By Goolgule.com
November 22, 2013
በሳዑዲ አረቢያ በኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰውንና እየደረሰ ያለውን ፈር የለቀቀ አስነዋሪ ግፍ ዓለምአቀፍ ይዘት እንዲኖረው ለማድረግ ከሰብዓዊ መብት ተሟጋች እና ሌሎች ዓለምአቀፋዊ ድርጅቶች ጋር እየሠሩ መሆናቸውን አቶ ኦባንግ ሜቶ በተለይ ለጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ ተናገሩ፡፡ የሳዑዲ ልዑል ሰብዓዊነት የረገፈበትንና በግፍ የተሞላ የወሮበላ ተግባር የሚፈጸምበትን አሰቃቂ ተግባር የሚከናውኑትን አንጋቾች አሞካሹ፡፡
ያለ አንዳች ልዩነት ኢትዮጵያውያን በኅብረት ድምጻቸውን በማሰማት እየተቃወሙት ያለውን ኢሰብዓዊ ተግባር አስመልክቶ በተለያዩ መንገዶች ይፋ ከሆኑት በተጨማሪ ድብቅ መረጃዎች እየተሰበሰቡ መሆናቸውን ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) ዋና ዳይሬክተር አስታውቀዋል፡፡ ዳይሬክተሩ አቶ ኦባንግ ሜቶ የጋራ ንቅናቄው ከዓለምአቀፍ የመብት ተቋማት ጋር በቅርበት እየተሰራ ስላለው ዝርዝር ጉዳይ ግን ከሁኔታው ምስጢራዊነት አኳያ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡
“አልዘገዩም” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱም “አኢጋን ችግር በተከሰተ ቁጥር የሚቋቋምና የሚፈርስ የዕቁብ ይዘት ያለው ድርጅት አይደለም፡፡ ወይም እሣት ሲነሳ ድምጽ እያሰማ እንደሚከንፍ የእሣት አደጋ መኪና የሚመሰል ድርጅት አይደለም” በማለት የጋራ ንቅናቄውን የተጠና አካሄድ በመጠቆም የመለሱት አቶ ኦባንግ ይህ ችግር እንደሚከሰት አስቀድሞ ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውን ተናግረዋል፡፡
ችግሩ አስቀድሞ እንደሚከሰት ቢታወቅም ምላሽ የሚሰጥ ብቃት ያለው አካል ባለመኖሩ አንገት የሚያስደፋና ኃፍረት የሚላብስ፤ “አገር አለኝ ወይ?” የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ በኢትዮጵያ ታሪክ ተሰምቶና ታይቶ የማይታወቅ ኃፍረት ሊደርስብን ችሏል፡፡ “ይሁን እንጂ” አሉ ኦባንግ “ይህ መራር ዜና ከተሰማበት ሰዓት ጀምሮ የጋራ ንቅናቄው የበኩሉን” ሲያደርግ መቆየቱን አመልክተዋል፡፡
“ከተለያዩ ዓለምአቀፋዊ ተቋማት፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ አግባብ ካላቸው መንግሥታዊ አካላትና በተለያየ ደረጃ ላይ ከሚገኙ የሳዑዲ ባለስልጣናት ጋር ተነጋግረናል” በማለት አቶ ኦባንግ ተናግረዋል፡፡ ለዓብነት ያህልም የሳዑዲ ም/ጠ/ሚ/ር እና የመከላከያ ሚ/ር፣ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር፣ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚ/ር፣ የፍትሕ ሚ/ር እና ሌሎች ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸውን የመንግሥት መ/ቤቶችን ጨምሮ በአውሮጳና በሰሜን አሜሪካ የሚገኙትን የሳዑዲ ኤምባሲዎችን እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽነርን፣ የአፍሪካ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ACHPR)፣ ወዘተ ማነጋገራቸውንና በየደረጃውም ምላሽ ማግኘታቸውን አመልክተዋል፡፡
በመላው የመካከለኛው ምስራቅ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ዕረፍት የሚሰጥ እንዳልሆነ የጠቆሙት “ጥቁሩ ሰው” ሳዑዲ ካላትና ከምትከተለው “የበርህን ዝጋ ፖሊሲ” አንጻር በአካል በቦታው ላይ ከመገኘት ይልቅ አቅም ካላቸው ዓለምአቀፋዊ አካላት ጋር በአፋጣኝና በቅርበት መሥራቱ ድርጅታቸው የወሰደው አማራጭ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የሎጂስቲክሱ ጉዳይ መስመር ሲይዝም የጋራ ንቅናቄው ከዚህ በፊት በየአገራቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ጉዳይ ሲያስፈጽምበት የነበረውንና በውጤታማነቱ የሚታወቀውን አማራጭ እንደሚተገብር ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ኢህአዴግ አገርን እንደሚያስተዳድር ድርጅት በዜጎቹ ላይ እየደረሰ ያለውን አስነዋሪ ተግባር ትኩረት ሰጥቶ አለመመከቱ ተቃውሞ አስነስቷል፡፡ ይህንኑ አስመልክቶ አቶ ኦባንግ ሜቶ “ወገኖቻችንን ድንበር በማሻገርና ኤጀንሲ ከፍተው ወደ አረብ አገራት ሲልኩ የነበሩት ሁሉ ሕግ ፊት ቀርበው ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ የተለያዩ ተግባራት” እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ሼክ መሐመድ አላሙዲ የሠራተኛ ኃይል ወደ ሳዑዲ እንዲላክ ከኢህአዴግ ጋር በይፋ ስምምነት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡ ኢንቨስትመንትን በተመለከተ ከሚፈልጉበት ክልል መሬት ለመውሰድ፣ ከሚፈልጉበት ባንክ ኮሪደር ገንዘብ ለመበደር ገደብ የሌላቸውና በሞቀበት ሁሉ ባለመጥፋት በጀት መድበው በሚያስተዳድሯቸው ሚዲያዎች እንዲሁም አንደበታቸውን በሙስና ላሰሯቸው ባለሥልጣናት “ኢትዮጵያዊ ነኝ” እያሉ በተገኙበት ቦታ ሁሉ ለሚዲያ ፍጆታ የሚደሰኩሩትና ግጥም የሚያስደረድሩት ሼክ መሐመድ አላሙዲ፣ “ወገኔ” የሚሉት ሕዝብ በአባታቸው አገር ወሮበሎች ሲያልቅና ሲጨፈጨፍ ዝም ማለታቸው ኢንቨስትመንቶቻቸውን ጥያቄ ውስጥ ከትቷል፡፡
አንዳንዶች እንደሚሉት ይህ አሰቃቂ ድርጊት መስመር ለቅቆ ከመውጣቱ በፊት የሳዑዲ አረቢያ ዜጎችን ከርስ እንዲሞላ በኢትዮጵያ የተቋቋመው ሳዑዲ ስታር ኩባንያ በገንዘብ እጥረት ሊዘጋ እንደሚችል መዘገቡ የሚታወስ ነው፡፡ በወቅቱ ሪፖርተር ባወጣው ዘገባ ሳዑዲ ስታር በኪሣራ ወደ መዘጋት መድረሱ የኩባንያው “ባለቤት የሆኑትን ሼክ ሙሐመድ አል አሙዲንና የሳዑዲ ዓረቢያን ስም የሚያጎድፍ ከመሆኑም ባሻገር፣ ኢትዮጵያ ውስጥ እስኪታክት የተወራለት ይህ ፕሮጀክት መና መቅረቱ ሁለቱን አካላት በሕዝቡ ዘንድ ለከፍተኛ ትችትና ወቀሳ እንደሚያጋልጣቸውም” ጠቁሞ ነበር፡፡
በአሁኑ ጊዜ “ሕገወጥ ናችሁ” በሚል ሰብዓዊነት የጎደው እርምጃ እየተወሰደባቸው ያለው የበርካታ አገራት ዜጎች በተለይም ኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈጸመውን ሰቅጣጭ ተግባር ሕገወጦችን የማባረር “ዘመቻ” በማለት ያቃለሉት የሳዑዲው አገር ውስጥ ሚ/ር ልዑል ሞሐመድ ቢን ናይፍ ወንጀለኛ ሬንጀር ለባሾችን፣ ፖሊሶችንና ወሮበሎቹን ሸባቦች አደፋፍረዋል፡፡ “ዘመቻው ይቀጥላል … በተወሰነ ጊዜ የተገደበ አይደለም” በማለት “እስክንጨርስ እንጨርሳችኋለን” የሚመስል የማፊያ መሪ መሰል መልዕክት ለአንጋቾቻቸው አስተላልፈዋል፡፡
አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን በሕጋዊነት የሚኖሩትም ጭምር በሳዑዲ ያለው ሁኔታ አሳሳቢነት ወደፊት ችግር ውስጥ ሊከትታቸው እንደሚችል በመገመት ወደ አገራቸው መመለስ ይፈልጋሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ለከፍተኛ ሰቆቃ የተጋለጡት ኢትዮጵያውያን “ቤት አለን ቤታችን መልሱ” እያሉ የሰቆቃና የድረሱልን ጥሪ በሚያስተላልፉበት ወቅት ሰብዓዊነት የጎደላቸው የኢህአዴግ መሪዎች ይህ ነው የሚባል አፋጣኝ ምላሽ መስጠት አለመቻላቸው “በእርግጥ ኢትዮጵያውያን አገር አላቸው?” ብሎ የሚያስጠይቅ እንደሆነ በርካታዎች የሚጋሩት ነው፡፡
አቶ ኦባንግ በበኩላቸውም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለአንድ ሳምንት ሥራውን አቋርጦ እንኳን ቢሆን ስደተኞቹን ባፋጣኝ የማመላለስ ተግባር መፈጸም ይገባው ነበር በማለት ቁጭታቸውን ተናግረዋል፡፡ ዜጎች በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ህይወታቸው እየተቀጠፈ “3ሺህ ዛሬ ገቡ … ድምሩ 10ሺህ ሆኗል …” የሚል የሞላ ጎደለ ቁማር ዓይነት ጨዋታ በትዊተር መጫወት የቴድሮስ አድሃኖምን ዘመነኛነት ሳይሆን ለሰውልጅ ህይወት ያላቸውን ደንታቢስነት የሚያሳይ መሆኑን ሁኔታው ያስቆጣቸው አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ አቶ ኦባንግም “ቤቴ መልሱኝ” ብሎ ለሚለምን አንድ ዜጋ የተከፈለው ተከፍሎ ትራንፖርት በማቅረብ ክቡር ህይወትን በአስቸኳይ ለመታደግ አለመቻል ለትውልድ የሚተላለፍ የታሪክ ጠባሳ መሆኑን በአጽዕኖት ተናግረዋል፡፡