ሰላም አስከባሪነት ለኢትዮጵያና ለሩዋንዳ ገቢ እያሰገኘ ነው

በሰላም ጥበቃ ስም ወታደር ማከራይት ትርፋማ  ንግድ ሆንዋል

Addisadmassnews

November 29, 2014

በአፍሪካ፣ ወደ ግጭት ቀጣናዎች እየተሰማራ በስነ-ምግባርና በሙያ ብቃት ስምካተረፉት መካከል የኢትዮጵያ መካከል ሃይል አንዱ እንደሆነ የገለፀው ዘኢኮኖሚስት መጽሔት፤ ኢትዮጵያና ሩዋንዳ በሰላም አስከባሪነት ጥሩ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን ዘገበ፡፡

Making troops for hire available is an important source of income for the Ethiopian regime

Making troops for hire available is an important source of income for the Ethiopian regime

ቀደም ሲል ለሰላም አስከባሪነት የአውሮፓ ወታደሮች ሲሰማሩ እንደነበር መጽሔቱ አስታውሶ፤ ከ20 አመታት ወዲህ ግን በርካታ የአፍሪካ አገራት የአህጉራቱን ግጭቶች ለማብረድ የሰላም አስከባሪነት ስራዎችን እየተረከቡ ነው ብሏል፡፡

በተለይ ኢትዮጵያ እና ሩዋንዳ፤ እምነት የሚጣልባቸው ሰላም አስከባሪ ሃይል በማሰማራት መልካም ስም እንዳተረፉ መጽሔቱ ገልጿል፡፡

በርካታ ሺ ወታደሮችንና ቁሳቁሶችን፣ ለሰላም ተልዕኮ እንዲያሰማሩ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኩል በተደጋጋሚ የሚመረጡት ኢትዮጵያና ሩዋንዳ፤ ለሚያሰማሩት ጦር የስልጠና እና የጦር መሳሪያ ወጪያቸው በተመድ እንደሚሸፈንላቸው ዘኢኮኖሚስት ገልፆ፤ ይህም የመከላከያ ሃይላቸውን ይበልጥ ዘመናዊ ለማድረግ ያግዛቸዋል ብሏል፡፡

በዚህም በተጨማሪ ብዙዎቹ የአፍሪካ አገራት በራሳቸው ወጪ ለጦር መሳሪያ ገዢ የሚያውሉት ገንዘብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡

የአንጐላ መንግስት ባለፈው አመት የመከላከያ በጀቱን ከ4.5 ቢሊዮን ዶላር ወደ 6 ቢ ዶላር (ወደ 120 ቢሊዮን ብር ገደማ) እንዳሳደገ መጽሔቱ ጠቅሶ፣ የናይጀሪያ መንግስትም ለአዳዲስ የጦር አውሮፕላኖች ግዢ አንድ ቢሊዮን ዶላር መመደቡን ዘግቧል፡፡
ከፍተኛ ገንዘብ ለጦር ሃይል በመመደብ በአፍሪካ ቀዳሚነቱን የያዘችው አልጀሪያየ በአመት 10 ቢ ዶላር ታወጣለች ብሏል – ዘገባው፡፡

የዛሬ 25 አመት ገደማ ሶቪዬት ህብረት የምትመራው የሶሻሊዝም አምባገነንነት ሲፈራርስ፣ በአፍሪካም በርካታ መንግስታት ከስልጣን እንደተወገዱና አንዳንዶቹም የተቃውሞ ፓርቲዎች እንዲንቀሳቀሱ የሚፈቅድ ማሻሻያ ለማድረግ እንደተገደዱ የሚታወስ ሲሆን፣ የነፃ ገበያ እና የዲሞክራሲ ስርዓት ጅምር ማሻሻያ ላይ በማተኮር ለመከላከያ ሃይል የሚያወጡት በጀት ለ15 አመታት ሳይጨምር እንደቆየ መጽሔቱ ያመለክታል፡፡

ባለፉት አስር ዓመታት ግን፣ የሃይማኖት አክራሪነትና የሽብር አደጋ፣ በዘር የሚቧደኑ ታጣቂዎችና ቡድኖች ግጭት፣ እንዲሁም የባህር ላይ ውንብድና ከፍተኛ ስጋት የሆነባቸው የአፍሪካ መንግስታት ለመከላከያ ሃይል ከፍተኛ ገንዘብ መመደብ ጀምረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ዴቪድ ሺን ለመጽሔቱ በሰጡት ገለፃ፣ አንዳንድ የአፍሪካ መንግስታት ጉድ የሚያሰኙ የጦር መሳሪያዎች እየገዙ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ T-72 የተሰኙ ዘመናዊ ታንኮችን ከዩክሬን ማስገባት ጀምራለች፡፡ ደቡብ ሱዳን ደግሞ መቶ ታንኮችን፡፡
ሰፊ የባህር በር ያላቸው እንደ ካሜሩን እና ሞዛንቢክ፣ ሴኔጋልና ታንዛኒያ የመሳሰሉ አገራት የባህር ሃይላቸውን በጦር መሳሪያ እያፈረጠሙ መሆናቸውን ዘኢኮኖሚክስ ጠቅሶ፣ አንጐላ ደግሞ የጦር አውሮፕላኖችን የሚሸከም ተዋጊ መርከብ ለመግዛት የጀመረችው ድርድር አስገራሚ መሆኑን ጠቁሟል፡፡

የአፍሪካ አገራት ጦር፣ በስልጠናና በመሳሪያ ይበልጥ “ፕሮፌሽናል” ለመሆን እየተሻሻሉ መጥተዋል የሚለው ዘኢኮኖሚስት፣ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገባቸው ለመከላከያ ሃይል ደህና ገንዘብ እንዲመድቡ ከማስቻሉም በተጨማሪ እንደ ኢትዮጵያና ሩዋንዳ ደግሞ በሰላም አስከባሪ ሃይል ተልእኮ አማካኝነት የማይናቅ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን ገልጿል፡፡

እንዲያም ሆኖ የጦር መሳሪያ ግዢ በሁሉም አገራት ውጤታማ ሆኗል ማለት አይደለም፡፡ ኮንጐ ብራዛቪል ፈረንሳይ ሰራሽ ሚራዥ የጦር አውሮፕላኖችን ብትሸምትም፣ በብሔራዊ በዓላት የበረራ ትርዕት ከማሳየትና የበዓል ማድመቂያ ከመሆን ያለፈ ጥቅም አላስገኙም፡፡ ደቡብ አፍሪካም ከስዊድን 26 ተዋጊ አውሮፕላኖች ከገዛች በኋላ፣ በበጀት እጥረት ግማሾቹ ከአገልግሎት ውጭ የጋራዥ ሰለባ ሆነዋል፡፡

SU 30 አውሮፕላኖችን ከራሺያ የገዛችው ኡጋንዳ ደግሞ፤ ተስማሚ ሚሳይሎችን ስላልገዛች ዘመናዊዎቹን አውሮፕላኖች በአግባቡ ልትጠቀምባቸው አልቻለችም ብሏል መጽሔቱ፡፡

 

 

 

_____________________

__________________________________________________________________________________