Ethiopia’s opposition is now setting the agenda

The following is an insightful analysis [in Amharic] about how the Ethiopian opposition has started to set its own agenda, instead of always reacting and responding to the Woyanne tribal junta that is currently ruling Ethiopia. The author, Abakiya, analyzes President Isaias Afwerki’s interview with Ethiopian Review and eppfonline.org, and points out the paradigm shift among the opposition. [If you are unable to read the Amharic text below, click her for PDF]

የኤርትራ ስጦታ፡ የታሪክ እስር ቤት፡ የህወሀት ጥፋት

የራስን እድል በራስ መወሰን እስከመገንጠል የሚለው አንቀጽ በሕገ መንግስቱ ውስጥ መጨመር ሰህተት ነው።
— ፕሬዚደንት ኢሳይያስ አፈወርቂ-2009

የራስን እድል በራስ መወሰን እስከመገንጠል መብት እንቀበላለን።
— መለስ ዜናዊ፡ ገብሩ አስራት፡ ስዬ አብርሀ፡ አረና ትግራይ-2009

አጀንዳን ስለመቅረጽ፡ የኛን አጀንዳ በኛው

ልቤ እንደተንጠለጠለ፡ የላፕቶፔ ሰሌዳ ላይ እንዳፈጠጥኩ ነው ልብ የሚሰቅል ቦታ ላይ ቃለ ምልልሱ የተቆረጠው። የሚቀጥለው ክፍል ምንም ይሁን ምን እስካሁን ያየሁት ክፍል አንድና ሁለት ብቻ አርክቶኛል። ከዚህ በኋላ አጀንዳችን የኛ ነው። እስካሁን አጀንዳችንን የሚደረድርልን ሕወሀት ነበር። አሁን እኛው ነን። “ማንም የታሪክ እስረኛ ሆኖ መኖር የለበትም። እኔም ራሴ የታሪክ እስረኛ መሆን አልፈልግም።” አልጨመርኩም፡ አልቀነስኩም። እንዳሉት እንደወረደ ሳልፈነክት ሳልተለትል ነው ያቀረብኩት። አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ ናቸው ይሄንን ያሉት። እኛ ትናንት አቶ ኢሳይያስ ምን አደረጉ አይደለም እንዲሾፍረን የምንፈልገው። ዛሬ አይተ ኢሳይያስ ምን አሉ እንጂ። እነሆ ኤርትራ በተገነጠለች በአስራ ስምንተ ዓመቷ፡ ኢህአዴግም ምኒሊክ ቤተመንግስት ገብቶ እኛንና አትዮጵያን እንደ ከብት መንዳት በጀመረበት ባስራ ስምንት ዓመቱ ኤልያስና ስለሺ የኤርትራውን ፕሬዚዳንት ቃለምልልስ በገጸ በረከትነት አበረከቱልን። ዛሬ አጀንዳችንን እኛው ቀረጽነው። እስከዛሬ ኢህአዴግ ነበር የሚቀርጽልን። ከግንቦት 7 መፈንቅለ መንገስት እስከ ታምራት ገለቴ ጥንቆላ፡ ከብርቱከን መታሰር እስከ ቅንጅት መፍረስ፡ ከምርጫ ዘጠና ሰባት እስከ ቴዲ አፍሮ መታሰር ድረስ፡ ኢህአዴግ በተናገረ ማግስት ነው ያንን ኢህአዴግ ያበጀልንን አጀንዳ እየተከተልን እንነጉድ የነበረው። ዛሬ የራሳችንን አጀንዳ ራሳችን ቀረጽን።

ኤልያስ ክፍሌ እና ስለሺ ባህር ተሻግረው፡ አገር አቆራርጠው ከኤርትራ ወርደው፡ የአቶ ኢሳይያስን ቃለምልልስና፡ ፈንጂ፡ እውነተኛ፡ የሚያሳዝኑም የሚያስደስቱም፡ አንዳንድ ግዜ ትንሽ ትንሽም ቢሆን የሚያበሳጩ፡ ነገር ግን ጠላትን ደም የሚያስቀምጡ፡ ሰላም የሚነሱና የሚያሸብሩ፡ ያለተበረዙ፡ ፍልሚያ ለዋጭ፡ ያለተሰረዙ ያልተደለዙ ሀሳቦቻቸውን አቀረቡልን። አሁን ኳስ በኛ እጅ ናት። አጀንዳው የኛ ነው። ሕወሀትን አንድ ርምጃ ቀድመነዋል። እነሆ የአቶ ኢሳኢያስ ቃለ ምልልስ አዝማች፡ “ኑ እና እንወያይ። እንነጋገር። መነጋገርና ነገሮችና ማጽዳት አለብን። ኢትዮጵያን ማዳከም ፍላጎታችን አይደለም። የታሪክ እስረኞች መሆን የለብንም። የታሪክ ባሮች አንሁን።” የሚል ነው።

ቃለምልልሱ፡ ልብ አድርሱ፡ እንባ አብሱ፡ ያለፈውን እርሱ …

ከዚህ በፊትም ጽፈናል። ከፈራረሰች ኢትዮጵያ ይልቅ፡ ለኤርትራ፡ የማታሰጋት ግን አስተማማኝ ጎረቤት ያስፈልጋታል ብለናል። አቶ ኢሳይያስም ይሄንኑ ነው ያሉት። “We need a safe neighbourhood::” ኤርትራ በባዶ አየር ላይ አትኖርም። በምድር ላይ እንጂ። “Eritrea will not survive in a vacuum።” በቅርቡ በአሜሪካና በአውሮፓ ስለተደረጉ የሁለቱ አገር ህዝቦችና ምሁራን ውይይትና ንግግር ሲጠየቁ፡ በሁለቱ ህዝቦች መካከል የሚደረጉ ውይይቶች መበረታታትና መጨመር አለባቸው። በሁለቱ ህዝቦች መካከል የሚፈጠርና የሚጠናከር ኢኮኖሚአዊና ፖለቲካዊ ትስስር እንቅልፍ የሚነሳቸው ስልጣናችንን ያሳጣናል ብለው የሚሰጉትንና የሚሸበሩትን የወያኔ ቡድኖች ነው። እነዚያ ጥቂት እና አናሳ ሀይሎች በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖራቸውን ስልጣን ይሸረሽራል ብለው ሰግተው ነበር። ስለዚህም ነው የኤርትራ ጉዳይ አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ያደረጉት። ስሙን ምንም እንበለው ምንም፡ ኮንፌደሬሽንም ይሁን ፌደሬሽን፡ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል እንዲኖር ይፈለግ የነበረው የኢኮኖሚ፡ የደህንነትና የንግድ የባህልና የህልውና ውህደት ይመጣል። ይሄ ውህደት አደገኛ ነው ብለው በመስጋት ነው ወያኔዎች ወደዚህ አሁን እብደት ነው ወደምለው የድንበር ግጭት የገቡት። የድንበር ግጭቱ ግን የሀሰት ምክንያት ነው። ዋና ስጋት ስልጣናቸውን የማጣት ነው። ስለዚህም የሆነ ሆኗል። ማንም የታሪክ ታጋች፡ እስረኛ አይሁን። መጪ ዘመናችንን ግን እናበጀው አሉ። እነሆ የአቶ ኢሳኢያስ ቃለ ምልልስ አዝማች፡ “ኑ እና እንወያይ። እንነጋገር። መነጋገርና ነገሮችና ማጽዳት አለብን። ኢትዮጵያን ማዳከም ፍላጎታችን አይደለም። የታሪክ እስረኞች መሆን የለብንም። የታሪክ ባሮች፤ የታሪክ ታጋቾች አንሁን።”

ስለሕወሀት፡ ስለብሄረ ድርጅቶች፡ ስለኢትዮጵያ

በዚህ ውይይት ላይ ከምንም በላይ የማረከኝ መልሱ ብቻ አይደለም። ጥያቄዎቹ። የዛሬ ሁለት ሶስት ወር አቶ ኤልያስ ክፍሌ ለአቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ የሚሆኑ ጥያቄዎች አምጡ አለን። አፌዝንበት። ተዘባበትንበትም። ጥያቄ ቀረበ። ፈጣጣው ኤልያስም ይሆን ቆፍጣናው ስለሺ ጥያቄውን አይናቸውን ሳያሹ አቀረቡት። “እንደው ከዚህ ከመለስ ጋረ እስካሁን ማታ ማታ ትገናኛላችሁ፡ ለተቃዋሚውም ታሰጋላችሁ የሚል? አቶ ኢሳይያስ ፈገግ ይላሉ። አንዳንዴ ብዙ የማይቆይ ሳቅም ይስቃሉ። ፊት ማንበብ ለሚችል ሰው፡ የፊታቸው ወዝ፡ የአይናቸው እንቅስቃሴዎች፡ የሰውነታቸው ምላ እውነት ወይንም ወደ እውነት የቀረበ ነገር እየተናገሩ እንደሆነ ያናገራል። “የታሪክ እስረኞች/ታገቾች መሆን የለብንም” አሉ ደግመው ደጋግመው። ይሄ ሰውዬ፤ አቶ ኢሳያስ እነዚህ ሰዎችን ያውቃቸዋል። በተለይ “እነዚህን ሰዎች የሰራቸው የፈጠራቸው እሱ ነው” የምንል ከሆነም፡ ይሄ ሰው የሰራቸውን ፍጥረቶች ባህርይ ያውቃል ማለት ነው። ስለዚህ እነዚህን ሰዎች ለመጣል ከዚህ ከምንጩ መስማማት የግድ ነው ጎበዝ። ቀጠሉ አቶ ኢሳይያስ። “ይሄ የኤርትራና የኢትዮጵያ አጋርነት ቃልኪዳን ነው። ለኛ ትግሬ ከኦሮሞ ወይንም ከአማራው የቀረበ ነውና አሳልፋችሁ ትሰጡናላችሁ የሚለው የማይታሰብ ነው። ያ ወያኔ የፈጠረው የጥርጣሬና ያለመተማመን በሽታ ነው።” ህወሀትን ከኢሳይያስ የተሻለ የሚያውቀው የለም። እንዲህ ሲሉ ስለወያኔ መሰከሩ። “የህወሀት ስተራቴጂክ ምርጫ፡ ለአማራውም ለኦሮሞውም ለደቡቡም እነሱ እንዳሻቸው የሚጠፈጥፉት ድርጅት መፍጠር ነበር።” ይሄን የሚጠራጠር አለ? ከመጀመሪያውም ወያኔዎች ከሌሎች ብዙሀን ድርጅቶች ጋር በመተማመን መስራት ከፍተኛ ስጋታቸው ነበር። በፍጹም አይፈልጉትም። ስለዚህ የወያኔ ቡድን እንጂ፡ ኤርትራ ከኢትዮጵያ መከፋፈል በምንም መልኩ አታተርፍም። ኤርትራ ለትግራይ የቀረበ ለሌሎቹ ደግሞ የራቀች አይደለችም። ሀሰት ነው። ሕወሀቶች ያንን መቀራረባችንን አይፈልጉትም።

ስለብሄር ድርጅቶች ተጠየቁ። በተለይ በኤርትራ በኩል መግፋተ ያስፈልጋል ስንል ከዚህ በፊትም የመከርን ሰዎች አንዳንዱ ጥያቄ ባይጠየቅ ሁሉ እንመርጥ ነበር። ምክንያቱም ሰውዬው እንዲፋጠጡብን ወይም እንዲቆጡብንና መንገዳችን እንዲደናቀፍ አልፈለግንም ነበራ። እነ ኤልያስ ግን ፍንክች የለም። ፈታጦች። ጠየቁ። “ግን ታዲያ ለምን በብሄር የተደራጁ ድርጅቶችን ትደግፋላችሁ?” ለሽግግር። አጭርም ረጅምም መልስ ነው። አቶ ኢሳያስ፡ ከቶውንም ቋሚ በሆነ መልኩ በብሄር መደራጀትን አይፈቅዱትም። ለነገሩ ትክክል ናቸው። የኤርትራ እንጂ የኩናማ ወይ የሳሆ ወይ የዚህ ብሄ ድርጅት ብለው አልተዋጉም። “በብሄር መደራጀት ለጊዜው የምንፈልገውን እስክናገኝ አስፈላጊ ነው። ነገር ግን ቋሚ አይደለም፡ ከዛሬ ሀያ ሰላሳ አመታት በኋላ ኢትዮጵያ በብሄር ብሄረሰቦች ተከፋፍላ ማየት አንፈልግም። ያ በኤርትራ እንዲሆን አንሻም። ያ በሱዳን እንዲሆን አንሻም። ያ በኢትዮጵያ እንዲሆን አንሻም። ያ በየትኛውም አፍሪካ እንዲሆን አንሻም። ስለዚህ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎችን አሳልፎ መስጠት የማይታሰብ ነው። የማይሞከር። ቀድሞውን ነገር ያ ትልቅ ስህተት ነው። የኢትዮጵያ በብሄሮች ተከፋፍላ መኖር። ያ ጊዜያዊ ነገር ነው። ዋናው ነገር ኢትዮጵያ እንደሀገር መኖሯ፡ነው። በራስህ እንዲሆን የማትፈልገውን በባልንጀራህ አታድርግ የሚለው ቃል በአቶ ኢሳይያስ ተፈጸመ። ጭፍን ልመስል እችላለሁ። ግን አውቃለሁ፡ አቶ ኢሳይያስ ቀድሞ ጸረ-ኢትዮጵያ ድርጊቶችን ፈጽመው ይሆናል። ግን ያ ድሮ ነው። አሁን ግን ዘንድሮ ላይ ነን። ሌላ ዘመን ሌላ ስርአት መጣ። ከዘያ የሳቸው አዝማች አለ። እነሆ የአቶ ኢሳይያስ ቃለ ምልልስ አዝማች፡ “ኑ እና እንወያይ። እንነጋገር። መነጋገርና ነገሮችና ማጽዳት አለብን። ኢትዮጵያን ማዳከም ፍላጎታችን አይደለም። የታሪክ እስረኞች መሆን የለብንም። የታሪክ ባሮች አንሁን። የታሪክ ታጋቾች።”

ተጨማሪ፡ ስለበሄሮች: የታሪከ እስረኛ ስለመሆን

የኢትዮጵያን አንድነት አይፈልጉም? በዚህም ምክንያት የብሄር ብሄረሰበችን ድርጅቶች ይደግፋሉ? የአርበኞች ግንባርንም አያንቀሳቅሱትም? ተብለው ተጠየቁ። በነገራችን ላይ አሁንም እነ ኤልያስ ጥያቄዎቹን እንደወረዱ ነው ያቀረቡዋቸው። እነመለስ እንኩዋን፡ የበላው ይመለስና፡ የኢትዮጵያ መሪ ተብለው ከኢትዮጵያዊያን የማይቀበሏቸውን ጥያቄዎች ነው ያስተናገዱት። ጠያቂዎቹንም ተጠያቂውንም አደንቃለሁ። ያለምንም መጎላደፍና መኮላተፍ፡ ግን በልበ ሙሉነትና በትህትና ነው ያቀረቡት ጥያቄዎቹን። ይሄ የማይጨበጥ ግምት ነው። ይሄ የመነጨው ኤርትራ ራሷን ችላ ልትኖር የምትችለው ወይንም የኤርትራ ህልውና የተመረኮዘው በኢትዮጵያ መጥፋት ላይ ነው ከሚል የተሳሳተ ግምት ነው። “We can live side by side with a strong and powerful Ethiopia.” ከዚህ በላይ ይሄ ሰው ምን ቃል ይስጠን? ቃሉን ብቻ እንመን አይደለም። ግን፡ መጀመሪያ ቃል ነበረ ነው የሚለው መጽሀፍ ቅዱስ። ከዚያ ቃልም ስጋ ሆነ። የምንም ነገር መነሻው ቃል ነው። የመጀመሪያ መገለጫው ቃል ነው። ባንናገረውም ሀሳብ ራሱ ቃል ነው። ለራሳችን የሚወጣ ቃል። “የተባበረችና የተዋሀደች ጠንካራ ኢትዮጵያ ለኤርትራም ጥንካሬ ነች።” ትክክል ነው። ስጋት ከነበረ ያለፈ ነው። ታሪክ። It is Nostalgic. ትናንት የነበረ። በድሮ በሬ ያረሰ ደግሞ የለም። ይሄ የኛ ዘመን ነው። በዚህ በኛ ዘመን የምንኖረው። የኛን ዘመን ደግሞ በኛ አዲስ መንገድ እንጂ በአባቶቻችን ቂም ልንቃኝ አይገባም ብዬ ጽፌያለሁ ከዚህ ቀደም።

ኑ እና ታሪክ እንስራ

በዚህ ቃለ ምልለሰ ላይ፡ አቶ ኢሳይያስ ለኛ ኢህአዴግን እንዋጋለን ለምንለውና ለኢትዮጵያ ተቃዋሚ ህዝቦች በሙሉ ግልጽ ጥሪም አቅርበዋል። ኑና እንወያይ። ኑ እና የእግዚአብሄርን ቤት እንስራ አይነት ነገር። ኑና የተበላሸውን የኢትዮጵያና የአካባቢአችንን ሁኔታ እንገንባ። ለመስማትና ለመነጋገር ዝግጁ ነኝ ብለዋል። አድምጥ ብርሀኑ። አድምጥ አንዳርጋቸው። አድምጥ ኢህአፓ። አድምጥ ኢህአዴግም። ከኤርትራዊያንና ኢትዮጵያውያን ስብሰባዎችና ውይይቶች ባሻገር መሄድ አለብን። ከዚያም ልቀን ሄደን፡ አብረን መስራት አለብን። እንደጎረቤት መኖር ካስፈለገን፡ መነጋገር ምንም ምርጫ የለውም። አንዳንድ ሰዎች ኤርትራን አሁን ኢትዮጵያ ለደረሰችበት ጥፋት ተጠያቂ ከማድረገቸው የተነሳ፡ ቀድሞውንም ነገር፡ አይደለም ከኤርትራ መስራት፡ ጭራሹንም ስሟም እንዲነሳ አይፈልጉም። ለነገሩ የኤርትራ ጉዳይ ባለመነጋገርና በመሸሽ የምናመልጠው ጉዳይ አይደለም። እኛ ባንፈልግም ኤርትራ ጎረቤት እንደሆነች ትቀጥላለች። ኤርትራ የወረቀት አገር አይደለችም። መሬት ላይ፡ያለች፡ የመሬት የቆነጠጠች፡ ብዙዎቻችን ባይዋጥልንም አገር ነች። ሆናለች። ብድግ አድርገው አጥፍተው የሚገላገሏት ዝንብ አይደለችም። ተነስተው ሌላ ቦታ መሄድ አይችሉም። እስራኤሎች ከፍልስጤም ጋር አለመነጋገር አይችሉም። በሰላምም ይሀን በጠብመንጃ መነጋገራችን አይቀርም። ከሆነ ግን ሰላም ይበልጣል።

አሁንም ስለብሄሮች፡ አዲሲቱ ኢትዮጵያና አዲሲቱ ኤርትራ

የተለያዩ ድርጅቶችን የምንረዳው፡ ነጻይቱ ኤርትራ ከአዲሲቷ ኢትዮጵያ ጋር አዲስ አጋርነት እንድትመሰረት ስለምንፈልግ ነው። ሽግግርም ነው። እንጂ መጨረሻ ግብም አይደለም። የተዋሀደችና የተባበረች ኢትዮጵያ ኤርትራን ታሰጋለች ብየ አንድም ቀን አስቤ ሰግቼ አላውቅም። አቶ ኢሳያስ ቀጠሉ። ራሳቸው ኢህአዴጎች ለምን ከኤርትራ ጋር መንግስቱን ለማውረድ ሰሩና ነው አሁን ከኤርትራ ጋር መስራትን እንደ ወንጀል የሚሰብኩት? እነሱ ቀድሞውንም ነገር የሞራል ብቃት የላቸውም። በርግጥ ቃለ ምልልሱንም አቶ ኢሳይያስንም ምሉእ አድርጌ አላቀርብም። ያንን የሚመኝ ካለ ምኞት አይከለከልም። እዚህ ጋር ችግሩ፡ አቶ ኢሳይያስ ጥያቄው የሚነሳው በይበልጥ ከኢህአዴግ በኩል ሳይሆን ከኛው ከተቃዋሚዎች በኩል መሆኑን ስተዋል። የተቃዋሚው ወገን ነው በተለይ ይሄንን ነገር አጥብቆ የሚያነሳው። ይሄንን ስጋት የሚገልጸው። የወያኔ ክስ አንድም ቀን አሳስቦን አያውቅም። የሆነ ሆኖ እሳቸው ግን ቀጠሉ። “እኛ ኢትዮጵያን በብሄርና በጎሳ መከፋፈል ብንፈልግ፡ ይሄንን ኢትዮጵያን በብሄር የመከፋፈሉንና የማዳከሙን ስራ ሕወሀተ/ኢህአዴግ ኦልሬዲ በነጻ እየሰራው ስለሆነ፡ ለምን በዚያ ስራ ላይ ጊዜስ ገንዘብስ እናጠፋለን? ቆይ ትንሽ ያብራሩት። “ያንን ቀድሞውንም አንፈልገውም። ይልቅስ ራሱ ኢህአዴግ ያንን የጥፋት ስራ እዚያው ኢትዮጵያ አናት ላይ ቁጭ ብሎ እየሰራ ስለሆነ ኤርትራ እንዲህ አረገች ብሎ ሊከስ አይችልም። ያ ሆን ተብሎ የሚሰነዘር ውዥንብር ነው።” ይሄ ሀሰት ነው ሚል አለ?
በመሰረቱ፡ “በመከፋፈል የሚያምኑ ደካሞችና በራሳቸው እምነት የሌላቸው በራሳቸው የማይተማመኑ ናቸው።” ያ ደግሞ ወያኔ ነው። “there is no animosity, there is no hidden agendas there is no conspiracy” ማንም መጥቶ ማየት ይችላል። ሰውዬም በስሜትና በእልህ ነው እዚህ ጋር የተናገሩት። ያንን ብቻ ነጥለን ካየነው፡ እውነተኛነታቸው ምንም ቅንጣት ታህል አያጠራጥርም። ምንም ጠላትነት፡ ምንም የተደበቀ አጀንዳ፡ ምንም አይነት ሴራ የለም። ከዚያ የቃለ ምልልሱ አዝማች ይቀጥላል። እንወያይ። እንነጋገር። መነጋገርና ነገሮችና ማጽዳት አለብን። ኢትዮጵያን ማዳከም ፍላጎታችን አይደለም። የታሪክ እስረኞች መሆን የለብንም። የታሪክ ባሮች።

ያልተመቸኝ ነገር፡ ትንሽ ያልተቀበልኩት

ይሄ በትግራይ ያለው ወያኔን የመቃወም እንቅስቃሴ ወይንም መንፈስ በሌላ የኢትዮጵያ ክፍል ካለው የከፋና የባሰ ነው ያሉትን ነገር አልወደድኩላቸውም። ሁለት ነጥቦችን አነሳለሁ። አንደኛ የትግራይ ህዝብ ሕወሀትን አጥብቆ ይቃወማል የሚለው መሰረተ ቢስና ማስረጃ የለሽ ሀሳብ ነው። ቢሆንም ግን፡ ሁሌም እንደምንለው የትግራይ ህዝብ ህወሀትን የሚቃወምበት አጀንዳና እኛ ህወሀትን የምንቃወምበት አጀንዳ የተለያየ ነው። አንዱ እናቱ የሞተችበት አንዱ እናቱ ገበያ የሄደችበት ብለን ገልጸነዋል ከዚህ ቀደም። ለምሳሌ የዛሬ ሁለት ሶስት ወር ሪፖርተረ እንደዘገበው፡ በብሄራዊ ቲያትር የተሰበሰቡ የትግራይ ተወላጆች ስብሰባውን ለመራው የሕወሀት ሰው ያቀረቡተ አቤቱታ፡ እኛ መስዋእትነት ከፍለን ሳለ ከሌላው ክልል ያነሰ ጥቅሟ፡ትቅም ነው የምናጘነው የሚል ነው። ሁለተኛ የተቀረው ህዝብ ተቃውሞ ሁሉ በተለያየ መንገድ ሲገለጽ፡ ባለፉት 18 ዓመታት የትግራይ ህዝብ ተቃውሞ ባንድ ሰልፍ እንኩዋን ሲገለጽ አላየነውም። በመሰረቱ ለትግራይ ህዝብም ከዚህ የተሻለ መንግስት ይመጣል ብለን አናምንም። አቶ ኢሳይያስ ወያኔ የትግራይን ህዝብ ከተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ስለነጠለው በህዝቡ ዘንድ በወያኔ ላይ ከፍተኛ ቅሬታ አለ የሚሉት ነገር አልተዋጠልኝም። ችግሩ ከኔ እይታ ከሆነ፡ የጭንቅላቴን ጉሮሮ አስፍቼ ለማየት እሞክራለሁ።

የአቶ ኢሳያስ ቃለምልልስ አስደስቶኛል። የዚያን አካባቢ ውጥንቅጥ፡ ሚዛነዊ በሆነ መልኩ የሌሎች ድርጅቶችንም ስጋት ከግምት አስገብተው ጥያቄዎቹን መልሰዋል። ከአንዳንድ ድርጅቶች፡ ለምሳሌ ከኦነግ በኩል ምላሽ ሊኖር ይችላል። ለምሳሌ እነዚህ የብሄር ድርጅቶች ዘላለማዊና ቋሚ አይደሉም ለጊዜው እንጂ ለሚለው። ስለራስን እድል በራሰ መወሰን እስከመገንጠልመ ተናግረዋል። ከዚያ በተረፈ የቃለምልልሱ አዝማች ይመቻል። እንወያይ። እንነጋገር። መነጋገርና ነገሮችና ማጽዳት አለብን። ኢትዮጵያን ማዳከም ፍላጎታችን አይደለም። የታሪክ እስረኞች መሆን የለብንም። የታሪክ ባሮች አንሁን። ስለአሰብና ምጽዋ ያው The sky would be the limit for co-operation. ሉአላዊነት ሌላ ጉዳይ ነው። ትክክል ናቸው። ከዚህ በኋላ ለአሰብና ለምጽዋ አንሄድም። ኤርትራ ራሷ የኛ ትሆናለች መልሳ። የሁላችንም። እስከዚያው ግን ከታሪክ እስር ቤት ሰብረን ወጥተን፡ ከኤርትራ አይደለም ከሶማሌም ተባብረን እነዚህን ሰዎች ማስወገድ አለብን። እንደነግንቦት ሰባት ያሉ ድርጅቶች ይሄንን ወርቃማ እድል ሲሆነ ሲሆን መጠቀም፡ ቢያንስ ግን ከግምት ማስገባት አለባቸው። ያው እኔው ነኝ። እኔ አባኪያ።