Here is another well-presented argument in support of an Ethiopian Transitional Government in Exile.
Source: Ethiopian Current Affairs Discussion Forum
ትንቢተ ኤልያስ፡ የስደት መንግስት የኛም ፍካሬ ነው
የሚሳፈር ይሳፈር፡ የማይሳፈር ይቅር፡ ቀኑ ሲደርስ ግን ሁሉም ይሳፈራል
አገሬ መግባት አፈልጋለሁ!!
“አገሬ መግባት እፈልጋለሁ!! እኔ ሌላ ምንም ዓላማ የለኝም። ወያኔ አትገባም ብሎ ከሶኛል። ወያኔ ከተሰቀለበት የትእቢትና እብሪት ሰቀላ ተፈጥፍጦ ወርዶ ማየትና በአገሬ በነጻነት መኖር እፈልጋለሁ።” አለኝ ኤልያስ ክፍሌ፡ ከኤርትራ መልስ አንዳንድ ነገሮችን ስናወጋ። ይኸው ነው ይሄንን ልጅ እንቅልፍ አሳጥቶ ሰላም ነስቶ ከዲሲ አስመራ፡ ከዚህ እዚያ የሚያንከራትተው። ኤልያስ፡ አንዳንድ ግዜ ያበሳጭ ይሆናል። “ኤልያስ፡ ተው ሰው አትንካ፡ የትጥቅ ትግልን ለማራመድ የግድ ብርቱካንን ማውገዝ የለብንም። የለም ሰላማዊ ትግል አያዋጣም፡ የቀረን ትጥቅ ትግል ብቻ ነው ብለህ መከራከር ትችላለህ። ያንተን ክርክር አሳማኝ ለማድረግ ግን እነ ብርቱካን ሚደቅሳን መዘልዘል፡ እነ ዶ/ር ሀይሉን ማዋረድ የለብንም። እነ ዶ/ር መራራን ማበሻቀጥ አያስፈልገንም። እንደዚያ አይነቱ ነገር ትክክል ስላልሆነ ብቻ ሳይሆን፡ ይንን ባደረግክ ቁጥር ፍጥጫው በኛና በኢህአዴግ መሀከል መሆኑ ይቀርና፡ የትጥቅ ትግል በሚያራምዱ ወገኖችና በሰላማዊ ትግሉ አራማጆች፡ በተለይም ደግሞ በአንድነት ደጋፊዎች መካከል ይሆናል። ተው ሰው አትንካ።
የኢህአዴግ ስራ ይበቃል፡ የሕወሐት ጥፋት
ሰዉን የትጥቅ ትግልን እንዲቀበል፡ ኢህአዴግ የሚሰራው ስራ በቂ ነው። ኢህአዴግ የሰላማዊውን ትግል ምህዳር እያጠበበ እያጠበበ፡ ሲመጣ፡ በአራት ዓመት ውስጥ አንድ ሰላማዊ ሰልፍ ሲከለከል፡ በአራት አመት ውስጥ ሁለት ሕዝባዊ ስብሰባ ሲነፈግ፡ በአምስት ዓመት ውስጥ፡ አንድ የቴሌቪዥም ማስታወቂያ ማሰማት ሳይቻል ሲቀር፡ የሰማኒያ ዓመት አዛውንት ያለፍርድ ሲታሰሩ፡ የአስራሰባት ዓመት ወጣቶች በግንባራቸው ተመትተው ሲገደሉ፡ በየዓመቱ በረሀብ የሚቀጠፍ ሰው ቁጥር ሲጨምር፡ በየዓመቱ የሚሰደድ ሰው ሲያሻቅብ፡ የአገሪቱ መሬት ለአረብና ሱዳን ሲቸበቸብ፡ የአንድ ብሄር ልጆች እንደ እንቧይ እስኪያብጡ ሲፈነጨብንና ሲወቅጡን፡ ይሄ ሁሉ ሕዝቡን ወደለየለትና ወደባሰበት የትጥቅ ትግል ያመጣል። ከኢህአዴግ በኩል የሚሰራው ስራ በቂ ነዉና፡ ከኛ በኩል ሕዝቡን ወይንም ድርጅቶችን የትጥቅ ትግል እንዲመርጡ የሚያስገድድ ማስፈራሪያና ስድብ፡ አታካራና ጭቅጭቅ አያስፈልግም። ኢህአዴግ ያንን ስራ በሚገባ እየሰራ ነው። የኛ ስራ ሌላ ነው።
አብዮተኛው ኤልያስ፡ አብዮታዊ ሀሳቦች
ኤልያስ ዘወትር የሚያነሳቸው ሀሳቦች አብዮታዊ፡ ከዘመናቸው የቀደሙ፡ ደፋርና ሰው ለመግባትና ለማንሳት የሚፈራቸው ናቸው። ለምሳሌ አንድ ግዜ ኤልያስ በሌሊት ተነሳና፡ “የግዞት መንግስት ማቋቋም ያስፈልገናል አለ”። ብዙዎች ተንጫጩ። ይሄ ሰው ምንድነው የሚያወራው? ምነስ ነው የሚናገረው? ብለው ተሳለቁበት። ጥቂቶቻችን ግን አስደነቀን። አስፈነደቀንም። ወዳጄ ተክሌ የሻው፡ ሰሞኑን “ኢትዮጵያ የምትባለው አገር የለችም” የሚል አስደንጋጭ ክርክር አምጥቷል። የክርክሩን ሙሉ ቃል አልሰማሁትም። ግን ኢትዮጵያን ኢህአዴግ አፍርሷታል ነው የሚለው። ወይም ኢትዮጵያ መሆን እንደሚገባትና እንደነበረችው የለችም ነው የሚለው። ያ ለጊዜው ይቅር። ኢትዮጵያ ግን አሁን ትክክለኛና ሕጋዊ መንግስት የላትም። አጼ ሀይለስላሴ፡ በዚያም በዚህም ብለው በመለኮታዊ መቀባት ስልጣኔን አገኘሁ ብለው ለዓመታት ሕዝቡን አሳምነውት ሕዝቡም ጸሀዩ ንጉሳችን እያላቸው ኖሩ። ኢህአዴግ ግን፡ የሽፍታ ጭምብሉንና ኮንጎ ጫማውን በሲቪል ልብስ ለውጦ ስልጣን ላይ ያለ ምንም ህጋዊ መሰረት በጡንቻውና በዓለም አቀፉ መንግስታት ችሮታ ብቻ ስልጣን ላይ የቆየ አገዛዝ ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያን የሚወክል የግዞት መንግስት ለማቋቋም መብቱም ችሎታውም አለን። የኤልያስ ሀሳብ ትክክል ነው።
የግዞት መንግስተ ለምን? ከነማንስ ጋር?
የግዞት መንግስት ብናቋቋም የሚቀበሉን መንግስታት አናጣም። ኤርትራ በተማመን ከጎናችን ነች። ሌሎች ከኢህአዴግ ጋር የተጣሉ መንግስታትም ከጎናችን ናቸው። ኤርትራ ራሷ ልታመጣልን የምትችለው የወዳጅና የአቅም ብዛት የትየለሌ ነው። ብዙ ሰዎች ያለፈውን የጦርነትና የደም መፋሰስ አመታት በማሰብ ኤርትራን እንደ መንጸፈ ደይን ይፈሯታል። ብዙ ሰዎች እንደውም ከሀጢያት ይልቅ ኤርትራን ይፈራሉ። እዚህ ጋር ሲኦል እዚህ ጋር ኤርትራ አለች ቢባሉ፡ ወደሲኦል የሚመርጡም አሉ። ያ ስህተት ነው። ያለፈ አልፏል። ያለፈውን አንለውጠውም። ዘመን ይለወጣል። ከኤርትራ ጋር ለመስራትና ለመወዳጀት የሚያስፈልጉን ነገሮች በጣም ኢምንትና ጥቂት ናቸው። አንደኛ፡ ኤርትራ አገር መሆኗንና በምንም መልኩ የኤርትራን ሉአላዊነት እንደማናሰጋ ቃል መግባት። ቃል መስጠት። ሁለተኛ ኤርትራና ኢትዮጵያ እንደ ጎረቤት አገሮች አንዳቸው ባንዳቸው ላይ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ፈጥረው በሰላምና በትብብር እንደሚኖሩ መስማማት። እነሱ ባህር አላቸው። እኛም ምጣኔ ሀብት። እነሱ ጨው አላቸው። እኛም በርበሬ። ሶስተኛ ታላላቅ ሰዎችና ድርጅቶች ግንባር ፈጥረው በቀጥታ ከኤርትራ መንግስት ጋር ልኡካን ልከው መነጋገርና መቀመጫችውን በአስመራ አድርገው የግዞት መንግስት መቋቋም። አለቀ። ለጊዜው ብዙዎች ወይንም የኢትዮጵያ ህዝብ ይሄንን ላይደግፈው ይችላል። ግን ራሱን አህአዴግንና ሻእቢያን ጨምሮ ማንም ሀያል ሕዝብ በደገፈው መንገድ አይደለም ስልጣን ላይ የመጣው ወይም የወጣው። ካሸነፍን ሕዝብ ሁልግዜም ካሸናፊ ወገን ነው። የአጼ ምኒሊክ እርግማንና ግዝት ልጅ ኢያሱን አልጠቀመም፡ የሀይለስላሴ ድል አድራጊነት ግን ስልጣን ላይ አቆያቸው። 50 ዓመታት ግድም። ግማሽ ክፍለዘመን። ስለዚህ የምንፈልገው ማሸነፍ ከሆነና በኤርትራ መጓዙ እንዲሁም የግዞት መንግስት መቋቋሙ ለማሸነፍ ከረዳን ሰዎች ደገፉትም ተቃወሙትም ያንን ለማድረግ ማመንታት የለብንም።
ግንቦት ሰባት፡ ግንቦት ሀያ፡ ግንቦት ሰባት
አሁን የወሬ ግዜ አብቅቷል ብሏል ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ። አሁን የስራ ግዜ ነው። ኢህአዴግ ስራውን ሰርቷል። እየሰራም ነው። ከግንቦት ሀያ በፊትም በኋላም። የቀረው የኛ ክፍል ነው። የኛ ስራ። ኢህአዴግን ለመጣል ግንቦት ሰባት የሚጸየፋቸውና የሚያፍራቸው መንገደች ሊኖሩ አይገባም። ዶ/ር ብርሀኑ ጓደኞቹንና የስራ ባልደረቦቹን ሰብስቦ ወደ አስመራ ቢወርድ፡ አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ ለሙአመር ጋዳፊ የአደረጉትን ያህል ደማቅ አቀባበል ነው የሚያደርጉለት። ዝርዝሩን መነጋገር ነው። ካለመነጋገር ነው፡ ካለመጠየቅ ደጃዝማችነት ይቀራል። ኢህአዴግ የሰላምና የእፎይታ አገዛዝ መግዛት የለበትም። ሕወሀትም ይሁን ልጆቹ እንቅልፍ አጥተው፡ እንቅልፋቸውን እንግሊዝ እንዲተኙ ማድረግ አለብን። እስካሁን ለንደንና ዲሲ፡ ጀርመንና ሰዊዘርላንድ ሰርተናል። አሁን ደግሞ እዚያው ሜዳ ላይ መውጪያ ግዜ ነው። ከኤርትራ የተሻለ፡ ከኤርትራ የቀረበ፡ ከኤርትራ የተመቸ ሜዳና መንገድ እንደሌለ ደግሞ ከዚህ ቀደም ጽፈናል። ተራው የግንቦት 7 ነው። ከፍተኛ ልኡካን ልኮ ከኤርትራ መንግስት ጋር መነጋገርና ከኤርትራ ጋር መስራት፡ የስደት መንግስት ማቋቋምና ከዓለም መንግስታት ጋር መጻጻፍ ለብቸኝነት የቀረበ መንገድ ነው።
ልጅ ተክሌ ነኝ፡ ግንቦት 2009፡ ካናዳ