ኢትዮጵያ፡ ከዚህ በኋላ ቀጣዩ ጉዟችን (ወይም መቆሚያችን) ወዴት ነው?

ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም

ትርጉም ከነጻነት ለሃገሬ

በዴሞክራሲ የአንድነት ጎዳና ላይ?

በጁን 2012 ‹‹ኢትዮጵያ፡ በሕገ መንግስታዊ ዴሞክራሲ ጎዳና ላይ›› የሚል ጦማር አቅርቤ ነበር፡፡ ‹‹በርካታማ ሕበረሰቦች ከጭቆና ወደ ዴሞክራሲ ሽግግርን ሲያስቡና ሲንቀሳቀሱ፤ እንቅስቃሴያቸውን የሚገቱ በርካታ ፈተናዎች›› እንደገጠሟቸው በማስረጃ የተደገፉ ታሪካዊ እውነታዎችን ጠቅሼ ነበር:-

ከአረብ ‹‹መነሳሳት››ከታየው ልምድ በመነሳት ሕገ መንግስታዊ ቅድመ ውይይት እንደሚያስፈልግ ጠቁሜ አንዳንድ ሃሳቦችም ሰንዝሬ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግስት ፍለጋና የዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግስት ግቡ ዙርያ ጥምጥም መንገድ፤ አድካሚና ተስፋ ሞጋች ይሆናል፡፡ይም ሆኖ የማይቻል አይደለም………..ግጭትን አስወግዶ ሰላማዊ ሽግግርን ተግባራዊ ለማድረግ፤ተፎካካሪ አለያም በተናጠል ያሉት ሁሉ በአንድ ላይ መስራት ይኖርባቸዋል፡፡ ይሄ ደግሞ በዋናው ግብ ላይስምምነትንና መቻቻልን መግባባትን ይጠይቃል፡፡ በዚህ የሽግግር ወቅት ሕዝባዊ የሲቪክ ማሕበረሰብን በአዲሱ ሕገ መንግስት ዙርያ ማስተማርን ያካትታል፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ድርጅቶች፤ አመራሮች፤ ምሁራን፤ ሰብአዊመብት ተሟጋቾች፤ እና ሌሎችም የጉዳዩ አካላት፤ ስርአት ባለው ፕሮግራም ተካተው ትምህርትና አስተባብሮ ማሰለፍን መውሰድና ማዳረስ በዚህም ለዴሞክራሲ ሽግግር የሚጠቅመውን ሁሉ ተግባራዊ ማድረግ  ይኖርባቸዋል፡፡ ከጭቆና ስርአት ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ስኬታማ የሆነ ሂደት ለማድረግ ኢትዮጵያዊያን የመነጋገርንና የመመደራደርን ጥበብ ሊማሩ ይገባል…….››

እነሱ በታችኛው የጭቆና ጎዳና ላይ የኋሊት እየተዘወሩ ነው፤ እኛስ በዴሞክራሲ አውራጎዳና ላይ ወደፊት እየተጓዝን ነው?

ለአንዳንድ ሰዎች ለገዢዎች ባለስልጣኖች ወይንም ለመጪው እውነቱን መንገር ቀላል ነው፡፡ ያለምንም ችግር እነዚህን ስልጣንን አላግባብ የሚጠቀሙትን ጥፋት መስራታቸውንና ልክ አለመሆናቸውን ማሳወቅ፤ ጥፋታቸው ምን እንደሆነ፤ጥፋታቸውን እንዴት ማረም እንደሚችሉና ጥፋት ለፈጸሙባቸውም ትክክል በማደረግ ማሳረም አንደሚችሉ፡፡ ነገር ግን ‹‹ማንነታቸውን›› መለየት በማይቻልበት “ተቃዋሚዎች” እውነትን ማሳወቁ ቀላል አይደለም፡፡ ስለዚህም ላልታወቁት “ተቃዋሚዎች” ለማስረዳት ከሞመከር ይልቅ: “እነሱ በታችኛው  የጭቆና ጎዳና ላይ የኋሊት እየተዘወሩ ነው፤ እኛስ በዴሞክራሲ አውራጎዳና ላይ ወደፊት እየተጓዝን ነው? ከዚህ በኋላ ቀጣዩ ጉዟችን (ወይም መቆሚያችን) ወዴት ነው? የሚል ጥያቄ ማንሳት እመርጣለሁ፡፡ ይህን መሰሉ ጥያቄ መሰንዘር ያለበት ‹‹ለተቃዋሚ አመራሮች ነው››:: ግን ለጥቂትጊዜያትም እነዚህ አመራሮች እንማንናቸው እንማንስ አይደሉም በሚል ግራ መጋባት ውስጥ ነበርኩ፡፡

ባለፈው ሴፕቴምበር ‹‹የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች በዴሞክራሲ ማለዳ ወቅት?››  በሚል ርእስ አንድ ጦማር አቅርቤ ነበር፡፡ ድምጼን ከፍ አድርጌ (እስካሁን መልስ ባላገኝም) ‹‹በኢትዮጵያ ተቃዋሚው ማነው?›› ብዬ ጠይቄ ነበር፡፡ አሁንም ሆነ ያንጊዜ ግራ እንደተጋባሁ መሆኔን መናዘዝ እወዳለሁ፡፡ ‹‹በአግባቡ የተደራጀና የማያወላውል አስተማማኝ ተቃዋሚ ፓርቲ እንደሌለ እረዳለሁ:: አንድም ጠንካራና ግንባር የፈጠረ የህብረት ፓርቲ  የገዢውንመንግስት ፖለቲካም ሆነ ፍልስፍና የሚሞግት የለም፡፡ በምሑራን ግንባር ቀደምትነት የተቀናጀና የተጠናከረ አንድም ፓርቲ ያለ አይመስልም፡፡ ሁሉንም ሙያዎችና ማሕበራት፤ሃይማኖቶችን ያቀፈ የሲቪል ማሕበረሰብ ስብስብም የለም፡፡ ለወጥ ባለ አባባል፤ ‹‹ተቃዋሚው ያው ከዚህ በፊት እንደሚታወቀው ደካማ፤ ልፍስፍስ፤ ቅርጽ ያልወጣለት፤ ተጣምሮ አሁንም ከነድክመቱ፤ተከፋፍሎ፤ እርስ በርስ ለመናቆር የሚሽቀዳደሙትና ለገዢውፓርቲ የመጠናከርያና የግዛት ማራዘም አስተዋጽኦ የሚያደርጉት ናቸው? ያው አሁንም በማጉረምረም ብቻ ሰብአዊ መብትን ለማስከበር የሚጥሩት፤ የሲቪክ ማሕበረሰቡን የሚያደራጁት፤ጋዤጠኞች ተብዬዎቹ አገልጋዮች፤ እና ፈራ ተባ የሚሉት ምሁራን ናቸው? በመሳርያ ገዢውን ሃይል ገርስሰው የሚጥሉት ናቸው ተቃዋሚዎች? እራሱን በተቃዋሚነት ፈርጆና ሰይሞ ያስቀመጠችው/ው ሁሉ ናቸው ተቃዋሚዎች:  ወይስ ከላይ የተዘረዘሩት አንዳቸውም አይደሉም?

የመጨረሻዋን እንጥፍጣፊ ብሬን ለውርርድ የማቀርብበት ጉዳይ ግን የመለስ ዜናዊ አምላኪ ደቀመዝሙራን ከዚህ በኋላ ወዴት ወዴት ነው የምትሄዱት ቢባሉ ለማስረዳት አንዳችም ችግር የለባቸውም፡፡ በእርግጠኛነትም: ሰማይና መሬት ቢደበላለቁም፤ በመለስ ‹‹ዘልዓለማዊ አሸብራቂ ኮቴ ፈለግ›› እየተመራን አሸሸ ገዳሜያችንን እያስነካን፤ ጮቤ አየረገጥን የሀደሰና ግድብ ሥር የተቀበረልንን ወርቅ ለማፈስና በየዓመቱም 10. 12. 15 በመቶ የኤኮኖሚ እድገት እያልን ከፍ ከፍ ብለን በመብረር መንገዳችንን እንቀጥላለን ይሉናል……….›› እኔም የጉዞ አውራ ጎዳና ቀይሶ ወደ የህልም  መንገድ መሄዱ  ክእጅና እግርን አጣጥፎ ማፋጨት ለእናት ሃገር ከመቆዘሙይሻላል ባይ ነኝ፡፡

ለመሆኑ ጥያቄው ተቃዋሚ መሆን ወይም አለመሆን ነው እንዴ? በተቃዋሚ ጎራስ መሆን ማለት ምን ማለት ነው? በተቃዋሚ ጎራ ውስጥስ ለመካተት አንድ ሰው ምን ሊያከናውን ወይም ሊያደርግ ይገባዋል? ተቃዋሚ መሆንስ ገዢውን ፓርቲና በውስጡ የተካተቱትን በመሳደብ በማጥላላት፤ በመፎከር፤ጥርስ በመንከስ፤ ስልጣንን አለአግባብ የሚጠቀሙትን በመውቀስና በመተቸት በስድብ ላይ ስድብ መከመር ነው? ስልጣንን አለአግባብ የሚጠቀሙበትንስ በመቃወም በተቃውሟችን የሞራል የበላይነትስ ማግኘት? እነዚህን አለአግባብ ማንኛውንም ጉዳይ የሚጠቀሙበትን ያለ እቅድ ያለግብ መቃወምስ ተቃዋሚነት ነው?

በተደጋጋሚ እንዳስቀመጥኩት የመለስ እምነቱ ‹‹ተቃዋሚዎች እራሳቸውን ከሚያውቁት በላይ መለስ ተቃዋሚዎችን ማወቁ ነው››::

መለስ በተቃዋሚዎቹ ከምር የስቅባቸው ነበር፡፡ የተቃዋሚዎችን አመራሮች የእውቀታቸው ደረጃ ከሱ ታች አድርጎ ነበር የሚገምተው፡፡ባስፈለገው ወቅትና ጊዜ፤ ሊያፌዝባቸው፤ሃሳባቸውን ሊያጣጥል፤ ሊበልጣቸው፤ማንም ከማንማ ሳይል ሊያላግጥባቸው እንደሚችል ያምን ነበር፡፡እርባና ቢስ ብሎ ስለሚያስባቸው፤ ለስልጣኑ አስጊና ተቀናቃኝ ይሆናሉ የሚል ስጋት አልነበረውም፡፡ በሚያደርጋቸው ሕዝባዊ ዲስኩሮቹ ሁሉ እንዳፌዘባቸው፤ እንዳዋረዳቸው፤መሳቂያ መሳለቂያ ሊደርጋቸው እንደሞከር ነበር፡፡ ተቃዋሚዎቹን የዕለት ተዕለት ክትትልና ቁጥጥር  ከጥፋታቸው እንዲመለሱም ቁንጥጫና ትንሽም በሳማ ለብ ለብ እንደሚያስፈልጋቸው ጨቅላ ሕጻናት ነበር የሚያያቸው፡፡ እንደእውነቱ ከሆነም ባለፉት የግዛት ዘመኑ መለስ ተቃዋሚዎቹን እንዳለውም በሁሉም መልኩ ቀድሟቸው በልጧቸው፤ ቀልዶባቸው፤ መሳቂያ አድረጓቸው ነበር፡፡አሁንም የመለስ ደቀመዝሙሮችና እሱ የፈጠራቸው በፈጠረላቸው ብቻ የሚመሩት የራሳቸው የሆነ አንዳችም ነገር የሌላቸው ‹‹ሰብ ግዑዛን›› በመራቸው መንገድ የውርየድንብራቸውን ለመጓዝ ነው እቅዳቸው፡፡

‹‹ተቃዋሚዎች›› አሁን የት ናቸው? 

ምናልባት በኢትዮጵያ ያሉትን ‹‹ተቃዋሚዎች›› ከእንግዲህ ጉዟችን ወዴት ነው የሚለውን ጥያቄ ማንሻ ጊዜው አማካኝ ላይሆን ይችላል፡፡ይልቁንስ አሁን ተቃዋሚዎች የት አሉ (የትም የሉም) የሚለውን መጠየቁ አግባብ ሊሆን ይችላል፡፡ ለኔ አመቺው ነጥብ፤‹‹ተቃዋሚው በአሁኑ ጊዜ፤ ወደ በቃኝ፤ አጉራህ ጠኛኝ፤ ወደ ተስፋ መቁረጡ፤ ወደ መሳቀቁ፤  ገለል ወደ ማለቱ ነው፡፡ ‹‹ተቃዋሚውን›› እንደተደገመበት አይነት ፈዝዞ ስልጣንን አለአግባብ ተከተለ ነው ማለት እችላለሁ፡፡ ‹‹ተቃዋሚው›› ደህንነት ያጣ፤ አጀንዳ ቢስ፤ አቅመ ቢስ፤ አቅጣጫ ቢስ፤ ራዕይ የሌሌለው ሆኖ ነው የሚታየኝ፡፡ ‹‹ተቃዋሚው›› ግራ የተጋባ፤ ተሸመድምዶ ያለ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ‹‹ተቃዋሚው›› አንድ ላይ የሆነበት፤ በአንድ የቆመበት፤ጠላትን በአንድ ላይ የተጋፈጠበት፤እና በአንድ ላይ ለወህኒ የበቃበትም ጊዜ ነበር፡፡ የ2005 ምልሰት! ያኔ ‹‹ተቃዋሚው›› የዘርን፤ የጎሳን፤ የሃይማኖትን፤ የቋንቋን፤ የዓላማን እና ሌሎችንም ልዩነቶች ወደ ጎን አሽቀንጥሮ ጥሎ ለነጻነትና ለዴሞክራሲ በአንድነት የቆመበት ወቅት ነበር፡፡ ያ ራዕይ ደግሞ ተቃዋሚዎችን በወንድማማችነትና እህትማማችነት መንፈስ አስተሳሰራቸው፡፡ ‹‹ተቃዋሚው›› አንድ ሆኖ መለያየትን ትቶ በቅንጅት፤ ውስጣዊ መቆራቆስን በመተው ሊከፋፍሉትና ሊያለያዩትበሚጥሩት ላይ በአንድነት ቆሞ አሸነፋቸው፡፡

ባለፉት ሰባት ዓመታት፤ ‹‹የተቃዋሚዎች›› የነጻነትና የዴሞክራሲ ራዕይ ቀስ በቀስ ባለመግባባትና በመወነጃጀል እየከሰመ ሄዷል፡፡በተቃዋሚው ጎራ መወያየት በመነታረክ ተተክቷል፤ ተግባርም ወደ ባዶነት፤ ሕብረት ወደመለያየት፤ መቀናጀት ወደ ግላዊነት፤ መሰባሰብ ወደ መለያየት፤ መፈቃቀር ወደ መጠላላት፤ መቻቻል ወደ አለመግባባት ተለውጧል፡፡ ‹‹ተቃዋሚው›› ለውጥን ይፈልጋል:: በለውጡም ኢትዮጵያን ከጭቆና በማላቀቅ የዴሞክራሲ ባለቤት ሊያደርጋትይመኛል፡፡ ግን ዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁንየር እንዳሉት፤ ‹‹ለውጥ በመንኮራኩር ተጭኖ የማይቀር ነገር አይደለም: ሊገኝ አይችልም፤በማያቋርጥ የነጻነት ትግል እንጂ፡፡ ወገባችንን ጠበቅ አድርገን ለነጻነታችን መጣር አለብን፡፡ ወገብህ ለመጥ ካላለ ጠላትህ ሊጋልብህ አይችልም… ከልምድ እንዳየነው ጨቋኝ ገዢ ነጻነትን በፍቃደኛነት አይሰጥምበተጨቋኞች መገደድ ይኖርበታል››

የኢትዮጵያ ‹‹ተቃዋሚ›› ሃይሎች፤ ወገቡን ጠበቅ አድርጎና ጥርሱን ነክሶ ፍላጎቱን ማሳወቅና ማግኘት አለበት፡፡ ወገብን ማጥበቂያዎች በርካታ መንገዶች አሉ፡፡ስለሰብአዊ መብት መከበር መናገርና፤ ገዢዎች የሚያደርሱትን በደል ግፍና ጭቆና መናገርም ወገብን ማጠንከር ነው፡፡ ጥፋቶች መስተካከል እንዳለባቸው መሞገትም ቀበቶን ማጥበቅ ነው፡፡ በእኩዮች ፊት ዓይን መግለጥና የተደፈነ ጆሮን እንዲሰማ ማድረግ ጠንክሮ መቆም ነው፡፡ ለማንም ቢሆን አግባብነት ከሌለው አሻፈረኝ ማለት መቻል ብርታት ነው፡፡ ለገዢ ባለስልጣናት ስህተታቸውን ማሳወቅ ጥንካሬ ነው፡፡ ዶ/ር ኪንግ እንዳሉት ‹‹የፍፁምነት ሕግ አለያም ምሉዕ ሕግ ከሰው ሰራሽ ደንብ ጋር የሚጣጣም የሞራል ሕግ ወይም የፈጣሪ ሕግ ነው፡፡ ሕጋዊነት ያጣ ሕግ ደሞ ከሞራላዊ ሕግ ጋር የማይጣጣም ነው::››  በጃንዋሪ 2011 ሳምንታዊ የሆነ ጦማር ‹‹ከአፍሪካ ጨቋኝና ግፈኛ ገዢዎች ውድቀት በኋላ›› አቅርቤ የሚከተሉትን ጥያቄዎች አንስቼ ነበር፡፡‹‹በአሸዋ የተገነባው የፈላጭ ቆራጭ ገዢዎች ግንብ ሲደረመስና የቅዠት ቤተ መንግስታቸው ፍርስረሱ ሲወጣ አፍሪካ ምን ትሆናለች? አፍሪካ መላቅጡ የጠፋ ትሆንና መልሶ ለመገንባት የምታስቸግር ፍርስራሽ ትሆናለች? የፈላጭ ቆራጮቹስ መጨረሻስ ምን ይሆናል?

ባለፈው በጋ ወራት ያለፈው የጨቋኞች ስርአት ገንቢው መለስ ዜናዊ ካለፈ በኋላ በኢትዮጵያ ያለው የጭቃ ግንብ መስፋፋትን እያስመሰከረ ነው:: የታሪክ ሚስጥራዊነት ግን አሁን ያለው ጥያቄ እኩይ ገዢዎች ላለፉት ሁለት አሰርት ዓመታት ሊያደርጓት እንደሞከሩትና ኢትዮጵያ ትፈራርሳለች ወይስ ትጠነክራለች የሚለው አይደለም፡፡ እነዚያ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ቀና ማሰብ የሚጎመዝዛቸው የእርኩስ መናፍስት ስሪቶች ከሚያመልኩትና አንቀጥቅጦ ሲያምሳቸው ከነበረው የቅዠት ሳጥን ሞት በኋላ እርስ በርሳቸው ወደ ፍርስራሽነት በመንደርደር ላይ

ናቸው፡፡ ባለሕልም እንጀራቸው ሲሞት የነሱም እንጀራቸው እያረረና እየሻገተ ነው፡፡ አባባሉ እንደሚያስረዳው‹‹በዕውራን አምባ አንድ አይና ብርቅ ነው›› አሁን እንግዲህ አይነ ብርሃናቸው የለም ከዚሁ ጋርም በራሳቸው ጥፋት፤ ተንኮል፤ ድክመትና መሰሪነት የሚይዙት የሚጨብጡት ጠፍቷቸው በመደነባበር ላይ ናቸው፡፡

አሁን ‹‹አጣዳፊው ጉዳይ›› ኢትዮጵያዊያን ተቃዋሚ መሪዎች ለዴሞክራሲ ያላቸውን እቅዳቸውንና ራዕያቸውን በአስቸኳይ ማዘጋጀት ነው፡፡ኢትዮጵያዊያን የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በሕግ የበላይነት የሚመራ ሕብረተሰብ ለመፍጠር ራዕያቸውን ማቀድ ያለባቸው አሁን ነው፡፡ኢትዮጵያዊያን የተቃዋሚ መሪዎችም የመገናኛ መረቦቻቸውን በጥንቃቄና በእርጋታ በመዘርጋት ከየአቅጣጫው ያለውን የሕብረተሰብ ክፍል በማሰባሰብና በመረቡ ግለሰቦችንም ሆነ ማሕበረሰቡን፤ በአንድ የማሰለፉ ወቅት አሁን ነው፡፡ ከጭቆና አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርአት የሚደረገውን ሽግግር ምሁራን ማመቻቸት ያለባቸው አሁን ነው፡፡ ሁሉም ነጻነትና ዴሞክራሲን የሕግ የበላይነትን የሚፈልግ ሁሉ አሁን ነው በአንድ ላይ ለመቆም ስምምነታቸውን ይፋ በማድረግ መንቀሳቀስ ያለባቸው፡፡ ካለፈው የግፍ ሰንሰለት ማነቆ እራሳችንን ማለቀቂያው ጊዜ አሁን ነው፡፡ ለሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች ስንል የተጫነብንን የዘርና የጎሳ ፖለቲካ አሽቀንጥረን መጣያው ወቅት አሁን ነው፡፡ ለብሔራዊ አንድነት መቆሚያና መሰባሰቢያችን አሁን ነው፡፡ ለሃቅና ለይቅር ባይነት መወሰኛችን አሁን ነው፡፡ እራሳችንን ከጭቆና እኩይ ምግባርተኞች አላቀን፤ሰብአዊ ክብራችንን የምናረጋግጥበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ አሁን እርስ በርስ የመወነጃጀያና የመለያያ የጣት መቀሰርያ የእልህ መወጫና የእርስ በርስ መናቆሪያ ወቅት አይደለም፡፡ አሁን እስቲ ይሁና በማለት አፋችንን የምንለጉምበት ጊዜ አይደለም፡፡ አሁን አይናችን እያየ አላይም የሚልበት ጊዜ አይደለም:: ጆሯችን አሁን አይደለም አልሰማም ማለት ያለበት ሊከፈት ሊያዳምጥ ሊሰማ የግድ ወቅቱ ነውና፡፡

ከዚህስ በኋላ ጉዟችን ወዴት ነው? ከዚህ በኋላ የራሴን ጥያቄ እኔ አጠር አጠር እያደረግሁ ለመመለስ እሞክራለሁ፡፡ ተቃዋሚው ሃይል ዴሞክራሲያዊ አስተዳደርን ለመምራት በጎዳናው ላይ መሆን አለበት፡፡ በቅድመ ዴሞክራሲ ጭቆና የነበረችውን ኢትዮጵያን ለመገንባት

ተቃዋሚው ሃይል የዴሞክራሲ ድርጊት እቅዱን በአግባቡ መንደፍ አለበት፡፡ ዋነኛው ካለፉት ሰባት ዓመታት ልንማርና መስወገድ ያለብን ለመቃወም በሚል ብቻ ዝም ብሎ መቃወም መቃወም መቃወም ያለግብና ዓላማ ሊሆን አይችልም፡፡ የተቃዋሚዎች ሚና በስልጣናቸው የሚባልጉትን መቃወም ከሚለው ባለፈ ሊሆን ይገባል፡፡ የተቃዋሚዎች ድርሻ በሃገሪቱ ላይ በሚመሰረተው ዴሞክራሲያዊ ስርአት እቅድና ራዕይ ላይ መሆን ይኖርበታል፡፡ የጨቋኞች የተጠያቂነትን ጉዳይ ሰምተው እንዳልሰሙ ሊያስመስሉ ይጥራሉ::  ያ ምንም ማለት አይደለም፡፡ ዋናው ነገር ተጠያቂነትን መቼ አምነውይቀበላሉ ነው፡፡ ለተቃዋሚዎች ጨቋኞች ያደረሱትን ግፍና በደል መቁጠርና በዚያ ላይ ማላዘኑ በቂ አይደለም፡፡ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በአግባቡ በጥንቃቄ ታስበበትና ተመክሮበት ሊወጣ የግድ ነው፡፡

እንደ መግቢያ ተቃዋሚው ስለተጠያቂነትና ግልጽነት ጥርት ያለ አቋሙን ለሕዝቡ በማያዳግምና በማያወላዉል መልኩ ማስቀመጥ አለበት፡፡ለምሳሌ ስር ሰዶ ኢትዮጵያንና ሕዘቦቿን እየቦረቦረ በማጥፋት ላይ ያለውን የጨቋኞች ስሪት የሆነውን ሙስና ለማጥፋት ተቃዋሚዎች ምን ለማድረግ ነው ያቀዱት፡፡ የዓለም ባንክ በጥንቃቄ የተዳሰሰ 448 ገጽ ያለው ዘገባ ኢትዮጵያ በዓለም አሉ ከሚባሉት በሙስና የዘቀጡ ሃገሮች አንዷ እንደሆነች አስነብቧል፡፡ ከተቃዋሚ ድርጅቶች መሪዎችም አለያም ከአባሎቻቸው ይህን ዘገባ ምን ያህሉ እንዳነበቡት አለያም በሙስናና በብክነት ላይ የራሳቸውን ዳሰሳ እንዳደረጉ መናገር ባልችልም፤ ይህን ዘገባ ያነበበ ማንም ቢሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው ስር የሰደደ የሙስና ነቀርሳ ጥርጣሬ ሊኖረው አይችልም፡፡

ለሥልጣን ለሚበቃው እውነትን ማሳወቅ 

ይህ የጻፍኩት አንዳንዶቹን ሊያበሳጫቸው ሌሎቹን ደሞ ሊያንድዳቸው ይችላል፡፡ ብዙዎችን ደግሞ የሚያበረታታቸውና ጠንካራና ደፋር እርምጃ ነው እንደሚሉ እርግጠኛ ነኝ፡፡ አንዳንድ አቃቂር አውጪዎች እኔ በምቾት ፈረሴ ላይ ተኮፍሼ ‹‹ተቃዋሚውን እንደተሳደብኩ አድርገው በመውሰድ ምላሳቸውን ሊሰብቁ ይቃጣታቸው ይችላል፡፡ ተቃዋሚውን እያዳከምኩና ዝቅ አድርጌ እየተመለከትክ ነው ሊሉኝ ይችላሉ፡፡ሌሎችም የተቃዋሚውን ሚና አጋነንክ ሊሉ ይችላሉ፡፡ ከዚህ ባለፈም ለ‹‹ተቃዋሚዎች›› ባደረጉት መስዋእትነትና እኔ ከማደርገው በበለጠ ለሰብአዊ መብት መሟገታቸውን በማሳነስ የሚገባቸውን ከበሬታ አልሰጠሃቸውም ነፍገሃቸዋል ሊሉኝም ይችላሉ፡፡ እኔ የማደርገው ጨቋኝ የሆኑት አምባገነን ገዢዎች ከሚያደርጉት ጋር ተመሳሳይ ነው ሊሉም ይዳዳቸዋል፡፡ እኔ በተመቻቸ የምሁር ወንበሬ ላይ ተቀምጬ ያለሁ የተቃዋሚዎች ተግባርና አካሄድ ሊገባህ አይችልም ብለው ሊወቅሱኝ ይችላሉ፡፡ የሆነውይሁን!

ምንም እንኳን እነዚህ አባባሎች አቅጣጫ ማስለወጫ ቢሆኑም ሁላችንም ‹‹በተቃዋሚ›› ጎራ ነን የምንል ሁሉ ልንመልሳቸው የሚያስፈልጉን ሁለት ጥያቄዎች አሉ፡፡ ጨቋኞችና አምባገነን እኩዮች በጨቋኞች ጎዳና ላይ እንደግመልሽንት የኋሊት እየተዘወሩ ነው እኛስ በዴሞክራሲ አውራ ጎዳና ላይ ወደፊት አየገሰገስን ነው? የተቃዋሚው ጎራ ከ2005ቱ ከነበረበት ሁኔታ ዛሬ በተሸለ ደራጃ ላይ ነው?

*የተቶረገመው ጽሁፍ (translated from):

http://open.salon.com/blog/almariam/2013/02/10/ethiopia_where_do_we_go_or_not_go_from_here

(ይህን ጦማር ለሌሎችም ያካፍሉ::) ካሁን በፊት የቀረቡ የጸሃፊው ጦማሮችን  ለማግኘት እዚህ ይጫኑ::

http://www.ecadforum.com/Amharic/archives/category/al-mariam-amharic

http://ethioforum.org/?cat=24