በቀጣዩ ሚያዝያ ለሚካሄደው አከባቢና የማሟያ እንዲሁም የቀበሌ ም/ቤት ምርጫ አላማቸውን ማስተዋወቅ ለሚፈልጉ ፓርቲዎች በተዘጋጀና በወያኔ ካድሬዎች ቁጥጥር በሚደረግበት መድረክ ላይ የተለያዩ አመለካከቶች ተንጸባረቁ፡፡
‹‹ለውድድሩ ካቀረብናቸው ወጣቶች 1/3ኛ ያህሉ ታስረዋል፡፡›› – አቶ ቡልቻ ደመቅሳ
‹‹ብዙ አኮኖሚስቶች፤ብዙ አናሊስቶች፤ብዙ…አሉን›› – አየለ ጫሚሶ
‹‹አባሎቻችን የኢዴአፓ አባልነታችሁ ኤክስፓየር አድርጓል ተብለዋል፡፡›› – አብዱረህማን
‹‹ህዝቡን ወተት በቧንቧ እናስመጣላችኋለን አንለውም፡፡›› – መስፍን ሽፈራው/መኢብን/
‹‹ደሃው ካለመረጣችሁ ማን ይመርጣችኋል?›› – በስብሰባው የተገኙት የወያኔ ጋዜጠኞች ጥያቄ
የየፓርቲው አመራሮች አላማቸውን ከማንጸባረቅ በተጨማሪ ምርጫውን ተከትሎ እየደረሱባቸው ያሉትን እንግልቶችና ውክቢያዎች ይፋ አድርገዋል፡፡ገንቢ በሆኑ አስተያየቶች የብዙዎችን ትኩረት እየሳቡ የመጡት የኦፌዴን ሊቀ መንበር አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ለምርጫ በእጩነት ካቀረቧቸው ወጣቶች አብዛኞቹ ያለምንም የህግ ስርአት እንደታሰሩ የገለጹ ሲሆን ‹‹ኢህአዴግ በወጣቶች ላይ ምን እንዳየ አልገባንም፡፡›› ብለዋል፡፡
ለቅንጅት የስራ አስፈጻሚ አካል ፓርቲውን ለማስረከብ እንቅስቃሴ ጀምሮ የነበረውና በጸሃፊውና በምክትሉ እቅዱ የከሸፈበት አየለ ጫሚሶ በውይይቱ ላይ ያቀረበው አንድ ሃሳብም አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ ‹‹ቅንጅቱ…›› በማለት ዙርያውን ከገረመመ በኋላ ‹‹… ብዙ ኢኮኖሚስቶች፤ ብዙ አናሊስቶች፤ ብዙ ምሁራን… አሉን፡፡›› በማለት ስለማን እየተናገሩ እንዳለ ጠቋሚ ሊባል የሚችል ንግግር አድርጓል፡፡ በአሁኑ ሰአት በአየለ ዙርያ ያሉት ጥቂት ግለሰቦች ያላቸው የትምህርት ደረጃ የአብዛኞቹ ኮሌጅ ፈር በመሆኑ አሉኝ የሚላቸው ተሳክቶ ነገሮች መስመር ቢይዙ የምሁራን ስብስብ የሆነውን የስራ አስፈጻሚ ቡድን እንደሆነ ጠቁሟል፡፡ ይሁንና ይህ ግብ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በሚፈጠሩ ችግሮች መጨረሻውን ማወቅ አልተቻለም፡፡
በሌላ በኩል በትግሉ ውስጥ የቆየውና የመኢብን ሊቀ መንበር የሆነው መስፍን ሽፈራው የምርጫ ቅስቀሳ ሊፈጸሙ የሚችሉ ቃል ኪዳኖች ብቻ ሊፈጸምባቸው ሚገቡ መሆናቸውን ለማመልከት ‹‹ለህዝቡ ወተት በቧንቧ እናስመጣላችኋለን ብለን ቃል አንገባም፡፡›› በማለት ሁኔታውን ገልጧል፡፡
የኢዴአፓው አብዱረህማን አባሎቻችን ላይ በደል እየተፈጸመ ነው በማለት ያቀረበው ዝርዝር ማን ምንን ይነካል የሚል ከትዝብት ያላለፈ ጥያቄ አጭሮ አልፏል፡፡
ከሁሉም አሳዛኝ የተባለው አጋጣሚ ደግሞ በምርጫ 97 ወቅት ለይቶላቸው ለወያኔ ሲሟገቱ የነበሩት የወያኔ ጋዜጠኞች ለተቃዋሚዎች የተለመዱትን አፍራሽ ጥያቄዎች ሲያከታትሉ መታየቱ ነበር፡፡