በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ የመጨረሻው ዝቅተኛ ግምት በተሰጠው የሚያዝያው ምርጫ ላይ የህብረትና የኦፌዴን አመራሮች እጩዎቻቸው እየታሰሩባቸው መሆኑንና የተለያዩ ጫናዎች እንደሚደርሱባቸው በመግለጽ ላይ ሲሆኑ በማንም አእምሮ እንደተቃዋሚ የማይቆጠሩት የአቶ ልደቱና አየለ ጫሚሶ ቡድኖች ምርጫውን አስመልክቶ እንደሚጠበቀው አዎንታዊ መግለጫዎችን በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡
ለሚያዝያው ምርጫ ገዢው ፓርቲ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተወዳዳሪዎችን ያዘጋጀ ሲሆን በተለይ አዲስ አበባ ላይ በምርጫ 97 የደረሰበትን ክስረት ባለው እድል ሁሉ ተጠቅሞ ለማካካስና ከሁለት አመት በኋላ ለሚካሄደው 4ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ላይ ተጠምዷል፡፡ በዋና ከተማዋ ላይ ብቻ የመምረጥ መብት እንዳለው የሚገመተው ከአንድ ሚሊን በላይ ዜጋ ቢሆንም በምዝገባው የመጨረሻ ቀናት ላይ ‹ተመዘገበ› የተባለው አሃዝ ከግማሽ እንደማይበልጥ የመንግስት የመገናኛ ብዙሃን ሳይቀሩ ይፋ አድርገውታል፡፡ በዚህ የ520 ሺህ አሃዝ ላይ ህዝቡ ከፍተኛ ጥርጣሬ እንዳለው ያነጋገርናቸው የከተማዋ ነዋሪዎች አልሸሸጉም፡፡
የኦሮሞ ፌዴራላዊ ዴሞክራቲክ ንቅናቄ (ኦፌዴን) እና የህብረት እጩዎች ወደሚወዳደሩባቸው ክልሎች በመሄድ ህዝባቸውን ለማነጋገር ሲሞክሩ ፍጹም ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ወደ እስር ቤቶች ተግዘዋል፡፡
በሰሜን ሸዋ ዞን የሰላሌ የወሰን ከተማ በሆነችው በጎሃጽዮን ህዝቡን በማነጋገር ላይ የነበሩ 27 የኦፌዴን ተወካዮች በሙሉ ወደ እስር ቤት መነዳታቸው ለዚህ ተጠቃሽ መሆኑን አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ገልጸዋል፡፡ በዚህ የተነሳም ፓርቲዎች የእጩዎቻቸውን ማንነት ምርጫው እስኪቀርብ ላለመግለጽ እንደሚገደዱ በማስታወቅ ላይ ይገኛሉ፡፡