Ethiopia’s dictator Meles Zenawi is going after officials and members of the Oromo People’s Democratic Organization (OPDO) with a vengeance these days. So far over 150 officials and hundreds of members have been thrown in jail charged with corruption.
Ethiopian Review has interviewed Col. Abebe Geresu about the mass purging inside OPDO.
OPDO is one of the five parties that make up the the TPLF-dominated ruling coalition, Ethiopian People’s Democratic Front (EPRDF).
Col. Abebe left the current regime 2 years ago along with Gen. Kemal Gelchu and 600 other high- and mid-ranking officers mostly from OPDO.
The interview is in Amharic. Read below:
ጥያቄና መልስ ከኮ/ል አበበ ገረሱ ጋር
ጥያቄ – በቅርቡ የመለስ ዜናዊ አገዛዝ በርካታ ባለስልጣኖችን እያሰረና ከስራ እያባረረ ይጋኛል። ከሚታሰሩት መካከል አብዛኛዎቹ የኦሮሞ ህዝብ ዲሞክራሴያዊ ድርጅት (ኦህዴድ ) ኣባላት ናቸው። ለምን መለሰ ዜናዊ የኢህአዴግ አባል ድርጅት የሆነውን የኦህዴድን አመራር አባላት ማሰር የጀመረ ይመስሎታል?
መልስ- መጀመሪያ ለጥያቄህ በጣም አመሰግንሃለሁ። ኦህዴድ ድርጅት ተብሎ ይጠራ እንጅ የድርጅት ህልውና ያልነበረው ነው። ኣቶ መለሰ ዜናዊ በአንድ ወቅት «ኦህደድ ታክቲካዊ ድርጅት እንጂ ስትራትጅካዊ ድርጅት ኣይደለም» ብሎ ነበር። ሌላም ጊዜ «ኦህዴድ ሲፋቅ ኦነግ ይወጣዋል» እያለ በፊት ሌላ በኋላ ሌላ ወይም ፈጣን ሎተሪ ኣይነት ድርጅት መሆኑን በተደጋጋሚ እየገለጸ ቆይቷል። ለዚህም ምክንያቱ ኦህዴድ የሚባለው ድርጅት ወያኔዎች ወደ ኦሮሞ መሬት ለመግባት እርግጠኞች በነበሩበት ጊዜ ኦሮሞን የሚመስል ድርጅት ኣይነት ይዞ መሄድ የግድ ስለነበረባቸው ኦሮምኛ ተናጋሪ የደርግ ሰራዊት ምርከኞችን ኣሰባስቦ በድርጅት መልክ ማደራጀት ስለነበረበት በኣቶ ክንፈ ገብረመድህን በኩል ኣደራጃቸው። በዛኑ ዘመን «መደራጀታችን ለምን ያስፈልጋል፥ የኦሮሞ ድርጅት ኦነግ ኣለ?» ብሎ የጠየቁትን ኣጠፏቸው። ከዚያ በኋላ ምንም ማሰብ የማይችሉትን ምርኮኛች ወታደሮችን እነ ኩማ ደመቅሳ፥ እነ ኣባ ዱላ ገመዳ፥ እነ ኢብራሂም መልካና ባጫ ደበሌ የተባሉትን ዋነኞቹ የኦህዴድ ኣመራሮች ኣድርጎ ጉዞውን ወደ አዲስ አበባ ቀጠለ።
ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ ወያኔዎች ኦህዴድ ታክቲካዊ ድርጅትነቱን በግልጽ መጠቀም የጀመረው። ኢህኣዴግ አዲስ አበባን በተቆጣጠረ ማግስት በ1984 ዓ/ም መቱ ላይ ኦህዴድ ባደረገው ግምገማ ላይ በአንድ ጀንበር 400 ሰው አባረረ። ቀጥሎ በታጠቅ ጦር ሰፈር 16,000 የኦሮሞ ካድሬዎችን ካሰለጠነ በኋላ የደርግ ምርኮኞችን በሙሉ አባሮ የአካል ምርኮኞች ብቻ ሳይሆኑ የአዕምሮ ምርኮኞችን ኣመራር እንዲሆኑለት ለይቶ አስቀራቸው። «ትግላችን ካለፈው ይልቅ ቀጣይ፥ ውስብስና አስቸጋሪ ነው። በመሆኑም አዲሱን የትግል መስመራችንን መቀጥል የምንችለው ንቅል የሆነው ታጋይ ሳይሆን አዲሱ ትውልድ ነው በሚል» ነባሩ የኦህዴድ ታጋዮችን «ፈርተሃል፣ ጠጥተሃል፣ ሰርቀሃል፣ ትግሬዎችን ትጠላለህ፣ የደርግ ሰራዊት ናችሁ፣ የደርግ አመለካከት አለቀቃችሁም፣ ጠባብ አመለካከት አላቹ» በሚሉ ሰበቦች የአህዴድን ታጋዮች ማሰር፣ ማባረር እና ደብዛችውን ማጥፋት የጀመረው አሁን ሳይሆን ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ ነው።
የኦህዴድ ምክትል ሊቀ መንበር የነበሩት ኣቶ ኢብራሂም መልካም ሙስና በሚል ሰበብ የተባረሩት ትንሽ ከሌሎች ምርከኞች የተሻለ ህዝባዊ አመለካከት ስለነበራቸዉ ነበር። ሌሎችም በዚሁ በተልካሻ ምክንያቶች ተባረዋል። ወያኔ እነ ኣቶ ባዩን በመኪና ገጭቶ የገደለው በዚሁ ምክንያት ነበረ። ዛሬም ወያኔ የኦህዴድን ባለስልጣኖች ከክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት ጀምሮ በገፍ ማሰር የጀመረው ሙስና በሚል ሰበብ ነው። በእርግጥ በኢትዮጵያ ውስጥ ሙስና፣ ዘረፋ እና የንጹሃንን ዜጎች ዳም ማፍሰስ ወንጀል ቢሆን ኖሮ ክአቶ መለሰ ዜናዊ፣ ወ/ሮ አዜብ መስፍን እና ጀሌዎቻቸው በላይ በወንጅል የተዘፈቀ ያለ አይመስለኝም። ነገሩ ሌላ ነው።
የኦሮሞ ህዝብ ብሶቱ ጣራ ደርሶ ሊፈነዳ በደረሰበት ባሁኑ ሰዓት እነ መለስ ዜናዊ የዚህን ህዝብ ሃብት፣ ንብረቱን እና መሬቱን እየቀሙ ለጀሌዎቻቸውና ለ ባዕዳን ሃገሮች ባለ ሃብት ሽጠው ስለበሉ የኦሮሞን ህዝብ አመለካከት በኦህዴድ አመራሮች አሳብበን እንቀይራለን በሚል ግዜ ያለፈበት የወያኔ ከፋፍለ ግዛ አስተሳሰብ ነው።
ይህ ደግሞ ኦህዴድን ለዋውጦ የኦሮሞን ህዝብ በማታለል ተቃውሞን እና ህዝባዊ አመጽን ለማፈን ፈጽሞ የማይቻል፣ ነገር ግን የአምባገነን መሪዎች በውድቀታቸው ዋዜማ ላይ የሚያደርጉት መፍጨርጨር አንዱ አካል ነው።
የኦሮሞ ህዝብ የወያኔ ስርኣት ቃር ቃር ካለው ሃያ ዓመታትን አስቆጥሯል። ከአንግዲህ ወዲህ ወያኔ የኦህዴድን ባለስልጣኖች አሰራቸውም ኣባረራቸውም ገደላቸውም የኦሮሞ ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር ወያኔን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከራሱ ጫንቃ ላይ ካልጣለው በሃገሪትዋ ውስጥ ፍትህና ሰላም ምንም ቢሆን ሊመጣ ስለማይችል ህዝባዊ ትግሉን አጠናክሮ ይቀጥላል እንጂ ለኣፍታም ቢሆን ህዝባዊ ነውጡ በወያኔ ድራማ ሊገታ አይችልም። መሰረቱ የበሰበስውን ቤት ጣራውን ቢጠግኑት ቤት ሊሆን አይችልም። መሰረት የለውምና።
ጥያቄ – በሌሎቹ የኢህኣዴግ ድርጅቶች ለምን ተመሳሳይ ሁኔታ ኣልተከሰተም?
መልስ – በሌሎቹ ድርጅቶች ያልተነሳበት ምክንያት ኣሁን ህዝባዊ ነውጡ ወያኔን ያሳጋ ያለው ወይም ሕዝባዊ ነውጡ ይነሳል ተብሎ የሚጠበቀው በኦሮምያ ክልልና ኣዲስ ኣበባ ዙሪያ በመሆኑና ተቃዋሚ የኦሮሞ ድርጅቶች በሕዝብ ውስጥ የሚሰሩት ስራ ወያኔን በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ በመጣሉ ነው ዘመቻውን ኣስቀደሞ በኦህዲድ ድርጅት ባለስልጣናት ላይ የከፈተው።
ሁለተኛ፣ ሌሎች ድርጅቶች የሚባሉትስ እነማን ናቸው? በኢህኣዴግ ኣባል ድርጅቶች ውስጥ ኣንደኛው ህወሓት (ወያኔ) ነው። ህወሓት ማለት የመለስ ጉዳይ ኣስፈጻሚ ስለሆነ ምንም ዓይነት ችግር የሚያመጣ ኣይደለም። ብኣዴን ከሆነ ከኣዲሱ ለገሰ እና ከተፈራ ዋልዋ ውጭ ሌሎቹ ኣማርኛ ተናጋሪ ትግሪዎችና የመለስ ዜናዊ ቡችሎች የነበሩ ናቸው። ዴህዴግ የሚባሎት ድሮውኑ መለስ «ስዕብና የሌላቸው ሰዎች ስብስብ» ነው ብሏቸዋል። ሌሎችን ኣጋር ደጋፊ በሚል የኢህኣዴግ ተጎታቾች ኣድጓቸዋል። ለማናቸውም ተጎታች ድርጅቶቹ ሁሉ የሚቀርላቸው ጉዳይ ኣይደለም።
ጥያቄ – ይህ ሁኔታ ወዴት የሚያመራ ይመስልዎታል?
መልስ – ይህ ሁኔታ የሚያመራው ወያኔ የግዛት ዘመኑ ያከተመ መሆኑን በግልጽ የሚጠቁም ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ የወያኔ ስርዓት ኣንገሽግሾታል። ወያኔ በኢትዮጵያኖች ዘንድ በዝረራ የተሸነፈው በምርጫ 97 ነበር። ነገር ግን በማን ኣለብኝነት የሕዝቦችን ድምጽ በሰራዊት ሃይል ኣፍኖ ነበር እስከዛሬ ድረስ በስልጣን ላይ ያለው። የኢትዮጵያ ሕዝብ የራሱ የመከላከያ ሰራዊት የለውም። ኣሁን ያለው ሰራዊት የወያኔ የግል ሰራዊት ወይም የትግራይ ሚሊሻዎች፣ ማለትም የነመለስ የግላቸው ሰራዊት እንጂ ያገር ሰራዊት ኣይደለም። በመሆኑም ወያኔ ዛሬም ድረስ በነዚህ በግሉ ሰራዊት ኣባላት የኢትዮጵያን ሕዝብ ተቃውሞ እና ኣመጽን ለማፈን እስከመጨረሻ መጣጣሩ ኣይቀርም። ነገር ግን ወያኔ ምንም ያክል በትግራይ ልጆች ብቻ የሚመራውን ሕዝባዊነት የሌለው ወይም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ያልሆነውን ነፍሰገዳይ ስራዊት ቢያከማችም ወያኔና ሰራዊቱ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሊያሸንፉት ኣይችሉም። የወያኔ ሰራዊትም የኢትዮጵያን ሕዝብ ደም ኣፍስሶ የትም ሊያመልጥ ኣይችልም። ኣቶ መለስ ዜናዊም የኢትዮጵያን ሕዝብ ኣስጨፍጭፎ ከዚህ በፊት እንደተዋረዱት አንምገነን መሪዎች ተዋርደው በጦር ወንጀለኛነት ከመጠየቅ ኣያመልጥም። በርግጠኝነት ሁኔታው የሚያመራው ወደዚህ ነው።
አሁን እነ መለስ ዜናዊ ኦህዴድን ባለስልጣኖች ቢያስሩም፣ ቢፈቱም፣ ቢያባርሩም፣ የስልጣን ዘመናቸውን ሊያራዝምላቸው የሚችል ኣይመስለኝም። ስለዚህ የወያኔ ባለስልጣኖች በኢትዮጵያኖች ዘንድ ቃር ቃር ያለዉን ድራማቸውን ትተው የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ ጠይቀው በሰላማዊ መንገድ ስልጣኑን ለሕዝብ ቢያስረክቡ አገሪቱን ከከፋ ጥፋት ሊታደጉና እነሱም ከወንጀለኝነት ሊድኑ ይችላሉ። ያላቻዉም የማጨረሻ ምርጫ ይሄ ብቻ ነው። ኣለበለዚያ የወያኔ ስርዓት በከፍተኛ ሕዝባዊ ነውጥ ተመቶ ወደ ግባኣተ መሬቱ የሚመለስበት ዋዜማ ላይ ደርሷል።