በቀጣዩ የሚያዝያ የክልልና የም/ቤት የማሟያ ምርጫ ለመሳተፍ እጩዎቻቸውን ያቀረቡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተወዳዳሪ እጩዎቹ ያለ ህግ ስርአት እታሰሩባቸው መሆኑን ለዜና አገልግሎቱ ገለጹ፡፡
የኦፌዴን ጽ/ቤት ሃላፊዎች በዛሬው እለት ለዜና አገልግሎቱ እንደገለጹት በግራር ጃርሶ ጉለሌ ወርዳ ውስጥ ለሚወዳደሩት የፓርቲው እጩዎች አስፈላጊ ዶክመንቶችን በመያዝ ወደ አከባቢው የሄደው የወረዳው የእጩዎች ሊቀ መንበር ያለምንም ወንጀል በቁጥጥር ስር እንዲውል የተደረገ ሲሆን የያዛቸው ለምርጫው የሚረዱ መረጃዎች በሙሉ ተዘርፈዋል ብለዋል፡፡
ከፍተኛ ወንጀል የፈጸሙ ታራሚዎች ብቻ ወደሚታሰሩበት ወደ ድሬ ማረሚያ ቤት የተወሰደው ናኔሳ ቦጋለ ለማ የተባለው የወረዳው የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ በአሁኑ ወቅት በመርማሪዎች ከፍተኛ ድብደባ እየተፈጸመበት ሲሆን ሁኔታው ሰላማዊ ትግል በኢትዮጵያ ይሰራል ወይ የሚል ጥያቄ እንደፈጠረባቸውና ጉዳዩን ለመመርመር እንደሚገደዱ ማንነታቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የጽ/ቤቱ ሃላፊዎች ምሬታቸውን ገልጸዋል፡፡
ዋስትና ሰጥተን ወደ ምርጫ ክልሎች የምንልካቸው አባላት ለተለያዩ እንግልቶች እየተዳረጉ ነው ሲሉም ጨምረው ገልጸዋል፡፡ እንደሃላፊዎቹ አገላለጽ ከአዲስ አበባ ውጭ ያሉት የምርጫ ክልሎች በሙሉ የአደጋ ቀጣና ሆነዋል ብለዋል፡፡