የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ የስራ አስፈጻሚ አባላት በትናንትናው እለት ሊያካሂዱ የነበረውን ወሳኝ ጉባኤ አስተባባሪዎቹን በማሰርና ወከባ በመፈጸም የትግሉን አቅጣጫ መቀየር እንደማይቻል አንድ የአመራር አባል ለዜና አገልግሎቱ ገለጹ፡፡
በፓርቲው ፕሮግራም መሰረት የስራ አስፈጻሚ ቡድኑ እስከ ረቡዕ ባሉት ጊዜያት አስፈላጊዎቹን ቅድመ ዝግጅቶች በማጠናቀቅ ፓርቲውን ህጋዊ በማድረጉ ሂደት ላይ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ወደ ምርጫ ቦርድ የመሄድ እቅድ እንደነበር የአመራር አባሉ ጠቁመዋል፡፡ይሁንና ድርጅታዊ ስራዎች እንዳይከናወኑ ለማደናቀፍ ባለመ እንቅስቃሴ ሁለቱን የፓርቲውን አባላት ያለምንም ህጋዊ መሰረት ፖሊስ አስሮ መፍታቱ የትግሉን አቅጣጫ ለማስቀየርና ግለሰቦችንም ስጋት ውስጥ ለመክተት ቢሆንም ምንም ለውጥ እንደማያመጣና እቅዶቹ በተያዘላቸው ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቁ ገልጸዋል፡፡
አባሉ ጨምረው እንደገለጹት ወያኔ የሚፈልገው ለውጥ ማምጣት የሚችለው ሃይል ከስምና ስያሜ ጋር በተያያዘ በመወዛገብ ዋንኛውን የትግሉን ግብ ችላ እንዲል የማድረግ ተራ ጨዋታ ቢሆንም ያለፉ ስህተቶችን በማረም ህዝቡ የሚፈልገውን ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ቆርጠው መነሳታቸውን በመጠቆም አገር ወዳድ የሆነ ሁሉ በትግሉ ተሳታፊ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡