Skip to content

በደቡብ ኢትዮጵያ የቅንጅት ተወካይ በደህንነቶች ታፍነው ከተወሰዱ በኋላ በህዝብ ግፊት ተለቀዋል

በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የጎፋ ዞን ሳውላ ከተማ የቅንጅት ተወካይ የሆኑት አቶ እንድርያስ ኤሮ በዛሬው እለት የከተማዋ የፌዴራል የደህንነት ቢሮ ሃላፊ በሆኑት በአቶ ሚካኤል ዘሪሁንና የወያኔ/ኢህአዴግ ተወካይ በሆኑት በአቶ ታደለ ያዕቆብ ከቢሯቸው ታፍነው ከተወሰዱ በኋላ በህዝብ ግፊት መለቀቃቸውን የደቡብ ኢትዮጵያ ሪፖርተራችን ዘገበ፡፡

በአከባቢው ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍ ያላቸው የቅንጅቱ ተወካይ ከቢሯቸው ታፍነው ወደ ከተማዋ ማዘጋጃ ቤት ሲወሰዱ ህዝቡ ማዘጋጃ ቤቱን በመክበብ በፈጠረው ጫና አባሉ ሊለቀቁ ችለዋል፡፡

አቶ እንድርያስ በጽ/ቤቱ ውስጥ ለሰአታት የቆየ ምርመራ የተደረገባቸው ሲሆን ህገ ወጥ ስብሰባ እንዲካሄድ አስተባብረዋል፤ ህዝቡ ለቅንጅት ድጋፉን እንዲሰጥ ቀስቅሰዋል፤ ህጋዊ ላልሆነ አመራር ድጋፍ አሰባስበዋል፤ እንዲሁም ይህንኑ ሁኔታ በተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ ሜዲያዎች አስተዋውቀዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸው እንደነበር ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው ምንጮች ገልጸዋል፡፡

የቅንጅቱ ተወካይ ጽ/ቤቱ እንዲዘጋ የተሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ አስመልክቶ ትእዛዙ በጽሁፍ ይድረሰኝና ከህዝባችን ጋር እመክርበታለሁ ያሉ ሲሆን በአስቸኳይ ባይለቀቁ ኖሮ ማዘጋጃ ቤቱን ከቦ የነበረው ህዝብ ወዳልታሰበ የሃይል እርምጃ ሊገባ ይችላል ተብሎ ተሰግቶ እንደነበር ዘገባው ያመለክታል፡፡

Leave a Reply