Shaleqa Dawit Woldegiorgis, the author of Red Tears and former high-level Ethiopian government official, has released a new novel based on true stories. The book is written in Amharic and it is currently being distributed in Ethiopia through underground networks. Artist Debebe Eshetu has written the following book review:
እስከዳር:- ከዳዊት ወ/ጊዮርጊስ
እስከዳርን አነበብኩት፡፡ዳዊት ወ/ጊዮርጊስን እንደገና አወቅሁት፡፡እንደ ደራሲ፤አስተማሪ፤ታሪክ አሰታዋሽቱ፡በቅድሚያ አንዲት ገጸ ባሕሪን ከሃዲስ ዓለማየሁ ‹‹ትዝታ›› ወስዶ የበለጠ ነፍስ፤ጀግንነት፤ሰብአዊነት አላብሶ በግሏ ጠንክራ እንድትወጣና የራሷን አካሄድ በማጉላት ሲያቀርብልን አዲስ ምዕራፍ ከፍቶ ሰጠን፡
እስከዳር ከላይ እንዳልኩት የአንዲት የትዝታ ባሕሪ ታሪክ ብቻ እንዳልሆነም ሊጤን የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ ለልጆቻችን ለልጅ ልጆቻችን ስለ ቀድሞው ኢትዮጵያዊነት፤ አባቶቻችን ስለአሳለፉት የሃገር ፍቅር ወኔያቸውና የቆራጥ ትግል ውሳኔያቸው የት እንዳደረሳቸውና ሃገርን ሲሉ ከነሙሉ ክብሩና ማዕረጉ እንጂ፤ ሃገርን ሲሉ ከነክፉ አጋጣሚና ስለሚያስከፍለውም መስዋእትነት እንጂ፤ ሃገርን ሲሉ ኢትዮጵያን ከፍ አድርገው እራሳቸውን አውርደው እንጂ ጥቅምን በዚያ ውስጥ በማየትና ክብርና ዝናን ለመጎናጸፍ እንዳልሆነ አሳምሮ አሳየኝ፡፡አሳወቀኝ አስታማረኝ ለማለት እደፍራለሁ፡፡
ዳዊት በአጻጻፉ ልራቀቅ ብሎ አበባዊ ቃላቶች ድርደራ ጊዜ አላባከነም፡፡ ሁሉም ሰው እለት በእለት በሚጠቀምበት ቋንቋ ተጠቅሞ ግን ሊረሳ የተቃረበውን፤ ልጆቻችን ጭርሱን ሰምተውት የማያውቁትን ባህላችንን አመላከተን፡፡እዚህ ላይ አንድ ማስረጃ ላቅርብ፡፡ በገጽ 252 ላይ ‹‹እንማን ናቸው›› ብሎ ያስቀመጣቸው ኢትዮጵያዊያን የኢትዮጵያ ዳር ድንብር አስከባሪ ሃይሎች አቀናጆች የነበሩትን በስማቸው ብቻ ጠቅሶ አላለፈም፡፡ ማዕረጋቸውንም ደርቦላቸው አልተዋቸውም፡፡ ይልቁንስ ምን አደረጉ፤ ከየት ተወለዱ፤የሚለውን በአናሳ በአናሳው ቦታ ሰጥቶ ለማወቅ የሚፈልግ ትንሽ አፈላልጎ እንዲያነብና እንዲያውቅ መንገዱን አሳይቶናል፡፡ ከዚህ በመነሳትም ጸሃፍት ስለነዚህ ሀገር ጠባቂዎች፤ ከምንም በላይ ከምንም በፊት ሃገሬ ያሉትን አባቶች አያቶቻችንን በማንሳት ተመራምሮ መጻፍ የሚገባው መሆኑን ጠቁሞናል፡፡
ደራሲ ዳዊት ከመነሻው ጀምሮ ስለ ሃገር ፍቅር በተለይ ለወጣቱ ትውልድ በሚገባና በሚነበብ መልኩ ነው ሊያስታውሰው የጀመረውና እስከ መጨረሻውም የሄደበት፡፡ ሃገር ምን ማለት ነው? ለሃገር መሰዋትስ? የሚለውን ከነሙሉ ግንዛቤው ሰጥቶናል፡፡
ሌላው የ‹‹እስከዳር›› አጻጻፍ ነው፡፡ መጽሐፉን ለልጆቻችን እንደተረት መጽሃፍ ብናነብላቸው በቀለለ አማርኛ የቀረበ በመሆኑ ይገባቸዋል ይወዱታል፡፡ ከሕጻኗ እስከዳር ጀምሮ ስለሚተርክ ልጆቹ እራሳቸውን ያገኙታል ወይም ጓደኛ አድርገው ያውቋታልና ልጆቻችንን ስለ ሃገራቸው፤ ስለ ሃገራቸው ጀግኖች፤ ሊኖራቸው ስለሚገባው የሃገር ፍቅር ሁሉ እየገባቸው እንዲያድጉየማድረግ ሃይ ስላለው በዚህም አቀራረቡ ሊመሰገን ሊደነቅ ይገባዋል እላለሁ፡፡
የጅግና ስሜት እንዴት የጀግናን ልብ እንደሚሰርቅና እንደሚያስቀና ሲያሳየንም ገጽ 47 ላይ‹‹…….ይህንን ሁሉ ትምለከት የነበረችው እስከዳር ልቧ ቅልጥ አለ፤በደስታ በኩራት ታፈነች፡፡ ያ የምትንቀው አጎናፍር ለካስ የወጣለት ወንድ ኖሯል፡፡ ጀግና ትወዳለች እስከዳር፡፡ የአጎናፍር ጀግንነት ሰውነቷን ወረረው፡፡ በዚያ ቅጽበትና ስፍራ ልቧ ውሃ ሆነ፤ፈሰሰ፡፡ሰውነቷን ነዘራት፡፡ ተሰምቷት የማታውቀው የሴትነት ስሜት ከውስጧ ገንፍሎ ሲወጣ በገሃድ ይታይ ነበር፡፡ፊቷ አበራ፡፡ የአልታያት የአጎናፍር ወንድነት፤ መልክና ቁመና፤ አሁን በድንገት ግልጥ ብሎ ታያት፡፡አራት ዓመት ሙሉ ስትሸሸው፤ ስትንቀው የነበረው አጎናፍርን ወደደችው፡፡ የማይነቀል የፍቅርና የአድናቆት ጦር በልቧ ተተከለ፡፡ ዓይነ ጥላዋ ተገፈፈ፡፡›› ሲል ጀግንነት ያለውን የመያዝ የመማረክ ስሜት ውብ አድርጎ አሳየን፡
ዳዊት በዚህ ‹‹እስከዳር›› ባለው ድርሰቱ ውስጥ ኢትዮጵያ ጥንታዊትነት ብቻ ሳይሆን ለሃገራቸው ቀናኢ የሆኑ ሕዝቦችም እንዳሏትና ዘወትር ተከባብረውና ተፋቅረው መኖርን ባህላቸው ያደረጉ አዋቂዎች እንደሆኑ በማስረጃ አቅርቦልናል፡፡
ከዚህ በተረፈ ደግሞ አንብቡትና ለልጆቻችሁም አስነብቡት አለያም ማታ ማታ ሲተኙ አንብቡላቸው፡፡ እኔ በበኩሌ የተሰማኝና ለደራሲ ዳዊት ወንድሜ ላሳስብ የምፈልገው በሲዲ አለያም በካሴት ተነቦ ቢቀርብስ የሚለውን ጉዳይ ነው፡፡
ደበበ እሸቱ