ከፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም ከነጻነት ለሃገሬ
ወርሃ ኦክቶበር (ጥቅምት)በአለም የጡት ካንሰር ማሳሰቢያና ማስገንዘቢያ ወቅት ነው፡፡ ወሩን በሙሉ በዓለም ላይ ሕዝባዊና የግል ድርጅቶች የፕሮግራሞቻቸውና የእንቅስቃሴዎቻቸው ትኩረት ሁሉ በጡት ካንሰር መንስኤ ላይ በማትኮር፤ አደጋውን ለመቀነስ፤ ቅድመ ጥንቃቄ ስለማድረግ፤ ህክምናና ምርምር በማከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡ በእርግጠኝነት በተረጋገጠው መሰረት በአብላጫ በዓለም ላይ ሴቶችን በማጥቃት ላይ ያለው የጡት ካንሰር ነው፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶች በበሽታው በየዓመቱ ሲለከፉ ከነዚህም መሃል በሢ የሚቆጠሩት ለሞት ይዳረጋሉ፡፡ኮመን ፎር ዘ ኪዩር የተባለው የአሜሪካ ድርጅት እንደአስቀመጠው በአሜሪካን የሚገኙ አብላጫዎቹ አፍሮ አሜሪካውያን መሃል ሁለተኛው ገዳይ በሽታ የጡት ካንሰር እንደሆነ ያረጋግጣል፡፡ በአፍሪካ ስለዚህ ገዳይ በሽታ የታማሚ መጠንና ስለሚያደርሰውም አደጋ አያም ስለሚሰጠው ትኩረትና ህክምና በትክክል እንዲህ ነው ለማለት ዘገባም ሆነ መግለጫ ስለሌለ ብዙ ማለት ያስቸግራል፡፡ በአፍሪካ የበሽታው ሁኔታ ሊታወቅ የሚችለው ታማሚው በበሽታው ተይዞ ለህክምና ወይም ለመመርመር ወደ ጤና ጣቢያ አለያም ህክምና ማእከል ሲሄድ ብቻ ነው፡፡ አብላጫው የሴቶች ቁጥር በሚኖርበት የገጠሩ ክፍል ስለበሽታው ሁኔታ መዝግቦ መያዝና ማስረጃዎችን ማሰባሰቡ በብዙም የተለመደ ወይም ሁኔታ የተፈጠረለትም አይደለም፡፡ ስለበሽታው ሁኔታ ክትትልና ዘገባም ሆነ ስለበሽተኞቹ ሁኔታ ጥናት ማካሄድን ከምር ይዘው በማስኬድ ላይ የሚገኙት ጥቂት የአፍሪካ ሃገራት ናቸው፡፡
የጡት ካንሰርና የሕክምና አገልግሎት በኢትዮጵያ
በኢትዮጵያ የጤና ባለስላጣናት በሚያወጡት ሪፖርት ላይ የጡት ካንሰር ቅድሚያ የሚሰጠው በሽታ ሆኖ አይታይም፡፡ በሃገሪቱ ካለው የጤና ላዕላይ መዋቅር ደካማና ያልተመጣጠነ መሆን፤ የጤና ማእከል እጥረት፤ለጤና ካለው ደካማ ትኩረት አኳያ፤ ይህ አዲስ ነገር ሆኖ ባይታይም ይቅር የሚባል ጉዳይ ግን ጨርሶ ሊሆን አይችልም፡ ፡ በኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ላይ የሚታየው ስታትስቲክስ የጨለመና ልብ የሚሰብር ጉዳይ ነው፡፡
እንደ 2006ቱ የዓለም ጤና ድርጅት(WHO) ዘገባ መሰረት፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 77 ሚሊዮን ተብሎ ተገምቷል፡፡ ይህን ታላቅ የሕዝብ መጠን የህክምና አገልግሎት ለመስጠትም 1,936 ሃኪሞች አሉ (1 ዶክተር ለ 39,772 ሰዎች)፥ 93 የጥርስ ሀኪሞች (1 ለ 828,000 ሰዎች)፥ 15,544 ነርሶችና የልምድ አዋላጆች (1 ለ 4,985 ሰዎች)፥ 1,343 ፋርማሲስቶች (1 ለ 57,334 ሰዎች)፥ እና 18,652 የጤና ባለሙያዎች (1 ለ 4,128 ሰዎች) አሉ:: የሃገር ውስጥ ጠቀሜታ በመቶ ሲሰላ ለጤና ይሚወጣው 5.9 በመቶ ነው፡፡ አጠቃላይ የመንግስት የገንዘብ ፍሰት ድርሻን በጤና ላይ በተመለከተም 58.4 በመቶ ሲሆን ተራፊውን 41.6ቱን የሚሸፍኑት የግል ባለሃብቶችና ድርጂቶች ናቸው፡፡ የህክምና መኝታ አልጋዎች መጠን ለ10,000 ሰዎች ከ25 አላጋ ያነሰ ነው፡፡ የሕክምና የመንግስት ወጭ በግለ ሰብ ሲተመን ከ3 የአሜሪካ ብርን አያልፍም፡፡የዓለም የጤና ድርጅት አነስተኛው መጠን ለ 100,000 ሰዎች 25 ዶክተሮች ያስፈለጋሉ ይላል፡፡ በማርች 2007 ዓም፤ ሙት ወቃሽ አያድርገንና፤ ያለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ስለ ሃኪሞች ሲናገሩ እንዳሉት፤ ‹‹በኢትዮጵያ ዶክተሮች አያስፈልጉንም……. ሃኪሞቹ ወደያሻቸው ቦታ ሊሄዱ ይችላሉ፡፡ በፍጹም የተለያ አመለካከት ሊደርግላቸው አይችልም›› በማለታቸው በኮንፍራንሱ ላይ የነበሩትን ሁሉ ያስደነገጠና ያሳዘነ አባባል ነበር፡፡ እንደ ፎሪን ፖሊሲ መጽሔት አባባል፤ ‹‹በአፍሪካ ሁለተኛዋ ታላቅ የሕዝብ ቁጥር ባላት ኢትዮጵያ (80 ሚሊዮን) ካሉት ሃኪሞች የበለጠ ቁጥር በቺካጎ የሚሰሩት የኢትዮጵያውያን ዶክተሮች ቁጥር የበለጠ ነው፡፡”
በ ኦክቶበር 2010 በአምስት ተከታታይ ጽሁፍ ‹‹የኢትዮጵያ እናቶች›› በሚለው ዘጋቢ የጋዜጣ ጽሁፏ ሃና ኢንግበር ዊን ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ስላለው የአፍሪካን የውልደትና የጤና አሳሳቢና አስደንጋጭ ጉዳይ ስዕላዊ ድርሰቷን አቅርባ ነበር፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ የወላጆችን የጤና ሁኔታና የወሊድ ስርአትን በተመለከተ ተሃድሶ የሚያስፈለግው ጉዳይ ነው›› ብላ ዊን ጽፋ ነበር፡፡ ከስድስት በመቶ የሚያንሱት ኢትዮጵያዊያት እናቶች በወሊዳቸው ወቅት የህክምና እርዳታ እንደሚያገኙ የ2005ቱ የጤና ጥናት ያሳያል፡፡ በወሊድ የሚሞቱት ቁጥር በዓለም እጅጉን አስከፊ የሆነ ነው፡፡ በጥናቱ መሰረት ከ 100,000 ወላዶች መሃል 673 እናቶች በወሊድ ሰበብ ለሞት ይዳረጋሉ፡፡››
በዚህ አስደንጋጭ ዘገባና የጡት ካንሰርን ሁኔታ ማስጠንቀቂያና ማሳሰቢያ የግልም ሆነ መንግስታዊ ተቋም በሌለበት፤ ይህ የጡት ካንሰር በኢትዮጵያ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ፤ መወሰድ ስለሚገባው ጥንቃቄ፤ ሰለአጠቃላይ ሁኔታው እንዲህ ነው ብሎ ማስቀመጡ አስቸጋሪ ነው፡፡ ዘመን አመጣሹን ቅድመ ምርመራ ለማድረግ የሚያስችለው “ማሞግራም” የተባለው መሳርያ በአብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ጨርሶ አይታወቅም በእርግጠኛነትም ልመርመር ለምትል እናትም ዋጋው የሚደፈር አይደለም፡፡ በሽታው ስር ሰዶ የከፋ ደረጃ በሚደርስበትም ጊዜ ቢሆን ኢትዮጵያዊያን እናቶች አማራጭና አቅማቸው የሚፈቅድላቸው የባሕል መድሃኒትና የመሳሰሉትን ነው፡፡ ኪሞና ራዲዩቴራፒ ከጥቂት የተረፋቸውና ያላቸው ወደ ውጪ ሄደው ለመታከም ከታደሉት ባሻገር ለብዙሃኑ ኢትዮጵያዊያት እናቶች በሃሳብ ደረጃ እንኳ የማይታወቅ ነው፡፡
ስለካንሰር ኤች አይ ቪ /ኤይድስ የሚስጥራዊነትና የዝምታ ባሕል
ስለአንዳንድ በሽታዎች ሚስጥር ማድረግና ዝምታን መምረጥ በኢትዮጵያም ሆነ በዲያስፖራው የሚገኙ እትዮጵያዊያን መሃል እጅጉን የሚያስገርምና የሚያሳዝን ባሕል አለን፡፡ ሁለቱ የማይደፈሩትና በድብቅ የሚያዙት በሽታዎች ደግሞ ኤድስና ካነሰር ናቸው:: የዚህም ዝምታና ሚስጥራዊነቱ ህጉ እስከ እለተ ሞት ድረስና ከዚያም በኋላ ሚስጥረነቱን ማክበር ነው፡፡ ይህንንም አሳዛኝና አሳፋሪ የሚስጥራዊነት ባህል በቅርቡ ለህልፈት በተዳረጉት በመለስ ዜናዊ ሁኔታ አይተነዋል፡፡ የመለስ ሕመምና የሞቱ መንስኤ ምንነትና ሰበቡ ከፍተኛ ጥብቅ ሃገራዊ ሚስጥር ሆኖ ይኖራል፡፡ በስፋት እንደሚነገረውና እንደሚታመነውም የመለስ ሞት ሰበቡ የአንጎል ካንሰር ነው፡፡ የኒው ዮርክ ታይምስ የውጪ ዲፕሎማቶችን ጠቅሶ እንደዘገበው ‹‹መለስ በጉበት ካንሰር ይሰቃይ ነበር፡፡›› ጋዜጠኞችን ለመጠበቅ የተሰለፈው ድርጅት (ዘ ኮሚቴ ቱ ፕሮቴክት ጆርናሊስት) እንደዘገበው መለስ በብራስልስ ሆስፒታል በጉበት ነቀርሳ ሳቢያ ሞቷል ብልዎል፡፡ በአጠቃላይ ካንሰር በተለይም የጡት ካንሰር በብዙ ኢትዮጵያዊያን በተማሩትም መሃልና ውጪውን ዓለምም ባዩት መሃልም ቢሆን የማይነገር የማይነሳ የሚደበቅ ሚስጥር ነው፡፡
ይህ የሚስጥራዊነትና የዝምታ ባህል ለብዙ ሺህ ኢትዮጵያውያን ሞት ምክንያት ሆኗል፡፡ ለምሳሌ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ሴቶች በዲያስፖራው ለሞት የተዳረጉበት መነሾ አስቀድመው ስለበሽታው ምርመራን ባለማደረጋቸውና የፍርሃታቸውም ምክንያት የምርመራው ውጤት የበሽታው ተጠቂነታችንን ያሳውቀናል በሚል መሆኑ ይታወቃል፡፡ በበሽታው የተያዙት እነዚህ ሴቶች ጉዳዩን ከዘመድም ከወዳጅም ደብቀው በማቆየት እስከመጨረሻው ድረስ ሳያወጡት ኖረው በሽታው ስር ከሰደደና ሕክምናም ምንም ሊያደረግ ወደማይችልበት ደረጃ እስኪደርስ በሚስጥር ይይዙትና መደምደሚያው የሞት መቅሰፍትን መጠበቅ ይሆናል፡፡
የግልጽነትን ባሕል በማዳበር የጡት ካንሰርንም ሆነ ሌሎችን በሽታዎች በነጻ መወያየት
ለብዙ ዓመታት ስለ ጡት ካንሰር ምንም ግንዛቤ አልነበረኝም፡፡ ስለቅድመ ምርመራው በቂ እውቀት ሳይኖረኝ በሬን እስኪያንኳኳ ቆይቼ ነበር፡፡ቆይቼ ግን ብዙ ተማርኩ፡፡ አወቅሁ፡፡ ያም የሚከተለው ነው፡-
…….አስቀድሞ ከተደረሰበትና አስፈላጊው ቅድመ ምርመራ ከተደረገ፤ ዘመን በፈጠራቸው የሕክምና መሳርያዎች እርዳታ የጡት ካንሰር ሊታከም የሚችል በሽታ ነው፡፡ የጡት ካንሰር እንዳለባት ለአንዲት ሴት መንገር ማለት የሌት ተቀን ቅዠቷን ማስታጠቅ ማለት ነው፡፡ ሴቶች ሁኔታውን ሲሰሙ ወዲያው ወደ መደናገጥና ፍርሃት ውስጥ ይገባሉ፡፡ በአሜሪካ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ሴቶች ወቅታዊውን የሚሞግራፍ ምርመራቸውን ቸል ብለው ይተዉታል፡፡ ለአንዳንዶቹ እንደ ሰበብ የመመርመሪያውን ሂሳብ የመክፈል አቅም ማጣት አድርገው ይሸሹታል፡፡ ኢንሹራንስ ከሌለ በስተቀር በአሜሪካ ሕክምናን ማድረግ እጅጉን አስቸጋሪ ጉዳይ ነው፡፡ ሆኖም ለምርመራውም ሆነ ለህክምናው አቅሙና መንገዱ ያላቸውም ቢሆኑ አያደርጉትም፡፡ ለዚህ አደገኛ በሽታም አቅም እያለ ክትትልና ህክምና አለማድረግ ሰበብ አለው፡፡ ከሰበቦቹ ዋነኛ ተብሎ ሊጠቀስ የሚችለውም፤ ስለ ጡት ካንሰር ጉዳት በቂ ግንዛቤ አለመኖር ነው፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ጨርሶ ስለዚህ ጉዳይ ማንሳትም ሆነ መወያየት አይፈቅዱም፡፡ በጠና ካልታመሙ በስተቀር ወደሃኪም አይሄዱም፡፡በዚህም እራሳቸውን ለማዳን መንገድ አይኖራቸውም፡፡
የጡት ካንሰር ማንኛዋም ሴት ልትደብቀው አለያም ችላ ልትለው የማትችለው በሽታ ነው፡፡ የጡት ካንሰርን ችላ ማለት በደን ውስጥ መቀጣጠል የጀመረን እሳት ችላ እንደማለት ነው፡፡ በደን መሃል ችላ የተባለ እሳት ደኑን እንደሚያጠፋው አያጠያይቅም፡፡ የጡት ካንሰርም መኖሩ ተጠርጥሮ ከታወቀ በኋላ ችላ ከተባለና አስፈላጊው ክትትል ካልተደረገ በቀር ስር እየሰደደና በሰውነት ውስጥ በመሰራጨት ተጠቂውን ለሞት መዳረጉ አይቀሬ ነው፡፡ ለብዙዎቹ ሴቶች በጡት ላይ የሚሰማን መጎርበጥ አለያም የሚታይን እብጠትም ሆነ አዲስ ስሜት፤ ሕመም እስካላስከተለ ብሎ ችላ በማለት ተዘናግቶ መቆየት የተለመደ ቢሆንም ግን አግባብ አይደለም፡፡ምንም አይነት በጡት አካባቢ የሚታይ እብጠት አስጊነቱ ቅድሚያ ተሰጥቶ ወደ ዶክር ሄዶ መታየቱ እጅጉን አስፈላጊ ው፡፡
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ቃላቶች ከሁለት ዓመታት በፊት በባለቤቴ ‹‹ለኢትዮጵያዊያት እህቶቼ የተጻፈ ደብዳቤ›› በሚል ርዕስ የተጻፉ ናቸው፡፡ የጡት ካንሰርን በማሸነፍ ታሪኳንም ከኢትዮጵያዊያት እህቶቿ ጋር ተካፍላለች፡፡ ‹‹በርካታ ኢትዮጵያዊያን ስለ ጡት ካንሰር ምርመራና ህክምና ያላቸው እምነት ከአፈ ታሪክነት የማያልፍ ነው፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ኢትዮጵያዊያት ወቅታዊ የማሞግራፍ ክትትላቸውን የሚያቋርጡት ከመመርመርያው መሳርያ የጡት ካንሰር ይይዘናል ብለው ያምናሉ፡፡ ማሞግራፍ ግን የጡት ካንሰር አያሲዝም፡፡ ልክ ራጂ እንደመነሳት ቀላልና ህመምም የሌለው ነው፡፡›› በፅሁፏ ላይ ትኩረት ሰጥታ ያስገነዘበችው ‹‹አንዳንድ ኢትዮጵያዊያት በካንሰር መያዝን እንደ አሳፋሪ ተግባር አድርገው ይመለከቱታል፡፡ ጓደኞቻቸውም ሆኑ ቤተሰቦቻቸው እንዲያውቁባቸው አይፈልጉምና በሚስጢር ይዘውት አስጊ ደረጃ ላይ ደርሶ ህክምናም ምንም ሊያደርግ በማይችልበት ወቅት ወደ ሆስፒታል መሄዳቸው ግድ ይሆናል፡፡ የጡት ካንሳር በምንም መለኪያ አሳፋሪ አይደለም፡፡በሽታው ድሃና ሃብታም ሳይልና ልዩነት ሳያደርግ፤ጥቁር ነጭ ብሎ ቀለም ሳይለይ፤ የትም ዓለም ላይ በምትኖር ሴት ላይ የሚደርስ ነው፡፡››
አንዳንድ ኢትዮጵያዊያት ሴቶች ትኩረት ሊሠጧቸውና ሊገነዘቡት ስለሚገቡ ሁኔታዎች አበክራ ትናገራለች፡፡ ‹‹ከምንም በላይ ላተኮርበት የምፈልገው ጉዳይ ኢትዮጵያዊያት ሴቶች ወቅታዊ የሆነ የሃኪም ክትትል ማድረግና፤ በማሞግራፍም መመርመርንና የሚከሰተውን አላስፈላጊ ስሜት ምንነት መረዳት አስፈላጊነትን ነው፡፡ የጡት ካንሰር እንደ ኢንፍሉዌንዛ አይደለምና በጥቂት ቀናት የአልጋ ላይ እረፍት አይጠፋም፡፡ ችላ ከተባለ ህይዎትን ከባድ አደጋ ላይ ይጥላል፡፡ ከዚህ አስጊ ሁኔታ ለመዳን መፍትሔው ወቅታዊ ክትትል ማድረግ ብቻ ነው፡፡›› ባለቤቴም ስታስረዳ ‹‹ኢትዮጵያዊያት ሴቶች መሰረታዊ የሆነውን ነገር ለማድረግ ቸል በማለት፤ በጅምሩ ሊቆምና ሊገታ የሚችለውን በሽታ በመዘንጋትና በሌላም ሰበብ በርካታ ጓደኞቿን፤ ወዳጆቿን የስራ ባልደረቦቿን፤እና የቤተሰቦቿን አባላት በዚህ በሽታ አጥታለች፡፡›› በዚህም እጅጉን ታዝናለች ትጸጸታለች፡፡
ለኢትዮጵያዊያት ሴቶች የጡት ካንሰር ማስገንዘቢያ ወር ፡ – ለኢትዮጵያዊያን ወንድሞቼ የተጻፈ ‹‹ደብዳቤ››
በ‹‹ደብዳቤዋ›› ላይ ባለቤቴ ስለ ውይይት ማካሄድና የአካባቢም የተግባር እንቅስቃሴ ፤ ትኩረት አስፈላጊነትን አበክራ ትናገራለች፡፡
‹‹በአሜሪካ ለሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያዊያት የቋንቋ የባሕል፤የገንዘብ ጥያቄ ወቅታዊ ክትትልና የማሞግራፍ ምርመራ ለማደረግ ችግር ፈጣሪ እንደሆኑ እረዳለሁ፡፡ ይህን ችግር ለማሰወገድ ደግሞ ኢትዮጵያዊያት እህቶች እርስ በርስ በመረዳዳት፤ በአብያተ ክርስቲያናት በመነጋገር፤ በማህበረስብ ግንኙነቶች በመመካከር፤ ስለ ጡ ካንሰር በግልጽ በመወያየት፤ የአስቀድሞ ጥናቃቄን በማጎልበት ይህን ሀኔታ ሊወጡት እንደሚችሉም እምነት አለኝ፡፡ በዚህም ስለ ደም ግፊታችን እንደምንመካከረው ሁሉ ስለጡት ካንሰርም በመነጋገር በጊዜው እርዳታ ማግኘት እንችላለን፡፡››
ጥሪዋንና ተማጽኖዋን በተለይም ለኢትዮጵያዊያት ሴተ ዶክተሮች ስታስተላልፍ፤ ‹‹ሴቶች እህቶቻችንን የማስተማር ቀደምት ሚና እንዲጫወቱና፤ስለበሽታው በማስተማር፤ቅድመ ምርመራውንም በማድረግ በበሽታው የተያዙትንም አስፈላጊውን የክትትል ህክምና እንዲያደርጉ በመምከርና በመርዳት እንዲተባበሩ ትጠይቃለች፡፡›› በአሜሪካ ነጻ የጡት ካንሰር ምርመራ ለማድረግ አቅም ለሌላቸው ነጻ ምርመራ የሚያደርጉ በርካታ የአካባቢ ሆስፒታሎችና ክሊኒኮች አሉ፡፡›› ተስፋዋም ‹‹ሴቶች እህቶቿ በየአካባቢያቸው ተሰባስበው በመደራጀት በመላው አሜሪካ የመተጋገዝ ቡድን ለማቋቋምና ለመረዳዳት ይችላሉ፡፡›› የሃይማኖት ተቋማትንም ‹‹የሙያው እውቀት ያላቸውን በመጋበዝና ሴቶችንም በማስተባበር አስፈላጊውን ትምህርት እንዲያገኙ በማድረጉ ረገድ ቅድመ ምርመራን፤ የማሞግራፍ ምርመራ፤ለማድረግም ለማያውቁት መንገዱን በማሳየትና በማበረታታት ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ እንዲተባበሩ ታሳስባለች….በበርካታ የአሜሪካ ከተሞች ኢትዮጵያውያንን ለማገልገል የተቋቋሙ በርካታ የሬዲዮ ጣቢያዎች አሉ፡፡ እነዚህ ጣቢያዎችም የጡት ካንሰርን አስመልክተው በጣቢያቸው ላይ ጥቂት ደቂቃዎች በመመደብ ስለበሽታውን ቅድመ ምርመራው፤ ስለክትትል ህክምናውና ነጻ ሆስፒታሎችና ከሊኒኮች የሚገኙበትን መንገድ በመጠቆም ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ ይገባል፡፡ ከዚሁ ባልተናነሰ መልኩ በድህረ ገጾችም ላይ ይሄው እንቅስቃሴ ሊደረግ ተገቢ ነው፡፡ ተስፋዬም በሚቀጥለው ዓመት በሚከበረው የሴቶች የጡት ካንሰር ማሳወቂያና መሳሰቢያ ወር ላይ ብሔራዊ ፕሮጋራሞችም እንደሚቀናጁና እንቅስቃሴውም በሃገር አቀፍ ደረጃ ጎልብቶ ማየትን ነው፡፡››
በዚህ የማስጠንቀቂያና ማሳሰቢያ ወር፤ይህንን መሰሉን ጉዳይ ማካፈሉ በእጅጉ አስፈላጊ ነው ብለን እናምናለን፡፡ በቅድሚያ ይህንን ገዳይና ቀሳፊ በሽታ ደጋግሞ ማጥፋት ወሳኝ ነው፡፡ ምናልባትም ሌሎች የበሽታውን ቀሳፊነት የተገነዘቡና በበሽታውም የተጠቁ ፊት ፊት በመውጣት ልምዳቸውንና ያደረጉትን ምርመራና ቅድመ ጥነቃቄ በተመለከተ በዓለም ላይ ባሉ ኢትዮጵያዊያት መሃል ጠቃሚ የመነጋገርያና የመረዳጃ ቡድኖች ይቋቋማሉ የሚል ተስፋ አለን፡፡ የጡት ካንሰርን የማሸነፊያው መንገድ ስለበሽታው በቂ እውቀት ማግኘትና ቅድመ ምርመራንና ክትትልን ሳያስተጓጉሉ በማድረግ ብቻ ነው፡፡ ሁለተኛም ለእህቶቻችንና ለወንድሞቻችን ልናረጋግጥ የምንፈልገው፤ በጡት ካንሰርና በማንኛውም የካንሰር አይነት መያዝ፤ አንዳችም የሚያሳፍር፤ የሚያሸማቅቅ፤ ጨርሶ በሌላ ስም የሚያስጠራ፤ ፈጽሞ አጸያፊም ያልሆነ፤ እንዳልሆነ ነው፡፡ ይልቅስ የሚያሳፍረውና የሚያሳስበው፤ አጉል ተብሎም ሊጠቀስና ሌላም ስም ሊያሰጥ የሚችለው፤ አስፈላጊው አገልግሎት ሁሉ በተሟላበት ሃገር ተቀምጦ ቅድመ ምርመራውንን ክትትሉን በአግባቡ አለመወሰዱና በአጉል አፈ ታሪክና ባሕል ተሸብቦ፤ መገለል ይደርስብኛል በሚል ወሬና ተረት ለሞት መዳረግን መምረጥ ነው፡፡››
እንደ እውነቱ ከሆነማ ከጡት ካንሰርም ሆነ ከሌላውም የካንሰር ህመምተኝነት ድኖ መገኘት የትም ቢኬዱ የሚያኮራና የሚያስከብር ተግባር ነው:: ከጡት ካንሰር ጋር ገጥሞ በሽታውን ድል ማድረግ ልክ አንድ የጦር ተዋጊ ዘምቶ ጠላቶቹን ድል በማድረጉ ሂደት ከፍተኛውን ሚና በመጫወትና ለድሉም ጀግንነቱ ብቃት ያለው ተግባር በመፈጸሙ ለሜዳልያ ሽልማት እንደሚበቃው ጀግና መቆጠር ማለት ነው፡፡ ማለቴም የጡት ክንሰርን ተቋቁመው ድል ያደረጉና ከበሽታው የተፈወሱትን እህቶች ጥንካሬ፤ ቆራጥነት፤ አልበገር ባይነት፤ ጀግንነት፤ ድል አድራጊነት፤ተመልክቼ መስክሬያለሁና ነው፡፡ እንዲሁም ከበሽታው ጋር ትንቅንቅ ተያይዘው ፤ ሲሰቃዩ፤መከራ ሲበሉ፤ አቅም ሲያጡ፤ በሽታው ስር እየሰደደ ሲጨርሳቸውና ለሕልፈተ ሞት ሲዳርጋቸውም መስክሬያለሁ፡፡ ኢትዮጵያዊያን ወንዶች: ወንድሞች ስለጡት ካንሰር በሚደረገው ማንቂያ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ አምናለሁ፡፡ አንዳንድ ጥቃቅን ተግባራትን በቅድመ ምርመራውና ክትትሉ ዘርፍ በመውሰድ እንደሚረዱ እርግጠኛ ነኝ፡፡ለዚህም በቅድሚያ ራሳችንን ማስተማርና ማወቅ ይገባናል፡፡ የሁላችንም እህቶች፤ እናቶች፤ ሚስቶቻችን ባህላዊ ተጽኖና አለማወቅ ስላለባቸው ስለበሽታው ቅድመ ምርመራም ሆነ ክትትሉን በበሽታው ክፉኛ እስኪጠቁና መንገዱ እስከጠብ ድረስ በሚስጥር መያዝ ስለሚመርጡ መደረግ ያለበትን ሳያደርጉ ይቀራሉ፡፡ እነዚህ እናቶቻችን: እህቶቻችን፤ ሚስቶቻችንና ወዳጆቻችን ስለ ጡት ካንሰር አስፈላጊው እውቀት እንዲኖራቸውና ቅድመ ምርመራውንም ሆነ ማሞግራፍ ምርመራውን፤ ክትትሉንማ ማደረግ እንዳለባቸው ሳንሰለችና ሳንደክም በይሉኝታም ሳንታሰር በመንገርና በመጎትጎት አቅጣጫውን ማስያዝና ሂደቱንም ማገዝ ይገባናል፡፡ በዚህ ሁሉም ነገር ባለበት ሃገር ተቀምጠን በበሽታው ተይዘን ግን ምንም ሳናደርግ በሚስጥር ይዘን ለሞት መዳረግ ከማሳፈርም ያለፈ ጉዳይ ነው፡፡ ሁላችንም ተባብረን በዚህ የጡት ካንሰር ማስጠንቀቂያና ማሳሰቢያ ወር (የወሩን ሶስተኛውን አርብ) ልዩ እንቅስቃሴ በማድረግና ሴቶች እህቶቻችንን በማስተባበር ብሔራዊ ማሞግራም ቀን በማለት ሰይመን ለምርመራ ማስተባበር ይጠበቅብናል፡፡
ለጡት ካንሰር ማስጠንቀቂያና ማሳሰቢያ ወር በርካታ የእግር ጉዞዎችና ሌሎችም ተግባራት እየተዘጋጁ በመሆኑ፤ይህንንም በመጠቀም ማስተባበራችንን ማከናወን ይጠበቅብናል፡፡ በርካታ ኢትዮጵያዊያት ተሰባስበው በሚኖሩባቸው መንደሮች በነዚህ እንቅስቃሴዎች መሳተፍን ተግባራዊ ማድረግ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነውና ለዚህም መትጋትና መተግበር ያስፈልጋል፡፡ ተስፋ በመቁረጥ በዚህ ሕመም መሰቃየትና በግል መጨነቅ ለኢትዮጵያዊያት ሴቶች አዲስ ልምድ አይደለም፡፡ ድጋፍ ሰጪ ቡድኖች በተለይም የጡት ካንሰርን በመዋጋት ላይ ላሉት እጅጉን አስፈላጊ ነው፡፡ ስለ ጡት ካነሰር የሚያስረዱ ማንኛቸውም ነገሮች፤ (ነጻ የማሞግራም አገልግሎት፤የግልና የመንግስት ህክምና ቦታዎች) በጥንቃቄ ተሰባስበው ለኢትዮጵያዊያት ሴቶች ሊደርሱ ይገባል፡፡ በተለይም ወንዶች ይህን ጎታችና አስቀያሚ የሆነውን የሚስጥራዊነት፤ድብቅነትን፤ ጎጂ ባህል በተለይም የጡት ካንሰርን በተመለከተ የማጥፋቱ ሃላፊነትና በአደባባይ ስለጡት ካንሰር መነጋገርንና መወያየትን ባህል ማድረጉ እንዲለመድ ሃላፊነቱ የወንዶች ነው፡፡
በዚህ ወር በሽታውን ተቋቁመውና አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ ለድል የበቁትን እህቶቻችንን የምናከብርበት ወር እናድርገው፡፡ ከጡት ካንሰር ጋር ተዋግተው ድል ካደረጉ በላይ ጀግና የለምና፡፡ በጡት ካንሰርም ሕይወታቸው ያለፈውንም እናስባቸው እናስታውሳቸው፡፡ በትምህርትና በማሳወቅ ረግድ በሰፊው ማህበረሰብ ውስጥ የጡት ካንሰርን ለማሸነፍ የሚደረገውን እንቅስቃሴ በማጠናከር እንስራ፡፡ የክትትል ምርመራና ቅድመ ጥንቃቄ ትክ የማይገኝላቸው የጡት ካንሰርን ማሸነፊያ ሃይለኛ መሳርያ ናቸው፡፡ እጅ ለእጅ በመያያዝ አንድ ባንድ ሴቶቻችንን ከጡት ካንሰር ተጠቂነት ነጻ እናድርጋቸው!
‹‹በሽታውን ያልተናገረ መድሐኒት አይገኝለትም፡፡›› እንዲሉ!
የተቶረገመው ጽሁፍ (translated from):
http://www.ethiopianreview.us/42142
(ይህን ጦማር ለሌሎችም ያካፍሉ::)