እዚህም ሞት እዚያም ሞት፤ ሁሉም ያው ነው

አሰቃቂው የስደት ጉዞና የኢትዮጵያውያን ስደተኞች መከራ

Written by መታሰቢያ ካሳዬ | Addisadmassnews.com

May 16, 2015

“ኢትዮጵያውያን በአደገኛ ሁኔታ የሚደረገውን የስደት ጉዞ ይደፍራሉ” (ሂዩማን ራይትስ ዎች)

Ethiopia has little to offer them.  How many more must die?

Ethiopia has little to offer them. How many more must die?

በየመን የባህር ዳርቻዎች በውሃ ተገፍተው የሚወጡ አስከሬኖችን የሚቀብር ድርጅት ተቋቁሟል፡፡ ከሟቾቹ ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት ኢትዮጵያውን ናቸው ከእጅ ወደ አፍ የሆነው የቤተሰቦቹ ኑሮ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መሄዱ ተስፋ አስቆረጠው፡፡ ነገን ተስፋ በማድረግ ተምሬ ሰው እሆናለሁ በሚል ጥርሱን ነክሶ የገፋበት ትምህርቱ ለጥሩ ውጤት አብቅቶት ዩኒቨርሲቲ የመግባት ዕድል ቢገጥመውም ተመርቆ ድግሪውን ይዞ ሲወጣ ግን እንዳሰበው ሥራ ለማግኘት አልታደለም፡፡

አነስተኛ የቀን ሥራ በመስራት በሚያገኛት ጥቂት ገንዘብ ደካማ ቤተሰቦቹን ለመደጐም ብዙ ጥረት ደረገ፡፡ ሆኖም አልተሳካልኝም ይላል፡፡ እሱና ሁለት ታናናሽ እህቶቹ እንዲሁም የስኳር ህመምተኛ እናቱ ሰንጋተራ አካባቢ ከቀበሌ በ15 ብር ከ80 ሣንቲም በተከራዩት ባለሁለት ክፍል ደሳሳ ቤት ውስጥ ነበር የሚኖሩት፡፡ ይህቺ ደሣሣ ጐጆአቸው ግን በመልሶ ማልማት ሳቢያ እንደምትፈርስ ተነገረው፡፡ መርዶ ነበር የመሰለው፡፡ እናቱ ሲሰሙ ደግሞ በድንጋጤ የአልጋ ቁራኛ ሆኑ፡፡ በድህነት ላይ ረሃብ፣ በረሃብ ላይ በሽታ ተደራርበው አደካከሟቸው፡፡ አልጋ ላይ የዋሉትን፣ ህመምና ረሃብ የሚያሰቃያቸውን እናቱን የሚያደርገው አጣ፡፡ ሁሉም ነገር ከሚቋቋመው በላይ ሆነበት፡፡ ዕለት ተዕለት ተስፋ መቁረጡ እየተባባሰ መጣ፡፡
በዚህ መሃል ነው ከቀናት በፊት መርካቶ ጫማ ቤት አብረውት በቀን ስራ ከተቀጠሩ ጓደኞቹ የሰማው የስደት መንገድ ጆሮው ላይ ያንቃጨለው። “አሁን የእኔ መኖርና አለመኖር ለቤተሰቦቼ ምን ይጨምርላቸዋል? እንደውም ረዳት የላቸውም ተብሎ እንዳይታዘንላቸው እንቅፋት ነው የሆንኩባቸው፤ እናም መሄዴ ለእነሱም ጥሩ ነው” ሲል ለራሱ ደመደመ – ተስፋ የቆረጠው ወጣት፡፡ እናቱ እጅግ ለባሰ ቀን ብለው ያስቀመጧትን 8 ግራም የአንገት ሃብላቸውን ይዞ አብሮአደግ ከሆኑት የሰፈሩ ልጆች ጋር ለስደት ተነሣ፡፡ የስደቱን ነገር ለእናቱም ሆነ ለሁለት ታናናሽ እህቶቹ አልነገራቸውም፡፡በመተማ በኩል የሱዳን ድንበርን አቋርጠው ለመግባትና ወደ ሊቢያ ለመዝለቅ፣ ከዚያም የሜዲትራኒያን ባህርን በጀልባ አቋርጠው ጣሊያን ለመሻገር የሚችሉበት አቋራጭ መንገድ እንዳለ ነግሮ ባሳመናቸው ደላላ አማካኝነት ለጉዞ ተዘጋጁ፡፡ እዚሁ አዲስ አበባ አሜሪካን ግቢ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው የስደተኞች ማጠራቀሚያ ቤት ውስጥ ከአምስት ጓደኞቹ ጋር ገባ፡፡
ከአዲስ አበባ ተነስተው ወደ መተማ ጉዞ የጀመሩት ምሽት ላይ ነበር፡፡ ከአቅሟ በላይ ተሳፋሪዎችን የጫነችው ሚኒባስ፣ የምሽት ተጓዦቹን መተማ ለማድረስ በሰዓት 120 ኪሎ ሜትር ትፈተለክ እንደነበር ያስታውሳል፡፡

እዚህም ሞት እዚያም ሞት፤ ሁሉም ያው ነው

እዚህም ሞት እዚያም ሞት፤ ሁሉም ያው ነው

ጉዞው ነፍስ ውጭ ነፍስ ግቢ ቢሆንም እንደምንም መተማ ደረሱ፡፡ ወደ ሱዳን ድንበር የሚያደርሳቸውን፣ የሱዳንና የኢትዮጵያን ድንበር የሚያገናኘውን ገለባት የተባለ ድልድይ የሚያሻግራቸውን ደላላ ለሶስት ቀናትን ጠብቀው ካገኙት በኋላ ይዟቸው ሱዳን ገባ፡፡ እጅግ ዘግናኙን የሰሃራ በረሃ በእግር አቋርጠው ከበርካታ የስቃይና የመከራ ጉዞ በኋላ ሊቢያ ደረሱ፡፡ በዚህ ዘግናኝ ጉዞ መራራውን በረሃ መቋቋም አቅቷቸው፣ በረሃ የቀሩ በርካታ የጉዞ ጓደኞቹን ያስታውሳል፡፡ እንደ እሱ እድል ቀንቷቸው ሊቢያ መግባት የቻሉት ስደተኞች፤ የሜዲትራኒያንን ባህር በጀልባ አቋርጠው፣ ጣሊያን ለመግባት ሁለት መቶ ዶላር ከፍለው፣ አርጅታ ውልቅልቋ በወጣ ጀልባ ላይ ተሣፈሩ፡፡ ከአቅሟ በላይ የጫነችው የስደተኞች ጀልባ ጣሊያን ድንበር አካባቢ ለመድረስ ጥቂት ሲቀራት በቅኝት ላይ በነበሩ የጣሊያን ጀልባዎች እይታ ውስጥ ገባች፡፡
ይህንን የተረዱት የጀልባዋ ዘዋሪዎች ወደ ኋላ በመመለስ ጉዞ ወደመጡበት ሆነ። ከተያዙ የሚደርስባቸው ቅጣት የከፋ መሆኑን ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ወደተነሱበት የሊቢያ የወደብ ከተማ ተመልሰው የጫኑአቸውን ስደተኞች በማራገፍ ወደ የጉዳያቸው ሄዱ፡፡ ምስኪኖቹ ስደተኞች፤ ለጉዞው የከፈሉት ገንዘብ ግን የውሃ ሽታ ሆኖ ቀረ፡፡ ከዚህ በኋላ ፍፁም ከሊቢያ ድንበር ለመውጣትና ወደ ጣሊያን ለመሻገር በተደጋጋሚ ያደረገው ሙከራ ሳይሳካለት ቀረና ከፖሊስ እጅ ወደቀ፡፡ ከስድስት ወራት የእስር ቆይታ በኋላ በአለማቀፉ የስደተኞች ማህበር በኩል ወደ አገሩ እንዲመለስ ተደረገ፡፡
አዲስ አበባ ሲመለስ ግን ትቶት ወደሄደው ደሳሳ የእናቱ ጎጆ ለመመለስ ድፍረት አጣ፡፡ ነገ የተሻለ ደረጃ ላይ ደርሼ ህይወቷን እለውጣለሁ ብሎ ከእናቱ ጉያ የወሰደው የእናቱ የክፉ ቀን ቅርስ ተሸጦ ለህገወጥ ደላሎቹ ሲሳይ ሆኗል፡፡ ቤሳ ቤስቲን በኪሱ አልነበረውም። አዲስ አበባ ላይ ለጥቂት ቀናት ወዲያ ወዲህ ሲል ከቆየ በኋላ ግን አላስቻለውም፡፡ እሩህሩህ የእናት አንጀት ይቅርታውን እንደማይነፍገው አምኖ ይቅርታን ለመጠየቅ፣ አፈር ፈጭቶ ወዳደገበት መንደር ሲሄድ የጠበቀው የፍርስራሽ ክምር ነበር፡፡ ወጣቱ ከመሄዱ በፊት ቤቱ ለልማት እንደሚፈርስ ቢሰማም እንደ አዲስ በድንጋጤ ልቡ ለሁለት ክፍል አለ፡፡ ድንጋጤው በዚህ ብቻ ግን አላበቃም። የስኳር ህመምተኛ አሮጊት እናቱ ከወራት በፊት እስከወዲያኛው ማሸለባቸውንም ሰማ፡፡ የእናቱን መርዶ ችሎ ለመቀበል አቅም አጣ፡፡
የባህርና የበርሃ ሲሳይ ከመሆን ያመለጠባቸው አጋጣሚዎች እጅጉን ናፈቁት፡፡ “ምነው እዛው ሞቼ በቀረሁ፡፡” ሲል ክፉኛ ተመኘ፡፡ ጎጃም በረንዳ አካባቢ በሚገኘው የህገወጥ ሰዎች አዘዋዋሪ (ደላሎች) መናኸሪያ ውስጥ ያገኘሁት ይህ ወጣት፤ የስደት ህልሙን አስፈሪዎቹ የሰሀራ በረሃና የሜዲትራኒያን ስምጥ ባህር አላመከኑትም፡፡ ይልቁንም አገሩ ተመልሶ ያጋጠመውና ያየው ዘግናኝ ነገር ልቡን ይበልጥ አደንድኖት ዳግም ለስደት ንዲነሳሳ እንዳደረገው ይናገራል፡፡ ይኼ የ26 ዓመቱ ወጣት ሌት ተቀን ያገኘውን ሥራ በመሥራት ጥቂት ገንዘብ ቋጥሮ በሶማሊያ ቦሶሳ በኩል ወደ የመን ለመጓዝ መላ እያፈላለገ እንደሆነ ገልጿል፡፡ በቅርቡ በኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ የደረሰውን አሰቃቂ ሞትና መከራ አነሳሁበት፡፡
“እዚህም ሞት እዚያም ሞት፤ ሁሉም ያው ነው” አለኝ ወጣቱ፤ ተስፋ በቆረጠ ስሜት ፍርጥም ብሎ፡፡ የኑሮ ውድነት፣ ሥራ አጥነት እና ተስፋ ቢስነት አስመርሯቸው፣ በደላሎች ጉትጐታ ተታለው ለስደት የሚነሱ ትዮጵያውያን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው፡፡ ከዓለማችን ታላላቅ በረሃዎች አንዱ የሆነውን የሠሃራ በረሃ አቋርጠው፣ በሊቢያ በኩል ወደ አውሮፓ የመግባት ተስፋን ያነገቡ፣ በፋርስ ባህረሰላጤ ወደ የመንና ጣሊያን ለመግባት የሞከሩ፣ በኬንያ በኩል ወደ ደቡብ አፍሪካ የመሄድ እቅድን የነደፉ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በረሃው ውጦ አስቀርቷቸዋል፡፡ ባህሩም ውጧቸዋል። በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመለከተው፤ በ2004 ዓ.ም ወደ የመን ለመጓዝ በ228 ጀልባዎች ተሣፍረው ከነበሩ 14,486 ኢትዮጵያውያንና ሱማሊያዊያን ስደተኞች መካከል ስልሣ አምስቱ ሲሞቱ፣ ሠላሣ ስድስቱ የደረሱበት አልታወቀም፡፡
በአብዛኛው የስደት ጥንስሱ የሚጀመረው እዚሁ በመዲናችን አዲስ አበባ ውስጥ ነው፡፡ ከተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ሣውዲ አረቢያን፣ የመንን፣ ደቡብ አፍሪካንና ጣሊያንን መዳረሻ ህልማቸው አድርገው የሚነሱ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች፤ ለጉዞአቸው ዕቅድ የሚያወጡት አዲስ አበባ ውስጥ ከሚያገኟቸው ህገወጥ ደላሎች ጋር ነው። ይህ የአዲስ አበባው የድለላ መረብ እስከ ሱዳን፣ ሱማሊያና ሊቢያ ድረስ የዘለቀና በኔትወርክ የተሳሰረ ነው፡፡ ደላሎቹ ስደተኞቹን በጨው በረንዳ፣
ጐጃም በረንዳ፣ አሜሪካን ግቢ፣ ተክለሃይማኖት፣ ሰባተኛና ቦሌ ሚካኤል አካባቢ ላይ ለዚሁ ተግባር በተዘጋጁና ስደተኞችን ለማቆያ በሚያገለግሉ ቤቶች ውስጥ እያጠራቀሙ ለጉዞ ዝግጁ ያደርጓቸዋል፡፡ ስደተኞቹ ሁልጊዜም የስደት ጉዞውን የሚጀምሩት ምሽት ላይ ነው፡፡ ህልማቸው ወዳደረጉአቸው አገራት ከሚሄዱ የስደት ጓደኞቻቸው ጋር ዘግናኙን የመከራ ጉዞ ይጀምሩታል፡፡ በአብዛኛው የስደቱ ጉዞ በአራት ዋና ዋና መንገዶች የሚካሄድ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ በሊቢያ ጣሊያን፣ ከኢትዮጵያ ቦሳሶ ሱማሊያ የመን፣ ከሞያሌ ኬንያ ድንበር ደቡብ አፍሪካ እና አቦኮ፣ ኬላበር ጅቡቲ ዋንኞቹ የስደተኞች የጉዞ መዳረሻዎች ናቸው፡፡

 

ከአዲስ አበባ ተነስቶ መተማን አቋርጦ፣ በገለባት ድልድይ ሱዳን ድንበር በመግባትና የሰሀራ በረሃን በእግር አቋርጦ የባህር ላይ ጉዞ በማድረግ ጣሊያን ላይ በሚጠናቀቀው በዚህ የጉዞ መስመር ለመጓዝ ደላሎችን ፍለጋ የሚባዝኑ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄዱን በስደተኞች ድርጅት የተደረገው ጥናት ይፋ አድርጓል፡፡ በአብዛኛው ከደቡብ ወሎ፣ ከሚሴ፣ አላማጣ፣ ትግራይ፣ ጅማ፣ አርሲ፣ እንዲሁም ከደቡብ ክልል ሆሣህናና ሃዲያ አካባቢዎች የሚጓዙ ስደተኞች፤ የፑንት ላንዷን የወደብ ከተማ ቦሳሶ እንዳጨናነቋትና ሴቶቹ እጅግ አነስተኛ በሆነ ገንዘብ በወሲብ ንግድ ሥራ ላይ መሰማራታቸውን እንዲሁም ከUNHCR የሚሰጣቸውን የምግብ እርዳታ እየተቀበሉ ለአመታት ኑሮአቸውን እየገፉ እንደሆኑ አመልክቷል፡ከኢትዮጵያ በቦሳሶ ሶማሊያ፣ የመን በሚደርሰው በዚህ የስደት የጉዞ መስመር ተጉዘው ዕድል የቀናቸው ጥቂቶች የመንን የመርገጥ ዕድል ሲያገኙ፣ ብዙዎች የባህር ሻርኮች ሲሳይ ሆነው ይቀራሉ።
ከአዳማ ተነስቶ የፑንትላንዷ የወደብ ከተማ ቦሳሶ ገብቶ፣ በኤደን ባህረሰላጤ በኩል ወደ የመን ለመግባት ሞክሮ ያልተሣካለትና ህይወቱ በተአምር እንደተረፈች የሚናገረው የ22 ዓመቱ ኢትዮጵያዊ ያሬድ በቀለ፤ ይህ የስደት መስመር እጅግ አደገኛ መሆኑን ይናገራል፡፡ ያሬድ በመንግስት አልባዋ ሱማሊያ በኩል ከአገር ለመውጣት በሚፈልጉ እጅግ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ የሚፈፀመው ዘግናኝ ግፍ መሸከም ከሚቻለው በላይ መሆኑን ይገልፃል፡፡ አስገድዶ መድፈር፣ ዝርፊያና፣ ግድያ የተለመዱ ሲሆኑ በብዙዎቹ ስደተኞች ላይም በየዕለቱ የሚደርሱ ገጠመኞች እንደሆኑ ይናገራል። ከአዳማ በድሬደዋ፣ ሃረር፣ ጅግጅጋ፣ የቶጐ ጫሌን ኬላ አልፎ፣ ሱማሊያ ገብቶ ወደ ፑንትንላንዷ የወደብ ከተማ ቦሳሶ ደርሶ ወደ የመን የምታሻግረውን ጀልባ ጥበቃ ለአራት ወራት ያህል ቆይቷል፡፡ ለጀልባ መሳፈሪያው 120 ዶላር ከፍሎ በጀልባዋ ሲሻገርም ከተወለደበት አካባቢ ተነስተው እንደ እሱ የስደት ጉዞ ላይ ከነበሩ ሶስት ወጣቶች ጋር ተገናኝቶ ነበር፡፡ ጉዞአቸውን አጠናቀው አልወር ወደተባለችው የየመን ባህር ዳርቻ ለመድረስ ጥቂት ቀራቸው ጀልባዋ ተገለበጠች፡፡ በጀልባዋ ተጭነው ባህር ሲሻገሩ ከነበሩት ከ180 በላይ ስደተኞች ውስጥ በህይወት የተረፉት 27 ብቻ ነበሩ፡፡
በየመን ድንበር ጠባቂ ፖሊሶች ተይዞ ለጥቂት ቀናት በእስር ቤት ከቆየ በኋላ ወደመጣበት ሱማሌላንድ እንዲመለስ መደረጉን ይናገራል፡፡ በፑንትላንድ ቆይታውም እጅግ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች እሱ ባለፈበት መንገድ እያለፉ፣ የመን ለመግባት ሙከራ ሲያደርጉ ባህሩ ውጦ እንዳስቀራቸው ይገልፃል፡፡ የዚህ አይነቱ እጅግ ዘግናኝ የስደት ጉዞ መስመር ዛሬም የበርካታ ኢትዮጵያውያን ሞት ምክንያት ቢሆንም አሁንም በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በየመውጫ በሩ ለስደት ይጣደፋሉ፡፡ ሂዩማን ራይትስ ዎች የተባለው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሪፖርት እንደሚጠቁመው፤ ኢትዮጵያውያን በአደገኛ ሁኔታ የሚደረገውን የስደት ጉዞ ይደፍራሉ። ሴተኛ አዳሪነትና እጅግ አነስተኛ ሥራዎችን በመሥራት በድንበር አካባቢዎች ቆይተው ከአገር ለመውጣት ጥረት ያደርጋሉ፡፡
እንደ ሪፖርቱ፤ በባህር ተሻግረውና በረሃን አቋርጠው ለመግባት የሚሞክሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በየመን ባህር ዳርቻዎች የሚኖሩ ህዝቦች በውሃ ተገፍተው ወደ ባህሩ ዳርቻ የሚመጡትን አስከሬኖች የሚቀብር ድርጅት መስርተው በበጐ ፈቃደኝነት ይሠራሉ። ከሟቾቹ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙትም ኢትዮጵያውያን እንደሆኑ የሂዩማን ራይትስ ዎች ሪፖርት ይጠቁማል፡፡ እንዲህም ሆኖ ለስደት ያሰፈሰፉ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ነው ያሉት፡፡ ወደ መከራ ጉዞ – ወደ ስቃይ ጉዞ – ወደ ሞት ጉዞ ተባብሶ ጨምሯል፡፡ መንግሥት፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ሲቪል ማህበረሰቡ፣ ቤተሰብ፣ በአጠቃላይ ህዝቡ ይሄንን የዜጎችን ህይወት የሚቀጥፍ የስደት ጉዞ ለማስቆም በህብረት፣ ጥምረት ፈጥረው መትጋት ይኖርባቸዋል፡፡ ችግሩ መንግስት “በአገር ሰርቶ መክበር ይቻላል” ከሚለው በላይ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ በጥልቀትና በትኩረት መፈተሽና መመርመር ያለበት ትልቅ አገራዊ ችግር ነው፡፡ ትልቅ አገራዊ ደዌ!! ትልቅ አገራዊ ቀውስ!!

 

_______________________________________