ከፈቃደ ሸዋቀና
የሻምበል ፍቅረ ስላሴን ባለ 440 ገጽ መጽሐፍ ላነብ ስነሳ ጸሐፊው በሃያ ዓመታት የእስር ቤት ቆይታቸው በስልጣንና የሃላፊነት ዘመናቸው የነበሩትን ብዙ ክንዋኔዎች ፣ ውሳኔዎችና ተዋናዮችን አስመልክቶ የነበራቸውን እይታ እንደገና ለማጤንና ለማሰላሰል (Reflect ለማድረግ) እድል አግኝተው የጻፉት ሊሆን ስለሚችል ሚዛናዊ የሆነ ዕውቀት፤ እንዲሁም የመንግስታቸውን የውስጥ ለውስጥ ሥራዎች ከሩቅ እናይ የነበርን ተራ ዜጎች ሳናውቃቸው የቀሩ ነግሮችን የምናገኝበት ይሆናል የሚል ጉጉት ነበረኝ። በተጨማሪም በመግቢያው ሊተርኩልን ቃል የገቡትን የደርግን የግዛት ዘመን ዋና ዋና ቁም ነገሮችና ክንዋኔዎች እንደወረደ አቅርበውልን አንባቢዎች የሁሉንም ነገር ፋይዳ የራሳችንን ሚዛን ተጠቅመን እንድንረዳው ይተውልናል ብዬ አስቤም ነበር። ይህ ከንቱ ምኞት መሆኑን ወደገጾቹ ውስጥ ርቄ ሳልሄድ ነው ያረጋገጥኩት። በሁሉም የደርግ የግዛት ዘመን ክንዋኔዎችና የፖለቲካ ተዋናዮች ላይ የራሳቸውን ዳኝነቶች አመለካክቶችና ግለ-አይታዎች (bias) ጨምረውበታል።
ሻምበል ፍቅረ ስላሴ ከእስር በወጡ ባጭር ጊዜ ውስጥ ጊዜያቸውን ወስደው ይህን መጽሀፍ በመጻፋቸው ሊመሰገኑ ይገባል። ወደፊትም ሌሎች መጽሐፎች እንደሚጽፉ ቃል ገብተዋል። የሚቀጥሉት ላይ በበለጠ የሃልፊነት ስሜት እንዲጽፉ ለማሰቢያ የሚረዳ ነገር ካስተያይቴ ሊያገኙ ይችላሉ የሚል ግምት አለኝ። እውነት በመናገርና በሀቅ በመመስከር ከሚገኘው ብዙ ጥቅም ውስጥ አንዱ ለተናጋሪው የህሊና ፈውስ የሚያስገኝ መሆኑ ነው። ለሻምበል ፍቅረስላሴና ለቤተሰባቸው መልካሙን ነገር ሁሉ እመኝላቸዋለሁ። መጽሀፋቸው ላይ በማቀርበው አስተያየት ላይ ግን ርህራሄ የለኝም። የምንሟገትበት ጉዳይና ታሪክ ከያንዳንዳችን ስብዕና በላይ ስለሆነ።
የዚህን ጽሁፍ ርዕስ ግምገማ (Review) ከማለት ይልቅ አስተያየት(Observation) ያልኩት እውቄ ነው። መጽሀፉ እንደመጽሀፍ የሚገመገም ባህርይ የለውም። ብዙው የደራሲው ነጻ እይታ ዘገባ ነው። ትልልቅ ድምዳሜዎች ላይ የደረሱባቸውን ነጥቦችና በፖለቲካ ባላንጦቻቸው ላይ የሚያቀርቡትን ክስ ተዓማኒ የሚያደርግ ወይም የሚያረጋግጥ ወይም ደርግን ከክስ የሚያነፁበት ማስረጃ የሚሆን የግረጌ ማስታወሻም (Footnote) የዋቢ ዝርዘርም (Reference list) የለበትም። መጽሀፉ ባቀራረቡ ከሞላ ጎደል የደርግ በተለይም የኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም ገድል ነው። ለበርካታ ደርግ ላይ ለሚቀርቡ ወንጀሎችና ጥፋቶች ሁሉ የተገቢነት ማረጋግጫ (justification) ለመስጠት ደራሲው ሙከራ ሲያደርጉ ይታያል። ስለዚህ ግምገማ የሚገባው መጽሀፍ ነው ማለት ለመጽሀፉ የማይገባውን ነገር ማድረግ መስሎ ታይኝ። ማድረግ የሞከርኩት ፈጣን ወፍ በረር ቅኝት ብቻ ነው። ምሳሌ የሚሆኑ ነገሮችን አሳይቼ ብዙውን ነገር ትቼዋለሁ።
በደርግ የግዛት ዘመን ከደረሰው የጥፋት ከምር ላይ የተለያዩ የፖለቲካ ሀይሎችና ተራ ዜጎች የሚወስዱት የተለያየ መጠን ያለው ድርሻ እንዳለ ብዙ የሚያከራክር አይመስለኝም። ከዚህ የጥፋት ከምር ላይ አያንዳንዱ የደርግ አባልና በተለይ በከፍተኛ ሀላፊነት ላይ የነበሩ ደራሲውን የመሰሉ መሪዎች የሚያነሱት ትልቅ ድርሻ አለ። በሚያሳዝን ሁኔታ ሻምበል ፍቅረ ስላሴ ለይሉኝታ ያህል ብለው እንኳን በግልም ይሁን በጋራ ምንም ሀላፊነት አይወስዱም። የመንግስታቸውን ጥፋት ሁሉ በሌላ ያመካኛሉ። ኢህአፓን አጥብቆ በመወንጀል የደርግን ለመሸፈን ይቻላል በሚል ሀሳብ ይመስላል ኢህአፓ ገደላቸው የሚሏቸውን 271 ሰዎች ዝርዝር ከምጽሀፉ 21 ገጾች ሰጥተው አስፍረዋል። (ከገጽ 275 – 296). ዝርዝሩ ደርግ ራሱ እየገደለ ኢህአፓ ገደላቸው የሚባሉ ሰዎች ስም ሁሉ ይዟል። ለምሳሌ ዶክተር መኮንን ጆቴን የገደላቸው ራሱ ደርግ መሆኑን የሚያምኑ የመኢሶን አባላት አሉ። በአጸፋው ኢህአፓ ብለው የፈጁትን ሰው ዝርዝር ይቅርና ጠቅላላ ቁጥር እንኩዋን ሊነግሩን ፈቃደኛ አይደሉም። ተራ ተመልካች ካለችግር የተረዳውንና ብሎ ብሎ የጨረሰውን የኮሎኔል መንግስቱንና የደርግ መንግስት ጥፋቶችና ሀገርን አደጋ ላይ የጣለ ግትርና እምባገነናዊ አመራር በጨረፍታ እንኩዋን ለመተቸት አለመሞከራቸው ወይ ቀጥተኛ ክህደት ፣ ወይም የውሻ አይነት ቅድመ-ሁኔታ አልባ ታማኝነት ፣ ከዚህ ከዘለለ ደግሞ “በምኒልክ ጊዜ የደነቆረ ምኒልክ ይሙት እንዳለ ይኖራል” የሚባለው አይነት ነገር አስመስሎባቸዋል።
በመከረኛይቱ ሀገራችን ላይ ብዙ መታከም የሚገባው ትልልቅ ቁስል አለ። የሚሻለው ወደማከሙ መዞር እንጂ ቁስሉ ላይ ጨው መነስነስ አይደለም። ሻምበል በመጽሀፋቸው ብዙ ቦታ ይህንን ጨው ቁስላችን ላይ ካለሀሳብ ነስንሰውታል። በህይወት የሌሉና ሊከራከሯቸው የማይችሉ ሰዎችን ሳይቀር በስልጣን ዘመናቸው ጊዜ እንደሚደረገው እሁንም በመደዳው ይወነጅሏቸዋል። ይህ አጻጻፍ በውድቀታቸው ላገኛቸው ለራሳቸው ቁስል ፈውስ ይሆነኛል ብለው አስበው ከሆነም ተሳስተዋል። ንጹህ ራስን እንደገና ማግኘት (redemption) የሚቻለው ለዕውነት ክብር በመስጠት ብቻ መሆኑ የተረዱት አልመሰለኝም። ዛሬ የሚገዙንን ገዥዎች እካሄድና አገዛዝ ስለጠላን የደርግን ዘመን ግፍ እንዳለ የረሳነው መስሏቸው ከሆነም በጀጉ ተሳስተዋል። የወጋ እንጂ የተወጋ አይረሳም። ደጉ፣ ቸሩና አስተዋዩ የአትዮጵያ ህዝብ በወደቀ እንጨት ምሳር ማብዛት አይገባም ብሎ ስለተወውና እነሻምበል ፍቅረስላሴ ትተውለት በሄዱት ምስቅልቀል ላይ በመጠመዱ እንጂ የደረሰበትን ግፍ ረስቷል ማለት አይደለም። ወዳጅ ዘመድ በግፍ የሞተበት ፣ ቤቱ የፈረሰበት ፣ ከነጠባሳው የሚኖር ዜጋ፣ ከገበያ ላይ ሳይቀር ካለፈቃዱ ታፍሶ ጦር ሜዳ የተማገደው ማገዶ ትራፊ አሁንም አለ እኮ!
በመጽሀፉ ላይ የምሰጠው አስተያየት ርሳቸው የሚወነጅሏቸው ድርጀቶች ወይም ሰለባዎች ወይም ግለሰቦች ወክዬ ለመሟገት አይደለም። ከሻምበል ፍቅረስላሴ መጽሀፍ ጋር ያጣላኝ አንዳንዱ ነገር በቅርብ በምናውቀው ታሪክ ላይ ያሳዩት ይሉኝታ የሌለው አጻጻፋቸው ነው። በጊዜው ያልተወለደውና ለዕውቀት ያልደረሰው ትውልድ የተሳሳት ግንዛቤ እንዲወስድ ሲጋበዝ ዝም ብሎ ማየትም ተገቢ አልመሰለኝም። ስለዚህ በዚህ መጽሀፍ ላይ የምሰጠው አስተያየትጨከንያለመስሎታይቷችሁከሆነ ከዚህ አቅጣጫ እዩልኝ። ሌላ የግል ወይም የቡድን ሂሳብ የማወራርደው የለኝም። የኛ ሀገር ሰው እንደሚለው ከጅብየሚያጣላጓሮዬያሰርኩት አህያየለኝም።
እኔ የቀዳማዊ ኃይለስላሴ መንግስት ተፈንቅሎ ደርግ ስልጣን ሲወስድ 18 የማይበልጠኝ የአዲስ አበባ ዩኒቭርሲቲ የሁለተኛ አመት ተማሪ ነበርኩ። በደርግ ዘምን ለነበረው ሁሉ እንግዳ አይደልሁም ማለት ነው። እንደብዙ ወጣቶች ኢህአፓ አካባቢ ልሳተፍ እንጂ ያደረኩት ተሳትፎ ብዙ አልነበረም። ካስተዳደጌ ይሁን ክሌላ በልጅነቴ ጀምሮ አንዳንድ ገዜ አስተማሪና ጉዋደኛ እስቲጠላብኝ ድረስ ጨቅጫቃ ተማሪ ነበርኩ። አንድ ነገር እስኪገባኝ ድረስ ሰው አስቸግር ነበር። በ1968 ዓም መጀመሪያ ኣካባቢ አንድ የኢህአፓ የጥናት ክበብ ላይ ስሳተፍ ደርግ የወዛደሩ ፣ ኢህአፓ ደግሞ የላብ አደሩ እምባገነንነትን እናሰፍናለን በሚሉት ነገር ላይ ችግር ነበረብኝ። ለካርል ማርክስ ጭንቅላት እስከዛሬ ድረስ ትልቅ አድናቆት ቢኖረኝም የሶሻሊዝም ሳይንስነትም አይገባኝም ነበር። የጥናት ቀጠሯችን ዕለት በኢትዮጵያ ያለውን የላባደር ቁጥር ፈልጌ ጠቅላላ ከ45ሺ እንደማይበልጥ አረጋግጬ መጣሁ። አዲስ አበባና አቃቂ አካባቢ ያለው በቻ 20 ሺ አይሞላም ነበር። 35 ሚሊዮን ህዝብ ባለበት አገር ላይ ሀምሳ ሺ ለማይሞላ ሰው ሺ ጊዜ ተበዝባዥ ሲሆን ቢውል አምባገነን እንዲሆን የምንታገልበት ምክንያት እልገባ ብሎ አስጨንቆኝ ነበር። ይህን ነገር ሳነሳ ሰብሳቢያችን የነበረው ልጅ ሳቀብኝ። ከማርክስ እየጠቀስ ሊያስርዳኝ ሲሞክር ይበልጥ አዞረብኝ። ማርክስ የሚያወራው አይነት ላባደርማ ጭራሹኑ እዚህ አገር የለም ብዬ ድርቅ እልኩ። የኛ አገር ላባደር ማርክስ እንደሚናገርለት እንዳውሮፓው ሳይሆን እንዴውም የተፈናቀለ (depeasantised) ገበሬ ነው ብዬ ተከራከርኩ። ሰብሳቢያችን ስደብ አዘል ሽሙጥ አሽሟጠጠኝና ተጣላን። ከዚያ ሴል ውስጥም ወጣሁ። እዚያ ሴል ውስጥ አብረውኝ የነበሩ ልጆች የነበራቸውን የህዝብና ሀገር ፍቅር በፍጹም አልጠረጥርም። እኔ የህዝብና ያገር ፍቅራቸውን እንደሆን እንጂ በጀግንነትና በመስዋዕትነት ስሜት አልወዳደራቸውም። እነሱ ለህዝብ ሲሉ ለመግደልም ሆነ ለመሞት ዝግጁ ነበሩ። እኔ የሚያገዳድል ነገር ባለበት አካባቢ መገኘት አልወድም። ሰው የሚገድል ሰው ምን አይነት ህሊና እንዳለው እስከዛሬ አይገባኝም። ሁሉም ማለት ይቻላል በኋላ አልቀው ተገደሉ። ብዙ ሊሞቱ የማይገባቸውና በህይወት ቢኖሩ ትላልቅ ሳይንቲስት የሚወጣቸው የቅርብ ጉዋደኞቼ በደርግ ተገለዋል። እኔ ቀጭኑን የቀይ ሽብር ዘመን አስተማሪ ሆኜ ገጠር ውስጥ አለፍኩት። መጨረሻ ላይ የቀይ ሽብሩ ዶፍ ሊያባራ አካባቢ ያበዱ ካድሬዎችና ባለስልጣኖች ርዝራዥ ኢህአፓ ብለው እኔንና ጥቂት ጉዋደኞቼን ሊበሉን የምኖርበት ወረዳ አብዮት ኮሚቴ ውስጥ መዶለታቸውን ሰማሁ። አምልጬ ባንድ ትንሽ፣ ግን ጠቃሚ ስልጣን በነበረችው አጎቴ ርዳታ ተረፍኩ። አጎቴ ለኔና ለታናሽ ወንድሜ ብቻ ሳይሆን ለጓደኞቼም መዳን ረዳ። ከሁሉ በላይ አብዱል ቃድር የሚባል የዩኒቨርሲቲ ታማሪ የደሴ ልጅ፣ አሁንም በህይውት አዲስ አበባ የሚኖር የጓደኛዬ ጓደኛ ባጎቴ ርዳታ ሞት ከሚጠብቅበት እስር ቤት ለማውጣት ስለቻልኩ እስከዛሬ ደስ ይለኛል። ከዚያ በኋላ ያለውን የደርግ ዘመን አጎንብሼና ትምህርት ላይ አተኩሬ የሆዴን በሆዴ ይዤ ባድርባይነት ነው ያሳለፍኩት። ስለዚህ የብዙ ሰው ያህል ቂም የለኝም። እነሻምበል ፍቅረስላሴ ላይ አሁን ከደረሰባቸው በላይ እንዲደርስባቸው አልፈልግም። ጉዳያቸውን ያየው ዳኛ እኔ ብሆን ኖሮ የሀያ ዓመት ቀርቶ የሁለት ወር እስራትም እልፈርድባቸውም ነበር። ሰው ሲዋረድና ሲሰቃይ ማየት አልወድም። የሰሩትን ስራ አልቅሼ ነግሬና ወቅሼ ንስሀ እንዲገቡ መክሬ ነበር የምለቃቸው። ግፈኛን በደግነት እንጂ በግፍ በመቅጣት ርካታ የሚገኝ አይመስለኝም።
ሻምበል በመጽሀፋቸው ሊሰጡን የሚሞክሩትን የማህበራዊ ሳይንስ ትንታኔ ቢተውት ይሻል ነበር። ኮሎኔል መንግስቱም መጽሀፋቸው መጀመሪያ ላይ እንዲህ አይነት የምሁር ተግባር ውስጥ ሲንጠራሩ ተመልክቼ ነው ሳላነብላቸው የወረወርኩት። ሻምበል ፍቅረስላሴ ሊቃውንት ተንታኞችን ሊጠይቅ የሚችለውን ማህበራዊ ሳይንስ ቀርቶ ከተመክሮ እንኩዋን ሊታወቁ የሚችሉ ነገሮችን ስተዋቸዋል። ለምሳሌ በጊዜው ተነስቶ ስለነበረው ስለጊዚያዊ ህዝባዊ መንግስት ጥያቄ አንስተው በተቹበት ክፍል ውስጥ ጊዜያዊ ህዝባዊ መንግስት ሊመሰርቱ ይገባል ተብለው የተጠቀሱትን የህብረተሰብ ክፍሎች በየተራ እያነሱ እንዴት እንደማይችሉ ያስረዳሉ። የገበሬውን ተሳትፎ በተመለከተ፣
“ገበሬው ንቃቱ እጅግ በጣም ዝቅተኛ ከመሆኑም በላይ የመንግስትን አወቃቀርና አሰራር ማወቅ ቀርቶ የሚኖርበትን አካባቢ እንኩዋን እንዴት እንደሚተዳደር ለይቶ ለማወቅ ችሎታ የሌለው መደብ ነበር” ይሉናል። (ገጽ226)።
ተማሪዎችን አስመልክቶ ሲናገሩ ደግሞ፥
“ተማሪዎች የስራም ሆነ የኑሮ ልምድ የላቸውም። ቤተሰብ ማስተዳደር እንኩዋን ብቅጡ አያውቁም። ……………………መንግስት ስልጣን ውስጥ ተካፋይ መሆን አለባቸው የሚል ሀሳብ ማቅረብ ከግዴለሽነት ወይም ግራ ከመጋባት የመነጨ ይመስላል” ይላሉ። (ገጽ226)”.
ይህን የሚጽፉት ሻምበል ፍቅረሰላሴ ከስልጣን አባሮ እስር ቤት ያጎራቸው ተማሪዎች የነበሩ ልጆች አደራጅተው ያሰማሩት የገበሬ ሰራዊት መሆኑን ፈጽሞ ረስተውታል። በታሪካችን ውስጥ ትንሽ ወደኋላ መለስ ብለው ቢያዩ ሀገሪቱን ለየዘመናቸው እንዲመች አድርገው አደራጅተው ፣ ሕግ አውጥተው ፣ ዳኝነት አይተው ፣ ገበያ አቋቁመው፣ ሲያስፈልግ የጎበዝ አለቃ መርጠው ፣ ጦርነት ተዋግተው ያቆዩልን አባቶቻችን ገበሬዎች መሆናቸውን መገንዘብ ይችሉ ነበር። የገዳን ስርዓት የሚያክል አስደናቂ የመንግስት ዘይቤ የፈጠሩት ያገራችን ከብት አርቢዎች እንደነበሩ ሻምበል የሚያውቁ አልመሰለኝም። ደርግን ከመሰረቱትና ሻምበል በመጽሀፉ እንደሚነግሩን የጨረባ ተስካር በሚመስል ጉብዔ ላይ 60 ሰዎች ላይ እጅ እያወጡ ካለፍርድ ይገደሉ ብሎ ከሚወስን ወታደር የተሻለ ፍርድ ሊሰጡ የሚችሉ ብዙ ያገሬ ገበሬዎች እንዳሉ አውቃለሁ።
በዘመኑ ስፖርተኞች በብዛት በወጡበት የሚቀሩትና የሚሰደዱት ሲአይኤና ኢህአፓ እያባበላቸው ነው ብለው ይከሳሉ። ደርግ ሀገሪቱን ለልጆችዋ የሲዖል ጎሬ ያደረጋት በመሆኑ መሆኑን ከሀያ አመት በሁዋላ እንኩዋን ማየት አለመቻላቸው ገርሞኛል። ኢትዮጵያ ከደርግ በፊት በውጭ ሀገር በምቾትም እንኳን ተሰዶ ለመኖር ፈቃደኛ የሆነ ልጅ የሌላት ሀገር እንደነበረች ረስተውታል። ስደት ተቋም መሆን የጀመረው በማን ዘመን ሆነና!
ሻምበል መጽሀፉ ውስጥ የነበረውን የኢኮኖሚ ችግር በሙሉ እንዱን እንኳን እኛ ስለተሳሳትን የተፈጠረ ነው እይሉም። በራሳቸው የፖሊሲና የማኔጅሜንት ችግር በጊዜው በነበሩት የመንግስት ርሻዎችና ሌሎች የኢኮኖሚ ተቋሞች ላይ የደረሰውን ውድቀትና ኪሳራ ሁሉ በኢህአፓ ላይ ለጥፈውታል። በጊዜው ኮሎኔል መንግስቱና ተራው የደርግ አባል ሁሉ የኤክስፐርት ቦታ ተክተው ካልሰራን ሲሉ እንደነበር እዚህ ጊዜና ቦታ የለኝም እንጂ ብዙ ምሳሌዎችን መጥቀስ እችል ነበር። አንዲት እንኳን ምስሌ ሳይሰጡን በደፈናው ኢህአፓ “በተለያዩ የተንኮል ዘዴዎች የማምረቻ መሳሪያዎች በማበላሸት ወይም በማቃጠል የምርት እንቅስቃሴ እንዲቋረጥ አድርጓል”። ይሉናል። (ገጽ 253)
ሻምበል ከ1967 ዓም ጀምሮ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ያመጹባቸውንና የደመሰሷቸውን ሰዎች ሁሉ ጨፍልቀው መሬታቸው የተወረሰባቸው የመሬት ከበርቴዎች ይሏቸዋል። ያመጹ ባለመሬቶች መኖራቸው እውነት ነው። ታሪኩ ግን ይህ ብቻ አይደለም። ጠመንጃቸውን እንደጌጥ የሚወዱ በርካታ ድሀ ገበሬዎች መሳሪያ አስረክቡ ሲባሉ እንደውርደት ቆጥረው ለወንድ ልጅነት ክብራቸው ሲሉ የሸፈቱ ብዙ ነበሩ። እኔ በግል ጅባትና ሜጫ አውራጃ ውስጥ ጀልዱ በሚባል አካባቢ አስተማሪ በነበርኩበት ቦታ የሆነውን አውቃለሁ። አማራና ኦሮሞ ገበሬዎችና አነስተኛ ነጋዴዎች ናቸው። መሳሪያችንን ተውልን ብለው ለምነው ሲያቅታቸው የሸፈቱ ሰዎች በስም የማውቃቸው ነበሩባቸው። የተወሰነ ጊዜ ቢሆንም ተዋግተው የሞቱት ሞቱ። የመሬት ከበርቴ በሌለበት ሰሜን ሸዋም ተመሳሳይ ነገር መሆኑን አውቃለሁ።
ደርግ ገበሬዎችን መሳሪያ ሲገፍ ትልቅ ጠቃሚ የህብረተሰብ ባህሪ እየቀየረ መሆኑ አልገባውም። በየጥምቀቱና በአላቱ በዘፈን ላይ እንኳን “ምንሽሬ ፣ ቤልጅጌ” የሚባሉ ዘፈኖችና “መራዥ ተኳሹ” የሚባሉት የጀግንነት ፉከራዎች ቆሙ። የጀግንነት መንፈስም አብሮ ተሰበረ። እሱ ዱሮ ቀረ ተባለ። የወያኔ ጦር ሰሜን ሸዋ ከደረሰ በኋላ ኮሎኔል መንግስቱ ደብረ ብርሃን ሄደው “ጀግናው የመንዝ የመራቤቴና የቡልጋ ህዝብ ሲዘምት እንጂ ሲዘመትበት አይተን አናውቅምና ተነስ” የሚል ሰበካ ካካሄዱ በሁዋላ አንድ ዘመዴ ገበሬ ያለኝን አልረሳውም። “ይቺ ሰውዬ” ፣ አለ መንገስቱን። ፊቱ ላይ የንቀትና የጥላቻ ገጽታ አይበት ነበር። “ያኔ መሳሪያችን ገፍፋ ሴት አድርጋን ስታበቃ ዛሬ ባንድ አዳር ወንድ ልታደርገን ፈለገች አይደል? እንግዲህ እንደፎከረች ራሱዋ ትቻለው። እኛማ አንድ ጊዜ ቁጭ ብለን ሸንተናል” ነበር ያለኝ። የባቄላ ፍንካች የምታክል አንጎል ያለው ሀገር እመራለሁ ፣ አገር እወዳለሁ የሚል ሰው አንድ ሶሺዎሎጂስት ወይም ከባላገሮቹ መህል ሽማግሌዎች ጠርቶ የሚሰራው ስራ ምን እንደሚያስከትል ይጠይቅ ነበር። እርግጠኛ ነኝ ብዙ ዓመታት ከደርግ ቀደም ብለው ሀገራችንን የመሩት አፄ ምኒልክ ቢሆኑ ኖሮ አዋቂ ሳያማክሩ እንዲህ አይነት ነገር አይሞክሩም ነበር። ቢፈሩት እንኳን እንደማትነካኝ ማልልኝ ብለው መሳሪያውን ይተውለት ነበር።
ደርግበችሎታማነስናበማያውቀውነገርገብቶሳይሳካለትየቀረውንነገርሁሉሻምበልፍቅረስላሴበተለይበኢህአፓላይብዙጊዜምከተጠቀሙባቸውበሁዋላበፈጁዋቸው መኢሶንን በመሳሰሉ ደርጅቶችናመሪዎቻቸውላይእየወስዱየለጠፉትነገርማመዛዘን የጎደለው ነው። ለምሳሌ በሶማሊያ ወረራ ጊዜ ደርጉ ወስጥ የነበረውን ያመራር መዝረክረክና የሰራዊት ሽሸት ሁሉ በኢህአፓ ያመካኛሉ።እንዲህ ይላሉ፤
“የኢትዮጵያ ጦር የያዘውን ቦታ እየለቀቀ እንዲያፈገፍግ የተደረገው በሶማሊያ ጥንካሬና ግፊት ብቻ ሳይሆን በጦሩ ውስጥ የተሰገሰጉት የኢህአፓ አባላት ጦሩን በማሸበራቸውና እንዲሸሽ ቅስቀሳ በማካሄዳቸው ጭምር ነው። … የኢህአፓ አባላት በጦሩ ውስጥ ሽብር ነዙ።….. ከዚህም አልፈው በግርግርና በተኩስ መሀል መሪዎችን ከጀርባቸው እየተኮሱ ገደሉ” (ገጽ 364)
በመጽሀፉ ውስጥ ብዙ ቦታ እንደሚያደርጉት ይህን ከባድ ክስ ያስቀምጡና ክሱን የሚያስረዳላቸው አንዲት መረጃ ወይም ምሳሌ አይሰጡም። ነገሩን በደርግ ዘመንም ሰምተነዋል። ይህ የተደረገበት ልዩ ምሳሌ (specific case) በጊዜ ፣ በቦታ፣ በስም ተለይቶ ሲሰጥ ሰምተን እናውቅም። የሻምበል አይነት ስልጣን የነበረው ሰው ደግሞ ለመረጃ ቅርብ ስለሚሆን ማስረጃ ማቅረብ ሊቸገር አይገባም።
ሻምበል ፍቅረ ስላሴ በስልጣን ዘመናቸው የደረሰውን ታሪካችን የማይረሳውን ግፍ ሁሉ እንዳለ በኢሕፓና ትግሉን እናግዛለን ብለው ከውጭ ሳይቀር በረው ሀገር ገብተው ሂሳዊ ድጋፍ በመስጠት ትግሉን ለመምራት በተሳተፉ ወግኖቻችን ላይ ካለምንም ይሉኝታ ለመደፍደፍ ያደረጉት ሙከራ በጣም ያሳዝናል። ተገኘ የተባለ ጥሩ ነገር ሁሉ የደርግና የመንግስቱ ኃይለማሪያም ይሆንና የተበላሸ ነገር ሁሉ ደግሞ በነዚህ ሀይሎች ላይ ይላከካል። ሐላፊነት መውሰድ ብሎ ነገር የለም። ሌላው ቀርቶ ደርግ ከውስጥ ኢህአፓ ከውጭ አጣብቀው መከራቸውን በሚያሳዩዋቸው የመኢሶንና የሌሎች ደጋፊዎቻቸው ድርጀት መሪዎችንም ካለይሉኝታ ይከሷቸዋል። መንገስቱና ደራሲው ራሳቸውን ሳይቀር የሚመጻደቁበትን የሶሻሊዝም ሀሁ እጃቸውን ይዘው ያስቆጠሩዋቸውን ደርጅቶች መሪዎች እነ ኃይሌ ፊዳን ስልጣን ባቁዋራጭ ሊይዙ ሲሉ ደርሰው እንደገደሏቸው እያማረሩ ይነግሩናል። ካለፍርድ የተገደሉበትን ሁኔታ ሁሉ ተገቢ አስመስለው ያቀርቡታል። ከአምቦ ከተማ አለፍ ብሎ ቶኬ ከምትባል ቦታ ተደብቀው የተያዙትን የመኢሶን መሪዎች እስር ቤት እንኩዋን ሳያደርሷቸው ሜዳ ላይ እንዳረዷቸው በዚያው አካባቢ እኖር ስለነበር እየተሸማቀኩ ሰምቻለሁ። የደርግ ሎሌ ሆነው ሲያገለግሎ ጥሩ ይሆኑና በነጻነት ለመንቀሳቀስ የዜግነት መብታቸውን የተጠቀሙ ዕለት ርኩስ ይሆኑባቸዋል ለሻምበል።
ሻምበል ፍቅረስላሴ ደርግ በጥይት የፈጀውን ሠራተኛና ወጣት ሁሉ ኢህአፓ አስገደላቸ ይላሉ እንጂ እኛ ገደልናቸው አይሉም። ያየር መንገድ ሰራተኞች መንግስት ያገተባቸውን የስራተኛ ማህብር መሪ ይለቀቅልን ብለው በተነሳ ግርግር ላይ 6 ሰራተኞች በመንግስት መገደላቸውን ይነግሩንና ይህም ስለሆነ “ኢህአፓ ድል አድራጊ ሆኖ ወጣ” ብለው ያሽሟጥጣሉ። እንዴውም ግርግር ላይ “የመጀመሪያውን ተኩስ የተኮሱት የአህአፓ አባላት እንደነበሩ በተደርገ ማጣራት ተረጋግጧል” ይሉናል (ገጽ 251) ። የተጣራበትን መንገድም ይሁን ሰነድ ላንባቢው ዋቢ ለመስጠት አይጨነቁም። ደርጎቹ ከስዎቹ መሀል የተወስኑ ሰዎች አስረው ዘቅዝቀው እየገረፉና ጥፍር እያወለቁ የመረመሩዋቸው ሰዎች እንደሚኖሩ የምንገምት ሰዎች አለን። ከዚያ ያገኙትን ማስረጃ ይሆን ወይ በዬ ለማሰብ እንድገደድ አደረጉኝ። ሻምበል ፈቅረስላሴን አወዛጋቢና አከራካሪ ሊሆን የሚችል መጽሀፍ መጻፍ ያማከራቸው ሰው ዋቢ መጥቀስና ማስቀመጥ ተገቢ መሆኑን የነገራቸው አልመሰለኝም።
ደርግ የገደላቸውን የመኢሶን አባላትም በራሱ በመኢሶን ያመካኛሉ። ለምሳሌ እንዲህ ይላሉ።
“የመኢሶን መሪዎች ከኮበለሉ ብኋላ በርካታ አባሎቻቸው ላይ የመጉላላት ፣ የመታሰርና ከሥራ መባረር በሎም የመገደል አደጋ ደርሶባቸዋል። ይህ የመኢሶን የስልጣን ጉጉትና የአመራር ድክመት ውጤት መሆኑ ነው”።(ገጽ 342)
የመሪዎቹ መኮብለል በምን ተአምር ነው ደርግ ካለፍርድ ተራ አባሎቹን እንዲፈጅ ምክንያት የሚሆነው? መሪህ ስለኮበለለ ተብሎ ተከታይ የሆነ ያገር ዜጋ ካለፍርድ ይፈጃል እንዴ? ሻምበል አንዳንዱ ሎጂካቸው የተዘቀዘቀ ነው። የደርግን ወንጀል በዚህ አይነት የተውገረገረ ዘዴ ለመሸፈን መጣር በታሪክ ላይ ትልቅ የሽፍትነት ስራ መሆኑ ሻምበል የገባቸው አልመሰለኝም።
ሌላ አንድ ልጨምር። የጄነራል ተፈሪ በንቲ፣ የሻምበል ሞገስ ወልደሚካኤልና መቶ አለቃ አለማየሁ ሀይሌ በኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም የተፈጸመባቸውን ዘግናኝ አገዳደል ድራማ ይተርኩልንና ምደምደሚያ ላይ እንዲህ ይላሉ።
“የኢህአፓ መሪዎች በሀገሪቱ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ጉዳዮች ላይ የመወሰንና የማዘዝ ሙሉ ስልጣን ያለውን መንግሥት በመለመሏቸው ጥቂት የደርግ አባላት አማካይነት አንበርክከው ስልጣን ለመያዝ ይቻላል ብለው በቀየሱት ከጀብደኝነት የመነጨ ስልት ምክንያት የደርግ አባላትን ለእሳት ዳረጉ” ይሉናል(ገጽ 127)።
በራሱ በደርግ አሰራር ተመርጠው ሀላፊንት ላይ የተቀመጡትን የደርግ መሪዎች በግል ውሳኔ ከደርግ ውጭ አሲረው የገድሉዋቸውን ኮሎኔል መንግስቱን አረዷቸው እንደማለት ኢህአፓ ለሳት ዳረጋቸው ሲሉ ትንሽ አያፍሩም። የሚገርም ነው። የቀድሞ የጃንሆይ የመኪና ማቆሚያ ጋራጅ ውስጥ ከታሰሩ በሁዋላ ድምጽ በማያወጣ ጠመንጃ አስቀድመው በሚስጥር አዘጋጅተው የረሸኗቸውን መንግስቱን ነፃ አውጥቶ ሌላ የሚከስ ሰው ምን አይነት ህሊና እንዳለው ለመገመት ይከብዳል። ጄኔራል ተፈሪ ፣ መቶ አለቃ አለማየሁና የሻምበል ሞገስን በጊዜው የነበረውን የርስበርስ መጨፋጨፍ ለማስቆም መላ ያሰቡና በስልጣን ጥም ያበዱትን ኮሎኔል መንገስቱን ገለል ለማድረግ ህልም የነበራቸው ቅን ሰዎች ነበሩ፣ ሆኖላቸው ቢሆን ኖሮ የተሻለ የሰላምና የእርቅ አቅጣጫ ሊመጣ ይችል ነበር፣ ብለን የምናስብ ብዙ ኢትዮጵያዊያን መኖራችንን እንዳይገምቱ ሻምበል ፍቅረ ስላሴ ህሊና ላይ አንዳች የሚያህል መርግ የተቀመጠበት ይመስላል። ለነገሩ ሶስቱንም የደርግ አባሎች የኢህአፓ ስርጎ ገቦች ይሉዋቸዋል እንጂ ለመሆናቸው ወይም ያደረጉትን ያደረጉት ከኢህአፓ በተሰጠ ትዕዛዝ ስለመሆኑ ምንም የቀረበ መረጃ የለም። ሙዋቾቹ የደርግ አባሎች በጊዜው የያዙትን ስልጣን ያገኙት ግን በዚያ ጨለማ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ በምትመስል የምርጫ አካሄድ መሆኑን ደራሲው ራሳቸው አልደበቁም። ለመሆኑ ፍቅረስላሴና መንግስቱ በምን ምትኃት ነው ከነጄኔራል ተፈሪና ከነመቶ አለቃ አለማይሁ የበለጠ ላገርና ሕዝብ ሃሳቢ ናቸው ብለን እንድናስብ የሚጠይቁን? ሙዋቾቹ የሰሩት ነገር ጥፋት ነው ብለን ብንስማማስ እንኩዋን በዚያ ሁኔታ ከሚታረዱ ለምን ታስረው ቃላቸውን ሰጥተው ለፍርድ መቅረብ ነበረባቸው ብሎ የሚከራክር ህሊና አጡ። ያን ጊዜ ህሊናው ባይኖራቸው አይገርመኝም። ዛሬ ከብዙ ዘመን ብኋላ ይህን ማሰብ አለመቻላቸው ግን ይገርማል።
ሻምበል የጻፉት ነገር የሚያስተዛዝበውን ያህል ሊዘለል የማይገባውን ነገር መዝለላቸውም ያኑ ያህል ያስተዛዝባል። በደርጉ የመጨረሻ እድሜ አካባቢ ተነስቶ የነበረውን የከሸፈ መፈንቅለ መንግስት በተመለከት ምንም አልነገሩንም። በጃንሆይ ጊዜ ስለደረሰው ችጋር በሰፊው ተርከዋል። ብ1977 ዓ.ም ስለደረሰው ዘግናኝ የችጋር እልቂት ትንፍሽ አላሉም። የሚያመካኙባቸውን ሁሉ ጨርሰው ስለፈጁ የሚለጥፉበት አካል ስላጡ አስመሰለባቸው። አከራካሪ ስለነበረው ቤተሰብን መተከልና ጋምቤላ እስከመክፈል ስለደረስው ቅጥ ያጣ የሰፈራ ፕሮግራም ምንም አላሉም። ስለዚያ በጅጉ በድንቁርና ላይ ስለተጀመረ መንደር ምስረታ ስለሚባል የዕብደት ስራ ምንም አላሉም። እኔ ከገበሬዎች እንደተማርኩት ገበሬዎች ዳገታማ ጭንጫማ ጥግ እየፈለጉ መኖሪያ ቤት የሚሰሩት መሬቱ ጭንጫማ ስለሚሆንና ተፋሰስም ስለሚኖረው በክረምት ከብቶቻቸው አረንቋ እንዳይገቡ ፣ የማይታረስ መሬትም ላይ ስለሚሰፍሩ የርሻ መሬት ለማትረፍ ፣ ለጥ ያለው ሜዳ ደግሞ ውሀ ስለሚተኛበት ለሳርና ለግጦሽ እንጂ ተፋሰስ ስለሌለው ለቤት መስሪያና ለከብት በረት ስለማይሆን ነው። ይህን ነገር አቅርበው መንደር ምስረታውን ስለሞገቱ የታሰሩ ገበሬዎች አጋጥመውኛል። ደራሲው ከነገሩን ነገር ይልቅ ያልነገሩን ብዙ ነው።
የፖለቲካ አመራር ማድረግ የሚቻለውን ነገር ባግባቡ የማድረግ ጥበብ በተለይም አስቸጋሪ ቅራኔን መፍታትና ስምምነት የመፍጠር ነው። ይህንን የማያውቁ፣ አንዴ እንዲቀናቸው የጠቀማቸው ዘዴ ለሁሉም ችግር መፍቻ የሚጠቅም የሚመስላቸው የፖለቲካ መሪዎችና ሀይሎች ከውድቀት አያመልጡም። ብዙ የፖለቲካ መሪዎች የሚፈልጉትን ነገር ወይም ለፕሮፓጋንዳ ብለው የሚያወሩትን ነገር ራሳቸው ደጋግመው ይሰሙና እንደውነት ያምኑታል። ያን ጊዜ ነገር ይበላሻል። ማስተዋል ሁሉ ቦታውን ለዕብሪት ይለቃል። በደርግም ላይ ሆነ በሌሎች አምባገነኖች ላይ የሆነው ይህ ነው። የደርግ ታሪክ ባጭሩ ሲጠቃለል ይኸው ነው። ሌተና ኮሎኔል መንግስቱን ሀገር ወዳድ እያሉ ሊሸጡልን የሚፈልጉ ሰዎች አሉ። ሻምበልም ሊሸጡልን እንደሚሞክሩት ኮሎኔል መንግስቱ ከስልጣናቸው በላይ ሀገራቸውን የሚወዱ ሰው አልነበሩም። በግትር አምባገነንነትና ራስ ወዳድነት ሀገርና ህዝብ የጎዱ ሰው ናቸው ኮሎኔል መንግስቱ። በተግባር ያየነው ይህንን ነው።
ስላለፈ ነገር መጻፍ ጥሩ የሚሆነው መማሪያና ማስተማሪያ የሆነ እንደሆን ነው። ሻምበል ስለደርግ ይኖራቸዋል ብለን የገመትነውን የሚያክል ከደርግ ጥፋትና ልማት የምንማርበት መማሪያ በዚህ መጽሀፍ ላይ አልሰጡንም። ወደፊት ይክሱን ይሆናል የሚል ተስፋ አለኝ።