በቀጣዩ ሚያዝያ ለሚካሄደው የአከባቢና የማሟያ ምርጫ በእጩዎች ላይ የሚደርሰው እንግልት ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረሱ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ጸሃፊና የጽ/ቤቱ ዋና ኃላፊ የሆኑት አቶ ተስፋዬ መንገሻ ለወያኔ ካድሬዎች የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ለመጻፍ ተገደዱ፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን፤ እጩዎችንና ደጋፊዎችን የማዋከቡ ተግባር በከፍተኛ ደረጃ ከመቀጠል አልፎ በሰላማዊ መንገድ የምርጫ ቅስቀሳ የሚያከናውኑ እጩዎችን ያለምንም የህግ አግባብ ወደ እስር ሲያግዙ ከቆዩት የወያኔ ካድሬዎች በተለይ በኦሮሚያ ክልል ወረጃርሶ ወረዳ ውስጥ የተፈጸሙት የመብት ገፈፋዎች መነጋገርያ መሆን በመጀመራቸውና ተቃዋሚ ፓርቲዎቹም ተደጋጋሚ አቤቱታ በማቅረባቸው ሃላፊው የማስጠንቀቂያ ደብዳቤቀውን ለመጻፍ መገደዳቸውን የውስጥ ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡
በደብዳቤ ቁጥር አባሪ/46/030/2000 በአቶ ተስፋዬ የተጻፈው ይህ ማስጠንቀቂያ የወረዳው ጽ/ቤት ይህን አይነቱን ድርጊት መፈጸሙ አግባብነት የሌለው በመሆኑ የወረዳው አስተዳደር አስቸኳይ የእርምት እርምጃ ወስዶ የታሰሩት የፓርቲ አባላት ተፈተው ፓርቲው ህጋዊ እንቅስቃሴውን እንዲቀጥል በሚል ማሳሰቢያ የሚደመድም ነው፡፡ የወያኔ ቀኝ እጅ እንደሆኑ የሚታመነው አቶ ተስፋዬ በትናንትናው እለት የጻፉት የዚህ ማስጠንቀቂያ አንድምታ እስካሁን እያነጋገረ ይገኛል፡፡