ኢትዮጵያ፤ በአዲስ ዓመት አዲስ ጠ/ሚኒስቴር

ከፕሮፌሰር  ዓለማየሁ  ገብረማርያም

ትርጉም  ከነጻነት ለሃገሬ

ኢትዮጵያዊያኖች አዲሱን ዓመታቸውን የዘመን መለወጫ በሴፕቴምበር 11 አክብረዋል፡፡ አሁን በኢትዮጵያ 2005 ዓም ነው፡፡ በሴፕተምበር 21 ደግሞ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ተሰጥቷቸዋል፡፡ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ከአዲስ ዓመት መግባት ጋር ተዳምሮ ሲቀርብ እንዴት ደስ ያሰኛል!! ከልብ የመነጨ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልእክትና መልካም ምኞት ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ተገቢ ነው፡፡

በልዩ ጥሪ በተሰበሰበው ፓርላማ መሃል ተገኝቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቃለ መሃላ ፈጸመ፡፡ ሊሆን በሚገባው መልኩ ስርአቱን አሟልቶ ባይከናወንም፤ ቀዝቀዝ ባለ ሂደት ነበር የተከናወነው፡፡ ቱልቱላ አልተነፋም:: ሰልፍ አልተከናወነም:: የሹመት ያዳብር ድግስም አልነበረም:: አነስ ቀዝቀዝ ባለ ቴአትራዊ አካሄድ በተቀረጸ ፕሮግራም ነበር ክንዋኔው፡፡ ከ547ቱ አባላት የተገኙት 375ቱ አባላት ትንፋሻቸውን ውጠው በመቀመጥ የሃይለማርያም ደሳለኝን የሰጠውን ዲስኩር ካዳመጡ በኋላ በጭብጨባ ተቀበሉት፡፡

ካለፈው ሜይ ጀምሮ የሃይለማርያም እንቅስቃሴ  ባልለየለት የፖለቲካ ወዠብ ውስጥ ነበረ፡፡ አጠራሩ ሳይቀር ያልለየለት ነበር፡፡ “ዴፒዩቲ” ፤ “አክቲንግ”፤ “ኢንትሪም” በመባል ለአንድ ቦታ ዝብርቅርቅ ያለ ተቀጥላ ነበር ሲለጠፍበት የነበረው፡፡ ያም ሆኖ የመጨረሻዎቹ ሁለቱ ስያሜመዎች በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ውስጥ ያለተጠቀሱ በጀርባ ሹዋሚ ሻሪዎች የተለጠፉ ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሌለበት ወቅት የዲፒዩቲው ተግባር ምን መሆን እንዳለበትም በአግባቡ ባለመቀረጹና የመተካካቱ ሂደትም ምን መምሰል እንዳለበት ባለመስፈሩ ጥየቄዎች ያስነሳና ግራ ያጋባ ጉዳይ ነበር፡፡ እነዚህን ሁኔታዎች ችላ ማለት ቢቻልም፤ የሃይለማርያም ደሳለኝ በስርአቸቱ ቃለመሃላ ፈጽሞ ወደ ተግባር የመግቢያው ቀን በተደጋጋሚ አለአንዳች ማስገንዘቢያና ሰበብ ሲተላለፍ ከረመ፡፡ ይህ በራሱ በአመራሩ ውስጥ አለመግባባት መጥፋቱንና በንትርክ ውስጥ ሊሆኑ ይችላሉ የሚለውን መላ ምትም በሰፊው አስነስቷል፡፡ ሁኔታውን የበለጠውን ውዥንብር ውስጥ የከተተው ደግሞ፤ከተቆረጠው የመሃላ መፈጸሚያ ዕለት ቀደም ብሎ ቃለ መሃላው በኦክቶበር መግቢያ ላይ ይከናወናል የሚልም መግለጫ ወጥቶ ነበር፡፡

ሰበቡ ባልታወቀ መነሾም ፓርላማው በአስቸኳይ እንዲሰበሰብ ጥሪ ተላልፎ፤ የበለጠውን የባለስልጣናነቱን አለመግባባት ጥርጣሬ ሊያባብሰው በሚችል መልኩ የቃለ መሃላው ዕለት ተወስኖ ፓርላማው ተሰበሰበ፡፡ ሃይለማርያም በስተመጨረሻውም በስጋት ደመና በተከበበ ሁነሜታ ስልጣን ተረክባል:: ታዛቢዎች እንደሚሉት ሃይለማርያም ቢሮውን፤ የ “ይስሙላ ሹም”፤ “ግንባር ቀደም ሰው”፤ “መቀመጫ አሟቂ” ለመሆን፤ ለቀሪ ጥቂት የሽግግር ጊዜ ቦታውን የተረከበነው ይሉታል፡፡ ገምጋሚዎች ከሁኔታው ግራ አጋቢነትና አጠራጣሪነት በመነሳት ሃይለማርያም በቅንጣቢ ነጻነት ብቻ በሌሎች ወሳኞችና የሂደት ትልም አፍላቂዎች የጀርባ ጉሽሚያ የሚንቀሳቀስ እንጂ ፖለቲካውን፤ኤኮኖሚውን፤የሚያሽከረክሩት ከበስተጀርባ ያሉት ናቸው ለማለት ችለዋል፡፡ አንዳንዶች እንደሚሉት ደግሞ ሃይለማርያም ቴክኖክራት በመሆኑ እንደዚህ በመርዝ ተለብጦ ባኮፈኮፈ የፖለቲካ መሳርያ ውስጥ ሊቆይ አይችልም ነው፡፡

አንዳንዶቻችን ደሞ ምናልባትስ፤ ቢሆንስ፤ በሚል አስተሳሰብ እስቲ እንሞክረው ቆየት ብለን እንየው እንላለን፡፡ የሃይለማርያም የስልጣን መረከቢያ ዲስኩር በአብዛኛው ያተኮረውና በተደጋጋሚ አጠናክሮ ያሰመረበት፤‹‹መንገዱን ሳንለቅ›› ‹‹ሳይሸራረፍ›› በሚለው ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ሲያረጋግጠውም በእሱ አመራር የተጀመረውን ፕሮግራምና የተቀየሰውን ፕሮጄክት ጨምሮ ለፍጻሜው መጣር ነው፡፡ ተግባራችንም በተቀየሰው ፈር በመጓዝ በፓርቲያችን ስትራቴጂና መመርያ መሰረት በፈሩ ላይ መቀጠል ነው፡፡ ልማትንና ዴሞክራሲን የተባበረ አመራራችንን በማጠናከርና ሕዝቡንም በማካተት የተጀመረውን ሂደት እንቀጥላለን››፡፡ በመቀጠልም ‹‹የገጠሩን ልማት በዘመናዊ መልክ በማደራጀት የእርሻውን ክፍል ኤኮኖሚ ማሳደግ ቅድመ እቅዳችን ነው፡፡›› የሚመራው መንግስት አለ ‹‹የእርሻውን መሰረተ ልማት ለማሻሻል ቅድሚያ እንደሚሰጠው፤ ስርአተ ትምህርቱንም፤ ከብት እርባታውንና አርቢውንም፤ እንደሚያበረታታን ለተሸለ እድገትም እንደሚጥር ወጣቱንም ወደ ተሸለ የትምህርትና ለአመራር የሚያበቃውን እውቀት ላማስጨበጥ እንደሚተጋ በንግግሩ አካቷል፡፡ ሃገሪቱ በሳይንስ፤ በቴክኖሎጂ፤እና በሂሳብ ላይ ያተኮረ ስርአተ ትምህርት እንደሚያስፈልጋት፤ ጠቅሷል፡፡ሴቶችንም በተመለከተ ለተሻለ ዕድል ተጠቃሚነት የሚያበቃ፤ለጤንነታቸው ትኩረት እንደሚደረግ፤የተሸሻለ የእናቶች ጤና አጠባበቅንም አስፈላጊነት ትኩረት እንደሚሰጠው አስገንዝቧል፡፡ ችግሮችን ለመፍታትም ምሁራን ምርመራቸውንና መፍትሔ በመሻት ላይም ትኩረት እንዲያደርጉና የሙያ ማሕበራትም በዚሁ ላይ ትኩረታቸውን እንዲያደርጉ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

‹‹ምኞቴ›› አለ ሃይለማርያም፤‹‹ኢትዮጵያ በሚቀጥለው አስር ዓመት የመሃከለኛ ገቢ ከሚባሉት ሃገሮች እኩል ተሰልፋ ማየት ነው፡፡ይህንንም ግብ ለማድረስ፤በኢንዱስትሪ ላይ የበለጠ መሻሻያ ሊደረግለት ይገባል፡፡ የልማት ማነቆ የሁኑትን ጎታቾች ልዩ ትኩረት ይደረጋል፤ የኤክስፖርት  ሃይላችንንም ማጠናከርና ማሻሻል፤በመንግሥትና በግሉ መሃል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር፤ያስፈልጋል፡፡ በአዲስ አበባ ያለውን የቤቶችና የትራንስፖርት ችግር ለማቃለልም ቃል ገብቷል፡፡›› ኤኮኖሚውንም በተመለከተ ምንም እንኳን ግሽበቱ  እየቀነሰ ቢሆንም የበለጠ ማውረድና ማስተካከል አስፈላጊ ነው በማለት ተናግሮ፤ ኢትዮጵያውያን ጥርሳችንን ነክሰን፤የታቀደውን የምድር ባቡር፤ ትራንስፖርት፤ሃይድሮ ኤሌክትሪክን ሃይልን፤ ቴሌኮሙኒኬሽንን፤በትክክል በስራ ላይ በአግባቡ መሄዳቸውን ማረጋገጥ ይኖርብናል፡፡ በአባይ ተፋሰስ ላይ የሕዳሴውን ግድብ ከግብ ለማድረስ ቃል ገብቷል፡፡በመሬት አስተዳደር ያለውን ሙስናና የአስተዳደር ስንኩልነት የኪራይና የታክስ አሰባሰብን በተመለከተ፤ ያለውን ብክነትና ስርአት የጎደለውን አካሄድ ለማስተካከል የሕዝቡ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን አንስቷል፡፡በመልካም አስተዳደር ድክመት፤በፖለስ፤ በፍትህ፤በደህንነትም በኩል ያለውን የተበላሸ አሰራር ማስተካከልና መስመር ማስያዝ ማስፈለጉንና መንግሰትም ትኩረት እንደሚያደርግ ሳያነሳ አላለፈም፡፡

ሃይለማርያም የሰብአዊ መብት ጉዳይ እጅጉን አስፈላጊ መሆኑን በማንሳት ፓርላማውም ለመሻሻሉ አስፈላጊውን በሚመለከተው ኮሚቴ በኩል እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል፡፡የኢትዮጵያን ምርጫ ቦርድ፤የሰብአዊ መብት ኮሚሽንን፤የነጻውን ጋዜጦች፤የተቃዋሚዎችን ጉዳይ በሃገሪቱ ያላቸውን ሚናና አስፈላጊነት በተመለከተ ለዘብተኛነት ያለው አመለካከት አሳይቷል፡፡በደፈናው ከሲቪክ ማህበረሰቡ፤ከነጻው ሚዲያ፤እና ከሌሎችም ተዛምዶ ካላቸው ጋር በህብረት እንሰራለን ከማለት ያለፈ አልተናገረም፡፡የውጭ ግንኙነትንም በተመለከተ፤ትኩረቱ የነበረው ሃይማኖታዊ ጉዳዮች፤ኢትዮጵያ ለሰላምና መረጋጋት በሶማልያ ስላደረገችው፤ሁለቱን ሱዳኖች በተመለከተ የነበራትን ሚና አነሳ እንጂ እልፍ አላለም፡፡

ንግግሩ ቴክኖክራት ተብሎ ሊጠቀስና ሃገሪቱን ወጥሮ የያዛትን ችግር ሊፈታ የሚችል ተብሎ ሊተረጎም የሚችል አይደለም፡፡ንግግሩ አጭርና በጥንቃቄ የተዋቀረ ነው፡፡ በሃገሪቱ ላይ ጎልቶ የሚታየውን የኑሮ ችግርና በዚህና በሌላም ሰበብ ምሬቱ ከቀን ወደ ቀን እየባሰ መሄዱን፤ የፖለቲካው ጉዳይ መላ ቅዱሱ ጠፍቶ ተቃዋሚ ተብለው የታወቁና የተፈረጁም እግር ተወርች ታስረው የባሰባቸውም ነፍስን ለማትረፍ ሲሉ ሃገራቸው ጥለው ስለመሰደዳቸውም ሆነ ስለመሰል ችግሮች የተነሳ የለም፡፡ በአጠቃላይ የተጀመረውን ለመጨረስ እጅን ጓንት ሆነን እንሰራለን ለዚህም ሕዝቡ አብሮን እንዲቆም እጠይቃለሁ ብቻ ነው በደፈናው፡፡ የሕዝቡን ኑሮና የስራ ፍላጎት የእድገትንና የልማትና ማፋጠን ዘዴ እንዲህ ነው ብሎ የተላለፈም መልእክት አልተደመጠም፡፡

እርግጥ የሃይለማርያም ንግግር ላለፉት በርካታ ዓመታት ስናዳምጠው ከነበረው በተለያየ መልኩ የተሸለና ለለውጥ የሚበቃ ነው፡፡ የንግግሩ አቀራረብ አክብሮት የታየበት በመሪነት ያለ ሰው ሊያደርገው የሚገባ ነበር፡፡ ዘለፋና ማን አለብኘነት እኔ ብቻ የሚል ስሜትም አልታየበትም፡፡ንግግሩ የተነደፈልንን የሚለው ዛላ ባይደጋገምበት፤ እንዳለፈው ወታደራዊ ሃይልና የኔ ብቻን በአውራው መንገድ ላይ የሚል አዘዥነት የተሞላውም አልነበረም፡፡ እንዳለፈው ቁልፍ የመሸንቆጫ የነበሩትን ኒዎ ኮሎኒያሊዝም፤ ኒዎ ሊብራሊዝም፤እና ኢምፔሪያሊዝም በሚከል የኢትዮጵያ ችግር ሰበብ ሆኖ የዘመቱበት የቃላት ድርድር አልነበረውም:: በሃገር ውስጥ ባሉ ተቃዋሚዎችና በአካባቢ ሃገሮች ላይ የጥላቻ ዘመቻ ጥሪም አልቀረበም፡፡ ብክነትን፤ ሙስናን፤የአስተዳደር ጉድለትን፤ሥልጣንን አለአግባብ መጠቀምን አንስቶ እንኳ ሲናገር ማስፈራራት ጨርሶ ሳይገባበትና አካኪ ዘራፍ ሳይጨመርበት፤ ህጋዊ ተጠያቂነት መኖሩን ብቻ በማሳሰብና ሁሉም ለዚህ ነቅቶና ተግቶ እንዲቆም ከማለት አላለፈም፡፡

ሌላው የሚያስገርመው ነገር፤ንግግሩ እንዳለፈው የፉከራ፤እራስን ማዋደድ እና በድል አድራጊነት ደረት ድለቃም አለመኖሩ ነው፡፡የገዢው ፓርቲም አልበገርም ባይነትና ገናናት አልመንጸባረቁ፤ እራስን ከፍ ከፍ፤እራስን ማዋደድም አልተደመጠበትም፡፡በለስላሳው ተቃዋሚዎችና ሕዝቡም በአንድነት በመስራት ሃገሪቱን ከችግር ማውጣት እንዳለባቸው አሳስቧል፡፡ንግግሩ አዲስ ተስፋና ራዕይ ከማሳየት ይልቅ ባለው ላይ በትጋት እንዲሰራ የሚጠይቅ ነበር፡፡ በጽሁፉ አርቃቂዎች የጎደለውን ሃይለማርያም በቃላት አጣጣሉ፤ በርቱእ አንደበቱ፤ በረጋ ስልቱ አሟልቶ አቅርቦታል፡፡

ያልተባለውስ

 ያልተነሱ በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ምንም እንኳን ሃይለማርያም ስለ ዋጋ መዋዠቅና ስለ ገንዘቡ መውደቅ፤ስላለው የኤኮኖሚ ችግር ቢነሳም ስለመፍትሔው ግን ምንም አልተናገረም፡፡በተደጋጋሚ በተሰመረው መንገድ ላይ እንሂድ ነው ያለው፡፡ብሔራዊ የእርቅን ጉዳይ አሁን ያለው መንግሥት ግንዛቤ የሰጠው ጉዳይ ነው? ስለሽግግሩም ጉዳይ ቢሆን እንዲህ ነው ወይም ይሆናለል የተባለበት ቦታ አልተደመጠም፡፡

ስለታሰሩትም ለቁጥር የታከቱ የፖለቲካ እስረኞች መፈታት ጉዳይ ምንም አልሰማንም፡፡ከዚሁ ጋር በተመሳሳይ አፋኝና ለሰበብ መፈለጊያ ስለተነደፉት አዋጆችና መሻሻል ስለሚገባቸውም ሆነ መለወጥ ስላለባቸው የሽብርተኝነትና የሲቪል ማሕበረሰቡን የሚመለከቱ አዋጆች ምንም የተባለ የተነሳ የለም፡፡ለበርካታ ዓመታት የኢትዮጵያ መንግሠት በሰብአዊ መብትና በዴሞክራሲ ጉዳይ ላይ አላግባብ ዜጎች ስለመታሰራቸው፤የፕሬስ ሕጎች አፋኝነት፤ ስለጋዜጠኞች መታፈንና መታሰር በዓለም ተሟጋቾች እንደተወቀሰና እንደተከሰሰ ነው፡፡ስለዚህም ጉዳይ የተባለ የለም፡፡

ቃልና ተግባር፤ የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር መጫሚያ አብዛኛውን ጊዜ የፖለቲካ ሰዎችን ከንንግራቸው መገመት አስቸጋሪ ነው፡፡ ዘወትርም ፖለቲከኞች ንግግር ሲያደርጉ ለሕዘቡ የሚጥመውንና በልቡ የቋጠረውን፤ ምኞቱንና ችግሩን የሚያኩለትን በአማሩ ቃላቶች ጠቅልለው ያቀርቡና በትግበራው ወቅት ፍየል ወዲያ ቅዘምዝም ወዲህ ይሆናሉ፡፡ ምንግዜም ቢሆን ተግባር ከቃላት ይበልጥ እውነትነት አለው፡፡ሃይለማርያም በንግግሩ እራሱን፤ ሕዝቡን፤ፓርቲውን በስራ ለማነሳሳት ጥሯል፡፡ ያም ሆኖ ያለበት ሁኔታ በእጅጉ ችግር የተበተበው ነው፡፡ በፍላጎቱና አምኖበት ይሁን አለያም እጁን ተጠምዝዞ ልኩ ያልሆነውን መጫሚያ ግባበት ተብሏል፡፡ ለዚህም ነው በተነጠፈለት የካባ መንገድ ላይ መራመድ እንዳለበት ግልጽ አድረጓል፡፡ እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ ለአንዱ በልክ የተሰራው መጫሚያ በውሰት ወይም ያለልኩ ልሞክረው በሚል ሰው እግር ሲገባ መላላጡ አይቀሬ መሆኑ ነው፡፡ ላለፉት ጥቂት ዓመታት መጫሚያ ሳይሆን ቡት ጫማ: ነበር የተደረገው:: ቡት ጫማ: የኢትዮጵያን ገጽታ ጨፍልቆ ጨፈላልቆ አበላሽቶታል፡፡ከባድ ጫማ አድርጎ መሬቱን ሁሉ በረገጠው ቁጥር መልኩን ሲያጠፋ ኖሮ አሁን አዲስ ተላባሽ ልሁን ማለት ለመመላለጥ ነውና የሚለወጠው ጫማው ነው ወይስ እግሩ? በጊዜ ብዛት ምናልባት ሃይለማርያምም በዚያ ጫማ ሳይሆን በተለመደው ሕዝባዊ የኢትዮጵያ ጫማ መራመድ ይለምድ ይሆናል፡፡እነዚያ ልካቸው የበዛበት ጫማዎች ጊዜያቸው ያለፈ የውስጥ ቆዳቸው (ሶላቸው) የተበሳሳ ናቸው፡፡ በነዚህ ጫማዎች አንድ ማይል ከተራመደ በኋላ ምናልባትም ኢትዮጵያዊያን በሙሉ አዲስ ጫማ እንደሚያስፈልጋቸው ይረዳ ይሆናል፡፡በዚህም ሃይለማርያምን የሚያደክመው ከፊት ለፊት ያለው ተራራ ሳይሆን በመጫሚያው ውስጥ የተሰገሰገው አሸዋ መሆኑን ይረዳል፡፡ ሁላችንም አዳዲስ ጫማ የምንፈልግበት ወቅት ሩቅ አይደለም፡፡ያ ጊዜ አሁን ነው፡፡ለረጂሙ የዴሞክራሲ፤ የሰብአዊ መብት ጉዞ የሚሆነን አዳዲስ ጫማ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ያስፈልገናል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም የአውርዱልኝ ጫማ አያስፈልገውም፡፡ በራሱ ልክ የተሰራና ለረጂሙና አድካሚው መንገድ ምቹ የሆነ መጫሚያ ነው የሚያስፈልገው፡፡

ሃይለማርያም የተከሸነና ጥሩ ብቃት ያለው ንግግር አድርጓል፡፡ ቢሆንም ግን ለጥቅስ የሚበቁ ቃላት አልነበረባቸውም፤ አለያም ጥልቀትና ራዕይን የሚጠቁሙ መስመሮችም አላካተተምና ለመጪው ጊዜያት ሊታወስ አይችልም ሊጠቀስም ብቃት ያንሰዋል፡፡ ንግግሩ አንድ በፓርላማው ፊት ቀርቦ ቃለ መሃላ ለፈጸመ ሰው የሚበቃ ነው፡፡ ለረጂም ጊዜ ድባብ አጥልቶበት ለነበረው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ በተምሳሌትነት ቀርቦ ቃለመሃላ ፈጽሟል፡፡ ማንም በጣም አናሳ ቁጥር ካለው ብሔር እንዲህ ያለ ደረጃ ላይ ሊደርስ የሚችል ሰው ይወጣል ብሎ ያሰበ ያለ አይመስልም፡፡ በስሌትም ይሁን በአጋጣሚ፤ወይም በድንገት ባልታሰበ ሁኔታ ለዚህ የበቃው ሃይለማርያም ቃለመሃላም አደረገ አላደረገ ንግግር አደረገ አላደረገ ቢሮውን መረከቡ፤በኢትዮጵያ ምንም ይሁን መቼም የማይቀረውንና ማንም ሊያቆመውና ሕዝቡን አሻፈረኝ በማለት የማይገታውን የዴሞክራሲ ሽግግር ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያበሰረ ነው፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ የሃይለማርያም ለዚህ መብቃት ማንም ኢትዮጵያዊ ወጣትና ክፉና ደጉን የለየ ዜጋ ከየትም ይሁን ከየት ዘር አካባ ሳይወስነው በኢትዮጵያ ውስጥ ወደ ከፍተኛ ስልጣን ደረጃ ለመውጣት መንገዱ በድርበቡ የተንገረበበና በቅርቡም በቂ ሆኖ እንደሚከፈት ተስፋ የሚያሳይ እውነታ ነው፡፡

የሃይለማርያምን የቃለማሃላ ዲስኩር እንደ ጨዋታ ለዋጭ አድርጎ ታሪክ ያስታውሰው አያስታውሰው እርግጠኛ አላውቅም፡፡ ታሪክ የሚያስታውሰው በንግገሩ ሳይሆን አለያም በቃለማሃላውም ሳይሆን ስልጣኑን ከተረከበና ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ቢሮውን ከያዘ በኋላ በሚያደርገው እንቅስቃሴና በሚያስገኘው ውጤት ብቻ ነው፡፡ አሁን ግምት መስጠት ጊዜው አይደለም፡፡ቃላቶቹን በጥንቃቄ መምረጡን፤ እንደሃገር መሪ ሰክኖ መናገሩን፤ በተጨባጩ እውነታ ላይ በማትኮሩና እራሱንም እንደአንድ የሥራ ሰው አድርጎ መቅረቡን ወድጄለታለሁ፡፡ ኢትዮጵያን ወደ መሃከለኛ ገቢ ወዳላቸው ሃገሮች ለማድረስ ነው ጥረቴ ያለውን አደንቃለሁ፡፡ ችግሮች እንደሚኖሩና ግን እንቅስቃሴውን እንደማያቋርጥ መናገሩ እውነትነት ያለው ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር፤መሆን ፤ወይም አለመሆን

‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን የብቸኝነት ስራ ነው››፡በማለት ማጊ ታቸር የታላቋ ብሪታንያ ቀዳሚ እንስት ጠቅላይ ሚኒስትር  ጽፋ ነበር፡፡ ለሃይለማርያም በቅድሚያ በቁጥር አነስተኛ ከሆነው በሔር ወጥቶ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን፤የብቸኛ ስራ ብቻ ሳይሆን በእጅጉም አስቸጋሪ ነው፡፡ ምን ይደረግ አንድ ሰው ሊያደርገው የግድ ነው፡፡ ለሃይለማርያም ምን ማድረግ እንዳለበት ቀድሞ የተቀረጸለት በመሆኑ ፈታኝ ፈተና ከአካባቢውም ከውስጥም፤በበለጠም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት የተነሳ ይደርስበታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር  ዊንስተን ቸርችል በዚያ የመከራ ወቅት ለሕዝቡ ያሰሙትን መልእክት በመጠቀስ ለሃይለማርያም መልካሙን ሁሉ እመኝለታለሁ፡፡

‹‹ከዚህ መንግሥት ጋር ለቆሙት እንዳልኩት ሁሉ ለቤቱም ያንኑ እደግመዋለሁ፡፡ከደም ከከባድ ሥራ እና ከላብ በስተቀር የማካፍለው የለኝም፡፡ ከፊት ለፊታችን እጅጉን ከባድና አስቸጋሪ የሆነ ፈተና አለብን፡፡ ከፊት ለፊታችን በርካታ ብዙ እጅግ ብዙ ትግልና መከራ ይጠብቀናል፡፡ዓላማችን ምንድን ነው ብላችሁ ትጠይቃላችሁ? ይህን በአንዲት ቃል እመልሰዋለሁ፡፡ዴሞክራሲ፡፡ በማንኛውም የከበደና ፈታኝ ክፍያ ዴሞክራሲ፡፡ከሽብርና ችግር መከራን በደል ምትክ፤ ዴሞክራሲ፡፡ መንገዱ የቱንም ያህል ረጂምና ፈታኝ ቢሆንም፤ዴሞክራሲ፡፡ ያለዴምክራሲ ኑሮ ሊታሰብ አይቻልምና!››

ኢትዮጵያ ኖራ የምታብበውና ወደ ዴሞክራሲ የምታደርገውም ሽግግር የማይቆም የማይቀለበስ፤ተፈጻሚነቱም የተረጋገጠ ነው!

በግል አስተያየቴም ለጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም አላስፈላጊ ቢመስልም አንድ ምክር ላካፍል እሻለሁ፡፡ትንሽ ፈገግ ይበሉ፤ ፈገግ ሲሉም መላ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን መላው ዓለም አብሮዎት ፈገግ ይላልና!

የተቶርገመው ጽሁፍ (translated from):

http://open.salon.com/blog/almariam/2012/09/23/ethiopia_a_new_prime_minister_in_a_new_year

(ይህን ጦማር ለሌሎችም ያካፍሉ::)

ካሁን በፊት የቀረቡ የጸሃፊው ጦማሮችን  ለማግኘት እዚህ ይጫኑ::

http://www.ecadforum.com/Amharic/archives/category/al-mariam-amharic

http://ethioforum.org/?cat=24