June 19, 2013
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ባለፈው ሳምንት በቻይና ጉብኝት አድርገው ነበር፡፡ ቻይና በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ተፈላጊነቷ እየጨመረ ከመጣባቸው ምክንያቶች ውስጥ ያለፖለቲካዊ ቅድመ ሁኔታና ከጣልቃ ገብነት ነፃ በሆነ መንገድ የምትሰጠው ድጋፍ፣ የምታካሂደው የግንባታ ሥራ እንዲሁም የምትሰጠው የረጅም ጊዜ ብድር ተደማምሮ አጋርነቷን የማይፈልገው አገርም መንግሥትም የለም፡፡
ከዚያም በላይ በዓለም ላይ ልዕለ ኃያልነቷ እየጨመረ በመምጣቱ ቻይናን ወዳጁ የማያደርግ አገርም ሆነ መንግሥት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ስሌቱ ላይ የስህተት መስመር እንዳሰመረ የሚቆጠርበት ጊዜ ይመስላል፡፡ የአፍሪካ ድሃ አገሮችን ብቻም ሳይሆን የአውሮፓ ሀብታም አገሮችም ጭምር ከገቡበበት ማጥ እንድታላቅቃቸው ቻይናን መማጸን የያዙበት የዓለም ታሪክ የቻይናን የበላይነት እያሳየ ነው፡፡
እንዲህ ያለው አቋሟ ግን እንደኢትዮጵያ ላሉት አገሮች ያስከተለው ጫና ጥቂት የሚባል እንዳልሆነ የሚናገሩ አሉ፡፡ ‹‹ገና ለገና ብድርና ዕርዳታ ይሰጡናልና በአገራችን ውስጥ እንዳሻቸው ሲሆኑ ዝም ማለት ተገቢ አይደለም፤›› የሚሉና ሌሎችም ትችቶች ከሚቀርቡባቸው ተቋማት አንዱ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ከፍተኛ ኃላፊዎቹ በእስር ላይ የሚገኙት የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ነው፡፡
ባለፈው ሳምንት ከምሥራቅና ከምዕራብ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ግብር ከፋዮች ጋር ‹‹ግብዓት ለመሰብሰብ›› በማለት ባለሥልጣኑ በጠራው ስብሰባ ላይ ከተደመጡ በርካታ የግብር ከፋዩ ችግሮችና እሮሮዎች ውስጥ ያልተለመደና አዲስ ሆኖ የቀረበው ይኸው የቻይኖቹ አጭበርባሪነት ነበር፡፡ ቻይኖችን ብቻ ሳይሆን ቋንቋና ባህላቸውን እንደሚያውቅ፣ ለሰባት ዓመታትም በቻይና ትምህርቱን እንደተከታተለ የገለጸው ወጣት (ስሙን እንዳንገልጽ ጠይቋል)፣ ኢንቨስተር ተብለው ከሚመጡት ቻይኖች ውስጥ አብዛኞቹ አቅም ሳይኖራቸው፣ በአገራቸው መሥራትም ሆነ የሥራ ጫናውን መቋቋም ሳይችሉ የሚመጡ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡ አቅም እንኳ ኖሯቸው ሲመጡ ቋንቋ የማይችሉ በመሆናቸው (ቢያንስ እንግሊዝኛ መናገር የማይችሉ) ቀድመው በመጡ የራሳቸው ወገኖች ሳቢያ ወደአጭበርባሪነቱ ጎራ እንዲገቡ ይደረጋሉ ይላል፡፡
ለቻይኖቹ ብቻ ሳይሆን ለባለሥልጣኑም ቻይንኛን (ማንዳሪን) በማስተርጎም ሲሠራ የቆየው ወጣት እንዳስረዳው፣ ለአገሩ እንግዳ፣ ለሕዝቡ ባዳ የሆኑ ቻይኖች ወደአገር ውስጥ ሲገቡ ካለባቸው የቋንቋ ችግር ሳቢያ ነባር ቻይኖችን ለመጠቀም ይሞክራሉ፡፡ ነባሮቹ ደግሞ በማጭበርና ጉቦ በመስጠት የተካኑ በመሆናቸው መጤዎቹን በዚያው መንገድ ያሰለጥናሉ፡፡
ከባለሥልጣኑ የሒሳብና የኦዲት ባለሙዎች ጋር በመመሳጠር፣ ጉቦ በመስጠት የታክስ ክፍያ ያስቀራሉ፣ አለያም ያሳንሳሉ፡፡ ለዚህ ውለታቸው ኦዲተሮቹና አካውንታንቶቹ ጠቀም ያለገንዘብ ይቸራቸዋል፡፡ እንዲህ ያለውን መመሳጠር ተክነውበት በቅርቡ ሦስት ቻይኖች የሐሰት የቫት ደረሰኝ አትመው ሲጠቀሙ መያዛቸውን ወጣቱ ለሪፖርተር ተናግሯል፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ሌላ ግለሰብም የሐሰት ቫት ደረሰኝ ከሚታተምባቸው የአዲስ አበባ መንደሮች ውስጥ ንግድ ሥራ ኮሌጅ አካባቢ አንዱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ባለሥልጣኑ በአካባቢው በተሠሩ አዳዲስ ሕንፃዎች ውስጥ ድንገተኛ ጉብኝትና ፍተሻ ቢያካሂድ በቀላሉ ሊደርስበት እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ከ600 ያላነሱ ቻይኖች ‹‹ቢዝነስ›› እየሠሩ እንደሚገኙ መንግሥት አስታውቋል፡፡ ሆኖም ከእነዚህ ውስጥ ምን ያህሉ ትክክለኛና የተፈቀደላቸው መስክ ላይ እየሠሩ እንደሚገኙ፣ ምን ያህሉ በትክክል ታክስ እንደሚከፍሉ መንግሥት ከመናገር ይቆጠባል፡፡ አይከታተላቸውም፡፡ ከዚህ በከፋ ሁኔታ በቻይና ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥረው በሚሠሩ ኢትዮጵያውያን ላይ ቻይኖቹ የሚያደርሱትን የጉልበት ብዝበዛም ሆነ አካላዊ ጥቃት አይቶ እንዳላየ፣ በማስረጃም ሲቀርብለት እንዳልሰማና እንዳላወቀ ማለፉ ክፉኛ ቢያስተቸውም ዝምታን ይመርጣል የሚባለው መንግሥት፣ አሁን ደግሞ ቻይኖቹ በሙስና አገሩን ከማበላሸት አልፈዋል የሚል ስሞታ እየቀረበለት ይገኛል፡፡
መጤዎቹ ቻይኖች ወደተለያዩ የመንግሥት መሥርያ ቤቶች ጉዳያቸውን ለማፈጸም ሲያቀኑ፣ የመንግሥት ኃላፊዎች ጉቦ ካልተሰጣቸው በቀር ጉዳያቸውን እንደማያስፈጽሙላቸው በአስተርጓሚ ስለሚነገራቸው፣ ለባለሥልጣኑ ሁሉ ገንዘብ ይሰጣሉ የተባሉት ቻይኖች ከዚህም የከፋ ሥራ ይሠራሉ፡፡ አብዛኞቹ ቻይኖች የባንክ ሒሳብ መግለጫ የሌላቸው ስለመሆኑ የአደባባይ ሚስጥር እንደሆነም ሪፖርተር ያነጋገራቸው ይናገራሉ፡፡ ቻይኖቹ አዘውትረው ገንዘባቸውን ወደአገራቸው የሚልኩት በባንክ በኩል ሳይሆን በከተማው ውስጥ የቻይና ሬስቶራንቶች ባለቤት ከሆኑት ጋር በመመሳጠር፣ በእነሱ በኩል በጥቁር ገበያ አማካይነት ገንዘብ የሚያስወጡ መሆኑን አጥብቀው የሚያውቋቸው ይናገራሉ፡፡ ጠጠር አምርተው የሚሸጡ ሁለት የቻይና ኩባንያዎች ሹዋን ሎንግ እና ጁ ሎንግ እንደሚባሉ ጭምር ተገልጿል፡፡ እነዚህ እንግዲህ ጠጠር ለማምረት ፈቃድ ያልተሰጣቸው እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከአትክልትና ፍራፍሬ ጀምሮ እስከ ራቁት ዳንስ ቤት ሳይቀር የሚቸረችሩ ቻይኖች በአዲስ አበባ መበራከታቸው እየታየ፣ በየጓዳው ያልተፈቀደላቸውን ሥራ በድብቅ ከመሥራት አልፈው በኢትዮጵያውያን ስም ፈቃድ በማውጣት የሚነገዱ እንዳሉም ወጣቱ በስብሰባው ወቅት ተናግሯል፡፡ በዘበኞቻቸውና በሾፌሮቻቸው ስም ንግድ ፈቃድ እያወጡ ለውጭ አገር ዜጎች የተከለከሉ መስኮች ላይ በመሠማራት እንደሚሠሩ ሲነገር የቆየ ቢሆንም፣ አንድም የመንግሥት አካል ዕርምጃ ስለመውሰዱ አስታውቆ አያውቅም፡፡ የቻይና መንግሥት እንዳይቀየም የሰጉ ይመስላሉ የሚል ስሞታ ለመንግሥት ባለሥልጣናት እየቀረበባቸው ይገኛል፡፡
የቻይኖቹን የገንዘብ መንገድ የሚያውቁት የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ኦዲተሮችና አካውንታንቶች፣ በአንድ ወቅት በቡድን ሆነው የባለሥልጣኑን ማኅተም በማስቀረፅ በየቻይኖቹ ደጅ እየሄዱ ከባለሥልጣኑ የተላኩ በማስመሰል ከፍተኛ ገንዘብ ይቀበሉ እንደነበር፣ ይህንንም ጉዳይ ለባለሥልጣኑ ኃላፊዎች አቤት ብሎ እንደነበር ወጣቱ የሪፖርተር ምንጭ አስታውቋል፡፡
ባለሥልጣኑ ከውስጥም ከውጭም እንዲህ ለሙስናና ለማጭበርበር መጋለጡ ብቻ ሳይሆን በእውነት ለመሥራት ብለው የሚመጡት ቻይኖች የአገሪቱን ገጽታ በመጥፎ መልኩ እንዲገነዘቡት የሚያደርግ መሆኑ እንደሚያሳስበው ወጣቱ ተናግሯል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ በቻይናውያን ዘንድ በሙስና የታወቀች ሆና ተገኝታለች፤›› ያለው ወጣት፣ በትክክለኛው መንገድ ቢዝነስ ለመሥራት የሚመጡ ቻይኖች በየቦታው ሲሄዱ ገንዘብ እየተጠየቁ ደንግጠው እንደሚጠፉ ተናግሯል፡፡ በቅርቡ የዓለም ባንክ ይፋ ያደረገው ጥናት ሙስና በአገሪቱ ሕዝብ ዘንድ እንደሚሰጠው ግዙፍ ሥዕል የገዘፈ አይደለም ማለቱ ቢታወቅም፣ ዋናውን የመንግሥት ገቢ ሰብሳቢው አካል በከባድ ሙስና ወንጀል የሚጠረጠሩ ባለሥልጣናት ሲመሩት እንደቆየ ከሰሞኑ ግርግር ለመረዳት ተችሏል፡፡
እንዲህ ያሉ ወቅታዊ የቻይኖችን አሳሳቢ እንቅስቃሴ ይፋ ያደረገው ስብሰባ፣ የተለመዱና ባለሥልጣኑ ላይ ሲሰነዘሩ የከረሙ ሌሎች ትችቶችንም ያስተናገደ ነበር፡፡ የማዕድን ዘርፍ እየተቀለደበት ነው ያሉት ከምሥራቅ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ግብር ከፋይ የሆኑ ነጋዴ ናቸው፡፡ ምንም እንኳ የከበረ ድንጋይ አገር ውስጥ የማይሸጥ ቢሆንም 20 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ እንደተጣለበት፣ ይህም ሳያንስ ለሚያመጡት ማሽን ቀረጥና ታክስ ክፈሉ መባሉ (መንግሥት ቅርፅ ያልወጣለት የከበረ ድንጋይ ለውጭ ገበያ እንዳይቀርብ ዕገዳ ጥሏል) መስኩ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የሚመደብ ቢሆንም፣ ባለሀብቶች እንደማይበረታቱበት ሲናገሩ ለውጤቱ ማሳያ ያደረጉት አገሪቱ በየዓመቱ ከዘርፉ የምታገኘውን የ4.5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በመጥቀስ ነበር፡፡ በአንጻሩ እንደህንድ ያሉ አገሮች ከኢትዮጵያ በጥሬው የሚረከቡትን የከበረ ድንጋይ (ከራሳቸውም ጭምር) በማስዋብና በቅርፅ በማበጀት በዓመት እስከ 35 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚያገኙበት ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ሁሉ ባሻገር ሙስና ሲሠራ ያየና የጠቆመ ሰው ‹‹አንተን ብሎ ጠቋሚ›› ተብሎ መታሰሩን እንደሚያውቁ የገለጹት እኒህ ባለሀብት፣ ሥጋታቸውንና ምክራቸውን ጨማምረው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ግድ የላችሁም እንተማመን ወንጀል ሠርተን የትም አናመልጥም፡፡ እናንተም የትም አታመልጡም ሰሞኑን እያየነው ነው፡፡ ለአንድ ዓላማ ከቆምን (የአንድ ዓላማ እኩል ባለድረቦች ነን የሚለውን የባለሥልጣኑን መፈክር በመንተራስ) ባለማወቅ የሚፈጸሙ ስህተቶችን ሆነ ተብለው ከሚፈጸሙት ጋር ለይታችሁ ተመልከቱ፤›› በማለት አስተያየታቸውን ያቀረቡት ጋስ የተባለውን የግል ኩባንያ ወክለው እንደመጡ የገለጹ ነጋዴ ሲሆኑ፣ ይህንን ቅሬታቸውን ያቀረቡትም ከሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ ቀላል ስህተቶችን ባለሥልጣኑ አክብዶ በማየት ለከፍተኛ ቅጣትና እስር እንደሚያበቃ በማስታወስ ነው፡፡
ግብር ከፍለው የማያውቁ ሰዎች ግብር በመክፈል አበሳውን ከሚያየው ዜጋ እኩል፣ አንዳንዴም ከዚያም በላይ የጥቅም ድርሻ እንዲያገኙ መንግሥትም ዕድሉን እንደሚፈጥርላቸው የገለጹት ደግሞ ሚካኤል መኮንን የተባሉ ነጋዴ ናቸው፡፡ ከኪነ ጥበብ ሙያ ጋር የተገናኙ ሥራዎችን የሚያካሂዱት እኒህ ግለሰብ እንደገለጹት፣ መንግሥት በቅርቡ እንኳ ገቢያቸው ዝቅተኛ ለሆኑ ሰዎች በማለት የቤት ልማት ፕሮግራሙ ላይ ማለትም የ20/80 አሠራርን ምሳሌ ሲያደርጉ በዚህ የቤት ባለቤት ለመሆን ከሚመዘገቡ ሰዎች ውስጥ ግብር ከፍለው የማያውቁና ቅድሚያ ሁሉ የተሰጣቸው ሰዎች የሚያገኙትን ገቢ ጠቅሰው እንዲመዘገቡ ማድረጉን በመግለጽ ተችተዋል፡፡ በአንጻሩ ግን ከ151 ብር ጀምሮ ገቢ ያላቸው ሰዎች ግብር የሚከፍሉ ሰዎች ከማይከፍሉት ጋር እኩል እንዲጋፉ መደረጉን በመጥቀስ የመንግሥትን አሠራር ነቅፈዋል፡፡ ለግብር ከፋይ ቅድሚያ የማይሰጥ ብቻ ሳይሆን ማግኘት የሚገባው ጥቅምም በመንግሥት ዕውቅና ግብር ከፋይ ላልሆኑ ሰዎች ተላልፎ እንደሚሰሰጥበት ተናግረዋል፡፡ ባልተከፋፈለ የትርፍ ድርሻ ላይ የተከማቸ ፍሬ ግብር ከነመቀጫውና ወለዱ እንድንከፍል ተደርገናል (ምንም እንኳ መቀጫው ተነስቷል ቢባልም)፣ የጉምሩክ ዋጋ አሰቃይቶናል፣ የግብር ከፋይነት መለያ ኖሮት የፌደራል ግብር ከፋይ ያልሆነ ነጋዴ በክልሎች አሠራር መቸገሩን የሚተቹና ሌሎችም ስሞታዎችን ያደመጠው የባለስልጣኑ ስብሰባ በለውጥና ሞደርናይዜሽን ሥራዎች ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አቶ አብርሃም ንጉሤ፣ እንዲሁም በምሥራቅና በምዕራብ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ መሥርያ ቤቶች ኃላፊዎች ታጅቦ የተካሄደ ሲሆን፣ ከሌሎቹ ጊዜያት የባለሥልጣኑ ስብሰባዎች በተለየ መልኩ የተካሄደም ነበር፡፡ እነዚህ ኃላፊዎች ለተሰነዘሩባቸው ተችቶችና ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ያልፈለጉበት፣ ይልቁንም የቀረቡትን ሐሳቦች እንደሚቀበሉና በቀጣዩ ጊዜ ሲገናኙ ምላሽ የሚያቀርቡ መሆናቸው ገልጸው፣ ግብር ከፋዩን ያሰናበቱበት መድረክ ነበር፡፡ ከአንዳንድ ታዛቢዎች እንደሚደመጠው፣ በአሁኑ ወቅት ያሉት ኃላፊዎች በእስር ላይ ከሚገኙት የቀድሞ ባለሥልጣናት መታሰር ጋር በተያያዘ ድንጋጤ ብቻ ሳይሆን በቀጥታ ውሳኔ መስጠቱን እየፈሩ እንደሚታዩ፣ አንዳንዴም በአደባባይ ‹‹በሕግና በመመርያ ብቻ እንሠራለን እስር ቤት የሚወረወርላችሁ የለም›› እስከማለት መድረሳቸውን የታዘቡ አካላት የሚናገሩት ነው፡፡