ይህ ጽሁፍ በቅርቡ ቪዥን ኢትዮጵያ ከኢሳት ቴሌቪዥን ጋር በመተባበር ባዘጋጀው ጉባኤ ላይ ያቀረብኩት ነው።
የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አሁን በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት በሰላም ወይም በሃይል ከስልጣን ለማውረድ ቢችሉም እንኳን፤ ባለፉት 24 አመታት የተዘረጋውን ዘውጋዊ ክፍፍል ለማብረድና ብሄራዊ አንድነትን መልሶ ለመገንባት የሚያስችል ራእይና ፖለቲካዊ መፍትሄ ያስፈልጋቸዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት ከሚስተዋሉት ችግሮች ሁሉ ተቀዳሚና እጅግ አስቸጋሪ የሆነው ዘውጋዊ ፖለቲካ በመሆኑ ያለውን መንግስት ለመጣልና አዲስ ስርዓት ለመመስርት ስለ ዘውግና ዘውጋዊ ፖለቲካ ትክክለኛ ግንዛቤ ማግኘትን ይጠይቃል። ወያኔ ከተሸነፈ የዘውግ ፖለቲካ በራሱ ይጠፋል ብሎ ማሰብ ከንቱ ምኞት ነው። ይህ ጽሁፍም “የዘውግ ፖለቲካ ዋና ዓላማ ምንድር ነው? ከብሔራዊ አንድነት ጋር በምን ሁኔታ ሊጣጣም ይችላል?” የሚሉትን ጥያቄዎች በአጭሩ ይዳስሳል።
የዘውግ ፖለቲካ ንድፈ ሃሳብ
የዘውግ ፖለቲካ በአካዴሚያ ዓለም ውስጥ ብዙ ጥናቶችንና ብዙ ውዝግቦችን የጋበዘ ጉዳይ ነው። ውዝግቦቹ በሶስት መስመሮች ማጠቃለል ይቻላል።
የመጀመሪያ የሃሳብ መስመር፤ ዘውግ ለሰው ልጅ ማንነት ተቀዳሚና መሰረታዊ መግለጫ ነው የሚል ነው(primordialism)። የዘውግ ቀዳሚነት የሚገለጠው በደም ትስስር፤ በቋንቋ፤ በባሕል፤ ወዘተ አንድነትና ይህ አንድነት በሚፈጥራቸው ኃይለኛ ስሜቶች ነው። ይህ በስሜት የተገንባ ማንነት እራሱን ለመከላከልና ለማሳደግ ፖለቲካዊ ሉዓላዊነት ይመኛል። በመሆኑም በአንድ አካባቢ የዘውግ ግጭት ከተነሳ ያለው ብቸኛና ዘላቂ መፍትሄ የዘውጉ አባላት በሚመርጡት ብሄራዊ መንግስት እንዲተዳደሩ መፍቀድ ነው፤ ምርጫቸው ከአለው መንግስት መገንጠል ቢሆንም እንኳን። ይህ አመለካክት መገንጠልን የዘውግ የማይነካ መብት መሆኑን ይቀበላል ማለት ነው።
ለዚህ ተቃራኒ ሆኖ የሚነሳው አመለካከት የፖለቲካ ወሰኖችን የራስን እድል በራስ መወስን መርሕ መሰረት መቀያይር ብዙ ጊዜ ዴሞክርሲ ወይ ሰላም አያመጣም የሚለው ነው። የህንድና የፓኪስታን፣ የቀድሞ ዩጎዝላቪያ፣ የኢትዮጵያና ኤርትሪያ የቅርብ ታሪክ እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።የዚህ አመልካከት ዋና ሃሳብ የዘውግ ፖለቲካ መንስኤ የዘውጋዊ ማንነት ተቀዳሚ መሆን ሳይሆን የመንግሥትን ስልጣን ለመቆጣጠር የሚደረገው ውድድር ነው። ዘውጋዊ ፖለቲካለ ማለት ለመንግሥት ሥልጣን ሽሚያ ሲፈጠር በዘውግ ኃይለኛ ስሜት በመጠቀም ሕዝብን ለማንቀሳቀስ ልሂቃን የሚጠቀሙበት መሳሪያ ማለት ነው (instrumentalism)። በዚህ ንድፈ-ሃሳብ ዘውጋዊ ግጭቶች የሚነሱት በማንነት ጥያቄ ሳይሆን በሥልንጣን ሽሚያ ዙሪያ በመሆኑ ሥልጣንን የሚያከፋፈል (በተለይም ከማእከላዊ ወደ ክልል መንግሥት የሚቀንስ) ፖለቲካዊ ሥርዓት ለግጭቶቹ ሰላማዊ መፍትሄ ያመጣል።
የዘውግን መሳሪያነት የሚያሰምር አመለካከት ዋና ድክመት የዘውግ ፖለቲካ የልሂቃን ማታለያ መሳሪያ ተደርጎ መቅረቡ ነው። ሕዝቦች በዚህ መሳሪያ ለምን አንደሚታለሉና ደም የሚያፋሥስ ኃይለኛ ስሜት እንደሚኖራቸው ግልጽ አይደለም። ስሜቱ ሊቀሰቀስ የሚችለው የልሂቃን ፖለቲካዊ ዓላማ ከሕዝብ ጥልቅ ፍላጎት ጋር ሲቀናጅ ነው። በመሆኑም ዘውጋዊ አንቅስቃሴ በጥንታዊ ማንነት ላይ የተመሰረት ሳይሆን ህዝብ ሊማርክና ሊያንቀሳቅስ የሚችል አዲስ ማንነት የሚፈጥር ነው(constructivism)። ዘውጋዊ ፖለቲካን ለሕዝብ ማራኪና ስሜት ቅስቃሽ የሚያደርገው፣ የሚሰጠው ተስፋ ካለው ጭቆናና በደል መላቀቅ አልፎ የላቀ (ideal) ሕብረተሰብ ለመመስረት የሚያስችል ርዮተአለም ይዣለሁ ማለቱ ነው።
ከላይ የተዘረዘሩት ሃሳቦች አንድ አመለካካት ሥር ሲጠቃለሉ የሚሰጡት ውጤት ግልጽ ነው። የዘውጋዊ እንቅስቃሴ ባሕሪይ የፖለቲካ የሥልጣን ትግል በከፍተኛ ደረጃ ስኬታማ ለማደረግ አዲስና ለትግሉ ተስማሚ የሆነውን ባህላዊ ማንነትን የሚቅርጽና የሚያሰራጭ እንቅስቃሴ ነው። ይህ ፍች የባህላዊ ማንነትን ጠንካራ ሚናና የፖልቲካ ጥቅምን ወሳኝ ሚና አጣምሮ የሚያቅርብ ነው።
ይህ አመለካከት የሚያረጋግጠው ዘውጋዊ እንቅስቃሴ የተፈጸመውን በደል በማስቆም ብቻ ኢንደማይወሰን ነው። የዘውግ ጥያቄ ለመብት እኩልነትና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ብቻ የሚታገል ቢሆን ኖሮ ሊቤራል ዴሞክራሲ መፍትሄ በሆነ ነበር።፡ የዘውግ ጥያቄ ለፖለቲካ ሥልጣንና ለራስ ገዝ ዓላማ የሚታገል በመሆኑ የሊበራል መርሆዎች፤ እንድ የብዙሓን በላይነት፣ የግለሰብ መብት ሉዓላዊነት፤ ወሳኝነት የላቸውም። ይልቁኑ የቡድን ባሕሪያት፣ እንደ ቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ ባህል፣ ተቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛሉ። እንቅስቃሴው ስለ አንድ የተበደለ ሕብረተስብ ነጻ መውጣት ስለሆነ ነጻነቱ እስከሚረጋግጥ ድርስ የቡድን መብት ቅድሚያ ያገኛል።
የዘውግን እንቅስቃሴ ኃይል ለመረዳት ከአሉታ ገጽታዎቹ አልፈን ወደ የእድሳት ሚናው መሄድ አለብን። የአንድ ዘውግ የበላይነት የሚዘረጋው የአድሎ ሥርዓት የተጨቆኑ ዜጎች ስለ ራሳቸው ያላቸውን አመለካከት የሚያዛባ ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊ ክብራቸውንም ያሳጣቸዋል። ይህ የክብር ጉዳይ የዘውግ ትግልን ከመደብ ትግል ለየት ያደርገዋል። የመደብ ጥያቄ የሚያነሳው የፍትህና የብሔራዊ ሀብት ክፍፍል ጥያቄ ነው፤ የዘውግ ጭቆና ግን ከዚህም አልፎ የአነድን አካባቢ ዜጎች የበታች የሚያደርግና የዜጎችን ሰብዓዊ ክብር የሚነካ ነው። በዘውጋዊ ፖለቲካ ዓይን የአንድ ማህበረሰብ ክብር የሚታደስው የተዋረደው ማህበርሰብ የራሱን መንግሥት ሲመሰርትና እራሱን በራሱ ሲያስተዳርር ነው። አንድ መንግሥት ዴሞክራሲይዊ ቢሆንም የራስ ገዝ መብት ካልተቀበለ ውርደቱን ሊያጠፋው ወይም ሊፍቅለት አይችልም።
የማንነት ፖለቲካ ሕዝቦች በዘውጋቸው ላይ ተፈጽሞብናል ብለው ለሚያስቡት በደል/ችግር ከነሱ የተለየ አንድ ኃላፊ ገዢ መደብ ለይቶ በማስቀመጥ ሃይለኛ ግፊት ይፈጥራል። ለተፈጠሩት ችግሮች ሁሉ በቀጥታ አንድ ተጠያቂ መሰየም በዘውግ አባላት ዘንድ ንዴትና ቁጭትን ይቀሰቅሳል። በመሆኑም የላቀ ማህበረስብን ሃሳብ በመንደፍ ቀሚቀሰቀስው ስሜት ሌላ ንዴትን በመጨማር ዘውጋዊ ፖለቲካ የሚገነፍል ስሜት ደርጃ ላይ በቀላሉ ይደርሳል። ይህ ደረጃ ነው ብዙን ጊዜ ወደ ደም መፋሰስ የሚወስድው።
ዘውጋዊ ፌደራሊዝም በኢትዮጵያ
ከላይ በአጭሩ የተተነተው የዘውግ ፖለቲካ ምንነት ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው የዘውግ ሥርዐት ጋር ይጣጣማል ወይ? ጥያቄው ወደ ኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ያመለክታል። ኢትዮጵያ የዘውግ ሥርዐት ባለቤት እስከሆነች ድረስ የኦሮሞ ሕዝብ ለምን መንግሥት ላይ አመጸ? አመጹ የተነሳው መንግሥት እንደሚለው ንቅናቄውን የሚመሩት ተገንጣዮች ስለሆኑ ነው ወይንስ ዘውጋዊ ፌደራሊዝም እራሱ የተዛባ በመሆኑ ነው?
መልሱ የሚያጠራጥር አይመስለኝም። ሥርዓቱ የተዛባው ከአመሰራረቱ ነው። ሥርዓቱ የተነደፈው ሰፊ ነጻ ውይይት ተደረጎ በሕዝብ ነጻ ምርጫ የጸደቀ ሳይሆን በጥቂት አሸናፊ ነን በሚሉ የፖለቲካ ቡድኖች ተወጥኖ በግድ ሕዝብ እንዲቀበለው የተደረገ ነው። ሥርዓቱ በግድ ሕዝብ እንዲቀበለው ከመደረጉም በላይ የተቀረጸው ፌደራሊዝም ዘውጋዊ ማንነትን የሚያጠናክርና የሕዝብን አንድነት የሚያፋልስ ነው። ሕንድና ሌሎች አገሮች የዘውግ መብት የአገር አንድነትንና ሉዓላዊነትን እንዳያፈርስ ጥንቃቄ ወስደዋል። የኢትዮጵያ ሥርዓት ግን ዘውግንና ብሔራዊ አንድነትን ያቃርናል።
ለዚህም ዋና ምክንያቱ ግልጽ ነው። ወያኔ የዘውጋዊ ፌደራሊዝም ለመመስረት የፈለገው በሁለት ምክንያቶች ነው።
1) በማያዳግም ሁኔታ የአማርን የበላይንት ከሥሩ ገንጥሎ ማጥፋት።
2) በሚገኘው ውጤ ላይ የወያኔን የበላይንነት በሁሉ ዘርፍ መገንባት።
በመሆንም ሥርዓቱ የተቋቋመው ለዘውጋዊ መብቶች ሥፍራ ለመስጠት ሳይሆን አንድ አናሳ ዘውግ እውክላለሁ ለሚለው የወያነ ቡድን በላይነት ዘላቂ መሰረት ለመስጠት ነው።
ይህ በአጀማመሩ፤ በአሰራሩ፤ በዓላማው የተበላሸ ሥርዓት አመጽ ጋባዥ መሆኑ የሚገርም አይደለም። አንዳንድ የውጭ አገር ተመራማሪዎች የኢትዮጵያን ዘውጋዊ ፌደራሊዝም ሥርነቀልነት ሲያደንቁ የሚረሱት ሥርዓቱ የተዘረጋው የዘውጎችን እኩልነት ለመደገፍ ሳይሆን የአንድን ዘዉግ ተወካይ ነኝ የሚል ቡድን የበላይነት ለማርጋገጥ ነው።
እርግጥ ነው፤ ብዙ ተመራማሪዎች በንድፈሃሳቡና በተግባር መካከል ብዙ ልዩነት እንዳለ ይሳያሉ። ይህ ግን ትክክል አቀራርብ አይደልም፤ ምክንያቱም ልዩነቱ ስህተት ሳይሆን ታቅዶ የተሰራ ነው። በወያኔ ዓይን በተግባርና በንደፈሃሳብ መካከል ልዩንት የለም። እንደሚፈለገው ሥርዓቱ እየሰራ ነው። ከውዥንብሩ ለማምለጥ ከልይ የተተነተነው የዘውጋዊ ፖለቲካ እውነተኛ ገጽታ መመልከት ይበቃል። በራስ ቋንቋ መናገር፤ በራስ ባህል ተክብሮ መኖር ወዘተ ላይ ብቻ ዘውጋዊ ፖለቲካ አይወሰንም። ከላይ እንደተመለከትንው፣ የዘውግ ፖለቲካ የራስ ገዝ የሥልጣን ጥያቄም የሚያካትት ነው። ፖለቲካዊ ገጽታው መልስ ካላገኘ የወያኔ ፌደራሊዝም የዘውግ ፖለቲካን መሰረታዊ ጥያቄ አይመልስም ማለት ነው።
በመሆኑም የወያኔ ፌደራሊዝም በሁለት አንጻር ሆን ተብሎ የተጣመመ ሥርዓት ነው። ሥርዓቱ የፌደራሊዝም ስያሜ ቢሰጠውም በጣም የተማከለ ከመሆኑ በላይ የተማከለው የአንድን ዘውጋዊ ቡድን በፖለቲካ የበላይ ለማድረግ ነው። በመሆኑም ሥርዓቱ ኢዴሞክራሳዊ ብቻ ሳይሆን የውሸት ፌደራሊዝም ነው። የማእከላዊው መንግስት ሥልጣን ምን እንደሚመስል ለማወቅ በኦሮሚያ ውስጥ የፌደራል ፖሊስና የአጋዚ ጦር የሚያደርሱትን ጥፋት መመልከት ብቻ ይበቃል። ክልሎች የራስ ገዝ መብት አላቸው ቢባልም ለአንድ ማዕከል ተገዚ የሚያደርጋቸው ኢአዴግ የሚመራበት የዴሞክራሲያዊ ማእከላዊነት መርህ ነው። ይህ ከቀድሞው ሶቪየት ህብርት የተወሰድ የፓርቲ አስራር ወያኔ ፌደራሊዝሙን ሙሉ በሙሉ እንዲቆጣጥር ያስችለዋል።
በወያኔ አተረጓጎም ክልላዊ ራስ ገዝ ማልት ክልሉ የራሱን ጉዳይ በራሱ ይወስናል ማለት ሳይሆን የወያኔን የበላይነት የሚያስጠብቁ የክልል ጥገኞችን ይፈበርካል ማለት ነው። የወያኔ ቁጥጥር ቀጥተኛ ሳይሆን በክልል ጥገኞች አማካይነት የሚፈጸም ነው። አሠራሩ ክልሉ በራሱ ልጆች የሚተዳደር ያስመስላል። እውነታው ግን የክልል ልሂቃን የሚሠሩት ለወያኔ መሆኑ ነው። ጥገኞቹ ለአገልግሎታቸው በቂ ክፍያ ስለሚያገኙ ሥርዓቱን ለማገልገል ወደ ኃላ የማይሉ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን በወያኔ ለመመስግን ይፎካከራሉ።
የዘውግ ፖለቲካን ምንነት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳየን የወያኔ አመሠርረትና አቋም ነው። ትግራይ የኢትዮጵያ አንዱ መስራች በመሆኗ ለረጅም ታሪክ ከአማራ ጋር በአንድነት የኖረች ብትሆንም ወያኔ የቋንቋን ልዩነት በመጠቀም ትግራይን እራሷን የቻለች ብሔር አድርጓታል። ይህ የሚያሳየው የዘውግ መሰረት ታሪክ ሳይሆን በአንድ ወቅት እንወክላልን የሚሉ ልሂቃን የሚፈጥሩት ማንነት ነው። የሚፈጥሩትም ክልላዊ ወይም አገራዊ ሥልጣን ለማግኘት ነው። ይህንን የፖለቲካ ይዘት የሚያጠናክርው ወያኔ ደርግን ካሸነፈ በኃላ የትግራይን ነጻነት ኣላወጀም። ይልቁኑ ወደ መኃል አገር በመግባት የኢትዮጵያን መንግስት ሥልጣን ተረክቢያለሁ አለ። የወያኔ አመሰራረትንና ጉዞ የዘውግ ፖለቲካን ልሂቃዊ ጸባይና ፖለቲካዊ ዓላማ ያረጋግጣል።
የሠላም መንገድ
የተዘረዘረው የዘውግ ፖለቲካ ንድፈሃሳብ በምን ሁኔታ የሠላምን መንገድ በመክፈት የዘውጎችን መኖር ከአገር አንድነት ጋራ ማጣመር ይችላል? የዘውግ መሰረታዊና ብቸኛ ጥያቄ የማንነት ግትር አቋም ነው ካልን ከመገንጣል በስተቀር ሌላ መፍትሄ አይፈልግም ማለት ነው። ይህ ደግሞ ብዙ አገሮች ላይ እንደታየው ከፍትኛ ምስቅልቅልና ጦርነት ይቀሰቅሳል። ነገር ግን ዘውጋዊ እንቅስቃሴ ፖለቲካዊ ዓላማ አለው ካልን ሠላማዊ መፍትሄ እንድንፈልግ ያደርገናል።
ዘውጋዊ ፖለቲካ የሚያስተጋባው የመንግስትን ሥልጣን ለመቆጣጠር ልሂቃን የሚያደርጉትን ፉክክር ከሆነ የሥልጣኑን አወቃቅር በመቀየር ፉክክሩን በአዲስ ተቋማት በማጠናከር የዘውግ ፖለቲካ ዓላማ እንዲሳካና የአገር አንድነትም እንዲጠበቅ ማድርግ ይቻላል። ይህን ማለት በመጀመሪያ ደረጃ የፌደራላዊ ሥርዓቱን እውነተኛ መልክ በመስጠት የማዕከል ሥልጣንና የክልል ሥልጣን በትክክል መወሰን አለበት ማለት ነው። የክልሎች አቀራረጽ ላይ ብዙ መሻሻል ሊኖር ይችላል፤ ቁም ነገሩ የክልሎች መኖር በመቀበል ፖለቲካዊ ስምምነት ላይ መድረስ ነው። ለክልሎቹ እውቅና አለመስጠት ዘውጋዊ ፖለቲካ የቀሰቀሳቸውን ኃይለኛ ስሜቶችን መዘንጋትና ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዳይኖር ማድረግ ነው።
መፍትሄው ክልሎችን ማጥፋት አይደላም። እነሱን ተቀብሎ ብሔራዊ ተቋማትና ብሔራዊ መግለጫዎችንና ምልክቶችን ማጎልበት ነው። የወያኔ ፌደራሊዝም ዋናው አስከፊ ገጽታ ክልሎችንና የአገር አንድነትን እንደ ተጻራሪ እንጂ እንደ ተደጋጋፊ እንዳይሰሩ ማድረጉ ነው። በተለይ የወያኔ የትምህርት ፖሊሲ የብሄራዊ አንድነትን የማሳደግ ዓላማ አያካትትም። ለምሳሌ የታሪክ ትምህርት የክልሎችን ታሪክንና ተጻራሪነት እንጂ የአንድ ኢትዮጵያ አካሎች አድርጎ አያቀርባቸውም።
ክልሎችንና ብሔራዊ አንድነትን ተደጋጋፊ ለማድረግ መከተል ያልብን መርህ አንድ ነው። እሱም የብሔራዊ ከፈተኛ ደርጃዎች ዘውጋዊ ማንነት መተውን ከመጠየቅ ይልቅ የእድገትና የሹመት ጎዳና ሲሆኑ ነው። በሌላ አባባል አገሪቱን አደጋ ላይ የሚጥላት ዘውግነት ሳይሆን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አለመኖር ነው። ዘውጋዊ እንቅስቃሴዎች በተፋፋሙበት አገር የዴሞክራሲ እጦት የሚያበረታታው ተገንጣይ ቡድኖችን ብቻ ነው።
ትልቁ መሪ ሃሳብ የዘውጎች መቀራረብና አብሮ ምስራት የሚበርታታው የብሔራዊ ሥልጣን ተቋማት ከአክራሪነት ተላቀው መካከለኛ (moderate) የሆነ አሠራርና መርህ ሲከተሉ ነው። ከፍተኛ የብሔራዊ ሥልጣን ደረጃዎች የመካከለ አመለካከት ሹመት ሲሆኑ ዘውጋዊ ወገናዊነት ወደ ብሔርዊ፤ ኢትዮጵያዊ ወገናዊነት ያድጋል።
ምንኛውም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የተማከለን ሥልጣን ቆርሶ ለክልል ማስተላለፍ ይጠይቃል። የዘውግ ጥያቄ ከተነሳ ደግሞ የዘውግ የራስ ገዝ መብትን ማካተት ይጠይቃል። የግለሰብ መብቶች መከበር ብቻ ዝውግ የሚያነሳው ጥያቄ አይመለስም። ይሁንና የዘውግ ክልል መቋቋም በሂደት የግለሰብን መብት ማእከላዊ ማድርጉ የማይቀር ነው። ክልሉ በትክክል ሲሰራ ቀስበቅስ የክልል ልሂቃን አንድ ወጥነት እየቀዘቀዘ ወደ ልዩነት ስለሚያመራ ለክልል ሥልጣን የሚፎካከሩ ቡድኖች ይፈጠራሉ። ይህ ደግሞ የግለሰብ መበት የበላይነት ያስከትላል።
በሌላ በኩል መካከላዊነት ለብሔራዊ ደርጃ እጩነት መለኪያ ከሆን የዘውግ ማንነትና ብሔራዊ አንድነት ተደጋጋፊ ይሆናሉ። ለዚህም ወሳኙ መሳሪያ ክብደት ያለው የፕሬዚደንት ሥልጣን መፍጥር ነው። የፕሬዚደንት ሥልጣን ህጋዊነት መካከለኛነት ላይ እንዲመሰረት ለማድረግ ዋናው መንገድ የሕዝብ ቀጥታ ምርጫ ነው። ሕጉ የኢትዮጵያ ፕሬዚደንት ሆኖ ለመመረጥ ተወዳዳሪዎች ከሁሉም ዘውጋዊ ክልሎች የአብዛኛውን ደምጽ መግኘት አለባቸው የሚል ከሆነ በብሄራዊ ደርጃ በሙሉ መካከላዊ አሰራርና ፖሊሲ እንዲዘረጋ ያደርጋል። ሕጉ ማንኛውም ተወዳዳሪ ፕሬዚደንት ሆኖ ለመመረጥ መካከላዊ ፖለቲካ ፕሮግራም አንዲኖረው የሚያስገድድ ብቻ ሳይሆን ፕሬዚደንቱን ከራሱ ዘውግ ውጪ የሁሉ ዘውጎች ተወካይና ተጠሪ ያደርጋል።
ይህ አሰራር እውን የሚሆነው በአንድ በኩል እራሱን የቻለ ፓርላማ ሲኖርና ይህ ፓርላም የዘውግ ፖለቲካ የሚልካቸውን ተወካዮች ሲያካትትና በሌላ በኩል ደግሞ በብሔራዊ ደምጽ የሚሰይም ፕሬዚደንታዊ ሥልጣን ሲኖር ነው። እዚህ ለይ ብዙ የአሰራር ዓይነቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ፕሬዚደንቱንና ፓርላማውን የሚያገናኘው ጠቅላይ ሚኒስትር በፕሬዚደንቱ በቀጥታ ሊሾመው ይችላል ወይም ፓርላማው በድምጽ ብልጫ መርጦ በፕሬዚደንቱ ሊያጸደቅ ይችላል።፡ቁም ነገሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመካከል ውሳኔዎች ተከራካሪና አስፈጻሚ ኃይል መሆኑ ነው።
የፕሬዚደንቱ ከክልላዊ ውስንነት መላቀቅና የፓርላማው የመካከላዊና ሚዛናዊ ወሳኔዎች ምንጭ መሆን ዘውጋዊና ፖለቲካና ብሔራዊ አንድነት አብረው እንዲሄዱ ያደርጋል። እያንዳንዱ ዝውግ በክልሉ እርሱን ያስተዳድራል፤ በብሔራዊ ጉዳዎች ላይ በመካከላዊ አሰራር ለብሔራዊ አንድነት አስተዋጽኦ ያደርጋል። የፕሬዚደንቱ ሥልጣን የሚመሰርተው ብሔራዊ ምርጫ የኢትየጵያዊነት ዋና መግላጫና ምልክት ይሆናል። የፕሬዚደንቱ ብሔራዊ ምርጫ የጋራ ውጤት በመሆኑ የአንድነት እሴቶችንና ስሜቶችን በየጊዜው ያድሳል፤ ያጠናክራል።
በግልጽ እንደሚታየው ይህ አመለካከት አማራጭ የሚሰጥ ነው። በአንድ በኩል ዘውጋዊ ፖለቲካ መጥፋት አለባት ወይም በራሱ ይጠፋል የሚሉ አሉ። በእኔ አመለካከት ይህ ከንቱና ለአገር አንድነት አደገኛ አቋም ነው። በሌላ በኩል የአገር አንድነት ከጥቅማቸው ጋር ስለማይሄድ ብሔራዊ ተቋማትና ስሜቶችን በማዳከም አንድነቱ በአንድ ዘውግ የበላይነት ብቻ ይጠበቃል የሚለው የወያኔ ፖለቲካ አለ። ይህ አሰራር አደገኛና ዘለቄታ የሌለው መሆኑ የኢትዮጵያ አሳዛኝ ሁኔታ በቂ ማስረጃ ነው። ያቀረብኩት ሃሳብ እነዚህን አደገኛ አቋሞች የሚወጋ መካከለኛ ሃሳብ ነው። እሱም ዘውጋዊ ፖለቲካን ማጥፋት ወይም መሰርታዊ ማድርግ ስይሆን በመካከላዊ አሠራር የአገሪቱን አንድነትና ዘውጋዊ ፖለቲካ እንዲተባበሩ ማድርግ ነው።