኛሉ፡፡እነዚህ ወገኖች የምርጫ ድምጻቸውን ለፕሬዜዳንት ኦባማ ቢሰጡ ለዚህ ከፍ ያለ አክብሮትና ምስጋና ይኖረኛል፡፡ በሌላ ጎኑ ደሞ ምርጫቸው ግላዊ መብታቸው ነውና የፈቀዱትንም ቢመርጡ አክብሮቴና ምስጋናዬ አይቀንስም፡፡ በኢትዮጵያ የታየው የ 99.6 በመቶ የአሸነፍኩ ባይነት አይነት ሁኔታ ያቃጠለውና ያሳዘነው ማንኛውም ኢትዮ አሜሪካዊ ድምጹን በመስጠት በዚያ ባይሆን እዚህ በነጻው አሜሪካ እልሁን ለመወጣት ድምጹን በተገቢው ተመራጭ ሳጥን ማሰማት ይኖርበታል፡፡

የተቶረገመው ጽሁፍ (translated from):

http://open.salon.com/blog/almariam/2012/11/02/ethiopian_americans_gotta_vote_in_2012

(ይህን ጦማር ለሌሎችም ያካፍሉ::)

ካሁን በፊት የቀረቡ የጸሃፊው ጦማሮችን  ለማግኘት እዚህ ይጫኑ::

http://www.ecadforum.com/Amharic/archives/category/al-mariam-amharic 

http://ethioforum.org/?cat=24

Leave a Reply