Skip to content

የኢትዮጵያ የነዳጅ ዘይት ፍለጋ ስምምነት

ኢትዮጵያ ከአንድ ነዳጅ አውጭ ድርጅት ጋር በኦጋዴን አካባቢ የተፈጥሮ ጋዝ ማውጣት የሚያስችል የአንድ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር ስምምነት ተፈራረመች ። አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የማዕድንና የኤነርጂ ሚኒስቴር ባለስልጣን ለሮይተርስ ዜና ወኪል እንደተናገሩት ፔትሮናስ በተባለው የማሌዥያ ኩባንያና በኢትዮጵያ መካከል የተፈረመው ስምምነት ኦጋዴን ውስጥ በካሉብና በሂላል የሚገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ ማልማትና ለገበያ ማቅረብን ይመለከታል ። በሮይተርስ ዘገባ እንደተጠቀሰው የኢትዮጵያ የማዕድንና ኤነርጂ ሚኒስትር አቶ አለማየሁ ተገኑ ጨረታውን ካሸነፈው ከፔትሮናስ ኩባንያ ጋር ባለፈው ወር ማሌዥያ ዋና ከተማ ክዋላላምፑር ውስጥ ተፈራርመዋል ። በስምምነቱ መሰረት ፔትሮናስ የተፈጥሮ ጋዙን በአቅራቢያው ወደ ሚገኝ ወደብ ማስተላለፊያ ቧንባ ይዘረጋል ተብሎ ይጠበቃል ። ሮይተርስ የጠቀሳቸው ተንታኞች እንዳሉት በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ስለሆነች የተፈጥሮ ጋዙ ምናልባትም ፑንትላንድ ወደ ሚገኘው የቦሳሶ ወደብ ወይም ደግሞ ወደ ሳማሌላንድዋ በርበራ ወደብ ነው ሊተላለፍ የሚችለው ። በኦጋዴን ክልል የሚንቀሳቀሰው የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃ አውጭ ግንባር ኦብነግ የውጭ ነዳጅ አውጭ ኩባንያዎች ወደ አካባቢው እንዳይመጡ ከዚህ ቀደም ማስጠንቀቁ ይታወሳል ።

Source: DW

Leave a Reply