[pdf]
ሚስተር ኦባማ የመጀመሪያው ጥቁር የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው በመመረጣቸው ታላቅ ታሪክ ሰርተዋል። አሜሪካ ውስጥ ለዘመናት በጥቁሮች ዘር ላይ ከባርነት አንስቶ ከፍተኛ ጭቆና፣አድልዎና ንቀት እንዲሁም በርካታ ኢሰብአዊና ዘግናኝ በደሎች ሲፈጸሙባቸው የቆዩ መሆኑ ይታወቃል። በመሆኑም የጥቁሮች ዘር ያለው ሰው ፕሬዝዳንት ሆኖ ለመመረጥ መቻሉ አገሪቱ ውስጥ የነጭ የበላይነት እየተፋቀ በመሄድ ላይ መሆኑንና አገሪቱ ለሁሉም ዘሮች እኩል ዕድል የምትሰጥ መሆኗን የሚያመላክት ነው አየተባለ በመነገር ላይ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ሚስተር ኦባማ የፕሬዝዳንት ክሊንተንን መረብ መበጣጠስ መቻላቸውና በአጭር ጊዜ ውስጥ በብሔራዊ ደረጃ ታዋቂነትን በማግኘት በዲሞክራቲኩ ፓርቲ ለፕሬዝዳንትነት መታጨት መቻላቸው ብቻ ትልቅ እንድምታ ያለውና ለወደፊቱም አሜሪካ ውስጥ ለሚኖሩ ጥቁሮችና ሌሎች “አናሳ” በመባል ለሚጠሩት ህዝቦች ፋና ወጊ እንደሚሆንላቸው መገንዘብ ይቻላል።
ተመራጭ ፕሬዝዳንት ኦባማ ለስምንት ዓመታት በፕሬዝዳንት ቡሽ መስተዳድር የወደቀውን የአገሪቱን ኢኮኖሚ ሊያሻሽሉ የሚችሉ እርምጃዎችን እንደሚወስዱና አገሪቱ በዓለም አቀፍ ግንኙነትዋ የደረሰባትን ጥላቻ ሊያስተካክሉ እንደሚችሉ ይጠበቃል። ሚስተር ኦባማ የውጭ ፖሊሲን በተመለከተ ግጭቶችን በውይይትና በድርድር እንዲፈቱ እንደሚያደርጉና አሜሪካ ከመፈራት ይልቅ በመወደድ ላይ የተመረካዘ የውጭ ፖሊሲ ይኖራታል በማለት በተደጋጋሚ ተናግረዋል። በመሆኑም በአሜሪካ የውጭ ግንኙነት አፈጻጸም ላይ ለውጥ ሊመጣ እንደሚችልና ፕሬዝዳንት ቡሽ ከአንዳንድ አገሮች ጋር የፈጠሩት አላስፈላጊ ውጥረት ሊረግብ እንደሚችልም ይጠበቃል።
በዚህም መሠረት በአሜሪካ ውስጥ የተካሄደው የፕሬዝዳንት ምርጫ ውድድር የበርካታ ኢትዮጵያዊያንም ቀልብ ስቧል። የአሜሪካ ዜግነት የወሰዱ ኢትዮጵያዊያንም ሚስተር ኦባማ እንዲመረጡ የራሳቸውን አስተዋኦ እንዳበተከቱ ይነገራል። ለዚህም ዋናው ምክንያት ሚስተር ኦባማ ፕሬዝዳንት ሆነው ቢመረጡ፣ የአሜሪካ የውጭ ፖሊሲ ኢትዮጵያን በተመለከተ ሊለወጥ ይችል ይሆናል ከሚል እምነት የመነጨ ነው። ሆኖም የሚስተር ኦባማ የውጭ ፖሊሲ የአፍሪካ አህጉርና በተለይም ኢትዮጵያን በተመለከተ ያራምዱታል ተብሎ ሊገመት የሚችለውን በጥንቃቄ ብንመረምር የምናገኘው ውጤት ብዙዎች አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በስሜትና በጉጉት ከምንጠብቀው ጋር የሚጣጣም አይመስልም። ይህንንም ከዚህ በታች በዝርዝር እንመልከት፤
(1) ሴናተር ኦባማም ሆኑ ከእርሳቸው ጋር አብረው ለምርጫ ዘመቻው የሚንቀሳቀሱት ባልደረቦቻቸው የውጭ ፖሊሲን በተመለከተ ከአፍሪካ ጋር ስለሚኖረው ግንኙነት ሊያመጡ ያቀዱትን ለውጥ በተጨባጭ ሁኔታ ይፋ አላደረጉትም። እንደውም እስከ አሁን ባለው መረጃ መሠረት የአፍሪካ አህጉርን በተመለከተ የዳርፉር ግጭትንና በደፈናው ድህነትን መቀነስና በሽታዎችን ማጥፋት ከሚል በስተቀር በፖሊሲ ደረጃ የተቀመጠ ከሚስተር ኦባማ አካባቢ የመጣ ምንም ዓይነት ፍንጭ የለም። ይህንንም ድረ-ገፃቸውን በመመልከት ለማረጋገጥ ይቻላል። ከዚህም በመነሳት ተመራጭ ፕሬዝዳንት ኦባማ ከበፊቶቹ ፕሬዝዳንቶች የተለየ ለአህጉሩ የሚጠቀም ተግባር ይፈጽማሉ ብሎ ለመገመት አይቻልም።
(2) ሴናተር ኦባማ ያቀዱትን የውጭ ፖሊሲ ብንመለከት ለምሳሌ ሽብር ፈጠራ መዋጋትን በተመለከተ የእርሳቸው መስተዳድር በአፍጋኒስታንና በሌሎች አገሮች ውስጥ በመካሄድ ላይ የሚገኘውን ዘመቻ በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚቀጥሉበት አስታውቀዋል። በመሆኑም አሜሪካ በሽብር ፈጣሪዎች ላይ የከፈተችው ጦርነት ብቻዋን ተዋግታ ለማሸነፍ የምትችለው ዓይነት ጦርነት ስላይደለ፣ በአጋዥነት ከእርሷ ጋር የተሳተፉት ወዳጆቿ ጋር ያላትን ግንኙነትን ትቀጥልበታለች ማለት ነው። ስለሆነም በዚህ ጦርነት ላይ ከተሳተፉ አምባገነንና ፈላጭ ቆራጭ አገዛዞች ጋር ይካሄዱ የነበሩ ግንኙነቶችም ይቀጥላሉ ማለት ነው። ይህ ለጥቅም ሲባል ከአምባገነን አገሮች ጋር የሚካሄድ ወዳጅነት አሜሪካ ውስጥ የተለመደና በተደጋጋሚ በዲሞክራቲክም ሆነ በሪፐብሊካን መስተዳደሮች ተግባራዊ ሲሆን የኖረ ነው። ከቀዝቃዛው ጦርነት ፍፃሜ ወዲህ እንኳን በፕሬዝዳንት ክሊንተን የተሰራበት ሲሆን አሁንም በፕሬዝዳንት ቡሽ በስፋት እየተሰራበት ይገኛል።
አሜሪካ ከወያኔዎች የምትፈልገው ጥቅም እስካለ ድረስ ማንኛውም ዲሞክራቲክም ሆነ ሪፐብሊካን ፐሬዝዳንት ቢመረጥ ግንኙነቱ ሳይለወጥ መቀጠሉ አይቀርም። ይህንን በዲሞክራቲኩ ፕሬዝዳንት ክሊንተን ጊዜ እንዴት ይካሄድ እንደነበር ወደ ኋላ መለስ ብለን አንድ ምሳሌ አስመርኩዘን ብንቃኝ፣ ሚስተር ኦባማም ሊያካሄዱት ካቀዱት ጋር ያለውን መስተጋብር ሊያሳየን ይችላል። ፕሬዝዳንት ክሊንተን እንደ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ የውጭ ፖሊሲያቸው በፀረ ሽብር ፈጣሪነት ላይ ያነጣጠረም እንኳ ባይሆን፣ ለምሳሌ የሱዳንን መንግሥት ለመገልበጥ የአገሪቱን ገዥ ፓርቲ የሆነውን “ብሔራዊ እስላማዊ ግንባር” በሽብር ፈጣሪነት በመፈረጅ በተቀነባበረው ሴራ የሱዳን አጎራባች የሆኑና የራሳቸው የሆነ ችግር ከሱዳን ጋር የነበረባቸውን ሶስት ከወንበዴነት ወደ መንግሥታትነት የተሸጋገሩ የኢሳያስ፣የመለስና የሙሴቬኒ (ዩጋንዳ) አገዛዞችን በአንድ ቡድን ውስጥ አሰባስበው እርዳታ በመስጠት መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ እንደሚባለው “የአዲስ ትውልድ መሪዎች“ (New Generation of Leaders) የሚል ስም በመስጠት ደፋ ቀና ይሉ እንደነበር አይዘነጋም። ይህ ቡድን ወያኔና ሻቢያ ሲዋጉ ፈርሷል። እንደውም ሻቢያና ወያኔ ሱዳንን በጦርነቱ እንድትረዳቸው በየፊናቸው መለማመጣቸው የፕሬዝዳንት ክሊንተን ፖሊሲ በአሳፋሪነት እንዲከሽፍና እንዲመክን አድርጎታል። የፕሬዝዳንት ክሊንተን መስተዳድር ምንም እንኳ ለወያኔና ሻቢያ ቀለብ ሰፋሪ የነበረ ቢሆንም እነዚህ ከዓለም በድህነት በአንደኛ ተርታ የሚገኙና ህዝባቸውን ለመመገብ እንኳ የተሳናቸው አገሮች ምክንያትና ዓላማ ለሌለው ጦርነት በርካታ ገንዘብ ሲያፈሱና የጦር መሳሪያ ከውጭ በገፍ ሲሸምቱ ጦርነቱ እንዳይጀመር ለማድረግና ከተጀመረም በኋላ በመቶ ሽህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ሳይቀጥፍ ለማስቆም አልቻሉም ነበር። መለስና ኢሳያስም በዚሁ ጊዜ እርስ በርሳቸው በአምባገነንነት በመወጋገዝ ከአሜሪካ የበለጠ ተወዳጅነት ለማግኘት ሲወራጩ ነበር።
የፕሬዝዳንት ክሊንተን መስተዳድር እነዚህ ለአብነት ያህል እዚህ የተጠቀሱ የኢሳያስ፣የመለስና ሙሴቬኒ አምባገነን አገዛዞች ከረዥም ጊዜ ጦርነት በኋላ ሥልጣን ላይ እንደወጡና ጫካ በነበሩበት ጊዜ ለበርካታ የአገራቸው ንጹሃን ዜጎች ግድያ፣ሰቆቃ፣እልቂት፣ንብረት ዘረፋና ውድመት እንዲሁም ለሌሎች ከፍተኛ ወንጀሎች ተጠያቂ መሆናቸውና ሥልጣን ኮርቻ ላይ ከተፈናጠጡም በኋላ “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ” አንደሚባለው የዲሞክራሲ መብቶችን በመርገጥ፣የሰብዓዊ መብቶችን በማፈን ህዝባቸው ላይ ሳንጃ ወድረው የሚገዙ መሆናቸው በስፋት እየታወቀ ከሌሎች የተሻለ ሁኔታ ውስጥ ከሚገኙ አገሮች ተለይተው ለወጃጅነት ተመርጠዋል። ዲሞክራቱ ፕሬዝዳንት ክሊንተን ሲያወድሷቸው የነበሩት እነዚህ አገዛዞች ከበርካታ የአፍሪካ ገዥዎች በከፋ ሁኔታ አፋኝ፣ አምባገነንና ሰብዓዊ መብት ረጋጭ ቢሆኑም አገሮቹ ከሚሰጡት ጥቅም አኳያ ሁኔታው ተገልብጦ የአሜሪካ የጥብቅ ወዳጅ ሆነው የወታደራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊና ሌሎችንም እርዳታ ከአሜሪካን ይጎርፍላቸው ነበር።
ከላይ የተመለከተው የአሜሪካ የውጭ ፖሊሲ አፈፃም የተለያየ አቀራረብና መልክ ቢኖረውም አዲስ ግን አይደለም። ይህ አሰራር “ብሔራዊ ጥቅም” በመባል ይታወቃል። የአሜሪካ ብሔራዊ ጥቅም ተብሎ በሌሎች አገሮች ላይ በተለያዩ ስልቶች ተፈፃሚ የሚሆኑ ፖሊሲዎች በዲሞክራቲክም ሆነ በሪፐብሊካን መስተዳድሮች ሲሰራባቸው የኖሩና ተቀባይነት ያገኙ አካሄዶች ናቸው።ማንኛውም አገር ትልቅም ሆነ ትንሽ የራሱ የሆነ ብሔራዊ ጥቅም አለው። ብሔራዊ ጥቅም በአገሮች መካከል ባለ ግንኙነት ውስጥ አብይ ቦታ የሚይዝ ነው። እያንዳንዱ አገር ብሔራዊ ጥቅሞቹን ለማስጠበቅ የሚያራምደው ፖሊሲ በወታደራዊ፣በንግድ፣በባህልና በሌሎችም መስኮች የሚጸባረቅ ነው። ዲሞክራሲያዊ የሆነ የመንግሥት አወቃር ያላቸው ለምሳሌ እንደ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ህንድ የመሳሰሉትና እንዲሁም አምባገነን መንግስታት እንደ ቻይና፣ የመሳሰሉት ከሌሎች አገሮች ጋር ባላቸው ግንኙነት የራሳቸውን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ጥረት ሲያደርጉ ይታያሉ። ስለሆነም ለብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማሟላት አገሮች ከፍተኛ እንቅስቃሴና ጥረት ያደርጋሉ። አገሮች ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስከበር በሚል ሽፋን በሌሎች አገሮች ላይ ኢሰብዓዊና ህገወጥ ድርጊቶችን ፈጽመዋል። ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በሚል ምክንያት በርካታ አገሮች ውስጥ በተለያዩ ጊዜዎች ህጋዊ መንግሥታት ተገልብጠዋል፣ በህዝብ የተመረጡ መሪዎች ተገድለዋል፣ንጽሃን ዜጎች ተጨፍጭፈዋል፣ምርጫዎች ተጭበርብረዋል፣ የኢኮኖሚ አሻጥሮች ተፈጽመዋል፣ የሰብዓዊ መብቶች ተገፈዋል እንዲሁም ሌሎች ተመሳሳይ ድርጊቶች ተደርገዋል።
በዓለም ላይ እንደ አገር ብሔራዊ ጥቅም የሌላት አገር ኢትዮጵያ ብቻ ነች። አንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ያለው አገዛዝ የአገር ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነትን የናደ እንዲሁም የህዝቡን አንድነትና ደህንነት የደመሰሰ በጠባብ የጎሳ ጥቅም ናላው የዞረ የቅጥረኞች ቡድን የሆነው ወያኔ ነው። ወያኔ በኢትዮጵያ አገራዊ ልዕልና ላይ አምጾ ነፍጥ በማንሳት ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ላይ የሚገኝ ከመሆኑም በላይ አገሪቱን በጎሳ ከፋፍሎ፣አዳክሞና በረሃብ እየቆላ በመግዛት ላይ ያለና ከሥልጣን በሚወገድ ጊዜ አገሪቱን በታትኖ ወደተነሳበት መንደር ለመወተፍ ዝግጅቱን አጠናቆ የመጨረሻውን ጊዜ በመጠበቅ ላይ የሚገኝው የትግራይ የገዥ መደብ ነው። ይህ የገዥ መደብ ለጠባብ የጎሳ ጥቅም ማስገኛና በሥልጣን ላይ ተፈናጦ ለመኖር የአገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ሥልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ለሌሎች አሳልፎ በመስጠት ላይ የሚገኝና ምንም ዓይነት ብሔራዊ ስሜት፣ተቆርቋሪነትና አመለካከት የሌለው የውጭ ቀጣሪዎቹን ጥቅም ለማስከበር የቆመ የነፍሰ ገዳዮች ጥርቅም ነው።
አሜሪካ “በሽብር” ላይ የከፈተችው ጦርነት በቀላሉና በተወሰነ ጊዜ ያልቃል ተብሎ ሊገመት የሚችል ስላይደለና እንደነ መለስ ዜናዊ ዓይነት እራሳቸውን እንደ ሸቀጥ ለሽያጭ ያቀረቡና “ሳይጠሯቸው አቤት፣ ሳይልኳቸው ወዴት” የሚሉ ሰው ሆነው ተፈጥረው እነሱ ግን በውሻነት ጌቶቻቸውን ለማስደሰት ጭራቸውን የሚቆሉ፣ ህዝባቸውን በጠላትነት ፈርጀው ከባዕዳን እርጥባን በመቃረም በስልጣን ኮርቻ ላይ ተፈናጠው ለመቆየት የሚቅበዘበዙ ነፈሰ በላዎች እስካሉ ድረስና “ዲሞክራሲያዊ” የሚባሉ አገሮች አሜሪካንን ጭምር እንደነዚህ ዓይነት ታዛዦች መኖራቸውን ስለሚፈለጉና እንዲኖሩም ስለሚያደርጉ፤ ሚስተር ኦባማም ከዚህ ለዘመናት ሲሰራበት ከቆየ አሰራር ውጭ ይወጣሉ ብሎ ለመገመት አይቻልም። ሚስተር ኦባማ በሽብር ላይ በመካሄድ ላይ ባለው ጦርነት ከእነ መለስ ዜናዊ ዓይነት ነፈሰ ገዳዮች የሚቀርብላቸውን የትብብር ጥሪ በደስታ የሚቀበሉ እንጅ የእነሱን ማንነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ከአምባገነኖች ጋር አብሬ አልሰራም በማለት እነመለስ ዜናዊን ፊት ይነሳሉ ማለት ከእውነታ ውጭ መሆን ነው።
እ.አ.አ. በኦክቶቨር 2008 “የሰብዓዊ መብት ተመልካች” (Human Rights Watch) የተባለው የሰብዓዊ መብት ተካራካሪ ድርጅት ባወጣው ሪፖርት ከዩናይትድ ስቴትስ፣እንግሊዝና ካናዳ ጨምሮ ከ18 አገሮች የመጡ ቁጥራቸው 150 የሚሆኑ እስረኞች ለሁለት ዓመታት ለፍርድ ሳይቀርቡ ኢትዮጵያ ውስጥ በእስር ሲማቅቁ የቆዩ መሆናቸውን አስታውቋል። እነዚህ እስረኞች ከአሜሪካ በመጡ መርማሪዎች ምርመራ የተደረገባቸው መሆኑንና ሰቆቃም የተፈጸማባቸው እንደሚገኙና ከነዚህም ሌላ ቁጥራቸው 22 የሚሆን የደረሱበት ያልታወቀ መሆናቸውን ገልጿል። መለስ ዜናዊ ከቡሽ መስተዳድር ጋር በማበር “የአፍሪካ ጓንታናሞ” በመክፈት ታማኝነቱን ለአሳዳሪዎቹ አሳይቷል። ይህንንም በማድረግ እሱ የሚፈጽመው ወንጀል ሳያንሰው ሌሎች አገሪቷ ውስጥ ወንጀል እንዲፈጽሙ በማድረግ ኢትዩጵያ በጥቁር መዝገብ ላይ ስሟ እንዲሰፍር አድርጓል። በመሆኑም እንደዚህ ዓይነት “ሲጭኑበት አነሰኝ ጨምሩልኝ” የሚል ታማኝ አጋሰስ እያለላቸው በሌላ በምንም ዓይነት እንዲተካ አያደርጉም። እንደዚህ ዓይነቱን ወንጀልና ኢሰብዓዊ ድርጊትስ መለስ ካልሰራላቸው ማን ሊሰራላቸው ይችላል?
በእርግጥ ሚስተር ኦባማ ለምሳሌ “የቀድሞ የፓኪስታን ፕሬዝዳንት ከነበሩት ከሙሻረፍ መሰሎች ጋር አብሬ አልሰራም ህዝቡን፣ መያዝ አለብን” የመሳሰሉ ሃሳቦችን ሰንዝረዋል። ነገር ግን ይሄ ለምርጫ ውድድር ከሚነገር ጉንጭ አልፋ የቅስቀሳ ዘዴ ያለፈ ስለማይሆንና በተግባርም ላይ ለማዋል የሚቻል ስላይደለ በዙ ሊባልበት አይገባም። ስለሆነም በሽብር ፈጠራ ላይ የሚካሄደው ጦርነት ላይ “በወዶ ገብነት” (Coalition of the Willing) የተሰለፉት እንደነመለስ ዜናዊ ያሉ ፈላጭ ቆራጮች በሚገዙት አገር ውስጥ ምርጫ ሰርቀውና አጭበርብረው በጉልበትና በማናለብኝነት ንፅሃን ዜጎችን እየፈጁና በረሃብ እየጨረሱ ስልጣን ላይ ቢቆዩ የሚስተር ኦባማ መስተዳድር “እናንተ እጃችሁ በደም የተጨማለቀ አራጆች ጋር አብሬ አልቆምም፣ የናንተንም ትብብር አልፈልግም” የሚል ወኔ ይኖራቸዋል ብሎ መገመት በአገሮች መካካል ያሉ ግንኙነቶችን ካለመረዳት የሚመጣ ነው የሚሆነው።
እንደውም ሚስተር ኦባማ በብሔራዊ ደህንነት ጉዳዮች ላይ ለዝብተኛ ናቸው፤ አገሪቱንም ከጥቃት ለመከላከል ልምዱና ብቃቱ የላቸውም፤ ተብለው በተደጋጋሚ የተተቹበትን ወቀሳ ለማስቀየር እንደሚፈልጉ ስለሚታመንና እንዲሁም ከአራት ዓመታት በኋላም ለድጋሚ ምርጫ መወዳደራቸው ስለማይቀር እራሳቸውን የአሜሪካ ብሔራዊ ድህንነት አስከባሪነታቸው ለማሳየት እነመለስን ተሸክመው ከመሄድ ሌላ አማራጭ የላቸውም። ለዚህም አንዱ ማስረጃ ሊሆን የሚችለው ሚስተር ኦባማ ለኢራቅ ጦርነት መታወጅ ከፍተኛ ሚና ከተጫወቱት አንዱ ከነበሩት ሪፐብሊካኑ ጄኔራል ኮሊን ፓወል ጋር የእርሳቸው መስተዳድር አብሮ እንደሚሰራ ማሳወቃቸውና የፕሬዝዳንት ቡሽን የመከላከያ ሚኒስቴር የቦኑትን ሚስተር ሮበርት ጌትስን የስራ ዘመን ማራዘማቸው ነው።
ምናልባት የኦባማ አስተዳደር አንዳንድ ከዚህ በፊት የነበሩ መስተዳድሮች የተጠቀሙባቸውን የተሰለቹና የተነቃባቸውን ማስመሰያዎች መጠቀም ሊያቆሙ ይችላሉ። ለምሳሌ እ.አ.አ. በ1997 ኢትዮጵያ ውስጥ በተካሄደው ብሔራዊ ምርጫ ጊዜ እንደታየው ትጥቅ ያልያዙና በሰላም ህገመንግስታዊ መብታቸውን ተጠቅመው “ምርጫ ተጭበረበረ፣ ድምፃችን ተሰረቀ” በማለት ተቃውሟቸውን የግለፁ በርካታ ቁጥር ያላቸው ንፁሃን ላይ የአጋዚ ጦር በአልሞ ተኳሾች እየለቀመ በመፍጀት አገሪቱን የደም አውድማ ሲያደርጋት፤ የፕሬዝዳንት ቡሽ እስቴት ዲፓርትመንት ወያኔን ጭፍጨፋውን እንዲያቆምና የሕዝቡን ውሳኔ እንዲያከብር በማድረግ ፈንታ በመገደልና በመሞት ላያ ያሉት ንፁሃን ላያ በማላገጥ “ሁሉም ወገኖች ማለትም በመገደል ላይ ያለው ህዝብ ጭምርና ወያኔ ሊታቀቡ ይገባል” የሚል እጅግ አሳዛኝ፣ የነሱንም ማንነት ያጋለጠ ለይስሙላ የተነገረ ፍሪቢስ መልዕክት ያስተላልፉ እንደነበር እናስታውሳለን። እንደዚህ ዓይነቱ ጭፍንና እርቃኑን የቀረ ማደናገሪያ በግላጭ መስጠት በሚስተር ኦባማ መሥተዳድር ሊቀር ይችል ይሆናል።
(3) ሌላው እዚህ ላይ መጠቀስ ያለበት አብይ ጉዳይ ከሚስተር ኦባማ የምርጫ ቡድን ጋር በቅርብ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙትን የዲሞክራቲክ ፓርቲው ከፍተኛ አባላት በተለይም በውጭ ፖሊሲ ቀረጻ ላይ የተሳተፉትን ሰዎች ብንመለከት ብዙዎቹ ከዚህ በፊት በፕሬዝዳንት ክሊንተን መስተዳድር ጊዜ በከፍተኛ ሥልጣን ላይ የነበሩና ኢትዮጵያን በተመለከተ የተዛባና የተወላገደ አመለካከት ያላቸውና ለወያኔም ጭፍን ድጋፍ ሲሰጡ የነበሩም ይገኙበታል። ሚስተር ኦባማ አዲስ ፖሊሲ ይዣለሁ ቢሉም የፖሊሲው ቀራፆች ያው የበፊቶቹ ሲሆኑ የፖሊሲው አስፈፃሚዎችም እነዚሁ ሰዎች እንደሚሆኑ ይጠበቃል። በተለይም ሚስ ሂላሪ ክሊንተንን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር (Secretary of State) አድርገው መሾማቸው፣የኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለውጥ ሊመጣ እንደማይችል አመልካች ነው ለማለት ይቻላል። ሚስተር ኦባማ ከከበቧቸው አማካሪዎቻቸው መካካል አንድም እንኳ ከሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች ወይም መንሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የመጣ ሰው አልተመለከትንም። ከዚህም በተጨማሪ ሴናተር ኦባማ የዲሞክራቲኩን ፓርቲ እጩነታቸውን በተቀበሉብት ጊዜ ባደረጉት ንግግር “አንድን ተግባር ተመሳሳይ ሰዎች በተደጋጋሚ እየሰሩት የተለየ ለውጥ መጠበቅ ዘበት ነው” ብለው ከተናገሩትም ጋር አሁን በማድረግ ላይ ያሉት የሚጣጣም አይደለም። ከሁሉም በላይ ሚስ ሂላሪ ክሊንተንን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አድርገው መሾማቸው የአሜሪካን የውጭ ፖሊሲ ከተለመደው ምህዋር ውጭ ሊሽከረከር የማይችል መሆኑኡ የሚያመላክት ነው።
እ.አ.አ. ኦገስት 28 ቀን 2008 የዲሞክራቲክ ፓርቲው የፕሬዝዳንት እጩውን በሚሰይምበት ጊዜ “የውጭ ፖሊሲ በኦባማ መስተዳድር” (Foreign Policy in an Obama Administration) በሚል ርዕስ በዴንቬር፣ኮሎራዶ ውስጥ የተካሄደው ጉባዔ ላይ የነበረውን ሁኔታ ብንመረምር የሚስተር ኦባማን የውጭ ፖሊሲ አፈጻጸም በሚገባ ያመለክታል። በዚህ ጉባዔ ላይ ከተሳተፉት ስድስት ግለሰቦች መካከል ሶስቱ በፕሬዝዳንት ክሊንተን መስተዳድር ጊዜ በከፍተኛ ሥልጣን ላይ የነበሩ ሲሆን እነሱም ሚስተር አንቶኒ ሌክ የብሔራዊ ድህንነት ምክር ቤት ዋና ኃላፊ የነበሩ፣ሚስ ሱዛን ራይስ ረዳት የእስቴት ዲፓርትመንት የአፍሪካ ጉዳይ ኃላፊ የነበሩ፣እንዲሁም ሚስ ጌል ስሚዝ የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ከፍተኛ አማካሪ የነበሩ ናቸው። ፕሬዝዳንት ክሊንተን ለስምንት ዓመታት በሥልጣን ላይ በነበሩበት እ.አ.አ. ከ1993 እስከ 2001 ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ወያኔ ኢትዮጵያ ውስጥ ይፈጽም የነበረውን የሰብዓዊ መብቶች ረገጣ፣ የዲሞክራሲ መብቶች አፈና በተለይም የንፁሃን ዜጎች ጭፍጨፋና ሌሎች በርካታ ኢሰብዓዊ ድርጊቶች በመቃወም፤ ለወያኔ ከአሜሪካ የሚሰጠው እርዳታ እንዲቆም በአሜሪካ ውስጥ በተለያየ ከተሞች ውስጥ በርካታ ትዕይንተ ሕዝቦች፣ሰላማዊ ሰልፎችና ሌሎችም አግባብነት ያላቸው ወያኔን የማጋለጥ እንቅስቃሴዎች በተደጋጋሚ የተካሄዱ መሆናቸው ይታወሳል።
ሆኖም የስቴት ዲፓርትመንት ኃላፊዎች ይሰጡ የነበረው ምላሽ ሲጠቃለል የኢትዮጵያ መንግሥት የብሔር ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሙከራ በማድረግ ላይ ስለሚገኝ፣ ሙከራው ስለመስራቱና አለመስራቱ ለማወቅ ጊዜ ሊሰጣቸው ይገባል በማለት በህዝባችን ላይ በወያኔ የደረሰውን ፍጅትና እልቂት እንዲሁም ረሃብ፣እርዛትና ስደት ሳይቆረቁራቸው በላቦራቶሪ ውስጥ እንዳለ አይጥ ሙከራ ሲካሄድብን ሆዳቸው እያወቀ ዝም ብለው ከመመልከት አልፈው ከፍተኛ ዕርዳታ ለወያኔ ማጉረፋቸውን ቀጠሉበት። በወያኔ “ቤተሙከራ” ንፅሃን ኢትዮጵያውያንን ለእልቂትና ለሰቆቃ መዳረጋቸውና የወያኔ “የክልል አስተዳደር” ብዙዎችን ለከፍተኛ መፈናቀል የኢኮኖም ኪሳራ እንደዳረጋቸው በሚነገራቸው ጊዜ ሁኔታው ከደርግ ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ነው እያሉ ሲያሾፉብን እንደነበር ያታወሳል። ይህም ሁኔታ እ.አ.አ. በ1991 ወያኔ አዲስ አበባን በወረረበት ጊዜ መርቀው ካስገቡት ከሚስተር ኽርማን ኮኽን ፖሊሲ ጋር የሚመሳሰልና “ዲሞክራሲ ከሌለ እርዳታ አይሰጥም” የሚለውን ለኢትዮጵያ ህዝብ የተገባውን ቃል አጥፈው በጭፍንና በማንአለብኝነት ለወያኔ ከአሜሪካን የሚጎርፈው እርዳታ መቀጠሉ ሆን ተብሎ የተደረገ የፖለቲካ ውሳኔ መሆኑን መገንዘብ ይገባል።
በዚሁ በዴንቬር ከተማ በተካሄደው ጉባዔ በቀጥታ ከወያኔ ጋር ግንኙነት ያላቸው እንደውም የወያኔ ድርጅት አባል ናቸው ተብለው የሚታሙት ሚስ ጌል ስሚዝ፣ ከሚስተር ኦባማ ዋና የውጭ ፖሊሲ አማካሪዎች አንዷ መሆናቸው የአሜሪካ ፖሊሲ ኢትዮጵያን በተመለከተ ፈቀቅ እንደማይል የሚያመላክት ነው። ወያኔ በእነዚህ ግለሰቦች እየተጠቀመና አግባቢዎችና ደላሎች (ሎቢስቶች) ከረሃብተኛ ኢትዮጵያዊያን እየቀማ በከፍተና ዋጋ በመቅጠር በሥልጣን ላይ ተንፈላንሶ ለመቀጠል መንደፋደፉን ይቀጥልበታል። የስቴት ዲፓርትመንት የአፍሪካ ጉዳይ ረዳት ኃላፊ የነበሩት ሚስ ሱዛን ራይስም ባልሥልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ የዲሞክራሲ ሥርዓት መስፈንና የሰብዓዊ መብት መከበር ረዥም ጊዜ የሚፈጅ ሂደት ነው በማለት ኢትዮጵያዊያን ለወያኔ ዘመን አሜን ብለውና ተስፋ ቆርጠው እንዲገዙ የተቃዋሚዎችን እጅ ሲጠመዝዙ እንደነበር አይዘነጋም።
ሚስተር ኦባማ እንደነዚህ ዓይነት አፍቃሪ ወያኔና አማካሪዎቻቸውን ይዘው ምን ዓይነት ለውጥ ለኢትዮጵያ ሊያመጡ ይችላሉ? እነዚህ አማካሪዎቻቸው ወያኔ በሥልጣን ላይ እንዲቆይላቸው እንጅ ሌላ ብሔራዊና ዲሞክራሲያዊ፣እንዲሁም ተጠሪነቱ ለኢትዮጵያዊያን የሆነ መንግሥት እንዲመሠረት ይፈልጋሉ ብሎ መገመት ከእባብ እንቁላል የእርግብ ጫጩት የመጠበቅ ያህል ነው። እነዚህ ባዕዳን “ሰዶ ማሳደድ ያማረው ዶሮውን በቆቅ ይለውጣል” የሚለው እንዲደርስባቸው የሚፈልጉ አይደሉም። እንደልባቸው የፈለጉትን ማስደረግና በር ተከፍቶላቸው መፈትፈት ለምደው በሌሎች ለእነሱ ሸከም ትከሻ በሌላቸው እንዲተኩ አያደርጉም። የጥቅም ጉዳይ ነውና።
ኢትዮጵያዊያን የምናካሂደው ትግል፣ የብሔራዊ የአርነት ትግል እንደሆነ ልንገነዘብ ይገባል። ኢትዮጵያ በታሪካዊ ጠላቶቿ ብዙ እንደተዶለተባትና እንደተሴረባት መገንዘብና እንዲሁም ትግላችን ከባድና ውስብስብ እንደሆነም መረዳት ይኖርብናል።ትግላችን የአገራችን ባለቤት የመሆንና የነፃነት እንጅ የሌላ እንዳልሆነ ብዥታ ሊኖርብን አይገባም። የዲሞክራሲ መስፈን፣የሰብዓዊ መብት መከበርና የፍትህ ሥርዓት ሊዘረጋ የሚችለው በመጀመሪያ ደረጃ ነፃነት ባለውና አገርና እራሱን በራሱ በአገሩ ተወላጅ በሚያስተዳድር ሕዝብ ነው። ከፈረሱ ጋሪው መቅደም የለበትም። ወያኔና ሻቢያ ኢትዮጵያን ወረው ከያዙበት ጊዜ አንስቶ ኢትዮጵያዊያን ተቀበልነውም፣ አልተቀበልነውም መራራው ሃቅ የአገራችንን ባለቤትነት ተነጥቀናል። ወያኔዎች ከዚህ በፊት እንደነበሩት እንደ ንጉሰ ነገስቱና እንደ ደርግ መንግሥታት ተራ አምባገነኖች ብቻ ሳይሆኑ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የህዝብ አንድነት ላይ ጦርነት ከፍተው በታሪካዊ ጠላቶቻችን በመታገዝ በቅኝ ገዥነት የተንሰራፉብን ጠላቶቻችን በመሆናቸውም ጭምር ነው።
በመጨረሻም ለችግራችን መፍትሄ የሚሆነው በውጭ አገር ሰዎችና በባዕዳን ላይ ተስፋ ማድረግ ሳይሆን፣ እራሳችን ኢትዮጵያውያን ተባብረን፣ በራሳችን ተማምነንና እራሳችንን አጠናክረን ያሉንን ጥቃቅን ልዩነቶቻችንን አቻችለን የወያኔን ፋሽስታዊ የቅኝ ገዥ ቡድን ለማስወገድ በትጋት ከመስራት ሌላ ምንም አማራጭ የለንም። የውጭ አገር ሰዎችና ባዕዳን የእኛን ሥራ ሊሰሩልን አይችሉም። ባዕድ ሁል ጊዜ ባዕድ ነው። ከባዕዳን ጋር ለመዛመድ ብዙ ጊዜ በከንቱ አጥፍተናል። ባዕዳን ችግራችን ችግራቸው፣ ስቃያችን ስቃያቸው ሊሆን አይችልም። ባዕዳን የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ እንጅ ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን ጥቅም ይቆሙሉናል ብሎ ማመን ከፍተኛ ስህተት መሆኑን ካለፉት አስራ ሰባት ዓመታት መገንዘብ ይቻላል። ዘላቂ ጥቅማችንን አውቀን፣ ካለፈው ስህተታችን ተምረንና በአንድነት ከሰራን ባዕዳን ወደ እኛ የሚመጡና የሚያከብሩን እንጅ እኛ እነሱን የምንለማመጥና ደጅ የምንጠና አንሆንም።
የኢትዮጵያ ነፃነት ቅርብ ነው!
ኢትዮጵያ በልጆችዋ ለዘላለም ተከብራ ትኖራለች!