የታሪክ ተጠያቂወች አንሁን፤***
አምባገነን ቢያልፍም፤ አምባ ገነናዊ ስርአት እንዳለ ነው።
ከፍል አስር
አክሎግ ቢራራ (ዶር)
ከ June 19, 2012 ወዲህ የኢትዮጵያን ሕዝብ በᎃሉ ሲያነጋግር የቆየው የጠቅላ ሚንስትር መለስ መኖር አለመኖር በኦፊሻል ደረጃ ለአለም ህዝብ ከዚህ አለም ማረፋቸው August 20, 2012 በህወሓት መንግስት ምክር ቤት አማካኝነት ይፋ ሆነ። ሰው እንደመሆናቸው መጠን፤ መለስ ዜናዊ ታመው ከዚህ አለም ማረፋቸው የፈጣሪ ስራ እንጅ የሰው ስራ አይደለም ብለን መቀበል የሰብአዊነት መለኪያችን ነው። አሰደናቂ የሆነው፤ በተከታታይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ቤተክርስቲያን አለቃ የነበሩት በመለስ የተሾሙት አባ ፓውሎስ ማረፋቸው፤ በመለስ ጥብቅ በሽታ ዙሪያ “ኢትዮጵያ የምትመራው በሕገ መንግስት፤ በስርአት እንጅ በአንድ ሰው አይደለም፤ (መለስ ዜናዊ ቢሞቱም)፤ስር አቱ ይቀጥላል” ያሉት ጀኔራል ሳሞራ ዩንስ በጥብቅ ታመዋል፤ መባሉ ወዘተ የተያያዙ መሆናቸው የኢትዮጵያን ሕዝብ እያነጋገረ ነው። በዚህ ጽሁፍ ለማሳሰብ የምፈልገው ከክፍል ዘጠኝ በጣም የራቀ አይደለም። ባጭሩ፤ አምባገነኑ መለስ ከዚህ አለም ቢለዩም፤ የፈጠሩት በጠባብ ብሄርተኝነት የተመሰረተ ኢትዮጵያዊነትን አጥፊ አስተዳደር፤ አምባገነናዊ ስርአት፤ “እድገታዊ መንግስት” ብለው የሰየሙት ከነጻነት ጋር ግንኙነት የሌልው የእድገት ፈር፤ ለጥቂቶች አገልጋይና መክበሪያ የሆነው የኢኮኖሚ አመራር፤ ፕሮግራምና ፖሊሲ አይለወጥም። እንዳለ ይቆያል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማረፍ ይለውጠዋል ማለት ዘብት ነው።
ከታች የመለስ ዜናዊይን ማረፍ ከማወቄ በፊት ያቀረብኩትን ትንተና እንዳለ ለአንባቢወች እነሆ። ለመጨመር የምፈልገው አበይት ጉዳይ ቢኖር፤ ለህወሓት አገልጋይ የሆነው ፓርላማ ሃይለማሪያም ደሳኝን ለጊዜው የመለስ ተተኪ ማድረጉ ነው። ይህ አሜሪካኖች በውስጥ ይገፉት የነበረ የድርድር ውጤት መሆኑን እንደገና አሳስባለሁ። መለስን በሌላ የትግራይ ተወላጅ መተካቱ የሚያመጣው ችግር በደንብ ታስቦበት የተደረገ የስልት ውጤት ነው። የደቡብ ብሄረሰብ አባል የሆኑትን ምከትል ጠቅላይ ሚኒስትር መሾሙ፤ ለህወሓት ፋታ ይሰጠዋል፤ እርሳቸው የስር አቱ አገልጋይ እንጅ የዲሞክራሳዊ ለውጥ ሃዋርያ ሊሆኑ አይችሉም። በአሁኑ ወቅት፤ በተለይ፤ ወጣቱ ትውልድ የሚጠይቀውን የፍትህ ጥያቄ ህወሓት/ኢህአዴግ ሊፈታው አይችልም። የሚያዋጣው፤ መለስ ዜናዊ የጠነሰሱትን በብሄር ልይኑት የተመሰረተ እራይ (Vision) ለውጦ በኢትዮጵያዊ፤ ህዝባዊ፤ ሁለ አቀፍ የሆነና ዲሞክራሳዊ እራይ መለወጥ ብቻ ነው። ይህን ለማድረግ፤ ህወሓት/ኢህአዴግ ልክ የጠነሰሱትና በስራ ላይ ያዋሉት ግለሰቦች ቀስ በቅስ እንደሚሞቱ ሁሉ፤ ድርጅቱም እንደሰው ማለፏ አይቀርም ብሎ ማሰብን ይጠይቃል። ህወሓት/ኢህአዴግ ከኢትዮጵያ በታች እንጅ በላይ አይደለም። ማንም ድርጅት ቢሆን ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ሊሆን አይችልም። አዲሲ ጠቅላይ ሚንስትር ለመደራደር በር ከከፈቱ አስተዋጾ ያደርጋሉ፤ ዝግ የሆነ ስርአት ከቀጠሉ፤ ከመለስ ሊሻሉ አይችሉም። ትግላችን ከስርአቱ ጋር ነው እንጅ ከአንድ ግለሰብ ብቻ ጋር አይደለም እያልኩ ስከራከር የቆየሁት ለዚህ ነው።
መልስ ልንሰጥበት የሚገባ ጥያቄ፤
ከፊታችን ተደቅኖ የምናየው አደጋ የኢትዮጵያ ዘላቂነት፤ የመላው ሕዝቧ ሰላም፤ ነጻነት፤ እኩልነት መረጋጋት፤ ዲሞክራሳዊ ስርአት ማግኘት፤ ዘላቂነት ያለው ፍትሃዊ እድገት መጎናጽፍ ናቸው። እነዚህ የራእይ ዘርፎች ህወሓት/ኢህአዴግ እንዳደረገው በጥላቻ፤ በቂም በቀልነት መገንባት የለባቸውም። ወደፊት የሚፈጠረው ስርአት ከሁሉ በላይ ለመጭው ትውልድ ተስፋ የሚሰጥ፤ ለሁሉም የኢትዮጵያ ዜጎች የሚያገለግል መሆን አለበት። ይህ እራይ፤ ባለፉት አርባ አመታት በሞከርናቸው መንገዶች ሊገኝ አይችልም፤ ያለፈውን ከተከተልን የትም አንደርስም። በአዲስ መንፈስ፤ በአዲስ እራይ ከተመራን ፍትሃዊ ስር አት ለመገንባት እድሉ አመችና ክፍት ነው። ስለሆነም፤ የችግሮቻችን መነሻወችን ወደኋላ ስናይ፤ መልሶችን ለማግኘት እንችላለን የሚል ግምት አለኝ።
በአጼ ሃይለ ስላሴ ዘመነ መንግስት፤ የህዝብ ብዛት ከሃያ ሚሊዮን በላይ ሆነ፤ የወጣቱ ክፍል እየበዛ ሄደ ሲባል ሰወች በድንጋጤ ሲነጋገሩ አስታውሳለሁ። “ወይ ጉድ፤ ምን ልንሆን ነው፤ ምን ሊመጣ ይሆን፤ ምን ልንበላ ነው” የሚሉ ነበሩ። አሁን የህዝብ ቁጥር አራት እጥፍ ሆኗል። የወጣቱ ቁጥር ከህዝቡ፤ ከአምሳ በመቶ በላይ ነው። በዚያ ጊዜ፤ ትኩረቱ በተለይ የወጣቱ ቁጥር እያደገ፤ የትምህርት እድሉ እየሰፋ ከመሔዱ ላይ እንጂ፤ ከሚያስከትለው የፖሊሲ ለውጥ አስፈላጊነት ላይ አልነበረም። ንጉሱና የቅርብ አማካሪወቻቸው፤ የወጣቱ ብዛት እያደገ፤ ትምህርት እየተስፋፋ በመሄዱ ሊመጣ የሚችለውን ለውጥ እንደ ችግር እንጅ እንደ እድል ከፋች አላዩትም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ወጣት እየሆነ ከሄደ፤ አዲስ አስተሳሰብ፤ አዲስ ፖሊሲ፤ አዲስ አመራር፤ ፍትህ፤ ነጻነት፤ አዲስ የመንግስት ስርአት አንደሚያስፈልግ አላዩትም። የስራ እድል መከፈት አለበት፤ የወጣቱ መብት መጠበቅ አለበት፤ በሃገሩ አገዛዝ፤ በሃገሩ እድል መኖር ማመን አለበት። ስደተኝነት፤ አጎብዳጅነት፤ ጥገኝነት እድሉ መሆን የለበትም። የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት ካለፈው ተምሮ የወጣቱን ጥያቄ ሊመልስ አልቻለም፤ ሊመልስም አይችልም። የመረጠው በፖለቲካው፤ በኢኮኖሚው፤ በማህበራዊ ኑሮው፤ ሌላው ቀርቶ በሃይማኖቱ ሁሉ እየገባ፤ ዘላቂነት ያለው፤ ለምርጥ የትግራይ ቡድንና ተባባሪ ለሆኑ ሌሎች አባላት (Narrow Ethnic Elites) የበላይነት የሆነ የመንግስት ስርአትን መቀጠል ነው። አሁን ያለውን፤ በመንግስትአመራር (መለስን በመተካት)፤ በኦርቶዶስ ቤተክርስቲያን ( ህወሓት የሾማቸውን ፓትርያርክ በመተካት) ሹክቻና ግብግብ ስናይ ህወሓት አሁንም የሚጥረው ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ እንጅ የመጣውን እድል ተጠቅሞ ሁሉን ለሚያካትት ዲሞክራሳዊ ለውጥ አይደለም። ይህ ባህሪ ዛሬ የመጣ ሳይሆን ከአርባ አመታት በፊት የመጣ ነው፤ በተለይ፤ ከኢርትርያ ነጻ አውጭ ግንባር፤ ከማርክሲዝም ሌኒኒዝም የተማርነው ፍልስፍና።
በ 1972 እ. አ. አ. ከአሚሪካ ወደ ኢትዮጵያ ለዶክትሬት ማእረግ (Research on land tenure and reform) ምርምርና ለማግባት ስመለስ፤ ያላሰብኩት ችግር ቦሌ ገጠመኝ። ወደ ጓደኞቸ፤ ዘመዶቸ፤ ከመሄድ ይልቅ በቀጥታ ወደ ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ተወሰድኩ፤ ታሰርኩ። ቁም ነገሩ ባልሰራሁት ወንጀል “ተገንጣዮችን ደገፍክ” ተብየ መታሰሬ አይደለም። የኤርትርያ ነጻ አውጭ ግንባር የሚያደርገውን ያውቅ ነበር። ወንጀሌ፤ በተገላቢጦሽ፤ የኤርትራን መገንጠል “እደግፋለሁ” የሚል ጽሁፍ ግንባሩ፤ በስሜ ጽፎ ለኢትዮጵያ መንግስት ስለላከ ነው። ግንባሩ የተጠቀመው የውጭ አገር ሰወችን፤ የኤርትራን ተወላጆች ሳይሆን፤ ሌሎች ኢትዮጵያዊያንን ነበር። በወቅቱ፤ የኤርትራ ነጻ አውጭ ግንባር እኛን ለመከፋፈል ይጠቀምበት የነበረውን ብልሃት አሁንም የህወሓት መሪወች ይጠቀሙበታል። አንዳንድ የህወሓት የበላይ ግለሰቦች ለኢትዮጵያና ለመላው ሕዝቧ ካላቸው ታማኝነት የበለጠ ለኤርትርያ ባለስልጣኖች ያላቸው ወዳጅነት “ወንድማማችነት” ያይላል። ለጠባብ ብሄርተኛነት ያላቸው ታማኝነት ያይላል። ያ፤ በኔ ትውልድ፤ በብሄር/ብሄረሰብ ስም ይካሄድ የነበረው መቀራረብ አሁንም በህወሓት ውስጥ እንዳለ ነው። አገራችን ወደቧን ያጣችው፤ ብዙ ሽህ ኢትዮጵያዊን የሞቱበት፤ መረጋጋት የሌለበት፤ ጥገኝነት የተፈጠረበት ወዘተ ለዚህ ነው። የመለስ ዜናዊ “አምልኮ” ራእይና ቅርስ (Legacy) ከዚህ ሊለይ አይችልም። እሳቸውና የቅርብ ጓደኞቻቸው ለሃገራችንና ለስብጥር ሕዝቧ(diverse population) የፈጠሩትን ችግር አውርሰውን ያለፉ መሆናቸውን ታሪክ ይመሰክራል::
ህወሓት ሆነ ሌሎች በብሄር/ብሄረሰብ የሚመሩ ሃይሎች የሚያደርጉት ብልሃታዊ መከፋፈል እንደቀጠለ ነው። ብንቀበል፤ ባንቀበልም፤ በተቃዋሚው ክፍል ውስጥ የሚካሄደው የእርስ በእርስ መወነጃጀል፤ ሽሙጥ፤ መጠላለፍ፤ የስም ማጥፋት ዘመቻ፤ የግለሰብን ክብርና ሰብእነት ማዋረድ፤ አገር ሳይኖር የስልጣን ውድድር፤ “እኔ ለሃገሬ ከእናንተ ይበልጥ አውቃለሁ” ወዘተ፤ የሚል አስተሳሰብ፤ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ግዛታዊ አንድነት፤ ለመላው ሕዝቧ ሰላም፤ ፍትህና የህዝብ ስልጣን እውን መሆን ጉዳት አምጥቷል፤ እያመጣ ነው፤ ወደፊትም ያመጣል። የዚህ አይነት የመከፋፍልና እርስ በእርስ የመነታረክ ባህል፤ አመለካከት ባህሪይና ተግባር ካልቆመ አሁንም ለውጥ ለማምጣት አይቻልም። አገራችን በአደጋ አፋፍ ላይ ስታንዣብብ ትቆያለች፤ ድህነትና ጥገኝነት ይቀጥላል፤ ወጣቱ ትውልድ እድሉ ስደት ይሆናል። ይህ፤ በብሄር ሆነ፤ በሃይማኖት የሚደረገው መከፋፈል መቆም ያለበት ከጥቂቶች በቀር፤ ለአብዛኛው ህዝብ ስለማይብጅ ነው።በቅርቡ የተጀመረውን የህብረት ጥሪና ከአንዳንድ ክፍሎች የሚደረገውን ትችት ስንመለከት ይህ የመዝለፍና የመከፋፈል ባህሪይ አሁንም እንደቀጠለ እናየዋለን። ልዩነቶችን የሚያባብሱት በተቃዋሚ ክፍሎች በብልሃት እየገቡ እኛን መስለው እኛን የሚከፋፍሉን ግለሰቦች ስላሉ ጭምር ነው። ልዩነቶች ካሉ፤ በጨዋነት ለመነጋገርና ለመፍታት ያልቻልነው ለዚህ ነው። እነዚህ ሰርጎ ገቦች በአጼ ሃይለ ስላሴ ጊዜ የኤርትርያ ነጻ አውጭ ግንባር፤ በደርግ ጊዜ፤ ህወሓትና ሌሎች ይጠቀሙበት የነበረውን ፈር (መንገድ) እየተከተሉ ናቸው። ሌላው ቀርቶ በኦርቶዶስ ቤተክርስቲያን አመራር ውስጥ እየገቡ፤በስደት ያለው ቤተክርስቲያንና አባላት ከሶስት ሊከፋፈል–የስደቱን ሶኖድ ደጋፊ፤ ህወሓት የመረጠውን ሲኖድ ደጋፊና “ነጻ” መሆን እንፈልጋለን የሚሉትን አብያተ ክርስቲያን ተቋሞች ደጋፊ የሆነ አንድ እምነትን ከሶስት የከፋፈለ ሂደት ለመፍጠር ችሏል። ይህ ሊሆን የቻለው እኛ ስለፈቀድን ጭምር ነው።
ከህወሓት የሚመጣው ክስና ስም ማጥፋት፤ የፖለቲካ ሆነ የሃይማኖት ክፍፍል መኖር ምንም አያስደንቅም። ካልከፋፈለ የበላይነትን ይዞ ለመቆየት አይችልም። ሰላም፤ ፍትህ፤ አብሮ መኖር፤ ዲሚክራሳዊ ለውጥ የምንፈልግ ከሆነ፤ ከተቃዋሚው ክፍል የሚመጣውን መከፋፈል፤ እርስ በእርስ መጋጨት ዝም ብለን፤ እያየን እንዳላየን፤ ለመመልከት አንችልም። ከሁሉ በላይ ተጠቃሚ የሚሆኑት ጠባቡ ህወሓት/ የኢህአዴግ የበላይችና የኢትዮጵያ የውጭ ጠላቶች ናቸው። የኢትዯጵያ የውጭ ጠላቶች በምንም አይነት አገራችን ሰላም፤ ዘላቂነትና ፍትሃዊ ያለው እድገት እንዲኖራት አይፈልጉም። በክፍል ዘጠኝ ለማሳየት እንደሞከርኩት፤ በተደጋጋሚ የምናየው ችግር፤ እኛ ኢትዮጵያዊያን ለመሰብሰብ ስንጀምር፤ ሀወሓት ነጥሎ ይከሰናል፤ ያስረናል፤ ያሳድደናል፤ ያዋርደናል፤ ይገድለናል። ለዚህ የሚጠቀምበት ዘዴ በመካከላችን ልዩነቶችን መፍጠር፤ መጠቀም፤ እርስ በርሳችን እንድንወንጃጀልና ጀሮ ጠቢወች እንድንሆን በማድረግ ጭምር ነው። እኛ ለህወሓት/ኢህአዴግ ዘላቂነት እየሰራን ነው ማለት ይህ ነው። በልዩነት ላይ የምናጠፋው ጉልበት፤ እውቀት፤ ገንዝብ ከሚያስማሙን ላይ ቢውሉ ኖሮ እስካሁን ለወገን የሚያኮራ ስራ በሰራን ነበር። በአንድ ድምጽ፤ ለአንድ አላማ በቆምን ነበር። የኢትዮጵያንና የአለምን ህዝብ ወደኛ ለመሳብ በቻልን ነበር። ፈቃደኞች ከሆን፤ አሁንም እንችላለን። ለዚህ ነው፤ ያለፈውን ስህተት አንድገም ብለን በጋራ መነሳት ያለብን።
ያለፈውን ስህተት አንድገም፤
ባለፍቱ አርባ አመታት ብዙ ስህተቶች ሰርተናል። እዚህ ላይ ለማስታወስ የምፈልገው አንድ አቢይ ነገር አለ። የንጉሱን ስርአት ለመጣል ብዙ የተማሩ ኢትዮጵያውያን፤ ከጀርባ ያለውን ሴራ ሳይመረምሩ፤ ለጠባብ ብሄርተኛ የፖለቲካ እንቅስቃሴወችና ለውጭ አገር መንግስታት ድጋፍ ሰጥተው አሁን ለደረሰው ቀውስ አስተዋጦ አድርገዋል፤ አድርገናል። ማንም “ከደሙ ንጹህ ነኝ” ለማለት የሚችል የለም። ህወሓት ደርግን ተቃውሞ በተሰማራበት ወቅት፤ ያን አሰቃቂ መንግስት በመጥላትና ለመጣል ስንል፤ ብዙወቻችን አብረን ተሰልፈናል፤ ረድተናል። መንግስቱ ሃይለማሪያም የመራው ደርግ፤ አገር ወዳድና ትውልድ የማይተካቸው፤ አገር ወዳድ መሪወች፤ የሰራዊትና እዝ አባላት፤ ምሁራንና ወጣቶች ሲገድል፤ ወይንም ሲያስገድል፤ ወይንም እርስ በርሳችን እንድንገዳደል ድጋፍ ሲሰጥ፤ በጀርባ የመጣ በዘር እርዩተአለም የተበረዘ፤ አገራችን ሰላም የነሳት፤ ቡድን በቀጥታም ሆነ በድብቅ አጠናክሯል፤ አጠናከረናል። ይህ፤ ያላሰብነውም ሆነ ያሰብነው ድጋፍ የእርስ በእርስ ንትርከን፤ ቂመኝነትንና ቂም በቀልነትን፤ አለመግባባትን፤ ለስልጣን ስግብግብነትን፤ ሆዳምነትን፤ መጥፎ የፖለቲካ ባህልን ትቶልን ሂዷል። ይህ አስተዋጾ ባይኖር ጠባብ ብሄርተኛው የህወሓት ቡድን የፖለቲካ የበላይ፤ የኢኮኖሚ ሙሉ-በሙሉ ተቆጣጣሪ ሊሆን አይችልም ነበር። አሁንም፤ ቢሆን ይህ የመከፋፈል፤ የቂም በቀል፤ የራስ ወዳድነት ባህል እያደከመን ባልሄደ ነብር። ብዙ የተማረ፤ ልምድና ሃቭት ያለው የሰው ሃይል ቢኖረንም፤ ለዚህ ድክመት ገና ብልሃት አልነደፍንለትም። ሌላው ቀርቶ የምንነጋገረው፤ የምንሰበሰበው፤ ከምናውቃቸውና ከለመድናቸው ጋር እንጅ ከሌች ከማናውቃቸው ኢትዮጵያዊያን ጋር አይደለም። የምንጠላቸውን ተቃዋሚወች እንደጠላት የምንወንጅለው መጥፎ ባህል ተከትለን ነው።
ከሃይለ ሰላሴ/ከደርግ መንግስት ጀምሮ፤ የጎሳ ፖለቲካ አለማዋጣቱን እያየን አሁንም በጎሳ የፖለቲካ አለም፤ “ከቄሳር በላይ ቄሳር ነኝ” የምንል ብዙ ነን። አገር ለውጭ መንግስታትንና ሃብታሞች እየተቸረቸረ፤ እኛ በብዛት እየተሰደድን፤ ብዙ ሚሊዮን ኢትዮጵዩያዊና በርሃቭ አለንጋ እየተገረፉ፤ በአመት ብዙ ቢሊየን ዶላር ከሃገር በስርቆት እየወጣ፤ ወዘተ፤ ለፖለቲካ ስልጣን የምንሻማ አለን። ችግሩ ሁሉን ብሄር/ብሄረሰብ የሚመለከት መሆኑ እየገባን የምናተኩረው ከቡድናዊነት፤ ከመንደረኝነት፤ ከልዩነቶቻቺን ላይ እንጂ በጋራ ከምንጋራቸው እሴቶች ላይ አይደለም። ያለውን ችግር በብዙ መለኪያወች ለማሰስ ይቻላል። ለምሳሌ፤ አገር ውስጥ የተቋቋሙትን ከዘጠና ያላነሱ፤ የብሄር ፖለቲካ ድርጅቶች ማየት በቂ ነው። አሁን ያለው አመራር በተአምር ቢወድቅ የብሄር ፖለቲካ ድርጅቶች በምን አገራዊ አጀንዳ እንደሚመሩ ማንም አያውቅም፤ አቋማቸውን አልገለጹም። ማን ከማን ጋር እጅና ጓንቲ ሆኖ እንደሚቀርብ አናውቅም። ግልጽነትና ድፍረት አለ ለማለት ያስቸግራል።
ለምሳሌ፤ በመተካካቱና በሕዝብ አልገዛም ባይነት የሕዝብ አመጽ ቢነሳና ለውጥ ቢመጣ፤ አንቀጽ ሰላሳ ዘጠኝን እንዴት እንደሚመለከቱ አናውቅም። የክልልን ጉዳትና ጥቅም እስካሁን አላወቁትም ለማለት አንችልም። ተጠቃሚው ማን እንደሆነ፤ የተጎዳው ማን እንደሆነ ያውቁታል። ካላቸው ፍልስፍና ግን ፈቀቅ አላሉም። ዘዴወቻቸው መቀየር ካላማቸው አይለያቸውም። ብዙ የውስጥ ታዛቢወች የሚሉት፤ እነዚህ የብሄር ስብስቦች፤ የህዝብ አመጽ ቢነሳ ከሌላው ህብረተስብ ጋር እንዴት እንደሚቆሙ አናውቅም ነው። ይህን ሊመልሱት የሚገባቸው መሪወቹ እንጅ እኛ አይደለንም፤ ተራውም አባል አይደለም። ህወሓት የተከለብንን በዘር የተከፋፈለ ስርአት አሁንም መከተላቸው ግን፤ ለቆሙለት ህብረተሰብምም ሆነ ለኢትዮጵያ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዘነ ነው። ህወሓትን ብንወስድ፤ የሚከተለው የጠባብ ብሄርተኛ አመራር፤ ለራሱ ተራ አባላትም ቢሆን አደገኛ እንደሚሆን እያደር እናየዋለን።
ጠቅላይ ሚንስትር መለስ “ባይመለሱ” ምን ይሆናል?
የጠቅላይ መለስ ዜናዊ “አምልኮ” ለህወሓት አባላትና ደጋፊወች ስጋትና አደጋ ማምጣቱ አያጠያይቅም። ሕዝብ በአንድ ላይ ከተነሳ፤ የፈለገው መተካት ቢመጣ፤ የመለስ ዜናዊ ፍልስፍና ማለፏ አያጠራጥርም። ሆኖም፤ በዘላቂነት ደረጃ፤ ምንም አይነት የአመራር መተካካት ቢመጣ፤ ሀወሓትና ተጠቃሚ የሆኑ የኢህአዴግ መሪወችና ምርጥ አባላት በቀላሉ ስልጣናቸውን አይለቁም። ሌላ ቀርቶ፤ ካልተገደዱ፤ ለመደራደርም ፈቃደኛ አይሆኑም። ለምን ብለው? በአሁኑ ወቅት አብዛኛው ዘገባ ስለ መለስ ዜናዊ መኖር ማረፍ ሲሆን፤ የውጭ ታዛቢወች–ለምሳሌ፤ ግራሃም ፖብልስ፤ ሪኔ ለፎርት፤ ቴሬንስ ላየንስ፤ የፋይናንሻል ታይምስ፤ ኢኮኖሚስት፤ ጋርዲያን፤ ዋሽንግቶን ፖስት፤ በሃገራችን የመተካካት ፉክክር እንደነበረ፤ አለመረጋጋት እንደምቀጥል እንጅ መለስን በርግጥ ማን የተቃዋሚው ክፍል ለመደራደር ብቃት እንዳለው ወይንም እንደሌለው አይጠቁሙም። ሊጠቁሙም አይችሉም።
ስብሰብ አድርጌ ስመለከተው፤ ከነዚህ ዘገባወች የገበየኋቸው ቁም ነገሮች አሉ።
• ጠቅላይ መለስ ዜናዊ እንደተጠረጠርው ከአሁን ከዚህ አለም ተለይተዋል፤ ህወሓት/ኢህ አዴግ ግን እሳቸውን በተመሳሳይም ባይሆን፤ በታማኝነታቸው የማያወላዱ ለመተካት ለመተካት ችሏል፤
• እድገት ያለምንም ነጻነት፤ ዘላቂነትና ፍትሃዊነት ይኖረዋል ያሉት የመለስ መንግስት ስርአት ከታላቅ ውጥረት ላይ እንዳለ፤ ያለ ሕዝብ ተሳትፎ ድህነት እንደማይወገድ፤ ሙስናና ከህግ ውጭ ከሃገር የሚወጣው የውጭ ምንዛሬ በብዙ ቢሊየን ዶላር እንደሚቀጥል፤
• በአመት ከሚገኘው አራት ቢሊዮን ዶላር እርዳታ፤ ከስደተኞች ከሚገኘው፤ በአመት ከሶስት ቢሊየን ዶላር በላይ ከሚሆነው የውጭ ምንዛሬ፤ አብዛኝው እየተሰረቀ፤ ለጥቂቶች ማክበሪያ ወደ ውጭ እንደሚጎርፍ፤ ለዚህ የሚቀጣው የኢትዮጵያ ድሃ ሕዝብ እንደሆነ ይቆያል፤
• የመለስ መንግስት በአንዳንድ፤ በተለይ በመሰረተ ልማት የሚጨበጥ እድትገን ሊያመጣ ቢችልም መዋቅራዊይና የፖሊሲ ለውጥ ለማምጣት አለመቻሉ፤ ለአብዛኛው ድሃ ክፍል አስተማማኝ ኑሮ አለመፍጠሩ፤ ሃግራችንና ተራውን ሕዝብ ለአደጋ እንደዳረገው፤ የዋጋ ግፍሸት እንደሚቀጥል፤ ምልክቶቹ ጎልተው ይታያሉ፤
• የመለስ መንግስት ከሶስት እስከ ሰባት ሚሊዮን የሚገመት (የተሸጠ/የተከራየና ለወደፊት የታቀደ) ሔክታር ለም መሬት ለውጭ መንግታትና የግል ሃብታሞች፤ ምርጥ የትግራይ ተወላጆች ማስተላለፉ ለምግብ ዋስትና ሆነ ለድሃው ገበሬ ጉዳት የሚያመጣ መሆኑ፤ ለሃገራችንም ግዛታዊ አንድነት አደጋን መጋበዙ ይታያል፤
• የመለስ ዜናዊ የእድገት መንግስት ከሁሉም በላይ የቁጥጥር ኢኮኖሚ ስርአት መዘርጋቱ የሃገራችን ከበርቴወች አድሎ በሌለበት ሁኔታ እንዳይሰሩ፤ እንዳያመርቱ፤ እንዳይወዳደሩ፤ ገንዘባቸውን በአገር ውስጥ አንዳይጠቀሙ እንደሚያግድ፤ ፓርቲውና እንደ ኤፈርት ያሉ ከመቶ በላይ የሆኑ ድርጅቶችን የሚቆጣጠሩ ተቋሞች ኢኮኖሚውን በሞኖፖሊ እንደያዙትና አድሎው ኢኮኖሚውን መንግስት ለመቆጣጠር ወደማይችልበት ደረጃ እየመራው ይታያል፤
• ህወሓት/ኢህአዴግ የፈጠረው ስርአት ለነጻነት፤ ለእኩልነት፤ ለሰላም፤ ለዲሞክራሳዊ ተሳትፎና አገዛዝ ጸር መሆኑ ችግርን እንደወለደ፤ እንደሚወልድ አመልካቾች እየሰፉ ይታያሉ፤
• የምእራብ መንግስታት፣ በተለይ አሜሪካ፤ አዲስ ወዳጅ አገሮች፤ በተለይ ቻይና፤ ከሁሉ በላይ መረጋጋትን እንደመረጡ፤ ወደፊትም እንደሚመርጡ በሃይለ ማሪያም ደሳለኝ መሾም እያየነው ነው፤
• የመለስ ክስልጣን በሞት መለየት፤ የነጻነትና የዲሞክራሲ ጭላንጭል ማሳየት ቢችልም፤ የተቃዋሚው ክፍል መከፋፈሉ፤ ደካማ መሆኑ፤ በአንድ ድምጽ ለአንድ አላማ አለመቆሙ መተካካቱ ከህወሓትና ከኢሓዴግ ቁጥጥር እንዳለወጣ አሳይቷል።
የተቃዋሚው የመደራደር አቅም ሊጠነክር የሚችለው፤ በልይነት ላይ በማተኮር ሳይሆን፤ በአንድ ላይ፤ ለፍትህ፤ ለሰላም፤ ለድርድር፤ ለብሄራዊ እርቅ፤ ለነጻነትና ለኢትዮጵያ ዘላቂ ጥቅም ለመቆም ሲቻል ነው። ለዚህ የሚረዳ ሁኔታን ለማመቻቸት የሚችለው በውጭ ያለው የተቃዋሚ ሃይል ሲሰበሰብና በዘላቂነት ተባብሮ ሲሰራ፤ ገንዘቡን፤ እውቀቱን፤ ምክሩን አገር ቤት ላሉ እውነተኛ ተቃዋሚወች ሲሰጥ ነው።
ከነዚህ ግንዛቤወች መካከል ለመረዳት የምንችለው፤የአንድ ፓርቲ ስርአት እንደሚቀጥል፤ ለዚህ የአሜሪካ መንግስት፤ ሌላ አማራጭ የለም ብሎ ስለገመተ፤ ለህወሓት/ኢህአዴግ የውስጥ ድጋፍ እንደሰጠ ነው። ከዚህ ድምዳሜ የደረሰበት ዋና ምክንያት ከአንድ ፓርቲ አምባ ገነን መንግስት ጋር ፍቅር ስላለው ሳይሆን (ይህ በዘላቂነት እንደማያዋጣ በሙባረክ አይተውታል)፤ የተቃዋሚው ክፍል የተከፋፈለ፤ የሚሰራውን በብልሃት የማይከተል፤ ደካማ፤ ብቃት የሌለው፤ የማይሰበሰብ፤ አብዛኛው በብሄር የተደራጀ ነው በማለት ነው። ሌላው፤ የወጣቱ ቁጥር እያደገ ቢሄድም፤ ለመታገል፤ የራሱን መብት ለማስመስከር ገና አልተዘጋጀም የሚል ግምትም ስላለው ነው። በወጣቱ ላይ ያለው አመለካከት የኢትዮጵያን ባህል አለማወቅን ያሳያል። ወጣቱ የህወሓት/ኢህአዴግን ስርአት እንደማይቀበል በዘጠና ሰባቱ ምርጫ አሳይቷል፤ አሁንም በተቻለው ይታገላል። የሕዝብ አመጽ ዳር እስከዳር ከተያያዘ፤ ፊት ለፊት የሚታገለው ወጣቱ ትውልድ መሆኑን አልጠራጠርም። ነጻ ምርጫ ካለ፤ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተቃዋሚ ክፍሉን እንደሚደግፍ አልጠራጠርም። ይህን ለውጭ መንግስታት ማሳመን ያለብን እኛው ነን። ባጭር አነጋገር፤ ጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሞቱም ህወሓት/ኢህአዴግ ከስልጣኑ ወደ ኋላ አይልም። በውስጡ ላሉ ደጋፊወች አስታራቂ የሆነ፤ ኢህአዴግና የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቀበለዋል ብሎ የሚገምተውን አማራጭ ከስራ ላይ ውሏል። ለጊዜው ፋታ ሰጥቷል።
ከላይ ያለው እንዳለ ሆኖ፤ የውስጥ የመተካካት ግብግቡ ግን የጦፈ ነበር ለማለት የሚያስችሉ ብዙ መለኪያወ ች አሉ። አንዱ ግብግብ በህወሓት ውስጥ የተካሄደው ዝግ ድርድር ነው። ሁለተኛው፤ በሕወሓት የበላዮችና በኢህአዴግ መካከል የተካሄደው “ጠቅላይ ሚንስትርነቱ ለኔ ይገባኛል፤ የኔ ተራ ነው” የሚል ግብግብ ነበር።ሁለቱም ግብግቦች ቀላል አልነበሩም። ለምሳሌ፤ ግልጽነት ቢኖረው፤ ህገ፤ መንግስቱም ባይደነግገው፤ ፓርላማው ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ መለስን ለመተካት ይችላሉ የሚለው መለስ በጥብቅ መታመማቸው ሲታወቅ ለህዝብ በተገለጸ ነበር። እንደተወራው ፤ ለጊዜውም ቢሆን፤ ይህ አማራጭ ከስራ ላይ ውሏል። ብይውል ኖሮ፤ በኢህአዴግ ውስጥ ያለው ልዩነት ሊፈነዳ ይችል ነበር። ሃይለ ማሪያም ደሳለኝ መለስን ባይተኩ ለገዥው ፓርቲ አደጋ እነሚፈጥር ያውቁታል። ማለትም፤ ህወሓት ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩን ወደጎን ትቶ ሌላ ትግራይ ቢሾም ሊመጣ የሚችለውን አደጋ አውቀውታል፤ ይህን በሚገባ የተገነዘበው ስብሃት ነጋ ነበር። አንዳንዶች የህወሓት አባላትና ደጋፊወች የፈሩት፤ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ መለስን ከተኩ፤ ቀስ በቀስ ስልጣን ከጥቂት የትግራይና የኤርትርያ ተወላጆች ወደ ሌሎች ይዞራል በሚል ነበር። ከሆነም ሌሎች ከኢኮኖሚጥቅሞች ጋር የተያያዙ ሁሉ ከአደጋ ላይ ይወድቃሉ የሚል ስጋት እንዳለ ለመገመት አያዳግትም።የመለስ መተካት በብልሃት፤ በምስጢር፤ በድብቅ፤ በውሸት ፕሮፓጋንዳ ተይዞ የነበረው ሽግግሩ ሊያመጣ የሚችለውን አደጋ በማመዛዝን ነው ለማለት ይቻላል።
ሶስተኛው ችግር በህወሓት/ኢህአዴግና በተገለለው ተቃዋሚ ክፍል ያለው መቃቃር ነው። የመለስ ከዚህ አለም ማለፍ የድርድር ጭናንጭል ሊያመጣ ይችላል የሚሉ አሉ። አሜሪካኖችም ድርድር እንዲደረግ፤ እርቅና ሰላም እንዲሰፍን፤ ተቃዋሚ ፓርቲወች ተደራድረው ወደፊት፤ አንድ አይነት የ “ሽግግር መንግስት” እንዲቋቋ፤ ቀጥሎም፤ ነጻና ተጽኖ የሌለበት ምርጫ እንዲካሄድ ይፈልጋሉ ቢባል አያስደንቅም። ይህ፤ የረጅም ጊዜ እቅድ ይመስላል። ከጥቅማቸው ግን ፍንክች አይሉም። አገራችን ከአደጋ ለመታደግ ከተፈለገ፤ ህወሓት/ኢህአዴግ፤ በአንድ በክሉ፤ በሌላ ደግሞ፤ተቃዋሚወች በሙሉ፤ አሜሪካኖችና ሌሎች መንግስታት፤ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወዘተ በአስታራቂነት ደረጃ ሆነው፤ ለብሄራዊ ሰላም እርቅና ሽግግር ያልተቆጠበ ጥረት ቢያደርጉ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ የመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲ አገዛዝ መሰረት ለመጣል ይቻላል፤ ሆኖም፤ ይህ አማራጭ፤ ከምኞት በላይ ላያልፍ ይችላል።
ለተቃዋሚው ህሉ፤ አማራጭ ሊሆን የማይችለው፤ አምባ ገነንን በአምባ ገነን፤ በአንድ ብሄርተኛ አገዛዝ የተመሰረተ ፓርቲን በተመሳሳይ መለወጥ ነው። ይህ ከሆነ፤ መሰረታዊና ፍትሃዊ ለውጥ ሊያመጣ አይችልም። መሰብሰብ፤ አብሮ መስራት፤ መፈላለግ፤ አገር ውስጥ ካሉ እምቅና ግልጽ ታጋይ ድርጅቶ ጋር በጥበብ መቆራኘት፤ ለእነዚህ አገራዊ ለሆኑ ፓርቲወች የገንዘብ፤ የቴክኒክ፤ የሃሳብ፤ የሞራል ውዘተ ድጋፍ መስጠት የሚያስፈልገው ይህ እንደገና የማይገኝ እድል እንዳያመልጥ ነው። በጠባቡ በማየት፤ ለጊዜያዊ ጥቅም ብቻ የቆሙ የብሄር ድርጅቶች የእርቅ፤ የሰላም፤ የአብሮ ተቻችሎ መኖር፤ የግለሰብ ነጻነት፤ የኢትዮጵያን ግዛታዊ አንድነት፤ ወዘተ የያዘ ድርድርን ለመፈለጋቸው ማስረጃ የለም፤ ማስታወቅ ያለባቸው መሪወቻቸው ናቸው። አንዳዶቹ መሪወች፤ ብቸኛ ተጠቃሚ ሆነው ለመቆየት ይፈልጋሉ። ለምሳሌ፤ ህወሓት ለራሱ በመከፋፈል ለሚገኝ ጥቅም የፈጠረውን የአማራውን ብአዲየንን ስናይ የአማራን ህብረተሰብ ማገልገል ቀርቶ የራሱንም አባላትና አመራር ጥቅምና ስልጣን ለማሰከበር አልቻለም፤ አይችልም። በአሁኑ የስልጣን ግብግብ ስልጣን ይገባኛል ብሎ በአንደበት ለመቆም የሚችል አመራር የለውም። ካለው፤ ለሚወክለው ህብረተሰብ የማስታወቅ ሃላፊነት አለበት። አጎብዳጅና ሎሌ እንዲሆን የተፈጠረ ድርጅት የክልሉን ጥቅም፤ የህብረተሰቡን መብት ለመታደግ ነጻነት የለውም።
ለምሳሌ፤ወልቃይት ጠገዴ፤ ወዘተ ለትግራይ ክልል ሲሰጥ፤ የዋልዳብ ገዳም በህወሃት ትእቢተኞች ተደፍሮ ሲታረስ፤ የአማራ “ህብረተሰብ ነህ፤ ወደመጣህበት ክልል” ተመለስ ተብሎ ብዙ ሽህ አማርኛ ተናጋሪ ከደቡብ ሲሳደድና ሲሰደድ፤ ቤቱ ሲቃጠል፤ ንብረቱ ሲወድም፤ ኑሮው ሲናጋ፤ ራሱን፤ የአማራ ወካይ ነኝ የሚለውን ድርጅት ተራው ህዝብ የሚስቅበት፤ “የት ነበርክ፤ ለማን ደረስክ” ብሎ የሚጠይቀው ለዚህ ነው። የኢትዮጵያ ወሰን ተደፍሮ፤ በመለሰ ትእዛዝ ለሱዳን መንግስት በምስጢር ሲሰጥ፤ ዋልድባ በልማት ስም ሲታረስ፤ ይህ የህወሓት ፍጥረት አጎብዳጅ ሆኖ በቃለ አቀባይነት ስራ አስፈጽሟል። የሰሜን ሱዳን መንግስት ለህወሓትና ለሱዳን ተብሎ ሁለት ቆንጽላወች በጎንደር ክፍለ ሃገር ሲያቋቁም ለምን ብሎ ያልጠየቀ፤ እንዲያውም “እልል” ብሎ አስተናጋጅ የሆነ ድርጅት ነው። የሚያሳየው አንድ ነገር ቢኖር፤ የትም ቦታ ቢሆን፤ የብሄር ፖለቲካ ድርጂቶች የሚያገለግሉት ህወሓትንና የራሳቸውን የበላዮች ጥቅም እንጅ ይወክላሉ የሚሉትን ህብረተሰብ አይደለም። በጋምብየላ፤ በኦሮምያ፤ በአማራ፤ በደቡብ፤ በትግራይ፤ ወዘተ የሚታየውም ሰእል ከጎንደሩ ጋር ይመሳሰላል። ስለዚህ፤ በአገር ውስጥና በውጭ ያለው የዘር፤ያለፈ የፖለቲካ ታሪክ፤ የመደብ፤ የጾታ፤ የፖለቲካ ወዘተ ክፍፍል ለህወሓትና ለኢህአዴግ የበላዮች አሁንም ጠቅሟቸዋል።
የውጭ ታዛቢወች ይህን “የከፋፍለህ ግዛው” ጠቢብ እምቢ ብለን አለመተባበራችን የድክመታችንን ጥልቀትና ስፋት ያሳያል ይላሉ። ይህን ጎጅ አስተሳሰብ ለመለወጥ የምንችለው በሃገር ቤትና በውጭ የምንገኝ ተቆርቋሪ ነን ባዮች ብቻ ነን። ይህን ችግር ለመፍታት፤ ተደጋግፍን በፍጥነት ስራ ከሰራን፤ ለመደራደር ያለንን አቅም ከፍ ያደርገዋል። ካላደረግን የመለስ ከዚህ አለም ማለፍ አይለውጠውም። ስለ መለስ ዜናዊ በየቀኑ በተከታታይ ስናወራ ቆየተናል። ነገ ስለምን እንደምናወራ አላውቅም። ህሉም መገናኛ ብዙሃን፤ ድህረገጾች፤ ስብስቦች ሊነጋገሩበት የሚገባው ያላጠናነው አበይት ጉዳይ ለመደራደር ማነቆ የሚሆን የማንከደው ሌላ ችግር አለ። የኢኮኖሚ ጥቅም ይባላል። የመለስ ከዚህ አለም ማለፍ፤ ይህን የጥቅም እትብት አይሰብረውም፤ እንዲያውም ሊያጠናክረው ይችላል።
የአጎብዳጅ አገዛዝ፤
ህወሓት/ኢህአዴግ ራሱን አጠንክሮ ለማቆየት ቡድኑና ደጋፊወቹ ሃብት የሚያካብቱበትንና የሚጠቀሙበትን መንገድ የሚያቃና፤ ደንቡን የሚያመቻች፤ ህጉን የሚጠመዝዝ ቡድን ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በጠቅላይ ሚንስትሩ ብርቱ ህመም ወቅት፤ መሪወቹ “በመኖር አለመኖራቸው” ዋሽቷል። በረከት ሰሞን መለስ ዜናዊ በመስከረም እንደገና ወደ ስልጣናቸው ይመለሳሉ ሲል፤ ስብሃት ነጋ፤ አድርጎት በማያውቀው፤ እንዲያውም “ጠላት ነው” በሚለው መገናኛ ብዙሃን፤ በኢሳት፤ “ መለስ ያሉበትን አላውቅም፤ አገር ቤት ያሉ አይመስለኝም፤ መረጋጋት አለ፤ አመራርና ውሳኔ የሚደረገው በጋራ ነው፤ መተካካት የሚካሄደው በሕገ መንግስቱና በፓርቲው አስተዳደር ደንብ” ነው ወዘተ ያሉበት ተጻራሪ የሆነ ገለጻ፤ ሆነ ተብሎ የተደረገ ነበር። በረከትና ስብሃት ነጋ አይነጋገሩም፤ አይገናኙም፤ የሚሰሩትን አያውቁም ብለን አንዳልተሞኘን አምናለሁ፤ ያውቃሉ። ማን ምንና ለማን እንደሚናገር ግምተው የቀርቡ መሆኑን መለስ ካረፉ በኋላ አየነው። ግልጽነት የሌለው መንግስት መለስ “በመጥፋታቸው” ለአዳማጭ ግልጽ ይሆናል ብሎ መገመት መለስ የፈጠሩትን በምስጢር የሚካሄድ ስርአት አለማወቅ ነው። መለስ ቢኖሩም ባይኖሩም ስርአቱ እንዳለ ይቆያል እያልኩ ደጋግሜ ያሳሰብኩት ለዚህ ነው። የስርአቱ ተጠቃሚወች ብዙ ናቸው። የሚደግፋቸው የስለላና የመከላከያ ሃይል ቀላል አይደለም።
ህወሓት ከራሱ ቡድን ውጭ የሆኑ ወይንም የሚቃወሙ፤ ወይንም ተፎካካሪ የሆኑ ሁሉ የመወዳደሪያ መስክ የሌላቸው/የማይፈቀድላቸው ስርአቱ በምስጢር፤ ለአንድ ቡድን የበላይነት፤ አገልጋይነት ስለተፈጠረ ነው፡፡ ነጻ የሆነ መገናኛ ብዙሃን የማይፈቀደው ለዚህ ነው። ነጻ የሆነ መገናኛ ብዙሃን ቢኖር ኖሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ በጨለማ አይኖርም ነበር። የበላይነትን ለመጠበቅ፤ ነጻ የሆነ መገናኛ ብዙሃን አጥፍቷል፤ ጋዜጠኞችን አስሯል፤ አሰድዷል። ተወዳዳሪን አጎብዳጅ ማድረግ፤ ወይንም ደካማ ማድረግ፤ ወይንም በጥቅም መግዛት ያስፈልገዋል። ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ሲመሩት የቆየው ህወሓት የግል ኩባንያ የመሰለ መዋቅርና ግልጽነት የሌለው አመራር ስር እንዲሰድ ያደረገውና ሁሉ አጎብዳጅ ሆኖ እንዲያገለግል ያስገደደው ለስልጣንና ጥቅም ሲል ነው። ተቋሞች መሪው በድንገት ቢሞት እንዲያገለግሉ የተሰሩ ናቸው። ከጽንሱ፤ የህወሓት አገዛዝ ለግልጽ ውድድር፤ ለነጻነት፤ በራስ ለመተማመን ባህል፤ ለእውነተኛ ኢትዮጵያዊነት የተዝጋጀ፤ ቡድን አይደለም። ለእርሱ ታዛዥ ያልሆነ ሁሉ፤ ተቀባይነት የለውም። ለአጎብዳጂነት፤ ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ለዚህ ነው። ህወሓት፤ አጎብዳጂ ድርጅት ወይንም ግለሰብ ክብርና ነጻነት እንደሌለው ያውቃል፡፡ በራሱ አይተማመንምና። ስርአቱን ቢቃወምም፤ በግሉ፤ በልቡ፤ በቤተሰቡ፤ በቅርብ ወዳጅ እንጂ በይፋ አይደለም።
የህወሓት/ኢህአዴግ ቡድን በመስማማት፤ ተቻችሎ በመኖር፤ ለስልጣን በመደራደር አያምንም። በተለይ፤ የፖለቲካ ስልጣ በመካፈል አያምንም። ህወሓት በኢትዮጵያዊነቱ ኮርቶ፤ ተባብሮ፤ ተቻችሎ፤ የሁሉም ጥቅም በህግ ተከብሮ፤ የሚኖርባትን ኢትዮጵያ ለመገንባት የተነሳ አለመሆኑን የሚያሳዩ ብዙ ማስረጃወች አሉ። የበላይነትን ለመጠበቅ ብዙሃኑን በፍርሃት፤ በመከፋፈል፤ በቂም በቀልነት፤ በማሰር፤ በመግደል፤ ያላጠፋውን፤ አጥፍቻለሁ ብሎ እንዲያምን በማስገደድ፤ በማሳደድ፤ ከስራ በማስወጣት፤አገር ለቆ እንዲወጣ በማድረግ ወዘተ ቆይታውን የሚያረጋግጥ ቡድን ነው። ስልጣኑን የሚያራዝመው በዚህ ጥበብ ነው። በድሃና ጥገኛ አገር፤ ከቻይና በተዋሰው ዘዴ፤ በብዙ መቶ ሚሊዮን የሚታስብ ብር ለስለላ፤ ለድጎማ፤ ለሃይማኖት መከፋፈያ፤ ለጉቦ የሚያወጣው ለዚሁ ነው። የግለሰብን መብት በማቀብ የራሱን ቡድን መብት ያጠናከራል። ስልጣኑ እንዲራዘም፤ የጥቅም አንድነት ይፈጥራል። ስለዚህ፤ ከሃገር አንድነትና ነጻነት፤ ከህዝብ ሉአላዊንትና እኩልነት ይልቅ ጠባብ የጥቅም መተሳሰርን ያስቀድማል። የጥቅም አንድነት ማስረጃው በፓርቲውና በጦር፤ በስለላ፤ በፖሊስ፤ በአስተዳደር እና በልዩ ልዩ ባለስልጣኖች መካክል ያለው እትብት፤ በውጭ የግልና የመንግስት ተጠቃሚወች ያለው የጥቅም ሰንሰለት የሚያንጸባረቀው ስእል ነው። በኢንቬስተሮችና በህወሓት መካከል ያለው መቆላለፍም የሚአመልክተው ይህን ነው። በአሁኑ ወቅት ሊታበል የማይችለው ጠባብ ዘረኝነት/ብሄርተኝነት፤ መንግስት፤ ተቋሞችና ፓርቲው የተሳሰሩ መሆናቸው ነው። ይህ የጥቅም መቆላለፍ ሊፈታ የሚችለው በመተባበር ብቻ ነው። መለስ ስላረፉ ይህ አይቀጥልም ለማለት የሚያስደፍር ማስረጃ የለኝም።
ሊሰበስቡን የሚችሉ አንኳር/አበይት ጉዳዮች፤ እሴቶች አሉ፤ እንጠቀምባቸው፤
መለስ ዜናዊ ለሃያ አንድ አመታት የመሩትን የሀወሓትን መንግስት የማንቀበለው፤ ለሃገር የቆመ መንግስት ባለመሆኑ፤ የጠባብ ዘረኝነት አገዛዝን በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ጭኖ ለራሱ ቡድን፤ ለውጭ ከበርቴወች፤ ለውጭ መንግስታትጥቅም አገሩን አሳልፎ በመስጠቱ፤ በእድገት አሳቦ፤ ነጻነትን ወንጀል በማድረጉ፤ የህዝብን ሰብአዊ መብቶች ለስልጣን ሲል ወንጀል በማድረጉ፤ ስልጣንን ተጠቅሞ ዘረፋንና ስርቆትን እንደ ጀግንነት በመቁጠሩ ጭምር ነው። ይህን፤ የህወሓትን የአጭር ጊዜ በጥቅም፤ለጥቅም የተገነባ እሥስር፤ በሃገር ጥቅም፤ በኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነትና ነጻነት፤ በሕዝብ ዲሞክራሳዊ መብትና ሉአላዊይነት፤ በሕዝብ እኩልነት፤ በህግ የበላይነት፤ የተመሰረተ ተሳትፏዊ መነጽር ስናየው ስርአቱ የፈጠረው አደጋ (system) ጎልቶ ይታያል። የነጻነትን ጥቅም ከተጋራን ይህ ስርአት መለወጥ አለበት ማለት ነው። ይህን ከተቀበልን፤ የመለስ መኖር አለመኖር መጥፎው አገዛዝ አይለውጠውም። ለለውጠው የሚችል የኢትዮጵያ ሕዝብና ለሕዝቡ የቆሙ ሃይሎች በዘላቂነት ለመታቸው ሲሰበሰቡ ብቻ ነው። ለዚህ የሚሰበስቡን አንኳር የሆኑ መሰረተ ሃሳቦችና እሴቶች አሉ። አስቸጋሪ የሆነው፤ እንዚህን ይዘን፤ ተከባብረን፤ ከጎሳ በላይ አስበን፤ ተቻችለን፤ ተደማምጠን፤ መጠላለፍንና ለስልጣን የመሻማት ጉጉትን ወደ ጎን ትተን፤ አገር ውስጣና ውጭ ካሉ የዲሞክራሳዊ ለውጥ ታጋዮች ጋር ተባብረን፤ ፍትህ ለሚፈልገውና ለሚገባው ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አብረን የመታገል ፈቃደኛነት አለመኖሩ ነው።የወቅቱ አንገብጋቢ ጥሪም ይህ ነው። በእነዚህና መሰል፤ አስተባባሪ ሃሳቦች ከተስማማን፤በጎሳ፤ በብሄር/ብሄረሰብ መደራጀቱ በምንም ሊያዋጣን አይችልም። ህወሓትን/ኢህአዴግን በራሱ እንደመተካት ይሆናል። ስብስቦችን ከሚያከራክሩት አንዱ አቢይ ጉዳይ፤ በብሄር መደራጀት መሆኑን አውቀን ውይይት ማድረግና መፍታት አለብን።
ካለፈው ድክመታችን ተምረን “ለሃገርና ለፍትህ” ስንል እንነሳ፤
ህወሓትን/እህአዴግን መቃወም ብቻ ችግሩን ሊፈታ አይችልም። ከባድ የሆነውና የማንነጋገርበት የራሳቺንን ድክመት ማየት ነው። አርአያ በመሆን ፋንታ ጠብና ጥላቻ ማሰፋፋት፤ መዘላለፍ፤ መከፋፈል፤ ልማዳችን ሆኗል። ችግሮችን በመመካከር፤ በእርጋታ፤ በመረዳዳት ለመፍታት አለመቻላችን ለዚህ ማስረጃ ነው። መንግስት ራሱ ባወጣው ህግ ከመገዛት ፋንታ የራሱን ህገ ጥሶ ህዝብን ማሳደድ፤ ማስር፤ ሰው አገሩን እንዲለቅ ማስገደዱን፤ ቀን በቀን እያየን፤ አሁንም ለአንድ ሃገር/ወገን አለመነሳታችን የታሪክ ተጠያቂ ያደርገናል። ተስፋ የሚሰጥ፤ ህብረ ብሄር አጀማመር ስናይ ለዚህም አቃቂር አናወጣለን። ሌላ አማራጭ እንፈጥራለን ብለን እንዘጋጃለን፤ ማፍረስ ሟያችን ሲሆን ለተተኪው ትውልድ ምን ትተን እንደምናልፍ አናስብም። ህያው ሆነን እንደምንቆይ የምንሳብ ብዙ ነን። አንዱ ከመለስ ማለፍ የምንማረው ለህያወነት ዋስትና እንደሌለን ነው። ይህ ድክመት፤ የስርአቱ ጥፋት፤ በደልና ሰቆቃ ብቻ ሳይሆን የራሳችን ችግሩን በሚገባ አለማየት፤ የራሳችን መበታተንና መዘላለፍ፤ የራሳችን አገር ሳይኖር ለስልጣን መወዳደር ወዘተ ጭምር ናቸው። የኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነት ዘላቂነት የሚኖረው፤ አድሎና የበላይነት ሲወገድ ነው። የማንክደው ግን፤ የኢትዮጵያ አንድነት የሚጠቅመው ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን መሆኑን ነው። ከኤርትራ መገንጠል ለመማር እንችላለን። ዘላቅነት፤ ከፍትህ ጋር መያያዝ ያለበት ለዚህ ነው።
ዘላቂነትና ፍትህ ከፈለግን፤ እኩልነት፤ ነጻነት፤ ለህግና ለህዝብ ተገዥ የሆነ የስርአት አማራጭ ለመገንባት ቀን ከሌት መስራት አለብን። በቅርቡ የተጀመረው በጋር የመስራት ሂደት አነዳለ ሆኖ፤ አሁንም ስለዚህ ድክመት በግልጽ፤ በሰፊው ስንወያይ አይታይም። አንድ የውጭ ታዝቢ ነገሩ አስገርሞት እንዲህ አለ። “እንደ ኢትዮጵያ ዲያስፖራ የሚያወራ፤ የሚነታረክ፤ የሚሰበሰብ፤ የሚንጫጫ፤ የለም። ግን ምን ቁም ነገር ለሃገራችሁና ለድሃው ህዝባችሁ ምን ሰራችሁ ብየ ስጠይቅ አጥጋቢ መልስ አላገኘሁም.” ፕሮፌሰር ዶናልድ ለቪን ደጋግመው፤ “ኢትዮጵያዊያን በጋራ ሁነው የሃገራቸውን ችግር የሚፈቱ መቸ ይሆን” የሚሉት ጥያቄ አሁንም አልተመለሰም። ለዚህ አባባል መልስ የመስጠት ሃላፊነት የሁላችንም ነው። የሚረዱንና የምንስማማባቸው አገራዊና ህዝባዊ ጉዳዮች እንዳሉ ከላይ ጠቅሻለሁ፡፡
ለማጠቃለል፤ የእኛ ትውልድ በኢትዮጵያና በመላው ሕዝቧ ስም ብዙ አገራዊ ሙከራወችና በተመሳሳይ ብዙ ስህተቶ ሰርቷል፤ አሁንም ይሰራል። መወያየት፤ መሰብሰብ፤ መደራጀት፤ አስፈላጊ መሆኑ አያጠያይቅም። ግን፤ መሞከር ብቻ በቂ አይደለም። መለስ ዜናዊ የሚደነቁት፤ በላማቸው የጸኑ በመሆናቸው ጭምር ነው። በቢቢሲ በሞታቸው ዙሪያ የተደረገውን ዘገባ ስሰማ ትዝ ያለኝ አላማቸውን እንዴት ለአፍሪካና ለቀረው አለም ህዝብ ለማሳመን አንደቻሉ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ በሰሩት ባንስማማም፤ ይህን ለመካድ አንችልም። በሃገር ውስጥ ፍትሃዊ ስር አት ቢያቋቁሙ ኖሮ አመለካከታችን በለወጡት ነበር። አላደረጉም። ስላልሆነም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ እስካሁን የበላይ እንዲሆን ጠቃሚና አገልጋይ የሆነ የአገዛዝ ስርአት ለመገንባት እንዲችል እሳቸው መሰናክል ሆነው ነበር፤ ተቃዋሚው ክፍልም ያደረገው አስተዋጾ አለ ለማለት አንችልም። በተቃዋሚው በኩል ሲታይ፤ በሕዝቡ ስም፤ ተሰብስበናል፤ ተመካከረናል፤ ሞክረናል፤ ነግደንበታል ለማለት የሚያስችሉ መለኪያወች አንዳሉ ብዙ ኢትዮጵያዊያን ታዛቢወች ጽፈዋል። ለዘላቂ የሃገር ግዛታዊ አንድነት፤ ለመላው ሕዝብ ነጻነት፤ እኩልነት፤ ፍትህ፤ ለዲሞክራሳዊ ስልጣን እውን መሆን በሃገር ውስጥና በውጭ ብዙ ስብስቦች ተካሂደው ‘የውሃ ሽታ’ ሁነዋል። አሁን፤ የመለስ ማረፍ ይህን ጎጅ ባህሪይ ይለውጠው ይሆን? ያለፉትን ስብስቦች እንይ።
ኢህአዴግ ስልጣን ከመያዙ ከአንድ አመት በፊት በቶሮንቶ፤ ካናዳ፤ አምስት የፖለቲካ ድርጅቶች– ኢህአፓ፤ ኢድህ፤ መኢሶን፤ ኢፒዲ ኤና ቲፒዲ ኤም– በወሰዱት እርምጃ፤ ሃያ ሁለት የሚሆኑ የማህረሰብ (Civic) ና፤ የሙያ ድርጅቶች ተሰብሰበው ያወጡት ፕሮግራም መሰረት ሳይዝ ቀረቷል። ይህን ድክመት የተመለከቱ ግለሰቦችና ድርጅቶች፤ እንደገና እ አ አ በግንቦት 1991 (ህወሓት ስልጣን በያዘበት ሰሞን) የኢትዮጵያ ዲሞክራሳዊ ሃይሎች ቅንጅትን መሰረቱ። ኢዲሃቅ፤ በኢትዮጵያ ስምና በመላው ሕዝቧ ፍትህ ፈላጊነት መሰብሰቡ የሚደነቅ ጅምር መሆኑን ያሳያል። ያደከመውና ህልውናውን ያሳጣው፤ የህወሓት ሰላዮች ሰርገው ገብተው ባደረጉት የማከፋፈል ተግባር ነው። ሆኖም፤ የኢዲሃቅ መሪወች ለዚህ ሰለባ ለምን ንቁና ታታሪ አለመሆናቸው ያጠያይቃል። ከህወሓት መሰሪነት ባሻገር ልንማረው የሚገባን ሃቅ፤ የኢዲሃቅ ስብስብስ በጋራ የሚጋራው ራእይ አልነበረውም። የጋራ ራእይ፤ ለምሳሌ፤ የኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነት፤ የመላው ሕዝቧ ስርጭትና እኩልነት፤ የህግ የበላይነት አስኳል መመሪያ ካልሆኑ፤ መሰብሰቡ፤ ዲስኩሩ፤ ዳንኪራው የትም አያደርስም። ለግል የመንፈስ ሰላምና እርጋታ ሊሰጥ ይችላል፤ መሰረታዊ ለውጥ አያመጣም። ኢዲሃቅ ሲመሰረት ስለነበርኩ፤ ለመመስከር ብቁነት አለኝ። የማስታውሰው፤ መተማመን፤ አብሮ መስራት፤ ገንዘብ አዋጥቶ ዘላቂ ተቋም መስርቶ መስራት አሰፈላጊ ነው ማለቴን አስታውሳለሁ። ከሁሉም በላይ ያሳሰብኩት፤ ዋናው ኢላማችን፤ መመሪያችን “ኢትዮጵያ” የምትባል አገርን፤ “ኢትዮጵያዊያን” የሚባሉ ዜጎችን ማእከል ማድረግ ( Put Ethiopia and the Ethiopian people as a whole on the radar screen) የሚለው መርህ አሰፈላጊ መሆኑን ነው። ባለመሆኑ፤ ኢዲሃቅ ወደቀ። የተወጣጣው ሩብ ሚሊዮን የኣሜሪካ ⶌላር ዋጋ አጣ።
ከኢድሃቅ በኋላ ሌሎች ብዙ ጥቃቅንና ታላላቅ ሙከራወች ተደርገዋል። እነዚህን ተከታታይ ስብስቦች ከህወሓት/ኢህአዴግ የሚለያቸው ብሄራዊና ህብረ ሕዝባዊ፤ ለሰላም፤ ለፍትህ፤ ለነጻነት፤ ለእኩልነት፤ ከነጻ ምርጫ ለሚመጣ የሕዝብ ስልጣን መቆማቸው መሆኑ ነው። ፓሪስ አንድና ፓሪስ ሁለት እአ አ 1993 እና 1997 የተካሄዱ ሲሆን፤ በቀደምተኛነት የተሳተፉት ዘጠኝ ድርጅቶች፤ መኢሶን፤ ኢህአፓ፤ ህብረ-ሕዝብ፤ መድህን፤ ህብኮፓ፤ ትትኢ፤ ኦነግ፤ ደቡብ ህዝቦችና አርዱፍ ነበሩ። አንዱ የሚለያቸው፤ በጥላቻ ይሰሩ የነበሩ የህብረ ብሄርና የብሄር ድርጅቶች (እያፓና መኢሶን) የሚጋሯቸው አንኳር ጉዳዮች ላይ ስምምነት መድረሳቸው፤ ከህወሓት/ኢህአዴግ ጋር በአንድ ላይ ለመደራደር መዘጋጀታቸው ነበር። ያላሰቡት ግን፤ አንደኛ በውስጣቸው ዘላቂነት ያለው የጋራ ራእይ አለመኖሩ፤ ሁለተኛ ከድርጅቶቻቸው በላይ ለተስማሙበት አገራዊ አላማ በዘላቂነት አለመቆማቸው፤ ሶስተኛ ስነ መግባርና ካሰቡት የሚያደርሳቸው የስራ እቅድ (Project) አለማውጣታቸው ናቸው። አራተኛ፤ ህወሓት/ኢህአዴግ ለመደራደር ያለው ፈቃደኝነትና ዝግጁነት በሚገባ ያላሰቡበት መሆኑ ነው። ለመደራደር፤ ሁለቱም ወገኖች ከስልጣን መጋራት የሚመጣውን ጥቅምና ጉዳት ማመዛዘን ነበረባቸው። የሚመጡ መሰናክሎችን ተቋቁሞ ስልት እየቀየሱ መጓዝ ነበረባቸው። ለምሳሌ፤ በፓሪስ ሁለት ኦነግ ባልታሰበ ምክንያት አልተሳተፈም። አሁን በአንዳድ ድርጅቶች አመለካከትና አሰራር የምናውየውም ይህን አይነት ተደጋጋሚ የሆነ ከሃገር በላይ ለድርጅት ተገዥነትን ነው። የድርጂት ነጻነት ተብሎ የሚነገርለት አሰተሳሰብ እስከ መቸ እንደሚያዋጣ ያየነው አይመስልም።
ካለፈው የምንማረው፤ ህወሓት/ኢህአዴግ ያለውን ሃይል አመዛዝኖ፤ የተቃዋሚወችን ድክመትና አቅም አውጥቶ አውርዶ አልደራደርም ብሏል። ተቃዋሚው ክፍል አብሮ ለሃገራዊ አማራጭ ካልተነሳ፤ ካልተባበረ፤ አሁንም ያለፈው ችግር ይደገማል። የተቃዋሚው ክፍል በሚገባ ያልተገነዘበው ልዩነቶችን አስወግዶ አቅሙን ካልገነባ፤ ማንም የሚረዳው ሃይል እንደ ሌለ ነበር፤ አሁንም ይህ ሁኔታ አንዳለ ነው። ከድርጅት በላይ ለሃገር፤ ለመላው ሕዝብ ነጻነትና ፍትሀ መቆም የሚያስፈልገው ለዚህ ነው። የድርጅት አምልኮ ካልተወገደ፤ የመለስ ማረፍ ለነጻነት ጎህ አይቀድም።
ከእነዚህ ስብሰቦች ግዙፍ የሆነው በዋሽንግተን ዲሲ፤ እአአ በ 2003 የተካሄደው የኢትዮጵያ ዲሞክራሳዊ ሃይሎች ህብረት (ኢዴሃሕ) የተባለው ከምርጫ ዘጠና ሰባት በፊት የተካሄደው ውይይት ነው። በዚህ ስብሰብ አለም ባንክ በሃላፊነት እየሰራሁ በነበረበት ወቅት፤ በግል ደረጃ ተጋብዠ ሰለተካፈልኩ፤ ሂደቱን አይቸዋለሁ። የማስታውሰው፤ ስብሰባው አገራዊ፤ ጥልቀት የነበረውና በጨዋነት የተካሄደ መሆኑን ነው። ስለሆነ ተስፋየ ከፍ ያለ ነበር። ያለኝን ሁሉ አበርክቻለሁ፤ ሊቀመንበሩ ሁሉን በማግባባት የመሩት ስብስብ ነበር። በዚህ ስብስብ የተካፈሉት፤ መኢአድ፤ ኢህአፓ፤ መኢሶን፤ ህብረ-ሕዝብ፤ ኢዴህ፤ ደቡብ ህዝቦች፤ ኢብሶ፤ ትዴት ናቸው። ትኩረቱ፤ ጥናትና ትንተና ላይ ነበር።
እኔን የሳበኝ፤ የስብሥቡ አገራዊነት፤ በፍትህና ሌሎች ዲምክራሳዊ ሃሳቦች ላይ የአላማ አንድነት የነበረበት መሆኑ፤ በብሄር የተደራጁና በህብረ ብሄር የተደራጁ ድርጅቶች የመተማመን ባህልን ለማጠናከር ሊያደርጉ የወሰኑት ሂደት፤በመወያየት፤ አብሮ በመስራት ችግሮችን ለመፍታት የሚያግደን ነገር የለም የሚል ስሜታቸው ነበር። ሆኖም፤ ሌሎች ግዙፍ ድርጅቶች፤ ለምሳሌ፤ ኦነግ፤ ባለመገኘታቸው ችግሮቹ የማይፈቱ መሆናቸውን የሚያሳይ ሁኔታ እንደነበር ለመረዳት ችያለሁ። በስብስቡ ካየኋቸው ነገሮች አንዱ፤ በስራ አለም ላይ የተሳተፈ፤ በተለይ በውጭ አገር የሰራ ግለሰብ እንደሚያውቀው፤ እኔም በአለም ባንክ የተማርኩት፤ ላወቀበት የአስተሳሰብ ልዩነቶች በመደማመጥና በውይይት እንደሚፈቱ ነው። ሃሳቡን ከግለሰቡ መለየት የሚያስፈልገው ለዚህ ነው።
የኢትዮጵያን ሕዝብ ለዘላቂ ሰላም፤ አብሮ ለመኖር፤ ለሃገር ግዛታዊ አንድነት፤ ለመላው ሕዝብ ከቀጥታ የመምረጥ ድምጽና መብት የሚገኝ ፍትሃዊና ወካይ የመንግስት ስነስርአት (Representative government) ሊያደርሰው የነበረው የምርጫ 97 (2005) የቅንጅት መንፈስ በታሪካችን ከፍተኛውን ቦታ ይዞ ይገኛል። ይህን ምርጫ የሚለየው፤ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ህወሓትን/ኢህአዴግን “አንፈልግም፤ ድምጻችን ይከበር፤ ለእኛ ተወካይ የሆነ መንግስት ይቋቋም” ማለቱ ነበር። አደጋውን ያየው የመለስ ዜናዊ መንግስት አጠፋው፤ የሕዝቡን ፍላጎት አኮላሸው። ለዚህ በሰላም የተመሰረተ የሕዝብ አመጽ መሰረት እንዲይዝ ያስፈልግ የነበረው የቅንጅት ድርጅታዊ ጥንክርናና የአመራር አዋቂነትና ጠንካራነት ነበር። ድርጅቱና አመራሩ በውስጥ የተከሰተውን ልዩነት ወደ ጎን ትቶ በስልት፤ በጥበብ፤ በዘዴ ቢሰራ ኖሮ የተሻለ ውጤት ባስገኘ ነበር። ልክ እንደ እምቧይ ካብ የተናደው አመራር ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተስፋ የሚያስቆርጥ አሰራርና ባህሪ አሳይቶ ተበታተነ። ይህን ድክመት፤ ሕዝቡ እስካሁን አልረሳውም፤ በመሪወች ላይ ያለው እምነት እንደገና መታደስ አለበት ማለት ነው።
ዘላቂነት ያለው አገራዊ የፖለቲክካ ድርጅትና የማይበገር አመራር የሚያስፈልግ መሆኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከቅንጅት ልምድ አስተምሮናል። ለዚህ ሌላ አማራጭ የለም። ተቃዋሚ ሃይሎች ይህን ያለፈ ድክመት አጢነው፤ ለወደፊቱ በሰብሳቢ አገራዊ ራእይ፤ ለፍትሃዊ ስርአት እውን መሆን፤ ሳይበገሩ በአንድ ድምጽ፤ በአንድ ስልት መነሳት አለባቸው። በተናጥል እንደራደር ቢሉ፤ የሚያቆዩት የህወሓት/ኢህ አዴግን ጸረ ፍትህ መንግስት ብቻ ነው። ይህን እውነት የመለስ ማለፍ አይለውጠውም።
የጋራ ራእይ ወሳኝነት፤
የምንጋራው ራእይ ከሌለ የትም አንደርስም። በአንድ ኢትዮጵያ ማመን ራእይ ነው። በሁሉም ዜጎች የእድል እኩልነት ማመን ራእይ ነው። በሰላም፤ በነጻነት፤ በሕዝብ ድምጽ፤ በሕዝብ የበላይነት፤ በህግ የበላይነት ወዘተ ማመን ራእይ ነው። ራእይ እውን የሚሆነው፤ በመተማመን፤ በመደማመጥ፤ በመቻቻል፤ ለሃገር ግዛታዊ አንድነት፤ ለመላው ሕዝብ ፍትህ በማሰብ ውይይት ተደርጎ በአንኳር አገራዊ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ ሲደረስ፤ እያንዳንዱ ተሳታፊ ስምምነቱን ወደ ኋላ ሳይል ከስራ ላይ ሲያውል ብቻ ነው።ለዚህ፤ ስነ መግባር ያሰፈልጋል (Code of Conduct)። ከላይ የተጠቀሱት ስብስቦች፤ የሚጋሩት ራእይ፤ የሚዳኙበት ስነ መግባር አልነበራቸውም።
ሁሉም እንደፈለጉ ወደ ድርጅቶቻቸው (Silo) ሂደው መስራት ጀመሩ፤ ስብስቦችና ሂደቶች አልተጣጣሙም።
የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚመኘውን ከሕዝብ ብቻ የሚመጣ፤ ለሕዝብ ብቻ አገልጋይ የሆነ ስርአት ለመገንባት ነው። እድሉ አሁንም ክፍት ነው። እድል ክፍት መሆኑ ብቻ ጥቅም አያመጣም። ወሳኙ አገራዊ የፖለቲካ ድርጅት፤ ለዚህ ብቁነት ያለው የማይበገር አመራር መገንባት ነው። በውጭ ያለን ተቃዋሚ ሃይሎች መጀመሪያ በመካከላችን ያሉ ጥቃቅን ልዩነቶችን ወደ ጎን ለመተው ከቻልን፤ አቅማችን በጋራ፤ ለጋራ አላማ ከገነባን፤ አገር ቤት ለሚንቀሳቀሱ አገራዊ ለሆኑ ለዋጭ ሃይሎች አስተዋጾወች ለማድረግ እንችላለን። የውጭ አምባሳደሮች ሆነን የአለምን አስተሳሰብ ለመለወጥ እንችላለን። ተቃዋሚ ሃይሎች በጋራ ለድርድር እንዲበቁ የአቅም ግንባታ ስራ ለመስራት እንችላለን። የመጀመሪያው እርምጃ፤ በቅርቡ የተመሰረተውን የተቃዋሚ ሃይሎች ስብስብ በያለንበት መደገፍ፤ ሌሎች ድርጅቶች እንዲተባበሩ፤ አብረው ገብተው እንዲሰሩ መጎትጎት፤ የድጋፍ ቅርንጫፎች በየቦታው እንዲቋቋሙና አብረው እንዲሰሩ መቀስቀስና ተግቶ መስራት ነው።
የመለስ ዜናዊ ከዚህ አለም መለየት ለመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ እድል ሊከፍት ይችላል። ይህን ሊያመለጥ የሚችል እድል የመጠቀም ጥበብ ግን ከተቃዋሚው ሃይል መምጣት አለበት። አዲስ ምእራፍ ለመክፈት ከተዘጋጀን ማንንም የማይለይ፤ ሁሉን የሚሰበስብ አማራጭ ማቅረብ አለብን። አለበለዚያ የችግራችን መነሻ መለስ ዜናዊ ነበሩ ብለን ማውራቱ ምንም አያዋጣነም።
ይቀጥላል
August 21, 2012