Ethiopian Scientists – poem by Getachew Abera

የኢትዮጵያ ሊቃውንቶች


ዶክተር፣ ፕሮፌሰር፣ ጠቢብ ኢንጂነሮች. . .
ባለ ሁለት ዲግሪ፣ ባለ “ሦስት” እውቀቶች፣
ባለም ዙሪያ ያላችሁ እናንት የ”ጨው ዘሮች”…!
እስኪ ተሰብስቡ ባንድጋ ምከሩ፤
የኢትዮጵያን እጣ እድሏን ቀምሩ፤
“ሙጃሌ” ለማውጭያ፣ ለእሾኽ መመንገያ…
እስኪ “መርፌ” ስሩ!

እናንት ምሁራን የኢትዮጵያ ሊቆች፤
መሰረተ-ግኝት የገበሬ ልጆች፤
እስኪ ላባታችሁ ማረሻ ስሩለት!
እስኪ ለናታችሁ ወፍጮ ትከሉላት!

ከግል ጥቅም ዝና ከወረት ባሻገር፣
እስኪ ጥቂት ጊዜ ከፍላችሁ ለአገር፣
የእውቀታችሁ ውጤት መላችሁ ይሰንዘር!

በፈረንጅ መጽሔት የወጣው ዝናችሁ፣
እናንት የጭቁን ልጅ፣ መነሻ ቤታችሁ…
አዝማለችና… ሳትፈርስ በሕይወት፣
በዚህ ጭንቅ ጊዜ ቶሎ ድረሱላት፤
ከመቀመቅ ጉዞ ከጥፋት Aድኗት!

ሊቀ-ሊቃውንቶች አንቱ የተባላችሁ፣
በገበሬው ግብር ለዚህ የበቃችሁ፣
እስኪ ለአንድ አፍታ አስቡት ያንን ሕዝብ፣
በረሃብ፣ በስቃይ፣ ባምባገነን ጡጫ በግፍ ሲደበደብ…፤
“የናቴ መቀነት ጠልፎኝ ነው” ሳትሉ፣
ለፍትህ፣ ለእድገት… እስኪ መላ በሉ!

“ኦክስፎርድ”፣ “ሐርቫርድ”፣ የ “የል”. . . ምሩቃን፣
ባለማረግ ጀግኖች እናንት ሊሂቃን፣
እድሜ ልካችሁን ባእድ ስትገነቡ፣
ከገበሬው ጎጆ ጠልቃችሁ ሳትገቡ፣
ምን ተብሎ ይጻፍ? ሕይወት ታሪካችሁ፣
መጪው ምስኪን ትውልድ እንዴት ያስታውሳችሁ?!

በሣይንስ ቅምራ በሂሳብ ስሌቱ፣
በእደ-ጥበብ ዘርፉ በምጣኔ ሃብቱ…፣
የባእድ ጎተራ ጥቅጥቅ የምትሞሉ፣
ለእማማ ኢትዮጵያም እስኪ መላ በሉ!

ጌታችው አበራ
ሐምሌ 1999 ዓ.ም.