Problems of raising funds in DC for the needy in Ethiopia

The following article by Reta Asrat discusses problems surrounding fund raising efforts by Ethiopians in the Washington DC area for the needy back home.

[pdf]

ለረሃብተኞችና ችግረኞች እርዳታ በማሰባሰብ ጉዳይ ላይ በዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ በተደጋጋሚ የተከሰተው ችግር

ከረታ አሥራት

ይህችን አጭር ጽሁፍ ለመጻፍ ያስገደደኝ በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ አካባቢ በየሳምንቱ ቅዳሜ ማታ የሚተላለፈው “መብት” የሚባለው ሬዲዮ እ.አ.አ. ዲሰምበር 20/ 2008 ያስተላለፈው የውይይት ፕሮግራም ነው። የውይይት ፕሮግራሙ ያተኮረው ኢትዮጵያ ውስጥ በቅርቡ ለተከሰተው ረሃብ እርዳታ ለማሰባሰብ ሃዋርድ ዩኒቨርስቱ ውስጥ የተካሄደው ስብሰባ ላይ ቁጥራቸው 40 የሚሆን ተሳታፊዎች ብቻ መገኘታቸው ምክንያቱ ምንድን ነው? የሚል ነበር። በርካታ የሬዲዮው አድማጮች ስልክ በመደወል፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያየ ጊዜ ለተከሰተው ረሃብ፣ድርቅና ሌሎች ችግሮች በተደጋጋሚ ገንዘብ የረዱ መሆናቸውንና በተለይም ከ 5 ዓመት ገዳማ በፊት “ደራሽ” በሚል ስም በርካታ ገንዘብ ከተሰበሰበ በኋላ ለረሃብተኛው መሰጠት ሲገባው ለሌሎች ተከፋፈለ መባሉና ከዚሁ ገንዘብ ውስጥ $40,000 ዶላር ሳይላክ እዚሁ አሜሪካ ውስጥ በግለሰብ የባንክ ሂሳብ ውስጥ መቅረቱ ያስቆጣቸው መሆኑንን አበክረው ገልጸዋል። በ”ደራሽ” ውስጥ ቁልፍ ሚና የተጫወቱና ኢትዮጵያ ድረስ በመሄድ የተዋጣው ገንዘብ ላይ ምዝበራና ሌብነት የተፈጸመበት መሆኑን ያጋለጡ ኃላፊነት የሚሰማቸው ኢትዮጵያዊት ያቀረቡትን መግለጫ በመጥቀስ አሁንም ጥንቃቄ ካልተደረገና ተጠያቂነት ያለው ግልጽ አሰራር ተግባራዊ ካልሆነ በስተቀር የሚሰበሰበው ገንዘብ የጥቂት ግለሰቦችን ኪስ ከማዳበር በስተቀር ለታቀደለት ዓላማ ሊውል አይችልም ብለዋል። የሬዲዮው አድማጮች ከዚህም በተጨማሪ ይህ ሁኔታ ካልተስተካከለ ለወደፊቱ ገንዘብ ለአገራቸው የሚያዋጡ ሰዎችን ተስፋ የሚያስቆርጥና ለሚቀርቡ የእርዳታ ጥያቄዎች ጆሮ ዳባ ልበስ እንዲሉ የሚያስገድዳቸው መሆኑን በመዘርዘር ጠንካራ ሃሳቦችን ሰንዝረዋል።

ይህንን ከሕዝብ የቀረበ ጥያቄን በአግባቡ በማስተናገድ መፍትሄ ከማፈላለግ ፋንታ ከካሊፎርኒያ ወደ ዲሲ ስልክ በመደወል ድምጻቸውን የሚያሰሙት አቶ መሸሻ ብሩ ኃላፊነት በጎደለው ሁኔታ ገንዘቡ ተበላም አልተበላም እናንተ አዋጡ፣ ጥያቄ ማንሳት ላለመርዳት ሰበብ ነው በማለት አድማጮችን ሲወርፉና ሲያወግዙ ተሰምተዋል። የካሊፎርኒያው አቶ መሸሻ ብሩ ለጠየቀ ሁሉ ዘም ብላችሁ ገንዘባችሁን ስጡ ማለታቸው ብዙም አያስገርምም። ይህም ስማቸው መሸሻ “ብሩ” ስለሆነ የብር ነገር አይሆንላቸውም ይሆን? ወይስ ካሊፎርኒያ ውስጥ ከኢንሹራንስ ጋር በተያያዘ ብዙ የገንዘብ ማምታታት ፈጽመዋል የሚባለውን ሃሜት ያልሰማን መስሏቸው ይሆን? እሳቸው የዘወትር የኢትዮጵያውያን እንቅስቃሴ በሌለበት በርቀት ካሊፎርኒያ ተቀምጠው ለጋሹንና ተቆርቋሪውን የዲሲን ነዋሪ ንፉግ ለማስመሰል ያደረጉት ሙከራ በጣም አሳዛኝ ነው። ሌላው ከዲሲ አካባቢ የሬዲዮኑን ፕሮግራም አብረው የሚያካሂዱት ዶክተር ክንፈ ሚካኤል አሥራት በ”ደራሽ” ለደረሰው ስርቆሽ መረጃ ካለ መጠየቅ ይቻላል የሚል፣ ቢያንስ ከአቶ መሸሻ ብሩ የተሻለ ተጠያቂነትን የሚያመላክት ሃሳብ አቅርበዋል።

ሆኖም ዶክተር ክንፈ “ቄሶችን እንመን” በማለት የተናገሩት በጣም አስደንግጦናል።

ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት ወያኔ የባዕዳ አዛዦቹን ለማስደሰት ሶማሊያን ለመውረር በሚዘጋጅበት ጊዜ ኢሉባቦርና ከፋ አካባቢዎች ውስጥ በተቀነባበረ ሁኔታ ባሰማራቸው ነፍሰ ገዳዮች ቪዲዮ እየቀረጸ በርካታ ቁጥር ያላቸውን የክርስትና እምነት ተከታዮች እንዲጨፈጨፉና ብዙ ቤተክርስቲያኖችና መኖሪያ ቤቶች መጋየታቸውና መውደማቸው ይታወሳል። ወያኔ ይህንን ያደረገው “ከፋፍለህ ግዛ” በሚለው ከደደቢት በረሃ ይዞት በመጣው መርሆው ክርስቲያኖችን “አክራሪ ሙስሊሞች መጡባችሁ፣ ሊያጠፏችሁ ነው፣ ሶማሊያም የአክራሪዎች መናኽሪያ ሆናለች” በማለት ድጋፍ ለማግኘት ያደረገው እጅግ ዘግናኝ ድርጊት እንደሆነ የአደባባይ ሚስጢር ነው። በዚህም ጥቂቶችን ለማጭበርበርና ለማወናበድ እንደቻለና እንዲሁም አመቺ ጊዜ ይጠብቁ ለነበሩ ከሃዲዎችዎችም ምክንያት እንደሆነላቸው አይዘነጋም።

እነዚህን ወገኖቻችንን መልሶ ለማቋቋምና ቤተክርስቲያኖቹን መልሶ ለመገንባት በሚል ምክንያት በአቡነ ገብርኤል ስብሳቢነትና በዲሲ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ቄሶች ግምባር ቀደምትነት ብዙ ገንዘብ ከተዋጣ በኋላ፣ የተሰበሰበው ገንዘብ ምን ያህል እንደሆነና ምንስ እንደተሰራበት ይፋ ሳይደረግ ተድበስብሶ ቀርቷል። እንደውም በቅርቡ በዋሽንግተን ከተማ የሚተላለፈው የሞአንበሳ ሬዲዮ “ነፍስ አድን ወይንስ ነፍሰ ገዳይ” በሚል ያስተላለፈውን ሐተታ እናስታውሳለን። በህገ ወጥ ሁኔታ በወያኔ ታጣቂዎች አማካይነት መፈንቅለ መንበር ያደረጉት ገብረመድሕን (አባ ጵውሎስ፣አባ ዲያብሎስ ወይም ታጋይ ጳውሎስ) ገንዘብ ስለሚያመልኩና ቤተክርስቱያኒቱንም በአምባገነን የካድሬ አሰራራቸው ለከፍተኛ ችግር ስለዳረጉ ይንንን አውግዣለሁ ብለው አሜሪካን አገር በስደት ይኖሩ የነበሩት አቡነ ገብርኤል፣ ይህንን የተሰበሰበውን ገንዘብ ከአባ ገብረመድህን ጋር ለመታረቂያ በእጅ መንሻነት (ጉቦ) ያድርጉት ወይንስ በስማቸው ይጻፍላቸዋል እንደሚባሉት ቼኮች ለግል ጥቅማቸው ያድርጉት ያቀረቡት ሪፖርት የለም። አሁንም በንጽሃን ደም ስም የሰሰበሰበ ገንዘብ ስለሆነ እርስዎም አባ ገብረመድህን በግፍ እንዳስገድሏቸው እንደ አባ ፈቃደ ስላሴ የማቾች መንፈስ ሳይፋረድዎት እውነቱን ለህዝብ ይፋ ማድረግ አሁንም አልመሸብዎትምና መልስ ከርስዎ ሕዝብ ይጠብቃል። በተለይም የዲስ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ቄሶች ወያኔ ወገኖቻችንን በአሰቃቂ ሁኔታ ያስገደለበትና ቤተክርስቲያናትና መኖሪያ ቤቶችን በእሳት ያስጋየበትን ቪዲዮ ለህዝብ ዕይታ በማቅረብ ገንዘብ ከለመኑበት በኋላ የተሰበሰበው ገንዘብ ምን ያህል እንደሆነና ለማንስ እንደተሰጥ ምንስ እንደተሰራበት ሲሆን እንደመለመኛው በቪዲዮ የተደገፈ ሪፖርትና ገለጻ መስጠት ሲገባቸው የውሃ ሽታ ሆነው ጠፍተዋል። ይህም እነዚሁ ቄሶችና ግብር አበሮቻቸው የእድር ገንዘብ ለመንጠቅ ካደረጉት አሳፋሪ ቅሌት ጋር ተዳምሮ ሲታይና 12 ዓመት በላይ ሊጠናቀቅላቸው ያልቻለው የቤተክርስቲያን እድሳት አዝጋሚ ስራቸው የእነዚህኑ ሰዎች ማንነት በግልጽ የሚያሳይ ስለሆነ ተጨማሪ ዝርዝር የሚያስፈልገው አይሆንም።

ዶክተር ክንፈ ቄሶችን እመኑ ሲሉን በተለይ ከአቡነ ገብርኤል ጋር ባላቸው ቀረቤታ ይህንን ከላይ የተዘረዘረውን አላውቅም ሊሉን ነው? ወይንስ ሌላ ምክንያት አላቸው? በሐሰት የፖለቲካ ጥገኝነት ጠይቀውና ስደተኛ ነኝ ብለው በማወናበድ ለብዙ ዓመታት አሜሪካን አገር ውስጥ ከኖሩና ብዙ ገንዘብ ካከማቹ በኋላ የማዕረግና የሹመት ጥማታቸውን ለማርካት እጃቸውን ለአባ ገብረመድህን ከጉቦ ጋር የሰጡትን አባ መላኩ ጌታነህን አላውቃቸውም ነው የሚሉን ዶክተር ክንፈ? ሌሎችም እራሳቸው ተዋርደውና ቀለው፤ በከፍተና መስዋዕትነት የተገነባችውን ጥንታዊቷንና ሐቀኛይቷን የኢትይጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ስም ያስጎድፉ ቄሶችን ስም መዘርዝር ይቻላል። ነገር ግን፣ እነዚህ መንጋውን የሚበጠብጡ አበያዎች ከአስከፊ ስራቸው እንዲመለሱ ጊዜ ለመስጠት እዚህ ላይ ስማቸውን መዘርዘር አስፈጊ አልመሰለንም።

ዋናው የዚህ አጭር ጽሁፍ ጭብጥ ጥቂት ግለሰቦች(ምዕመናን)፣አንዳንድ ቄሶችም ሆነ ጳጳሳት የሕዝብን ገንዘብ የዘረፉና አለአግባብ የተጠቀሙ፣ በቤተ ክርስቲያንና በአጠቃላይ በሕዝብ ላይ በደል ያደረሱ ሳላሉ የዶክተር ክንፈ “ካህናትን እንመን” አይሰራም ነው የምንለው። ይህም ማለት ሁሉም እርዳታ የሚያሰባስቡ በሙሉ በዚህ አሳፋሪ ቅሌት ውስጥ ተዘፍቀዋል ለማለት ሳይሆን እዚህ በምንኖርበት አገር ውስጥ እንደሚሰራበት በህዝብ የተመረጠ፣ህዝብ የሚቆጣጠረውና ለህዝብ ተጠሪነትና ተጠያቂነት ያለው ኮሚቴ በማቋቋም ወገኖቻችንን ለመታደግ እንችላለን። ማንም ተንስቶ በሬዲዮ ስለቀባጠረ ወይንም ክህነት ስላለው ብቻ አመኔታ ሊጣልበት ይቻላል ማለት ከፍተኛ ስህህተ ስለሆነ ለወደፊቱ እርምት ሊደረግበት የሚገባው አሳሳቢ ጉዳይ ነው። ህዝብን ለግል ጥቅም፣ሥልጣንና ማዕረግ አሳልፎ መስጠት ደግሞ ሁሉም የሕብተሰብ ክፍሎች የፈጸሙት ሰለሆነ ማመን አሰራርን (system) እንጅ ሰዎችን መሆን የለበትም። በመጨረሻም እስከዛሬ የተበላነው ይበቃናልና በዚህ በአዲሱ እስራ ምዕት በተለያየ ምክንያት ገንዘብ ለመመንተፍ የተዘጋጃችሁ ልማደኛ ጭልፊቶች ስለተነቃናችሁ አርፋችሁ ብትቀመጡ ይሻላችኋል።