Over 15,000 people attended Aleqa Ayalew's funeral

Ethiopian eminent scholar and theologian Aleqa Ayalew Tamiru was buried on Thursday at Tekle Haimanot Church in Addis Ababa in the presence of over 15,000 people. Read the full report below in Amharic by an Ethiopian Review correspondent in Addis Ababa:


የአለቃ አያሌው የቀብር ስነ ስርዓት በተክለ ኃይማኖት ቤ/ክርስቲያን ተከናወነ፡፡


የአቡነ ጳውሎስን ስርዓት ከእምነትነቱ ይልቅ የካድሬ ስራ የሚሰራበት ነው በማለት በተቃውሞ ሰማዕት ሆነው የኖሩት አለቃ አያሌው ሕይወት ካለፈ በኋላ ሐሙስ ነሐሴ 17 ቀን 1999 ዓ.ም በአቡነ ተክለ ኃይማኖት በተከናወነው የቀብር ስነ ስርዓታቸው ላይ ቁጥሩ ከ15 ሺህ በላይ የሚገመት ሕዝብ ቢገኝም ካህናቱና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በዝማሬ አስክሬናቸውን ሳያጅቡ ቀሩ፡፡ በተጨማሪም የድምፅ ማጉያ እንኳን ሳያወጡ የቤተ መቅደሱን በር ዘጋግተው ጠፉ፡፡

የአለቃ አያሌው የቀብር ስነ ስርዓት በደብረሊባኖስ ገዳም ይፈፀማል ተብሎ የነበረ ሲሆን አዲስ አበባ በሚገኘው ተክለ ኃይማኖት ቤ/ክርስቲያን እንደሚፈፀም ከተሰማ በኋላ ቤተሰቦቻቸው፣ ተከታዮቻቸውና ኃዘን የተሰማቸው በሙሉ በስፍራው ተገኙ፡፡

እንኳን ለአለቃ አያሌው ይቅርና አቅሙ የጎለበተ ባለኃብት ሲሞት በቤተክስቲያኑ የሚገኙ ካህናትና ወጣቶች ልብሳቸውን ለብሰው አስክሬን ሲያጅቡና ፍታት ሲፈቱ ይስተዋል የነበረ ሲሆን በእለቱ ግን የአለቃ አያሌው የቅርብ ወዳጆች የሆኑ ካህናት ብቻ በቤታቸው ፍታት አድርገውለላቸዋል፡፡

በቀብሩ ቦታ የነበሩ አንዳንድ የእምነቱ ተከታዮች እንደተናገሩት “ምድረ የቤተ ክህነት ሰራተኛ ዛሬ ካድሬነቱ ታወቀ፡፡ የአለቃ አያሌው አስክሬን መሸኘት ያለበት በዚህ መንገድ ነበር? ምንም አይደለም ለሁሉም አንድ ቀን ያስተዛዝባል” ሲሉ ተሰምተው ነበር፡፡

የአለቃ አያሌው የበኩር ልጅ ወ/ሮ ስምረት አያሌው ስለሁኔታው ሲናገሩ “አባታችን አሁን ባለው የአባ ገ/መድህን (አቡነ ጳውሎስ) አስተዳደር ስር ያሉ ካህናት ፍትኃት እንዳያደርጉልኝ በማለታቸው ከልክለናል፡፡ ይህን ያደረግነው የአባታችንን ቃለ ውግዘት ለመጠበቅ ስንል ነው፡፡ ያስተላለፈውን ቃለ ውግዘት የሚያከብሩና የሚፈፅሙ በርካታ ምዕመናን አሉ፡፡ የቀብር ስርዓቱ በነሱ ይፈፀማል፡፡” በሚል ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡

የዳግሚት ደብረሊባኖስ ደብረአሚን ፃድቁ አቡነ ተ/ኃይማኖት ምክኃ ድንግል ሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በበኩላቸው የደንብ ልብሳቸውን ለብሰው ካህናቱም ልብሰ ተክህኖአቸውን አድርገው አለቃ አያሌው መኖሪያ ቤት መሄዳቸውንና ቤተሰቦቻቸው ቃለውግዘታቸውን ለመጠበቅ ሲሉ ፍታት አታደርጉም ብለው እንደመለሷቸው ተናግረዋል፡፡ አንዳንዶቹም “እኛ ቃለ ውግዘታቸው ይጠበቅ ብለን እንጂ ከፓትሪያርኩ ጋር አብረን አይደለም አስክሬኑን ያላጀብነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የአለቃ አያሌው ደጋፊዎች ግን በዚህ አይስማሙም፡፡ ምንም እንኳን ቤተሰብ ቃለውግዘታቸውን ለመጠበቅ ቢከለክል ካህናቱም ሆነ ወጣቶች ልብሳቸውን እንደለሰቡ የቀብር ስርዓቱ ላይ መገኘት ይችሉ እንደነበር፤ እነሱ ግን ከዚህ ይልቅ ቤተ መቅደሱን ጠርቅመው መሄዳቸው ከኃይማኖት አስተማሪነታቸው ካድሬነታቸው እንደሚብስ ነው ያሳዩት ብለዋል፡፡

በቀብር ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት እንደታዘቡት ቤተ መቅደሱ ተጠርቅሞ ተዘግቷል፡፡ ለአለቃ አያሌው ቅኔ የሚቀኙ ወዳጆቻቸው የድምፅ ማጉያ አጥተው በቀበሌ ስብሰባ መጥሪያ ማይክራፎን ሲቀኙ ተስተውሏል፡፡

በዕለቱ በርካቶች በለቅሶ ኃዘናቸውን ይገልፃሉ፡፡ ከቤተክርስቲያኑ አናት በሚገኘው ጉልሏት አጠገብ ባለው መስታወት አንድ ሰው መጋረጃውን ገልጦ ወደህዝቡ ሲመለከት ታየ፡፡

ማን ይሆን? በሚል ይህን የተመለከትን ስንነጋገር የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ እንደሆኑ የተገመቱ ሰው መሆናቸው ታወቀ፡፡ በኋላም በተደረገው ማጣራት ካህናቱ ህሊናቸው እያወቀ የአለቃ አያሌው የቀብር ስርዓት ከውጭ እየተፈፀመ እነሱ ከውስጥ ሆነው የቤተመቅደሱን በር ጠርቅመው ቁጭ ብለዋል፡፡

ሊቀ ኅሩያን በላይ መኮንን በርካታ ቅኔ ለአለቃ አያሌው የተቀኙላቸው ሲሆን ከቅኔው መካከልም

የሦስት ሺህ ዓመት ታሪክሽን
እንደ ጁሊያን ቆጥሮ
በባህር ሀሳብ አትቶ በአቡሻ ክር ተምሮ
ታሪክ ከታሪክ አጣቅሶ
መፅሐፍ አመሳክሮ
ሳያስረዳን ወግ ባህልሽን አበጥሮ
ጥንተ ታሪክሽን አንጠርጥሮ
የተላቁ ሊቅ ያ አንደበቱ ታስሮ
በአምዓትሽ ዋዜማ
በሚሌኒየም ከተማ
አራት አይናውን አያሌውን ካጣነውማ
ምኑን ባተልን እማማ?

ሲሉ ተቀኝተውላቸዋል፡፡

በመጨረሻም ለወ/ሮ ስምረት በተሰጣቸው እድል “አለቃ አያሌው የተበላሸውን የቤተክህነት ስርዓት እየታገሉ ያለምንም ደም ሰማዕት እየከፈሉ እዚህ አድርሰዋል፡፡ አሁንም ይሄን ተጋድሎ የሚመራና ለውጤት የሚያበቃ እንዲሰጠን እግዚአብሔር ልንለምነው ይገባል” ብለዋል፡፡

በአለቃ አያሌው ቀብር የእሳቸው ዘመድና ጓደኛ ከሆኑ አንድ ካህን በስተቀር አንድም የጠቅላይ ቤተክህነት መንበረ ፓትሪያርክ ሰራተኛ አለመገኘቱን ለመታዘብ ችለናል፡፡