In the northern Ethiopian town of Humera, fire has caused major damage, including the displacement of 3,500 residents and burning down of 816 homes. Last October, I was at the border of Humera, across Tekeze river. Click here to see the video. It is a place stolen by the ruling Woyanne junta from the people of Gonder and given to Woyanne loyalists. – Elias Kifle
The Reporter presented news of the Humera fire as follows (in Amharic):
በትግራይ ክልል፣ ቃፍታ ሁመራ ወረዳ ልዩ ስሙ አደባይ በተባለው ከተማ በደረሰ የእሳት ቃጠሎ፣ በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን የአካባቢው ኃላፊዎች ለሪፖርተር ጋዜጣ ገለጹ፡፡ በቃጠሎው ምክንያት ከ3500 በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን ኃላፊዎቹ አስታውቀዋል፡፡
ባለፈው ዓርብ መጋቢት 3 ቀን 2002 ዓ.ም. በተጠቀሰው አካባቢ በተነሣው የእሳት ቃጠሎ፣ የከተማው አንድ ቀጣና ሙሉ ለሙሉ የወደመ ሲሆን፣ ከ800 በላይ ቤቶች ወድመዋል፤ ንብረትም ተቃጥሏል፡፡ የቃፍታ ሁመራ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ፣ አቶ ክፍሉ ኪሮስ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለጹት፣ በተነሣው የእሳት ቃጠሎ በበርካታ ሰውና ንብረት ላይ አደጋ ደርሷል፡፡ በኃላፊው ገለጻ፣ መንሥኤው በመጣራት ላይ ያለ ቢሆንም፣ በመጀመርያ ቀን በተመሳሳይ ጊዜና ሰዓት በአራት ቦታ ላይ የተከሰተ ሲሆን፣ በአደጋው ማሾ እና ኃይለማርያም የተባሉ ሁለት ወጣቶች ሕይወታቸው ሲያልፍ፣ በበርካቶች ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡
የቃፍታ ሁመራ ማስታወቂያ ቢሮ በተመሳሳይ እንደገለጸልን ደግሞ፣ በ816 ቤቶች ላይ በደረሰው ቃጠሎ በ450 አባወራዎች ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ከ3500 በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎች በአደጋው ተፈናቅለዋል፡፡ የቢሮው ኃላፊ አቶ ፀጋይ ገሰሰው እንዳሉት፣ አደጋው የተከሰተው መጋቢት 3 ቀን 2002 ዓ.ም. 8 ሰዓት ከ40 ደቂቃ ሲሆን፣ በአራት የተለያዩ አካባቢዎች በተመሳሳይ ጊዜና ሰዓት ቃጠሎው መከሰቱን ገልጸዋል፡፡
እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ በመጀመሪያው ቀን በተነሣው አደጋ፣ ከ800 በላይ ቤቶች ሙሉ ለሙሉ የተቃጠሉ ሲሆን፣ በተከታታይ ሁለት ቀናትም 16 ተጨማሪ ቤቶችም ወድመዋል፡፡
በአደጋው ዶሮዎችን ጨምሮ ከ1500 በላይ የቤት እንስሳት አልቀዋል፤ በሰብልም ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡ አቶ ፀጋይ እንደሚሉት፣ 1456 ኩንታል ሰሊጥና 1118 ኩንታል ማሽላ፣ ዘጠኝ ኩንታል ጤፍም በቃጠሎው ወድሟል፡፡
ስለ አደጋው መንሥኤ በውል ለመናገር እንደሚቸገሩና በምርመራ ላይ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊዎቹ፣ በአሁኑ ወቅት ሦስት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው በፖሊስ ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሆነና እስከ አሁን ባለው ጥርጣሬ የኤርትራ መንግሥት እጅ ሊኖርበት እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
አደባይ ከተማ ከሁመራ ከተማ 10 ኪሎ ሜትር በስተምሥራቅ የምትገኝ ሲሆን፣ በትናንትናው ዕለትም ባቅራቢያዋ በምትገኘው ሀገረ ሰላም ከተማ ተመሳሳይ የቃጠሎ ሙከራ መደረጉን አመልክተዋል፡፡
የአካባቢው አስተዳደር፣ የባለሀብቶችንና በአካባቢው በሥራ ላይ የሚገኙ የቻይና ተሽከርካሪዎችን ተጠቅመው ቃጠሎውን ለማቆም ጥረት እየተደረገ መሆኑንና አልፎ አልፎ ከሚነሣው ቃጠሎ ውጪ፣ በአሁኑ ወቅት ቃጠሎውን ለመቆጣጠር መቻሉን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡
ጉዳት የደረሰባቸው ከ3500 በላይ ነዋሪዎችም መጠነኛ የምግብና የተለያዩ የቁሳቁስ እርዳታ ተደርጎላቸው፣ በአብያተ ክርስቲያናትና በዳሶች ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ ለመረዳት ተችሏል፡፡ መጋቢት 5 ቀን 2002 ዓ.ም. የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ፀጋይ በርሔ ወደ አካባቢው በመሄድ የደረሰውን አደጋ መመልከታቸውም ታውቋል፡፡