“የቆየ ቁጭትና ቁርሾ ነው”
ከጎልጉል ድረ ገጽ
December 24, 2013
በአማራ ክልል የተካሄደውን ሹም ሽር ተከትሎ የተሰጠው ሹመትና የሹም ሽሩ አካሄድ መነጋጋሪያ ሆነ። “በቃኝ አሉ የተባሉትን ባለስልጣን አውርዶ እንደገና መሾም የተነቃበት የህወሃት የማረጋጊያ ጨዋታ ነች” ሲሉ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ተናገሩ። በሹም ሽሩ የአቶ ደመቀ መኮንን እጅ እንዳለበትና መንስዔውም “የቆየ ቁጭትና ቁርሾ” እንደሆነ ተጠቆመ።
የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አያሌው ጎበዜ ከመንበራቸው እንዲነሱ ተደርጓል። የመንግስት ልሳን መገናኛዎች እንዳመለከቱት አቶ አያሌው ከሃላፊነታቸው የተነሱት ታህሳስ 9/2006 በተጠራ አስቸኳይ የክልሉ ጉባኤ ነው። አዲስ ሹመት ያስፈለገው አቶ አያሌው ባቀረቡት “የመተካካት” ጥያቄ እንደሆነም ተመልክቷል። ምትካቸው የነበሩት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የክልሉ ፕሬዚዳንት ሆነዋል።
አቶ ገዱ ፕሬዚዳንትነታቸው በጉባኤ ተወስኖ ይፋ ከመደረጉ ጎን ለጎን ዜና የሆነው የሳቸው ሹመት ሳይሆን የአቶ አያሌው ስልጣናቸውን በፍላጎታቸው መልቀቃቸው ነው። አቶ አያሌው የ”በቃኝ” ጥያቄ ማቅረባቸው ከተሰማ ብዙ የቆየ ቢሆንም አሁን አስቸኳይ ጉባኤ ተጠርቶ የተወሰነበት ምክንያት ዜናውን አነጋጋሪ ያደረገው ጉዳይ ነው።
የአቶ አያሌው ከሃላፊነታቸው መነሳት ከግራና ቀኝ መነጋገሪያ በሆነ ማግስት ኢህአዴግ የሙሉ አምባሳደርነት ሹመት እንደሰጣቸው ይፋ መደረጉም ሌላ ግርምት ፈጥሯል። በ”መተካካት” ሰበብ ከስልጣን ተነሱ የተባሉት አቶ አያሌው “ባለሙሉ ስልጣን” አምባሳደር ሆነው መሾማቸው ደግሞ የሹም ሽር ተውኔቱን “ኮሜዲ” አሰኝቶታል ያሉና በማህበራዊ ድረገጾች መዝናኛ ያደረጉት ጥቂት አይደሉም።
ምክትላቸው የነበሩትና አሁን ዋናውን መንበር የጠቀለሉት አቶ ገዱ “ብዙ ጉድ አለባቸው” የሚሉ ወገኖች ወቀሳ መሰንዘርና መጠየቅ አለባቸው በማለት መከራከር ከጀመሩ ቆይተዋል። የአማራ ክልልን እንዳሻቸው ይጋልቡታል ከሚባሉት አቶ በረከት ስምዖን ጋር የጠነከረ ወዳጅነት እንዳላቸውና ከህወሃት የደህንነት ቁንጮ መዋቅር ጋር በቅርበት እንደሚሰሩ የሚታሙት አቶ ገዱ “ጉዳቸው የተሸፈነው ባላቸው የታማኝነት መረብ (ኔትወርክ) ነው” በማለት የቅርብ ሰዎቻቸው ይከሷቸዋል።
ገዱ አንዳርጋቸው
በድርጅት በተወሰነ ውሳኔ አቶ አያሌው እንዲለቁ የተደረገውን ወንበር የተረከቡት አቶ ገዱ “ህወሃት ለሚያወርደው ማናቸውም መመሪያ ለመተግበር የፈጠኑና የታመኑ ከመሆናቸው በዘለለ ክልሉን የመምራት ብቃት እንደሌላቸው እናውቃለን” በማለት አስተያየት የሰጡ፤ የአቶ አያሌው ወንበር ለመነጠቁ ደረጃቸው በውል የማይታወቀውን ምክትል ጠ/ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እንደ ምክንያት ያነሳሉ።
አቶ ደመቀ በክልሉ በግልጽ በሚታወቅ ስልጣን የአቶ አያሌው የበታች ሆነው የሚሰሩ ቢሆንም፣ የክልሉን የጸጥታና የደህንነት ጉዳይ ከህወሃት ሰዎች ጋር በመሆን ይሰሩ ስለነበር ከአቶ አያሌው ቁጥጥርና ትዕዛዝ ውጪ እንደነበሩ የሚጠቁሙት ክፍሎች “አቶ አያሌው በስብዕና ደረጃ እስካሁን በክልሉ ከተሰየሙት መሪዎች የተሻሉ፣ በባህሪያቸው ረጋ ያሉና ለክልሉ ህዝብም በንጽጽር ተቆርቋሪ የነበሩ” በማለት ይገልጹዋቸዋል። በዚህም የተነሳ “ሎሌ” በሚል ስያሜ የሚጠሩት አቶ ደመቀ ብዙም እንደማይፈልጓቸው፣ በዚህ ምክንያት የልብ ወዳጃቸውና ለህወሃት በታማኝነት በመታዘዝ የሚመሳሰሏቸውን አቶ ገዱን ለሃላፊነት እንዳበቋቸው ይገልጻሉ። በሌላም በኩል ለሱዳን እንዲሰጥ በተወሰነውና ሰሞኑንን የድንበር ማካለሉ ተግባራዊ እየሆነ እንዳለ የሚነገርለትን የኢትዮጵያን መሬት ለሱዳን እንዲሰጥ የተፈረመውን ስምምነት የሚያነሱም አሉ።
አቶ አያሌው ስምምነቱን አልፈርምም በማለታቸው ሳቢያ አቶ ደመቀ እንዲፈርሙና የኢትዮጵያን ህጋዊ መሬት ለሱዳን አጨብጭበው እንዲያስረክቡ በታዘዙት መሰረት ተግባራዊ ማድረጋቸው በክልሉ የተተፉ፣ በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ደግሞ የተረገሙ አድርጓቸዋል። እኚሁ ከህወሃት በቀር ዘመድና ወዳጅ የላቸውም የሚባሉት አቶ ደመቀ “አያሌው ተገዶ መፈረም ነበረበት” በሚል ሲቆጩ እንደነበር የሚናገሩ አሉ። በባህር ዳር የሚኖሩና ለአቶ ደመቀ ቤተሰቦች ቅርብ የሆኑ “አቶ ደመቀ በኩራት የኢትዮጵያን ድንበር እልል ብለው በባንዳነት ወደውና ፈቅደው ካስረከቡ በኋላ ልጆቻቸው ፊደል ከሚቆጥሩበት የህጻናት ማሳደጊያ እንኳን መቀመጥ አልቻሉም ነበር” በማለት አቶ ደመቀ ላይ የደረሰውን የጥላቻ ስርና ጥንካሬ ያስረዳሉ። እንደ እኚሁ ሰው ገለጻ ከሆነ አቶ ደመቀ የትምህርት ሚኒስትር ሆነው አዲስ አበባ እንዲዛወሩ የተደረገበት አንዱ ምክንያት ይኽው ልጆቻቸው ድረስ የዘለቀው ጥላቻ ጉዳይ ነው።
ከዚህ ማህበራዊ ቀውስ በኋላ አቶ አያሌውን በመልካም የማያይዋቸው አቶ ደመቀ የብአዴን ሊቀመንበርና ከአራቱ ጠ/ሚኒስትሮች መካከል አንዱ በመሆናቸው ጊዜ ወስደው አቶ አያሌው እንዲነሱ ጉባኤ ላይ ድምጽ ያሰጡባቸው፣ ድምጹንም አስቆጥረው ደስታቸውን የገለጹ፣ ወዲያውም ተመሳሳያቸውን መንበር አሰጥተው ደስታቸውን እጥፍ ድርብ ማድረጋቸውን ጉባኤው ላይ የነበሩ ለጎልጉል ገልጸዋል።
አቶ አያሌው በትክክል “ስልጣን በቃኝ፣ ለተተኪው ክፍል አስረክባለሁ” ቢሉ አምባሳደር ሆነው ባልተሾሙ ነበር የሚሉት እነዚሁ ወገኖች፣ “በቃኝ፣ ደከመኝ፣ ተኩኝ፣ ልተካ ብሎ የጠየቀ ባለስልጣን ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር አድርጎ በበነጋው መሾም ከሹም ሽሩ ጀርባ ችግር እንዳለ የሚያሳይ ነው” ብለዋል። አቶ አያሌው ባስቸኳይ ስብሰባ ከስልጣናቸው መነሳታቸው ቅሬታ እንዳይፈጥርና ሌሎች ባለስልጣናት ላይ የመደናበር ስሜት እንዳያስከትል በሚል “ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር” ተደርገው መሾማቸውን ያመለከቱት ወገኖች “አካሄዱ የህወሃት የተቃጠለ ስልት ነው። ብአዴን ውስጥ ውስጡን እየጨሰ ነው። አቶ ገዱ ያበርዱት እንደሆን ለወደፊቱ የሚታይ ይሆናል” ሲሉ ከሁሉም ጨዋታ ጀርባ ሌላ ችግር መኖሩን አመላክተዋል። አቶ አያሌው የልማት አርበኞችን ከማፍራት አኳያ በስኬት ጉድለት አቶ ገዱን ክፉኛ መገምገማቸውም ይታወሳል። አቶ ደመቀ የትምህርት ሚኒስትር ከሆኑ በኋላ ስራው ከክልል የስለላ ስራ የተለየ አቅም የሚጠይቅ በመሆኑ በሃላፊነታቸው ደስተኛ እንዳልነበሩ ሲገለጽ መቆየቱ አይዘነጋም።