[If you are unable to read this article in Amharic, download Ge’ez font here.]
ጉዱ ታዬ
አሪስ ጣጣሊስ ከሳን ፍራንሲስኮ
አሁን ለታ ዶ/ር ታየ ከአሜሪካ ድምጽ ራድዮ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ሰማሁና ነገሩ እጅጉን ቢደንቀግኝ፣ እንደው እነዚህ ስዎች ዝምታችንን ካለማወቅ ቆጠሩት እንዴ ብየ አሰብኩና ይህችን አጭር መጣጥፍ ቢጤ ለመጻፍ ወሰንኩ። ቃለ ምልልሱ በጥቅሉ ከስንዴው እንክርዳዱ የበዛ፣ ለመለየትም ረጅም ጊዜ የሚወስድ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። የሰማዉን ሁሉ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ቃል ተቀብሎ ለማነብነብ የቆረጠ ግለሰብ አምላኪ ካልሆነ በቀር በዚህ ቃለ ምልልስ ስለሰዉዬው ማንነት የነበረውን ሙጣጭ ተስፋ ያላንጠፈጠፈ ኢትዮጵያዊ ያለ አይመስለኝም።
ለማንኛውም አንድም ጊዜ ስለማይፈቅድልኝ፣ ሁለትም ደግሞ እኔ ጊዜዬን እንደ አንዳንድ አካይስት ሰው ከማጣላትና በድርጅት መሃል ገብቶ ከመፈትፈት፣ ከወሬና ከስም ማጥፋት ለላቀ ሁኔታ ላውል ጊዜውን ከስጠኝ ከፈጣሪዬ ጋር ኪዳን ያለኝ በመሆኑ እና በጊዜው እንደ ንባብ፣ ወቅታዊውን ጉዳይ ያማከለ ጥናትና ምርምር፣ እንዲሁም ለኤች-አር 2003 ድጋፍ ማሰባሰብን የመሰለ የከበረ ስራ ስለሚጠብቀኝ ለአካይስት መልስ ለመስጠት ብዙም ጊዜ አልወስድም። ነገር ግን መሰረታዊ በሆነው የዶፍተሩ ቅንጅትን መቀላቀል ላይ ትንሽ ማጭበርበር ቢጤ ስላስተዋልኩ ጠቀስ አድርጌ ማለፍ ወደድኩ።
ካልተሳሳትኩ ከጥያቄዎቹ አንዱ “እርስዎ በተደጋጋሚ በተላያየ መድረክ ቅንጅትን እንደማይደግፉ ተናግረዋል፤ እኔም ቤተሰቤም ቅንጅትን አልመረጥንም ብለዋል። ታዲያ አሁን በዚህ አጭር ጊዜ ከአባልነት አልፈው የቅንጅት አመራር እንዴት ሊሆኑ ቻሉ?” የሚል ነበር። ታዲያ ጥርስ የማያስከድኑት የአካይስት መሪ ሲመልሱ፣ “የህዝብን ድምጽ ሰምቼ ነው” አሉንና አረፉታ። እኔ የምለው እንደው እነዚህ ሠዎች ቂል አደረጉን እንዴ? እግዜርን አናየውም ብለው ባይፈሩት ጊዜንና እማኞችን አይፈሩም እንዴ? ሚልዮኖች በሚስሙት የአሜሪካ ድምጽ ራድዮ እንዲህ አይን ያፈጠጠ ደረቅ ውሸት ሲናገሩ ትንሽ እንኩዋን አይሸማቀቁም? ነውስ በሬድዮ ነው፤ ፊቴን ጭፍግግ፣ ምላሴን በጥርሴ ንክስ፣ ትከሻዬን በምን ቸገረኘ ስብቅ፣ አይኔን በጨው እጥብ አድርጌ በንቀት ስናገር የሚያየኝ የለም ብለው ነው? እንኩዋን ይቺ ሌላም አታመልጠን ጋሼ “የድሮ ፖለቲከኛ”፤ እንኩዋን እርስዎ አፈ ጮሌው መለስም አልሸወደን ጋሼ “አቁዋም የለሽ”፤ እንኩዋን ስራዎትን ሃሳብዎትን አንስተውም የኛ “የሥልጣን ሰቀቀናም”፤ እንኩዋን ተናግረህ ድምጽህን ሰምተን ሳንሰማህም ዓላማህን እናውቀዋለን የኛ “የመድረክ ጥመኛ ግላዊ ፋኖ”…
ለመሆኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ቅንጅትን እንደሚደግፍ ባሳየበትና አለምን ባስደነቀው የሚያዝያ 29ኙ ማዕበል ጊዜ ይሄ ዛሬ ሃሳብዎትን ያስቀየርዎት የህዝብን ድምጽ አዳማጭ ስብዕናዎ የት ነበር? ድጋፍ በሠላማዊ ሰልፍ አይገለጽም ብለው በለመዱት ምሁራዊ ሽምጠጣዎ እንድሚክዱ አያጠራጥርም። እስኪ እሱም ይቅር፤ ያ ያገሬ ወጣት- አዛውንት ያለበትን ጫና፣ ዛቻና ማስፈራሪያ ተቕቁሞ ወጥቶ ቅንጅትን ሲመርጥ እና ውጤቱም በአንዳንድ ከተሞች ከኢህአዴግ የማጭበርበር አድማስ እጅጉን ልቆ ሲታይ ይሄ የሚለፍፉት “የህዝብን ድምጽ አይቶ ሃሳብን ቀያሪ” ማንነትዎ የት ነበር?
እውነት ለኢትዮጵያ ህዝብ ትግልና ድምጽ መከበር የቆመ ፖለቲካዊ ስብዕና ቢኖርዎትማ ቅንጅትን የመደገፊያዎቹና የመቀላቀያዎቹ ዘመናት እነዛ ነበሩ። ግን እርስዎ እቴ! ጉዳይዎ ከህዝብ ድምጽ ጋር መቼ ተገናኝቶ! የርስዎ ዓላማ፣ የቀን ቅዠትዎና የሌሊት ህልምዎ ስልጣን መሆኑን አንድ አናርኪስት እንኩዋን ይመሰክራል። አለም ሁሉ ቅንጅት የኢትዮጵያ ህዝብ ምርጫ እንደሆነ አምኖ ተቀብሎ ኢህአዴግን ከስልጣን ላለማውረድ ሌሎች (እንደ ሽብርተኝነትን መዋጋት፣ አበረታች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እና ለአካባቢው ሰላምና መረጋጋት አይነት) ቁንፅል ምክንያቶችን ያቀርብ በነበረበት በዛን ወቅት፣ ኢህአዴግ እንኩዋን ከርስዎ ተሽሎ እውነታዎችን አምኖ ተቀብሎ የቅንጅትን እንቅስቃሴ ከዩክሬኑ የህዝብ ማዕበል ጋር እያመሳሰለ መሪዎቻችንን በእስር ቤት አፍኖ ቤተ መንግስቱን እና ከተማውን በልዩ ሃይሎች እያስጠበቀ ስልጣኑን የሙጥኝ ሲል- እርስዎ ግን ከሃገር ሃገር፣ ከመድረክ መድረክ እየዞሩ “እኔ ቅንጅትን አልመረጥኩም”፤ “ቤተሰቤም ቅንጅትን አልመረጠም”፤ “ፓርላማ ያልገቡት ስልጣን አንሶአቸው ነው” እያሉ ሲለፍፉ ነበር። የለም ዶክተር ታዬ እንዲህ በቀላሉ እንዲሸዉዱን እንኩዋን አንፈቅድም። በፍጹም አያስቡት። መሪዎቻችን ታስረው እኛ እነሱን ለማስፈታት ላይ ታች ስንል፣ ሁሉም ያለውን እየተጠቀመ ሲጣጣር እርስዎ ግን የአገልግሎት ዘመናቸውን በ1969 በማብቃቱ እስከ 1971 ድረስ ለሁለት አመታት የስንቱን ወጣት ህይወት ከቀጩ እና ካስቀጩ፣ የብልሽት ግዜአቸውን ደብቀው ወጣቱን የአምባገነን ሲሳይ ካደረጉ የነፈሰባቸው የትላንት ስዎች ጋር ሆነው ከአገር አገር እየዞሩ “ሲሞጣሞጡ” ነበር። (አንባቢዎቼ በጣም ይቅርታ ለአጉራ ዘለል ቃሉ- የሳቸዉን የዛን ሰሞን የመድረክ ባህርይ ሸጋ አድርጎ የሚገልጽልኝ “የተማረ” ቃል በማጣቴ ነው።)
ታዲያ አሁን ምን አዲስ ነገር ተፈጠረ ዶፍተርየ? የ 2 እና 3 ሚሊዮን ህዝብ የድጋፍ ድምጽ ያልከፈተዉን ጆሮዎን፣ የ90% “ለምርጫ ተመላሽ” ጨዋ ህዝቡ ምርጫ ያላበራውን አይንዎን ዛሬ ምን ከፈተው? ምንስ አበራው? አንድ አይነት መለኮታዊ መገለጥ ከአርያም ተቀበሉን? አንድዬ ራዕይ ቢጤ ከላይ ከፀባዖት ለቀቀለዎትን? እንዲያ ከሆነ እባክዎ “የታየ ራዕይ” ብለው እሱን እንኩዋን ባይሆን በጽሁፍ መልክ ያቅርቡትና (በዚህ እንኩዋን የተጠናወትዎት “ምሁራዊ ስንፍና” ቢለቅዎት) የእርስዎ ቢጤ የሆኑትን እንማርክበት፤ እኛስ ጣጣችንን ከጨረስን ቆየን። መቼም ከርስዎ የሆነ “ብሄራዊ ራዕይ” ባንጠብቅም ጽሁፉ አይጎዳም። ለእርስዎም እኮ እንዲሁ ስራ ፈትቶ ከመቀመጥ እንደው የሆነች ነገር ጫር ጫር ማድረጉ ይሻሎታል።
ነገሩ አጭር ነው!!! ራዕይ በመሰለ የቀን ቅዥትዎ አንድ ነገር አዩ- ስልጣን!! መቼም ቀዳዳ ሁሉም ጋር አይጠፋምና “ሀይሉኛ” ቀዳዳ አስተዋሉ፤ ገቡበት፤ ተጠቀሙበትና አሁን እንዳሉ አሉ። ያልተረዱት ነገር ቢኖር ግን- የኢትዮጵያን ህዝብ ትግል ያስቀደሙ ባተሌዎች አይተኙልዎትም።