አመቱን ሙሉ ሲዘፈንለትና ሲነገርለት በነበረው የኢትዮጵያውያን ሚሌኒየም በዓል ላይ ቢያንስ ሕዝብን ሊያሳትፉ ይችላሉ ተብለው የታሰቡት የመስቀል አደባባይ ዝግጅቶች ከፀጥታ ጋር በተያያዘ ችግር ሊፈጠር ይችላል በሚል የስጋት ሰበብ ተሰረዘ፡፡ የበዓሉን ዝግጅት ያዘጋጃል በሚል ተቋቁሞ የነበረው የሚሌኒየም በዓል አከባበር ምክር ቤትም በመጨረሻ ከአንድ የዋዜማ ዝግጅት በስተቀር ሌላውን አመቱን ሙሉ ነው የምሰራው ሲል አስታውቋል፡፡
ከአቶ መለስ አንደበት ከ500 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ከውጭ ወደ አገር ውስጥ ይገባሉ ተብሎ መነገሩ በነዋሪዎቹ ላይ የኑሮ ውድነት ከመጫኑ ውጪ ምንም የታየ በርካታ እንግዳ የለም፡፡
በመስቀል አደባባይ ለስምንት ቀናት መንደር በመገንባት ዝግጅት ለማዘጋጀት ከአዲስ አበባ ሚሌኒየም ጽ/ቤት ፍቃድ አግኝቶ የነበረው “ቴስት ኦፍ አዲስ” የተባለ ድርጅት ዝግጅቱን ማድረግ እንደማይችል በደብዳቤ ተገልፆለታል፡፡
በመስቀል አደባባይ ሚሌኒየሙን በማስመልከት ምንም አይነት ዝግጅት እንደማይደረግ በመንግስት በኩል የተገለፀ ሲሆን እንደምክንያት የተጠቀሰውም የኤርትራ መንግሥት የኢትዮጵያውያን ሚሌኒየም በዓል እንዲደናቀፍ በየቀኑ ከሽብርተኞች ጋር መልዕክት እየተለዋወጠ በመሆኑ ለደህንነት ሲባል ክፍት በሆኑ ቦታዎች ዝግጅት አይደረግም የሚል ነው፡፡
ሚሌኒምን በሚመለከት ካሁን በኋላ በኢትዮጵያ የሚደረጉ ዝግጅቶችም በዋዜማው በስታዲየም እና በጃን ሜዳ “ሕብር” በሚል የብሔር ብሔረሰቦች ጭፈራና ቀልድ ይታያል አዘጋጁም ብሔራዊ ሚሌኒየም ጽ/ቤት ከአዲስ አበባው ጋር በመተባበር በአርቲስቶች ተሳታፊነት ነው፡፡
በተጨማሪም በቦሌ በእነ አላሙዲን በተገነባ አዳራሽ የሙዚቃ ፌስቲቫል የሚዘጋጅ ሲሆን እስረኞቹ ካልተፈቱ ኮንሰርት አላዘጋጅም በሚል መግለጫ የሰጠው ቴዲ አፍሮም በሚቀጥለው ሳምንት የሙዚቃ ኮንሰርት ያዘጋጃል፡፡
ሚሌኒየምን በዓል ለማክበር በርካታ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ይገባሉ በሚል በተነገረው መሰረት አከራዮች ለእንግዶች እናከራያለን በሚል ተከራይን ለማስለቀቅ በሚያደርጉት ጥረትና ተከራይ ከምለቅ ኪራይ እጨምራለሁ በሚል ግብ ግብ የቤት ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ከመጨመሩ ውጪ ከሆቴል ተርፎ ቤት የሚከራይ እንግዳ መምጣቱን የተመለከተ አንድም ሰው የለ፡፡
በተጨማሪም የተለያዩ ምክንያቶች የሚሰጠው የኑሮ ውድነት ከሚሌኒየሙ በዓል ጋር ሊሆን እንደሚችል በሚገመቱ አንዳንድ ምክንያቶች ለምግብነት የሚያገለግሉ እቃዎች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ውድነት ታይቷል፡፡
ከዚህ በላይ ግን ከሰኔ ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ ይጎርፋል ተብሎ የተጠበቀው ትውልደ ኢትዮጵያዊ አልፎ አልፎ በአሉን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለማክበር ከሚመጡት በስተቀር እንደታሰበው እየመጣ ያለ እንግዳ የለም፡፡