­

የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሰጠን ኃላፊነት ብቁ ሆነን አልተገኘንም – ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም

ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም፥ የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ም/ሊቀመንበርና የውጪ ግንኙነት ኃላፊ የነበሩ

የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና የውጪ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም ፓርቲያቸውን በቃኝ በማለት ተሰናብተዋል፡፡ ከፓርቲው ራሳቸውን ያገለሉበትንና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ ከሪፖርተር ጋዜጣ አሰግድ ተፈራና ሰብለወንጌል ሃብታሙ አነጋግረዋቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎን የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያውቆት ከ1997ቱ ምርጫ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ከምርጫ 97 በፊት ከኢህአዴግ የሹመት ጥሪ እንደደረስዎት ይነገራል?

ዶ/ር ያዕቆብ፡- በአንድ ወቅት ደርሶኛል፡፡ በሽግግር መንግሥቱ ጊዜ የወቅቱ አፈጉባኤ ከነበሩት ከአቶ ዳዊት ዮሐንስ ጋር እንተዋወቅ ስለነበርና ኢሕአፓም ሆነን ስለሰራን ጥያቄ አቅርቦልኝ ነበር፡፡ በወቅቱ አሜሪካ አስተምር ስለነበር ስልክ ደውሎ የፍትሕ ሚኒስትሩ እየለቀቁ ነው፣ የእሳቸውን ቦታ ወይንም የቀይ ሽብር ፍርድ ቤት ገና መቋቋሙ ነበርና ልዩ አቃቤ እንድሆን ጠይቆኝ ነበር፡፡ በኋላ እኔም ትንሽ ጊዜ ላስብበት ብዬ አንዳንድ አስተማሪዎችን ካማከርኩኝ በኋላ ኢህአዴግ በርግጥ ለቀይ ሽብር ተዋንያን ፍትህ እሰጣለሁ የሚል ከሆነ እኔ ከእዛ ልሸሽ አልችልም የምችለውን አስተዋፅኦ አደርጋለሁ፡፡ ስለዚህ ልዩ አቃቤ ሕግ ቦታ ለመያዝ ፈቃደኛ ነኝ፡፡ ሆኖም ግን በዚህ በስራዬ ላይ መንግሥት ምንም ዓይነት ጣልቃ እንዳይገባ ከበጀት በስተቀር እገሌ ይከሰስ (ትከሰስ”፣ እገሌ ይለቀቅ (ትለቀቅ) የሚለውን በምንም ጣልቃ ገብነት ዓይነት መልኩ የማልቀበል መሆኑን፤ ሹመቱ ከዚያ ውጭ ከሆነ ግን የአቃቤ ሕግ ስራን ለመስራት ፈቃደኛ ነኝ ብዬ ለአቶ ዳዊት ዮሐንስ ነገርኩት፡፡ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ታምራት ላይኔ ነበሩ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጥቂት ቀናት ይደውሉልሃል፤ እናም ይሄንኑ እንድትሠራ ይጠይቁሃል በሚል አቶ ዳዊት ቃል ገባልኝ፡፡ ከዛ በኋላ ግን ከእነሱ ምንም ሳልሰማ ነገሩ የውሃ ሽታ ሆነ፡፡ በኋላ ግን ስሰማ ያዕቆብ ኢሕአፓ ስለነበረ ለተከሰሱ ሰዎች ፍትህ ለመስጠት ያዳግተዋል፡፡ በቂም በቀል ይነሳሳል በሚል ቦታው ለእኔ እንዳልተሰጠ ሰማሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በቅንጅት አመራሮች ውስጥ ዴሞክራሲ የሚባል ነገር የለም፡፡ አምባገነንነትና ለሥልጣን መጓጓት አለ፡፡ እነዚህ ነገሮች በወቅቱ ባይኖሩ ኖሮ ምርጫውን ተከትለው የሚመጡትን ችግሮች ሁሉ መጋፈጥ/መወጣት ይቻል ነበር የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ የእርስዎ አቋም ምንድነው?

ዶ/ር ያዕቆብ፡- ይህንን አስተያየት የሚሰጡት ስህተት ነበሩ ማለት አይቻልም፡፡ ግን ደግሞ ሌላም ሁኔታም አለ፡፡ እርግጥ እነዚህ ነገሮች በሙሉ ነበሩ፡፡ አንድ መዘንጋት የሌለበት ነገር ቢኖር እኛ እራሳችን ከጀርባችን ምን ዓይነት ሰዎች ነበርን? የሚለው ነው፡፡ ከጀርባችን በማርክሲዝም ሌኒንዝም ታንፀን የመጣን፣ ቅራኔዎች በውይይት ሳይሆን በመጠፋፋት መፈታት አለባቸው የሚል እምነት ይዘን የመጣን ሰዎች ነበርን፡፡ እናም ችግሮችን በውይይት ለመፍታት አመቺ ሁኔታ አልነበረም፡፡ የመጣንበት የፖለቲካ ባህል ችግሮችን በውይይት የሚፈታ አልነበረም፡፡ ይሄ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ እንደሚታወቀው የአመራሩ አባል ሁሉም ማለት ይቻላል መኢሶን፣ ኢሠፓ ወይም ኢህአፓ የነበረ ነው፡፡ ሁላችንም የየፓርቲያችንን ባህል ይዘን የመጣን ነን፡፡ እነኚህ ፓርቲዎች ደግሞ በጊዜው አስተሳሰብ እንደነበረው ሁሉ ችግሮች በውይይት ሳይሆን በመጠፋፋት ይፈቱ የሚሉ ነበሩ፡፡ እነዚህ ሁሉ ችግሮች ተደራርበው ከተባለው ከአምባገነንነት፣ ከሥልጣን ጉጉት ጋር ተደማምረው ለቅንጅት መፍረስ ምክንያት ሊሆኑ ችለዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከምርጫ በኋላ ፓርላማ እንግባ አንግባ በሚለው ውዝግብ እርስዎ ፓርላማ እንግባ የሚል አቋም ይዘው ነበር ይባላል፡፡ እውነት ነው?

ዶ/ር ያዕቆብ፡- በመጀመሪያ ፓርላማ መግባት የለብንም ብዬ ብዙ ስከራከር የነበርኩት እኔ ነበርኩ፡፡ ከብዙ ውይይት በኋላ ፓርላማ መግባቱንና ከተማውን መረከቡ የሕዝብ አደራ እንደመሆኑ መጠን ይሄንን ማድረግ አለብን፤ የሚል አቋም ይዤ ነበር፡፡ ይህ እንዲሆን ግን አንዳንድ ቅድመ ሁኔታዎች የምንላቸው ነገሮች መፍትሄ ማግኘት አለባቸው የሚልም አቋም ነበረኝ፡፡

በአንድ ወቅት ድርድሩ በተካረረበትና በተወጠረበት ወቅት ለአንዲት የአሜሪካ ዲፕሎማት ሌላው ቢቀር በምርጫ አካባቢ አንድ ዓይነት መግባቢያ ከመንግሥት ብታመጪልን እኔ ጓደኞቼን አነጋግሬ ፓርላማ የምንገባበት መንገድ ይፈልጋል፡፡ ይሄንን ሞክሪ ብያት ነበር፡፡

ስምንት ቅድመ ሁኔታዎች ነበር ያስቀመጥነው፡፡ ከስምንቱ አንዱ ብቻ ኢህአዴግ ይቀበል፡፡ የምርጫ ቦርድ ገለልተኝነት እንደሚሆን ማረጋገጫ ይስጠንና ወደ ፓርላማ የመግባቱ ነገር ጓደኞቼን ላሳምን እሞክራለሁ አልኩኝ፡፡ ሴትየዋ እሺ እሞክራለሁ ብላ ሄዳ ያነጋገረችውን አነጋግራ ስትመለስ ግን “ምንም ዓይነት መለሳለስ ላገኝ አልቻልኩም” አለች፤ ከዛ በኋላ ድርድሩም ውይይቱም ፈረሰ፡፡ እኛም በአቋማችን ፀናን፡፡ ወደ ፓርላማ ገብተን ከተማውን እንድንረከብ ያልኩት ቢያንስ ቢያንስ የዚህ የምርጫ ቦርድ ገለልተኝነት ብቻ ይረጋገጥልን የቀሩትን ሰባት ቅድመ ሁኔታዎች ፓርላማ ውስጥ ከገባን በኋላ እንወያይበታለን፡፡ የሚል አቋም ነበረኝ፡፡ በመንግሥት በኩል ስለምርጫ ቦርድ ሁኔታ ምንም ፍንጭ ሊሰጠን አልተፈለገም፡፡ ስለዚህ ድርድሩ ፈረሰ፡፡

ሪፖርተር፡- ዛሬ ላይ ሆነው ሲያዩት በወቅቱ የተወሰነው ውሳኔ ትክክል ነው ወይስ ብለው ያምናሉ?

ዶ/ር ያዕቆብ፡- እንግዲህ ዛሬ ላይ ሆኜ ሳየው ምን አልባት ፓርላማ ገብተን መሞከር ነበረብን እላለሁ፡፡ ፓርላማ ገብተን በሙከራ ደረጃ እንኳን የሚያሰራን ከሆነ መስራት፣ ሁኔታው የማያሰራ ከሆነ ጥለን ልንወጣ እንችል ነበር፡፡ እርግጥ ሁኔታው በጣም አስቸጋሪ ነበር፡፡ እንደሚታወቀው የከተማው በጀት ወደ ሌላ ቦታ እየተዛወረ፣ ኃላፊነቱም ወደ ሌላ ቦታ እየተቀየረ ነበር፡፡ አዲስ አበባን ብንረከብ የማያሰራ ሁኔታ ስለመኖሩ ብዙ ፍንጭ ነበር፡፡ ግን ያም ቢሆን የኢትዮጵያን ሕዝብ ፈቃድ ፈፅመን፣ ፓርላማ ገብተን ይኸውና መስራት አልቻልንም፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የራስህን ምርጫ ውሰድ፡፡ ሞክረናል፣ አቅቶናል መስራት አልቻልንም ብለን ያኔ ብንወስን የተሻለ ነበር፡፡ አሁን ሳየው የሰራነው ጥፋት ይህ ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ቅንጅትን ከፈጠሩት ፓርቲዎች ውስጥ በርካታ እጩዎችን ያቀረበውና በርካታ አባላትን ያስመዘገበው ፓርቲ የሚፈለገውን ቦታ አልተሰጠውም፤ እነዚህ ችግሮች ናቸው ፓርቲውን ወደ ከፋ ችግር የከተቱት የሚሉ ወገኖችም አሉ፤

ዶ/ር ያዕቆብ፡- ከዚህ በፊት በቅንጅትም ሆነ በራሱ ፓርቲ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረገ፣ ብዙ መስዋዕትነት የከፈለው አቶ ልደቱ አያሌው፣ ከምክትል ሊቀ መንበርነት ሊያልፍ አልቻለም፡፡ በርካታ አስተያየት ቢሰነዘርም እኔ እንደሚገባኝ አቶ ልደቱ ከፓርቲው ጋር መናቆር የጀመረው ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ይመስለኛል፡፡ ከዛ በፊት ከፓርቲ ጋር አብሮ ነበር የሚሄደው፡፡ በእውነት ሊካድ የማይቻል ብዙ መስዋዕትነት የከፈለ ሰው ነበር፡፡ ም/ሊቀመንበር መሆን ይገባኛል የሚል እምነት ነበረው፡፡ ከዚህ በፊት በትግሉ ብዙም የማትታወቀው ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በመመረጧ እኔ እንደገመገምኩት አቶ ልደቱ ቅሬታ እንደተሰማው ነው፡፡ አቶ ልደቱ ከፓርቲው መለየትና ከቅንጅት ተቃራኒ እርምጃ መውሰድ የጀመረው ከዚያ በኋላ ይመስለኛል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ከዚያ በፊት ብዙ የሚያወሩት ነገር አለ፡፡ እኔ ግን አልቀበለውም፡፡ እኔ የሚመስለኝ የአቶ ልደቱ ቂም የተጀመረው በምርጫው ይገባኛል የሚለውን ቦታ ባለመሰጠቱ ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ምክትል ሊቀመንበር መሆናቸው ትክክል አይደለም እያሉ ነው?

ዶ/ር ያዕቆብ፡- በእኔ በኩል ትክክል ነበረ ነው የምለው፤ ወ/ት ብርቱካን ተሞክሮዋ በፓርቲ ውስጥ ያደረገችው ትግል ብዙም የተመዘገበ ነገር ባይኖራትም፤ በጊዜው ለወጣቶችና ለሴቶች ጥሩ ማደፋፈሪያና ግሩም ምሳሌ ነበረች፡፡ በምክትል ሊቀመንበርነት ልታድግና ለወደፊቱ ሊቀመንበር ልትሆን የምትችል መሪ መሆኗን ያየንበት ነውና የምክትል ሊቀመንበርነት ምርጫው ትክክል ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- የአቶ ልደቱ ኩርፊያ ስህተት ነው?

ዶ/ር ያዕቆብ፡- እንግዲህ የአቶ ልደቱ ኩርፊያ ስህተት ነው ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ በእሱ ዓይን ሆነን ብናየው ብዙ መስዋእትነት የከፈለ፣ ብዙ አስተዋፅኦ ያደረገ ሰው ነው፡፡ እና ይገባኛል የሚል እምነት አለው . . .

ሪፖርተር፡- በቅንጅት ውሰጥ ያሉ ሰዎች ለእኔነት፣ ለዝናና ለክብር የሞቱ ናቸው ይባላል፡፡ እርስዎ እኔ እንዲህ ነኝ የሚሉት ነገር . . . .

ዶ/ር ያዕቆብ፡- እኔነትና ዝና ፍለጋ ነበር፡፡ ገንዘብ የሚፈልግ የፓርቲ አመራር ግን አልነበረም፡፡ በአብዛኛው ገንዘብ ያለን፣ ራሳችንን የቻልን ነን፡፡ የስልጣን ጥም ፍላጎት ግን አልነበረም ማለት አይቻልም፡፡ ይሄን ግላዊ ስሜት ለሀገርና ለሕዝብ ጥቅም ማስገዛት ይገባ ነበር፡፡ ይህ ማለት ቅንጅትን አስቀድሞ፤ አስፈላጊም ከሆነ ራስን ማግለል ይገባ ነበር፡፡ በእውነት ይሄም ሲባል በአመራር ደረጃ የነበሩት እኔ እስከማውቃቸው ድረስ ለሥልጣን የሞቱ፣ ለዝና የሚስገበገቡ ሰዎች ነበሩም ብዬም መመልከት እቸገራለሁ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለቅንጅት መድከምና መሞት ሌላ ምን ምክንያት አለ ማለት ይቻላል? የራስን ስሜት ለሕዝብና ጥቅም ሲባል ማስገዛት ያለመቻል ካልሆነ በስተቀር፡፡ ለቅንጅት መፍረስ ሌላ ምን ምክንያት ሊቀርብ ይችላል? እኔ ግራ ይገባኛል፡፡ አንዳንዶቹም በጣም ሀብታም የሚባሉ ሰዎች አሉ፡፡ ከስሜታቸውም የገንዘብ ፍቅር የነበራቸው ሰዎች አይደሉም እገሌ፣ እገሌ ማለቱ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ገንዘብ አይደለም ያሸነፋቸው እኔ የሚመስለኝ ያሸነፋቸው እልህ ነው፡፡ እገሌ ከእገሌ ጋር በመጣመድ “እሱ አያሸንፈኝም፤ እኔ ግን አሸንፈዋለሁ” የሚል ዓይነት እልህ መገባባት ይመስለኛል፡፡ አንዳንዶቹ ሥልጣንን ያዩ የቀመሱትም ነበሩ፡፡ የችግሩ መንስኤ በግለሰቦች መሃል ያለው አለመጣጣምና አለመግባባት ይመስለኛል፡፡ የግል ስሜትና የቂም በቀል እንጂ እነኚህ በአመራር ደረጃ የነበሩ ሰዎች በገንዘብም ሊታሙ የሚችሉ ሰዎች አይደሉም፡፡ የሥልጣን ጥም ያሰከራቸው ናቸው ማለትም አስቸጋሪ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እልህና ቂም በቀሉ የቱ ነው የነበረው?

ዶ/ር ያዕቆብ፡- መቼም እገሌና እገሌ ናቸው ማለት አልችልም፡፡ ከፍተኛ አመራር ውስጥ በነበሩ ሰዎች ውስጥ የሚንፀባረቅ ነበር፡፡ በከፍተኛ አመራር ውስጥ የነበሩ፣ በከፍተኛ ደረጃ በቂም፣ በጥላቻና በእልህ የሚፈላለጉ ሰዎች ነበሩ፡፡ ይሄ ደግሞ ቅንጅትን ካዳከሙት ውስጥ አንዱና ዋናው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እነዚህ ሰዎች እንዴት አንድ ላይ ሊደራጁ ቻሉ? ምንድን ነው ላያስማማቸው ያልቻለው? ቂም እና ጥላቻ ደረጃ እንዴት ደረሱ?

ዶ/ር ያዕቆብ፡- እንግዲህ ይሄ መቀያየምና መጠላላት የጀመረው ቆይቶ ነው፡፡ ከበፊት የተጀመረ አይደለም፡፡ ቀደም ሲል እንዲያውም ወዳጅ የነበሩና በጣም የሚቀራረቡ ናቸው፡፡ ኋላ ግን ቂሙ እየሰረፀ ነው የመጣው፡፡

ሪፖርተር፡- ምንድን ነው የቂሙ መነሻ?

ዶ/ር ያዕቆብ፡- ሥልጣኔን ቀማኝ ወይም ደግሞ አምባገነን ሆነብኝ የሚል ነው፡፡ ይሄ ደግሞ በሁለት ወይም በሦስት ሰዎች ብቻ ላይ የሚመሠረት አይደለም፡፡ ጠቅላላውን ቅንጅትን የዳሰሰ ጉዳይ ነው መጠላላቱ፣ ምቀኝነቱ በየደረጃው ያለ ስሜት እንጂ በከፍተኛ አመራሮች ደረጃ የተወሰነ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- የእርስዎ ስም ባይነሣም የኢንጂነር ኃይሉ ሻውልና የዶክተር ብርሃኑ ነጋ ችግር ቅንጅትን አደጋ ላይ ጥሎታል የሚሉ አሉ፤

ዶ/ር ያዕቆብ፡- እኔ ሙሉ ለሙሉ አልስማማም፡፡ እርግጥ የእነሱ ችግር ብዙ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- ፓርቲ መሪ እንጂ ተመሪ አይደለም፡፡ ቅንጅት ተመሪ ሆና ወደቀ የሚሉ የፖለቲካ ተንታኞች አሉ፡፡ ይስማሙበታል?

ዶ/ር ያዕቆብ፡- ይሄ ተአማኒነት ያለው አነጋገር ነው፡፡ ፓርላማ በመግባትና ላለመግባት ሕዝቡን እናነጋግር ብለን በተሰማራንበት ወቅት ከአንድ ቀበሌ በስተቀር “እራሳችሁ ወስኑ እናንተ የወሰናችሁትን እንከተላለን እንቀበላለን” ነው ያሉት፡፡ አንዳንዶቹ ግን “የእኛ ምርጫ ባትገቡ ነው፤ ግን እናንተ መሪዎች እንደመሆናችሁ እናንተ ወስናችሁ እንግባ የምትሉ ከሆነ እንከተላችኋለን” ብለዋል፡፡ ስለዚህ ከአንድ ቀበሌ በስተቀር ፓርላማ አትግቡ የተባልንበት ቀበሌ የለም፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ቅንጅት በወቅቱ የመሪነት ሚና ሳይሆን የተመሪነት ሚና ሲጫወት ነበር?

ዶ/ር ያዕቆብ፡- ይሄ ጥፋት ነው፡፡ መሪ መንገዱን አሳይቶ ሕዝቡን መርቶ ማሳመን እንጂ፣ ሕዝቡ በሚፈልገው መንገድ መጎተት የለበትም፡፡ መሪ የበለጠ ዕውቀት አለው ይባላል፡፡ ከተራው ሕዝብ የተሻለ ግምትና የተሻለ አስተሳሰብ ሊኖረው ይችላል፡፡ ስለዚህ ሕዝቡን የመምራት ግዴታ አለበት፡፡ ሕዝቡ አንድ ሀሳብ አቅርቦለት ያን ሀሳብ እንዲቀበል ማሳመን እንጂ፣ በፖለቲካው በቂ ግንዛቤና ዕውቀት የሌለውን ሕዝብ የወሰነውን ውሳኔ መከተል የለበትም፡፡ ይሄ የአመራር ድክመት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የሕዝብ አደራ በጥፋትና በድክመት ተሳቦ መቅረት አለበት?

ዶ/ር ያዕቆብ፡- ከቃሊቲ ከወጣን በኋላ አስራ አንድ የአውሮፓ አገሮችን ጎብኝተናል፡፡ በቡድን ሆነን አሜሪካም በቀረብኩበት መድረክ ሁሉ እኛ የአመራር አባላት የሕዝቡን ልብ በመስበር፣ ሕዝቡን በማስቀየም ለተሰጠን እምነትና ድጋፋ ብቁ ሆነን ባለመገኘታችን በተገኘሁበት መድረክ ሁሉ ይቅርታ ጠይቄያለሁ፡፡ ዛሬም ማንንም አልወክልም . . . . . ለሥልጣን ጉጉት ወይንም ፓርላማ ለመግባት አይደለም፡፡ ሕዝቡ ለጣለብንን አመኔታ ብቁ ሆነን ባለመገኘታችን ጥፋት ሰርተናል፡፡ እኔ በመፅሐፍም ሆነ በሕይወት ተሞክሮዬ አንድ ፓርቲ እንዲህ ዓይነት የሕዝብ ድጋፍ ሲኖረው አይቼም፣ ሰምቼም፣ አንብቤም አላውቅም፡፡ ለእዚህ ታላቅ ድጋፍ፣ አደራ፣ ውክልና ብቁ ሆነን አልተገኘንም፡፡ አዝናለሁ፡፡ እድሜዬን በሙሉ የሚቆጠቁጠኝ ነገር ሆኖ ይኖራል፡፡

ሪፖርተር፡- እስር ቤት እንኳን ተማምናችሁ ተስማምታችሁ አልወጣችሁም ከእስር ስትፈቱ ወዲያው መጣላታችሁን ያዩ እንኳንም መንግሥት ያልሆኑ ብለዋል፡

ዶ/ር ያዕቆብ፡- እስር ቤት በዚያች በጠባብ አካባቢ ለ18 ወር አብረን በቆየንበት ጊዜ አንዳንድ ግላዊ መናቆሮች ነበሩ፡፡ ይሄ ግን ወደ ፓርቲ የዘለቀ አልነበረም፡፡ አነስተኛ የሆነ የግለሰቦች መቀያየምና መነቋቆር ታይቷል፡፡ እርግጥ ይሄ ከእስር ከወጣን በኋላ በሁለት ቡድን ተከፋፍለን ግማሾቻችን አውሮፓ፣ ግማሾቻችን ደግሞ አሜሪካ በሄድንበት ወቅት ተከስቷል፡፡ ለሆነው ነገር ሁሉ የምወክለው ፓርቲ የለም፤ በግሌ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ ጠይቄአለሁ፡፡ በአመራር ውስጥ የነበርን ሰዎች ሁሉ ሕይወታችንን የሚቆጠቁጠን ነገር ተፈፅሟል፡፡ ለኢትዮጵያ አንድ ጮራ ፈንጥቆ ነበር፡፡ አገራችን ልዩ አቅጣጫና መንገድ ትይዝ ነበር፡፡ ሁሉም ነገር ያልተሳካውና የመከነው ደግሞ በእኛ በአመራሮቹ ጥፋት እንጂ ከሕዝቡ ድጋፍ በማጣት አይደለም፡፡ ወይንም ደግሞ በባላንጦቻችን ጥንካሬ አይደለም፡፡ በእኛ ድክመት ብቻ ነው፡፡ አመቺ በሆነ ጊዜ ሁሉ የኢትዮጵያን ሕዝብ ተንበረክከን ይቅርታ መጠየቅ ይኖርብናል፡፡

ሪፖርተር፡- ፖለቲካ እኮ ነው?

ዶ/ር ያዕቆብ፡- እንግዲህ ምን ይደረጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ግን ከአሁን በኋላ ያ መንፈስ የሚመለስ ይመስልዎታል? በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የ1997ቱ የምርጫ መነቃቃት ዳግም አይታይም የሚሉ አሉ፤

ዶ/ር ያዕቆብ፡- በእውነት አስቸጋሪ ነው፤ በቅንጅት የነበረው መንፈስ እንደገና እንዲያንሰራራ ጊዜ የሚወስድ ይሆናል፡፡ ምንአልባት ከ5 ዓመት ወይም ከ10 ዓመት ከዛም በላይ ሊወስድ ይችላል፡፡ ምክንያቱም እንዲህ ዓይነት ሁኔታ በየቀኑ አይከሰትም፤ ሕዝብ በእኛ ምክንያት ቆስሏል፡፡

ሪፖርተር፡- ከእስር ቤቱ ከወጣችሁ በኋላ የቅንጅት ሕጋዊ መብት በምርጫ ቦርድ ተቀባይነት ይኑረውም አይኑረውም እንዲገፋፋ ተደርጎ ለሌላ ከተሰጠ በኋላ አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ተቋቁሟል በዚህ የቀድሞ ስህተታችሁን ገምግማችሁ ነበር?

ዶ/ር ያዕቆብ፡- የቅንጅትን ተሞክሮ አንስተን የተነጋገርነው ነገር የለም፡፡ መጀመሪያ ሀሳቡን ያመጣችው ወ/ት ብርቱካን ነች፡፡ የቅንጅት ወራሽ ነን በሚለው ተስማማን፡፡ የቅንጅት መንፈስ ይዘን እንጓዛለን የሚል እምነትና ፍላጎት ነበረን፡፡ አንዳንዶቹ አሁንም የቅንጅት መንፈስ ይዞ እየተጓዘ ነው የሚል እምነት አላቸው፡፡ በእውነት አንድነት ፓርቲ በሂደት በተወሰነ ጊዜ ቅንጅትን ሊተካ፣ የቅንጅትን መንፈስ ይዞ ሊሄድ ይችል ነበር፡፡ በመንገዱ ግን ብዙ እንቅፋቶች ነበሩት፡፡ በተለይ የሊቀመንበሯ የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ መታሰር ይሄን የአንድነት ፓርቲ ሂደት በከፍተኛ ደረጃ አደናቅፎታል፡፡ በፓርቲ ውስጥ መከፋፈል ተፈጥሮ የተለመደው መናቆርና መጠፋፋት እየቀጠለ ነው፡፡

ምናልባት ሕዝቡ ቂሙን ረስቶ በቅንጅት ለተፈፀመበት በደል ይቅርታ ብሎ፣ ሌላ ትውልድ ተክቶ ቅንጅት አስመዝግቦት የነበረውን ድል እንደገና ለማስመዝገብ የኢትዮጵያ ወጣት ችሎታ ቢኖረውም በአሁኑ መልክ ግን ሊሳካ አይችልም፡፡ የኢትዮጵያ ወጣት አንፀባራቂ የሆነ የትግል ታሪክ አለው፡፡ ከፊውዳሊዝም ጋር ተዋድቋል፡፡ ከፋሺዝም ጋርም ተዋድቋል፡፡ አሁንም ሁኔታውን ለመለወጥ ብዙ ትግል እያካሄደ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ወጣት ላይ ከፍተኛ እምነት አለኝ፡፡ አሁንም፣ የአሁኑ ወጣት እንደቀድሞዎቹ ኃላፊነቱን ይዞ ሀገሪቱን ወደ ዲሞክራሲ፣ ወደብልፅግናና ልማት ያመራል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ዛሬ በአንድነት ፓርቲ ውስጥ ለተፈጠረው ችግር ትልቁ ምክንያት ምንድነው ብለው ነው የሚያምኑት?

ዶ/ር ያዕቆብ፡- ቀደም ሲልም ሆነ አሁን አንድ መረሳት የሌለበት ትልቅ ጉዳይ አለ፡፡ ኢህአዴግ ቅንጅትን ለማፍረስ የራሱን ሚና ተጫውቷል፡፡ የሚጠበቅም ነው፡፡ በሰላማዊ መንገድ ለሥልጣን የምንራኮት ኃይሎች ነበርን፡፡ እናም ኢህአዴግም አልተኛልንም፡፡ ቅንጅት እንዲፈርስ ትልቁ ድርሻ የኢህአዴግ አስተዋፅኦ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለቅንጅት መፍረስ የእኛም ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ተናግሬያለሁ፡፡ አሁንም ቢሆን አንድነት ፓርቲ የተፈጠረው ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ኢህአዴግ ምን አደረገ?

ዶ/ር ያዕቆብ፡- ወ/ት ብርቱካንን አሰረ፡፡ በየአካባቢው የፓርቲው ንቁ ተሳታፊዎችና በወረዳ አመራር ደረጃ የነበሩትን ብዙዎቹን አስሯል፡፡ አንገላቷል፡፡ ስብሰባ ለማካሄድ እንኳን አይፈቀድልንም፡፡ የፓርቲውን ሊቀመንበር እስር ቤት ከመወርወር ሌላ ምን ያድርግ?

ሪፖርተር፡- አንድነት ጠንካራ ተቃዋሚ ሆኖ መቀጠል ሲገባው የእርስ በርስ ሽኩቻ ውስጥ ገብቷል፡፡ የፕሮፌሰር መስፍን ወገኖችና የአንድነት አመራሮች መሠረታዊ ልዩነት በእርስዎ እምነት ምንድነው?

ዶ/ር ያዕቆብ፡- መሠረታዊው ችግር ፍርጥርጥ አድርጎ በግልፅ አለመወያየት ነው፡፡ በግልፅ ጠረጴዛ ዙሪያ ልዩነትን አስቀምጦ፣ አፍረጥርጦ መናገር አለመቻል፣ እገሌ ይቀየመኛል፣ ይጣላኛል፣ በሚል ፍርሃትና የባህል ተፅዕኖ ሳቢያ፣ እያንዳንዳችን በጀርባችን ያዘልነው የቀደመው አመለካከት ሁሉ ተደማምሮ በግልፅ ለመወያየት አለመቻል ነው ዋናው ምክንያት የሚመስለኝ፡፡ በእውነት ለእኔ የገባኝ የሚያጣላና የሚያለያየው ነገር ይሄ ነው ማለት አልችልም፡፡

ሪፖርተር፡- የፓርቲው አመላመል የፓርቲው ምስጢር እንዲወጣ አድርጓል ይባላል?

ዶ/ር ያዕቆብ፡- የአንድነት ፓርቲው አመላመል ራሱ በጣም ልቅ ነው፡፡ ፎርም በመሙላት ብቻ የፓርቲ አባላት የሆኑ ሰዎች አሉ፡፡ አባላት ሲመለምሉ ጀርባቸው ሳይፈተሸ ዝም ብለው አባል የሆኑ አሉ፡፡ በዚህ ክፍተት ኢህአዴግ የሚችለውን መስራቱ የማይቀር ነው፡፡ መረጃ የሚያወጡ ተደርሶባቸዋል፡፡ ቢሆንም ግን ሙሉ በሙሉ የቆመ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ ምክትል ሊቀመንበር ነዎት? እርስዎ ይሄ እንዳይሆን ይከላከሉ ነበር? አባል ስንመለምል ሰርገው እንዳይገቡብን እንዲህ እናድርግ ብለው ያውቃሉ?

ዶ/ር ያዕቆብ፡- ምንም አላልኩም፡፡ የኔ ስራ ብዙ ጊዜ ከውጭ ግንኙነት ጋር ስለነበረ የድርጅት ጉዳይ፣ የፓርቲ ምልመላ ጉዳይ፣ እነዚህን ሁሉ የሚመለከታቸው ሰዎች አሉ፡፡ የእነሱ ተግባር ነው በሚል፡፡ ነገሩ ይመለከተኛል ማለት ነበረብኝ፡፡ ጥፋት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአብዛኛው የስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ላይ አይገኙም፡፡ ይቀራሉ፡፡ ምክንያቱ ምንድን ነው?

ዶ/ር ያዕቆብ፡- የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ወይም የምክር ቤት ሰብስባ መቅረት የጀመርኩት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው፡፡ ይህም ራሴ የወሰንኩት ነው፡፡ በፖለቲካው መድረክ ብዙ ጊዜ ስለቆየሁ ለሌሎቹ እድል መስጠት ይገባል፡፡ ወጣቶች መተካት አለባቸው የሚል ፅኑ እምነት አለኝ፡፡ ዛሬ ጊዜው የተለየ ነው፡፡ ጊዜው የዴሞክራሲ ነው፡፡ የመወያያና የመነጋገሪያ ጊዜ እንጂ የመጠፋፊያና የመነቋቆሪያ ጊዜ አይደለም፡፡ የመጠፋፊያ ባህል ያልተጠናወታቸው ሰዎች ሥልጣን ላይ መውጣት አለባቸው፡፡

ገዢው ፓርቲ ይበልጥ አክራሪና አናቋሪ ፓርቲ ነው፡፡ ከሁሉም የበለጠ ገዢው ፓርቲ የድሮ ማርክሲስቶችን አስወግዶ ወጣቶችን መተካት አለበት፡፡

ለሀገሪቱ ሰላምና እድገት አስተማማኝነት ከተፈለገ በማርክሲዝም ሌኒንዝም ታንፀው ስር ሰደው የመጡ ሰዎች በሙሉ ከየትኛውም የፖለቲካ አመራር መውጣት አለባቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ራሳቸው መጀመሪያ ከሁሉ ሰው በፊት ሥልጣናቸውን መልቀቅ አለባቸው፡፡ እሳቸው የማርክሲስት ሌኒኒስት አደገኛ አክራሪ የነበሩ ናቸው፡፡ አሁን ከማየው አንፃር ሙሉ በሙሉ ተቀይረዋል፡፡ የሚል እምነት የለኝም፡፡ የሀገሪቱ ፖሊሲ በአብዛኛው የሶሻሊስት ፖሊሲ አቀንቃኝ ነው፡፡ የንብረት አያያዝ፣ የመሬት ባለቤትነት ከተመለከትን የኮሚኒስት ሥርዓት ነው፡፡ ብዙ ድርጅቶች በመንግሥት እጅ ናቸው፡፡ ይሄ ደግሞ የኮሚኒስት ሥርዓት ገፅታ ነው፡፡ ዴሞክራሲን ማፈን፣ የንግግር ነፃነትን ማፈን፣ የኮሚኒስት ሥርዓት መመሪያ ነው፡፡ በሀገራችን እነዚህ ሁሉ አሉ፡፡ ስለዚህ አሁን ሀገራችን በብዙም ባይሆን በከፊል ሶሻሊስት ናት ማለት ይቻላል፡፡

ዘመኑ የሊበራል ዲሞክራሲ በመሆኑ እነዚህ በኮሚኒስት የታነፁ ሰዎች ቦታውን መልቀቅ አለባቸው፡፡ ይሄ ሩሲያና በምስራቅ አውሮፓም ሆኗል፡፡ በኮሚኒዝም የታነፁ ሰዎች ሁሉ ለቀው፣ ዛሬ ከኮሚኒዝም በኋላ የተወለዱ፣ ኮሚኒዝም ሊያበቃ ሲል የተወለዱ ትውልድ ነው የሥልጣን ባለቤት የሆኑት፡፡

የሩሲያ መሪ ሃምሳ ዓመት አልሞላቸውም፡፡ የአሜሪካንም ብንወስድ አርባ ስምንት ዓመታቸው ነው፡፡ ምስራቅ አውሮፓም ተመሳሳይ ነው፡፡ ሁሉም ወጣቶች ናቸው፡፡ ኮሚኒዝም ከተዳከመ በኋላ ያደጉ ሰዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ በአዲስ ትውልድ፣ በአዲስ አስተሳሰብ አመራሮቻቸው ተክተዋል፡፡ ኢትዮጵያውያንም ይህንን ፈለግ መከተል አለብን፡፡ የአገራችን ወጣቶች ለዚህ ይሰንፋሉ አልልም፡፡ አኩሪ የሆነና አንፀባራቂ ታሪክ አላቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ጠቅላይ ሚኒስትር መለስን የሚተካቸው ሰው የለም የሚሉ አሉ፡፡ ፓርቲያቸው በተለይ ያለእሳቸው የሚል እምነት አለው፤

ዶ/ር ያዕቆብ፡- ፈረንጆቹ ይሄንን ዓይነቱን ነገር ካሳይኮፋንትካ (Sycophant) ይሉታል፡፡ ባዶ ነገር የሚናገሩ አሞጋሾች የሚሉት ነው፡፡

ይሄ አሞጋሾች የሚሉት ነገር ነው፡፡ ማንም ማንንም ይተካዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስም ሰው ናቸው፡፡ በግል ችሎታቸውም ቢሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚመጥናቸው ኢትዮጵያዊ የለም ማለት ኢትዮጵያውያንን ሁሉ መስደብ ነው፡፡ ደግሞ የሲስተም ጉዳይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በቃኝ እያሉ ነው? ለምን? ሽሽት ወይስ መሰላቸት?

ዶ/ር ያዕቆብ፡- አዎን” አሁን እኔ በቅቶኛል፡፡ ይሄም ማለት ከትግል ሜዳ እወጣለሁ ማለት አይደለም፡፡ በፓርቲ አመራርነት ግን አልቀጥልም፡፡ ደብዳቤም አስገብቻለሁ፡፡ ለደብዳቤው ገና ምንም ምላሽ አላገኘሁም፡፡ ምላሹም ደግሞ ተቀባይነት እንደሚያገኝ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ምክንያቱም የበቃኝ ጉዳይ ነው፡፡ በሌላ ደረጃ ልሰራ እችላለሁ፡፡ በአማካሪነት ልሰራ ላማክር እውቀቱ ካለኝ ችሎታው ካለኝ የማውቀው ነገር ከሆነ ለማማከር ዝግጁ ነኝ፡፡ ሌላም የፅሑፍ ስራም አስፈላጊ ከሆነ ልሰራ ዝግጁ ነኝ፡፡ ግን በአመራሩ ደረጃ ከአሁን በኋላ አላደርገውም፡፡

ሪፖርተር፡- በፖለቲካው መስመር ካልሆነ በምን መልኩ ሊታገሉ አስበዋል?

ዶ/ር ያዕቆብ፡- ለአገር ዕድገትና ልማት በየአቅጣጫው መስራት ያስፈልገዋል፡፡ ንግድም ላይ እንኳን ብሰማራ ለአገር ዕድገት ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ አንዳንድ ትንንሽ ነገሮችንም ብፅፍ እሱም ለአገር አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡ እንዲሁም በምፈለግበት አካባቢ እንዲህ ዓይነት የተወሰነ ስራ ብባል ለመስራት ዝግጁ ነኝ፡፡ እኔ ሙሉ በሙሉ ከፖለቲካ ወጥቻለሁ አልልም፡፡ ማንም ከፖለቲካ ሊወጣ አይችልም፡፡ ከፖለቲካማ አይሸሽም፡፡ ፖለቲካ ልሽሽህ የሚባል ነገር አይደለም፡፡

ሰው የፖለቲካ እንስሳ ነው ይባላል፡፡ ከፖለቲካ ልወጣ አልችልም፤ ከብዙ ጊዜ ጀምሮ የያዝኩት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በተደጋጋሚ ኢህአዴግ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊረሳው የማይችለውን ታሪካዊ ስህተቶች ሠርቷል ብለው ሲናገሩ ይሰማል፡፤ እነዚህን ነገሮች የመታገያ ስልቶችም አድርገው ይቀጥላሉ?

ዶ/ር ያዕቆብ፡- ኢትዮጵያን የባሕር በር የማሳጣት ጉዳይ ዋናው ነው፡፡ አሰብን የማጣቱ ጉዳይ መቼም ቢሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚረሳው ጉዳይ አይሆንም፡፡ እኔም አቅሜ በፈቀደ፣ በሌሎችም እንቅስቃሴ የምተወው አይደለም፡፡ የባሕር በር መዘጋት የኢኮኖሚ ጥያቄም ብቻ አይደለም፣ የፀጥታም ጉዳይ ነው፡፡ ማንኛውንም ኢትዮጵያዊ ኢህአዴግ የሰራው ትልቅ ስህተት ምንድነው? ተብሎ ቢጠየቅ የባህር በር መዝጋቱ ነው የሚል መልስ እንደሚሰጥ ጥርጥር የለውም፡፡ አሰብ የኢትዮጵያ ሉአላዊ ግዛት ናት፡፡ ለዚህ ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡ ይሄ መንግሥት ሊያሰከብር የሚችለው የነበረ፣ ነገር ግን በድክመቱና በማንአለብኝነቱ ለቆት እንጂ አሰብ የኢትዮጵያ አካል ነበረች፡፡

ከስዊድንና ከጀርመን አምባሳደሮች ጋር በጊዜው ስለ አሰብ አንስተን ስንነጋገር በአሰብ ላይ ኢትዮጵያ ጥያቄ ብታነሳ የጀርመንና የስዊድን መንግሥት ይደግፉት ነበር ብለዋል፡፡ ዛሬ የዓለም አስተሳሰብ አብዛኛው እንደዚህ ነው፡፡ በአንድ ወቅት አሜሪካ አሰብ ወደ ኢትዮጵያ መታጠፍ ይገባዋል በሚል በተመድ ጽ/ቤት ፊት ለፊት ሰላማዊ ሰልፍ አደረግን፡፡ የፀጥታ ም/ቤት አባላትን ለማነጋገር ተከፋፈልን፡፡ እኔ የፈረንሳይና የአሜሪካ የፀጥታ ም/ቤት አባላትን አገኘሁና ስንጠይቃቸው ያሉት መንግሥታችሁ አልጠየቀንም፤ እኛ እንዴት አድርገን እንጠይቅና እንደግፍ፤ መንግሥታችሁ ቢጠይቅ ኖሮ ይሆን ነበር የሚል መልስ ስጡኝ፡፡

መንግሥታችሁ አሳልፎ የሰጠውን ነገር እኛ በምን መልኩ እንቃወማለን ብለው አሉ፡፡ በተለያዩ መድረኮች ከውጭ ሀገር ሰዎች ጋር ተነጋግሬአለሁ፤ ከወደብ የስድስት ሰዓት ርቀት ላይ ሆነን የባህር በር ተዘግቶብናል፤ ስንል የሚያምን የለም፡፡ ብዙ ሕዝብ እያላት የባህር በር የሌላት አገር ኢትዮጵያ ናት፡፡

መፍትሄ ካልተገኘለት ለትውልድ የሚቀር ቁስል ነው፡፡ ማንም ኢትዮጵያዊ የሚለቀው አይደለም፡፡ በ60 ኪ.ሜ. ርቀት ታፍነህ ሙት የሚል ሕግ የለም፡፡ በሠላማዊ መንገድ እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ በመደራደር ቢሆን ተስፋ እናደርጋን፡፡ ሌሎችንም ብዙ መፍቻ መንገዶች አሉ፡፡ ለሰላምና ለዕርቅ ሲባል ምናልባት መሬት ማሸጋሸግ ይቻላል፡፡ ለኤርትራውያኑ የእርሻ መሬት ሰጥቶ አሰብን ሊሰጡን ይችላሉ፡፡ ለሰላም ሲባል እንጂ ሃብትነቱ በመርህ ደረጃ የኢትዮጵያ ነው፡፡

ሁለተኛው የኢህአዴግ ስህተት ብዬ የምቆጥረው፣ ሕዝቡን በብሔረሰብ መከፋፈል ነው፡፡ ይሄ ሲባል ግን በቅድሚያ ላስጠነቅቀው የምፈልገው ብሔረሰቦች የራሳቸውን ቋንቋ የመናገር፣ ባህላቸውን የማክበር፣ ታሪካቸውን የማሳወቅ፣ የውስጥ አስተዳደራቸውን የመምራት መብት አላቸው፡፡ አሁን ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው ብሔረሰብ ተከፋፍሎ ከዚህ በፊት ባልታየ መልኩ ምንአልባት አንድ ሳምንት በማይሞላ ጊዜ የብሔረሰቦች ግጭት በተለያዩ አካባቢዎችና የትምህርት ተቋማት፣ ወጣቶች በብሔረሰብ እየተቧደኑ ብዙ ጊዜ ጉዳት የደረሰበት ሁኔታ አለ፡፡ የሰንደቅ ዓላማ ባህል በተከበረበት ወቅት አንድ ጥፋት አስተውያለሁ፡፡ ሕፃናት “ሰንደቅ ዓላማ ምን ማለት ነው?” ተብለው ሲጠየቁ የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት፣ በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ አንድነት ማለት ነው እያሉ የተነገራቸውን ይመልሳሉ፡፡ እንግዲህ አንድ ትውልድ ኢትዮጵያ በብሔር ብሔረሰብ የተከፋፈለች አገር ናት ብሎ እያደገ ነው ማለት ነው፡፡ ከአፋቸው እነዚህ ሕፃናት አንድ ጊዜ ኢትዮጵያ ሲሉ አልሠማሁም፡፡ ይህ አደገኛ አካሄድ ነው፡፡

አንድ ሰው “ትልቅ አገር ተከፋፍሎ ትንሽ ይሆናል፤ ትንሽ አገር ደግሞ ተባብሮ ትልቅ ይሆናል” ብሏል፡፡ አሁን እኔ ስጋቴ የወደፊት ኢትዮጵያ እኛ የምናውቃት ሆና ትቀጥላለች ወይ . . . . . አንድ ብሔረሰብ ከአንድ መንግሥት ጋር ውል የመፈራረም መብት የለውም፡፡ አሜሪካ ግን ይደረጋል፡፡ አሜሪካ የተዋሃዱት እኮ ሉአላዊ ሀገር የነበሩ ናቸው፡፡ አሜሪካ እያንዳንዱ ስቴት ከሌላ መንግሥት ጋር ውል መፈራረም ይችላል፡፡ ከዛ ሌላ እኔ የማውቀው አገር የለም፡፡ በኢትዮጵያ አንዳንድ ብሔረሰቦች ወደ ሀገርነት እያመሩ ነው፡፡ የራሳቸው ልዩ ሀገር እየሆኑ ነው፡፡ ቀስ በቀስ ወዴት እየተኬደ ነው? ይህ ታሪካዊ ስህተት ነው፡፡ ስለታሪካዊ ስህተት ካነሳን ቅንጅትን ማፍረስም ሌላ የታሪክ ጉዳይ ነው፡፡