“ከኢንጂነር ኃይሉ ተለይቻለሁ” አቶ በድሩ አደም
Wednesday, 05 March 2008
Source: The Reporter
(Read in PDF)
ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል ቅንጅት እንዲያንሰራራ የማድረግ አቅም እንደሌላቸው፣ በሰሩት ተደጋጋሚ ጥፋት ቢመከሩም ሊያዳምጡ ባለመቻላቸው አሜሪካ ጥላዋቸው እንደመጡ፣ በሃሳብም እንደተለዩዋቸው አቶ በድሩ አደም ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አስታወቁ፡፡
እንደ አቶ በድሩ ገለፃ ኢንጂነር ኃይሉ በቅርቡ አዲስ አበባ መጥተው በሚጠሩት ጠቅላላ ጉባኤ የቅንጅትን እውነተኛ አባላት ማግኘት አይችሉም፡፡ “ይልቁንም ” ይላሉ አቶ በድሩ “ይልቁንም እስር ቤት ገሀድ የሆነው የብሔር ጉዳይ ይፋ የሚወጣበት የቀድሞ የመኢአድን አባላት ያገኙዋቸዋል ”
“ኢንጂነር ኃይሉ ብቻ ሳይሆኑ ሁለቱም ቡድኖች ከጨዋታ ውጪ ሆነዋል ” እንደ አቶ በድሩ ገለጻ፡፡ ቅንጅት በህይወት እያለ ብቻ ሳይሆን ሞቶም ቢሆን ዴሞክራሲንና ነፃነትን ለህዝብ እንዳስተማረ የገለፁት አቶ በድሩ “ፖርቲው የጀመራቸውን አጀንዳዎች መንግሥት ቀጥሎበታል ” ብለዋል፡፡
“ቅንጅት ከጅምሩ አልተቀናጀም፡፡ እስከ መጨረሻውም ቢሆን ሊቀናጅ አልቻለም፡፡ ነገር ግን ሕዝብና መንግሥት ጠንካራ ፓርቲ መስሏቸው ተሳስተዋል ” ሲሉ የፓርቲውን የውስጥ ድክመት ባለማወቁም ህዝብና መንግስት መታለላቸውን ያስረዳሉ፡፡
መንግሥት የቅንጅትን የውስጥ ችግር አስቀድሞ ቢያውቅ ኖሮ ፓርቲው በራሱ ችግር ተፈረካክሶ አንደሚጠፋ ይረዳ ነበር፡፡ ይህንን ሊረዳ ባለመቻሉ የፓርቲውን አመራሮች ለማሰር ጊዜና ጉልበት ለማባከን ተገዷል ሲሉ አቶ በድሩ የቀድሞውን ቅንጅት ችግር ይገልፃሉ፡፡
የቅንጅት አመራሮችን ከእስር ለማስፈታት የጣሩ፣ የኢንጂነር ኃይሉን ዓይን ለማሳከም ከፍተኛ ርዳታ ያደረጉ፣ በሐሰት በሌብነት በመወንጀላቸው፣ በኢንጂነር ኃይሉ ላይ ቅሬታ እንዳደረባቸው ያስታወቁት አቶ በድሩ ዶ /ር ታዬ ወልደሰማያትን ኢንጂነሩ በራሳቸው ፊርማ ሐምሌ 20 ቀን 1999 ዓ .ም የፈረሰውን የቅንጅት የዓለም አቀፍ ምክር ቤት ሰብሳቢ አድርገው መሾማቸውንና የሰሜን አሜሪካ የጉብኝት ጉዞ አባልና አስተባባሪ ማድረጋቸው አግባብ እንዳልሆነ አቶ በድሩ አመልክተዋል፡፡ “እኔን ጨምሮ ሌሎችም የማይቀበሉት ውሳኔ በመወሰናቸው ጥያቸው መጥቻለሁ ” ብለዋል፡፡
“ከሁሉም በላይ አስገራሚ ” በማለት አቶ በድሩ የሚገልጹት የአቶ አባይነህ ብርሃኑን ውክልና ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ወደ ሰሜን አሜሪካ ከተጓዙት አባላትና በአሜሪካ የዚህ ቡድን እንቅስቃሴ ይደግፉ ከነበሩት መካከል አቶ ገ /ፃዲቅ፣ ዶ /ር በዛብህ፣ ሻለቃ አድማሱ፣ ወ /ሮ ንግስቲና ራሳቸውን አቶ በድሩን ሳያማክሩ አምስት የላዕላይ ምክር ቤት አባላትን ከማባረራቸው በላይ አቶ አባይነህን መወከላቸው ከፍተኛ ቅሬታን ፈጥሯል፡፡ ውሳኔውም አስገራሚ ተብሏል በማለት አቶ በድሩ ተናግረዋል፡፡
አገር ቤት ካለውም ይሁን ከኢንጂነር ኃይሉ ቡድን ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነበት ማቆማቸውን ያመለከቱት አቶ በድሩ ራሳቸውን ስለማግለላቸው ሲያብራሩ “ሁለቱም ቡድኖች የግለሰቦች እኩልነትን፣ የብሔር ብሔረሰቦችን መብት፣ የዘርና የሃይማኖት ልዩነት የማይታይበት ስርዓት ሊፈጥሩ አልቻሉም ወደፊትም ቢሆን መፈጠር አይችሉም ”
“ከሁለቱም ቡድኖች ውስጥ የዋህና የአመራሩ የተንኮል ፖለቲካ ያልገባቸው ንፁህና ለአሪቱ ጠቃሚ የሆኑ ዜጎች አሉ፡፡ ህዝብ እነዚህን ዜጎች ሊያውቃቸው ይገባል ” በማለት አቶ በድሩ ተናግረዋል፡፡